2022 ኦክቶበር 25, ማክሰኞ

ከወለጋ መርዷቸው ሲጠበቅ ተሸልመው የመጡት አማሮች (ይህን ጽሑፍ ስታነቡ በአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመረዳት እንደማታለቅሱ ዋስትና አልሰጣችሁም!)

 

ከወለጋ መርዷቸው ሲጠበቅ ተሸልመው የተመለሱት አማሮች

(ይህን ጽሑፍ ስታነቡ በአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመረዳት እንደማታለቅሱ ዋስትና አልሰጣችሁም!)

 



በፊት ከንቲባነት ለጥቂት ያመለጣቸው የአሁኑ ሚኒስትር

ያለፉትን ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ እንቅስቃሴዎቻቸውን ስናይ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በፖለቲካው መድረክ ታይተዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. በቅንጅት የምርጫ ዘመቻ፣ የምርጫና ድህረ ምርጫ ወቅት በተደጋጋሚ የታዩት የትምህርት ሰው ከምርጫው በኋላ በፓርቲያቸው ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ታጭተው ነበር፡፡ ያ ውጥን ከሽፎ ለሁለት ዓመታት የተጠጋ የእስር ጊዜ አሳልፈው ከተፈቱ በኋላ ወደ ዉጪ በመውጣት የግንቦት ሰባትን ሁለገብ ትግል መርተዋል፡፡ ከ2010ሩ ለውጥ በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ በኢዜማ መሪነት ቀጥለው ከ2013ቱ ምርጫ በኋላ መንግሥት የተቃዋሚ መሪዎችን ወደ ሥልጣን ሲያመጣ የትምህርት ሚኒስትር ለመሆን ቻሉ፡፡ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ልዩ ልዩ ጉልህ የፖለቲካ ለውጦችን ሊያመጡ ይችላሉ በሚል ደጋፊዎቻቸው የጠበቁ ቢሆንም ትምህርት ላይ ተመድበዋል፡፡ በትምህርት ዘርፍ ተፈጥሮ ምክንያት አነጋጋሪና የሁሉንም ትኩረት የሚስብ የፖለቲካ ሥራ ይሠራሉ ተብሎ ባይጠበቅም ወቅትና ሁኔታዎች የፈቀዱትን የዚህን ዓመቱን ዓይነት ጥንቅቅ ያለ ዘመቻ ሊመሩ መቻላቸውን የገመተ አልነበረም፡፡ መጻሕፍታቸውን እንዳነበበና በእንግሊዝኛ ሲናገሩ እንደሰማቸው ሰው በትክክል የተማሩ መሆናቸውን ስለምረዳ የትምህርትን ፍሬ በእርሳቸው ተግባር አይቻለሁና ጋዜጠኛ ይመስል ይህን ሰፊ ዘገባ ለማጠናቀር ባተልኩ፡፡  

 

እንደ ከተማ ይፍሩ ወይስ እንደ ጆርጅ ማርሻል?

አቶ ከተማ ይፍሩ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት በንጉሣዊ ቤተሰብነት ሳይሆን በጥረታቸው ከትልቅ ደረጃ ከደረሱት ሚኒስትሮች አንዱ ነበሩ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሃሳብ ያመጡት ስለመሆናቸው ይነገርላቸዋል፤ ምንም እንኳን የድርጅቱ ምስረታ ታሪክ ሲነሣ በብዛት ስማቸው አብሮ የሚነሣው ንጉሠ ነገሥቱ ቢሆኑም፡፡ የመሠረተ-ትምህርትንስ ሃሳብ መንግሥቱ ኃይለማርያም መቼ አመጡት የሚል ሞጋች ሌላም አገርኛ አብነት ሊጨምር ይቻለዋል፡፡ ጆርጅ ማርሻል በፕሬዘዳንት ሃሪ ትሩማን ዘመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተንኮታኮተውን አውሮፓን ለማነቃቃት ብድርና ድጋፍ የሚያደርግ ዕቅድ ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የፕሬዘዳንቱ ስም ሳይሆን የዚያኔው ዉጪ ጉዳይ ሴክረተሪ ስም ይወሳል፤ ዕቅዱም በስማቸው ‹ማርሻል ፕላን› ተብሎ ሲጠራ ይኖራል፡፡ ይህ የአሁኑ የብሔራዊ ፈተና አዲስና መጠቅ ያለ ዕቅድ እንደአጀማመርና አካሄዱ ሁሉ መጨረሻውም ካማረ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደ ከተማ ይፍሩ ስማቸው ይረሳ ይሆን ወይስ እንደ ጆርጅ ማርሻል በትውልድ ይታወሱ ይሆን? እርሳቸው ይታወሱ ወይም የአሁኑ የአገሪቱ መሪ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የጊዜ የቤት ሥራ ቢሆንም ዕቅዱ ለሳምንታት ከዳር እስከዳር የህዝቡን ስሜት ሰቅዞ ይዞ የቆየ መሆኑን ማንም አይክድም!

 

ፈተናው ፈታኝነቱ ለፈታኞች የነበረበት ጊዜ

የብሔራዊ ፈተናን ፍትሐዊነት አስመልክቶ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና ሃሳቦች በየዓመቱ ሲነሱ ቢቆዩም ጉዳዩ ዋነኛ የፖለቲካና የፀጥታ አጀንዳ የሆነው ግን በ2008 ዓ.ም. በታዋቂው የኦሮሞ አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ ፊትአውራሪነትና በኦሮሞ ፖለቲከኞች ግብረአበርነት ፈተናው ቀድሞ ወጥቶ በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ ነበር፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ወደ በይነመረብ በማቅናት ባደረኩት ጥናት ጃዋር ለዚያን ዓመት የኦሮሞ ተፈታኞች የጊዜ ማራዘሚያ ለመጠየቅ ፈተናውን ማውጣቱን ጠቅሰው የሚያመሰግኑት ደጋፊዎች እንዳሉት ሁሉ አድራጎቱ ላስከተለው ውጥንቅጥ የሚተቹት አልጠፉም፡፡ ከዚያም በኋላ ባሉት ዓመታት ፈተናውን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ መለቀቅና በቡድን መሰራትን የመሳሰሉ ትችቶች ሲቀርቡ፤ ከፍ ሲልም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያው መንገድ በዘር መድሎ የተቃኘ ነው በሚል መተቸቱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም መንግሥትና በተለይም ፈተናው የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በጽኑ ተተችተውበታል፡፡ እንደ አማራ ክልል ባሉ ቦታዎች በመቶኛ ከአጠቃላዩ ቁጥር እጅግ ዉሱን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡበትንና ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ ያስከተለውን የባለፈውን ዓመት ውጥንቅጥ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር በመፍራት የአማራ የዲያስፖራ ድርጅቶች በክረምት ለመምህራን ደሞዝ በመክፈል ለአማራ ክልል ተፈታኝ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እስከማሰጠት ደርሰዋል፡፡ ተማሪዎች፣ ቤተሰብ፣ መምህራንም ሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በጭንቀት የሚጠብቁት ፈተና እንደዚህ በተደራጀ ሁኔታ መካሄድ እንደሚችል የገመተ ለመኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡    

 

 

ከማሻሻያዎች ወሬ እስከተጨበጭ ለውጦች

ጀዋር መሐመድ የከፈተው የፓንዶራ ሙዳይ በትምህርት ዘርፍ ምን ቀውስ እንዳመጣ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ በሌሎች ዘርፎች እሱና በሱ የትግል ዘመን የወጡ ፖለቲከኞች ያስተዋወቋቸው በርካታ ቀውሶች ይኖራሉ፡፡ የፈተናውን ችግር ለማስተካከል ታስበው ከነበሩት ለውጦች አንዱ በታብሌት መፈተን ነው የተባለ ቢሆንም ከፈታኙ፣ ከአቅራቢው፣ ከአጓጓዡ በሚል መመከኛኘት ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ ሌሎችም ጥረቶች ፍሬ ሲያፈሩ አልታየም፡፡ በ2015 ዓ.ም. የተዋወቀውና ተማሪዎችን በአቅራቢያቸው ወዳሉ ዩኒቨርሲቲዎች በማጓጓዝ መፈተን የሚለው ፕሮጀክት ሲታወጅ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሚዲያ ብቅ ብለው ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፤ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ስለሚኖረው ስኬታማነት የጠየቁ ብዙዎች ቢሆኑም፡፡ ወሬው በተሰማ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ የእንቅስቃሴው ሁኔታ ይታይ ጀመር፡፡ መሳካትና አለመሳካቱም የብዙዎችን ልቦና ሰቅዞ ይዞ ቆይቷል፡፡   

 

