2023 ዲሴምበር 13, ረቡዕ

የአስተሳሰባችንን መሰረት አነቃንቅልን!

ማስታወሻ

ማክሰኞ ታህሳስ 2፣ 2016 ዓ.ም.

ደብረብርሃን

 

ይህ ጽሑፍ ስለአንድ ሳምንቱ የአዲስ አበባ ቆይታዬ ነው፡፡ ቆይታዬ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከባድ የሆነው በተለይ ከጤና አንጻር ነበር፡፡ ጉንፋን መሰል የመተንፈሻ አካል ችግር ገጠመኝ፡፡ ምልክቶቹን ገልጬ ጉግል ላይ ሳይ ኮቪድ ወይም ተዛማጅ ነገር የመሆን ዕድል እንዳለው ስረዳ ማድረግ የምችለውን አላውቅም ነበር፡፡ ቀደም ባለው ሳምንት በደብረብርሃን በሰላም ያሳለፍኩትን ሰው በድንገት ከዚህ ሁኔታ ላይ የጣለኝ ነገር አልገባኝም፡፡ ብርድ ሊሆን ይሆናል፡፡ የሆቴሉም የሌሊት ልብስ አይረባም፡፡ ጭማሪ ልብስም መጠየቅ የሚቻል አልመሰለኝም፡፡ ወይ ከቤቴ ብርድልብስ ይዤ አልሄድኩ! አዲስ አበባ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደሄድኩባት ሳትሆን ክረምት መሰል አየር አዘጋጅታ ጠብቃኛለች፡፡ ራስ ምታትም፣ ብርድ ብርድ ማለትና መቆርጠም ተጠራርተው ሰፍረውብኛል፡፡ ሆኖም ቀኑን ሙሉ በጽናት ስብሰባ መሰብሰብ ችያለሁ፡፡ ሌሊት ግን ለማንበብና ለመጻፍ ባስብም አልቻልኩም፡፡ ለማንበብ ይዣቸው የሄድኳቸው መጻሕፍት ይቁለጨለጫሉ፡፡

ቀደም ሲል በዚህ ዓይነት ደረጃው ከፍ ያለ ሆቴል አልጋ እንደሚያዝልኝ የነገረኝ ወዳጄ ሳውናና ስቲም ሳልጠቀም እንዳልመጣ አሳስቦኝ ነበር፡፡ እኔ ህመሙም ስለተጫነኝ አልፈለግሁም፡፡ ሰዎች መታመሜን ሲያዩ እንድሞክረው ስለጠቆሙኝ ገባሁ፡፡ ማለዳ 1፡00 ተከፈተ፡፡ እስኪሞቅ 1፡15 ያለፈ ይመስለኛል፡፡ ከሌሎች ሁለት መምህራን ጋር ገባን፡፡ ስቲም ውስጥ ሳለን ስለ አመጋገቤና አስተሳሰቤ ወሬ ተነሳ፡፡ ስለ ፆሙ ሁኔታ ጥያቄ ይጠይቁኝና እመልስ ጀመር፡፡ በቀን አንዴ ብቻ ለምን ትመገባለህ ለሚለው ያለኝን መልስ በመጀመሪያ ስንገናኝ ከጤናና ከምቾት አንጻር እያልኩ ስመልስ ቆይቻለሁ፡፡ የማወቅ ጉጉታቸው ተነሣሣ፡፡ እኔም እንዲያነቡ በማለት መልሱን ገደብኩት፡፡ ስለ አስተሳሰቤ የጠየቁኝን ግን አቆምኩት ማለት ይቻላል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ያዳበርኩት ከትምህርት፣ ከአካባቢና ከአስተዳደግ ወይም ከማሰላሰል ይመስለኛል፡፡ የኔን ሃሳብ እነሱ ላይ ለምን እጭናለሁ ብዬ ዝም አልኳቸው፡፡ የአስተሳሰባቸውን መሰረት እንዳነቃንቀውና የኔን የዓለም ዕይታ እንዳጋራቸው የጠየቁኝን ግን ከውሱን ነጥቦች ውጪ አልሄድኩበትም፡፡ ምክንያቱም ቅሬታ እንዳይሰማቸው፣ ያላቸው አስተሳሰብ እንዳይሸረሸርና የተገናኘንበት ጉዳይ እርሱ ስላልሆነ ነው፡፡ አንደኛው ከአማራ፣ ሌላኛው ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ አንደኛው ‹‹ስለጻፍካቸው መጻሕፍት ስትናገር አስተሳሰብህን ገመትኩ›› አለኝ፡፡ ሲቆሰቁሱኝ ግን ሳይንስን የተዳፈሯት መሰለኝ፡፡ በዚህም መልኩ ቆሰቆሱኝ፤ ነደድኩም፤ ወላፈኑም ሞቃቸው፡፡  ለሳይንስ የበኩር ልጇ ባልሆንም ጥብቅና ቆምኩላት፡፡ ‹‹ሳይንስን መረዳት ካልቻልክ…›› የሚል አንድ ጥቅስ ትዝ አለኝ፡፡ ሳይንስን በጥሩ ሁኔታ አልገነዘባትም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይንስን የምረዳበት አቅም ባላጎለብትም በመጠኑ እቃኛታለሁ፡፡ ወዳጆቼ ግን እንዲጠይቁ ክብሪት ለኮስኩ፡፡ የቁርስ ሰዓት ስለደረሰ ቀድሜ ሄድኩ፡፡ ቀጠሮ ጠየቁኝ፤ በተመቻቸው ሰዓት እንደምናወራ ተስማምተን ተለያየን፡፡ የአስተሳሰቡ አምድ በሃሳብ መራጃ እንዲቀጠቀጥ የሚፈልግ ትውልድ እየመጣ መሆኑ አስገረመኝ፡፡

