2024 ፌብሩዋሪ 20, ማክሰኞ

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

 

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

ረቡዕ፣ የካቲት 13፣ 2016 ዓ.ም.

 

ከብዙ ጭንቀት በኋላ በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 4፡15  ስልክ ደወልኩ፡፡ የደወልኩላቸው የአንደኛው ተማሪ አባት ያውቁኝ ዘንድ የልጃቸውን ስም ጠርቼ ‹‹የእከሌ መምህር ነኝ›› አልኳቸው፡፡ አወቁኝ፡፡ ከእርሳቸው ጋር ልዩ ትዝታ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ልጃቸውን ከዘመድ የተላከ 800 ብር ልሰጠው ብዬ ወላጅ አምጣ አልኩት፡፡ እሱም አንድ ወጣት ይዞ መጣ፡፡ እኔም ‹‹ይህ ወላጅ አይሆንም!›› ብዬ መለስኩት፡፡ ከሰዓት በኋላም አባቱን ይዞ መጣ፡፡ ገንዘቡን ያሰብነው ሃያ ልጆች አነስተኛ ስራ እንዲጀምሩ ለእያንዳንዳቸው 800 ብር በመስጠት ነበር፡፡ ልጆቹ ያንን ገንዘብ ይዘው ፎቶ ተነስተው ለላኩልኝ ወዳጄ እልካለሁ፡፡ ይህም ልጅ እንደዚያው ለማድረግ ወላጅ ማምጣት ነበረበት፡፡ ስለሆነም አባቱ መጡ፡፡ ‹‹ትምህርት አልማር አለኝ፡፡ ጠላብኝ፡፡ እኔ እንዲማርልኝ ነው የምፈልገው፡፡ አትስጡብኝ፡፡›› አሉኝ፡፡ እኔም ይህን በመረዳት ‹‹በቃ! ንግዱ ይቅር፡፡ ለእለት ችግርዎ ያውሉት›› ብዬ ተማሪውን ወደ ቤተመጻሕፍት አንብብ ብዬ አስገብቼ ከሌሎቹ ጋር ቀላቀልኩት፡፡ ገንዘቡን ለአባቱ ሰጠሁ፡፡ የተቀበልኩት ምርቃት አንድ ሚሊዮን ብር የሰጠሁ ያህል ነበር! ቀደም ብለን ለ33 ልጆች ካሰፋነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ አንዱ ተጠቃሚ የእርሳቸው ልጅ ስለነበርም ያን እንደውለታ ያስታውሳሉ፡፡ ብቻ ሁኔታው ልብ ይነካል! ልጃቸውም እንደአብዛኞቹ ልጆች በኦሮሚያ ሳለ በአማርኛ ስላልተማረ ከስድስተኛ ወይም ከሰባተኛ ክፍል ወደ አንደኛ ተመለስ ተብሎ ይሆናል ትምህርት የጠላው፡፡ ልጆቹ ካዩት ሰቆቃና ካሳለፉት ግፍ እነዲሁም እየገፉ ካሉት ከባድ ሕይወት አንጻር ትምህርት የሚያስወድድ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም፡፡ ለማንኛውም በምሽቱ የደወልኩት ለእርሳቸው ነው፡፡

በየሚሄዱባቸው ቦታዎች ያሉ ሰዎች በስልካቸው እየደወሉ ብትመጡ እናደርስባችኋለን ያሏቸውን የግፍ አገዳደል ስለነገሩን ስጋት ላይ ነን፡፡ የፖለቲካውም ነገር ስላላስተማመነ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ አካል ይኖራል ብሎ የሚያምን ሰው አልገጠመኝም፡፡ የደወልኩላቸው ተፈናቃይ ባኮ እንደገቡ ነገሩኝ፡፡ ባኮ ሸዋ ውስጥ ነው፡፡ ከአምቦ ይርቃል፡፡ የተጠለሉት በሳምንት ውስጥ ሊበጣጠስ በሚችል ከገበያ የሚገዛው ሸራ ውስጥ ነው፡፡ የተወሰዱት ከነቤተሰባቸው ነው፡፡ ምን እንደሚፈልጉ ስጠይቃቸው ‹‹ማሰብህ ብቻ በቂ ነው!›› አሉኝ፡፡ ‹‹እንመለሳለን ብለን በምንም ነገር አላሰብንም፡፡ ባለፈው ሳምንት በድንገት እዚያው ደብረብርሃን ውስጥ ወዳዘጋጁት ቦታ አስገቡን፡፡ አትወጡም ተባልን፡፡ ተከለከለ፡፡ እዚያም ውለን አድረን ከደብረብርሃን ጫጫ ድረስ የአማራ ክልሎቹ አመጡን፡፡ ከጫጫ የኦሮሚያው ‹መከላከያ› ተረከበን፡፡ አምቦ ዙሪያ ነው የምትሰፍሩት ብለው በመከላከያ አምቡላንስ ተቀበሉን፡፡ ጥሩ አቀባበል አደረጉልን፡፡ 15 ኪሎ ሩዝ ሰጥተውናል፡፡ አንተስ ደህና ነህ ወይ? ቤተሰብህስ?›› አሉኝ፡፡

እኔ ደህና መሆኔን ነገርኳቸው፡፡ ቤተሰቦቼ ያሉበት ሳሲት አቅራቢያ በድሮን የተመቱ ሰዎች መኖራቸውን ገልጬ የኔ ቤተሰቦች ግን ለጊዜው ደህና መሆናቸውን ነገርኳቸው፡፡

ልጃቸው እንደተኛና ጠዋት እንደሚያገናኙን ነገሩኝ፡፡

ግርታ ገባኝ፡፡  ለአሁኑም ቢሆን ፈጽሞ ሰላም ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. እና የስራ ባልደረቦቼ ከደብረብርሃን ወደ አምቦ ስንሄድ የመጠቃት ወይም የሆነ አደጋ የማጋጠም ስጋት ጠብቀን ነበር፡፡ ስንደርስ ግን በቀለ ባየታ ቶለሳ የተባሉ አንድ ድንቅ የአምቦ አዛውንት መንገድ ላይ በስተቀኝ ስንሄድ አይተው እንግዶች መሆናችንን አውቀው ተቀብለው ምግብ ቤት አሳይተው ስለ ኢትዮጵያዊነት እያወጉልን ራት በልተን እስክንጨርስ ጠብቀው ወደ ማደሪያችን የሸኙንና በአምቦ በሰላም ከርመን የተመሰለስነው ትዝ አለኝ፡፡

ብሔራዊ ፈተናም በዩኒቨርሲቲ መሰጠት በጀመረ ዓመት ወደ ነቀምትና ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች ለመፈተን የሄዱ መምህራን ሲመለሱ ቃለመጠይቅ አድርጌ ስለቆይታቸው ጽፌ ነበር፡፡ የጽሑፉ ርዕስ ‹‹ከወለጋ መርዷቸው ሲጠበቅ ተሸልመው የመጡት አማሮች›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹ይህን ጽሑፍ ስታነቡ በአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመረዳት እንደማታለቅሱ ዋስትና አልሰጣችሁም!›› የሚል ማሳሰቢያም ነበረው፡፡

 

