መሐል ሜዳ - ሜዳ መሐል
ሲቪል መሐንዲስና የሥራ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ የስራና የሕይወት ታሪካቸውን
በሚያትተው መጽሐፋቸው ላይ ‹የመሐል ሜዳ ከተማ መቆርቆር› በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን አካተዋል፡፡ ‹‹በ1959
ዓ. ም.፣ በመንዝ ጌራ ምድር፣ በመሐል ሜዳ፣ እንደ ጎዴ ዓይነት ከተማ ተቆረቆረ፡፡ ይህ ቦታ ከአዲስ አበባ 300
ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሕዝቡ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዐይነተኛ ሥራ፣ እርሻና በግ ርቢ ነው፡፡ የመሐል
ሜዳ ከተማ፣ በአባይ ሸለቆ ጥናት ኤክስፐርቶች እና በልዩ ልዩ ሚኒስቴሮች ኤክስፐርቶች ተጠንተው በቀረቡት ሐሳቦች
መሠረት የተቆረቆረ ከተማ ነው፡፡ ለመንዝ ሕዝብ አስተዳደር ማዕከላዊ ቦታ ሆኖ በመገኘቱም ነው፡፡ ይህንን ቀበሌ
ካለበት ሁኔታ በማንሳት፣ የእርሻና የበግ ርቢ ውጤት የልማት አስተዋጽኦ እየተሻሻለና እያደገ እንዲሔድ ለማድረግ፣
የአውራጃ አስተዳደር ከተማ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር የከተማውን ፕላን፣ የሥራ ሚኒስቴር
ደግሞ፣ የመንግስት ሕንፃዎች እንዲሰሩ ተደረገ›› (60)
የሚገርም ንድፍ ያላት ከተማ መሆኗን ማንም አይክድም
- መሐል ሜዳ! ግራና ቀኝ የሚያስኬዱ ሰፋፊ መንገዶችና በመሃላቸው ሰፊ አትክልት የተተከለበት መናፈሻ አለ፡፡
ከተማዋ በተመሰረተችበት በ1959 ዓ.ም ግንቦት 29 ቀን ጃንሆይ መሐል ሜዳ ሄደው የቆሙበት ሥፍራ ላይ ለመንዝና
ግሼ አርበኞች አነስተኛ መታሰቢያ ሐውልት ተሰርቷል፡፡ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ንጉሠ ነገሥቱን በሰልፍ የተቀበሉ
አንድ ሰው በስፍራው አግኝቼ ለማዋራት በቃሁ፡፡ መሐል ሜዳ ላይ በንጉሡ ጊዜ አንድ አሜሪካዊ እንደነበረና በሱም
ምክንያት ፕሮቴስታንት የሆኑ ሰዎች እንደነበሩ ነገሩኝ፡፡ አሁን በመሐል ሜዳም ሆነ በቀያ የፕሮቴስታንቶቹ ብዛት
በመቶዎች እንደሆነ እኝህ አባት ገምተዋል፡፡ የዚህ ማስታወሻ ጸሐፊ አንዱ ኃይማኖት ከሌላው ይበልጣል ወይንም ያንሳል
የሚል አመለካከት ባይኖረውም የመንዞች ማንነት በዚህ ሁኔታ እየተሸረሸረ መሄዱ በጽኑ ያሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ ኃይማኖቱ
ተቀይሮና አስተሳሰቡ ተሸርሽሮ እስኪያልቅ ድረስም የውጪው ዓለም እንደማይተኛ ይታየዋል፡፡ በመሐል ሜዳ አቅራቢያ
በምትገኘው በፀሐይ ሲና ሁለት ወጣት ወንዶች አሜሪካውያን፣ በሞላሌ ደግሞ አንድ እንደነበሩ ለመረዳት ችያለሁ፡፡
ሁሉንም ደርግ ከሀገር አስወጥቷቸዋል አሉ፡፡ ስለንጉሡ የመንዝ ጉብኝት ብዙ የተባለና የተቀለደ ነገር ስላለ መንዞችን