ሁለቱ ደግሞ አንድ ምሽት ላይ በተመሳሳይ ፆታ ጋብቻና ግንኙነት ላይ ያላቸውን ሃሳብ ያወሩ ጀመር፡፡ የግለሰብ ነጻነት ነው የሚል የተለመደና የተሰለቸ ወግ ጀማመራቸው፡፡ የግለሰብ ነጻነት ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ከግለሰብ በላይ ህብረተሰብ እንዳለ፣ ባህል የኛ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው፣ አረቦች ባህላቸውን በገንዘባቸው ሲያስከብሩ እኛ በብልሃት ማስከበር እንደማያቅተን ሞገትኩ፡፡ ተቀባይነት የሌላቸውን የወሲብ አባዜዎችን መከላከል ስለሚገባን ሁኔታ ተናገርኩ፡፡ በባህላችን የማይበሉ እንስሳት ስጋ መመገብ እንደሌለብንም ከአስተዳደግና ከልማድ ተነስቼ ተናገርኩ፡፡ የዱሮ ሰው አድርገው ያዩኝ መሰለኝ፡፡ የሚያምኑበት ኃይማኖት የሚቃረነውን ነገር እንኳን ለመደገፍ ወደ ኋላ የማይሉ ሰዎች መምጣታቸው ስለ ነገ እንድናስብና እንድንመክር አያደርግም ትላላችሁ? የግሎባላይዜሽን ተጽዕኖ!

ሌላ ቀን ደግሞ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት መምህራን ሆነው ስለ ዝግመተለውጥ ቲዎሪ ጠያየቁኝ፡፡ ካነበብኩትና ከሰማሁት ለመፈተሽ ዝግጁ የሆኑ ትውሮችንና ሃሳቦችን አንስቼ ቢቃወሙም እንደማልናደድባቸው አሳውቄ ለውይይት ክፍት መድረክ ዘረጋሁ፡፡ ማሰብንና ለአንድ አፍታ እንኳን መጠየቅን አበረታታሁ፡፡ ያው በየትምህርት ዘርፋቸው የሚጠይቁ፣ የሚያስተምሩና የሚመራመሩ ቢሆኑም ስለ ሕይወት ለመጠየቅ ፍላጎታቸው ዉሱን መሆኑን በመረዳቴ ነው፡፡ ሕይወት ስንል አጽናፈ-ዓለም ከየት እንደመጣ፣ ወዴት እንደሚሄድ፣ ስንሞት ምን እንደምንሆን፣ ሲጠይቁኝ መጠየቃቸው መልካም መሆኑን ገልጬ ጥያቄውን በጥያቄ መልሼላቸዋለሁ፡፡ መልስ ፍለጋ ያነባሉ ወይንስ አያነቡም የሚለውን ጊዜ ይፈታዋል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ አንብበው ወይም በግል ጥናት መርምረው ሳይሆን ሌላ ሰው ምን እንደሚያስብ በመጠየቅ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን አየሁ፡፡