የዛሬው የስልክ ጥሪ እነዚህን ከአሁን በፊት የታዘብኳቸውን ምልከታዎች አስታወሰኝ፡፡ ከአሁን በፊት የታዘብኳቸው ጉዳዮች እንደሚያሳዩት መንግስት ከፈለገ ሰዎች በሰላም መኖር እንደሚችሉ ነው፡፡ አንድ አማራ መምህር ደምቢዶሎ ሄዶ ፈትኖ መምጣት ከቻለ ከደምቢዶሎ ወዲህ ባለ ቦታ ሌላ አማራ ለምን ይሞታል! ስደት፣ የግፍ ግድያ፣ አካል ጉዳትና ሌሎችም አሰቃቂ ድርጊቶች ለምን ይፈጸማሉ? መንግስት እነዚህ ከደብረብርሃን የተመለሱ አማራ ተፈናቃዮች በሰላም እንዲኖሩ ከፈለገ እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ በአምቦና በባኮም የተደረገላቸው አቀባበል ይህንኑ ያሳያል፡፡

 

በደብረ ብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ከሁለት መቶ ያላነሱ የኦሮሚያ ተፈናቃይ አማራ ልጆችን በሳምንት መጨረሻ ቀናት ስናስነብብ፣ ስናስተምር፣ ስንመግብና ስናበረታታ ቆይተናል፡፡ ይህን ልናደርግ የቻልነው ጊዜ ተርፎን አይደለም፤ ገንዘብም የለንም፤ አቅማችንም ውሱን ነበር - ነውም፡፡ የደብረብርሃን ህዝብ በሚያደርገው ድጋፍ፣ በቤተመጻሕፍት መረባችን ምክንያት የተዋወቅናቸው ወገኖቻችን በሚያደርጉልን እገዛ፣ የቤተመጻሕፍቱ አባላት የሆኑ ወጣቶች በድህነት፣ በኑሮ ውድነትና ተስፋ መቁረጥ እየተገረፉ በሚያደርጉት ልገሳና በጎፈቃደኝነት ነው፡፡ እነሱ ሳይመቻቸው ቅዳሜና እሁድን ከቤተክርሰቲያን ቀርተው፣ ስራቸውን አስታጉለው፣ እረፍታቸውን ትተው ለእነዚህ ልጆች አስበው ሲያስተምሩ፣ ሲመግቡና ሲያበረታቷቸው ቆይተዋል፡፡ አንድ ቀን አርባ ተፈናቃይ ልጆች ቢመጡ በቀጣዩ ዘጠና ይመጣሉ፡፡ ስድሳና ሰባ አማካይ የልጆች ዕለታዊ ቁጥር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በአጠቃላይ ከወይንሸት ካምፕ ቤተመጻሕፍቱን ብዙ ልጆች አይተውታል፡፡ ከትልልቆቹ የቻይና ካምፕና ባቄሎ ካምፕ ተብለው ከሚጠሩት የሚመጡት ዉሱን ናቸው፡፡ ዋነኛው ምክንያት የቦታው እርቀት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ዙር ተመላሽ ተብለው ሊሄዱ የተዘጋጁት ወደ ልዩ ጊዜያዊ ማቆያ ከገቡ በኋላ ዉጪ ባሉት ዘንድ የነበረውን መሸበር የምገልጽበት ቃል የለኝም፡፡ አሁንም ልገልጸው አልችልም፡፡ ለማናቸውም ሄዱ፡፡ ከሄዱ በኋላ ስለሚገጥማቸው ሁኔታ ያለን ስጋት ጽኑ ነው፡፡

 

እነዚህ ተፈናቃዮች በእጅጉ የሚያሳዝን ሕይወት ያሳለፉና እያሳለፉ ያሉ ናቸው፡፡ ደብረብርሃን እንዳይቆዩ እርዳታ ቆሟል ብለውኛል፡፡ እርዳታ ብቻም ሳይሆን ቤት ተከራይቶ ለመኖር አይችሉም፡፡ ሁሉ ነገር ታጥሯል፡፡ እስረኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ለአካል ጉዳተኛ ልጄ የተሰጠኝን ዊልቼር የሚገዛ ፈልግልኝ ብለው ልጃቸውን የላኩብኝ እናት አሉ፡፡ የሚገዛ ሰው ግን አላውቅም፡፡ ሌላዋ እናት እሁድ 10/06/16 ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው ለአንዷ ስለተሰፋው የደንብ ልብስ አመስግነው ወደ ወለጋ ሊሄዱ የመሆናቸውን ወሬ አስረድተውኛል፡፡ በብዛት አዋቂዎችን አላገኘሁም፡፡ የተሸበሩት ልጆች ግን ሁሉንም ጉዳይ ነግረውኛል፡፡ እኝህ እናት ስላሉት አማራጮች ስጠይቃቸው ደብረብርሃን መቅረት እንደ ወንጀል መታየቱን አልሸሸጉኝም፡፡ ወደ ወሎም ለመሄድ እዚያ ያሉትን ዘመዶቻቸውን አያውቋቸውም፡፡ አክስትም አጎትም ቢባሉ በደህናው ቀን ስላልጠየቋቸው የመሄድ ድፍረት የላቸውም፡፡ ልሂድ ቢሉስ መሳፈሪያ ይኖራቸው ይሆን? ልጆቹ ዛሬ ቤተመጻሕፍት ሊያነቡ መጥተው ነገ ስለመመለሳቸው እርግጠኞች አይደሉም፡፡  

 

የደወልኩላቸውን ተፈናቃይ ‹‹የወለጋዎቹስ እንዴት ሆኑ?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ መረጃ የላቸውም፡፡ ደብረብርሃን ላሉት ደውዬ በደህና እንደገቡ ነግረውኛል፡፡ ወደፊትም እከታተላለሁ፡፡ መኪኖቹ ከአምቦና ወለጋ ወደ ደብረብርሃን ሲመለሱ ሌሎቹን በየተራ እንደሚወስዱ ትናንት ምሽት ያገኘሁት ልጅ ነግሮኛል፡፡ የሚመልሳቸው አንድ የትራንስፓርት ድርጅት ኮንትራት ይዞ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ በአሁኑ አካሄድ ቅድሚያ የተሰጣቸው እዚያ ተመን ኖሯቸው ግብር የሚገብሩትን ነው ተብሏል፡፡ የስም ዝርዝራቸውም ከዚያው ከኦሮሚያ ይኖሩበት ከነበረው ስፍራ መጥቶ ነው፡፡ ግብር የማይገብርና የሰው መሬት ተከራይቶ የሚያርሰውን ለጊዜው አልወሰዱም፡፡ በሂደት ይወስዱ ይሆናል፡፡ የደብረብርሃን ሰዎች ስጋት ግን እነዚህን መሬት ያላቸውን ሰዎች ለምን ወሰዷቸው የሚል ሲሆን፤ ምናልባት ወደፊት ሰላም ሲሰፍን መሬታችንን መልሱ ብለው በህግ እንዳይጠይቁ ይሆን ወይ የሚል ነው፡፡

የእነዚህ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ሰላም ባልሰፈነበትና እርግጠኝነት በሌለበት ሁኔታ ባይሄዱ እጅግ ተመራጭ ነው! 

ልጆቹን በመጨረሻ ቀናችን ያልኳቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ሁላችሁም ስልኬን፣ ስሜንና የቤተመጻሕፍቴን ስም ያዙ፡፡ አዲስ ነገር ሲኖር ደውሉልኝ፡፡ አገር ሰላም ከሆነ ወለጋ ያላችሁበት ጋ መጥቼ ቤተመጻሕፍት እንከፍት ይሆናል!››

ብቻ ሰላም እንደናፈቀን እንዳንቀር!

