2017 ሴፕቴምበር 2, ቅዳሜ

ደጋ…ግሞ ማዳመጥ  የታከተው መምህር




ከትምህርት ተመልሶ ተገናኘን፡፡ ከኔ ጋር ያወራነው በመሃላችን ብዙም የተለመደ ወሬ አይደለም፡፡ ስለ ፍጥነት ንባብ ነበር፡፡ በዚህ ጉደይ ላይ ከዚህ ውይይታችን በኋላ አስፈላጊውን ዶሴ በአድራሻው ልኬለት አመስግኖኛል፡፡

‹‹የጥበብ ሰዎች ሳይቀሩ በቴሌቪዥን ላይ ተመሳሳይ የዱሮ ወሬ ማውራት ልማዳቸው ነው፤ ምክንያቱም ሌላውም ጓደኛቸው ሲደጋግመው ስለሚውልና ስለማይሳታቸው ነው›› አለኝ፡፡ የወሬ መደጋገም አሰልችቶታል፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን እስከ መስሪያቤት፣ ከቤተሰብ እስከ ጓደኛ ሁሉም አዲስ ነገር አልባ ሆነውበታል፡፡

‹‹ጓደኛህን አግኝተኸው ባለፈው ያወራህን ተመሳሳይ ወሬ ያወራሃል፡፡ ‹እሱን እኮ ባለፈው ነግረኸኛል››› ስትለው አይሰማህም፡፡ ‹‹ለምንድነው ግን ሰዎች አዲስ ወሬ ያጡት›› ሲል አማረረ፡፡  

ይህን የወሬ መጠንዛት የታዘቡ ታዝበዋል፤ የተማረሩ ተማረውበታል፤ የሰለቻቸውና ድፍረቱን ያገኙ አልፈው ተናግረዋል፡፡ አዲስ ወሬ ከየት ሊገኝ እንደሚችል ነጋሪና መካሪ ያሻቸው ይሆን? ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ደጋግመወው ቢያወሩ የማሰለቹ አሉ፡፡ የመንግስቱ ለማን ፍጡር አለቃ መክፈልትን አስታወስኩ በግሌ፡፡

‹‹ስለችግርህ ማውራት ስትችል ለምን ከዱሮ ጋር ትንገታገታለህ፤ ከራስህ ጋር ስታወራ ነው መፍትሔ የሚመጣው፡፡ ለራሳችን የማሰቢያ ጊዜ ሲኖረን ነው መፍትሔና ለውጥን የምናመጣቸው፡፡ እስኪ የቅድመ ምረቃ ትውስታ ማውራት ለኛ ምን ይጠቅመናል?››

‹‹ወሬኛ ሰው ደግሞ ያለ ምንም ዳራ ያወራሃል፡፡ ሲፈልገው ቤቱ ሊበላኝ ነው ይልሃል፡፡ አሁን ነገሩ ያው ወጣቱንም ያየህ እንደሆነ Noshall ሆኗል፡፡ – without social life የሚኖር ነው - በቅርቡ የሳማሁት ጥሩ አገላለጽ ነው፡፡ ምናልባት ያለ የሌለ ወሬ ማዳመጥ ሲሰለቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለችግርህ ለበርካታ ቀናት ቤት ዘግተህ ተቀምጠህ መነጋገር ትችላለህ፡፡ ቤት ካልዘጋህ እኮ ማንበብ አትችልም፡፡ ገለባ ነው የምትሆነው፡፡ ዘፈኖች ራሱ ይገርሙኛል፡፡ ጨፍር ተዝናና ይሉሃል፡፡ አዲስ ነገር አይታይባቸውም፡፡››

ወንድሜ ጽናቱን ይስጥህ፤ አዲስ ወሬም አይንሳህ፤ የድርሻህን ለመወጣትም ሞክር እላለሁ!

2017 ኦገስት 21, ሰኞ

‹‹ይሄ የማነው ቤት የደራ የኮራ የምኒልክ ነዋ የዚያ የቀብራራ!››



በመዘምር ግርማ የተጻፈ የጉዞ ትውስታ

ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፡፡

14.12.2009 ዓ.ም.



ወጧ የጣፈጠላት ባልቴት መስለናል



ብዙዎቻችን ይህችን ቀን ስንናፍቅ የነበርን ሰዎች ወጣችን ጣፍጧል፡፡ ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ በራስ አበበ ቤተመጻሕፍት ተመዝግበው በዕለተ-እሁድ 14.12.2009 ወደ እንቁላል ኮሶ፣ አንጎላ፣ ጉዞ ያደረጉ 75 ወዳጆቻችንን የፈካ ፊት ስናይ ነው የዋልነው፡፡ በስፍራው የተገኘው ህዝብ የነበረው የአብሮነት ስሜት፣ የአገርና የንጉሥ ፍቅር ብርቱ ስሜትን የሚያጭር ነው፡፡




የአንጎለላ አድባር መርቃችኋለች፡፡



ሰውኛ ፕሮዳክሽን፣ መገዘዝ መልቲሚዲያ፣ ደብረብርሃን ዩነቨርሲቲ፣ የባሶ ወረዳ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ለዚህ ክብረ-በዓል መስመር የተጉ ወገኖቻችን ባይኖሩ አኛም ለዚህች የደስታ ብስራት ባልበቃን ነበር፡፡ እናመሰግናለን - ባያሌው፡፡ የወጣችሁና የወረዳችሁትን የምታውቁት እናንተ ስለሆናችሁ እኛ ድካማችሁ መሉ በሙሉ አይገባንም፡፡ 



የዝግጅቱ ሂደት



አንዳንድ ወገኖቻችን ከአዲስ አበባ በፌስቡክ የተለቀቀውን ቅስቀሳ አንብበውና አዘጋጆቹን አነጋግረው በአጤ ምኒልክ፣ በእቴጌ ጣይቱና በፊታውራሪ ገበየሁ ልደት አከባበር ላይ እንድንሳተፍ ይወተውቱን ገቡ፡፡ እንኳንም አነቁን፡፡ አንዱ ዳምጠው አድማሱ ነበር፡፡ ወጣቱ የሒሳብ አያያዝ ምሩቅ ሚኪያስ ካሣዬ በአንጻሩ ‹‹እኛ በያመቱ እዚህ ደብረብርሃን ስለምናከብር ለምንድነው ሌሎች ባዘጋጁት ዝግጅት ላይ የምንሳተፈው?›› የሚል ተቃውሞ አንስቶ ነበር፡፡ ሚኪዬ ምን መሰለህ? ለብቻህ የምታደርገውና ተሰባስበህ የምታደርገው ነገር ውጤቱ ይለያያል፡፡ ያንንም ዛሬ የታዘብክና የረካህ ይመስለኛል፡፡

ይህ ምክክር የተካሄደው ከዝግጅቱ አንድ ሳምንት በፊት በነበረው ሐሙስ ነበር፡፡ ለነገሩ የፌስቡክ ማስታወቂያውን እኔም ሳላየው ቀርቼ አይደለም፡፡ ያዘናጋኝ ነገር ቢኖር የቤተመጻሕፍቱ ባልደረቦች በጉዞ እየተቀዛቀዝን መሄዳችን ነበር፡፡ ባላፈው ወደ ግድብ እንደናደርግ በተቀጣጠርነው ጉዞ ላይ ስምንት ሰው ብቻ መገኘቱ ያልተጠበቀ ነገር ስለነበረ አሁንም ጉዞ ጠርተን የሚቀረው ይበዛል ብዬ ነበር፡፡



ዘንድሮም እንዳምናው

ምን አዚም እንደያዘን አላወቅም፤ ባለፈው ዓመት ከዘንድሮው የላቀ ዝግጅት አድርገን ዘንድሮ ግን ተቀዛቅዘናል፡፡ የጓደኞቻችን ውትወታ ባይኖር በዓሉ ተቀዛቅዞ ባለፈ ነበር፡፡  ባለፈው ዓመት እኮ ከዩኒቨርሲቲ የአዳማ ልጅ የክረምት የታሪክ ተማሪ ጋብዘን ነበር በደማቅ ውይይት ያከበርነው፡፡ ቦታ ጠቦ መሬት ላይ ተቀምጠን አታስታውሱም? ባለፈው ሐሙስ በነበረን ሳምንታዊ የውይይትና የስነ-ጽሁፍ ምሽት የሦስቱን ጀግኖና የራስ አበበ አረጋይን ልደት አክብረናል፡፡ ራስ አበበን ግን አትርሱብን!

ባለፈው አርብ ዕለትም በጌትቫ ሆቴል የልደት አከባበሩ በደብረብርሃን ወጣቶች ተካሂዶ ነበር፡፡ ወድንኳኗ ውስጥ ያደረግነው ውይይት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አሁን ዶክተር አዲሱ ይህን በፌስቡክ ስላስታወስከኝ አመሰግናለሁ፡፡




 የዛሬ ውሏችንን እነሆ!



ከማለዳው 12፡00 ከእንቅልፌ ተነስቼና ባጭር ጊዜ ዝግጅቴን ጨራርሼ ወደ ቤተመጻሕፍቱ በማቅናት ቤቱን አሳምር ጀመር፡፡ ወንበሮችን በሙሉ ወደ ውጪ አውጥቼ አስቀመጥኩ፡፡ መጻሕፍቱን አውደ-ርዕይ በመሰለ መልኩ ደርድሬ በቤቱ ላይ ውበት ዘራሁበት፡፡

ልክ እንደትናንተቱ ስልኬ አሁንም አሁንም ይጮሃል፡፡ እኔም መልስ እሰጣለሁ፡፡ እየረፋፈደ ሲሄድ ተጓዦች ይሰባሰቡ ጀመር፡፡ የቲሸርት ያለመኖር ችግር ሁሉንም ያስቆጨ ስለሆነ ለብዙዎቹ ቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ ከአዲስ አበባ ይመጣል የተባለው ሳይመጣ ስለቀረ ነው የኛ መቀዛቀዝ እንጂ እዚሁ ማሰራት በተቻለ ነበር፡፡ እድሜ ለኢሳይያስ ፍቅሬ - 30 ቲሸርት አሰርቶ ለተወሰኑት ሰዎች አምጥቶልናል! ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ በመቶዎች የሚቆጠር ቲሸርት ሊሸጥ እንደሚችል እተማመናለሁ፡፡

ተጓዦች በአቅራቢያችን ባሉ ካፌዎችና በቤተመጻሕፍቱ በበረንዳ ቡናና ሻይ ሲጠጡ፣ ሁለቱ መኪናዎቻችን መጥተው ቆሙ፡፡ ደረጀ ጌታቸው እነዚህን መኪኖች በጥሩ ዋጋ ስላመጣልን አመሰግናለሁ፡፡ ክፍያው በሰላሳ ብር በነፍስወከፍ ስለሆነ ለዳቦና ለለስላሳ ገንዘብ ተርፎን ለስላሳ ለሌሎችም ተሳታፊዎች ለመጋበዝ ተችሎናል፡፡ ይህን ግብዣ ላስተባበረችው ለጌጤ ፈለገ ምስጋና ባያሌው!