ሌሎቹ ሁለቱ አንድ ምሽት ስለ ቁጠባ ባህል አስፈላጊነት አስተማሩኝ፡፡ ስለ ፍቅርና ትዳርም አብራሩልኝ፡፡ ሀብት ማፍራትና በዚያም ተጽዕኖ መፍጠርንም አልዘነጉም፡፡ በምችለው አቅም እንድሯሯጥ መከሩኝ፡፡ የጠጣሁትን ቡና ዋጋ ከፈልኩ፡፡ የድራፍቱን እንዲከፍሉ በማሰብ ነው፡፡ በዚህም ተገርመው የበለጠ ዋጋ ያለው መጠጥ ስለተጠቀሙ እነሱ ሊከፍሉ እንደሚገባ ነገሩኝ፡፡ ይቺን ትምህርት ቤት ገብተን ህብረተሰብ መጽሐፍ ላይ የተማርናትን አብሮ መብላት የምትባል ነገር ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ስላጠናከራት እውነት ትመስላቸዋለች መሰለኝ፡፡ በጥቁርና ቀይ ሚስት ምርጫ ላይም ያልነው ነበር፡፡ እሱ ቢጀምሩትም አያልቅ!

ምሳ ሲበሉ ከደብረብርሃን በዉሱን ቁጥር ከያዝኳቸው ከኔ መጻሕፍት የተወሰኑትን ለመሸጥ የተጠጋኋቸው ደግሞ ስፆም ምን ዓይነት ምግብ እንደምመገብ፣ ረሃቡን እንዴት እንደምችለው፣ ትዳር እንዳለኝ፣ ወዘተ ይጠይቁኛል፡፡ በተቻለኝ መጠን ስመልስ ደግመውና ሰልሰው ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ሲኖሩ፤ የሚሞግቱም አይጠፉም፡፡ ከህይወት ግብ አንጻር ተምሮ ስራ መያዝ አንድ ግብ ሆኖኝ እንደሚያውቅ ገልጬ ከሱ ዉጪ ጎላ ያለ እንዳልነበረኝ ነገርኳችው፡፡ ለዚያም ራሴን ግቡን የመታ አድርጌ ቆጥሬ ይሆናል፡፡ አሁን በነሱና መሰል ተመልካቾች ምክንያት ግብ ለመቅረጽ እየዳዳኝ መሆኑን ሲረዱ ላስብባቸው የሚገቡ ነጥቦችን አስያዙኝ፡፡ የሰው ምክር ጥሩ ነው ብዬ ወደ ማመኑ እያዘነበልኩ መሰለኝ፡፡   