እንድትጠይቋቸው የቤት ሥራ ልስጣችሁ፡፡ ጃማይካዎች ጃንሆይ የረገጡትን መሬት ሁሉ መጎብኘት ስለሚፈልጉ እንደዚህ
ዓይነት ቦታ አፈላልግ ያልከኝ ወዳጄ ሆይ፣ ይሄው አንድ ነጥብ አስቆጥሬያለሁ፡፡
መሐል ሜዳ ደርሰን በዝነኛው
ነጻነት ሆቴል አረፍን፡፡ ግማሾቻችን አልጋ ስላላገኘን ወደ ነጻነት ሆቴል ቁጥር ሁለት ተዛወርን፡፡ የብርዱን ነገር
ዝም ነው፡፡ እግሬን ስታጠብ ያየኝ አንድ መምህር ‹‹ምኑ ቂል ነው እናንተ! አሁን ትታጠባለህ እንዴ!›› ብሎኛል፡፡
አስተያየት ሰጪው እውነቱን ነው የተናገረው፡፡ እንዲሁ ማታ ላይ እግር የመታጠብ ልማድ ነው እንዲህ ያስደረገኝ፡፡
‹‹እምዬ ደብረብርሃን ማሪኝ!›› ነው ያልነው የብርዱን ጽናትና ተወዳዳሪ አልባነት ባየን ጊዜ፡፡ ‹‹በመኝታ
ክፍላችን በር ስር ያልፍ የነበረ ሰራተኛ ለሌሎቹ ሰራተኞች ጮክ ብሎ ‹‹አንድ ጭማሪ ብርድልብስ›› ሲል ሰምተን
የተለመደ ትዕዛዝ መሆኑ ነው? ብለን ደንቆናል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ መንዞች ደብረብርሃን ሲመጡ በረደን
ማለታቸው ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ከሆነ ግን የብርዱና የንፋሱ ዓይነት መለያየቱ ነው አንዳችን ሌላው ጋ ስንሄድ
እንዲበርደን ያደረገው፡፡ እኔ ሳሲት ወይም ሰላድንጋይ ስሄድ አሁን አሁን ይበርደኝ ይዟል!
የደግነት ጥጉ!
ወደመጣንበት እስከምንመለስ ድረስ የቤርጎ ክፍያ አልተጠየቅንም፡፡ ይህም መምህራኑን አስገርሟል፡፡ ሰው የማመን
ጥግ! ሹሮ በድስት አርብ ማታ በላን እንጂ ከዚያ ውጪ ያለው ምግብ በሙሉ ስጋ ነክ ብቻ ነው፡፡ ቅቤው ከአምስት
ዓመት በኋላ አይኖርም የሚል መላምት አብረውኝ በነበሩት ምሁራን ተሰጥቷል፡፡ ምግብ ቤቶች ውስጥ አትክልት ያለበት
ምግብ የጠፋበት ምክንያት የከተማዋ ከአትክልት ማምረቻዎች መራቅ ወይንም የኅብረተሰቡ የአመጋገብ ልማድ ይሆናል፡፡
አንድ ሰው ደብረብርሃን ላይ በጾም ቀን ምግብ ቤት ሄዶ እንደማይመገብ ነግሮኝ ነበር፡፡ ያቀረበውም ምክንያት የሹሮ
የሹሮ እቤቱ መብላት እንደሚችል ነበር፡፡ ይቺ አስተሳሰብ መንዝም ትኖር ይሆን? መጠጥ ደግሞ ብርዱን ለመቋቋም ጥሩ
መፍትሔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጋቢም ዘመድ ሰጥቶኝ ለብሼ ብርዱን ቀንሶልኛል፡፡ ምንም ተባለ ምን ይህን መስተንግዶ
ያየን መምህራን ስለ መንዝ ክፉ ለማውራት አንችልም - የበላነው እንጀራ ያንቀናል! መንዝ አለመታደል ሆኖ ያላዩት
ሰዎች ብዙ ክፉ ሲያወሩበት ይሰማል፡፡ ክፉው ከምኑ ላይ ነው ብለን እንጠይቃለን! የተሳሳተ አመለካከት እንዴት
እንደሚቀረጽ የስነልቦና ምሁራን የሚናገሩትን ካለ እዚህ ጋ እንጋብዛለን፡፡ መንዞች፣ ሌሎች ስለነሱ ያላቸውን
አመለካከት ለማሻሻል መስራት ይኖርባቸዋል!