ከጠዋቱ 1፡30 እንነሳለን ብዬ የቀጠርኳቸው ሰዎች ተሟልተው (ግማሹ በስልክ ጉትጎታ) ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ ተነሳን፡፡ ጉዞ ወደ አንጎለላ፡፡ ስፍራው ስምንት ኪሎሜትር ስለሚርቅ የደረስንው በአንድ አፍታ ነበር፡፡ የክረምት ልምላሜው የሚያስደስት መስክና ማሳ ይታየናል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ኩሳዬ ትምህርት ቤት፣ ጅሩ፣ ወደ ራስ አበበ አገር ለወላጆች በዓል ስሄድ እንደጻፍኩት ይህን መስክ እነራስ አበበ አረጋይ ያባረሩት ፈረንጅ እንዳያይብን ጸልዩ ብያችሁ ነበር፡፡ ጸሎታችሁ ከደመና በታች ቀርቶ ይሁን ጨርሶ ሳትጸልዩ ረስታችሁት ይህ መንገድ ግራና ቀኙ ዓይን እየበዛበት ነው፡፡ ዓይን ብቻ አይደለም፣ ገመድም ተመትሮበታል!



‹‹ይሄ የማነው ቤት የደራ የኮራ

የምኒልክ ነዋ የዚያ የቀብራራ!››



እንዲህ እያልን በሆያ ሆዬ ወደ አንጎለላው ክሊኒክ ግቢ ስንቃረብ የነበረውን ትዕይንትና የስለት ስምረት ስሜት የነበራችሁ ታስታውሳላችሁ! በቅርቡ በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትብብርና ጥረት እንደገና ስራ እንዲጀምር የተደረገው ይህ ክሊኒክ ዛሬ አምሯል፡፡ በባንዲራ አሸብርቋል፡፡ በብርቅዬ አርቲስቶቻችን፣ በምሁራን፣ በአካባቢው ማህበረሰብ አባላት፣ በመንግሥት ተወካዮችና በበርካታ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ምስል ያለባቸውን ቢጫ ቲሸርቶች የለበሱ ሰዎች በግቢው ውስጥ ይታያሉ፡፡ ፎቶ መነሳት፣ ስራ ማስተባበር፣ በዓል ማክበር ይዘዋል፡፡ በወርቀዘቦ ጌጥ የተሰራ ጥቁር ቲሸርት የለበሱም አሉ፡፡ አጤ ምኒልክ እንደሚያደርጉት ሁሉ በነጭ ጨርቅ ራሳቸውን ያሰሩ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ባዶ እግሩንም የሆነ አይቻለሁ፡፡ የኛ የደብረብርሃኑ ቡድንም ቀይ ቲሸርት ለብሶ መቀላቀሉ የበለጠ ድምቀትን አመጣ፡፡ ሁሉም በደስታ ስሜት ፎቶ ይነሳል፣ ይጨፍራል፣ ይዘምራል፡፡ ዝግጅቱ ጀመረ፡፡

ለበዓሉ ከዞኑ፣ ከወረዳውና ከዩኒቨርሲቲው የተጋበዙት እንግዶች አጤ ምኒልክን በብዙ የአሀኑን መንግሥት በመጠኑ አሞገሱ፡፡

አጤ ሚኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱና ፊታውራሪ ገበየሁ ልደታቸው ሲከበር የታወሱ ግጥሞች አሉ፡-

‹‹ባቡሩም ሰገረ ስልኩም ተናገረ

ምኒልክ መልዓክ ነው ልቤ ጠረጠረ››

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ
ትዝ ይሉኛል፡፡



ሽልማትና ችግኝ ተከላ

ለበዓሉ ስምረት አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበረከተ፡፡ በፈረስ ጉግስ ውድድር ላሸነፉ ሰዎችም ሽልማት ቀረበ፡፡ ይህም ሽልማት የዳቦና የፎቶ ነበር፡፡ ፎቶዎቹ በጥሩ ሁኔታ የተሰሩ የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ ዕውቅናው ለወደፊትም የሚያበረታታ በመሆኑ ያስደስታል፡፡

ከህብረተሰቡና ከተሳታፊው የተመረጡ 12 ሰዎች የንጉሡ እትብት በተቀበረበት ስፍራ የኮሶ ችግኝ ተከሉ፡፡ ቦታው እንቁላል ኮሶም አይደል! ቦታውን አሳምረው ያሳጠሩትን የእምዬን ወዳጆች ማመስገን ይገባል፡፡




የመጨረሻው መጀመሪያ

ዝግጅቱ ሊያላልቅ ሲል ዝናቡን አመጣዋ! አብዛኞቻችን ከድንኳን፣ ሌሎቻችን ደግሞ ከክሊኒኩ በረንዳ ተጠለልን፡፡ በዝግጅቱ ላይ አንድ ዘፈን እንዲያቀርብልን የፈለግነው የኛ ቡድን አባል መምህር ታደለ አንባዬ እንዲያቀርብ ብጠይቅም ጊዜ የለንም አሉ እንጂ ጣዕመ-ዜማም እንሰማ ነበር፡፡ እጅግ የተደሰትንበት ይህ ዝግጅት አልቆ ወደየመኪናዎቻችን አቅንተን ያለንን ዳቦና ለስላሳ ቀማምሰን ጉዞ ወደ ደብረብርሃን ሆነ፡፡ ግማሾቹ ጎብኝዎች ወደ አንጎለላ ኪዳነምህረት ሄደው የንጉሥ ሣህለሥላሴን ቤተመንግስት ፍርስራሽና የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም ሳይጎበኙ አልቀሩም፡፡ እኛም በመጪው ዓመት ማየት ይኖርብናል፡፡ ምንም እንኳን እኔና የተወሰንነው ጓደኞቼ በየካቲት የዓድዋን በዓል በማሰብ በየዓመቱ በምናደርገው ጉዞ እየጎበኘነው ቢሆንም፡፡ ሌሊት በመነሳቴ ስለደከመኝ የጥናትና ምርምር መድረኩ ላይ በሕይወት ሆቴል ባልገኝም አስተማሪ መድረክ እንደነበር የተገኙ ወዳጆቼ ነግረውኝ ተደስቻለሁ፡፡

ከዚህ ዝግጅት ብዙ ትምህርት ቀስመናል፡፡ ለወደፊቱም የምናደርጋቸውን ጉዞዎች (የአንኮበሩን የየካቲት 23ቱን ጨምሮ) እንደዚህ ማቀናጀት ይኖርብናል፡፡ ለዝግጅቱ ብዙ ወጪ ያወጡት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የገንዘብ ድጋፍ ሳናደርግላቸው ይህን ዝግጅት ስላደረጉልን ብዙ መስዋዕትነት ሳይከፍሉ አልቀሩም፡፡ ለወደፊቱም ደብረብርሃንም የራሷን ብትወጣና ከስፖንሰር የጸዳ የበዓል አከባበር ብናደርግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ራስን የመቻልን ትምህርት ምኒልክ ሳያስተምሩንም አልቀሩ!



ማሳሰቢያ

አጤ ምኒልክን የማይወዱ ሰዎች አለመውደዳቸውን በደንብ እንዲመረምሩት አሳስባለሁ፡፡ እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ ይህንን ጽሑፍ በአሉታዊ አስተያየት እንዲያበላሹብኝ አልፈልግም፡፡ ቢጽፉም የማይሆን ምላሽና ስድብ አትመልሱላቸው፡፡ አሉታዊ ነገር ሲበዛ ዓላማችንን ስለምንስት፡፡ ከፌስቡክ ወዳጅታቸውም ባትሰርዟቸው - የሐሳብ ብዝሃነት ስለማይከፋ፡፡   

ስለጉዞው የዘነጋሁትን አናንተ ሙሉልኝ፤ ፎቶዎቻችሁንም በአስተያየት መስጫው ላይ አስገቡልኝ፡፡    

2017 ኦገስት 14, ሰኞ

ጥርሠ-ፍንጭቱ ከበርቴ ይመክራችኋል


(ማህበራዊ ሚዲያችን ለምን የምንፈልገውን ሰው ብቻ ማሰባሰቢያ ሆነ?) እና ሌሎችም
የጽሑፉ ርዝመት 1496 ቃላት፤ የሚፈጀው ጊዜ በአማካይ 10 ደቂቃ