ያንተ አስተሳሰብ ትክክል ከሆነና የተቀዳበትን ካወቅነው ልንሰማው ዝግጁ ነን ያሉ፣ ለመሞከር የተዘጋጁ፣ የተማሩና ለለውጥ ያቆበቆቡ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥሩ የሚሆነው እነሱ ባላቸው ልምድ፣ ዕውቀትና የትምህርት ዝግጅት ፈልገው የሚደርሱበት ሃሳብ እንጂ እኔ ከዉጪ ስጫናቸው መሆን የለበትም፡፡ አእምራቸው እንዲጠይቅ ማድረግን ላስገነዝብ እችላለሁ፡፡ ከሥራዎቼ የመጀመሪያው የሆነው የትርጉም መጽሐፌ ‹‹ሁቱትሲ›› የሩዋንዳን የዘር ፖለቲካና ፍሬውን ያስቃኛል፡፡ ከዘር ማጥፋቱ በፊት፣ ወቅትና በኋላ የነበሩትን ሁኔታዎች ይዳስስና የይቅርታንና እርቅን አስፈላጊነት ያስተምራል፡፡ ገንዘብ ለምን እንደምቆጥብ ሳላውቅ ቆጥቤ ክፈል ስባል በደስታ የከፈልኩበት የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ህትመት 62 000 ብር (በ2008 ዓ.ም.) ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ገንዘቤ መቶ ሺ በሚሆንበት ጊዜ ሮጬ ማተሚያ ቤት ነኝ፡፡ ለሁቱትሲ፣ ‹‹ለፆም ጣዕም››ና ‹‹ለብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› የከፈልኩት ከሚሊዮን ብር በላይ ደረሰኝ አለኝ፡፡ ከዚህ የመጣው ገንዘብ ደግሞ ለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መጻሕፍት መግዣና ስራ ማስኬጃ ሆኗል፡፡ 36 000 ኮፒ የታተሙት መጻሕፍቱ አስተርጉሜ ያሳተምኩትን የኦሮምኛ ሁቱትሲ ጨምሮ በሶፍት ኮፒ ለህብረተሰቡ እንዲለቀቁ አድርጌያለሁ፡፡ አንድ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ስለማገኘው ገንዘብ በጠየቀኝ ጊዜ ገንዘብ እንደማገኝ፣ ሳገኝም የንግድ ባንክ ሞባይል አፕሊኬሽኔን ሳይቀር ስክሪንሾት አንስቼ ሰዎችን ለስራ ለማነሳሳት በፌስቡክ መለጠፌን ገልጫለሁ፡፡ የማገኛት ገንዘብ ዉሱን ብትሆንም ለማምንበት ዓላማ አውያታለሁ፡፡ ነገ የሚፈርስ ቤት ወይም የሚገለበጥ መኪና ከምገዛ ቆይቶ የሚታወስ ስራ ልስራ ብዬ ነው፡፡ በምሽቱ ወግ ያወጋሁላቸው ሁለቱ ወሳኝ ነጥቦች አነሱብኝ፡፡ አንዱ ‹‹ደብረብርሃን በእግርህ ስትሄድ ባለ ቤተመጻሕፍቱ ይቺትና›› መባል ትፈልጋለህ ወይንስ ቤትና መኪና ኖሮህ ‹‹እሱ ነው ባለ ቤተመጻሕፍቱ ተብለህ መከበር›› አለኝ፡፡ ሌላኛው ስለ ግልጽ ራዕይ፣ ስለ ግል ፋይናንሽያል ዕቅድ አነሳልኝ፡፡ ‹‹የትርፍ ሰዓት ስራ ሰርተህ ለቤተሰብህ ስጣቸው›› ያለኝን አንድ ወዳጄን በተወሰነ መልኩ አስታወሱኝ፡፡ ጊዜያችንን እና ገንዘባችንን እንዲሁም ትኩረታችንን እንዴት እንደምንይዛቸው እኛው እንድንወስን ቢተውልን ጥሩ ይመስለኛል፡፡

በራሴ ምህዋር ላይ ስለምዞር ስለ ጦርነት፣ ፖለቲካ፣ ቀጣናዊ ጉዳዮች፣ የብሔር አዙሪት፣ ጥቅመኝነት፣ ሰሞነኛ ነገሮች ያወራልኝ ሰው አልነበረም፡፡ አውርተንስ ምን አመጣን! ተመልካች እንጂ ተዋናይ አይደለሁ! ተሰብሳቢቹ ከኔ ጋር ሲገናኙ የትኩረት ነጥብ ሆኛለሁ፡፡ ጉዳዩ ከተሰብሳቢዎቹ አልፎ ሰብሳቢዎቹም ጋ ደረሰ፡፡ ወደ ራሳችን መለስ ስንል ብዙ ትኩረት መሳብና መስራት እንደምንችል  ይታሰበኛል፡፡ እናንተስ?

በደብረብርሃን ከተማ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትን ከፍቼ በራሴ ወጪ ህዝቡን በነጻ ማስነበቤ ከሚያስደንቋቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የአብርሃም ማስሎውን የፍላጎት እርከን ገለበጥከው ያለኝ አንደኛው ወዳጄ ንግግር ምናልባት በትክክል ገልጾኝ ይሆናል፡፡ ወጣ ያሉ ቃንቄ ሃሳቦች እንዳሉኝ አስገንዝበውኛል፡፡ ከሃሳብም በዘለለ ግዘፍ ይነሱ ዘንድ ለመተግበር መሞከሬ ይሆናል በሰዉ አእምሮ ውስጥ ጥያቄዎች አጫረ፡፡ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ እንዳግዛቸው ወይም አሰራሩን ከልምድ እንዳሳያቸው አድራሻዬን የሚወስዱና የሚያዋሩኝ ነበሩ፡፡ ለመደምደሚያ ያህል አልፈልጋቸውም ያልኳቸው ሦስት በ‹ት› ፊደል የሚያልቁ ነገሮች እየተሸረሸሩ መሆኑን መጠርጠራቸውን ነግረውኛል፡፡ እነርሱም ትምህርት፣ ቤትና ሚስት ናቸው፡፡

 

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...