 

 

2024 ጃንዋሪ 23, ማክሰኞ

የ ቋ ን ቋ ወግ

 የቋንቋ 


ለመሆኑ ኦሮምኛ? አማርኛ? ትግርኛ? እንግሊዝኛ? የትኛውን ተማራችሁ? 


ሁለት የደብረብርሃን ልጆችን አውቃለሁ። ስለ ቋንቋ ጉዳይ ያወጉኛል። ስለ እንግሊዝኛ ተነጋግረናል። ከእንግሊዝኛ አንፃር የተሻለ ችሎታ አላቸው። ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። የከተማ ልጆች ስለሆኑ፣ የተማረ ወላጅ ስላሳደጋቸው ወይም በሌላ ምክንያት። 

ኦሮምኛን አስመልክቶም አንዳንድ ነገሮችን አንስተውልኝ እንደነበር አስታወስኩ። ለማወቅ ይፈልጋሉ። ምክንያታቸውን ስጠይቅ "የኦሮምኛ ሙዚቃ ለመስማት፣ ወደ ሌላ ቦታ ስንሄድ እንድንጠቀምበት" አሉኝ። 

አፋን ኦሮሞ የሚማሩ ሰዎች "ኦሮምኛ ለምን ትማራላችሁ?" ተብለው ቢጠየቁ ኦሮሞ ስናገባ አማቶቻችን ጋር ስንሄድ እንድናወጋበት ሊሉም ይችላሉ። ዘውግ-ዘለል ፍቅር ባልተጠናከረበት በዚህ ጊዜ።

የኦሮምኛ ቃላት ለመያዝ ሐሳቡ የመጣልኝ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የክፍሌ ልጅ ከሆነው ምናልባትም ከብቸኛው የቋንቋው ተናጋሪ ከተክሌ ወልዱ ጋር 

ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስንሄድ ተክሌ ያቺን ልጅ "ኢንተሎ ነኤጊ" በላት አለኝ። ምን ማለት እንደሆነ ስጠይቀው "አንቺ ልጅ፣ ጠብቂኝ" ማለት መሆኑን ነገረኝ። ጠብቂኝም አላልኩ፤ አረፍተነገሩን ብቻ ተማርኩ።

ፈተና ተፈትነን ውጤት ስንጠብቅ የሳሲቱ ጎበዝ ተማሪ አንዳርጌ ገብረማርያም ዩኒቨርስቲ ስንገባ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ተማሪዎችን እንደምናገኝ ጠቅሶ ቋንቋዎቹን መማር እንዳለብን አነሣ። ተስማማን። ከነዚህ ቋንቋዎች በጓደኞች መኖርና በአጋጣሚዎች የአፋን ኦሮሞው ተሳካና ጀመርኩ። ያው ያዝ ለቀቅ ነው። 

ከወለጌው ነብዩ ዓለማየሁ ጋር የምንግባባው በእንግሊዝኛ ነበር። እሱ አማርኛ አያውቅም፤ እኔም ኦሮምኛ አልችልም። አንድ ቀን ከጓደኛው ጋር ሲገናኙ ሲያስተዋውቀኝ ጓደኛውን "ኮቱ" አልኩት። ሰላምታ መስሎኝ። 

ሌላ ቀን ተውላጠ ስሞችን ማለትም አኒ፣ ኑ፣ አቲ፣ ኢሲን፣ ኢሺ፣ ኢኒ፣ ኢሳን ተማርኩ። መጠይቅ ተውላጠ-ስሞችን ኤኙ፣ ማሊ፣ ኤሳ፣ ኢሳ ከሚ፣ ዮም፣ ማሊፍ፣ አከም ለበለብኩ። 

የሳምንቱ ቀናት በደፍኖ ወይስ በዊጠታ የሚጀምረው ይሻልሃል ተብዬ ሰባት ከሰባት ደፈንኩ። 

የዓመቱ ወራትን ፉልባና፣ ኦንኮሎልሳ ...

ከኦሮምኛ ወቅቶች የተረሳኝ ቢራ/ፀደይ ነበር። ራ ይጠብቃል። 

ቁጥሮች ወይም ለኮፍሶታ መጀመሪያ ቢለክፉኝም አሁን ተግባብተናል። 

ቃላትን ልክ እንደአማርኛው ገጣሚ ሰለሞን ዴሬሣም ባይሆን የቱን ከማን እንደተማርኩ አስታውሳለሁ። 

ከታሪኩ አነጋ አዳነ - ኢዶ፣ ዳኢመ፣ ነዲዴ፣ አኮ፣ ሊቄፈቹ፣ 

ከሌሊሴ ከበደ - ኡታልቻ መልካ በለኣ ቦረፈቱ ደንዳ፤

ኛታ ወጪቲ ዲጶ ፈላነቱ ደንዳ፤

ነሚቻ ኢየምሲሴ፤

ከአማን ቃዲሮ አቢቹ - ሸመረን፣ ዊርቱ፣ ኩፉ፣ አሬዳ

ከዘውዲቱ - ደፊሱ፣ ፉናና

ከአብዮት ዲባባ - ከጠፋም ይጥፋ እንጂ የድመትን ዓይን አያጥቡላትም የሚለውን የኦሮምኛ ምሳሌ

ከለማ ሚደቅሳ- ጉቡ (በእርግጥ በጣት የሚቆጠሩ ቃላት ይመስለኛል የሚያውቀው።) አንድ ቀን ቡናው ፈጀኝ ለማለት። "ነ ዱኩቤ" ስል "ነ ጉቤ ጀዲ" ብሎኛል።

በዚህች አነስተኛ ጽሑፍ አትኩሮቴን የሳበችውን ነጥብ ላንሣ ብዬ እንጂ ምንም ቢጻፍ መሬት ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም።

በአዲስ አበባም ቋንቋው ይሰጣል ይላሉ። እውነት ነወይ? እስኪ አስቡት ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ኦሮምኛ ለማስተማር ክፍል ገብቶ "ኢጆሌ ፊንፊኔ አከም ጅርቱ" የሚለው በርሲሳ የሚሰማውን ስሜት። በርሲሳ በሉኝ ብሎ ራሱን ያስተዋውቃል። "ቀብሶ ኬኛ ጡመረሜራ" የሚል ይመስለኛል። በቋንቋዎች ዲፓርትመንት ከአማርኛ መምህር ጋር ይነጋገራሉ ወይስ ይኮራረፋሉ የሚለውን መመለስ አልችልም። እንደ ሰዎቹና አውዱ ይወሰናል። ከተማሪዎችም ጋር ሰልፍ ላይ በባንዲራና መዝሙር ጦርነት ነበር ይባላል።

ወጣም ወረደ ቋንቋዎቻችን ሀብቶቻችን ስለሆኑ እንንከባከባቸው። የልዩነትና የጦርነት መነሻ ባይሆኑ መልካም ነው። የማንነት ፖለቲካ መጨረሻው የሚያምር አይመስለኝም።

