የናይሮቢ ጉዞ
ወግ
መዘምር ግርማ
ነሐሴ 2015
ዓ.ም.
በዚህ ዓመት
ወደ ናይጄሪያ ለመሄድ ብፈልግም አልሆነልኝም፡፡ ይሁን እንጂ አንድ የአፍሪካ ጉዞ ለማድረግ አስቤ ስለነበርና መሄድም ግድ
ስለሚለኝ በቅርባችን ባለችው በኬኒያ ጉዞ ተክሻለሁ፡፡ ለ2023ቱ 13ኛው የፓን አፍሪካን ሊትሬሲ ፎር ኦል (PALFA) ማለትም
የአፍሪካ ማንበብና መጻፍ ለሁሉም ስብሰባ ከዘርፉ ኢንዱስትሪ የልዑክ አባል ሆኜ ናይሮቢ እንድከት መልዕክት ከደረሰኝ
ከራርሟል፡፡ አስፈላጊውን ዝግጅትም ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ከኢንተርኔት ሳጣራ ወደ አገሪቱ ስትገቡ ፌስታል ከተገኘባችሁ ትቀጣላችሁ
የሚለውንና የቢጫ ወባ ክትባት ካርዴን መርሳት እንደሌለብኝ የሚያትተውን ማሳሰቢያ ጨምሮ ሌሎቹን ለመተግበር ጥሬያለሁ፡፡
እንደ
እስከዛሬዎቹ ጉዞዎቼ የፓስፖርትና ቪዛ እንግልት የሌለው ይህኛው የጎረቤት አገራችን ጉዞ ለሰባት ወራት ሳላያት የቆየኋትን አዲስ
አበባን በክረምቱ ማብቂያ እንዳያት አስችሎኛል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ከምሰማው ሁኔታ የተነሣ በነፃነት የምዘዋወር ስላልመሰለኝ
ሄጄ ወደ ማረፊያዬ ወደ ፒያሳ አቀናሁ፡፡ በብሔራዊ ባንክም የዉጪ ምንዛሬ ለማስፈቀድ እክል ይገጥመኛል ብዬ ባስብም ያለምንም
ችግር የጠየቅሁትን ያህል ገንዘብ ተፈቀደልኝ፡፡ ኢንተርኔት ከተዘጋበት አማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ስገባ ከዓለም በቀላሉና
በማናቸውም ደቂቃ መገናኘት በመቻሌ ልዩነቱ ገብቶኛል፡፡ ከጦርነት ቀጣናም በመውጣቴ እፎይታው ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አበባስ
ምን ደግ ይወራለታል እንጂ!
የአሜሪካ
የሠላም ጓዶች ያሳዩኝ ሰላማዊና ፀጥታ የሰፈነበት የፒያሣው ባሮ መኝታ ቤት እንደ ወትሮው ገዳም መስሏል፡፡ በጠዋት ሰለደረስኩ
ያልደረቀ አንሶላ አንጥፈው ሲያስበርዱኝ አደሩ፡፡ በእርግጥ በሚያውቁት ቦታ ዕቃን አሳርፎ ፒያሳን መዞር ያስደስታል፡፡ ከአልጋ
ቤቱ ኃላፊ ጋር ቤቱን በምን ሁኔታ እንደማውቀው ስነግረው የአሜሪካ የሠላም ጓዶች በኢምባሲ ጥቆማ እዚያ እንደሚያርፉና አልጋ
ቢጠፋ እንኳን ደብል ቤድ ይዘው እንደሚያድሩ በትዝታ መልክ ነገረኝ፡፡ አሁን ከኮቪድ በኋላ ከአገሪቱ ስለወጡና ስላልተመለሱ ግን
አለመምጣታቸውን ታዝቧል፡፡ እዚያ ቤት ሳርፍ የአሜሪካውያኑ በጎፈቃደኞች የሥራ መንፈስ ይታወሰኝና እነሣሣለሁ፡፡ ከበጎፈቃደኞቹም
ዉጪ ያለው ፈረንጅ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ለጉብኝት መምጣት ማቆሙን ሰራተኛው አልደበቀኝም፡፡
በባለፈው
ጉዞዬ ጀዋር መሐመድ ተከበብኩ ብሎ እንዳስጀመረው ዓይነት ሁከት እንደማይኖርና አየር ማረፊያ ቁጭ ብዬ አድሬ በዚያው
እንደማልሳፈር ተስፋ አድርጌ የነበረ ሲሆን ተሳክቶልኝ በማለዳ በሰላም ወደ ቦሌ በታክሲ ሄድኩ፡፡ በዋዜማው ብሔራዊ ባንክ
በሠጠኋቸው የአውሮፕላን ትኬት ምትክ ፕሪንት ሳላደርግ አድሬ ስለነበር ለማድረግ ቦሌን ብዙ ስዞር አረፈድኩና በግድ ተሳክቶልኝ ጨራርሼ
2፡00 ላይ ተርሚናል 2 ደረስኩ፡፡ የትኬት ኮፒ ልጠየቅ እችላለሁ በሚል ስጋትና የአየር መንገዱም ድረገጽ ያንን ስለሚመክር
ነው መሯሯጤ፡፡
አየር
መንገዶች ውስጥ አሰልቺ ፍተሻ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ቼክ ኢን ምን ያህል እንደሚያሰለች ያየ ያውቀዋል፡፡ ኦንላይንም ቼክ ኢን አላደረኩም፡፡
ለእኔ እንኳን ነገሩ ብዙም አይደንቀኝም፡፡ ምክንያቱም ከደብረብርሃን እስከ አዲስ አበባ የመጣሁት መታወቂያ ሳሳይ፣ ስወጣ
ስወርድና ስፈተሽ ስለሆነ ነው፡፡
በዚህ
የጦርነት ወቅት ዉጪ ስለመሄድ ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ዶክተር
ጌታቸው ቦሎዲያ ሲበዛ ቀልድ አዋቂ ነበሩ። በደርግ ጊዜ አንድ ቀን ወደ ዉጪ አገር ሊሄዱ ቦሌ እንደደረሱ ሁሉን ነገር ጨራርሰው አንድ ጥያቄ ቀረበላቸው።
"500 ብር ያስይዙ።"
"እሱ ደግሞ የምንድነው?"
"ዜጎች ዉጪ አገር ሄደው እንዳይቀሩ በሚል የወጣ ትዕዛዝ ነው።"
"እኔ ጌታቸው ነኝ አገሬን ለማንም አስር አለቃ ትቼ የምቀረው!"