ዘመድ በሚል የወል ቃል ከምጠራቸው ግን ላመሰግን ግድ ይለኛል፡፡
ሸዋዬ ተስንቱ እኔን፣ ዳዊትንና መሰለን በደንብ አስተናግዶናል፡፡ ኧረ እንዲያው የአማርኛ ማጠር ምንድነው!
አንቀባሮናል ነው የሚባለው! ማሰሮ በሚያካክል ጠርሙስ የቀረበልን ዋልያ ቢራ መቼም አይረሳንም! ደግሞ ባናት ባናቱ!
የቆረጥነውን ጮማ የሚገልጽ አማርኛ በቋንቋው ዲግሪ የሰጠኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አላስተማረኝም! (አማርኛን
በንዑስ መማሬን ልብ ይሏል) መንገሻ ገበያውን ጥሎ ለኛ ሲል ሲንከራተት የዋለና ያመሸ ትሁት ሰው ነው፡፡ አሁን
መንገሻ 12ኛ ክፍል የደረሰች ልጅ አለችኝ ቢል ማን ያምነዋል! መንዝ ወጣት ያደርጋል ልበል! አቶ ከበደ
ደብረብርሃን ላይ ጭማቂ ቤት ከፍተው እንደነበርና ታክሲ ነጂም እንደነበሩ አውግተውናል፡፡ ኤርትራን ጭምር ያውቃሉ፡፡
አባታዊ አቀባበላቸውና የሐገር ቅፍራቸው ይምጣብኝ! ከእርሳቸው ጋር ስለ ኢትዮጵያ ማውራት የሰሞኑን የኢንተርኔት
ክርክርና ግርግር ሲሰማ ለከረመ ሰው መድኅን ነው፡፡ ደስታ ደግሞ ወጣት ልጅ ሲሆን ባለትዳር መሆኑን መስማቴ
አስደንግጦኛል፡፡ ቢያንስ ከሸዋዬ የሚያንስ ይመስለኛላ በዕድሜ! ሸዋዬ ትዳር ሲመሰርት ሰርግ እንደሚጠራኝ
አልጠራጠርም፡፡ የጋሽ ጌታቸው ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ግሩም ዘመዶቻችን ናችሁ - በግብዣችሁ
አስመስክራኋልና! ባልና ሚስት አሳድረውት በምግብ የበደሉትን የቆሎ ተማሪ ታሪክና አዲስ አበባ ወንድማቸው ዘንድ
ሄደው የመጡበትን አስቂኝ ወግ ያወጉልን ጋሽ ተዋበ ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡ ጋሽ ተስንቱ ነፍሳቸውን ይማረውና ጋሽ
ተዋበን አንድ ቅዳሜ ጠዋት የስጋ ቤቱን ሂሳብ እንዲቀበሉ ይጠይቋቸዋል አሉ፡፡ ‹‹ተው እንዲያው እንዳልቸገር በኋላ
ሲብዛዛ›› አሉ አሉ እየተባለ ይተረታል፡፡ የያገሩ ደማም!
