2017 ጃንዋሪ 10, ማክሰኞ

የፈረንጁ ተልዕኮዎች - ከሠሞኑ ጉዳይ ጋር የሚሄድ ልቦለድ ታሪክ





መቼም አሜሪካዊ ሆኖ እንጓዝ ከተባለ እምቢ የሚል አይኖርም - እንደውሃ መሄድ ልምዳቸው ነውና፡፡
ከመሐል ሜዳ ሸሾ ድረስ ያለው መንገድ በጣም ሩቅ ነው፡፡ ቢሆንም ያን ሁሉ መንገድ ግማሹን በመኪና ግማሹን በእግራቸው  ለመሄድ ተዘጋጁ፡፡ መንዝ ብዙም ለዓይን የሚስብ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ልማት የለውም፡፡ ያንንና ሌሎችንም እያወሩ በእግራቸው ሄዱ፡፡ ከቆሎ ማርገፊያ ወዲያ ያለው የእግር መንገድ አሰልቺና የመንዝን እርቃን የሚያሳይ አሳባቂ ነው፡፡
መንገድ ላይ ልትስመው ትፈልጋለች፤ ልትላፋው ትጥራለች፡፡ እሱ ግን ግድም አልሰጠውም፡፡ ‹‹ምን ነካው!›› የሚል ዓይነት ጥያቄ አጭሮባታል፡፡ ‹‹ያለወትሮው ደግሞ ምን አኮራው!›› የሚል ሃሳብ በአእምሮዋ ቢመጣም በዚህ ሰው ዝር በማይልበት መንገድ ላይ ምንም ጥያቄ አንስታ ልትጨቃጨቀው አልፈለገችም፡፡ በሰው አገር የሰው ሆዱ ምን ይታወቃል?
እሱ በመሐልሜዳ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ሲሆን፤ እሷ ደግሞ ከአሜሪካ በበጎ ፈቃደኝነት የመጣች ጥቁር አሜሪካዊት ነች፡፡ ከጥቁር ይልቅ አፍሪካን አሜሪካን ሲሏት ነው ደስ የሚላት፡፡ ሄደው ከእናቱ ቤት ደረሱ፡፡
መንገድ ላይ ፍዝዝ ብሎ ሲያስብም ሆነ በተደጋጋሚ ፊት ሲነሳት አንዳንዴም ከንፈሩን ሲነክስ ምን ሆነ ብላ አስባለች፡፡ ጓደኛዋ ያለወትሮው አልሆን ስላላት በዚህ ‹‹ያልሰለጠነ›› አገር ነጻነትና ስለ ሕልውናዋ ዋስትና አልተሰማትም፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በሚሰራበት መስሪያ ቤት በሚገኘው የመምህራን ቢሮ በር ላይ አንድ ልጅ ቆሞ ‹‹ጋሼ ሀብቱ አሉ?›› ይላል፡፡ ተማሪው ቢሮ መፈለጉን ሊነግረው ከርዕሰ መምህሩ ዘንድ የተላከ ልጅ ነው፡፡ ርዕሰ መምህሩም በታማኝነቱና እንግሊዝኛም እንደሚሞካክር በማወቃቸው ሀብቱን ወደ አዲስ አበባ ለአንድ ተልዕኮ ሊልኩት እንደሆነ ነገሩት፡፡ አዲስ አበባ ሄዶም በጎ ፈቃደኛዋን ከፈረንጆችና ኢትዮጵያውያን አስተባባሪዎች ተረክቦ ትልቅ አደራ ተሸክሞ መጣ፡፡
አሜሪካዊቷ ካሏት ድብቅ አላማዎች አንዱ መጥበስ ነው፡፡ ወንድ ጓደኛ መፈለግ፡፡ ከዚህ ሌላ ማድረግ እንደሚያስቀስፋት ታውቃለች፡፡ ሌላውን ለሌላ ጊዜ ለራሷ የቤት ስራ ሰጥታ ለአሁኑ ይህንን መምህር በፍቅር ወጥመዷ ውስጥ አስገባችው፡፡ መንዝ ካሉት ሴቶች ያነሰ ውበት ስለነበራት በመጀመሪያ ያልተሸነፈላት ይህ ለፍቅር አዲስ የነበረ ወጣት መምህር ተሸነፈ፡፡ ‹‹የሴት ልጅ ልቧ ከንፈሯ ላይ ነው›› የተባለው ለወንዶች የተነገረ ይመስል ገና ስትስመው ልቡ ፍስስ አለች፡፡
በመሐል ሜዳ ብርድ የሷን ፍላጎት ለማሟላት ማታ ማታ ከከተማው አንደኛው ወደሌላኛው ጠርዝ  የእግር ጉዞ አብሯት ያደርጋል፡፡ የሰው አፍ እንደእሳት በላኝ ብሎ ያስባል፡፡ በሳይክል ወደ ሃያ ኪሎሜትር ወደሚርቀው ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ አብሯት ይሄዳል፡፡ እሱ ራሱን ለማዝናናትና እሷን ለማጀብ ሲሆን፤ እሷ ደግሞ በዚያ ያሉ በእንስሳትና እጽዋት ሀብት ላይ የሚመራመሩ አሜሪካውያንን በካምፓቸው ለማግኘትና የሆድ የሆዷን ለማውራት ስለምትፈልግ ነው፡፡ በቃ እነዚህ ደግሞ አንዴ ከገጠሙ ይልና የጓሳን ጥብቅ ስፍራ በሳይክል ሲዞር፣ ዝንጀሮ፣ ቀበሮና አይጥ ሲያይ ይውላል፡፡ የጓሳውን ምድር ሽታ ይናፍቀዋል፤ ሰላም ከከተማ ወጥታ እዚያ የተደበቀች ይመስለዋል፡፡