ይህ
ቀልድ ወይም ቁም ነገር ትዝ ያለኝ ከአገር ወጥቶ ስለመቅረት አንዳንዶች ከሚያወሩት በመነሣት ነው፡፡ እኔ መቅረትን ፈጽሞ አላስበውም፤
እንደ አጋጣሚ ሆኖ በቅርብ ዓመታት በምሄድባቸው ጊዜያት ሁሉ አገር ውስጥ ሰላም የደፈረሰባቸው ቢሆኑም፡፡ እንደ ዶክተር ጌታቸው
ባይሆንም እኔም ለምን ውጪ አገር አትሄድም ወይም ስትሄድ አትቀርም ለሚሉኝ ወዳጅ ዘመዶቼ ‹‹አንቺ እዚህ ብቻሽን አገሬን ልትግጪ!››
የምትል አስቂኝ ምላሽ አለችኝ፡፡
በጆሃንስበርግ
ሁለት ጉዞዎቼ ወቅት የጎበኘኋቸው የቀድሞ እስርቤትና የአሁን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያውያን የንግድ ሰፈርና
ሌሎች፣ በጋና ጉዞዎቼ ወቅት የጎበኘኋቸው የአትላንቲክ ዳርቻ፣ የባሪያዎች የመጨረሻ መሳፈሪያ ቦታ፣ የኩዋሜ ኑክሩማህ ሙዞሊየም፣
የአሻንቴዎች ሰፈር፣ የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ ሰፈር ወዘተ ነበሩ፡፡ በ2019 በናይሮቢ የሁለት ሰዓታት ትራንዚት ሳደርግ አርፌ
የኬኒያ ሻይ ከመጠጣቴ በቀር አላውቃትም፡፡ ስለ አፍሪካ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አለኝ፡፡ ዋና ከተሞችን ብቻ በማየት ያልተገደቡ ጎዞዎች
እንዲኖሩኝ ዕቅድ ቢኖረኝም ላሁኑ ግን ናይሮቢን በተቻለኝ አቅም ለማየት እጥራለሁ፡፡
እስከዛሬ
ካየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ በረራችን ዘገየ፡፡ ምክንያቱም የአየር ማረፊያው ማኮብኮቢያ በሌሎች አውሮፕላኖች በመያዙ ነው፡፡ የአዲሱ
አየር ማረፊያ ሥራ ቢፋጠን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አውሮፕላኑ
ውስጥ ብዙም ኢትዮጵያዊ ተጓዥ አላየሁም፡፡ ይልቅ ወጣት ኬንያውያን ሴቶችን አይቻለሁ፡፡ እነርሱም ከአረብ አገሮች የሚመለሱ
በቤት ሰራተኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ እንደሆኑ ተረዳሁ፡፡ ስላሉበትም ሁኔታ ጠይቄያለሁ፡፡ ብዙዎቹ አንድ ልጅ ወልደው የሄዱ
ናቸው፡፡
ኢምባሲ መሄድ አያስፈልገንም። ኤሌክትሮኒክ ቪዛ ዳውንሎድ ማድረግም እንዲሁ። ወደ ጎረቤት አገራችን በፓስፖርት ብቻ እንገባለን። ለአሁኑ ምክንያት ይጠይቃሉ። እሱም ገብታችሁ መሄጃ እንዳታጡ ነው። የምሄደው
ለጉብኝትም ማለት ይቻላል። "ቪዛ ለዉጪ ዜጎች ነው የሚያስፈልገው!" አለኝ በጆሞ
ኬኒያታ አየር ማረፊያ ከኋላዬ የቆመ ኢትዮጵያዊ። ከኬኒያ ወደ ዩጋንዳ ደግሞ የታደሰ መታወቂያ ካሳዩ ለኬንያውያን በቂ ነው። በሂደት በመላው አፍሪካ ለማድረግ ታስቧል አለኝ አንድ
ኬንያዊ፡፡ ከአንድ የአሜሪካ ግዛት ወደ ሌላው መሄድ እንደሚቻለው እስኪሆን መሥራት ይኖርብናል። የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጥሩ እየሠሩ ነው። እኛም ለመቀላቀል አስፈላጊውን ብናደርግ ይሻለናል። አፍሪካውያን
ለመተባበር ገንዘባችን፣ ንግዱ፣ ፖለቲካው ምኑ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፡፡
ናይሮቢ እንደደረስን ስሜ በትልቁ የታተመበትን
ወረቀት የያዘ ሰው አይቼ ቀረብኩት ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ወደ ሆቴል ጉዞ ጀመርን፡፡ በየመንገዱ ዳር የቆሙ በቆርቆሮና ብረት የተሰሩ የዱር እንስሳት ቅርፆች ይታያሉ። ፓርክ
ለመጎብኘት የሚያገለግሉና እንስሶች የማይሰብሯቸው የመስክ መኪኖችም በየመንገዱ ውር ውር ሲሉ ይስተዋላሉ። ሹፌሩ
ስለቦታዎቹ ሁሉ ማብራሪያ ይሰጠኛል፡፡ በቻልኩት መጠን ማስታወቂያዎችን በማየት የአገሩን ሁኔታ ለመረዳት እየጣርኩ ነው፡፡ አንድ
የምግብ ማስታወቂ ‹‹Finger licking good›› ይላል፡፡ ጣት የሚያስልስ መሆኑ
ነው፡፡ ከኛ ግነት የተሞላበት ‹‹ጣት የሚያስቆረጥም›› ይሻላል ብዬ አለፍኩት፡፡ ወጣ ወዳለው ሆቴላችን ስናመራ የ KFC ማስታወቂያዎችን አይቻለሁ፡፡ ማታቱ በመባል የሚጠሩትን ታክሲዎችንም እንዲሁ፡፡ ሞተር ሳይክልም
ቦዳ ቦዳ እንደሚባልና ሰውን ለመጫን እንደ ራይድ እንደሚጠራ ገባኝ፡፡ ባጃጅ ቱክ ቱክ ትባላለች፡፡ ለማየት ግን አልቻልኩም፡፡
የናይሮቢ
ብሔራዊ ፓርክን መግቢያ አይቻለሁ፡፡ አለመጎብኘቴ ግን ይቆጨኛል፡፡ ትልልቆቹ አምስቱ የተባሉትንም ሆነ ሌሎችን የዱር እንስሳት
ባይ መልካም ነበር፡፡ አነስተኛ አውሮፕላኖች በየጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሲነሱና ሲያርፉ የሚሰማና የሚታይበትን የግል አየር ማረፊያ ዊንስተንን ሹፌሩ አሳየኝ፡፡ የዱር
እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት የአገሩ ኢኮኖሚ መሰረት መሆኑ ያስታውቃል።
ፓርኮች በጣም ተጎብኚ ናቸው፡፡ አሁን አገሩን ቀጥ አድርጎ ከያዘው ገቢ የተወሰነው የሚገኘው ኬንያውያን የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንደነበሩ እንግሊዞቹ ከኢትዮጵያ በሄሊኮፕተር ከነዱት የዱር እንስሳት መንጋ ሊሆን ይችላል የሚል ነገር በአእምሮዬ አቃጨለ። ሌላ
የምንዋጋው አገር አግኝተናል፡፡ በእርግጥ በዓመት ለአንድ ሺህ ወጣቶች የትምህርት ዕድል ቢሰጡልን ወይም በቱሪዝም ዘርፍ
ቢያሳትፉን የመዋጋት ፍላጎታችን ይቀንስ ይመስለኛል፡፡ እናንተስ ምን አሰባችሁ?