ገበያው
አዙሪት የያዛት በግ ታሪክ
እመጓ ላይ ላነበባችሁ ሰዎች አንድ የዓይን ምስክርነት አለን፡፡ ከ350 ብር በታች ወይ ፍንክች! የተባለላትን በግ
ገዥው 300 ብር ሊገዟት ቢቋምጡም አልሆነም፡፡ ‹‹አዙሪት አደለም፤ ባሪያ ውግ ነው፤ አሁን ትነሳለች›› ይላል
ባለቤቷ፡፡ አንዱ ገዥ ታዲያ አልስማማ ሲሉ ‹‹አይ መንዜ›› ብሎ ሄደ፡፡ ከተሜው ራሱን እንደ መንዜ አልቆጠረም
ማለት ይሆን? ያው አንተ አንቺ መባባል ደግሞ ብርቅ ነው፡፡ ይህንንም እያየን አውግተንበታል፡፡
የበግ ጸጉር ምርት
አንድ ተራ ተሰጥቶት የሚገበያዩት አንድ ነገር መንዝ ውስጥ አለ፡፡ ይህም የበግ ጸጉር ምርት ነው፡፡ የበግ ጸጉር
በኪሎ 15 ብር ይሸጣል፡፡ የገዙትን የበግ ጸጉር ይፈትሉትና ኩባውን መልሰው ይሸጡታል ወይም ዝተት አለያም ምንጣፍ
ይሰሩበታል፡፡ አንድ ውስጡ በበግ ጸጉር የተሞላ ፍራሽ 280 ብር ሲሸጥ አይተናል፡፡ ገበሬዎች WELCOME የሚል
ጽሑፍ ያለበት ምንጣፍ ሰርተው ወደ ገበያ ይዘው ሲመጡ አይተን ፈገግ ማለታችን አልቀረም፡፡ በራሳችን ቋንቋም
እየጻፍን እንድንሸጥ አስቤያለሁ፡፡ ማናቸውንም ነገር መጻፍም ሆነ መሳል እንደሚቻል ባሙያዎቹ ነግረውኛል፡፡ ጀርመኖች
የስጋጃውን አሰራር ለማሻሻል እየሰሩ መሆኑን የባህል ጽ/ቤቱ አቶ ኤርሚያስ ሹክ ብሎኛል፡፡ አሜሪካውያን በፊት
ይህን ነበር የሚሰሩት፡፡
መንዞች ግን እዚህ ጋ አንድ ወቀሳ ተቀበሉኝ፡፡ እባካችሁ በየበራችሁ ላይ የቻይና ምንጣፍ አታድርጉ! የራሳችሁን ስጋጃ ራሳችሁ ካልተጠቀማችሁበት ሌላው እንዴት ይወደዋል? ባለቤቱ ያቀለለውን…
የመሐል ሜዳውን አሮጌ አየር ማረፊያ አየነው! እንደ ግብር ከፋይነታችን ስራ እንዲጀምር ግፊት ለማድረግ አስበናል!
መንዝ ላይ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር አልነበረም በሚል ክርክር ተጠምደን ለነበርነው ማስረጃ አለ! ከማስረጃው በፊት
ግን በወዳጃችን በጋሽ ጌታቸው ቤት መንዝ ላይ አውሮፕላን አርፎ ያውቃል አያውቅም የሚል ክርክር ተነስቶ እንደነበር
ልጠቁም፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር ስለመንዝ የአውሮፕላን ወሬ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ በማግስቱ ስንጎበኝ ያገኘነው
ማስረጃ የአውሮፕላኑ ማኮብኮቢያ ነው፡፡ አሁን ወደ አሞራ ማረፊያነት የተቀየረው ይህ ሜዳ መልሶ አውሮፕላን ማረፊያ
እንዲሆን አንዲት ልጅ በፌስቡክ አስተያየቷ መገንጠልን መክራለች፡፡ ‹ኢትዮጵያ ግን ሳንገነጠልም ታሰራልናለች› ብዬ
ልናገር ግድ አለኝ፡፡ ከአስጎብኝዎቻችን መቻኮል የተነሣ አውሮፕላን ማረፊያውን ሳናይ ማኮብኮቢያውን ብቻ ያየነው
ማኮብኮቢያው ራሱ በጣም ረጅም ስለሆነ ነው፡፡ ዝም ብላ airstrip ነገር አይደለችም ያየናት ለማለት ፈልጌ
ነው፡፡
ደብረብርሃን ተመልሼ አንዳንድ ሰዎችን ስለመንዝና የአውሮፕላን ወግ ለመጠየቅ ሞክሬያለሁ፡፡ አንድ
በመንዝ ህዝብ ዘንድ በአደራጅነታቸው የታወቁ ምሁር እንዳሉት ከሆነ ሰዉ ሁሉ ስንቅ እየያዘ ለሳምንት ያህል
አውሮፕላን ማረፊያውን ለመስራት ይሄድ ነበር፡፡ ከእርሳቸውም ቤት አውሮፕላን ማረፊያውን ለመስራት የሄዱ ነበሩ፡፡
ከምቦልቻ ላይ አውሮፕላን ማረፊያ ስላለ ይሄኛው አያስፈልገንም ሲሉ አውግተውኛል፡፡ እኔ ግን አልስማማም - ከምቦልቻ
ወሎ፣ መንዝ ሸዋ! ከአዲስ አበባ በ332 ኪሎሜትር ርቀት (ቅርበት አላልኩም) ላይ ሆነን በአየር መጓዝ ይብዛብን
እንዴ!