የፊርማ ማሰባሰብና ግብግብ ቀናት

ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ ፈታኞቹም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ነበሩ፡፡ መምህራኑም  ከትውልድ ክልላቸው ዉጪ እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡ ተመዝግበው ቆይተው ምድባቸውን ስላወቁበት ሁኔታ መምህር ሳሙኤል አድማሱ (በዚህ ዘገባ የመምህራን ስሞች በሙሉ ተቀይረዋል) ሲናገሩ ‹‹ስመዘገብ በቂ መረጃ ባይኖረኝም ከምሰራበት ዩኒቨርሲቲ ዉጪ እንደምንመደብ ግን አውቃለሁ፡፡ ወለጋ የምመደብ ግን አለመሰለኝም፤ አልጠበኩም፡፡ በእርግጥ የመመደብ ዕድሉ አለ›› ይላሉ፡፡  ይህን ወቅት ሲያስታውሱ የነበረውን ጭንቀት ከፊታቸው ላይ ለማንበብ ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ ትረካቸውን ይቀጥላሉ ‹‹ሌሊት ስድሰት ሰዓት ነበር ቴክስት ደረሰኝ፡፡ ከዚያም ቀድሞ ቺፎችና ሱፐርቫይዘሮች ቀድሞ ስለሚደርሳቸው አይቶ ነገረኝ ኃላፊ ነበር፡፡ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እስከ አባቱ የኔ ስመ-ሞክሼ የሆነ ሰው ወለጋ ተመድቦ ኖሯል እንጂ የኔ አልነበረም፡፡ ሰው የሱን አይቶ ነግሮኝ ደንግጬና ተረብሼ ነበር፡፡ እንደፈራሁት ወለጋ ሲደርሰኝ በመሄድ ውሳኔዬ ከቤተሰብ ተኮራርፌ ነው የሄድኩት፡፡ ባልሄድና ስራዬም ይሻላል ያስብላል የነበረው ጭንቀትና ስጋት፡፡››  

ሌላኛው ደምቢዶሎ የተመደቡት መምህር ይርጋለም አለኸኝ በበኩላቸው ‹‹ስንሄድ የትምህርት ሚኒስቴርን ቅጣት ፈርተን ነው የሄድነው፡፡ ስመዘገብ የማልፈልገው ቦታ ከደረሰኝ እቀራለሁ የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ መንቀሳቀቁን እፈልጋሁ፡፡ ፈተናው በዚህ መልኩ መሰጠቱን እደግፍ ነበር፡፡ ተመዘገብኩ፡፡ መስከረም 24 ተገናኝተን አዲስ አበባ ለአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ፊርማ ተፈራርመን አስገባን፡፡ የደህንነት ዋስትና ይሰጠን እንጂ እንሄዳለን ያለ አለ፡፡ ፈቅጄ ስለተመዘገብኩ እሄዳለሁ ያለ አለ፡፡ ይቀየርልን ያለ አለ፡፡ ተጨባጭ የደህንንት ስጋት ስላለብን ተወዛግበናል፡፡›› የፊርማ ማሰባሰቡን ከሰሩ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ለበርካታ ተቋማት ማስገባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ሌሎች ሳይሄዱ የቀሩ ከደርዘን ያላነሱ መምህራንም አውስተዋል፡፡ እነሱ የሁኔታውን አዝማሚያ አይተው ማናቸውንም ቅጣት ለመቀበል ወስነው የቀሩ ናቸው፡፡

አስፈሪው የኤሊ ጉዞ

ከዚያ ሁሉ የፊርማ ዘመቻና ግብግብ በኋላ በማግስቱ ጠዋት አብዛኞቹ መምህራን የወለጋ ጉዟቸውን ለመጀመር መቁረጣቸውን ያዩ አንድ ተመድበው ያልሄዱ መምህር በአማራ ምሁር ተስፋ መቁረጣቸውን መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ ‹‹በግድ ወደ ሞት ሂድ ሲሉት አልሄድም ብሎ ለመናገር ያልደፈረ መምህር፣ ሲያስፈልግ ፈተናው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አለያም እዚያው ባሉ መምህራን እንዲሰጥ መጠየቅ ይገባው የነበረ መምህር፣ ከስራ ላለመባረር ሲል በዋዜማው አምርሮ ሲቃወመው የነበረውን ጉዞ ለማድረግ ወሰነ፡፡ ታዲያ ይህ ምሁር ነው ሌላ ጊዜ አማራ ወገኔ በማንነቱ ምክንያት ተገደለ ብሎ ሊቆም የሚችለው!›› ብለዋል፡፡ በአንጻሩ ሄደው ፈትነው ከተመለሱት አንዱ የሆኑት መምህር ሳሙኤል ቡናቸውን ፉት እያሉ ሲያስታውሱ ‹‹መስከረም 26 ጠዋት በ100 ተገኙ ተባልን፡፡ ሁለት ልብ ሆኜ ሄድኩ፤ አይቼው እወስናለሁ ብዬ ነው፡፡ 20 በላይ መኪና ቆሟል፡፡ ተደፋፍረን ገባን፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች በአጃቢነት ተመድበዋል፡፡ እነሱ ይመጣሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር፡፡ መከላከያ ወይም ፌደራል ጠብቀን ነበር፡፡ እሁድ መስከረም 29 ከአዲስ አበባ ወደ 230 ላይ ጉዞ ጀመርን፡፡ 328 ኪሎሜትር ነበር፡፡ ማታ 130 ላይ ደረስን፡፡ ወደኋላ የሚቀሩትን ባሶች እየተጠባበቅን ነው የሄድነው፡፡ መጀመሪያ እንደደረስን የገጠመን የአልጋ ችግር ነው፡፡ ወደ 600 ሰው ስለነበር አልጋ ለማግኘት ተቸገርን፡፡ የሦስት ካምፓስ መምህር ነው፡፡ ሆቴልና ዩኒቨርሲቲ አደርን፡፡ ደምቢዶሎ ሂያጆች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዶርም አደሩ፡፡ እሱ ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ እኔ ፋርምላንድ ሆቴል አደርኩ፡፡›› የጉዞውን ሁኔታ ካለንበት ለምንከታተለው ሰዎች አስጊነቱንና የመቆሙንና የመውረዱን ተደጋጋሚነት የሚያስታውሱ የፌስቡክ ማስታወሻዎች ከተጓዥ መምህራን ደርሰውናል፡፡ ደርሰው በሰላም ይከርሙ ይሆን?

 

ወሬና ተግባር የሰማይና የምድር ያህል

በወለጋ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ወለጋና ደምቢዶሎ ናቸው፡፡ ወለጋ ሦስት ካምፓሶች ማለትም ነቀምት፣ ጊምቢና ሻምቡ አሉት፡፡ መምህር ሳሙኤል ስለመጀመሪያዎቹ ቀናት ሲናገሩ ‹‹ነቀምት ደርሶኝ ስሄድ ያንንም ሞክሼየን አስተባባሪ ሆኖ አገኘሁት፡፡ በቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ ስሰጥ አይቶኝ ኖሮ ሚዲያ ላይ አይቼሃለሁ አለኝ፡፡

በተለይ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞችና እና ነዋሪው ሆቴል ይጠቀማል፡፡ አዳዲስ እንቅስቃሴዎችና ኢንቬስትመንቶች እንደቆሙ አየን፡፡ ምግብ አለ፡፡ የኑሮ ውድነቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ እንዲያውም የጦርነት ቀጣና እንደመሆኑ የተጋነነ አይደለም፡፡ ያልጠበቅነው ነው›› ይላሉ፡፡

መምህር ይርጋለም በበኩላቸው ‹‹የድርጅቶች ማስታወቂያ ሳይቀር ከላይ ኦሮምኛ ከታች አማርኛ ነው፡፡ በአማርኛ ብቻም አይተናል፡፡ እኛ የጠበቅነው የለየለት የጦርነት ቀጣናና ምንም አማርኛ የማይደመጥበት ነበር፡፡ ፊደልቀመሱና በወሬ የሚያበጣብጠው የህብረተሰብ ክፍል በተጨባጭ ሄዶ አየ፡፡ በፍጹም ያልጠበቀው ነው፡፡ ሰውን በወሬ ሲያሳስት ከርሞና ለራሱም ተስፋ ቆርጦ ሄዶ ተስፋ ሰንቆ መጣ፡፡ ሶሻል ሚዲያ ወሬ ያጋንናል፡፡ ቴዲ አፍሮን፣ አስቴርን፣ ፍቅር አዲስን (በተለይ የምትወደድ ነሃ) ደምቢዶሎ ላይ ሰምተናል፡፡ ነዋሪዎች በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ዝግጅቶችም ሲዝናኑ አይቻለሁ፡፡›› ብለው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ተፈታኞቹ ተማሪዎች