በስልጣን ላይ ያለውን መሪ ፎቶ ቢዝነሶች እንዲለጥፉ ይገደዳሉ፡፡ ይህንንም በየቦታው አየሁ፡፡ አሜሪካውያን የኃይማኖት
ሰዎች ለአንድ መንፈሳዊ ጉባኤ መጥተው ካረፍንበት ሆቴል አይቻለሁ፡፡ ለኃይማኖት ስብከት የማይፈልገን የለም! የምስራቅ አፍሪካ ልጆችም
ለኪስዋህሊ ቋንቋ ትምህርት መነሻ የሚሆን የሦስት ቀናት ካምፕ በሆቴሉ አካሂደዋል፡፡
እኛ አፍሪካውያን የተለያየን ዓይነት ህዝቦች ነን። በባህል፣ በኃይማኖት፣ በቆዳ ቀለም፣ በአለባበስ፣ በቁመት ወዘተ ልዩ ልዩ ሰዎችን እንኳን በአፍሪካ በአንድ አካባቢም ማየት የተለመደ ነው። በግሌ ዘንድሮ አፍሪካውያንን በተለይም ከኢትዮጵያ ዉጪ ያሉትን ሴቶች በማድነቅ ወይም በማዳነቅ
ተግባር ላይ እገኛለሁ። በመሆኑም ስለኬንያውያን ሴቶች አንዳንድ ነገር እናነሣለን። ከአሁን በፊት በእርግጥ በአካልም ሆነ በሚዲያ የማውቃቸው ኬንያውያን አሉ። የደቡብ ኢትዮጵያ ሴቶችን ሳይቀር ኬንያውያን መስለውኝ በእንግሊዝኛ ማናገሬ የቅርብ ጊዜ ትውስታዬ ነው። እስካሁን የናይሮቢ ሴቶችን ለማየት ብዙም አልቻልኩም ነበር። በታክሲ ሆቴል እስከምደርስ ከኢትዮጵያውያን አንፃር
ጠቆር ያሉና አፍንጫቸው ጎረድ ያሉ ብዙ ሴቶችን አየሁ። እንደ ኢትዮጵያውያን ሰውነታቸው ድቅቅ ያሉ አይደሉም። ፀጉራቸው ግን ሕይወት የለውም። ምክንያቱም ዊግ ስለሆነ። ዊግ
ካልሆነ በጣም አጭር ጉንጉን ወይም እኛ አገር ወንዶች አንደምንስተካከለው የተስተካከለ ነው፡፡ ሆቴል
ደርሼ ወደተያዘልኝ አልጋ ለመሄድ የምትወስደኝ ልጅ ሰላምታ ስታቀርብልኝና ስታወራኝ ምንም እንኳን በእንግሊዝኛ ቢሆንም ኢትዮጵያዊት መሰለችኝ። ያው ኢትዮጵያ "ቆንጆ" የሚባሉትን ዓይነት የሌላ
አገር ሰው ስናይ ኢትዮጵያዊ ማለት ይቀናናል አይደል? ጥርሷ የወንጂ ልጅ ዓይነት ነው። ፀጉሯም የራሷ ይመስላል። "አቡሽ ዘለቀን እወደዋለሁ። ሌሎቹንም ዘፋኞች እንዲሁ። ሞያሌን አውቀዋለሁ። ኢትዮጵያውያን እዚህ ሲያርፉ እንደ አገሬ ልጆች የማስተናግዳቸው ከሰሜን ኬንያ ስለመጣሁ ነው። ... " አለችኝ። ሰላምታ
ሳቀርብላት እጅ ከተጨባበጥን በኋላ ወደኔ ስቤያት ግራ ትከሻዋን በቀኝ በትከሻዬ መግጨቴ በአገሬ የለመድኩት ያልተገባ የሰላምታ
ዓይነት መሆኑ ገባኝ፡፡ እሷም ግር አላት፡፡ የምሳተፍበት ፕሮጀክት ሰዎች ከደቡብ ሱዳን፣ ከካሜሮንና ከኬንያ መጥተው ስብሰባ ስለሚሳተፉ እዚሁ ሆቴል ናቸው። ስለ
ልጅቱ ስነግራቸው "አግባት"
ብለው አደፋፈሩኝ። ሲጣራ ልጅም ባልም አላት። ካርኒቮር
በተባለ ሆቴል ሐሙስ በነበረን የእራት
ግብዣ ላይ ከአንዷ
አስተናጋጅ
ጋር ሳወራ ጊኪዩ
ተናጋሪ መሆኗን ነገረችኝ። "ጋሂካ ዴንዳ" ብዬ አሳቅኋት። የጊኪዩ ሴት መተዋወቅ እንደምፈልግ ስነግራት ከእሷ ከተዋወቅሁ እንደሚበቃ ነገረችኝ። ለተግባቢነቷ አመስግኜ ከጓደኞቼ ተደባለቅሁ። አንዷ ቀጭን፣ ጥቁር፣ ቆንጆ ወጣት ልጅ የስጦታ ዕቃ መግዣ ሱቅ "ጃምቦ" ብዬ በኪስዋህሊ ሰላምታ ሳቀርብላት "ሰላም ነው?" በማለት መለሰችልኝ። በድንጋጤ ዝም አልኩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ያየችውና የምነግራት አለቃዬ የሞያሌዋን መርጣልኝ ነበር። ባለ ትዳር ስትሆንባት ተወችው እንጂ።
‹‹ካልሆነ የእህቴን ልጅ አግባ!›› ስትለኝ የተሰማኝ ድንጋጤ ከባድ ነበር። በቀልድና በቁምነገር መሃል እዋልላለሁ። ሴት ልጁን እንዳገባ እንደፈቀደልኝ እንደ ናይጀሪያዊው የፕሮጀክታችን አባል ጓደኛዬ እንደ ተርኩሌ ሁሉ ዶርካስም የእህቷን ልጅ እንዳገባ ፈቀደችልኝ። ግልጽ ምላሽ አልሰጠኋትም። የእህቶቿን ልጆች አውቃቸዋለሁ። ልጅ ያልወለዱትንና ወጣቶቹን ከሆነ በጨረታው እገደዳለሁ። በቤተሰብ