መንዝ ላይ የበሰለ ምግብ መሸጥ ውርደት እንደነበርና ፀሐይ ሲና ላይ ቤተክርስቲያን ያሰሩ አንድ
ታዋቂ መንዜ 25 ጉራጌዎችን ወስደው ህዝቡን ምግብ መሸጥና ንግድ አንዳስለመዱም ነግረውኛል እኝህ መምህር፡፡
ለአምስት ዓመት ደርግን ብቻውን የተዋጋ ህዝብ ተብሎ የሚሞካሸው የመንዝ ህዝብ ለአንቶኖቭና ለሌሎችም አውሮፕላኖች
አዲስ አልነበረም ቢሏችሁ እንዳይገርማችሁ፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው በዚህ መቅረቱ ልብ ሰነባሪ ነው የሚሉት ደብረ
ብርሃን ላይ ያናገርኳቸው አንድ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ‹‹መንዝ ካለው የመንገድ አለመመቸት የተነሣ የአየር ጉዞ
አማራጭና ቀልጣፋ የመጓጓዣ አማራጭ ሊሆን ይችላል›› ብለው ያስባሉ፡፡
በሌላ አስገራሚ ወሬ፡-
ሬም፣ የአምሳ በር፣ ንገት ስለሚባሉ ስፍራዎች ሰምታችሁ ታቃላችሁ? ግሼ ውስጥ ያሉ መንደሮች ናቸው፡፡ የአውሮፕላን
አደጋ ወሬ የነገሩኝ መምህር ትዝታቸው አሁንም ትኩስ ነው፡፡ የመንዝ ሳይሆን የለንደን ወሬ ይመስላችኋል፡፡ መንገድ
ላይ አግኝቻቸው ወደ 20 ደቂቃ ለሚጠጋ ጊዜ በፀሐይ ላይ ቆመው አናገሩኝ፡፡ እርሳቸው ልጅ ሆነው እንደዚህ ያሉ
ትልልቅ ሂደቶችን ማስታወስ በማይችሉበት ወቅት እናታቸው ያዩትን ስለነገሯቸው ያዩ ያህል ነው ንግግራቸው፡፡ እናታቸው
ያዩት አውሮፕላን በሸለቆ ውስጥ ይሄድ ነበር፡፡ በተራሮች የተከበበችው የንገት ሸለቆ ለአውሮፕላን ጉዞ አትመችም፡፡
አውሮፕላኑን እዚያ ምን አመጣው ከተባለ ደግሞ ጉም ይሆናል መልሱ፡፡ ደመናና ጉም ሲያስቸግረው ብርሃን ፍለጋ ወደ
ንገት መጣ፡፡ ወደላይ ወደ ሰማይ መውጫ መንገድ ሲፈልግም መንገድ ያገኘ መሰለውና ሽቅብ ሄደ፡፡ ከተራራው ወጣ
እንዳለ ደግሞ ሜዳ ያገኘ መሰለውና ከሌላው ተራራ ጋር ተጋጨ፡፡ ከገደል ገደል ይላተምና የአደጋው ድምጽም ከሸለቆ
ሸለቆ ያስተጋባ ጀመር፡፡ አንድ በስራ ላይ የነበሩ እና ወሬውን ያዩ ገበሬ በመደናገጥና ሕዝብም እንዲደርስ በማሰብ
‹‹ውውው የመንግስት ሮቢላ!!›› እያሉ መጮሃቸው ይተረታል፡፡ ሙሽሮች ናቸው አሉ የተሳፈሩት፡፡ በሕይወት
አልተረፉም፡፡ ከአውሮፕላኑ ስብርባሪ ውስጥ ገንዘብ ተገኘ፡፡ ያንን ገንዘብም ቀድመው የደረሱ ግማሹን ወሰዱት፡፡
በኋላ አስተዳዳሪዎቹ መጥተው አገሩ ሲረጋጋ እየገረፉ ገንዘቡን ተቀበሏቸው፡፡ የዘረፉትም የአውሮፕላን ብር ሌባ የሚል
ስም ወጣላቸው፡፡ የአውሮፕላኑ ቁርጥራጭም በየማሳው የወፍ ማስፈራሪያ ይሆን ዘንድ ተተከለ፡፡ የቤት ቁሳቁስም
ተሰራበት፡፡ በአጭሩ በሸዋ አማርኛ ራስ አበበ አረጋይ የጣሏትን አውሮፕላን ዓይነት ዕጣ ገጠመው!