‹‹ተማሪዎች ከየወረዳው ሲገቡ አገኘናቸው፡፡ በሰዓት ደረስንና ገባን፡፡ ሦስት ቀናት የቅድመዝግጅትና ክላስ ልየታ ሰራን፡፡ በእርግጥ እነሱም ቅድመዝግጅት ሰርተዋል፤ አደራጅተዋል፤ ተረካከብን - 30 እስኪጀመር፡፡ ኩረጃ የለም፡፡ ስርዓት ያላቸው ተማሪዎች ናቸው፡፡ አልፎአልፎ ካልሆነ በቀር፡፡ ከደምቢዶሎ የመጡ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አጤሬራ ይዘዋል፡፡ ለመኮረጅ ይሞክራሉ፡፡ የከተማ ልጆች ናቸው›› የመምህር ሳሙኤል ምልከታና ወግ በሰፊው ይወርዳል፡፡

‹‹ነቀምት ከተማ ላይ ንግግር ኦሮምኛ ነው፡፡ በተሰባበረም ቢሆን ግን አማርኛህን ይሰሙሃል፡፡ ተማሪው ትንሽ እንግሊዝኛ ይሞካክራል፡፡ አንዳንድ ተማሪ በአማርኛ ንገሩን ይላል፡፡ ሶሻሎች አማርኛ ደካማ ናቸው፡፡ ናቹራሎች ግን ይሻላሉ፡፡ ‹‹ከዞናቸው ዉጪ የተፈተኑ ተማሪዎች አሉ፡፡ የደንቢዶሎው ወደ ነቀምት ወይም የሌላ ቦታም የመጡ አሉ፡፡ ተማሪዎች መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ ምንድነው ብዬ ስጠይቅ ‹‹ምነው በኛ ተጀመረ!››  የሚል ነው አሉ፡፡ ለምግብ ካፌው ስለማይበቃ ዛፍ ስርም ይበላሉ፡፡ ስልክ የለም፤ ከግቢ መውጣት የለም፡፡ የፈተናው ስርዓት ትልቅ ጅምር ነው፡፡ የኢቫንጀሊካል ቸርች ተማሪዎች ደምቢዶሎ ውስጥ በብዛት አማራና ትግሬ የሆኑ ትሁትና ተግባቢ ቢሆኑም ለመሸወድ ግን ይሞክራሉ፡፡ ቀድሜ አብሮኝ ከሚያድር መምህር ስለሰማሁ አላስኮረጅኳቸውም፡፡ እስከ አርባ ደቂቃ ምንም ሳያጠቁር ጎበዝ ተማሪን የሚጠባበቅ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት የሚሰሩትን ልጆች አርቄ አስቀምጫለሁ፡፡ ነቀምት ካምፓስ ውስጥ ቄለም ትልቁ ማዕከል ሲሆን የተፈቱትም አዳራሽ ነው፡፡ ›› ብለውኛል ዶክተር በቀለ ምንውዬለት፡፡  የዶክተር በቀለ አጠቃላይ ምልከታና የአፈታተን ስልት ከሌሎች ተጠያቂዎች ሲበልጥ ምናልባት የትምህርት ዝግጅታቸውና ዕድሜ ያስተማራቸው ይሆናል የሚል ግምት አሳድሮብኛል፡፡

 

ህዝቡ፣ አካባቢውና ፀጥታው

‹‹ህዝቡ የፖለቲካ ምልከታው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሰው እንዲሄድላቸው፣ ምግብና ቡና ሸጠው ከሰው ጋር እንዲኖሩ ይፈልጋሉ፡፡ ቆመው ያስታጥቡሃል፡፡ በአማርኛ ‹ያልበላችሁ ቅደሙ› ይሉሃል፡፡››

‹‹አማርኛ ያናግሩሃል፡፡ ማንኛውም ሰው ያስተናግድሃል፡፡ ከተማ ውስጥ ገና ሲያዩህ ይለዩሃል፡፡ አገሩ፣ ሰዎቹ፣ ልጆቹ ተስማምተውኛል፡፡››

ምግብ ቤት ላይ አንቸገርም፡፡ አልጋ በአማርኛ አትይዝም የሚባለው ውሸት ነው፡፡ በተቃራኒው ነው፡፡ የአማርኛ ሙዚቃዎች የቴዲ አፍሮና የዳኜ ዋለ ይደመጣሉ፡፡ ይገርመን ነበር፡፡ አማራ ነዋሪ ያለ መሰለኝ፡፡ የአማራ ናቸው ብለን የገመትናቸው አሉ፡፡

እዚህ የማውቀው የክረምት ተማሪዬ ተባበረኝ፤ ከሱ ጋር ሻይ ቡና ስንል ውይይት አድርጌያለሁ፡፡ ቀድሜ ነግሬው ነበር፡፡ ምዕራብ ወለጋ ነው እንጂ እዚህ ችግር የለም አለ፡፡ የስልክ አገልግሎትና ዳታ አለ፤ ዋይፋይም ሆቴል ጋር አለ፡፡ ዝቅ ያለ ሆቴል ከሆነ ዋይፋይ የለም፡፡ ሱፐርቫይዘር ቅድሚያ ሴናፍ ሁቴል ተያዘላቸው፡፡ ሜርሲሞይም ተይዟል፡፡

‹‹ከተማው ላይ ከጠበቅነው በላይ ሰላማዊ ነው፡፡ በጎጃምኛ ሙዚቃ ታጅበን ከረምን፡፡ ምግብ ቤት እጅህን የሚየስታጥቡህ እነሱ ናቸው፡፡ እንደፈለክ ትንቀሳቀሳለህ፡፡ የደህንነት ችግር እንዳለ ግን ታያለህ፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እግረኛ አያልፍባቸውም፡፡ ክልክል ነው፡፡ ጠባቂዎች በመንግስት መስሪያ ቤት ደጃፍ ስናልፍ በኦሮምኛም አትለፉ ቢሉን አልሰማንም፡፡ በተጨባጭ የፀጥታ ችግሩ የነካውን ታያለህ፡፡

አብሮኝ የተማረ ሰው አገኘሁ፡፡ ስላረጀብኝ ረስቼው እሱ ነው ያወቀኝ፡፡ ህዝቡ እኛን ክፉ ያገኛቸዋል ብሎ ይሰጋልናል፡፡ ያረፍኩበት ሆቴል በሸኔ ደጋፊነት ተጠርጥሮ የታሰረ ሰው ንብረት ነው፡፡ በር ከፍተው ልብሴን ሰርቀውኝ ማግኘቴን ስናገር ባስቸኳይ እዚያ የነበርነው ወደ ሌላ ቦታ ተዛወርን፡፡ ለደህንነታችን ሁሉም ይሰጋሉ፡፡

ሕዝቡ እንደሚወደን አይተናል፡፡ በተለይ ወጣቶቹ፣ ሴቶቹ ነጻነት አላቸው፡፡ ትጥቅ ትግሉ የደንቆሮ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ትምህርትንም የጣለውና ተማሪ ስሙን መጻፍ እንዳይችል ያደረገው ፖለቲከኛው ነው፡፡ አንድ ሱፐርቫይዘር 12 ጊዜ መፈተኑን ነገረኝ፡፡ ሙክት ታርዶ ይቀለቡ እንደነበር አውስቶልኛል፡፡

ከተማው ላይ ነበርን፡፡ 17 ቀን ቆየን፡፡ ስለ ገጠሩ መናገር አንችልም፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በፌደራል ፖሊስ ታጅቦ ነው የሚሄደው፡፡ የዞን አመራሮችም በከባድ ኃይል ታጅበው ይሄዳሉ፡፡ ስጋት እንዳለ ታያለህ፡፡ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር የሚመሳስሉ ነገሮች አሉት ወለጋ፡፡ እኔ ተስፋ ነው የታየኝ፡፡ ያየነው የለቅሶ ስርዓት እንደኛው ነው፡፡ ነጠላ ዘቅዝቀው ነበር፡፡ እዚያ ከራሳቸው ስታፍ በቀሩ መምህራን ምትክ መድበዋል፡፡ አብዛኛው ፈታኝ ግን ደቡብና አማራ ነው፡፡ ታስቦበት ነበር የተሰራው፡፡ በሌላ በኩል ገጽታ ግንባታ ነበር የተሰራው፡፡ ከፈተናዎች በኋላ የቡና ስርዓት ነበር፡፡ እሁድ ዕለት ቡና በየጥጋጥጉ ነበር፡፡ ጭምቦ የሚባል የባህል ምግብ ተጋብዘናል - የጥቁር ጤፍ ቂጣ በቅቤና አይብ ማለት ነው፡፡ በቅቤ ታጠብኩ አለ አንዱ፡፡ እዚህ እንኳን ቅቤ ዘይት የተወደደብን ሰዎች ቅቤ ቀንሱ ማለት ጀመርን፡፡ የበግ ቅልጥም ያለው ናሽፍ  አለ፡፡

ዶክተር በቀለ ምንውዬለት ያጋሩኝ ሃሳቦች ጥልቅ ምልከታቸውን የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ የሚናገረውም በተመስጦ ነበር፡፡ ‹‹በሕይወቴ ወደ ወለጋ እሄዳለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ አምቦም አልሄድኩም፤ ሆሎታ እንኳን አልሄድኩም፤ ቡራዩን አልፌ አላውቅም፡፡ እዚያ ስሄድ ያየኝ ሁሉ የሚያባርረኝ መስሎኝ ነበር፡፡››