የሚደረግ የማጨት ተግባር ከቆመ መቆየቱን ረሳሁት መሰለኝ! ችላ ካልኩ ወይ ከፕሮጀክቱ ትቀንሰኛለች። ሌላ ቦታ ያዋራኋት ልጅ ‹‹እናንተ ካገራችሁ ሰው ዉጪ አታገቡም አልተባለም እንዴ!›› ብላ
አስደንግጣኛለች፡፡ እኔም አስተባብያለሁ፡፡ በተያያዘ ዜና ቆንጆ ሴት አይታችሁ በድንጋጤ የምትሸበሩ ወንዶች ካላችሁ አደራችሁን ከሩዋንዳ ለስብሰባ የመጣችውን አሎይዜን እንዳታዩ! የሩዋንዳው
ቡድን ሲገባ ከአፍሪካ ቆንጆዎቹ እንደገቡ ገብቶኛል፡፡ አገራቸውን ሲነግሩኝም ገባኝ፡፡ በደንብ ስንተዋወቅ የማውቀው ብቸኛ
የኪንያሩዋንዳ ሃረግ ‹‹ምዋሚ ሽሚርዋ›› እንደሆነ ነገርኳቸው፡፡ መዝሙርም ስለሆነ ዘመሩልኝ፡፡ ከኢማኪዩሌ መጽሐፍ ያገኘሁት
ነው፡፡
ኬንያ እስካሁን ካየኋቸው ሁለት የአፍሪካ አገሮች ከፀጥታ አንፃር ሲታይ ሁለተኛ ነው - ከደቡብ አፍሪካ የተሻለ፤ ከጋና ያነሰ። ደቡብ አፍሪካ ከሆቴልና ከስብሰባ ቦታ ለመውጣት በብዙ ችግርና አጀብ ሲሆን እዚህ ግን ከመጠነኛ የጥንቃቄ መልዕክት በላይ ያስፈራራኝ የለም። ገንዘብ ሰው ፊት እንዳላወጣና ለችግረኛ እንዳልመፀውት ይህን ሙከራዬን የታዘቡ አስጠንቅቀውኛል። ሕዝቡ በባለሥልጣናት ሌብነትና በዲሞክራሲ እጦት ያለቃቅሳል። ዜጎቹ
ስለ ባለስልጣናቱ ሀብት ብዙ ነገር እንደሚያውቁ ግን የሚያደርጉትን ነገር እንዳጡ ታዝቤያለሁ። ባለስልጣናቱ
በሌብነት እንደሚፎካከሩ ሰምቻለሁ፡፡ አንዱ ሆቴል የሰራበት ቦታ ሌላው ይሰራል፡፡ በሌብነት ከቀድሞዎቹም መሪዎች ይፎካከራሉ፡፡ መንግሥትን
አስመልክቶ የሚያቀርቧቸውን ከባባድ ወቀሳዎችና ቅሌቶች በማስታወሻዬ የምይዘው በአማርኛ ነው። ያው ለጥንቃቄ ብዬ ነው። አንዳንድ የማያስጨንቁ ነገሮች ያስጨንቁኛል። በእንግሊዝኛ ጽፌ ስሄድ ደብተሬን እንዳያነቡት ብዬ ነው። "1984" የተባለውን ድርሰት ከሳምንታት በፊት ሳነብ የተገለፀው የስለላ ሁኔታ በአገሬ መስሎኝ አስደንግጦኝ ማንበቤን እንዳቆምኩት የሚያሸብረኝ ነገር አይነሳኝም። ሕዝቡ ያለቃቅስ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ እየጨመረ በሚሄድ የችግር ብዛትና በአእምሮ እረፍት ማጣት የተሸበረ አይመስልም። እረስቼው
- የኢትዮጵያውያንን የባህል ሱቅ ጎብኝቻለሁ፡፡ በያዝኩት የኬንያ ሽልንግ አንዳንድ ነገር እንዳልገዛቸው እነሱ የሚሸጡት የኢትዮጵያ
የባህል ዕቃ አዲስ አበባ በተሻለ ዋጋ ስላለ ትርፉ ሸክም ነው ብዬ ተውኩት፡፡ ቢሆንም ፀሐይና ፍሬሕይወት በጉብኝቴ
ተደስተዋል፡፡ ስላገራችን ሰላም ተጨንቀን አውርተናል፡፡
ምንዛሬን ያየን እንደሆነ በየቦታው
ያለ ሲሆን እንደማንኛውም ሸቀጥ ዶላር ይገዛል፤ ይሸጣል። ይህም ነፃነትን የፈጠረ ይመስላል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ስመጣ በየመሃሉ የሚተላለፈው መልዕክት የአማርኛው እንጂ የእንግሊዝኛው እምብዛም አልተያዘልኝም። ይህን የንግግር ዘይቤ የሚክስ ኬንያ አገኘሁ። ይኸውም ኬንያውያን ከሚናገሩት የጠራ እንግሊዝኛ ነው። ኢትዮጵያውያን ከኬንያውያን አንፃር በሰውነት መጠንም አነሱብኝ። እስኪ አንድ ኢትዮጵያዊ ኬንያዊት ቢያገባ ለሠርጉ እንዴት ሊሸከማት ነው! ያለ ሠርግ ካላገባ በቀር። የኛ አመጋገብ
ደግሞ መጠናት አለበት ባይ ነኝ። እዚህ የጠያየኳቸው ከዘር፣ ከአጥንት ስፋት፣ እንዲሁም ሰውነት አፈጣጠር ጋር አያይዘውታል። እስኪ ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር እግርኳስ ስንጫወት የምንሆነውን አስታውሱ። ኢትዮጵያ ሻይቅጠል በዉኃ ተፈልቶ ስኳር ተጨምሮበት እንደሚሸጥ ነግሬያቸው አዝነዋል። ወገኖቼ! ተጠምተናል! ተርበናል! ያለን መስሎናል! ከግማሽ ሊትር የሚበልጥ ወተት ተፈልቶ በጀበና ይመጣላችኋል። በዚያ ላይ ነው የታሸገ የሻይ ቅጠል ወይም የቡና ዱቄት የምትጨምሩት።