የጀመርኩት በሁለቱ ልጆች ጉዳይ ነበር። ባልገመትኩት ሁኔታ ቋንቋውን እየለመዱ ነው። ጠቃሚ ሐረጋትንና ቃላትን ለምደዋል። በአማራ ክልልና በኦሮሚያ የተማሩ ሲሆን ከክፍልና ዶርም ጓደኞቻቸው እገዛ ተደርጎላቸው ከዚህ ደርሰዋል። የቋንቋ ፖሊሲ ከወጣና የአሁኑ ወይም ያለፈው ሁኔታ ከተቀየረ ምናልባት በአማራ ክልል ያሉ ተማሪዎች ኦሮምኛ ሊማሩ ይችላሉ። ያኔ የብሔር ፖለቲካ የሚያበቃለት ይመስለኛል። ምክንያቱም ማን ምን እንደሚያወራ መረዳት ይቻላል። ቋንቋውን ተጠቅሞ ኬላ ላይ አላሳልፍም የሚለው ፖሊስ ስራውን በትክክል ይሠራል። (ኬላ ላይ ስለማላሳልፍህ ቋንቋዬን ተማር ዓይነት ሒሳብ ያስቀኛል።) ቋንቋ ከቻለ ወደ ስም ማጣራት ይገባል። በኃይማኖት ወይም በሌላ መንገድ ይከፋፍላል። በአንፃሩ ኦሮምኛ መማር ማለት ከአክራሪ ፖለቲከኞች "እናንተ ሌላ ማንነት የላችሁም። ይኸው ኦሮምኛ ትችላላችሁ። ኦሮሞዎች ናችሁ።" የሚል ጫና ሊያመጣ ይችላል። ማንነታችን ይዋጣል የሚሉ ይኖራሉ። ሌሎች እንደዚህ ሊጠያየቁና ሊመላለሱ ይችላሉ፦ 

- በላቲን ለምን ትጽፋላችሁ? 

* በምንስ ብንጽፍ!

- ኢትዮጵያዊነት ይሸረሸራል።

* ጥርግ ይበል። ፖለቲካው የብዙ ዘመን የትግል ታሪክ ስኬት አይደለም ወይ? ድላችንን እናጣጥምበት።

- የዉጪ ኃይሎች አገራችንን ለማፍረስ ያቋቋሟቸው ፓርቲዎች ህዝቡን ከፋፈሉት።

* እንዲያውም የህዝቡ ትግል ውጤት ነው። ከውስጥ ነው የፈነዳው። በታሪክ ሁነኛ ምዕራፍ ላይ አይደለንም ወይ?

- የምን ምዕራፍ?

* ኦሮምኛ የአማርኛን ቦታ ይተካል። እኛ አማርኛን ተቸግረን እንደተማርነው አንተም ትማራለህ።

- መተባበር ይሻላል ወይስ መፎካከር? 

* የኛ ዕድል ሲደርስ ስለ ትብብር ታወራለህ።

ሁለቱም ግን ተናገርልኝ ብሎ የወከላቸው ህዝብ የለም። 

ትውልዱ የራሱን መንገድ ይዞ ይቀጥላል። 

ሰላማዊ አገርና ወደፊትን እመኛለሁ።


2023 ዲሴምበር 22, ዓርብ

ስለ ኢየሱስ እንደኔ የተሰቃየ የለም!

 ስለ ኢየሱስ እንደኔ የተሰቃየ የለም!

እውነተኛ ታሪክ

ምግብ ላዘጋጅ ስራ ስጀምር ትመጣለች። በርጩማዋን ይዛ ትቀመጥና ነገር ትጀምረኛለች። "ኢየሱስ ያድናል!" ትለኛለች። ዝም እላለሁ። ከምግብ ዝግጅት በፊት ሳነብ የነበርኩትን ለማሰላሰል ዕድሉን ትነሳኛለች። የማበስለው በቡታ ጋዝ ስለሆነ ወደ ቡታ ጋዙ አያለሁ። ለመኮረኒ መቀቀያ ወደማፈላው ዉኃም አያለሁ። ከሰዓት ስለማቀርበው አሳይመንት እንዳላስብ ትከለክለኛለች። ሽንኩርት መክተፍ ስጀምርም አትተወኝም። "ሃሌ ሉያ" ትለኛለች። ጆሮዬ ስር መጥታ ትጮህብኛለች። ስመገብም አታቆምም። በልጅነቴ ስናደድ ክፉ ልጅ እንደነበርኩ ትዝ ይለኛል። ድንገት ይሰውረኛል። እነሱ ዲፓርትመንት መምህራን ውጤት የሚሰጡት በብሔር ነው ይባላል። አያጠኑም። እኔን ግን አጥንቼ መመረቅ ከለከለችኝ። ስለሷ ጩኸት ሳስብ ውዬ አድራለሁ። "ኢየሱስ አዳነ አላዳነ እኔ ምን ቤት ነኝ!" ብዬ ስመልስላት አትሻሻልም። ይብስባታል። መናኸሪያ ያሉ ሰዎች የሚሳደቧቸውን ዓይነት ፀያፍ ስድቦች መሳደብ ጀመርኩ። በጨዋ ደንብ ያደግሁትን የገጠር ልጅ ባለጌ አደረገችኝ። ሊመልሳት አልቻለም። 

አንዳንዴ ቤተመጻሕፍት አድራለሁ። ለሰዎች ስለአድራጎቷ ስናገር እሷ እንደማትጮህና ድምጿ እንደማይሰማ ይነግሩኛል። በምን ምክንያት አብረን ለመኖር እንደወሰንን በአግራሞት ይጠይቁኛል። ኖኪያ ስልኬ ድምፅ ስለማይቀርጽ አንድ ቀን ስትጮህብኝ ለጓደኞቻችን ደውዬ አሰማኋቸው። ተገረሙ። ቆማ "ውስጥሽ ሰይጣን አለ" ትለኛለች። "ኢየሱስ ጌታ ነው!" ትለኛለች። አንድ ዓመት ተኩል ታገስኳት። በየቀኑ 12:00 ከኦሮምኛ ዜና ጀምራ በየቋንቋው የሚደጋገመውን ፕሮግራም ስታይ ታመሽና ምሽት 4:30 ኢቲቪ የሱማሌኛ ዜና ሲጀምር ትተኛለች። ሰራተኛ ስለቀጠረች ምግብ እንኳን አትሰራም። በደሞዝ ትበልጠኛለች። ቀድማኝ ስትተኛ ክፉ ነገር ታሳስበኛለች። ተስፋ ስትቆርጥና ሳኮርፋት እኔ ክፍል ጠረጴዛ ላይ ቤቱን ለቅቄ እንድወጣ የሚያዝ መልዕክት ተወችልኝ። "እህቴ" በሚል የሚጀምረውን መልዕክት ሳይ ቃሉን የተጠቀመችው ጠላቴ ጠላቴ ለማለት ነው ብዬ ተረዳሁት። ቀጥሎ ምን ወሰንኩ? መቼም ያለፈ ታሪክ ስለሆነ ችግር የለውም። እስኪ ገምቱ። 

"ኢየሱስ ጌታ ነው"፣ "ኢየሱስ ያድናል" ወዘተ የሚል ጥቅስ ስሰማ ያን ክፉ ጊዜ በንዴት አስታውሳለሁ። 

2023 ዲሴምበር 13, ረቡዕ

ከግራኝና ፋሽስት ወረራ በኋላ የተከሰተ የዘመናችን የስደት ታሪክ

ከግራኝና ፋሽስት ወረራ በኋላ የተከሰተ የዘመናችን የስደት ታሪክ

መዘምር ግርማ

ታህሳስ 4፣ 2016

ደብረብርሃን


 