ስትራይቭ ማሲይዋ  ይባላል፡፡ ዝምባብዌያዊ ቢሊየነር፣ ሥራ ፈጣሪና በጎ አድራጊ ነው፡፡ ዕድሜው 57 ዓመት፡፡ በቅርቡ ወደ ዳሬ ሠላም ብቅ ብሎ ከወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ጋር የንግግርና የምክር ቆይታ አድርጓል፡፡ እኔም እንግሊዝኛ ለምትረዱ ቪዲዮውን አጋራችኋለሁ፡፡ በትናንትናው ማለትም ሐምሌ 7፣ 2009 ምሽት ከሌሊቱ 8፡20 ድረስ ያስቆየኝ ስራ የዚህን ሰው የመድረክ ቆይታ ማድመጥና ማስታወሻ መውሰድ ነበር - ሰባት ገጽ ማስታወሻ በደብተሬ ወስጃለሁ፡፡ ለኔ በጣም ያስደሰተኝና ፍላጎቴ የተነቃቃበት ይህ ትምህርት እናንተን እንዴት እንደሚያደርጋችሁ አላውቅም፡፡ በስራ ፈጠራ፣ በቢዝነስ፣ በበጎ አድራጎት ምን ደረጃ ላይ እንዳላችሁ የምታውቁት እናንተ ስለሆናችሁ፤ በትምህርቱ ላይ የሚኖራችሁን ፍላጎት እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡
ጥቁር ሀብታም ሁሉ ናይጀሪያዊ ነው ብዬ ላመንኩት ለኔ ስትራይቭ ናይጀሪያዊ ነበር፡፡ ዛሬ ይህን ጽሑፍ ለማዳበር ስል የቃኘሁት አንድ ድረ-ገጽ ግን ግምቴ መሳሳቱን አስረዳኝ፡፡ ይሁን እንግዲህ፣ ማነው ናይጀሪያ ብቻ ትበልጽግ ያለው? አላሙዲን፣ ዳንጎቴ፣ ኖህ ሰማራ፣ ጃክ ማ፣ ቢል ጌትስ፣ ዋረን ባፌት፣ ኦፕራ፣ ትራምፕ እያልኩ ቢሊየነሮችን እግር በእግር እየተከታተልኩ ያለሁት ለምን ይመስላችኋል? መልሱን ከንባቡ በኋላ ልትገምቱት ትችላላችሁ፡፡
በዝምባብዌ፣ በዛምቢያና ስኮትላንድ የተማረው ይህ ሰው እናቱን የስኬቱ አርአያ ያደርጋቸዋል፡፡ ‹‹በሌሊት እየተነሳች የምትሰራበት ትጋቷ አርአያ ሆኖኛል›› ይላችኋል፡፡ የእርስዎስ እናት እንዴት ነበረች? እኔ ምናልባት አያቴ ልትሆን ትችላለች ትጉህ፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በፊት እነሱ ቤት አይተኛም፡፡ ‹‹የርቀት ብትማሪ እኮ ዶክትሬት ትይዢ ነበር›› እላታለሁ ለአያቴ፡፡
በዝምባብዌ ይሰራበት የነበረው የቴሌኮም ድርጅት ስራ ወጣቱን የ26 ዓመት መሐንዲስ ሊያረካው አልቻለም፡፡ አንድ ሰው በአማካይ ስልክ ሊገባለት የሚችለው ካመለከተ ከ14 ዓመታት በኋላ መሆኑ ስላበሳጨው ስራ ለቀቀ፡፡ ለዚህም የስልክ ችግር መፍትሔ ይፈልግለት ገባ፡፡ ያም እንዴት እንጀራ እንደፈጠረለት ታያላችሁ፡፡
እኔኑ ራሴን ‹‹አሁን ባለሁበት ሁኔታ በትምህርት፣ በጊዜ አጠቃቀም፣ በሕይወት ዓላማ ልረካ ያልቻልኩት ለምንድነው?›› አስባለኝ፡፡ ‹‹አለመርካት የለውጥ መነሻ ነው›› ይላችኋል፡፡
ከመድረክ ላይ ለምትጠይቀው የታንዛኒያ ተወላጅ ምላሽ በመስጠት መድረኩን የተቆጣጠረው ማሲይዋ ትዊተር የለውም፡፡ ፌስቡኩ ግን በዛሬዋ ዕለት 2 473 163 አባላት አሉት፡፡ ‹‹ትዊተር ከፍቼ እንድትከተሉኝ ሳይሆን የጋራ መድረክ እንዲኖረንና እንድንነጋገር እንዲሁም እንድንሰራ ነው የምፈልገው›› ይላል፡፡ ፌስቡክ በማሳተፍ መጠኑ ከፍተኛ ያለው ይህ ገጹ በርካታ የስራ ፈጠራ ምክሮችና ውይይቶች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ እሱ የሚለጥፋቸው ብቻ ሳይሆኑ እሱ በለጠፋቸው ምክሮችና ጽሑፎች ላይ የሚንሸራሸሩት መልሶች፣ ውይይቶችና ክርክሮች በአባላቱ ተሳትፎ ከማናቸውም የፌስቡክ ተጠቃሚ በላይ ያደርገዋል፡፡ ፌስቡክንና ስራውን እንዴት እንዳመጣጠነ ሲናገር ከአንድ ዩጋንዳዊ የዕድሜ ባለጸጋ ያገኘውን ምክር እንደ ሕይወት መርህ መጠቀሙን ያነሣል፡፡ ይህም ‹‹ለአስፈላጊዎች ነገሮች ጊዜ ፈልጉ፤ በጣም አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ግን ጊዜ ውለዱ›› ይላል፡፡ ለእናንተ ስል ጊዜ እወልዳለሁ፤ ጊዜ አድኜ አመጣለሁ›› ይላቸዋል፡፡
ወገኖቼ፣ ለኔና ለእናንተ አስፈላጊውና ጊዜ ልንወልድለት የሚገባው ገር ምንድነው?  ለእርሱ እኛን ማስተማርና ማሰልጠን ግድ የሚለው ነገር ሆነ - የደረሰበት የአስተሳሰብ ደረጃ! ድፍን አፍሪካን ያስተምራል፡፡
‹‹እናንተ ባለሐብት ለመሆን ሳይሆን የአፍሪካን ችግሮች ለመቅረፍ ተነሱ እንጂ ገንዘቡ ከዚያ ለራሱ ይጨነቃል›› ይላችኋል፡፡ ‹‹በርካታ ፍላጎቶችና ችግሮች ያሉባት አፍሪካ ትፈልጋችኋለች፡፡››
የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ድርጅት የኢኮኔት ዋየርለስ መስራችና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ይህ ሰው አፍሪካ ወደ ኋላ የቀረችባቸው ነገሮች ያሳስቡታል፡፡ ይህ የታላላቆቹ ስራ ፈጣሪዎች የታናናሾቹን ማሰልጠንና መደገፍ ጉዳይ በአሜሪካ እጅግ የታወቀና የተሰራበት ቢሆንም እኛ ጋ ገና ነው፡፡ ‹‹እስከዛሬ እንዲህ ስላልተደጋገፍን ቀኑ ዛሬ ነው›› ይላል፡፡ መቼ ማለት ብቻ! - በተግባርም ዘምቷል፡፡
‹‹መጽሐፍ ከምጽፍ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ ብጠቀም እናንተን የተሻለ እንደማነቃቃ ስላወቅሁ ነው እዚያ የምንገናኘው›› ለሚላቸው ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን የሚመልሰውና ጽሑፎቹን የሚጽፈው ራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ብፈልግ ግማሽ ደርዘን ወጣት መቅጠር እችል ነበር›› ሲል ሌላውን የማያሰራ አቅጣጫ ያሳየናል፡፡
‹‹እናንት የአፍሪካ አሊባባ፣ ጉግል … መስራች የምትሆኑ ወጣቶች ትልቅ ድርጅት ስትመሰርቱ ግን ስሙን አፍሪካዊ አድርጉት - ልክ አንኔው ክዌሲ ቴሌቪዥን፡፡ የአስተሳሰብ አድማሳችሁን አስተካክሉ፡፡ የተለያዩ ዳራዎች ያሏቸው 54 አገሮቻችን የናንተን የተለየ የአስተሳሰብ አድማስና አተያይ ይሻሉ፡፡››
ወጣቶች ወደፊት በምን ዘርፍ ይሰማሩ ትላለህ?
‹‹እኔ በዚህ ስሩ በዚህ አትስሩ አልልም፡፡ የማህበረሰባችን ችግሮች ምንድናቸው የሚለውን አጥንታችሁ ተንቀሳቀሱ ነው የምላችሁ፡፡ የለውጥ ዕድሎች ያሉት ችግሮቹ ላይ ነው፡፡ ዕውቀቴና ክህሎቴ የትኛውን ችግር ለመፍታት ይጠቅማል የሚለውን ግን አትርሱ፡፡ ከዚህ በስተቀረ ሁሉም ዘርፍ የየራሱ ጥንካሬ አለው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ትልቅ ገንዘብ አለ - ግብርና፣ አይቲ፣ ሱፐርማርኬት …. ››
አሞራ በማዕበል የሚለው ለረጅም ጊዜ በፌስቡክህ ላይ በተከታታይ በተስተናገደው ጽሑፍ ላይ እስኪ ትንሽ ነገር በል፡፡
 ‹‹አሞራ እኮ ማዕበል ፈርታ ዛፍ ላይ አትወሸቅም፡፡ በማዕበሉ አልፋ ታድናለች፡፡ ከማዕበሉ ምን ተማርኩ ብለሽ ማሰብ አለብሽ፡፡ አፍሪካም ወደ ማዕበሉ እየመጣች ነው፡፡ አስደማሚ ለውጦች፣ ማዕበሎች፣ እርማቶች ይጠብቁናል፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንታገላለን እንጂ ሁኔታውን ራሱን አንታገለውም፡፡ ታላላቆቹ የምዕራቡ ዓለም ድርጅቶች የተመሰረቱት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መሆኑን ልብ በይ፡፡ ታላቅ ማዕበል!››
አሁን ስትራይቭ ማሲዋ ወደኔ የአስተሳሰብ ደረጃ መጣልኝ - መዘምር ነኝ -
ባለፈው ስለ ስራ ፈጠራ ንግግር ሳደርግ ስራ ፈጣሪ ለመሆን ‹አይሰሩ - ሰሪ› መሆን አለባችሁ›› ብዬ ነበር፡፡ ይቺን አሁን ደገመልኛ! ‹‹ስትጀምሩት እኮ ምን ነካው ይህ ሰው ነው የሚያስብላችሁ›› አለ፡፡ ተቺዎች መቼም አሉ፡፡ በለንደን ፓርላመንት አደባባይ ያሉት ሐውልቶች ሲሰሩ የተቹ ነበሩ፡፡ አሁን ሐውልቶቹ አሉ፤ ተቺዎቹ ግን የሉም፡፡ ጭብጨባ!!!
‹‹ግትር ሳልሆን ችግርን ተቋቋሚ ነኝ፡፡ ማንም ሳይሰራው ለኔ የሚታየኝ የስራ ዕድል አለ፡፡ ስራ ፈጣሪነት ደግሞ በዘር ማንዘር አይመጣም፤ በስልጠና ነው - አንቺው ራስሽ ራስሽን አሰለጥኚው - እልሻለሁ፡፡ ፌስቡክ፣ ዋትዛፕ፣ የምንጠቀምበት ካፌ ሁሉ ስራ ፈጠራና ቢዝነስ መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡
‹‹ታዲያ ደግሞ ስራ ፈጠራ፣ ብር ማባዛት ብቻ አይደለም - ሰብዓዊ ነገርም አይጥፋ -
በስራ ፈጠራችን የህዝቡን ችግር መፍታት አንድ ነገር ሆኖ ማህበረሰባዊ ለውጥ አራማጆች የሚባሉም ሌሎች አሉ፡፡  ችግሮቻቸውን በለጋሾች ሳይሆን እዚሁ እኛው በኛው በቋሚነት እንድንፈታ የሚያስችሉ ጠንካራ ሰዎች፡፡    