ሲሬ ላይ ነቀምት ልትገባ ስትል የተቃጠለና የፈረሰ ቤት አይተናል፡፡ ስንለመስ ልዩ ኃይሎቹ መሬት ላይ ወርደው እያሰሱ ነው በእግር ያሳለፉን፡፡

የተኩስ ልውውጥ አለ፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምግብ ለተፈናቃይ ሲያደርሱ የታገቱበትን ሹፌሮችን ለማስለቀቅ ነው፡፡ ወደ ደምቢዶሎ ቀይ ቦኔት የለበሰው ጦር እየገባ አይተናል፡፡ ለማስለቀቅ መሰለኝ፡፡ ባለ ቀይ ቦኔቶቹ ነቀምትም አሉ፡፡  

ዋና መንገዶች ላይ በርቀት የአካባቢው ታጣቂዎች ይጠብቃሉ፤ የኛ አጃቢዎች ደግሞ ከመንገድ ግራና ቀኝ በእግራቸው እየሄዱ መኪናውንና ተጓዡን ይጠብቃሉ፡፡ መጨረሻ ላይ ለልዩ ኃይሎቹ ስጦታ ፍሬም ሰጠናቸው፡፡ ከውሎ አበላችን አዋጥተን ብር ይሰጣቸው ሲባል ብር ስለማይጠቅመን ብለው ዋና መስሪያ ቤት ሄደው ለሥራ ላይ ዕድገት የሚጠቅማቸው የምስክር ወረቀት ፍሬም ተሰጣቸው፡፡ የልዩ ኃይል አዛዦቹ አመሰገኑን፡፡ የመጨረሻው ቀን የስንብት ንግግር በአማርኛ ሲደረግ ተማሪዎቹ እሪ አሉ፡፡ አማርኛ አይሰሙም፡፡ በአማርኛ መደረጉም አስፈላጊ አልነበረም፡፡ እኛ ግድም የለንም፡፡ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለፈታኝ መምህራን ቡና ሸልሞ ነው ወደየቤታችን የሸኘን፡፡ ስንሄድ ከነበረው ስጋትና ከጠበቅነው በታቃራኒው የሆነ ክስተት ነው፡፡ በጣም ተደስተናል፡፡ ኮርተናል!

 

የትኩሳቱ ምልክቶች

ያልሄድነው መምህራን ከብሔራዊ ፈተናው የተመለሱ መምህራንን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ ስንል ቆይተናል፡፡ ምድባቸው የት መሆኑን ስንጠይቅ ወለጋ የሚሉንን ግን በስስት እያየን ሰላምታችንም ሞቅ ያለ ነበር፡፡ መምህራኑን እናቴ የሩዋንዳ የትርጉም መጽሐፌን ‹ሁቱትሲ›ን አንብባ ‹ልጅቱ ከቀብር እንደወጣች ይቆጠራል› እንዳለችው ቆጠርኳቸው፡፡ አንድም ውሎአበል ለማግኘት ብለው፤ አለያም ከተመዘገቡ በኋላ መቅረት ከስራ መባረርን ያስከትላል በሚል የካሮትና ዱላ አቀራረብ ወደ ወለጋ የሄዱትን መምህራን ሁኔታ ከመጀመሪያውም በሰመመንና በግርታ ነበር የተከታተልነው፡፡ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላውንጅ በያዝነው የቡድን ወግ ወቅት መምህራን የወለጋ ተመላሽ ፈታኞችን ከበው ያደምጣሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት የዚህን ዓመት ፈታኞች ከመከላከያ ያልተናነሰ ግዳጅ የተወጡ ናቸው እንዳሉ ተሰምቷል፡፡ ከዚህ አንጻር የወለጋዎቹ ደግሞ ባለድርብ ድል ኮማንዶዎች ናቸውና እነሱ ሲያወሩ መርፌ ቢወድቅ ይሰማ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ጥያቄ ከመጠየቅ በቀር ሌሎቻችን ዝም ብለን እናዳምጣለን እንጂ የሚያወሩትና ትዝታቸውን የሚነግሩን እነሱ ናቸው፡፡

 

 

 

ደምቢዶሎ

‹‹በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረውና ወደ ደምቢዶሎ በሹመት የሄደው ምክትል ፕሬዚዳንት ዮሴፍ አድራሻው ስለነበረን አግኝተነው ጥሩ አቀባበል አድርጎልናል፡፡ አቀባበላቸው ቢያምርም ለፈተናው በአንጻራዊነት ደካማ ዝግጅት ነበራቸው፡፡››

‹‹የጃልመሮ ባነር ዶርም ላይ ተሰቅሎ ያዩ መምህራን አሉ፡፡›› ይርጋለም፡፡

‹‹ህንጻ ስያሜ በአካባቢው ታዋቂ ሰዎች መሆኑን አይቻለሁ፡፡››

‹‹አምቦ ባላምባራስና ሌላም የዱሮ ባላባት ሆቴል አይቻለሁ፡፡›› ሳሙኤል፡፡

‹‹በታገቱት አማራ ሴት ተማሪዎች ሁኔታ በቅርቡ የተፈረደባቸው አሉ ያሳገቱ ተብለው፡፡›› በዚህ ላይ እኔ ጸሐፊው በቅርብ ቀን አንድ የኃይማኖት አባት ከስፍራው ካሉ አማሮች የደረሳቸውን የኦዲዮ መልዕክት አድምጫለሁ፡፡ በስልክ የሸኔ ሰው ለአማራው በዛቻ የነገረው ሴቶቹ ልጆች በሕይወት እንዳሉና ሸኔዎች እንዳገቧቸው ነው፡፡ የአንዷን ክብረንጽሕና የወሰደው ከንቲባው መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከተጓዦቹ ግን ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡

ወለጋዎች ራሳቸው በሚፈልጉት መልኩ የሰሩት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በአደረጃጀትና ግቢ በማሳመር ደምቢዶሎ ወለጋ  ይሻላል፡፡  

የፖለቲካ ትኩሳትም ተባለ ጽኑ ሕመም አገሪቱ የገባችበት ችግር መድረሻው የሚታወቅ አይመስልም፡፡  ተጠያቂዎቼ ፈተናው በዚህ መልኩ መሰጠቱ ለትምህርት ጥራት እንዳለው ተስማምተዋል፡፡ የአንዱ ክልል ወደ ሌላ መሄዱን ከህዝብ ህዝብ ትውውቅ አንጻር ወደውታል፡፡ በየዘርፉ ተመሳሳይ የትውውቅ ዕድል እንዲኖር ተመኝተዋል፡፡ ጽንፈኛ ቡድኖች አገሪቱን እንደማያፈርሷት ተስፋ አድርገናል ይላሉ፡፡ አቅጣጫ የሚጠቁሙን አሉ ብለዋል፡፡ መምህራን ወደ ግቢ ሲገቡ ልዩ ኃይሎቹ የሚያደርጉት ጥንቃቄ ልዩ ነው፡፡ አትንኩ ተብለው ነው የሚሉ አሉ ብለዋል፡፡ መንግስትን ገጥመው አያሸንፉም ኦነጎች- ደፈጣ ውጊያ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ‹‹ከከተማ ውጪ ህዝቡን ፊቱን ወደ መንገድ ሳይሆን ከመንገድ በተቃራኒው አቅጣጫ ያስዞሩታል እንዳያየንና መረጃ እንዳይሰጥ፡፡›› 

ከነቀምት በኋላ ደምቢዶሎ 307 ኪሎሜትር ይርቃል፡፡ ጫካ ይበዛል፡፡ ጥበቃው የተጠናከረ ነው፡፡ አማራ ብቻ የሚኖርባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አማራና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰቦች አሉ፡፡ የተፈናቀሉና ዝግ ቤቶች እንዳሉት ሁሉ አሁንም የሚኖሩም አሉ፡፡  

‹‹እዚያ ደርሰን እንዳየነው በጣም ተባባሪ ናቸው፡፡ መጀመሪያ በኦሮምኛ አውርተው ካልቻልክ በአማርኛ ያናግሩሃል፡፡ አልጋም ባንክም ሁሉም ቦታ፡፡ ራስህ ግን ትፈራለህ፡፡ የተማሪዎቹ ስርዓት የሚገርም ነው፡፡ ቋንቋ እንግሊዝኛም አማርኛም አይችሉም፡፡ በኦሮምኛ ነው የሚያስተምሯቸው፡፡ ብዙዎቹ ‹‹ኢዝ ዜር ፕሮብሌም›› የሚለውን አይሰሙም፡፡ አንዳንድ ተማሪ እየጠየቅን ‹‹ረኮ ጂራ›› እንላለን፡፡ ‹‹ጡምሬ›› የመሳሰለውን ተምረናል፡፡ በእርግጥ ሲጠሩህ በአማርኛ ‹‹አስተማሪ›› ይሉሃል፡፡›› ይርጋለም አለኸኝ፡፡