በአማራ ክልል ደቡባዊ ጫፍ የምትገኘው ደብረብርሃን ከተማ ከኦሮምያና ከአዲስ አበባ የሚፈናቀሉ አማሮችን ስታስተናግድ የተወሰኑ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያ ካምፖች የችግር ሕይወት የሚመሩት ስደተኞች ከወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከአምቦ ወዘተ የመጡ ናቸው፡፡ ሙሉ የቤተሰብ አባላት ባዶ እጃቸውን ምናልባትም ሌሊት ከእንቅልፋቸው መሐል የአሳዳጆቻቸውን መምጣት አይተው ሸሽተው መጥተዋል፡፡ የቤተሰብ አባላት የሞቱባቸው ያለ ወላጅ የቀሩ ሕጻናትና ልጆች በካምፖች ያለ በቂ አገልግሎትና እንክብካቤ ይኖራሉ፡፡ 


 

አገራችን በአሁኑ ወቅት ባለችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ምክንያት ዜጎችን በማንነት ማጥቃት ተዘውትሯል፡፡ ሕገመንግስቱ አንዱን ክልል ለአንድ ዘውግ ሰጥቶ ሌላውን በጥገኝነት ስለፈረጀው ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ ማለቂያ በሌለው መከራ ይሰቃያል፡፡ ለከፋ ሰቆቃ፣ ሞትና ስደት የተዳረጉት ዜጎች በአሁኑ ወቅት ባለው ህገወጥ አሰራር ምክንያት ከጥቃት አንድንበታለን ብለው ወደሚያስቡት ቦታ ይሰደዳሉ፡፡ በመጠለያ ካምፖች ከሚኖሩትና በከፍተኛ ቁጥሮች ከየቦታው ከፈለሱት በላይ በደብረብርሃን ቤት ተከራይተው ለመኖር የሚመጡም አሉ፡፡ በትናንትናው ዕለት ከአንድ የኦሮምያ ከተማ ተፈናቅለው የመጡ አንድ እናት አግኝተን ነበር፡፡ ዕቃቸውን ከጫኑበት አይሱዙ መኪና አውርደን ወደ ቤት በማስገባት ያገዝናቸው መምህርት እስከ ጡረታ ዕድሜያቸው ድረስ በዚያው ከተማ የኖሩ ናቸው፡፡ በከተማቸው አቅራቢያ በሚገኙ ቦታዎችና በከተማቸው የሚታገተው ሰው እየበዛ ሲመጣ ሰዎች ተደናገጡ፡፡ እኝህም አረጋዊት የተማሩ ስለሆኑ የውሳኔ ሰው ናቸው፡፡ ከመሰደዳቸው በፊት የተከሰትት ነገሮች ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላሉ፡፡ በፊት ለመምህራን የስብሰባዎችን መልዕክት ይተረጉም የነበረው የትምህርት አስተዳደር መተርጎሙን አቆመ፡፡ የቁጠባ ማህበራቸው ለሚጠራቸው ወርሃዊ ስብሰባዎች ሲሄዱ ስብሰባው ሙሉ በሙሉ በኦሮምኛ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መድሎና ማግለሉ ህዝባዊ ሳይሆን መንግስታዊ ነው ይላሉ፡፡  ቀስ በቀስም ነዋሪዎች እየተሰደዱ ከተማቸውን ለግማሹ ነዋሪ ተዉለት፡፡ ‹‹የኦሮሚያ መንግስት በኢሳት ኃላፊነት አልወስድም፤ በየሰፈራችሁ ተደራጅታችሁ ጠብቁ ሲል ሰምቼ ለመውጣት ወሰንኩ›› ይላሉ እኚህ እናት፡፡ ይህም መልዕክት የግብር ይውጣ ይመስላል፡፡ ከተማዋ በሸኔ ተከባለች፡፡ ወደከተማዋም ገባ ወጣ አብዝተዋል፡፡ አርባ ዓመት በመምህርነት ኖረው ጡረታ ከወጡበት ከተማ ሲወጡ የቀበሌው ሊቀመንበር በዕቃቸው ምክንያት መንገድ ላይ ኬላ ጠባቂዎች እንዳያንገላቷቸው የተፈተሸና ባዕድ ነገር የሌለበት መሆኑን ገልፆ በኦሮምኛ ጽፎላቸዋል፡፡ ከዚህም በፊት መደረግ ያለባቸውን ነገሮች አድርገዋል፡፡ እድራቸው ተበትኖ አባላት ገንዘባቸውን ተከፋፍለዋል፡፡ በኦሮሚያ ደረጃ ያለውን በሰፊው ስናይ በአርሲ አስተዳደሩ የአማሮችን ጠመንጃ ገፎ ለእርድ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ እንደ ደሴት መሃል ላይ ቀርተዋል፡፡ ከወለጋ እስከ አዲስ አበባ ጫፍ ሸኔ መረቡን ዘርግቷል፡፡ ቅልቅል የሆነው ሸዋም ውስጥ ውስጡን ተቦርቡሯል፡፡ ጅማም የጥቃት ታሪክ ያለውና የሚያሰጋ ነው፡፡ ጥቃቱ በየአካባቢው አይሏል፡፡ ሁለንተናዊ መፍትሔም ያሻዋል፡፡

ምስል - ጓደኛዬን ያስተከዘው ከአንድ አሮጌ ቁምሳጥን ውስጥ ያሳየሁት በ1996 ዓ.ም. ጽፎ የለጠፈው የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ፡፡ ሌላ ጥሩ ወይስ መጥፎ ዘመን እየመጣ ይሆን?


ሰዎች ከከተማው ሳይቀር እየታገቱ ገንዘብ ሲጠየቅባቸው ነዋሪዎች ተደናግጠው መወሰን እንደነበረባቸው ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ሂዱ ማለትንም ሆነ እንዲሄዱ ማድረግን አጣምሮ የያዘው የማይነገር ፖሊሲ ሌሎችን ኦሮሚያ ተብሎ ከተከለለው የዘር ክልል የማጽዳት ስራ እዚህ አማራ ክልል ያለነውን ብዙ ጉድ እንድናይ አድርጎናል፡፡ ሰዎች ጣራቸውን አፍርሰው፣ በርና መስኮት ገንጥለው፣ ሙቀጫና ዘነዘና ጭነው አማራ ክልል ይገባሉ፡፡ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር የሚገቡ ቢሆንም ነገ ነገሮች ቢቆየሩ ለመመለስ በሚል ወይም ባለው ቅርበት ምክንያት ይመስላል ሰሜንሸዋን ይመርጣሉ፡፡ በሰሜንሸዋ ወረዳዎች በበርካታ ቁጥር የተበታተኑ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ለማወቅ የቻልኩት በቅርቡ ከ1000 ኩንታል በላይ ለተፈናቃዮች የመጣ ዱቄት በአንድ ወረዳ መጋዘን ተከዝኖ መገኘቱን ስሰማ ነበር፡፡ ይህን ያህል እህል በየሁለት ወሩ የሚመጣ ከሆነ የተፈናቃዩን ቁጥር አባዝታችሁ ድረሱበት፡፡    