ስትራይቭ ማሲይዋ፣ ዝምባብዌያዊው ቢሊየነር፣ ትንነት እንደተነጋገርነው መድረክ ላይ ቃለ ምልልስ እያደረገ ነበር፡፡ ጠያቂዋ የጠየቀችው ቀጣይ ጥያቄ፡-
ወጣቶች ሀብት እንጂ እዳ እንዳይሆኑ ባለድርሻ አካላት ምን ማድረገ ይጠበቅባቸዋል?
የዚች አህጉር ትልቁ ሀብት የህዝቧ አእምሮ እንጂ ሌላ ስላልሆነ እሱን የምንጠቀምበትን መንገድ መዘርጋት ግድ ይለናል፡፡ በአፍሪካ ደግሞ ከህዝቡ ስድሳ በመቶ ወጣት ስለሆነ ያንን ዕድል ተጠቅመን መለወጥ ይኖርብናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት እኮ በሳምንት 500 አፍሪካውያን አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ሜዲትራኒያን ባሕር ገብተው ይቀራሉ፡፡ ስራ ፍለጋ አውሮፓ የሚሄዱትን እነዚህን ወገኖቻችንን ወደ ታንዛኒያ ነው ማምጣት ያለብን፡፡ ስራ አንፍጠርና ከሰሐራ አናስቀራቸው፡፡ ይህ አጣዳፊ ችግር እያለብን መተኛት አይታሰብም፡፡ ለዚያ ነው እኔ እዚሀ የመጣሁት፡፡ ይህን ስናደርግ እንደ አባቶቻችን እንደነ ጁሊየስ ኒሬሬ ታላቅ ታሪክ መስራት እንችላለን፡፡
ሌላ ነገር ደግሞ በዚህ ዘመን አያንዳንዱ ከናንተ የሚወጣ ነገር ይመዘገባል፡፡ አስኪ ፌስቡኩንና ጉግሉን እዩት - ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንደሚባው፡፡ የምትናገሩትን ነገር መጠንቀቂያው አሁን ነው፡፡ ቀጣሪዎች እኮ ሲቀጥሯችሁ የማህበራዊ ሚዲያችሁን ንገሩን ይላሉ፡፡ ያኔ አሁን የማይሆን ነገር ከተናገራችሁ ችግር ይመጣል፡፡ የናንተ የዛሬ ቃል እንደ ንግድ ስማችሁ ነች ማለት ይቻላል፡፡
እኔ ጸሎተኛና መንፈሳዊ ሰው ነኝ፡፡ እስኪ እርስ በእርሳችን ትዕግስትና አክብሮት ይኑረን፡፡ በእጅጉ የተሳሰርን ነን፡፡ አንድ ሳልናገር የማላልፈው ነገር ግን አለ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያችን ለምን የምንፈልገውን ሰው ብቻ ማሰባሰቢያ ሆነ?
መሰሎቻችንን ስናሰባስብ ነው የምንውለው፡፡ እስኪ የሚቻቻል አህጉር ይኑረን፡፡ ለጎረቤታችን ስፍራ ይኑረን፡፡

የተሳታፊዎች ጥያቄዎችና የስትራይቭ መልሶች (ተመልሰውም አልተመለሱም ይሆናል)
የፈጠርከውን ስራ ለማቆም ስታስብና ካጠገብህ የፈጠርከውን ስራ የሚብቁ ሲኖሩ ምን ታደርጋለህ?
የፈጠርከውን ስራ ትተህ ተጨማሪ ገቢ ፍለጋ ወደ ሌላ ለመቀየር ስታስብ አንዴት ነው በነባሩ ላይ የምታተኩረው?
ማህበራዊ ሚዲያንና ስራን እንዴተ ታመጣጥናለህ?
80 በመቶ ድርጅት እንደተጀመረ ይጠፋል፤ ይህን መጥፋት እንዴት እንከላከል?

ጓደኞቻችሁና ወዳጆቻችሁ የፈጠራችሁትን የሚያበረታቱ ይሁኑ፡፡ የስራ ፈጣሪዎች መረብ ይኑረን፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢንተርኔት አለልን፡፡ እርስ በእርሰ ተደጋገፉ፡፡ ጎረቤታችሁ የሚሰራውን ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ ምናልባት ዳንጎቴ የሚሰራን ከማወቅ በበለጠ አጠገባችሁ ያለው ሊጠቅማችሁ ይችላል፡፡
80 በመቶ የተፈጠሩ ስራዎች በተፈጠሩ ሰሞን ይጠፋሉ፤ ቢሆንም እናንተ መስጋት የለባችሁም፡፡
ያለብን ችግር ስራፈጠራ ሳይሆን ያለንን ድርጅት ምን ያህል እናሳድገው የሚለው ነው፡፡
ሕይወትንና ስራን እንዴት ታመጣጥነዋለህ ለሚለው እጅግ ጊዜ የሚየስፈልገውን ነገር እለያለሁ፡፡ ጊዜዬን እቆጣጠራለሁ፡፡ ሌላው የቀጠራችሁት ሰው የሚሰራውን ለዩለት፡፡ ስራዎቹን ቅድሚያ የሚገባውንና የማይገባውን ለዩ፡፡

ከሌላ ድርጅት ጋር ጥምረት ማድረግ የማይኖርብንና የሚኖርብን መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
የአህጉሩን ትልልቁን ድርጅት የምትመሰርቱ ስለሆናችሁ ብቻችሁን አትሰሩትም፡፡ 90 በመቶ ውድቀትም ሆነ እድገትን ያመጣልና ግን በጥንቃቄ ይሁን፡፡ ከመግባታችሁ በፊት አጥኑ፡፡ ምን ዓይነት ክህሎት እንደሚያስፈልጋችሁ እወቁት፡፡
ሰራተኞቻችሁ ስራቸውን አነዲሰሩ ፍጹም ነጻነት ስጧቸው፡፡ የራሳችሁን ስርዓት ለድርጅቱ ንደፉ፤ በዚያም መሰረት ስሩ፡፡  የማያስፈልግበት ቦታ እየገባችሁ አታስቸግሩ፡፡ ባለሙያዎችን ከቀጠራችሁ በኋላ እምነት አትንፈጓቸው፡፡

ዝግጅቱ በኢንተርኔት በቀጥታ ይተላለፍ ስለነበር ከዚያም የመጡ ጥያቄዎች ነበሩ፡-
ከቻይኖች ጋር ስላለው ፉክክር ምን ትላለህ
እናሸንፋቸዋለን፡፡ እንድናሸንፋቸው ግን እንረዳቸው፡፡ እኔ ለአንድ ወር ቻይና ሄጄ ሳጠናቸው ነበር፡፡ የቻይናም የአሜሪካም አጋሮች አሉኝ፡፡ የእነዚህ ጥንካሬ ምንድነው ብሎ ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ ዘ ፕሮፊት የተባለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ገዝቼ በክዌሲ ቴሌቪዥን እያሰራጨሁ ነው፡፡ ስለስራፈጠራ የተሻለ ስለሚያስረዳንና እነሱን እንድናውቅ ስለሚያግዘን ነው፡፡ ሰዎች፣ ምርቶችና ሂደቶች የሚለውን ዝግጅት ብታዩት እንዴት ደስ ይለኛል መሰላችሁ፡፡ ሂደት የሚባለው አወቃቀራችንና የዘረጋነው ስርዓት ሲሆን የኛ ድርጅት ለምሳሌ በጥሩ ሁኔታ ስለተዋቀረ አንድ ሰራተኛ ሊሰርቅ ሲያስብ እንደርስበታለን፡፡

ቢዝነስና ህይወት እንዴት ይጣጣምልሃል?
የአጎቴ ልጅ ገንዘብ አበድረኝ ብሎ መጣብኝ ባለፈው፡፡ በየሚዲያው ሃብታም ነው ሲባል ሰምቶ ይሄ ሁሉ ድርጀት ስላለህ እባክህ ተቸገርልኝ አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ያ ገንዘብ የድርጅቱ እንጂ መች የኔ ነው አልኩት፡፡ ድርጅቱም እናንተም ህይወት ይኑራችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የምኖረው እንግሊዝ ነው፡፡ ልጆቼም የክፍል ጓደኞቻቸው ሃብታም ነው ሲሉ ስለሚሰሙ ይጠይቁኛል፡፡ እኔ ግን እንደ አባት እንጂ እንደ ስራ አስኪያጅ ልጆቼንም ሆነ ባለቤቴን መቅረብ ስለማልፈልግ ድንበር አበጅለታለሁ፡፡

ቅን ነህ፤  ለሌላው ታስባለህ፡፡ በዚህ አህጉር ያለውን ማሳደድ እንዴ አለፍከው?
የአፍሪካ ምርት የአህጉሩን ፍጆታ ሸፈኖ ጥራት የሌለውን የውጪ ምርት መተካት የሚችለው እንዴት ነው?
ወጣቱ ሊሰማራበት በሚፈልገው የስራ ዘርፍ ዕውቀቱና ክህሎቱ ላይኖረው ይችላልና ምን ትመክረናለህ?
አፍሪካ የደኸየችው በእምነተ ሰበብ ነው ይባላል፡፡ እንተ ታዲያ አማኝ ሆነህ እንዴት ልትለወጥ ቻልክ ?
ከተሳታፊዎች የተጠየቀ ነበር፡፡

ገበያ ስለማጠያየቅ፣ መረጃ ስለማፈላልግና ሃሳብህን ለኢንቬስተር ስለማካፈል ስለጻፍኩት ጉዳይ የጠየቃችሁት ልከ ነው፡፡ ጥንቃቄ ብዙ ትርፍ ያመጣልናል፡፡ ባለፈወ ሰባት መቶ ሚሊየን ዶላር አስይዤ የላኳቸው ሰራተኞቼ በዓለም ታሪክ በግል ባለሀብት የመጀመሪያውን ታላቅ ቦንድ ሊገዙ ነበር አካሄዳቸው፡፡ ስንትና ስንት ሰው ጠይቀው ላለመግዛት ወስነው መጡ፡፡ እንዲህ ያለ ጥንቃቄና ንቃት ያሻል፡፡
ጥራቱ የወረደ ምርትን አስመልክቶ በተጠየቀው ላይ ሁሉም አካላት፣ መንግስት፣ መያዶች፣ ተጠቃሚዎችም ሆኑ ስራፈጣሪዎች የተሳተፉበት አሰራር መኖር ይኖርበታል፡፡ አካባቢያችንን የጠበቀ፣ ቀጣይነቱን ያረጋገጠ፣ ደህንነታችንን የጠበቀ የፈጆታ እቃዎች ስርጭት ሊነረን ይገባል፡፡ ግንዛቤው ማደግና ስርዓቱ መዘረጋት አለበት፡፡ ታማኝነት ትልቁ ሀብት ነው፡፡ እሱን ወደ ስርዓታችሁ ካስገባችሁ ….
እምነት ከስኬት ጋር ይያያዛል ወይ ብለን ከጠየቅን ማናቸውንም እምነት አከብራለሁ፡፡ ብዙ የተለያየ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር እሰራለሁ፡፡ አሁን በምናገርበት ርዕስ ግን ሁላችንም የየራሳችን አተያዮች አሉን፡፡
ስራ ፈጣሪዎች ብዙ ነገር መስራት የለባቸውም፡፡ አንዱን አድምታችሁ ብትሰሩት ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
ለወጣቱ አቅጣጫ እንድናሳየው እንጂ ገንዘብ እንድንሰጠው አያስፈልግም፡፡
100 000 ልጆችን እረዳለሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 40 000ዎቹ ወላጅ አልባዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ስራ ፈጣሪ ማህበራዊ ሃላፊነተም አንዳለበት አይዘንጋ፡፡
አፍሪካን በኢኮኖሚ ነጻ እናውጣት፡፡
https://www.facebook.com/strivemasiyiwa/

2017 ኦገስት 7, ሰኞ

The Rude Shepherd



Based on a true story told by Gebriye Zenebe

Writer: Mezemir Girma

The sheep are busy grazing, whereas the cattle are sleeping beside the river above the historic Engidwasha Cave. Two siblings are in charge of all these animals.