የከተማ ነዋሪዎች ሲያገኙን ‹‹ልጆቻችንን እንዳታስጨንቁ›› ይላሉ፡፡ ‹‹በስርዓት ተፈትነው ቢያልፉ ደስ ይለናል፡፡›› ሲሉም ይጨምራሉ፡፡ አንድ ብቻ ችግር ያለበት ሰውዬ አየን፡፡ ከበላን በኋላ ስቲኪኒ ንጠይቅ አንዱ ተስተናጋጅ አገጣበረን፡፡ ጓደኛዬ ተናግሮታል፡፡ በነገራችን ላይ መዝገበቃላት ገዝቻለሁ፡፡ ከመግዛቴም በፊት የማውቀውን የኦሮምኛ ቃል ጽፌ 100 አድርሻለሁ፡፡   

ወደ አማራ የሄዱት የኦሮሞ መምህራን ተመተዋል የሚል ነገር ሰምተው ቅር ያላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የነቀምትና ደምቢዶሎ ክስተት ብዙም አይደለም፡፡ በጥሩ አማርኛ ይህን የነገሩን አሉ፡፡ የኛን ልጆች እያስቸገራችሁ ያሉ አሉ፡፡ ልጆች ሲሉ በአማራ ክልል ያሉ ኦሮሞ ፈታኝ መምህራንን ነው፡፡ ለአንዷ መምህርት ‹‹ተመድበው ሳይመጡ የቀሩ ፈታኝ አማራ መምህራን አሉ›› ስላት ‹‹እኛ እናስፈራለን እንዴ!›› አለችን፡፡ እዚህ ያለውን ስሜት የማይረዱ አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ስልክ ይዞ ባገኘው ጊዜ የተቆጣውን መምህር ስንብት ላይ ይቅርታ ጠይቆታል፡፡ ስልክ ያመጡ መምህራንን አንድ ቦታ እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ስርዓት ነው እንደአገርም የተዘረጋው፡፡ ደምቢዶሎ ከተማ ውስጥ ችግር ስለነበር የባጃጅ አገልግሎት ቆሟል፡፡ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ቀይ ቦኔት ለባሾች ይቆማሉ፡፡ ከተማ ላይ ሲቪል ለብሰው የሚቆሙ ሸኔዎች አሉ ተብለናል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ የኛን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ይጠብቃል፡፡

በልምላሜ ጎጃምና ወለጋ ተመሳሰለብኝ ያለ መምህር አለ፡፡ ለምለሚቷ ኢትዮጵያ የሚል የተዘፈነው ለደምበዶሎና ለዙሪያዋ ነው ያስብልሃል፡፡

ለተወያዮቹ የቢሆን ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ ‹‹ችግር ተከስቶ ቢሆንስ ኖሮ›› ስል፡፡ ቢሆን ኖሮ ለፖለቲካ መጯጯህ ምክንያት ስለሚሆን ከባድ ይሆን ነበር፡፡ አስተማሪው ሳይቀር ለምን ሄዱ ሊለን ይችላል፡፡ የአንድ ሰሞን የዜና ሽፋን ሊኖር ይችላል፡፡ የሚጠቀሙበት ኃይሎች ይኖራሉ፡፡አንድ ሰሞን ቆይቶ ግን ይረሳል፡፡›› 

ወለጋ ላይ ትኩረት ባደርግም የልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲ ፈታኝ መምህራንን ለማናገር ሞክሬያለሁ፡፡ ለየት ያለ የሰማሁት ‹‹ጅጅጋ ተማሪው ድንጋይ መወራወር ጀምሮ ነበር፡፡ ግን ወዲያው ቆሟል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ቀጠቀጣቸው፡፡ አስተካከለው፡፡›› የሚል ነበር፡፡ የጅጅጋ ፈታኞች ቶጎጫሌ፣ ሶማሊላንድ ሄደው መጥተዋል፡፡

 ‹‹ቦረና ደህና ነው፡፡ እንደፈራነው አይደለም፡፡ የአቡሽ ዘለቀና የታዬ ቦጋለ አገር ነው፡፡ ኦነጎች ቡሌ ሆራ እንጂ እዚያ ተቀባይነት የላቸውም ተብሏል፡፡ ቡሌ ሆራ ነው የፖቲካ ችግር ያለው አሉ፡፡ ያቤሎ ደርሰን መጣን፡፡ ኬኒያም ደርሰን መጣን፡፡ የኮንትሮባንድን አሰራር አይተን መጣን፤ ፊልም በለው፡፡››

‹‹በመዳ ዋላቡ ዩኒቨርሲቲ የተፈተኑ ተማሪዎች አማርኛ የማያውቁ መስለው በኦሮምኛ ብቻ ለመግባባት የሞከሩት ለመኮራረጅ በመፈለግና ሲነጋገሩ ፈታኙ እንዳይረዳቸው ለማድረግ መሆኑን መጨረሻ ላይ አንድ የልዩ ኃይል አባል መሆኑን የነገረኝ ተፈታኝ አጫውቶኛል፡፡›› አንድ መምህር፡፡

‹‹የአማራ ክልሉ ነው ባልተጠበቀ ሁኔታ አሳፋሪ ነገር የተከሰተበት፡፡››

በአጠቃላይ ሲታይ የፈተናው እርማት፣ የተማሪው ምደባ፣ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው ተማሪ የብሔር ስብጥር ጉዳይ አሁን በብዙኃኑ አእምሮ ያለ ጥያቄ ቢሆንም የሱ ውጤት እያደር ይታያል፡፡ የፈተናው አፈጻጸም ብቻውን ግን ተባብረንና በዕውቀት ላይ ተመስርተን ልስራ ካልን ምን ያህል መስራት እንደምንችል ያሳየ ነው፡፡

ትንሽ ምልከታ ወይም ጥርጣሬ ሰምቻለሁ፡፡ ‹‹ፖለቲከኞቹ የፋኖን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ የሚጠብቁት ሳይሆን አልቀረም፤ የአማራ መምህር ኦሮሚያ ሲሄድ በንቃት መከታተከላቸው አይቀርም፡፡ ዕቃ የጠፋብንም መኝታ ቤታችን በጥርጣሬ ተበርብሮ ይሆናል፡፡ የምንበትነው ነገር የሚኖር ሊመስላቸው ይችላል፡፡ የምናነበውንም ለማወቅ መሞከራቸው አይቀርም፡፡››

መዘምር ግርማ

ጥቅምት 15፣ 2015 ዓ.ም.

ከበሬሳ ወንዝ ዳርቻ

 

2022 ኦክቶበር 13, ሐሙስ

ባሕረኛ፣ ጋዜጠኛና ኃይማኖተኛው ዓለማየሁ

 


ዳሰሳ

በመዘምር ግርማ

ጥቅምት 3፣ 2015 ዓ.ም.

ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረብርሃን

 

‹‹የሕይወቴ ፈርጦች፣ እንደ መርከበኛ በባሕር፣ እንደ ጋዜጠኛ በምድር›› የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ በተጉለት ጉዞዬ ወቅት ከሳምንት በፊት ጀመርኩት፡፡ ማንበብ እንደጀመርኩ ከአጠገቤ የተቀመጡት መነኩሴም የራሳቸውን ዳዊት አውጥተው መድገም ጀመሩ፡፡ የተወሰነ ስናነብ ቆይተን ወግ ጀመርን፡፡ ምን እያነበብኩ እንደሆነ ለጠየቁኝ ጥያቄ መልስ ስሰጥ ‹‹እያንዳንዱ ሰው የራሱ ታሪክ አለው›› በማለት ወደ ሌሎች ወጎች አመሩ፡፡ በወለጋ በተለይም በደምቢዶሎ ስለሚያውቋቸው ትጉህ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችና የአሁኑ ሁኔታቸው፣ በጻድቃኔ ማርያም ገዳም ስላሳለፉት የዓመታት ጊዜ፣ ስለ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ወዘተ.፡፡ እኔም ፀሐፊና የግል ቤተመጻሕፍት ስራ አራማጅ መሆኔን፣ በወቅቱም አዲስ የመጻሕፍት የውይይት ክበብ ለመክፈት እየሄድኩ መሆኑን አሳውቄ አውግተን ተለያየን፡፡  