ኬንያ ስገባ የነበርኩበት ሁናቴ ያሳዝናል። የሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ማጀር ዮስ
ሄርመንስ ኃይሌ ታሞ መሮጥ ያቃተው ቀን የተከሰተውን የአትሌቱን የሕይወት ታሪኩን ለፃፈው ለጂም ዴኒሰን ሲናገር እስከዛሬ ሲሮጥ ‹/› ምልክትን የሚመስለው ሯጭ ዛሬ የእንግሊዘኛዋን
'C' ፊደል ይመስል ጎብጦ ነበር ያለው ነገር ነው የሆነው። ከአዲስ አበባ እየተንዘፈዘፍኩ የመጣሁበት ምክንያት ያረፍኩበት የእንግዳ ማረፊያ ረፋድ ላይ አልጋ ስይዝ የተነጠፈልኝ አልጋ ከተሰጣው ያልደረቀ አንሶላ ተነስቶ ስለነበረ እሱ ቀዝቅዞኝ ነበር
ብያችኋለሁ። ከሰዓት ብይዝ ኖሮ የደረቀ ይሆንልኝ ነበር። ናይሮቢ ደርሼ ማታ ስተኛ ያለፈው ቀን እንቅልፍ ነበረብኝ። ብርዱ ግን ከብዶኛል፡፡ አስቡት - ከደብረብርሃን ሄጄ! የአልጋ
ልብሱን ለብሼ ተኝቼ እንደነበር ሲነጋጋ ገባኝ። ከታች
ብርድልብስ ኖሯል። እሱን ለብሼ ሰላሳ ደቂቃ ነፍሴ ከተመለሰች በኋላ ወደ ቁርስ ሄድኩ። በዚያውም ወደ ስብሰባ። አየሩ ቀዝቃዛ እንደሚሆን ሲነገረኝ ከደብረብርሃን አይብስም ብዬ የነበረ ቢሆንም ጃኬት ይዣለሁ። ቢሆንም ግን ብርዱን አልቻልኩትም። ወፍራም
ጃኬት ገዛሁ፡፡ በፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ኦቶባዮግራፊ የተጠቀሰው ከእርሳቸው ጋር ሶቭየት ሕብረት ለትምህርት ሄዶ በብርድ የሞተ ልጅ ትዝ አለኝ። የተወሰነ
የጎዳና ላይ ንግድና ልመና፣ ዘመናዊ አደጋ መከላከያ የእግረኛ መሻገሪያዎች፣ ረጃጅም ፎቆች፣ ዩኒቨርስቲ፣ ብዙ ነገር አይቻለሁ። ከኢትዮጵያ የሚመሳሰልም ሆነ የሚለያይ ነገር አለ።
ምቹ መኝታ ላይ ማስተኛትን
ብቻ
ሳይሆን የመንፈስን እረፍትም ታሳቢ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ በእንግዳ ማረፊያው (መኝታ ቤታችሁ) ይቀመጣል። ማዕዱ ባህላዊውን የአፍሪካውንም ሆነ የዓለምአቀፉን የያዘ ነው። የየዕለቱ
ጉባኤ ሲጀምር የኬኒያ፣ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ፣ የአፍሪካ ህብረትና የናይሮቢ ዩኒቨርስቲ መዝሙሮች ተዘምረው ነው። በዛብኝ ካላችሁ መች አበቃና። የሙስሊም ፀሎት ከምዕራብ አፍሪካ በመጡ ባለረጃጅም ቀሚስ ወንዶች ተሰብሳቢዎች ይካሄዳል። የክርስቲያን ደግሞ በኬኒያ ሴት ተሰብሳቢዎች ይከናወናል። ብዙ የተለዩ ገጽታዎች ያሉት ቆይታ ነው።
ማታ በሚካሄደው የእራት ግብዣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ የአፍሪካ ኃይማኖት ወዘተ አባላት የሆኑ ሴት ወንድ ሳይለዩ ሲጨፍሩ ታያላችሁ። ሁሉም በአፍሪካ ልብሶች ያጌጡና በአፍሪካዊነታችሁ የሚወዷችሁና አድራሻችሁን ለመቀበልም ሆነ ለማውራት የሚሯሯጡ ናቸው። ይህችን
አገር ከሽርሽር እስከ ጫጉላ የመጎብኘት ዕቅድ ብትይዙ ያገኘኋቸውን ቡሽብሌዘርስ
የተባሉትን ጨምሮ በርካቶች አስጎብኝ ድርጅቶች ያግችኋል፡፡ የድርጅቱ ሰዎች ያስጎበኘነው አፍሪካዊ አንድ ከሩዋንዳ የመጣ ብቻ
እንጂ አብዛኛው የአሜሪካና የአውሮፓ ነው ሲሉኝ አዝኛለሁ። አፍሪካ አጀንዳ
2063 ሲሳካና ስንበለጽግ ቀጣናዊ
ትስስርም ሲያድግ ኬኒያን
ለመጎብኘት እንችል ይሆናል።
አብራኝ
የከረመችው የአንዲት ካሜሩናዊት መምህርት ወግ ፈገግ ያስብለኛል፡፡
እኔ: ስምሽ 'ቢትሪስ' ለምን ሆነ? አፍሪካዊ ስም የለሽም?
እሷ: ይህን ቤተክርስቲያን አውጥታልኝ ነው እንጂ አፍሪካዊ ስም አለኝ። ቦንግሊ ይባላል።
እኔ: መልካም። ትርጉሙስ?
እሷ: ጥሩ ፀባይ ያላት ማለት ነው ምናምን ብላ አስረዳችኝ።
እኔ፡ በአማርኛ ልንገርሽ?