“Kasa, it is your turn to bring those sheep back here before they go to that farm. You know the owner will punish us today too,” said Kelem.

“Hey! I will hit you! You go bring them!” he said waving his stick.

“No! No! You deny? It is your turn. I will not go another time. I will bring them only now and you will go for two rounds. If not, I will tell Baba in the evening.”

“You tell him and tomorrow I will hit you,” he threatened her.

Kelem went murmuring and brought the sheep.

Kasa threatens his sister as such. Sometimes he punishes her. He has also a habit of abusing other people and running towards his parents or elder brothers for protection. At this particular moment, along the road from the side of the church comes a passerby.  

Kasa told his sister that he will insult the man. His sister warned him that the man would punish him. Kasa insists that he will insult the passerby. He could not listen to the advice of his sister. He even threatened to hit him by a sling.

The man approached. Seeing that he wore a lowlanders’ gabi Kasa shouted, “Lowlander wanderer! Lowlander robber! You dirty lowlander!” However, the man kept walking as if he didn’t hear what that boy said. Kasa kept insulting the man until the man went down the road and disappeared from sight. Kasa laughed happily over his small victory.

“He heard what I said. He kept quiet only because he is afraid. Lowlanders are cowards,” said Kasa to his sister who looked indifferent.

As he was bragging, a man emerged from the side the previous man went to. This man hid his hands towards his back. As he approached the children, it was difficult to know he was the previous man since he held the gabi he wore in his armpits.

“Hello children. How are you? Can you show me where Asrat’s home is?” asked this man. Kasa told him that Asrat is his father and their home is nearby. “But, you know, my parents went to a distant farm. You cannot find them now,” said Kasa.

“Ok, good! Are you his children? Come, greet me children,” said the man.  The man approached Kasa and immediately held his two hands together by his left hand. It was a stick that this man held in his hands. The man started to flog Kasa, who kept crying. None of Kasa’s family members were around to save him.

As soon as the man left, Kasa began to throw stones towards the man using a sling. He narrowly missed the man two, three times. The man tried to avoid the flying stones and started to run towards the boy. He caught him and punished him for the second time. He pinched him sending his hands under his shorts. He slapped him with his hard hands.

 His sister, Kelem, observes what happens to Kasa and learns that insulting people causes such punishments. After the man punished Kasa and told him he would punish him more if he hears he insults other people, the man went down the road. This time Kasa didn’t insult the man. He just murmured “I would tell my father if he were here.” This single incidence made Kasa a boy who respects young and old people alike.

Moral: Abusing people causes troubles.


Camel Narratives




I grew up in a highland. The animals I knew as a child include cows, oxen, sheep, goats, donkeys, horses and mules. I saw a picture of camels only in books. Some people told me what a real camel looked like. Even there is a story of a certain highlander who went to a lowland area and was confused about this animal. Then, he is quoted to say, “Some people do not know that.” Then, they would ask him if it were the camel and he responded affirmatively. In this wise way he learnt the name of that new creature. Welela, a beautiful woman I knew as a high school student related what she knew about camels. “After they told me camels weep when they discover that they are going to be slaughtered, I stopped eating camel meat altogether,” says this woman. Her cousin Mrs. Merima told me how camels could be aggressive and attack people. A few years ago I came to discover that its back legs fold twice – what a unique creature! It was during my visit to the Lalibela rock-hewn churches that I saw camels. Yordanos, a guy who went with me said that this animal looked like a dried tree when seen from afar. The most recent time I saw a camel is last year. It was in Adama, Nazareth, that I had a closer look at this beast. In the culture I was brought up in, we neither eat camel meat nor drink its milk.

መጽሐፍ ስናነብ መምረጥ አለብን?






የመጸሐፍ ነገር ከተነሳ በዓለማችን እስካሁን ስንት መጻሕፍት ለህትመት በቅተዋል የሚለውን ጉዳይ እንይ፡፡ ጉግል ወደ መቶ ሠላሳ ሚሊዮን የሚጠጉ መጻሕፍት ለሕትመት እንደበቁ ያስረዳናል፡፡ ይህ የሆነው አንድ ደራሲ በአንድ ወቅት ያወጣውን መጽሐፍ አንድ ብለን ቆጥረን እንጂ ያሳተማቸውን የመጽሐፍ ቅጂዎች ብዛት ቆጥረን አይደለም፡፡ ብዛቱ ያስደምማል - በዓመት ዐሥር ሺህ ገዳማ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ይታተማሉ፡፡ ቁጥሩ ብዙ የተጋነነ እንዳይመስላችሁ - ግዕዝም በሕይወት ዘመኑ በዐሥር ሺዎች መጻሕፍት ታትመውበታል፡፡



‹‹ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ አፅንዑ›› ባይ ተከራካሪዎች በዕለተ እሁድ 16/11/2009 በደብረ ብረሃን ከተማ በተምሳሌት ኪነጥበባት የኪነማዕድ ዝግጅት ላይ ‹‹መጽሐፍ አንዴት ተደርጎ ይመረጣል?›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ‹‹አንብበን አተረጓጎማችንን ማስተካከል እንጂ እንዴት ይህን አላነብም ይህን አነባለሁ ብለን ማዕቀብ እንጥላለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መጥፎውን ካላነበብህ ጥሩውን ልታውቅ አትችልም፡፡ የተነሱት ሐሳቦች የማይመቹን ከሆነ መተው አንችልም ወይ?›› ብለው ሞግተዋል፡፡ ወንፊት እንደሚያጠለው ሁሉ ከተነበበ በኋላ የመምረጥ ችሎታ ጠቃሚነቱ ታይቷቸዋል፡፡ ባጠቃላይ ለነሱ መጽሐፉ ሳይሆን አወሳሰዳችንና አተገባበራችን ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከመራጮች ወገን በተደጋጋሚ የተነሣው ደራሲ ማን ይመስላችኋል? ‹‹የሱን መጻሕፍት ካነበባችሁ ጉዳችሁ ፈላ! እንደሱ ዓይነቶቹን ችላ በሏቸው! ያለዚያ ወዮላችሁ፤ ሰማይ ይደፋባችኋል!›› ትባላላችሁ፡፡ ኦሾ ጉድህ! ሰውን ለማስፈራራትና ከዚህ መጽሐፍ ታቀቡ ለማለት አይደለም የኛ ክርክር መሆን ያለበት፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው!



የንባባችን ዓላማ ምንድነው? ለመዝናናት፣ ለምርምር፣ ክህሎትን ለማዳበር፣ መረጃ ለማግኘት፣ አመለካከትን ለማነጽ፣ ለማጥናት? በዚህ ምክንያት ምርጫ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡



በኛ አገር የህብረተሰቡ አንባቢ ያለመሆንና የብዙ መጻሕፍት ያለመዳረስ ችግር አለ፡፡ ስለዚህ የህብረተሰቡ አካላት ምናልባት ወደ ንባብ ከመጡና መጻሕፍትን ማግኘት ከቻሉ የየምርጫቸውን መጻሕፍት ማንበብ አለባቸው፡፡ በባለፈው የንባብ ፌስቲቫላችን በተሰጠ የዓይን እማኝነት ከጀርመኖች፣ ከጣሊያኖችና ከሌሎችም ህዝቦች ጋር ሲነጻጸሩ አንባቢዎች በተባሉት አሜሪካውያን ዘንድ እንኳን ሁለት ሦስተኛው ህዝብ በዓመት አንድ መጽሐፍም አያነብም ተብሏል፡፡ በጣም አንበቢው ሰው አነበበ ቢባል እንኳን አምስት ሺሀ ገደማ መጸሕፍትን በሕይወት ዘመኑ ሊያነብ ይችላል ብለው አስተያየት የሰጡ ጸሐፊ አሉ፡፡ ዳቢት፣ ንቃይ፣ ታናሽ፣ ታላቅ፣ ወርች፣ ሽንጥ፣ ሳልገኝ፣ ጎድን (ሳብራዳ)፣ ፍርምባ፣ ጭቅና፣ ኪርኪሳ፣ ፍሌቶ፣ ደንደስ፣ ሻኛ፣ ሹልዳ፣ ነብሮ እያለ የሥጋ ዓይነቶችን ሲቆጥርና ሲበላ ወይም ሲመኝ ለሚውል ሰው እንደ አብዛኛው አሜሪካዊ ንባብ የሕይወቱ አካል ስላልሆነ የምንነጋገረው ከተወሰነው የህብረተሰብ አንባቢ ልምድና ተግባር በመነሳት ይሆናል፡፡ የንባብ ልማድ ከልጅነታችን ስላልዳበረ ነው ንባባችን ችግር የገጠመው፡፡ ምናልባት ኦባሳንጆ እንደሚሉት መልሰን መማር ባይኖርብንም ቀለል ባሉ ንባቦች ራሳችንን ብናላምድ መልካም ነው፡፡ ባህላችን ጭራሹኑስ ማንበብን ያበረታታል ወይ? ብላችሁ ብትጠይቁ ማንበብና መጠየቅ የሚበረታታ አይመስለኝም፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትን እንኳን የሚያነበው አማኝ ስንት ነው? ከሚነበቡት ነገሮች ተደራሽነት ባሻገር የመጻሕፍት እገዳ፣ የአንባቢያን የቋንቋ ችግር ወዘተ. የየራሳቸው ተጽዕኖ እንዳላቸው በማስረገጥ ወደ ቀጣዩ ምክንያት እንሂድ፡፡