የያዝኩት መጽሐፍ በቋንቋም ሆነ በይዘት ሳቢ መሆኑን በየገጹ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ‹‹ከየት አምጥቶ ይህን አገላለጽ ጨመረው? ምን ቢያስብ እንዲህ ቃላትን አቀናጀ? ጽሑፍና ጸሐፊ ተገናኙ ማለት ይህ ነው!›› አስብሎኛል፡፡ በኪራይ ቤትና በገላማጭ አከራይ ፊት ተወልዶ ያደገው፣ ከልጅነቱ ጀምሮ በተደጋጋሚ ከሞት አፋፍ ያመለጠው፣ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከባድ ሕይወትን ያሳለፈው ባለታሪኩ ደጋግሞ ‹ሰው የለኝማ› እያለ የበደሉን ሁኔታ ያወሳል፡፡ እኔማ የመጽሐፉ ርዕስ ስለምን ‹ሰው የለኝም› አልሆነም አልኩ፡፡ በስተመጨረሻ ሰው አገኘሁ የሚል ቃል አስፍሮና ያም ሰው የዋለለትን ውለታ ጠቃቅሶ ሳነብ እስኪ ይሁን ብዬ ዝምታን መርጫለሁ፡፡ ሳሲት ማምየለኝ ማርያም ለአስተርዮ ንግሥ

‹‹አንድ መልዳ ስሙን አበዛችው፣ አንድ ወልዳ ስሙን አበዛችው፣ አንዱ አገር ስትሄድ አማኑኤል አለችው፣ ሌላ አገር ስትሄድ ባለወልድ አለችው … ››

እንዲሉ በኦርቶዶክስ ውስጥ ስሙ የሚበዛው ኢየሱስ ከኃይማኖት ወደ ኃይማኖት ሲሄዱም አንዴ አምላክ፣ አንዴ ሰው፣ አንዴ ራስ ይሆናል የሚሉትን ነገር ቀድሜ ጫፍ ጫፉን ስለሰማሁ ዝም ብዬ ከማንበብ ሌላ የምሞግት እኔ ማነኝ!   ለአንባቢ ግርታን ለመቀነስ ዓለማየሁ ሰው አገኘሁ ያለው ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ ተቀብሎ ወይም ባጭሩ ጴንጤ ሆኖ ነው፡፡

መጽሐፉን ከገዛሁበት ከስምንት ዓመታት በፊት እስካሁን ባለው ጊዜ እንደ መርከበኛ የሚለውን ንዑስ ርዕስ ሳይ የሥነጽሑፍ ትምህርቴ ትዝ ብሎኝ ሳይሆን አይቀርም እውነት መርከበኛ ሆኖ ነው ወይንስ መርከበኛ ይመስል ማለቱ ይሆን ስል ቆይቻለሁ፡፡ ለካ ባህር ኃይልን ተቀላቅሎ ኖሯል፡፡ የወጣና የወረደበት የወታደር ሕይወት አንባቢን ቁጭ ብድግ ያደርጋል፡፡ የቀይ ባህርን ቀጣና ከሰላሙ እስከ ጦርነቱ ጊዜ ያስቃኘናል፡፡ የሳሲቱ መንገሽ ኪዳኔ ባጭር ስለተቀጨው ስለ ባህር ኃይል ሕይወቱ የነገረኝን ከዚህ መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ ‹አይ ምፅዋ› ላይ ያነበብኩትንም አስታወሰኝ፡፡ ለአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ የሚጽፍላት ደብዳቤ በግሏ ሳይሆን ከአምስት የዶርሟ ልጆች ጋር በምርጡ ደብዳቤ ዝግጅት እየተነበበ የአንደኝነትን ደረጃ ደጋግሞ መያዙን ከልጅቱ መስማቱ ሲጽፍ በቅርቡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላውንጅ ከጀርባዬ ተቀምጠው ጓደኞቻቸው የጻፉላቸውን የፍቅር መልዕክቶች እያነበቡ የሚሳሳቁ ሁለት ሴቶችን አስታውሼ የአንዳንድ ሴቶች ፀባይ በሰላሳ ዓመትም ያልተለወጠ መሆኑን ታዘብኩ፡፡ ይህን ዓይነት ብዙ ታሪክ አለው፡፡ የጓደኛው የዘነበ ወላ ‹መልህቅ› እንዲሁ ሳቢ ሊሆን ስለሚችል ማንበቤ አይቀርም፤ መጽሐፍ ሲበዛብኝ ያነበብኩት እየመሰለኝ ተዘናጋሁ እንጂ!

የደራሲው ሕይወት በተደጋጋሚ ያልተጠበቁ አቅጣጨዎችን ሲይዝ እናያለን፡፡ ‹‹ጉልበቴ ላይ እያስደገፍኩ መጻፌ ቀረና ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ተቀመጥኩ›› ሲል የገለጸውን የጋዜጠኝነት ቅጥር ብዙ አይቶበታል፡፡ የፕሬስን ጓዳ ጎድጓዳ ባየው ልክ አስቃኝቶናል፡፡ ጋዜጠኝነትን ከፕሬስ ወደ እፎይታ ሲቀይር አለቃው ተስፋዬ ገብረአብ ነበር፡፡ ከዚያም ፊታቸውን ሲያዞሩበት ወደ ድርሰትና ትርጉም ሥራ ገብቶ መንፈሳዊ ጽሑፎች ላይ አተኮረ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ለማንበብ ለመንፈሳዊም ሆነ ኃይማኖታዊ ጽሑፍ ቅርብነት ወይም ቀናኢነትን ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የሥልጠና ገጠመኞቹ፣ የውጪ ጉዞ ታሪኮቹና ትዝብቶቹ ሁሉ አስተማሪና አዝናኝም ናቸው፡፡ ራይንሃርድ ቦንኬን ጨምሮ በዕምነቱ እንደ አርአያ የሚያያቸውን ሰባኪያን አግኝቷል፡፡ ዕምነትና ዕውቀት ወይም ልምድና ኃይማኖት የተደበላለቁበትን ይህን መጽሐፍ እንዳነብ ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ በንባብ መስፋፋት ምክንያት ደራሲውን ጨምሮ 25 ሰዎች የተሳተፉበትን የዙም ስብሰባ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ጋባዥነት ስለተሳተፍኩ ነው፡፡ ምክንያት ሆነኝ፡፡ ያው አልፎ አልፎ ብቅ የሚል አጋጣሚ ነው፡፡ የአምባሳደር አማኑኤል አብርሃም የሕይወት ታሪክም እንዲሁ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ክርስቲያናዊ የሆነ የሕይወት ታሪክ ግን አላነብም ብዬ መልሻለሁ፡፡ የትዕግስት አማት የጻፉት አንድ ምሳሌ ነው፡፡ በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍም ሆነ ታሪክ የኦርቶዶክስ ተጽዕኖ በእጅጉ የጎላበት ስለሆነ ከዚያ ላመልጥ አልችልም፡፡ የተለያዩ ኃይማኖቶች መኖራቸው አይደንቀኝም፡፡ ሰው እንደ ፍላጎቱ ነው፡፡  በአጋጣሚ ግን ለማንበብ ትገደዳላችሁ፡፡ በ2007 ዓ.ም. የተረጎምኩትና ‹ሁቱትሲ› የሚል ርዕስ የሰጠሁት የሩዋንዳዊቷ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ መጽሐፍ ንዑስ ርዕሱ ‹በሩዋንዳው ጭርጨፋ ውስጥ እግዚአብሔር ሲገለጥልኝ› የሚል ነው፡፡ ክርስትናን እንደሚሰብክም እሙን ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ስተረጉምና ለንባብ ሳቀርብ፣ ሲወደደልኝም የታዘበው አንድ መምህር ወዳጄ ‹የኛ አምላክ ባንተ ውስጥ አድሮ ተዓምር ሰራ› ብሎኛል፡፡ ያ ሌሎች ወንጌላውያን ጓደኞቹ ጸልየው ቀና እስኪሉ ድረስ ምግባቸው ላይ ጨው የመነስነሱን ሃሰብ ያነሳውና የተገበረው ባሕረኛ አሁን የኃይማኖት ሰው ሆኗል፡፡ ቆንጆ ፍለጋ የገባባት ቸርች አጥምዳ አስቀርታዋለች፡፡ ኦርቶዶክስንና አዲሲቱን ቤቱን በንጽጽር የሚያይ ብዕርም አለው፡፡ ያቺን ጣል ጣል፤ ይቺን ከፍ ከፍ፡፡ አንዲት እናት በዘመናቸው ስለታዘቧቸው ወጣቶች ሲነግሩኝ፣ ‹‹በጉብኝቱ ጊዜ ወጣቶቹ ሻርል ደጎልን ከፍ ከፍ፣ ጃንሆይን ጣል ጣል አደረጉ›› ያሉትን መሰል ብሎኛል፡፡ ዓለማየሁ 29 መጻሕፍት ያሉት ደራሲና ትጉህ የብዕር ሰው ነው፡፡ በብዕሩ ምን እንዳስተላለፈ ግን ሳናነብ ማወቅ አይቻለንም፡፡ ለሦስት ወራት ያህል ጊዜ ቀን ሙሉ ጻፍኩ ብሎ ስለመጀመሪያ ስራው ሳነብ እኔስ እንዲሁ አይደል ያደረኩት ብዬዋለሁ፡፡ ለመተዋወቂያ የሆነችኝን ይህችን መጽሐፉን ካነበብኩ ዘንዳ ወደፊት ሌሎች ዓለማዊ መጻሕፍት ካሉት ባነብ ደስታዬ ነው፡፡ እናንተም ይህንን መጽሐፍ እንድታነቡት ስጠቁም እንደ ሕይወት ታሪክ አፍቃሪነቴና ዳሳሽነቴ እንደምታተርፉበት በመተማመን ነው፡፡ የቋንቋውን ውበት ወዳጄ ይድነቃቸው ሰለሞን ለኔው ‹ያንተን ጽሑፎች እወዳቸዋለሁ፤ ምክንያቱን ግን እንጃ› እንደሚለኝ ሁሉ እኔም የዓለማየሁን አጻጻፍ የብዙ ነገሮች ጥርቅም ሳይሆን ባልቀረ ምክንያት እወደዋለሁ፡፡ አጫጭር ክፍሎቹም እንዳይሰለች ያደርጉታል፡፡  

 

2022 ኦክቶበር 12, ረቡዕ

ሳሲት በዕውቀት ጎዳና

 ሳሲት በዕውቀት ጎዳና

የጉዞ ማስታወሻ

በመዘምር ግርማ

ጥቅምት 2፣ 2015 ዓ.ም. 