‹‹ቆላው
ውስጥ አውሮፕላን ደመና አስቸግሮት ሲያርፍ ምግብና ጠላ እንወስድ ነበር›› ብለው እኝሁ ምሁር አውግተውኛል፡፡
‹በአደጋ አውሮፕላን ቢያርፍ አይገርምም› ብትሉ ተሳስታችኋል፡፡ ለመጓጓዣም አውሮፕላንን መንዝ ተጠቅማለች፡፡
ለጉብኝት፣ ባለስልጣኖችን ለማድረስ፣ የእርዳታ እህል ለማመላለስና ለሌሎችም ዓላማዎች አውሮፕላኖች መንዝ ብዙ ጊዜ
አርፈዋል፡፡ ‹‹አውሮፕላን እያየን እኮ ነው ያደግነው! ወደኋላ እንደሄድን ይሰማኛል›› ይሉኛል እኚሁ ምሁር
በቁጭት፡፡ ተራ የአውሮፕላን ማየትን ያለፉት በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪነታው ወቅት እንደሆነ የሚናገሩት
ምሁሩ አውሮፕላን ሲመጣ ተሯሩጠው እንደሚሄዱ ይናገራሉ፡፡ አንድ ትዝታቸውም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
የማይረሳ የህጻን ሞት! ፡-
አንድ የእርዳታ ሰጪዎቹ ፈረንጆች ልጅ (ስምንት ዓመት ገደማ ይሆነዋል አሉ) መጋዘን ውስጥ የእርዳታ እህል የያዘ
ጆንያ ወድቆበት ሞተ፡፡ ሲላቀሱ ያዩትን ሳይኮሎጂስቱ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ፈረንጆቹ ሐዘኑ ልባቸው ገባ›› አሉ፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ ‹‹መንዝ ሩቅ ስለሆነ አውሮፕላን ያስፈልገዋል›› ይሏችኋል፡፡
‹መንዜ› ፈረንጆች
ጓሳ ውስጥ ፈረንጆች ካምፕ አላቸው፡፡ ዶ/ር ካናታ መንዝ ውስጥ የሚኖር ሚሽነሪ ሐኪም ነበር፡፡ ዶናልድ ሌቪን
መንዝ ኖሮ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ የሰላም ጓዶች አሁንም አሉ፡፡ መሐል ሜዳ መሰናዶ 12ኛ ክፍል የምታስተምረውም
የእንግሊዝኛ መምህርት አሜሪካዊት ነች፡፡ ለማንኛውም የመንዝና የፈረንጆች ግንኙነት አንድ ትኩረታችንን የሚስብ ነገር
ነው፡፡ ንገት ላይ ስለተከሰከሰችው አውሮፕላን መረጃ ለማፈላለግ ወደ ኢንተርኔት ገብቼ በነበረበት ወቅት ስለሌላ
ወደ መንዝ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሄዱ ግለሰብ የሚያትት መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ እንደሚከተለው እንግሊዝኛውን እንዳለ
በፎቶ አቀርዋለሁ፡፡ ፎቶው ካልከፈተላችሁ Our God Still Speaks ብላችሁ ፈልጉ፡፡
በተያያዘ ወሬ
የልጅ ኢያሱ ጉግስ መጫወቻ መንዝ መኖሩን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የአሁኑን የመንግስት አስተዳደር ሁኔታ አስመልክቶ ብዙም ለመሰለል ባልችልም ቅሉ መንዝ ላይ የቤተሰብ ፖሊስ እንዳለ ደርሼበታለሁ፡፡