ስብሃት ነጋ አማሮችን መንዝ ላይ በትነን እንሄዳለን ያለው ፖሊሲ እየተፈጸመ ሲሆን፤ እኛም መንዝ ላይ ሆነን የአትዮጵያን ስብርባሪ በመልቀም ላይ ሳንሆን አንቀርም እላለሁ፡፡ የእኝህን እናት ዕቃ ስናወርድና በልጃቸው ቤት ስንደረድር ቆይተን ማታ ቡና ተፈልቶ፣ ጠላ ተከፍቶ፣ አረቄ ተቀድቶ አውግተናል፡፡ ደብረብርሃን ልጅ የሌለውን ምስኪን ተፈናቃይ ሰቆቃ አስቡት፡፡ ቤት የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ሲሆን፤ ቢያገኝ የማይመች ኪራዩም ከባድ ይሆናል፡፡ ራሳቸውን ችለው ሻሸመኔ፣ አርሲ ወዘተ የሚባሉ ሰፈሮች ደብረብርሃን ውስጥ እየተመሰረቱ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ገብተን ጨዋታ ከመጀመራችን በፊት እኔ ለጓደኛዬ ከአንዳርጋቸው ፅጌ መጽሐፍ ‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› ያነበብኩትን አወጋሁለት፡፡ የአንዳርጋቸው ፅጌ አባት ከሐረርጌ ወደ አዲስ አበባ በልጅነታቸው ያደረጉት ስደት የጣሊያን ወራሪ በወልወል በኩል በመምጣቱ ነበር፡፡ ኦሮሞዎችንና ሶማሌዎችን በሐረርጌ የነበረውን አማራ እንዲያባርሩ ኢጣሊያ በሰበካቸው መሰረት ያባረሩት እያጠቁ ነበር፡፡ አገረገዢው ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኔልም ሁሉም ወደ ሸዋ እንዲከት ባዘዙት መሰረት ህዝቡ ከብቱን እየነዳ፣ ልጆቹን ይዞ፣ ቅሌን ጨርቄን ሳይል ያደረገው ስደት የሰው ውቅያኖስ ነበር፡፡ ፅጌ ከአንድ ተራራ ላይ ሰዉን ቁልቁል ሲያዩት ጥቁር ፀጉሩ በፀሐዩ ሲያንፀባርቅ ባህር እንደሚመስል ገልፀውታል፡፡ አገር ተነቅሎ የሚመጣ ይመስል ነበር፡፡ የፅጌም እናት ሁለት ወንድ ልጆቿን አገሬው ከፊቷ አረደባት፡፡ ፅጌም ከእናቱ ተለያይቶ ጉራጌ አገር አርበኞች በአደራ ሰጥተውት አደገ፡፡ ይገናኙ ይሆን? ይህ ስደት ከ89 ዓመታት በኋላ ራሱን የደገመ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የተሰደዱትም ተመልሰዋል፤ ተጨማሪም ሄዷል፡፡ በእርግጥ ማፈናቀሉ ደርግ ሲገባም ሆነ ኢህአዴግ ሲገባ ተሞክሯል፡፡ በዚያች ምሽት የተነጋገርነው ነገር የቤተሰብ ወግና ጨዋታ ሲሆን ስለ ስደቱ አላነሳንም፡፡ ምናልባት እርሳቸው ሆድ እንዳይብሳቸው ይሆናል፡፡ ነገሩ ሁሉ ዝም የተባለ ይመስላል፡፡ አዝማሚያው ግን ተፈናቃዮች እንደሚመለሱና ስደትም እንደሚቆም የሚያሳይ ይመስላል፡፡ የፖሊሲ ለውጥም የግድ ይላል፡፡  

ጓደኛዬ በጣሊያን ወረራው ምክንያት የነገርኩትን የስደት ሁኔታ አስታውሶ አንድ ነገር ጨመረልኝ፡፡ በኢያን ካምቤል መጽሐፍ የተገለጸው ይህ ነገር ጣሊያን አማሮችን ካፈናቀለ በኋላ የገጠሙትን ሁለት ነገሮች ይመለከታል፡፡ አንዱ አማሮች ሲፈናቀሉ መሬቱን የሚያርሰው ስለጠፋ ረሃብ መከሰቱ ሲሆን ሌላው ደግሞ አማሮቹ አርበኞችን መቀላቀላቸው ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ፋሽስቱ ፖሊሲውን ቀይሮ አማሮችን ወይም ሸዋዎችን ወደተፈናቀላችሁባቸው ቦታዎች ተመለሱ የሚል ፖሊሲ ማውጣቱን ነው፡፡     

ሌላ ከአጠገባችን ተቀምጦ የነበረ ጓደኛችን ደግሞ የአሁኑ ስደት ከጣሊያን ወረራው ጋር ብቻ ሳይሆን ከግራኝም ጋር መታየት እንዳለበት ነገረን፡፡ የግራኝ ወረራ ብዙ ህዝብ ያፈናቀለና አገር ያጠፋ እንደነበር ታሪኩን አስታወሰን፡፡ የአባ ባህርይንም ድርሰቶች እንድናነብ ጋበዘን፡፡ በዚህም መሰረት የአሁኑ ሦስተኛው ነው ማለት ነው፡፡ መልካም ቀን ይመጣል ብለን ተስፋ ሰንቀናል፡፡

 

የአስተሳሰባችንን መሰረት አነቃንቅልን!

ማስታወሻ

ማክሰኞ ታህሳስ 2፣ 2016 ዓ.ም.

ደብረብርሃን

 

ይህ ጽሑፍ ስለአንድ ሳምንቱ የአዲስ አበባ ቆይታዬ ነው፡፡ ቆይታዬ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከባድ የሆነው በተለይ ከጤና አንጻር ነበር፡፡ ጉንፋን መሰል የመተንፈሻ አካል ችግር ገጠመኝ፡፡ ምልክቶቹን ገልጬ ጉግል ላይ ሳይ ኮቪድ ወይም ተዛማጅ ነገር የመሆን ዕድል እንዳለው ስረዳ ማድረግ የምችለውን አላውቅም ነበር፡፡ ቀደም ባለው ሳምንት በደብረብርሃን በሰላም ያሳለፍኩትን ሰው በድንገት ከዚህ ሁኔታ ላይ የጣለኝ ነገር አልገባኝም፡፡ ብርድ ሊሆን ይሆናል፡፡ የሆቴሉም የሌሊት ልብስ አይረባም፡፡ ጭማሪ ልብስም መጠየቅ የሚቻል አልመሰለኝም፡፡ ወይ ከቤቴ ብርድልብስ ይዤ አልሄድኩ! አዲስ አበባ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደሄድኩባት ሳትሆን ክረምት መሰል አየር አዘጋጅታ ጠብቃኛለች፡፡ ራስ ምታትም፣ ብርድ ብርድ ማለትና መቆርጠም ተጠራርተው ሰፍረውብኛል፡፡ ሆኖም ቀኑን ሙሉ በጽናት ስብሰባ መሰብሰብ ችያለሁ፡፡ ሌሊት ግን ለማንበብና ለመጻፍ ባስብም አልቻልኩም፡፡ ለማንበብ ይዣቸው የሄድኳቸው መጻሕፍት ይቁለጨለጫሉ፡፡