 

ቅዳሜ መስከረም 28፣ 2015 ዓ.ም. ከደብረ ብርሃን ተነሳሁ፤ ወደ ሳሲትም ለመሄድ ወደ መናኸሪያ አቀናሁ፡፡ ‹የሕይወቴ ፈርጦች፣ እንደ መርከበኛ በባሕር፣ እንደ ጋዜጠኛ በምድር› የሚል ርዕስ ያለውን የዓለማየሁ ማሞን መጽሐፍ መኪና ውስጥ እያነበበብኩ ነው፡፡ ከሁለት ወራት በፊት መጽሐፍ እያነበበ እንዲሄድ ሃሳብ ያቀረብኩለትና መጽሐፍ ሰጥቼ የላክሁት ግሩም አስናቀ በሞላና በተጨናነቀ መኪና ውስጥ ስለተሳፈረ አለመቻሉን ስለነበረኝ ሰግቼ ነበር፡፡  የጃፓንን ምቹ የመንገደኞች ባቡሮች ሁኔታ አይቼም በእኛ ሁኔታ ተበሳጭቼ ነበር፡፡ ቀለል ባለው የተሳፋሪ ቁጥር ምክንያት ሳነብ የነበረበትን ሁኔታ በሚከተለው መልኩ ለፌስቡክ ህብረተሰብ አስተላለፍኩ፡፡ ‹‹የሁለት አንባቢያን ወግ - እኔ የአማርኛ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ስከፍት እርሳቸው የግእዝ የፀሎት መጽሐፍ መዝሙረ-ዳዊት አወጡ፡፡ ጮክ ብለው እያነበቡ ነው፡፡ በፀጥታ አነባለሁ፡፡ ዘግይተው ምን እያነበብኩ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ ስነግራቸው ‹እያንዳንዱ ሰው የሕይወት ታሪክ አለው› በማለት ጀመሩ፡፡ ለማናቸውም በሠላድንጋዩ መኪና ውስጥ እየተነበበ ነው፡፡ የዓለማየሁ ማሞ መጽሐፍ እጄ ከገባ ስምንት ዓመት ቢሆነውም በቅርቡ ደራሲውን ስለተዋወቅሁ አንስቼ ለማንበብ ቻልኩ፡፡›› መነኩሴው በጻድቃኔ ማርያም የሚኖሩ ሲሆኑ፤ ስለቤተክርስቲያን ህንጻና አስተዳደር ሁኔታ ብዙ አጫወቱኝ፡፡ እኔም ስለስራዬ ነገርኳቸው፡፡ በወለጋ መኖራቸውንና እዚያ ስላሉት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሁኔታም አውግተዋል፡፡

ሠላድንጋይ ከተማ ደርሼ ያየሁትን የልማት ጅማሮም ለወዳጆቼ በፎቶ አጅቤ አጋራሁ፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹የሠላድንጋይ የልማት እርምጃ - ዛሬ በሞጃ ቆይታዬ ከሰዓት በፊት በዘመድ ጥየቃና የከተማዋን ለውጥ በማገናዘብ ቆይቻለሁ፡፡ በከተማዋ ያሉት ባንኮች ሰባት እየደረሱ ነው፡፡ የሞጃ ህዝብ ትጋት እየጨመረ መሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ በሰብዓዊ መብት፣ በጦርነት ትውስታ፣ በኪነጥበብና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂጃለሁ፡፡››

ከአፍታ ቆይታ በኋላ የሞጃ ዘነበወርቅ ባህል ቡድን አባል የሆነው ይበል ወርቁ ወደ ቤቱ ይዞኝ ሄደ፡፡ በዚያም ያገኘኋቸውን ግለሰብ ጉዳይ እንደሚከተለው በማስታወሻዬ ያዝኩ፡፡ ‹‹የፍትሕ ያለህ- ወይዘሮ አዛለች ይባላሉ፡፡ በሀሰት ሰው መግደል ወንጀል ተፈረደባቸው፡፡ ሞተች የተባለችውና በሀሰት የተመሰከረላት ጠፍታ ቆይታ ስለመጣች በይቅርታ ተፈቱ፡፡ ሲፈቱ ሀብት ንብረታቸው በሃራጅ ተሸጦ አገኙት፡፡ የአገራችን ፍትሕ ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማሳያ ናቸው፡፡ በሠላድንጋይ ከተማ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በቤታቸው ስደርስ ያገኘኋቸው ስልክ ሲደዋወሉ ነበር፡፡ የሚያወሩትም የሚኖሩበት የቀበሌ ቤት ኪራይ ስለመጨመሩና መክፈል እንደማይችሉ ነበር፡፡ ከእማወራነት ወደ ጉልበት ሰራተኛነት እንዳወረዷቸው ነገሩኝ፡፡ ሕዝቡ በሰልፍ ወጥቶ ትገደል ሲል እንዳልነበር አሁን ንፁህ ሲሆኑ ምንም አላላቸውም፡፡ ያሳዝኗችኋል፡፡ ያላናገራቸው ሚዲያ የለም፡፡ ያገኙት ነገር ያለመኖሩን ግን ነገሩኝ፡፡ እንዳናግራቸው ለጠቆመችኝ አንዲት ወጣት ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ መፍትሔ ብንፈልግላቸው ጥሩ ነው፡፡ በተለይ የሕግ ባለሙያዎች፡፡››

ከወይዘሮ አዛለችና ከጌጤ ቤተሰብ ጋር ባለፈው ዓመት ስላሳለፉት የጦርነት ጊዜ ሁኔታም አውግተናል፡፡ እኔ ደብረብርሃን ሆኜ የጦርነት ስጋት ቢኖርብኝም እንደነሱ ለቀናት የመድፍ ጥይት ስላልተተኮሰብኝ የነሱን ታሪክ ፀጥ ብዬ ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ ሠላድንጋይ ማርቆስ አካባቢ ከሚገኘው ከእርሳቸው ቤት ወጥቼ ወደ ከተማዋ ስወርድ አንድ ባለ ግርማ ሞገስ አባት አየሁ፡፡ ይህንንም ጻፍኩ፡፡ ‹‹የሞጃው መስፍን - ሠላድንጋይ ማርቆስ አካባቢ ጌጤን ጠይቄ ወደ ከተማው ስወርድ እኝህን አዛውንት አየሁ፡፡ በራቸው ላይ ተቀምጠው ሲያስቡ ሳይ ባላባት መሰሉኝ፡፡ ይህን ገልጬ ስለፎቶ ሳወራ ይበል አስፈቀደልኝ፡፡ የተሰማኝን ነገርኳቸው፡፡

‹ጃንሆይ እኮ ዘመዴ ናቸው› አሉኝ፡፡

ጃንሆይ አጤ ምኒልክ?› ስል ጠየኳቸው፡፡

‹አጤ ኃይለሥላሴ› በማለት መለሱ፡፡

ተገረምኩ፡፡ ያቺን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያቸው የነበሩባትን ቅጽበት መልሰን ባናገኝም ፎቶ አነሣናቸው፡፡ የታሪክ ዕውቀታቸውን ያካፍሉን ያዙ፡፡ ያነበቡት ብዙ መሆኑን ነገሩን፡፡ ከእርሳቸው በዕድሜ የሚበልጡም መኖራቸውን ነገሩን፡፡ እርሳቸውንም ሌሎቹንም የመጠየቁንና የመጻፉን ሥራ አብረውኝ ለሚዞሩት የሞጀ ዘነበወርቅ የባህል ቡድን ሰጥቼ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡››

