በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት
ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም.
መዘምር ግርማ
ደብረብርሃን
ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረት መናኸሪያ ወደ ደብረብርሃን እየመጡ እንደሆነ ደውለው ነገሩኝ፡፡ እኔም ሲመጡ እንደምቀበላቸው ነገርኳቸው፡፡ ሲደርሱ ደውለው ቤተመጻሕፍት ተገናኘን፡፡ ከመስሪያ ቤት መጥቼ እዚያ ስላገኘኋቸው አመሰገኑኝ፡፡ እኔም ላደርግላቸው የምችለው ቀላሉ ነገር ስለሆነ እንዳያስቡ ነገርኳቸው፡፡ ወደ ሆስፒታል በቀጥታ ሄድን፡፡ ስላለፋቸው ቀጠሮ ትናንት ጠይቄላቸው ስለነበር በተባለው ክፍል ሄደን አጣራን፡፡ ፋይላቸውን ማስወጣት ያስፈልግ ስለነበር አወጣን፡፡ ሰሞኑን የመታከም ዕድል እንደሚኖራቸው ተነግሮን ወደ ጠባሴ ተመለስን፡፡ ጠባሴም ሌሎች ቤት የተከራዩ ተፈናቃዮች ዘመዶች ስላሏቸው ወደነሱ እሄዳለሁ ስላሉ ምሳ በልተው ሄዱ፡፡ ነገና ሰሞኑን ተከታትለን እንደምናሳክማቸው ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ለእያንዳንዷ ጉዳይ ሲያመሰግኑኝ ዋሉ፡፡ ይህም ለኔ የሚያሳፍር ነበር፡፡ ወደ ወለጋ ከተመለሱ እኔ የማውቃቸው የቤተመጻሕፍት አንባቢ ልጆች የእርሳቸውን ልጅ ስለማውቅና ስልካቸው ስላለኝ ከሄዱ ጀምሮ እንደዋወላለን፡፡
ቆይታችን የሁለት ሰዓት ገደማ ይሆን ነበር፡፡ የነገሩኝን ነገር እንደሚከተለው አቀርበዋሁ፡፡
‹‹ደውዬ እዚህ ጠይቅልኝ ያልኩህ እዚያ ያለው ሆስፒታል ለአምቦ ጽፎልኝ አምቦ መታከም ስላልቻኩ ነው፡፡ በእርግጥ በስልክ አልነገርኩህም፡፡ አምቦ ሆስፒታል ጥሩ ፊት አላሳዩኝም፡፡ ወጣት ሐኪሞች ናቸው፡፡ ሁኔታው ጥሩ አይደለም፡፡ ሕክምናውም ሆነ ዕቃውም ያላቸውም አይመስለኝም፡፡ ለአዲስ አበባ እንጻፍልህ ሲሉኝ አዲስ አበባ ለመታከም ሰውም ስለሌለኝ እዚሁ ለመምጣት ወሰንኩ፡፡ አዲስ አበባ ሌላ ህመም አሞኝ ከሁለት ዓመት በፊት ታክሜ ድኛለሁ፡፡ ጥሩ ህክምና ያለው ነቀምት ነበር፡፡ ነቀምት አይርቀኝም፡፡ ችግሩ እዚያ እንዴት ተደርሶ! መንገድ ላይ ይገድላሉ፡፡ እዚያስ አላክምም ቢሉ በምን ይታወቃል?