ቀደም ሲል በዚህ ዓይነት ደረጃው ከፍ ያለ ሆቴል አልጋ እንደሚያዝልኝ የነገረኝ ወዳጄ ሳውናና ስቲም ሳልጠቀም እንዳልመጣ አሳስቦኝ ነበር፡፡ እኔ ህመሙም ስለተጫነኝ አልፈለግሁም፡፡ ሰዎች መታመሜን ሲያዩ እንድሞክረው ስለጠቆሙኝ ገባሁ፡፡ ማለዳ 1፡00 ተከፈተ፡፡ እስኪሞቅ 1፡15 ያለፈ ይመስለኛል፡፡ ከሌሎች ሁለት መምህራን ጋር ገባን፡፡ ስቲም ውስጥ ሳለን ስለ አመጋገቤና አስተሳሰቤ ወሬ ተነሳ፡፡ ስለ ፆሙ ሁኔታ ጥያቄ ይጠይቁኝና እመልስ ጀመር፡፡ በቀን አንዴ ብቻ ለምን ትመገባለህ ለሚለው ያለኝን መልስ በመጀመሪያ ስንገናኝ ከጤናና ከምቾት አንጻር እያልኩ ስመልስ ቆይቻለሁ፡፡ የማወቅ ጉጉታቸው ተነሣሣ፡፡ እኔም እንዲያነቡ በማለት መልሱን ገደብኩት፡፡ ስለ አስተሳሰቤ የጠየቁኝን ግን አቆምኩት ማለት ይቻላል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ያዳበርኩት ከትምህርት፣ ከአካባቢና ከአስተዳደግ ወይም ከማሰላሰል ይመስለኛል፡፡ የኔን ሃሳብ እነሱ ላይ ለምን እጭናለሁ ብዬ ዝም አልኳቸው፡፡ የአስተሳሰባቸውን መሰረት እንዳነቃንቀውና የኔን የዓለም ዕይታ እንዳጋራቸው የጠየቁኝን ግን ከውሱን ነጥቦች ውጪ አልሄድኩበትም፡፡ ምክንያቱም ቅሬታ እንዳይሰማቸው፣ ያላቸው አስተሳሰብ እንዳይሸረሸርና የተገናኘንበት ጉዳይ እርሱ ስላልሆነ ነው፡፡ አንደኛው ከአማራ፣ ሌላኛው ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ አንደኛው ‹‹ስለጻፍካቸው መጻሕፍት ስትናገር አስተሳሰብህን ገመትኩ›› አለኝ፡፡ ሲቆሰቁሱኝ ግን ሳይንስን የተዳፈሯት መሰለኝ፡፡ በዚህም መልኩ ቆሰቆሱኝ፤ ነደድኩም፤ ወላፈኑም ሞቃቸው፡፡  ለሳይንስ የበኩር ልጇ ባልሆንም ጥብቅና ቆምኩላት፡፡ ‹‹ሳይንስን መረዳት ካልቻልክ…›› የሚል አንድ ጥቅስ ትዝ አለኝ፡፡ ሳይንስን በጥሩ ሁኔታ አልገነዘባትም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይንስን የምረዳበት አቅም ባላጎለብትም በመጠኑ እቃኛታለሁ፡፡ ወዳጆቼ ግን እንዲጠይቁ ክብሪት ለኮስኩ፡፡ የቁርስ ሰዓት ስለደረሰ ቀድሜ ሄድኩ፡፡ ቀጠሮ ጠየቁኝ፤ በተመቻቸው ሰዓት እንደምናወራ ተስማምተን ተለያየን፡፡ የአስተሳሰቡ አምድ በሃሳብ መራጃ እንዲቀጠቀጥ የሚፈልግ ትውልድ እየመጣ መሆኑ አስገረመኝ፡፡

ሁለቱ ደግሞ አንድ ምሽት ላይ በተመሳሳይ ፆታ ጋብቻና ግንኙነት ላይ ያላቸውን ሃሳብ ያወሩ ጀመር፡፡ የግለሰብ ነጻነት ነው የሚል የተለመደና የተሰለቸ ወግ ጀማመራቸው፡፡ የግለሰብ ነጻነት ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ከግለሰብ በላይ ህብረተሰብ እንዳለ፣ ባህል የኛ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው፣ አረቦች ባህላቸውን በገንዘባቸው ሲያስከብሩ እኛ በብልሃት ማስከበር እንደማያቅተን ሞገትኩ፡፡ ተቀባይነት የሌላቸውን የወሲብ አባዜዎችን መከላከል ስለሚገባን ሁኔታ ተናገርኩ፡፡ በባህላችን የማይበሉ እንስሳት ስጋ መመገብ እንደሌለብንም ከአስተዳደግና ከልማድ ተነስቼ ተናገርኩ፡፡ የዱሮ ሰው አድርገው ያዩኝ መሰለኝ፡፡ የሚያምኑበት ኃይማኖት የሚቃረነውን ነገር እንኳን ለመደገፍ ወደ ኋላ የማይሉ ሰዎች መምጣታቸው ስለ ነገ እንድናስብና እንድንመክር አያደርግም ትላላችሁ? የግሎባላይዜሽን ተጽዕኖ!

ሌላ ቀን ደግሞ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት መምህራን ሆነው ስለ ዝግመተለውጥ ቲዎሪ ጠያየቁኝ፡፡ ካነበብኩትና ከሰማሁት ለመፈተሽ ዝግጁ የሆኑ ትውሮችንና ሃሳቦችን አንስቼ ቢቃወሙም እንደማልናደድባቸው አሳውቄ ለውይይት ክፍት መድረክ ዘረጋሁ፡፡ ማሰብንና ለአንድ አፍታ እንኳን መጠየቅን አበረታታሁ፡፡ ያው በየትምህርት ዘርፋቸው የሚጠይቁ፣ የሚያስተምሩና የሚመራመሩ ቢሆኑም ስለ ሕይወት ለመጠየቅ ፍላጎታቸው ዉሱን መሆኑን በመረዳቴ ነው፡፡ ሕይወት ስንል አጽናፈ-ዓለም ከየት እንደመጣ፣ ወዴት እንደሚሄድ፣ ስንሞት ምን እንደምንሆን፣ ሲጠይቁኝ መጠየቃቸው መልካም መሆኑን ገልጬ ጥያቄውን በጥያቄ መልሼላቸዋለሁ፡፡ መልስ ፍለጋ ያነባሉ ወይንስ አያነቡም የሚለውን ጊዜ ይፈታዋል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ አንብበው ወይም በግል ጥናት መርምረው ሳይሆን ሌላ ሰው ምን እንደሚያስብ በመጠየቅ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን አየሁ፡፡

ሌሎቹ ሁለቱ አንድ ምሽት ስለ ቁጠባ ባህል አስፈላጊነት አስተማሩኝ፡፡ ስለ ፍቅርና ትዳርም አብራሩልኝ፡፡ ሀብት ማፍራትና በዚያም ተጽዕኖ መፍጠርንም አልዘነጉም፡፡ በምችለው አቅም እንድሯሯጥ መከሩኝ፡፡ የጠጣሁትን ቡና ዋጋ ከፈልኩ፡፡ የድራፍቱን እንዲከፍሉ በማሰብ ነው፡፡ በዚህም ተገርመው የበለጠ ዋጋ ያለው መጠጥ ስለተጠቀሙ እነሱ ሊከፍሉ እንደሚገባ ነገሩኝ፡፡ ይቺን ትምህርት ቤት ገብተን ህብረተሰብ መጽሐፍ ላይ የተማርናትን አብሮ መብላት የምትባል ነገር ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ስላጠናከራት እውነት ትመስላቸዋለች መሰለኝ፡፡ በጥቁርና ቀይ ሚስት ምርጫ ላይም ያልነው ነበር፡፡ እሱ ቢጀምሩትም አያልቅ!