እሷ: አዎ።
እኔ: ትህትና።
በእስኪርቢቶ ጻፍኩላት። በዋትሳፕም መልዕክትም ላኩላት። አማርኛ ለመጻፍ የሚያስችላትን አፕሊኬሽን ጠየቀችኝ። መማሩ አንድ ሂደት መሆኑን አስረዳኋት። ለካ ቋንቋችንን ማስተማር ይጠበቅብናል።
የኢትዮጵያን
ሴቶች ውበት እንደማንኛውም አፍሪካዊ ታደንቃለች፡፡ የራሷ የማንበቢያ ክፍልና የልጆች የንባብ መወያያ እንደነበራት ነገረችኝ፡፡ ጦርነቱ
ባያቋርጥብኝ እንዳንተ ይሆንልኝ ነበር ብላኛለች፡፡
ልጇ
መምህር ሲሆን የለበሰችውን ማራኪ ጃኬት በትርፍ ጊዜው የሰራላት እሱ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ እኔ ደግሞ ቻይና ሰራሽ መስሎኛል፡፡ የአፍሪካ
የጎጆ ኢንዱስትሪ ቢያድግ ያለውን አቅም አሰብኩት፡፡ በስብሰባው የሚሳተፉትም የምዕራብ አፍሪካ ሰዎች የሚሸጡ ጨርቆችንና ሌሎችን
ይዘው መጥተዋል፡፡ መንግሥታት ያልደፈሩትን አፍሪካ ለአፍሪካ ንግድ መምህራንና የዕውቀት ሰዎች መጀመራቸው ድንቅ ነው!
በካሜሩን የፈረንሳይ ተጽዕኖ እንደሌሎቹ ሁሉ የፈረንሳይ ቅኝግዛቶች አለ፡፡ ፈረንሳይ የአገሪቱን ገንዘብ የማስተዳደርና
ግብር የመሰብሰብ ስልጣን አላት፡፡ በእንግሊዝኛ ተናጋሪ አናሳዎቸችና በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ብዙኃን መካከል ግጭት አለ፡፡ ምናለ ወደ
ናይጄሪያ ቢያካልሉን ኖሮ ብላኛለች የአገሪቱ ዜጋ፡፡ መሪያቸው ዘጠና ዓመትን ያለፉና ከአርባ ዓመት በላይ የገዙ መሆናቸው መነጋገሪያ
ነው፡፡ መሰረተልማት የለም፡፡ በልማት ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡
በወሬ
ወሬ ስለ ኤርትራ ተነሳና ዩኒቨርሲቲ እንደሌላቸው መስማቴን ነገርኳቸው፡፡ በኬኒያ በማህበራዊ ሚዲያ ገቢ የሚያገኙ ላይ ቀረጥ እንደተጣለም
ተነሳ፡፡ ሊስትሮ የሚጠርገው ቆሞ ነው፡፡ አስጠራጊው ትልቅ ወንበር ላይ ይቀመጣል፡፡ ልዩ ነው፡፡
የቻይና ነገር አስጊ ነው። ቀስ እያሉ እኛን
አፍሪካውያንን ይጠቀልሉናል። አገሬውን አግብታ ቋንቋዋን ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ በከፈተው ኮንፊሸስ ኢንስቲትዩት የምታስተምር አንዲት ቻይናዊት አግኝቻለሁ። አህጉሪቱን
አምባገነን መሪ በተበደረው ዕዳ ይዘፍቃሉ። አስፈሪ
ነው ነገሩ፡፡ ዲፓርትመንቱ አዲስ አበባም አለ፡፡
ባህርዳርም አለ ይላሉ፡፡ እኛን የነሱን ቋንቋ በማስተማር ሳያበቁ የኛን በአገራቸው ለዜጎቻቸው ያስተምራሉ፡፡ ነገሩ ጣሊያኖች
አማርኛን ከወረራው በፊት ሮማ ላይ ያስተምሩ እንደነበረው ነው፡፡ አሁን ጮቤ እንረግጣለን፤ ነገ እንረገጣለን፡፡
የኢትዮጵያና የኬኒያ ቡድኖች በቡዳፔስት
በሚወዳደሩበት ሰሞን ነበር ናይሮቢ የነበርኩት፡፡ መጀመሪያ ላይ ድል ለኢትዮጵያ ሲሆን፤ በኋላ ወደ ኬኒያ ዞሯል፡፡ አፍሪካዊ ድል
ብዬ አልፌዋለሁ፡፡
አእምሮዬ
ከጥቁሮች ጋር ስሆን አማርኛ ይችላሉ ብሎ ያምናል መሰለኝ፡፡ ሰላምታና አንዳንድ ነገር በአማርኛ ማቅረቤ የሚታወቀኝ ካልኩት
በኋላ ነው፡፡ ሰላም ነው፣ ችግር የለም፣ አዎ ምናምን እልና ወዲው ትዝ ይለኛል፡፡ አእምሮዬ ምናልባትም ድብቁ ክፍል ጥቁሮቹን
እንደ ኢትዮጵያውያን ሳይቆጥራቸው አልቀረም፡፡
ካርኒቮር ናይሮቢ የአዞና የሰጎን ሥጋ የሚያቀርበው ከየት አምጥቶ ነው ብዬ ጠየቅሁ። የዱር እንስሳትን ሥጋ ማቅረብ ህገወጥ አይሆንም ወይ ብዬ ጠየቅሁ። ተማሪ ሆኜ ህንዳዊው መምህራችን ሚስተር ሻርማ "'የዋልያ ሥጋ በልቻለሁ። በጣም ይጣፍጣል።' ያለኝ ኢትዮጵያዊ አለ። ይህ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው። የገቢ ምንጭ የሚሆነውን ዋልያ መብላት!" ያለው ትዝ አለኝ። ካርኒቮር ኬንያ ግን እንስሶቹን እያረባ እንደሚያርድ ተረዳሁ። የተለየ አሰራር ነው! እኛስ አገር የሚፈልግ ካለ የዱር እንስሳቱን አርብቶ ሥጋቸውን ስለማቅረብ ምን ታስባላችሁ?
ናይሮቢ ሊስትሮ የሚሰራው ቆሞ ሲሆን፤ ጫማ አስጠራጊው ከፍ ያለ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነው። በቀጣዮቹ ፎቶዎች ሲጠርጉ፣ ደንበኛ እየጠበቁ ስልክ ሲያወሩ፣ ሂሳብ ሲቀበሉ ይታያል።
የኢትዮጵያ ሻይ ከኬንያ/አፍሪካ ሻይ አንፃር፡፡ የሆቴሉ አስተናጋጆች በሙሉ አስተናጋጅ ጓደኛቸው የነገራቸውን ባለማመን መጥተው ይጠይቁኛል። ስነግራቸው ከት ብለው ይስቃሉ። "ኢትዮጵያ ውስጥ ሻይቅጠል በዉኃ አፍልታችሁ ነው የምትጠጡት? ወተት አይጨመርም?" ሲሉኝ በአዎንታ አረጋግጥላቸዋለሁ። በሳቅ ይፈርሳሉ። የኢትዮጵያ ሻይ መከለስ አለበት። ንፁህ ዉኃ በሻይ ቅጠል ይብቃን!