ድሮም አንድ አንድ አሜሪካዊ የማያጣውን መንዝ ይህች ልጅ - ሊዛ ሲንግልተን - ትንሸራሸርበት ይዛለች፡፡ ትምህርት ቤቱም ከተለመደው አሰራሩ በመጠኑ ለየት ያሉ አሰራሮችን ጨምሯል፡፡ የእንግሊዝኛ ክበቡ በጣም ተጠናክሯል፤ መምህራን በቋንቋ ስልጠና እየታገዙ ነው፡፡ አንዳንድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ ጊዜ አጠቃቀምንና የማንበብ ልምድን የመሳሰሉትን ከአሜሪካዊቷ ለመኮረጅ የሚሞክሩ እየበዙ ነው፡፡  
ሀብቱ ከዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ ልቦለድ ላይ ‹‹እንግዲህ ምን አውቃለሁ … በእንዴት ያለ መንገድ ቅኝ አገዛዛቸውን ሊቀጥሉ እንደሚፈልጉ ነጮች›› የሚለውን የአደፍርስን ንግግር ሸምድዶ ሁሌ ሰው አጥብቆ ሲጠይቀው ይናገረዋል፡፡ ለማናቸውም እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው አልገባ ብሎታል ሀብቱ፡፡ ሙሉጌታ ኢተፋ የተባሉ ደራሲም የአሜሪካ ቆይታቸውን በተረኩበት ዘ ቢተር ሃኒ በተባለው መጽሐፋቸው በበጎ ፈቃደኝነት ስም የሚመጡት ሰዎች የአገሪቱ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ መልምሎ የሚያሰለጥናቸው አባላቱ እንደሆኑ የጻፉትን አንብቧል፡፡ በቅርቡ ያነበበው በዊኪሊክስ አፈትልኮ የወጣ ፋይልም ኢትዮጵያ ያለ ማናቸውም አሜሪካዊ ሰላይ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ አንድ ዘመዱን አዲስ አበባ አግኝቶ ጠይቋቸው ግን ‹‹ልጄ ልሙትልህ ፕሬዚዳት ኬኔዲ የኢትዮጵን ሕዝብ በቅንነት ለመርዳት ያቀዱት ነው፡፡ ምንም ሌላ ተልዕኮ የለውም›› ብለውታል፡፡
‹‹አሁን እኛስ ብንሆን አሜሪካ ሄደን ስለአገራነችን መጥፎ ሊደረግ ነው የሚል ነገር ብንሰማ ዝም እንላለን?›› እያለ ራሱን ያጽናናል፡፡ አገራቸውን የሚጎዳባቸውን ነገር መከታተል ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ዓላማ የሰውን አገር የሚጎዳ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉም ይገምታል፡፡ እሱንም እየሰለለችውና የመረጃ መሰብሰቢያ እያደረገችው እንደሆነ ይጠረጥራል፡፡ ራሱን እንደከሃዲ የሚቆጥርበትም ጊዜ አለ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት መቼም መጥፎ ይሰራሉ ብሎ ቢያስብ አያስገባቸውም ነበር›› ብሎም ሳያስብ አልቀረም፡፡
በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ወቅት ይግባባቸው የነበሩት ሕንዳዊ መምህሩ በሀገሩ ላይ የአሜሪካ ተጽዕኖ መብዛቱ በጣም እንደሚያሳዝናቸው ነግረውት ወደፊት ግን ይህን ለመቀልበስ መሰራት እንዳለበት አሳስበውት ነበር፡፡ ‹‹ሕንድ በፍጹም አሜሪካውያንን ወደ ፖለቲካዋ አታስገባም›› ያሉትን አይረሳም፡፡ ‹‹ብናስገባ እንደ ሽንት ቤት ወረቀት ተጠቅመው እንደሚጥሉን እናውቀዋለን፤ እስኪ ኢራቅንና አፍጋኒስታንን እይ!››
በዚህ ሁሉ መሀል የወደዳት የዚህች ልጅ ነገር ይከነክነዋል፡፡ መቼም አንድ ጊዜ ተነካክቷል፡፡ ‹‹ወይ አሜሪካ ትወስደኝ ይሆናል›› እያለም የተመኘበት ጊዜ አለ፡፡ እዚያ ሄዶ እንደሁኔታው አብሯት ለመኖር ወይንም ትቷት ላሽ ለማለት አስቧል፡፡ እቤታቸው በተሰቀለው የቀን መቁጠሪያ ላይ ሳይቀር የኖሯቸውን ቀናት እየሰረዘ አሜሪካ ለመሄድ የቀሩትን ቀናት ይቆጥራል፡፡ እንደ እርጉዝ አድርጎታል፡፡ የምን እርጉዝ ነው ደሞ? ይቺ ልጅ አታስረግዘው!