አንባቢያን የንባብ የምቾት ቀጠና አላቸው፡፡ ዘውግ ይመርጣሉ፡፡ ልቦለድ፣ ስነልቦና፣ የሕይወት ታሪክ፣ ግጥም፣ ፍልስፍና፣ ሙያዊ ነገር፣ ወዘተ. - ከአንዱ ይሆናል ፍላጎታቸው፡፡ በተያያዘ ወሬ ማሰባጠር ጥሩ እንደሆነ ለአንባቢያን ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡



በውይይታችን ላይ ጨርሶ አላነብም ላሉ ግን መልዕክት አለኝ፡፡ ታሪክን የማያነብ ታሪክን የመድገም ዕድል አለው፡፡ ከትናንት ካልተማርን ዛሬንና ነገን በትክክል ለመኖር እንቸገራለን፡፡ ‹‹እንዴት እናንብብ›› የሚል መጽሐፍም ስለወጣ ብታነቡት አይከፋም፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ቃላት ቢይዝ ነው የሚያሳብደው›› ያልሽው ልጅ ንባብ ብዙ ጉልበት ስላለው አንብበሽ ድረሺበት፡፡ መቀመጥ መቻልም ማንበብን ለማዳበር ወሳኝ ነገር ነው፡፡ መጽሃፍ ሲወፍር ደግሞ ደስ ይበላችሁ እንጂ ለመቼ አልቆልኝ አትበሉ፡፡ ደራሲው ጉዳዩን በጥልቀት ዳሶታል ማለት ነው፡፡



አንብበን እንደ ወንፊት እናጣራ በሚለው ብዙም አልስማማም፡፡ የምናነበው ነገር ስብዕናችንን ስለሚቀርጽ የተገኘውን ማንበብ የለብንም፡፡ በተዘዋዋሪ ሳናውቀውም ቢሆን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ ስለሚያሳድርብን መምረጥ ይኖርብናል፡፡



የምንመርጠው በባህልና በቤተሰብ በተቀረጽንበት ስብዕና መሰረት ሊሆን ይችላል፡፡ መሆን ያለበት የሚመስለኝ ግን እንዲህ ነው፡፡ ራሳችን የራሳችንን የነገ ህይወት መቅረጽ ግድ ይለናል፡፡ እንስሶች ናቸው ከአካባቢየቸው ጋር ተስማምተው የሚኖሩት፡፡ ሰዎች ግን አካባቢያችንን መቅረጽና መለወጥ አለብን፡፡ የህይወታችንንም መንገድ ራሳችን መጥረግ አለብን፡፡ ከዚያ የሕይወት መርሆ ጋር የሚሄድ ንባብ ማንበብ ይኖርብናል፡፡ ለመምረጥ የሚያስገድደን እርሱ ነው፡፡



ካላነበብን ጥሩውን እንዴት እናውቀዋለን ለሚለው ሀሳብ የተወሰኑ ምክሮች አሉኝ፡፡ የምናምናቸውን ሰዎች ምክር መስማት፣ ዳሰሳዎችን ማንበብ፣ ደራሲውንና ይዘቱን ማገናዘብ ወዘተ ጠቃሚ መንገዶች ናቸው፡፡



ስለንባብ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችም አሉ፡፡ ጫት እየቃሙ ማንበብ ጥሩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ የተወሰኑ አንባቢዎች የተሳሳተ ነገር ያደርጋሉና እኛም እነዚያን ነገሮች ማድረግ አለብን ማለት አይደለም፡፡ አንብቦ ጨርቅን መጣልም ጥሩ አይደለም፡፡

ለመሰናበት ያህል ማንበብ የመርሳት በሽታን ይከላከላል፤ ለመረጃ ቅርብ ያደርጋል፤ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡




2017 ሜይ 24, ረቡዕ

የትምህርት ቤቶቹ የስፖርት ድግስ፤ የጉዞ ማስታወሻ፤ መዘምር ግርማ እንደጠረቀው



በየሁለት ዓመቱ የኩሳዬ ትምህርት ቤትና የዳዎ ትምህርት ቤት የስፖርት ፌስቲቫል ስለሚካሄድ በ10/9/2009 ወደስፍራው ያቀናነው ሦስት የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ልዑካን ቡድን አባላት አረፋፍደን ነበር የደረስነው፡፡ መቼም በቅጥቅጥ መኪና ስንጓዝ ይቺ ቅጥቅጥ ለምን ከአገራችን እንደማትጠፋ ጠየቅ አደርጋለሁ፡፡ ለሰው መሳፈሪያ የሚሆን መኪና ይመጥነናል፡፡ መኪና መግዣ ገንዘብ እንደሆነ መውጣቱ አልቀረ፡፡ ስለሆነም የሚመለከተው ይመልከተው በማለት ወደሌላ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡ ለዚያውም አዳሩ ካፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ ሞልቶ ነው የሚሄደው፡፡  ኮርቶመጋላ ላይ ሳይቀር ሰው እንደሚጫን አገሬው መኪና ውስጥ ሲያወራ ነበር፡፡ ይህን መቼም አታኑም አይደል!በእጃቸው ጥብቅ አድርገው ብረቷን ይዘው በአየር ላይ እየተንሳፉ ሲሄዱ መኪናዋ እንደፎቅ ሆነች ማለት ነው፡፡ የጭነት መኪና እንዳሆነ ግንዛቤ አድርጉ፡፡
እነዋሪ ልንደርስ ስንል ተማሪዎች ይዞ ይጓዝ የነበረ መኪና መንገዱን ስቶ ዘንበል ማለቱን ስናይ እንኳንም ተሳፋሪዎቹ አልተጎዱ አልን፡፡
የእነዋሪ ጥብስ፣ ያው የጅሩ ሰንጋ ባጠቃላይ፣ ልዩ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡ በልተናልና ግድ ስለሚለን! ሸክላ ጥብስ ስለማልወድ ይህንን ግማሽ ኪሎ ስጋ አስጠብስልን አልኩት፡፡ ሦስት ነን፡፡ ‹‹በቃ ውስጥ ስለሚጠበስላችሁ 15 ብር ያስጨምራል - የዘይቱ ምናምን - መቶ ብራችሁ ቻለ›› አለን፡፡ እስኪ ይሁን እያልን ገባንና መጣች ያች የፈረደባት ጥብስ፡፡ እንጀራው በመረቅ ሟሙቶ እንጀራ አነሰን፡፡ ግማሽ እንጀራ ጨመሩ - ሦስት ብር አስጨመሩን፡፡ አንድ እንጀራ ስድስት ብር ነው ማለት ነው ብዬ ለነዋሪ አዘንኩ፡፡ የጅሩ ሆቴል ቆይታችን ይህን ይመስላል፡፡ በየመንገዱ የማውቃቸውን ሰዎ ሰላም እያልኩ ወደ መናኸሪያ!
ከእነዋሪ ኩሳዬ ቅርብ መንገድ ስለሆነ ክፍያውም ስድስት ብር ብቻ ነው፡፡ ኩሳዬ ደርሰን የኩሳዬን እምብርት (የራስ አበበን ግቢ) ጎበኘን፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ሐውልት ሊገነባ እንደታቀደ ሰምቻለሁ፡፡ ይበል ብያለሁ፡፡ ኩሳዬ ላይ ቦታ ስንጠይቀው ‹‹ካስፋልቱ ሄድ ብሎ›› ያለን ልጅ አስቆኛል፡፡ አስፋልት ጅሩን አያውቃትም - እነዋሪ ከተማው ውስጥ ግን ለህዝቡ ጤና ተብሎ ተሰርቷል መሰለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሰራር ተጀምሯል በወረዳ ከተሞች፡፡ ቁልቋል በከበባቸው ቤቶች የሚኖሩት ኩሳዬዎች የውሃ ነገር አልሞላላቸውም፡፡ ውሃ ላይ ቆመው ውሃ ስለሚጠማቸው በአህያ መጫን ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ መጀመሪያም የተጋነነ በጀት ክልሉ ያዘ፡፡ ያንንም ገንዘብ ያለአግባብ አባክነው ጥቅም ላይ ሳያውሉ ቀሩ፡፡ የተበላሸ ዕቃ ገጠሙለት፡፡ ችግሩን ለማስተካከል እየተሞከረ መሆኑን ያየሁት አምና ተሰቅሎ የነበረው የላሜራ ብይድ የውሃ ጋን ወርዶ ዘንድሮ የፕላስቲኩ ስለተሰቀለ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ ቅርብ እንደሆነ ያየነው ከጎበኘነው በኋላ ነው፡፡ በውሃው ልማትም ሆነ በቤተክርስቲያኑ ስራ ሁለት ሰዎች ተደጋግሞ ይመሰገናሉ - አንደኛው በትምህርት ሌላኛው በመከላከያ ዘርፍ ያሉ ናቸው፡፡ ማን ማን እንደሆኑ ገምቱ፡፡
ትምህርት ቤት ስንደርስ ፌስቲቫሉ ቀልጧል፡፡ ተማሪዎች ቡድናቸው ግብ ሲያስመዘግብ እየጨፈሩ ሜዳውን ይዞራሉ፡፡ ሳሲት ትምህርት ቤት ዓመታዊ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ሲካሄድ የነበረውን የልጅነት ትውስታ ቀሰቀሰብኝ፡፡ 1500 ሜትር የፈላ ትምህርት ቤት በተለይም የውቤ ነበር፡፡ ሳሲቶች ምን እንደምናሸንፍ ጠፋኝ፡፡ እምቧይባድ አጭር ርቀት ላይ ዳኜ የተባለ ተርብ ነበረው፡፡ የወረዳው ምርጦች  ሸዋሮቢት ሄደው በስፖርትም በጥያቄና መልስም ተወዳድረዋል፡፡ ተሳታፊ የነበራችሁ ትዝታችሁን ጻፉልን፡፡ ዳምጠው አድማሱን እንዲጽፍ ለማነሳሳት ነው፡፡ ተመለስን ወደ ጅሩ ፡-  አቶ አሳምነውን አግኝተነው በቤተመጻሕፍቱ አቀባበል አደረገልን፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሰራዊት ከሚለው መጽሐፍ ስለ ራስ አበበ አረጋይ አበበልን፡፡ ከዚያም ወደ መምህራን ቤት ሄደን ተጋበዝን፡፡ ስለትምህርትና ስለተለያዩ ነገሮች ተነሣ፡፡ መምህራንና ሰራተኞች ያላቸው ቤተሰባዊ ፍቅር ያስደስታል!
አቶ አሳምነው ባለፈው ዓመት የለገስኳቸውን መጻሕፍት ከርዕሰመምህሩ ቢሮ ተቀብሎ አምጥቶ መዝግቦ አሳየኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ለጥቅም ሳይውሉ መክረማቸው እሱንም አሳዝኖታል፡፡ የ580 ብር መጻሕፍት አግዘኸናል ያለኝ ግን አልተዋጠልኝም፡፡ እኔ ጊዜው ረዝሞ ካልረሳሁት በስተቀር የአንድ ሺህ ብር መጽሐፍ ነበር የሰጠኋቸው፡፡ ጠፍቶባቸው ይሆን እንዴ? አቶ አሳምነው መምህራንን ››እናንተ ሳይኮሎጂ አታነቡ፣ ምን አታነቡ፤ መመሪያውን አታውቁት፤ በቀደም ያ ልጅ መባረር የለበትም ብዬ መመሪያውን ያሳየኋችሁ እኔ ነኝ›› እያለ ይወቅሳቸዋል፡፡ ድፍረቱ ገረመኝ፡፡ እኛ መምህራን እናነባለን እንዴ? በፊት የሕብረተሰብ መምህር እንደነበረና አሁን በፍላጎቱ ወደ ቤተመጻሕፍት ሰራተኝነት እንደገባ ነገረኝ፡፡ ተግባቢና የዕውቀት ሰው ነው፡፡ መምህሩ በሳይክል ብር እያለ እነዋሪ ነው የሚውለው የሚል ነገርም አወጋኝ፡፡ ቤት ስራ ጀምረዋልና ከክፍለጊዜያቸው በኋላ ትምህርት ቤት ግቢ አይታዩም፡፡ ባለፈው ዓመት ለመደራጀት ገንዘብ ስላጡ ቦታውን ለገበሬ ሊሸጡት ነው ያለኝ ነገር ለማናቸውም ተስተካክሏል ማለት ነው፡፡ የአቶ አሳምነው ባለቤት የበቻሬ የልጅ ልጅ በመሆኗ ከራስ አበበ ትዛመዳለች - ራስ አበበ አረጋይ በቻሬ፡፡
ለውድድር ከመጣው ከዳው ትምህርት ቤት አንድ የደብረ ብርሃኑን የራስ አበበ ቤተመጻሕፍት የሚያውቅ መምህር አገኘን፡፡ መምህሩ በክረምት መርሃግብር ዩኒቨርሲቲ ስለሚማር ነሐሴ 12፣ 2008 ባደረግነው የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ልደት አከባበርና ውይይት ላይ እንደተገኘ ሲነግረኝ አስታወስኩት፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በስልጠና ቢታገዙ ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
እና ምን አለፋችሁ መቼ በትምህርት ቤትና በራስ አበበ ግቢ ጉብኝት ያበቃል የኛ ቆይታ! ይህ ተርብ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ አገር ላሳያችሁ ብሎ ይዞን መሄድ፡፡ የቲያትር ቤት የወንበር አቀማመጥ በመሰለ አደራደር የተደረደሩ ተራሮችን አይተን ሆዳችን ባባ፤ ደስ አለን፤ ብረሩ ብረሩ አለን፤ የሳሲትን መንገድም አቅጣጫውን አየሁት፡፡ በነገራችን ላይ የሞጃና ወደራንና የሞረትና ጅሩን ወረዳዎች የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ ጅሩ ቅርባችን ሳይሆን አይቀርም ለሞጃዎች፡፡ ሳሲት ብዙ ወሬዎች አሉ ስለጅሩ፡፡ ስርጦቹን ራስ አበበና ወታደሮቻቸው እየወጡ እየወረዱ ከጣሊያን ጋር እንደሚዋጉባቸው አሳምን ሲነግረኝ እኔ ራሴ ይህን አስቸጋሪ መንገድ መሄድ እንደሚከብደኝ እያሰብኩ አድናቆቴን ለሸዋ አርበኞች! ‹‹እዚች ጋ አንድ ጀግና ተመቶ አርፏል፡፡ መጀመሪያ መሳሪያ አልነበራቸውም - በኋላ ግን ማርከው የኃይል ሚዛኑ ተስተካከለ›› እያለ ታሪክን የኋሊት አስቃኘን፡፡ የውሃ ጋኑ ታች ቆላው ላይ ነው፡፡ ውሃው ሞልቶ ይፈሳል፤ በባህላዊ መስኖ የለማውን አገር አየነው፡፡ ባለመስኖዎቹና የኩሳዬ ነዋሪዎ በውሃ ያለባቸውን ግጭት ፍቱላቸው - አስታርቋቸው - እትዬ ዘወድነሽ መሯታል የውሃው መቆራረጥ ነገር፡፡ ሚኪና ሩት አገሩን ማስጎብኘት እንደሚቻል ሃሳብ እያቀረቡ እኛ አገራችንን የማየት ልማድ ለምን እንደሌለን ሲጠይቁኝ ነበር፡፡ እነዚህን በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች በማስጎብኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ሚኪ ጸጉሩን እንደራስ አበበ አጎፍሮ ነበር፡፡ ሁለት ገጽ የጉዞ ማስታወሻ በወረቀት ጽፎ ኮምፒውተር ቤት ሰጥቷል፡፡ ከዚያ በፍላሽ ወስዶ ለእናንተ ለማጋራት፡፡ ደረሰልህ ወይ በሉት ደውላችሁ - 0912906228 - አንቺ ማነሽ- አደራ መጥበስ አይቻልም፡፡
ማታ ተመልሰን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ያው ሐሙስ ስለነበር የውይይትና የስነጽሑፍ ምሽቱ ላይ የጉዟችንን ሪፖርት አቀረብን፡፡ እኔ ስለ ሕዝቡ፣ ሚኪ ስለ አካባቢው እና ሩት ስለ ታሪኩ፡፡ ያልሄዱ ቢቆጫቸውም አሳምን የላከላቸውን የጅሩ ዳቦ እንዳምናው እየበሉ ታድመዋል፡፡ የሚጋገረው ዳቦ ብዛት ለቁጥር አዳጋች ነው፡፡ የስፖርት ወይስ የዳቦ ፌስቲቫል! ለጥቅምት አቦ ሁላችሁም ተጠርታችኋል፡፡ ያኔ አገሩ ይለመልማል - ይምራል አሉ፡፡
ረስቼው 1. በፈረስ ሲታረስ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡
ረስቼው 2. መኪና ውስጥ ስንሄድ ያገኘኋቸው እናት ንቃተህሊና ይገርማል፡፡ ሸዋዎች ቀላሎች አይደሉም ያስብላችኋል!
ረስቼው 3. መንገዱን አስፋልት እንዲያደርጉት መቀስቀስ ያሻል፡፡
ረስቼው 4. የኩሳዬን ትምህርት ቤት ያሰራው ሜንሽን ነው፡፡
ረስቼው 5. ኩሳዬ ብዬ በይነመረብ ላይ በአማርኛ ብፈልግ ብዙ ነገር አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ በአማርኛ ጉግል ላይ ብትፈልጉ ብዙ ነገር አለ፡፡
በመጨረሻም ሌላ ብዙ አውቄ የረሳኋቸው ነገሮች ስላሉ ሄዳችሁ እንድታዩ ይሁን!


2017 ሜይ 12, ዓርብ

2017 ሜይ 9, ማክሰኞ

አሁንም አርበኞች አሉ!




ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የዘንድሮውን የአርበኞች በዓል አከባበር አስመልክቶ የተጻፈ በመሆኑ የአንዲት ግራርንና የአርበኞችን ታሪክ በጥልቀት አይዳስስም፡፡ ያንን የምትፈልጉ አንባብያን ባለፉት ዓመታት የጻፍኳቸውን ጽሑፎች እንድታነቡ እመክራለሁ፡፡
በዓል በሚበዛበት በዚህ በሚያዝያ ወር፣ በተለይ በመጨረሻው ሳምንት፣ ስራ በዝቶብኝ ከረምኩ፡፡ በወሩ የመጨረሻው እሁድ ቅዳሜ የተለያዩ ጥሪዎች ነበሩብኝ፡፡
ሀ.  የዩኒቨርሲቲያችን ባህል ማዕከል ዓመታዊውን አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ያካሂድ ነበር፡፡
ለ. ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት 75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ ያዘጋጅ ነበር፡፡
ሐ. የሞጃ አርበኞች ዓመታዊ በዓል ነበራቸው፡፡
መ. የአንዱ ወዳጄ ሠርግ ነበር፡፡
ሠ. የጓደኛዬ ልጅ ክርስትና ነበር፡፡

ሐሙስ (26/8/9)
ይህን ሁሉ ዝግጅት አብሮ ማስኬድ ስላቃተኝ ተጨነቅሁ፡፡ ዘወትር ሐሙስ ማታ በሚከናወነው የውይይትና የሥነጽሑፍ ምሽታችን የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ቤተሰቦችን ስለ አርበኞች አወያየን፡፡ በዚሁ ሳምንት በቤተመጻሕፍቱ የአርበኞችን ሳምንት አስመልክተን በሁሉም የሽያጭ መጻሕፍት ላይ የ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርገን ነበር፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ገዛዝተዋል፡፡ እንደሚያነቡም ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት ታሪክ አዋቂው አቅራቢያችን አቶ አዲሱ ሞላወርቅ የጅሩ ተወላጅ በመሆናቸው ስለራስ አበበም ሆነ ስለሌሎቹ አርበኞች ሲሰሙ ያደጉ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ እስኪ ከትምህርታቸው በጥቂቱ ላቃምሳችሁ፡- ‹‹የአገሩን ታሪክ የማያውቅ ህዝብና አባቱን የማያውቅ አንድ ነው፡፡ ትውልዱ ታሪክ-ጠል እና አባቶቻችን የሚንቋቸውን አውሮፓውያንን የሚናፍቅ ሆኗል፡፡ ታሪክን ለማሳወቅ ሃላፊነት ያለብን በመሆኑ እንዲያነቡና አባቶቻችን ሳያነቡና ሳይማሩ የአገር እሳቤ እንዴት እንዳዳበሩ እንዲገነዘቡ ማገዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለ አያቶቻችን ሳናውቅ አገራዊ ስሜት ልናሳድግ አንችልም፡፡ አባቶቻችንና እናቶቻችን ከ1000 ኪሎሜትር በላይ ሄደው ሞተው ያቆዩልንን ታሪክ ለምንድነው የማናቆየውና የማንወደው ብላችሁ እስኪ ጠይቁ፡፡ የኛን ታሪክ በብዛት የጻፉት ነጮች ናቸው - እንደፈለጉት እያደረጉ፡፡ እኛ ምን እየሰራን ነው?››
ዐስራ ስድስት ሰዎች በተገኘንበት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ስለነበር እናንተ ያልተገኛችሁት ሰዎች ደግሞ እስኪ ለጥያቄዎቹ የየራሳችሁን መልስ ስጡን፡-
ሀ. ቅኝ ተገዝተናል ወይስ አልተገዛንም?
ለ. መገዛት ነው መወረር የሚለውን ሰው አወቀልን አላወቀልን ምን እንጠቀማለን?
ሐ. የሞሶሎኒ ዕቅድ ተሳክቶ ነበር ወይ?
መ. ስለዚህ ታሪክ ማውራታችን አሁን ምን ይጠቅመናል?
ሠ. ሃገራዊ ስሜት ጠፍቶ እንዴት ጠበን ጠበን ጋጣ ውስጥ መጣን?
ረ. የአሁኑ ትውልድ ስለ ሐገር ሲነሳ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ለምን ይላል?