ከሌላ እናት የተወለደ ወንድሜ! በናይሮቢ የስጦታ ዕቃ መሸጫ ያገኘሁት ይህ ሻጭ የሰሜን ኬንያ ተወላጅ ኦሮምኛ ይችላል። አነጋገርኩት። መግባባት አላቃተንም። እንግሊዝኛም አላስፈለገንም። አማርኛም ይሞካክራል። ያቤሎን ያውቃል። ጥቁሮቹ በህንዶች የስጦታ ሱቆች ተቀጥረው ይሠራሉ። ህንዶቹ አንድ ጥግ ሆነው ገንዘብ ይቀበላሉ። አንደኛው ሱቅ ህንዱ እጣን እያጨሰ ዕፅ ነገር በአፉ ይዟል። ጫት እንደሆነ ስጠይቀው የህንድ እጽ መሆኑን ነገረኝ። ለኬንያዊው የራሱን ሱቅ ቢከፍት ጥሩ እንደሆነ በኦሮምኛ ነገርኩት። በሄድንበት ሁሉ ጥሩ ሰዎች አሉ።
የአዞና የሰጎን ሥጋ ቅመሱ ቢባልም እንደማይሆን ተናገርኩ። "ኧረ ተው አዞው ጥርሱ ወጥቶለታል።" ይለኛል አስተናጋጁ። ሌሎቹም ሁለት ኢትዮጵያውያን ስቀው አልፈውታል። "ያስተዛዝባል" የሚል የአማርኛ ዘፈን ተከፍቶልናል። በአፍሪካ ሙዚቃ በቡድን ተጨፈረ። የየአገሩ ምሁራን፣ የቤተመጻሕፍት ሰራተኞች፣ የመያድ ሰዎች፣ መምህራን .... አስነኩት።
ጎልፍ
የሚጫወቱ ሃብታሞችን ሳይ ከጎኔ የተሳፈረችው ዶርካስ ኃይለሥላሴ
ጎዳናን እንዳየው ጋበዘችኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ፎቶም
አነሳሁ፡፡ ይህ ጎዳና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስም የተሰየመና በናይሮቢ የሚገኝ ነው። ንክሩማህን ጨምሮ ለሌሎቹም ቀደምት የአፍሪካ አባቶች ልዩ ልዩ ማስታወሻዎች ተሰይመውላቸዋል። ለመሆኑ ለንጉሠነገሥቱ በአገራቸው ምን ተሰይሞላቸዋል? የአፍሪካ ህብረቱ ሐውልት መጀመሪያ የንክሩማህ ከተሠራ በኋላ በስንት ጭቅጭቅ የተሰራ ነበር።
ካረን በተባለው ሃብታሞች የሚገበዩበት
ስፍራ ስሄድ ዕቃ ለመግዛት ከመዟዟር ይልቅ ሃብታሞች ምን ዓይነት መጻሕፍት እንደሚያነቡ ዝርዝሩን በማየት ነበር ጊዜዬን ያሳለፍኩት፡፡
የሃብታሞች ትምህርትና ስልጠና እንደሚለይ ይታወቃል፡፡ በአየር ማረፊያው ባለው የመጻሕፍት መሸጫ ቦታም እንዲሁ አይቻለሁ፡፡ ከመንገድ
ላይ
የመጻሕፍት ነጋዴ በ900 ሺልንግ ሁለት መጻሕፍት ገዝቻለሁ። አንዱ ባለፈው የጠፋብኝን ለመተካት '5 AM Club' ሲሆን፤ ሌላው Eat the Frog Alive ነው። ሁለት የንጉጊን መጻሕፍት ገዛሁ፡፡ አንዱ ዘ ሪቨር ቢትዊን ሲሆን፤ ተማሪ
ሆኘየ አንብቤዋለሁ፡፡ ሌላው የሕይወት ታሪኩ ኢን ዘ ሃውስ ኦፍ ዘ ኢንተርፕሬተር ነው፡፡ ግሩም የቅኝግዛትና የልጅነት ትውስታ
ነው፡፡ የአሊያንስ ተማሪው ንጉጊ ማካሬሬ ለመግባት ከብዙዎች ጋር ታግሏል፡፡
ባህልና አውድ በሁለተኛ ደረጃ
የሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት የሚል ይዘት ያለው ምርምር በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ቀርቧል፡፡ ኢትዮጵያዊ በስብሰባችን ማግኘቴ
አስደስቶኛል፡፡ ከየአገሩ የመጣን እንድንነሳና እንድንተዋወቅ ሲጠየቅ ነው ያየሁት፡፡ በስብሰባው በርካታ ሃሳቦች በየዕለቱ እንግዶችም
ሆነ በአቅራቢዎች ቀርበዋል፡፡ አንዱ የሰማሁት የቋንቋ ገደል ወይም Linguistic cliff ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም በአፍመፍቻችን ተምረን የዉጪ ቋንቋ ሲመጣብን የሚገጥመን ችግር
ነው፡፡ ቅኝገዥዎችና በሚስዮናውያን የፆታና ጤና ትምህርትን ማስቆማቸውና የግርዣ ዘፈኖች መቆማቸው ስለ ጤናና የመራቦ ሂደት መሰረታዊ
ትምህርት በቀረበው ወረቀት ሰምቻለሁ፡፡ በስደተኞች ጣቢያዎችም፡፡ ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ስለሚኖር የክህሎት ሽግግር ከመስማቴ እንግሊዝኛንና
ሌሎችን ትምርቶች በአፍመፍቻ ማስተማር ስላለው ጠቀሜታ ጨመሩበት፡፡ ይህ እኛም አገር የሚደረገው ነው፡፡ በሩዋንዳ የነበሩ ቋንቋዎችና
የቋንቋው ምህዳር ታሪክ ሲቀርብ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኪያርዋንዳና ኪስዋህሊ በአገሪቱ እንደተፈራረቁባትና የቱን ለትምህርት
እንምረጥ የሚለው ፈተና ሆኖ እንደቆየ አቀረቡልን፡፡ የሁለት ቋንቋ ማስተማር ዘዴ ተማሪዎች ውጤት ጠቃሚ መሆኑ በሴኔጋል ተደርሶበታል፡፡
የአፍ መፍቻን መሰረት ያደረገ ወይም ሁለት ቋንቋን የሚጠቀም የማስተማር ዘዴ ተተኩሮበታል፡፡ ዲጂታል የታሪክ መንገሪያ አማራጮችን
ጨምሮ የዲጂታል ክህሎት ጉዳይ የቀረበ ሲሆን መሰረተ ትምህርቱ እሱንም ይጨምራል፡፡ በካሜሩን ከ230 በላይ ቋንቋዎች