‹ኤቲኤም በመጠቀም የመጀመሪያው ነኝ መሰለኝ ማሽኑ በጣም አዲስ ነው› አለኝ አንድ ወዳጄ፡፡ ‹ሙዚቃም ጋበዘኝ
ማሽኑ› ሲል አከለ፡፡ ጨዋታ አዋቂው ወሎዬ ጓዴ ለረጅም ሰዓት ለርቀት ትምህርት ተማሪዎቹ ማጠናከሪያ እንዳስተማረና
በበቃኝ እንዳሰናበታቸው አውግቶልኛል፡፡
የባህል ነገር
መንዝ ላይ አልፎ አልፎ የስነጽሑፍ ምሽት
ይካሄዳል፡፡ ስፖንሰር በማፈላለግ ቢራ ይጋበዛል፤ ሻማ እያበሩም ይመሰጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ግን ለባህል ግድ
የሚሰጠው አስተዳደር ቢኖር እንዴት በሰመረ! በሐገራችን በጣም ከተበደሉ ዘርፎች አንዱ ባሕል ስለሆነ የሰራተኞቹ
ድካም አጋዥ የለውም፡፡ ስለ ባህልም ሆነ ስለ ማናቸውም ስራ መዘመንና መሻሻል ስታወሯቸው ብዙ የመንግስት ሰራተኞችም
ሆኑ ነዋሪዎች የዩኒቨርሲቲውን እገዛ ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ እኛም መልዕክቱን አድርሰናል፡፡
አንዳንድ ተጠያቂዎች እንዳሉትና እኔም እንዳየሁት
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ሸዋ ከከፈታቸው ስድስት የርቀት ትምህርት ማስተባበሪያ ማዕከላት አንዱ በመሐል ሜዳ ስለሚገኝ ነበር ከመምህራን የስራ ባልደረቦቼ ጋር ወደ ስፍራው የተጓዝኩት፡፡
የርቀት ትምህርቱን አሰጣጥ አስመልክቶ የጠየኳቸው አንድ መምህር እንዳሉት ተማሪዎቹ በዚያ ብርድ ተጠብሰው ነው
ብሩን የሚያገኙትና የሚከፍሉት፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ግን ፈተና ስላከበደባቸው ከግማሽ በላይ ተማሪ ወድቋል፡፡ ለምን
እንደርቀትነቱ አይታይም?›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ሌሎች ምልከታዎቻቸውንም እኝሁ ከደቡብ ኢትዮጵያ የሚወለዱ
ምሁር አውግተውኛል፡፡ ‹‹ልገስግስ ልሂዳ የሚለውን ዘፈን እንኳን አንዴ ነው የሰማነው፤ ዘመናዊ ዘፈን ነው ያለው
በየስፍራው፡፡ ሆቴል አላየሁም፡፡ ሌላ ቦታ ስጋ ቤቱ ውጪ ላይ ነው ያለው፡፡ መሐል ሜዳ ግን ስጋው ጓዳ ነው፡፡
በዚያ ላይ ሴቶች ናቸው ስጋ የሚሸጡት፡፡ በዚያ የገጠር ከተማ ውስጥ ሁለት፣ ሦስት ሺሻ ቤት ማየቴ አስደንግጦኛል፡፡
በመምጫችን ዋዜማ ካልሆነ በቀር መብራት ያለመጥፋቱ ግሩም ነው፡፡ ገበያው ደግሞ ያልተደለደለ ቦታ ነው - ገደላማ -
ድንጋይ - ቁልቁለት - ዳገት! ቱቶሪያል መስጫ ዋይትቦርድ፣ ኤልሲዲ ቢኖር ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አሁን መንገድ
ላይ ተገናኘን እንጂ ብዙ ነገር እነግርህ ነበር፡፡››