የሞጃና ወደራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆነችውን ሙሉጌጥ ጎርፉን ከቤቷ ጠርተን በእረፍት ቀኗ ቅዳሜ ቢሮ ገባችልን፡፡ በቢሮዋም ስለጀመሩት የማስነበብ ስራና ወደፊት በመስሪያቤቱ ግቢ ለመክፈት ስለታሰበው አነስተኛ የንባብ ቦታ ነገረችን፡፡ የባህል ቡድኑ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትንም ሁኔታ እንደሚነጋገሩ አሳወቁኝ፡፡ የባህል ቡድኑ አባላት ድጋፍ እንደሚፈልጉ፣ የአባላት መመናመን እንዳለባቸውና የቦታ እጥረት እንዳስቸገራቸው ነግረውኛል፡፡ የሥልጠናና ድጋፍ ዕድል ቢያገኙ እንደሚሹና አቅም ከተገኘ የባህል ቤት መክፈት እንደሚፈልጉ አጫውተውኛል፡፡ በቅርቡ ወረዳው በዞን ደረጃ የተከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን እንዳስተናገደ አስታውሰው በወቅቱ የሸለሙኝንና መገኘት ባለመቻሌ ያልወሰድኩትን ጋቢ አበረከተችልኝ፡፡ ከምስጋናና ውለታ በዛብኝ ከሚል አስተያየት ጋር ተቀበልኩ፡፡

ወደ ሳሲት ከሰዓት አቀናሁ፡፡ ወዳጅ ዘመድን ጠያየቅሁ፡፡ ቅዳሜ ስለሆነ ደማምቃለች፡፡ የገበያ ቀን ከሌሎቹ በላይ የደመቀ ነው፡፡ በየቦታው የሚወራው ገንዘብ መሆኑ የመጀመሪያው ምልከታዬ ነበር፡፡ በየቤቱ እየዞሩ መጋበዝ (ጋ ይጠብቃል)፣ ቡና፣ አረቄና ቢራ መጋበዝ (ጋ ይጠብቃል) ስራዬ ሆኗል፡፡ እሁድ ጠዋት ቀበሌው ከወረዳ የመጡ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ መኖሩን በማሳወቁ ለከሰዓት ያሰብነው ስብሰባ ምን ያህል ሰው እንደሚመጣበት መጨነቃችን አልቀረም፡፡ ጋቢውን ለእናቴ አሳይቻት መቋጨት እንዳለበት ነገረችኝ፡፡ በእውቅ የተሰራ እንደሚመስልና ቆንጆ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ ተቋጭቶ ወፍ እግር እንደሚሰፋ ስትነግረኝ እኔ እስከዛሬ ጋቢ ውሰድ ስባል ስለማልወስድ ነገሩ ብዙም አልገባኝም፡፡ ጋቢ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ስትነግረኝ አንድ ሰው ሲሞት አራት ጋቢ እንደሚያስፈልገው በማስረዳት ነው፡፡ ሁለቱ አስከሬኑ የሚሸፈንበት ሲሆን ሁለቱ የሚጋረድ ነው፡፡ በአሁኑ የገበያ ዋጋ አንድ ሰው ሲሞት አራት ጋቢ ማለትም የ6000 ብር ሀብት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡

እሁድ ጠዋት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የሞጃና ወደራ አባላት ወርሃዊ ስብሰባቸውን በህብረት ሱቁ ደጅ ተቀምጠው ሲያካሂዱ አየኋቸው፡፡ ሰላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ንግግርም እንዳደርግ ጋብዘውኝ ተናገርኩ፡፡ ያለ ሥራ የተቀመጠውን የቀበሌውን አዳራሽ ተንከባክበው ለመያዝና ለስብሰባና ስራቸው ለማዋል ጥያቄ እየጠየቁ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ አዳራሹንም ጎበኘሁት፡፡ በጣም ቆሽሿል፡፡ እኔም ምናልባት ለነሱ ቢሰጥ ለኛ የመጻሕፍት ውይይት ክበብም መወያያ ይፈቅዱልናል ብዬ አሰብኩ፡፡ በኋላ እንደተረዳሁት ግን ቀበሌው ራሱ የስብሰባ አዳራሽ ስለሌለው ይህንኑ መንከባከብ ይኖርበታል፡፡           

ለከሰዓቱ ስብሰባ ሰዎችን በአካል፣ በፌስቡክ፣ በስልክና በመልዕክት ስናስታውስ ቆየን፡፡ ሰዓቱም ሲደርስ እንደተሰጋው የቀበሌው ስብሰባ ስለነበር ሰዎች አልወጡም ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ሄደን ተማሪዎች ስለመጡ ስራ ከመፍታት በማለት ‹ከገንዘብና ከዕውቀት› በሚል ርዕስ ክርክር አደረጉ፡፡ ይህን ርዕስ እኔም ያሰብኩት ሲሆን ተማሪዎች ሳልጠይቃቸው እሱኑ መምረጣቸው አስደስቶኛል፡፡ ስለ ሳሲት ቡክ ክለብ ሁለት ጊዜ በፌስቡክ ላይቭ ቃለመጠይቅ ያደረኩለት ዮርዳኖስ ግሩም በክርክሩ ተሳትፏል፡፡

መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች በአጠቃላይ 22 ሰዎች ተገኝተው ውይይቱ ተጀመረ፡፡ በመጀመሪያ ስለ መጻሕፍት ውይይት ክበብ ምንነትና አሰራር የሳሲት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ-መምህር ፀጋ ገለጻ አደረጉ፡፡ በመቀጠል ግሩም አስናቀ ስለ ሳሲት ቡክ ክለብ አጀማመር ሃሳቡን አቀረበ፡፡ በሁለቱም ሃሳቦች ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡ ቀጥሎ ለዕለቱ መወያያ በተመረጠው ‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ› በተባለው የኔ መጽሐፍ ላይ ተወያያን፡፡ ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ ያቀረበው ክብሩ ማሞ ሲሆን እርሱም ከንባቡ ያቀረበውን ከማጋራት በዘለለ ከእኔ ጋር በጥያቄና መልስ መልኩ ውይይት አድርጓል፡፡ ከዚያም ለቤቱ ክፍት ተደርጎ ተወያይተናል፡፡ በመቀጠል በዝግጅቱ ተሳታፊ የሆኑት አብዛኞቹ ተማሪዎች በቅርቡ የደብተር እገዛ ያገኙት በመሆናቸው ከሠው ለሠው በጎ አድራጎት ክበብ ተጠሪ  መምህር አበበ ሃሳብ ቀርቦ ለወደፊቱ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሚሰሩበትንና ራሳቸውን የሚደግፉበትን መንገድ እንዲሁም በትምህርታቸው ጎበዞች የሚሆኑበትን ጉዳይ ተነጋግረናል፡፡ ዕድሎች ውሱን በሆኑባቸው እንደ ሳሲት ያሉ ቦታዎች ተስፋ ያላቸው ልጆች መኖራቸውን ከተረዳሁባቸው ሁኔታዎች አንዱ በዕለቱ ተሳታፊ የነበረው ተማሪ ቶማስ ብርቅነህ በፈጠራ ስራ ከዞን አንደኛ፣ ከክልል ሦስተኛ ወጥቷል መባሉ ነው፡፡ የዕለቱ ዝግጅትም በአጠቃላይ አስደሳች በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ ነበር፡፡

በማግስቱ ሰኞ ጠዋት ወደ ሳሲት ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄጄ ከአስተዳደሩና ከቋንቋ መምህራን ጋር እንግሊዝኛ ክበብ እንዲጀመር ሃሳብ አቅርቤ መተጋገዝ በምንችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተነጋግረናል፡፡ የተማርኩበትን ትምህርት ቤት መጎብኘቱ፣ ተማሪዎችን ማየቱ፣ ስለትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ማየቱ ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱም በመሄድ ተመሳሳይ ውይይት ከእንግሊዝኛ መምህር ጋር አድርጌያለሁ፡፡

ሰኞ ከሰዓት ብዙ ሰዎች ወደ ለቅሶ የሄዱበት ስለነበር ከተማው ለተወሰነ ጊዜ ጭር ብሎ ነበር፡፡ ሲመለሱ በዘመዶቼና ወዳጆቼ ጋር ስለምሰራቸው የበጎፈቃደኝነት ስራዎች በግል ለመወያየትና ሃሳብ ለመቀያየር ችያለሁ፡፡ ማክሰኞ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ የሳሲት ቡክ ክለብ ውይይት በየወሩ መጨረሻ እሁድ ስለሚቀጥል እገኛለሁ፡፡  

በአማራ ክልል ከተሞች ንባብን፣ ዕውቀትንና የበጎፈቃደኝነትን  የማስፋፋት ሙከራችን ላይ የሞጃ/ሳሲት የሦስት ቀናት ቆይታዬን አስመልክቼ የጻፍኩት ይህ ጽሑፍ ዋና ዋና ነጥቦችን የሚነካካ እንጂ ሁሉንም የሳሲት ትዝብቶቼን የያዘ አይደለም፡፡ 

 

 













በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...