ምሳ ሲበሉ ከደብረብርሃን በዉሱን ቁጥር ከያዝኳቸው ከኔ መጻሕፍት የተወሰኑትን ለመሸጥ የተጠጋኋቸው ደግሞ ስፆም ምን ዓይነት ምግብ እንደምመገብ፣ ረሃቡን እንዴት እንደምችለው፣ ትዳር እንዳለኝ፣ ወዘተ ይጠይቁኛል፡፡ በተቻለኝ መጠን ስመልስ ደግመውና ሰልሰው ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ሲኖሩ፤ የሚሞግቱም አይጠፉም፡፡ ከህይወት ግብ አንጻር ተምሮ ስራ መያዝ አንድ ግብ ሆኖኝ እንደሚያውቅ ገልጬ ከሱ ዉጪ ጎላ ያለ እንዳልነበረኝ ነገርኳችው፡፡ ለዚያም ራሴን ግቡን የመታ አድርጌ ቆጥሬ ይሆናል፡፡ አሁን በነሱና መሰል ተመልካቾች ምክንያት ግብ ለመቅረጽ እየዳዳኝ መሆኑን ሲረዱ ላስብባቸው የሚገቡ ነጥቦችን አስያዙኝ፡፡ የሰው ምክር ጥሩ ነው ብዬ ወደ ማመኑ እያዘነበልኩ መሰለኝ፡፡   

ያንተ አስተሳሰብ ትክክል ከሆነና የተቀዳበትን ካወቅነው ልንሰማው ዝግጁ ነን ያሉ፣ ለመሞከር የተዘጋጁ፣ የተማሩና ለለውጥ ያቆበቆቡ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥሩ የሚሆነው እነሱ ባላቸው ልምድ፣ ዕውቀትና የትምህርት ዝግጅት ፈልገው የሚደርሱበት ሃሳብ እንጂ እኔ ከዉጪ ስጫናቸው መሆን የለበትም፡፡ አእምራቸው እንዲጠይቅ ማድረግን ላስገነዝብ እችላለሁ፡፡ ከሥራዎቼ የመጀመሪያው የሆነው የትርጉም መጽሐፌ ‹‹ሁቱትሲ›› የሩዋንዳን የዘር ፖለቲካና ፍሬውን ያስቃኛል፡፡ ከዘር ማጥፋቱ በፊት፣ ወቅትና በኋላ የነበሩትን ሁኔታዎች ይዳስስና የይቅርታንና እርቅን አስፈላጊነት ያስተምራል፡፡ ገንዘብ ለምን እንደምቆጥብ ሳላውቅ ቆጥቤ ክፈል ስባል በደስታ የከፈልኩበት የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ህትመት 62 000 ብር (በ2008 ዓ.ም.) ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ገንዘቤ መቶ ሺ በሚሆንበት ጊዜ ሮጬ ማተሚያ ቤት ነኝ፡፡ ለሁቱትሲ፣ ‹‹ለፆም ጣዕም››ና ‹‹ለብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› የከፈልኩት ከሚሊዮን ብር በላይ ደረሰኝ አለኝ፡፡ ከዚህ የመጣው ገንዘብ ደግሞ ለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መጻሕፍት መግዣና ስራ ማስኬጃ ሆኗል፡፡ 36 000 ኮፒ የታተሙት መጻሕፍቱ አስተርጉሜ ያሳተምኩትን የኦሮምኛ ሁቱትሲ ጨምሮ በሶፍት ኮፒ ለህብረተሰቡ እንዲለቀቁ አድርጌያለሁ፡፡ አንድ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ስለማገኘው ገንዘብ በጠየቀኝ ጊዜ ገንዘብ እንደማገኝ፣ ሳገኝም የንግድ ባንክ ሞባይል አፕሊኬሽኔን ሳይቀር ስክሪንሾት አንስቼ ሰዎችን ለስራ ለማነሳሳት በፌስቡክ መለጠፌን ገልጫለሁ፡፡ የማገኛት ገንዘብ ዉሱን ብትሆንም ለማምንበት ዓላማ አውያታለሁ፡፡ ነገ የሚፈርስ ቤት ወይም የሚገለበጥ መኪና ከምገዛ ቆይቶ የሚታወስ ስራ ልስራ ብዬ ነው፡፡ በምሽቱ ወግ ያወጋሁላቸው ሁለቱ ወሳኝ ነጥቦች አነሱብኝ፡፡ አንዱ ‹‹ደብረብርሃን በእግርህ ስትሄድ ባለ ቤተመጻሕፍቱ ይቺትና›› መባል ትፈልጋለህ ወይንስ ቤትና መኪና ኖሮህ ‹‹እሱ ነው ባለ ቤተመጻሕፍቱ ተብለህ መከበር›› አለኝ፡፡ ሌላኛው ስለ ግልጽ ራዕይ፣ ስለ ግል ፋይናንሽያል ዕቅድ አነሳልኝ፡፡ ‹‹የትርፍ ሰዓት ስራ ሰርተህ ለቤተሰብህ ስጣቸው›› ያለኝን አንድ ወዳጄን በተወሰነ መልኩ አስታወሱኝ፡፡ ጊዜያችንን እና ገንዘባችንን እንዲሁም ትኩረታችንን እንዴት እንደምንይዛቸው እኛው እንድንወስን ቢተውልን ጥሩ ይመስለኛል፡፡

በራሴ ምህዋር ላይ ስለምዞር ስለ ጦርነት፣ ፖለቲካ፣ ቀጣናዊ ጉዳዮች፣ የብሔር አዙሪት፣ ጥቅመኝነት፣ ሰሞነኛ ነገሮች ያወራልኝ ሰው አልነበረም፡፡ አውርተንስ ምን አመጣን! ተመልካች እንጂ ተዋናይ አይደለሁ! ተሰብሳቢቹ ከኔ ጋር ሲገናኙ የትኩረት ነጥብ ሆኛለሁ፡፡ ጉዳዩ ከተሰብሳቢዎቹ አልፎ ሰብሳቢዎቹም ጋ ደረሰ፡፡ ወደ ራሳችን መለስ ስንል ብዙ ትኩረት መሳብና መስራት እንደምንችል  ይታሰበኛል፡፡ እናንተስ?

በደብረብርሃን ከተማ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትን ከፍቼ በራሴ ወጪ ህዝቡን በነጻ ማስነበቤ ከሚያስደንቋቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የአብርሃም ማስሎውን የፍላጎት እርከን ገለበጥከው ያለኝ አንደኛው ወዳጄ ንግግር ምናልባት በትክክል ገልጾኝ ይሆናል፡፡ ወጣ ያሉ ቃንቄ ሃሳቦች እንዳሉኝ አስገንዝበውኛል፡፡ ከሃሳብም በዘለለ ግዘፍ ይነሱ ዘንድ ለመተግበር መሞከሬ ይሆናል በሰዉ አእምሮ ውስጥ ጥያቄዎች አጫረ፡፡ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ እንዳግዛቸው ወይም አሰራሩን ከልምድ እንዳሳያቸው አድራሻዬን የሚወስዱና የሚያዋሩኝ ነበሩ፡፡ ለመደምደሚያ ያህል አልፈልጋቸውም ያልኳቸው ሦስት በ‹ት› ፊደል የሚያልቁ ነገሮች እየተሸረሸሩ መሆኑን መጠርጠራቸውን ነግረውኛል፡፡ እነርሱም ትምህርት፣ ቤትና ሚስት ናቸው፡፡

 

 

 

W. F., the boy who alerted his family to the dangers of armed individuals in the woods

  W. F., the boy who alerted his family to the dangers of armed individuals in the woods I am W. F., a native of Menz Kebele , Dano Wer...