‹‹ካምፓስ እንጂ የርቀት ትምህርት ቅርንጫፍ መክፈት
ሌሎች ብዙ የግል ኮሌጆች ስላሉ ብዙም አያበረክትም፡፡ ካምፓስ ለእድገት ይጠቅማል፤ መንገዱ ወደፊት ዋና መንገድ
ስለሚሆን የህዝብ ለህዝብ ፍሰትንና ገበያን ስለሚያበረታታ ጥሩ ነው፡፡ ‹አንዱን ካምፓስ በደንብ መጠቀምና ጥራቱን
ማስጠበቅ ነው› ይላል ዩኒቨርሲው ሲጠየቅ፡፡ እስኪ የዩኒቨርሲቲውን ቦርድ ወይም ዞኑን ጠይቅ፡፡ የዩኒቨርሲተው
ኃላፊዎች ብዙም ያመኑበት አይመስለኝም›› የሚለው የአንድ የአካባቢው ተወላጅ መምህር ሃሳብ ነው፡፡
ደቦ በሚል
ስም የተከፈተው ቤተመጻሕፍት የአንዲት የከተማው ተወላጅ እንስት ዶክተር ስራ መሆኑን ሰምቼ ደስ ብሎኛል፡፡ ፈረስ
የሚያስፈትን አዳራሽ! የኮድ ኢትዮጵያን ቤተመጻሕፍትም አይተናል፡፡ ትንሽ ትኩረት ቢጨመርለትና መጻሕፍቱ ቢታዩ
መልካም ነው፡፡ የመሐል ሜዳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልን ግዝፈት አይቼ ምን አሰብኩ መሰላችሁ - አቤት ማማሩ ነው
ያልኩት! ከተማው ውስጥ አስፋልት ረግጫለሁ - ጥራቱ የተጓደለ ቢሆንም፡፡ ወደ ዓለም ከተማ የሚወስደው የአዲሱ
መንገድ አካል ነው መሰለኝ፡፡
‹‹መንዝ ትኩረት አጥታለች፡፡ የመሰረተ-ልማት ችግር አለባት፡፡ መሐል ሜዳ
አቧራውን ለማስታገስ ኮብልስቶን እንኳን ቢሰራ ምን አለበት?›› እያሉ አንዱ መምህር ሲያወሩ ሁሉም መምህር እየሰማ
በመስማመት ራሱን ይነቀንቃል፡፡
የመጨረሻው መጀመሪያ
‹‹አገርሽ ሄጄ መጣሁ፤ በጣም ደስ የሚል አገር
ነው ያላችሁ›› ያልኳት አንድ የመሐል ሜዳ ልጅ በአስተያየቴ አልተደሰተችም፡፡ ‹‹ሰዉ ክፉ ነው! ምናልባት አገሩ
ጥሩ ሊሆን ይችላል!›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም አንዳንዴ ስለትውልድ ስፍራዬ ስለ ሳሲት የሚሰማኝን ነገር ነው
የተናገረችው፡፡ አብሬያቸው ብዙ ስቆይ ፀባያቸው ይቀየር አይቀየር ባላውቅም በአሁኑ ቆይታዬ ግን መንዞች ተወዳጅ
ናቸው!
በመጨረሻም
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ከዞኑ ባህል ጽ/ቤት ጋር
በመተባበር ሰሞኑን የውይይትና ጉብኝት መርሃ-ግብር ነበራቸው፡፡ በዚህም ወቅት መንዝ ጓሳንና መሐል ሜዳን
ጎብኝተዋል፡፡ ለአትኩሮታቸውና ለጥረታቸውም አመሰግናለሁ፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያውን ነገር ግን አደራ! ቶሎ
እንዲሰራልን እንደ ግብር ከፋይነቴ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
መጪው የጉዞ ማስታወሻችን ስለ አምቦ ይሆናል፡፡
አቹማ ወልሃገራ!