የኛ ነገር ያሳዝል መቼም፡፡ እዚህ ደብረ ብርሃን እኮ 80 ኦሮሞ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ አማራ አግብተው አንለይም ብለው የመጡ፡፡ እዚያ አላስኖር አሏቸው፡፡ እኔ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁለቱ ትልልቆቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ትዳር ይዘዋል፡፡ ሁለቱ ትንንሾቹ ወንዶች ናቸው፡፡ አንተም ጋ ይማሩ ስለነበር ታውቃቸዋለህ፡፡
ከደብረብርሃን ሲወስዱን ሌሊት ነው ካምፕ መጥተው ስም እየጠሩ የወሰዱን፡፡ እኔ ማክሰኞ የሕክምና ቀጠሮ ስላለኝ ልጆቼና ባለቤቴ ይሂዱ እኔ ታክሜ ልሂድ ብል አይሆንም ብለው ወሰዱኝ፡፡ እዚያ እንደደረስን አቀባበሉ ደማቅ ነበር፡፡ የገባን ዕለት እንጀራ አበሉን፡፡ 15 ኪሎ ሩዝም ሰጡን፡፡ ጀሪካን ሰጡን፡፡ ብረት ድስት የሌለው ስላለ በምን አብስሎ ይብላ? ሰዉ ተራበ፡፡ ለልጆቻችን ሩዝ አብስለን ስንሰጣቸው ማታ በልተው ጠዋት አልደግም አሉ፡፡ ትምህርት የለ ምን የለ! ልጆቻችን ተሰላችተዋል፡፡ ደብረብርሃን ከካምፕም ወጥተው ይሰሩ ነበር፡፡ ትምህርት ቤትም ይሄዳሉ፤ ቤተመጻሕፍትም ቅዳሜና እሁድ ይመጣሉ፡፡ ልጆቼን እንደልጃቸው አድርገው የሚይዙልኝ ባገኝ አሾልኬ እልካቸው ነበር፡፡ ከገበያ የሚገዛውን ሸራ ዳስ ሰርተው እሱ ውስጥ ነው በካምፕ የሚያኖሩን፡፡ ፖሊስና ሚሊሻ ነው የሚጠብቀን፡፡ ትልልቁ ሰው መጣችሁልን ብሎ መጥቶ ጠየቀን፡፡ ተደሰተ፡፡ ለምን ሄዳችሁ ጠየቃችሁ እንባላለን ብለው ፈርተውም የቀሩ አሉ፡፡ እኔ ነዋሪነቴ ከተማ ነበር፡፡ የገጠሮቹ ቤታቸው ስለተቃጠለ መመለሻ የላቸውም፡፡ የህይወትም ዋስትና የለም፡፡ የኔ ግቢ ትልቅ ነው፡፡ ሰርቪሱ ውስጥ የተከራዩ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ እኛ ወደ ደብረብርሃን ስንሰደድ ግቡበት አልናቸው፡፡ እነሱ ግን አንገባም አሉ፡፡ ሴቷ በተለይ ‹‹ለነሱ ያልሆነ ቤት ለኛም አይሆነንም፤ አንገባም!›› አለች፡፡ ከደብረብርሃን ደውለን ለምነን ነው ያስገባናት፡፡ አሁን ባሏም እሷም እየተፈራረቁ እንጀራ እየያዙ ይጠይቁናል፡፡
የሰላሙ ነገር አሁን የተረጋጋ ቢመስልም ችግሩ መልሶ ይነሳል፡፡ ይህን ሰሞን ህክምናዬ ቢያልቅልኝ እመለስ ነበር፡፡››
እኔም ተከታትለን እንደምናሳክማቸው ነግሬ ሸኘኋቸው፡፡
ማስታወሻ - ይህ ምስክርነት ከደብረብርሃን ወደ አንድ የኦሮሚያ ወረዳ የተወሰዱትን ብቻ የሚመለከት እንጂ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የተወሰዱትን አይመለከትም፡፡
ሁለተኛ ቀን
ከወለጋ ተመልሰው ደብረብርሃን የሕክምናቸውን ሁኔታ የሚከታተሉትን አዛውንት ለሁለተኛ ቀን አገኘኋቸው። ስለአሜሪካ ድምፁ ዘገባም ነገርኳቸው። ችግሩን አስመልክተው እዚያ ከካምፕ መውጣት ከባድ መሆኑን፣ ቢወጡም በፖሊስ አጀብና በዓይነቁራኛ ተጠብቀው መሆኑን ነገሩኝ። ስጋቱ በተቃዋሚዎች እንዳይጠለፉ እንጂ እንዳይጠፉ አይደለም። እነሱን ጠልፎ ማስረከብ ገንዘብም እንደሚያስገኝ ይገምታሉ። ፈንጂ ወይም መሳሪያ ተጠቅመው ካምፑን እንዳያጠቁም ስጋት አለ። በምጽዋት መኖር እንዳንገፈገፋቸው ነገሩኝ። ደብረብርሃን አቅም ላለው የጉልበት ሥራም ሰርቶ ለመኖር ህዝቡ ካለው ተቀባይነት አንፃር የተሻለ መሆኑን ነገሩኝ። ሕክምናቸውን በዘመናዊም በባህላዊም እየተከታተሉ ነው።
ከሰዓት
ድንገተኛ ለውጥ
አዛውንቱ ከወለጋ ተመልሰው ደብረብርሃን ለዓይን ቀዶ ሕክምና ቀጠሯቸው መጡ። ሐኪሙ ተቀይሮ ኖሮ የዕለቱ ተረኛ ሐኪም ቀዶ ሕክምና አይሰራም ብሎ መድሐኒት አዘዘላቸው። ለሳምንት ወስደው እንየው አላቸው። በዚያም ሲበሳጩ የሰሙ ሌላ ታካሚ የሕመሙን ሁኔታ አይተው ወደ ባህል ሐኪም ላኩን። በጥጥ ብዙ ጉድፍ ወጣላቸው። የሚቆረቁረኝ ተሻለኝ አሉ። የባህል ሐኪሟ መድሐኒቱን ተዉት አሏቸው። ውጤቱን እናያለን።