ሲኖሩ ማናቸውም በብሔራዊ ደረጃ ለማስተማር የሚሆን ሰፊ ተናጋሪ የላቸውም፡፡ ይህም በአንዱ ለማስተማር አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ ግን ያለንን ብሔራዊ ቋንቋ የማጥፋት ዘመቻ ከጀመረ ቆየ፡፡ የዓለም አቀፉ የመሰረተትምህርት ማህበር ኃላፊ በዙም ንግግር ያደረገችበት ይህ ስብሰባ በእጅጉ ደማቅና በተለያዩ አዳራሾች
የተካሄዱ ትይዩ መርሐግብሮች የነበሩት ነው፡፡ የአፍሪካ
ልጆች ማንበብና መሰረታዊ ሂሳብ አለመቻላቸው በዕድሜ ዘመናቸው በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያሳጣቸው፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣
ደራሲ ወይም ሳይንቲስት ሆነው አህጉራቸውን የመቀየር አቅማቸውም እንደሚሞት በምርምር የተደረሰበት ስለሆነ ያንን ችግር
ለማስተካከል የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ ከኛም ፕሮጀክት የማንበብና መጻፍ ጉዳይ አንቀሳቃሾችን እንደሚጠይቅ ያተኮረ ወረቀት ቀርቦ
ልምዳችንን አጋርተናል፡፡ ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲም ከራዕይና ተልዕኮው
ጀምሮ ሳቢ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ ዩኒቨርስቲ ማለት እንዲህ ነው። ከፖለቲካ ፓርቲ የተቀዳ የሚመስል ራዕይ የለውም። ለማሰብና ለማወቅ ያነሣሣል። ሌብነትንም ይጠየፋል። በዙር የሚደርስ የስብሰባ አስተናባሪነት የደረሳት ኬኒያ የኢትዮጵያን ተወካዮች 14ኛውን
እንድናስተናግድ ጠይቀውናል፡፡ እያሰብንበት ነው፡፡ በዘርፉ ብዙ ይሰራል፡፡ ዩጋንዳ የልጆች መጻሕፍት ደራስያንና ሠዓሊያን ማህበር
አላት፡፡ እኛም የመሰረተትምርት ማህበር አቋቁመን ስብሰባውን ማህበሩ ማካሄድ እንዳለበት የቀረበውን ሃሳብ ብንተገብረው የሚለውን
ጉዳይ ከባህርዳሩ ወዳጄ ጋር ተነጋግረናል፡፡
ከሀብታምነት ወደ ድህነት ወረድን፤ አብረን ተከዝን፡፡ ትናንት ምሽት ከወዳጆቼ በተለይም ከኛ ፕሮጀክት ሰዎች ጋር የመጨረሻዋ ራት ላይ ተገናኘን። የደብረብርሃኑ የቤተመጻሕፍታችን አባል የሆነውና የስምንተኛ ክፍሉ ታዳጊ አዲሱ ዘወትር የሚለው ነገር ትዝ አለኝ። አንኮበር፣ ሳሲት፣ ደብረሲና ወይም እነዋሪ ሄደን ስንመጣ "መሄዱ ደስ ይለኛል። መመለሱ ግን ያስጠላኛል።" ይለናል። ይህንን አስታውሼም ይሁን በሰዓቱ በትክክል የተሰማኝን ለመግለጽ ፈልጌ ለሦስቱ ወዳጆቼ እንዲህ አልኳቸው። "ይህ በዶላር የሚከፈልበት ሆቴል መኝታውም ይሁን መስተንግዶው እኛ በተለምዶው ሕይወታችን ልናስበውና ልንጠቀመው የምንችለው አይደለም። ሁለታችሁም እንደነገራችሁኝ ደሞዛችሁ ከኔ አይበልጥም። የወር ደምወዛችን ለአንድ ቀን ክፍያ አይበቃም። ስለዚህ በዚህ ሳምንት እንደ ሀብታም ኖረናል። ከነገ ጀምሮ ግን ወደ ድህነት ኑሯችን እንመለሳለን።" ብዬ መድረኩን ለአስተያየት ክፍት አደረኩት። የተሳታፊዎችን ድህነት ያየሁት ዕቃ ሲገዙ ዝርዝር አጣሁ እያሉ የተበደሩትን ገንዘብ አልመልስ ያሉኝ ሁለት ሰዎች ከገጠሙኝ በኋላ ነው። አንዱን ሰው ፊት ጠይቄ ስቀበል ሌላዋን ግን ከዕድሜም አንፃር አፍሬ ዝም አልኩ። ገንዘብ ስጠኝ ያለኝም አለ። የሆነው ሆኖ የካሜሮኗ የኮሌጅ መምህርት ቢትሪስ አቀረቀረች። ልታለቅስ ነበር። በአገሪቱ ካሉት ሁለት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ክልሎች የአንዱ ነዋሪ ስለሆነች እንግሊዝኛ ትችላለች። በቆንጆ እንግሊዝኛዋ ያለንበትን የኑሮ ሁኔታ ገለጸች። የደቡብ ሱዳኑ ፊሊፕም ተከዘ። ምናልባት ዶርካስ ደሞዟ ብዙ ሊሆን ስለሚችልና ባሏ ፈረንጅ ስለሆነ ሀሳቡን አትጋራው ይሆናል። የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ባህላዊ ጨዋታዎች ፕሮጀክት ድላላ ለኔ፣ የርቀት ትምህርት ተቋሙ ለፊሊፕ ባይከፍሉልን አንሳተፍም ነበር። ነገሩ ሁለታችን ለኬንያ ስለምንቀርብ የመጓጓዣ ወጪ ቅነሳ ነው እኛን የጋበዙት። አዲስ አበባ ስገባ የተሰማኝ ደስታና የእፎይታ ስሜት ልዩ ነው። አንድ ሰሞንም ቢሆን ከአገር መራቅ ያስተክዛል። ሀብታምነቱን እዚሁ ለመድገም ግን ይከብደኛል። ደብረብርሃን ጌትቫ ሆቴል ከስንት አንዴ ስሄድ አንድ መምህር ጓደኛዬ ያለውን የሜኑ አስተያየት አይቼ ነው የማዘው። ይኸውም ከቀኝ ወደ ግራ ነው - ከዋጋው ወደ ምግቡ።