አርብ (27/8/9))
በማግስቱ አርብ ጠዋት ጉዞ ነበረብን፡፡ ወደ አንዲት ግራር፣ ሳሲት አቅራቢያ፣ በሰላድንጋይ መንገድ፣ እንሄድ ነበር፡፡ ጠዋት መናኸሪያ ደረስኩ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሄደውና ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከኔ ጋር የሄደው ሳለአምላክ ጥላሁን መጣ፡፡ እኔም ባለፈው ዓመት ስላልሄድኩ እንደሱው ነኝ፡፡ ቆየት ብላ ሩት መጣች፡፡ የራስ አበበ ቤተመጻህፍት ባልደረባ ነች፡፡ ከዚያም ለዚሁ ዝግጅት ስትል በዋዜማው ከአዲስ አበባ የመጣችው ብርቱካን ካብትህይመርም ብቅ አለች፡፡
በመጀመሪያ እኔ ሰው ካልመጣ እመለሳለሁ ይል የነበረው መምህር ሳለ አሁን እየተረጋጋ መጣ፡፡ ቆየት ብለው ሁለት የህግ መምህራን ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ገጣሚው መስፍን ወንድወሰንና ባልደረባው አብርሃም ተቀላቀሉን፡፡ ከሆነ አይቀር ብለን ከመናኸሪያው ፊት ለፊት በመሰራት ላይ ባለው ህንጻ ምድር ቤት ላይ ቁርስ እንበላ ያዝን፡፡ የአዲስ አበባው የማህደረ ሸዋ ልዑካን የሆኑ ሁለት ወጣት ትውልደ -ሞጃ ጋዜጠኞች መጡና ቁርሳቸውን በልተው ወደ ሰላድንጋይ በሚሄደው መኪና ውስጥ ገባን፡፡ እዚያም ያለ ስራ አልተቀመጥንም ነበር፡-
ሀ. ቼ በለው ኧረ ቼ በለውን እየተቀባበልን ዘፈንን
ለ. ከዚያም ለተሳፋሪው የምናውቀውን የአርበኞች ታሪክ ለማስገንዘብ ተነስቼ ስጀምር መቀዛቀዝ ታየኝ፡፡ ወዲያው አካሄዴን ቀይሬ በአርበኞች ግጥም መጣሁ - በጥሞናና በፍላጎት መከታተል መጀመራቸውን ሳውቅ ወደ ጉዳዬ ገባሁ፡፡ በጥያቄና መልስም በደንብ ሊዳብር የቻለ ውይይት አደረግን፡፡

ሰላድንጋይ
ይህች የጠበለተኛ ከተማ እያማረባት ነው፡፡ አዲሱ ህንጻ ንብረትነቱ የአብቁተ ነው አሉ፡፡ መኪናው ከዱሮው በተለየ መልኩ ይርመሰመሳል፡፡ ባጃጁ ምኑ ቅጡ! ያለ ብዙ ረፍት በቀጥታ ወደ ሳሲት አመራን፡፡ ሳሲት መገንጠያ ባለው የመንግስት አስተዳደር ጽ/ቤት በአንዲት ፒካፕ መኪና ላይ በርካታ ወጣቶች ተጭነዋል፡፡ የወረዳው የባህል ቡድን አባላት መሆናቸውን ነጋሪ አላስፈለገኝም፡፡ በባንዲራ አሸብርቀው መኪናችንን ተከተሏት፡፡ የሳሲቱ መንገድ አስፋልትን ያስንቃል፡፡ የአገራችን መንገድ በአካባቢችን በሚገኘው ቀይ አፈር የተሰራ ነው፡፡

ሳሲት
ሳሲቶችን ተዘዋውሬ ሰላም አልኳቸው፡፡ በሁለት ዓመቴ ስላገኘኋቸው ደስ አለኝ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ማስታወሻ እንዳስተናገደችን የገለጽኩት እህታችን ዘነበች አስፋው በጸና ታማ ነበር፡፡ አሁን እያገገመች ባለችበት ሁኔታ ሄጄ መጠየቄ ደስ አለኝ፡፡ ራበን ባዩ ስለበዛ ምግብ ቤት ገብተው ምግብ ተመግበው በባጃጅ ወደ አንዲት ግራር አቀናን፡፡ አንድ ባጃጅ አምስት ሰው የምትይዝ አነስተኛ ታክሲ ነች እዚያ፡፡ ምቹው መንገዳችን አገሩን ለመቃኘት ሁነኛ እድል ሰጪ ነው፡፡

አንዲት ግራር
ግራር ጋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ዓለም ገና የምትባል ‹ከተማ› ቢጤ ተቆርቁራ በማየታችን ለካ ቆይተናል የሚል ስሜት ተሰማን፡፡ ግራር ደረስን፡፡ እኒያ በሩቅ ሲታዩን የነበሩት ሰዎች አሁን ቀርበው ሲያዩዋቸው ፈገግታቸው ደስ ይላል፡፡ ማንነታቸውም ተረዳን፡፡ የወደቀችውን ግራር ወደ ጎን አድርገን ክብ ሰርተን ቆምን፡፡ የዕለቱ መርሃ-ግብር በግሩም ሁኔታ ቀጠለ፡፡ የሞጃ አርበኞች ሰብሳቢው የአቶ አያሌውና የወረዳው አፈጉባኤ የአቶ ለጤ ንግግሮች ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ ከፈቱልን፡፡ ከእንግዶች ደግሞ የአዲስ አበቦቹ ጋሻው ደበበና የተክለሐይማኖት ማሞ ተራ ተከታይ ነበር፡፡ ጋሻው ያቀረበው ግጥም አበባበቡም ሆነ ይዘቱ ግሩም ነበር፡፡ ግጥሙ ልብ ይገባል፡፡ አንዴ እጄን ከደረቴ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከኪሴ ያስደርገኝ ነበር፡፡ ተክለሐይማኖት ስለ ማህደረ ሸዋ ገለጻ አድርጎ ዓላማቸውንና የአባላቱን መልዕክት አደረሰ፡፡ በየመሃሉ የሞጃ ባህል ቡድን ውዝዋዜና ግጥም ሌሎችንም ስራዎች አቅርቧል፡፡ አባቶችም ፉካሮና ቀረርቶ አቀረቡ፡፡ አንድ ካህን ቡራኬ ሰጥተው ዳቦ ቁረስ ተባልኩ፡፡ ‹‹ኧረ አይሆንም ስንት ትልቅ ሰው እያለ›› ብልም አልሆነም፡፡ ቆረስኩ፡፡ ዳቦ ታደለ፡፡ አረቄም ተሰጠን፡፡ የዘንድሮው በዓል በመንግስት ሃላፊዎች፣ በሞንታርቦና በባህል ቡድን የታጀበ ቢሆንም ከነዋሪው ህዝብ በኩልና ከተማሪው የቁጥር መመናመን ይታይ ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት በአካባቢው ለቅሶ መኖሩ መሆኑን ሰማን፡፡ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ሲሚንቶና ብሎኬት ተዘጋጅቶለት የግንባታውን መጀመር እየተጠባበቀ የሚገኘው የአንዲት ግራር አጥር የሞጃ ሃላፊዎች ቀና ውጥን ነው፡፡ በርቱልን፡፡ ይህ ጅምር ብዙ ስራዎች እንዲሰሩ ሌሎችን ያነሳሳል፡፡

የመልስ ጉዞ
በፒክአፕ መኪናዋ እንግዶቹ ቅድሚያ ተሰጥቶን ወደ ሳሲት አቀናን፡፡ ከዚያም ሳለአምላክ ቤቴን እንዳሳየው በጠየቀኝ መሰረት ወደ እናቴ ቤት ወሰድኳቸው፡፡ ትንሽ ቀደም ብዬ እንደምንመጣ የነገርኳት ታናሽ እህቴ ጋበዘችን፡፡ ቡና ተፈላ፡፡ አያቴንም አገኘኋት፡፡ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈን እንግዶቼን ሰላድንጋይ ድረስ ሸኝቼ ልመለስ መኪና ውስጥ ገባን፡፡ ሰላድንጋይም በገና ሆቴል ወረዳው ሌላ ግብዣ አዘጋጅቶ ኖሮ በጥሩ ሁኔታ ተጋበዝን፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን፣ የአፈ- ጉባኤና የባህል ጽ/ቤቶች ሰዎች ለእኛ ሲሉ ተፍ ተፍ ሲሉ ስለነበር ውለታቸው አለብን፡፡ እንግዶቼን ወደ ደብረብርሃን ሸኝቼ ወደ ሳሲት ልመለስ ነው ሰል ጋዜጠኞቹም እኛም ልንመለስ ነው አሉ፡፡ ሦስታችን ተመልሰን በተክለሐይማኖት ቤት አመሸን፡፡ እስከ ሦስት ሰዓትም አቶ ደምሴ ስለአርበኞች ግሩም ትምህርት ሰጡን፡፡ አንድ የሚሳሳቱት ነገር የለም፡፡ እኔ እንዲያውም ለእርሳቸው ቃለመጠይቅ ማድረግ ከአቅማችን በላይ መሆኑን ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ወደ ቤቴ ሄጄ ከቤተሰብ ጋር ስጫወት ቆየሁና ሌሊቱን ይታይ የነበረ አንድ ጽሑፍ ስለነበረኝ ሳይ አደርኩ፡፡ በማግስቱም ዘመዶቼን ጠያይቄ ጠዋት 3፡30 ወደ ሰላድንጋይ ሄድኩ፡፡ እዚያም ዘመድ ጠያይቄ ሰመሻሽ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ ብዙ የተዘነጋ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ የነበራችሁ ሰዎች በአስተያየት አዳብሩልኝ፡፡ በመጨረሻም አርበኞቻችንን ያከበርነው ሁሉ የዚህ ዘመን አርበኞች ነን፡፡ ተቃዋሚ አለ?



































በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...