ዘ አዲስ ኦብዘርቨር የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ‹‹አሜሪካዊቷ መንዝ ውስጥ ታግታለች›› የሚል ዘገባ ይዞ ከወጣ ወዲህ ነገሮች በጣም ተካረዋል፡፡ በሁለቱ መንግስታት በጋራ የሚመራ ግብረሃይል ተቋቁሞ መንዝን ያስስ ይዟል፡፡ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፍለጋው ተጧጡፏል፡፡ ልጅቱ ያለችበትን ላወቀ የሚሰጥ ገንዘብ ግን የአሜሪካ መንግስት ቃል አልገባም፡፡ በአገሪቱ ህግ ይህን ማድረግ አሸባሪዎችን የበለጠ ስለሚያጠናክር አይበረታታም - ወንጀልም ነው፡፡
መንዞች ደርግ በአውሮፕላን ስለደበደባቸው አውሮፕላንም ሆነ ማናቸውንም በሰማይ ላይ የሚበር አካል ይፈራሉ፡፡ አሁን ሄሊኮፕተሮች መንዝን ያስሷት ገቡ፡፡ ድሮኖችም በፍለጋው ተሰማርተዋል፡፡ ህዝቡም እንዳሞራ ይቆጥራቸው ይዟል፡፡ ከየማሳው ዳር ሄሊኮፕተሮች እያረፉ ገበሬዎችን ይጠይቁ ይዘዋል፡፡ የመሐልሜዳው ትምህርት ቤት መምህራንና ማህበረሰብ፣ የልጅቱ ቤት አከራዮችም ሆኑ ጓሳ ላይ ያሉት አሜሪካውያን ይታመሳሉ፡፡ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር መጥፋቷን የሚጠቁሙ መረጃዎች የደህንነት ባለስልጣናት አግኝተዋል፡፡ ግን ወዴት ጠፉ ነው ጥያቄው፡፡ አሜሪካዊቷን የሚያውቋት ሰዎች በአንድ መሐልሜዳ ባለ ጠጅ ቤት ስለጉዳዩ ያወራሉ፡፡ ‹‹አሁን ይችን ባሪያ የአሜሪካ መንግስት ፈልጓት ይሆን? ጠብሶስ ቢበላት ምን ቸገረው? የያዘችው የስለላ መረጃ ይኖራል እንጂ? ደሞ ለጥቁር ምን አስጨነቃቸው! የማናውቃቸው!›› ይላል አንድ የቀድሞ ወታደር፡፡ ጡረተኛው ወታደር ብዙም ለሕይወቱ ስለማይሰጋ ነው እንጂ ሰላይ እንደ አፈር ሞልቶበታል በሚባለው ከተማ ማንም ደፍሮ ስለዚህ ጉዳይ አያወራም፡፡
ሀብቱ በቤተሰቦቹ ቤት አቅራቢያ ባለ ዋሻ አጠገብ እንደታየ የአካባቢው ሰዎች ጥቆማ ሰጡ፡፡ ለመሾምና ለመሸለምም ተጣጣሩ፡፡
‹‹አሁን ሆድሽን ሳልዘረግፈው እውነቱን ታወጫለሽ አታወጪም?›› እያለ ጩቤውን እያሳየ ዋሻ ውስጥ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ያሽቆጠቁጣታል፡፡ ‹‹እዚህ አገር ለምንድነው የምትላኩት?› ዓላማችሁስ ምንድነው? ባለፈው ከጓደኞችሽ ጋር በስፓኒሽ ስታወሩ ቋንቋውን አያውቅም ብላችሁ ነበር?›› እያለ ወጥሮ ይዟታል፡፡ ጎንደር አስጎብኚ ለሆነ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብሮት ለተማረ የቅርብ ጓደኛው ከጓደኞቿ ጋር ሲያወሩ የቀረጸውን ኦዲዮ ልኮለት ትርጉሙ ባለፈው ሳምንት ነው የደረሰው፡፡ ‹‹በሀገሬ ላይ የምታደርጉትን አውቃለሁ›› አላት እንባው እየፈሰሰ፡፡ በስፓኒሽ ካወሩት ውስጥ ወንዶቹ አሜሪካውያን ወንድ ኢትዮጵያውያን ፍቅረኞች እንዳሏቸው ያወራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መጤ ሳይሆን ነባር እንደሆነ ህዝቡን ማሳመን እንዳለባቸው ያቅዳሉ፡፡
ሊጨክንባት እንደሚችል በመገመት ሁሉንም አፍረጥርጣ ነገረችው፡፡
‹‹እሺ እኔንስ የሰራሽኝ ጉድ?›› ብሎ አንድ ከእናቱ ጋር የቆመ ልጅ ፎቶ አወጣ፡፡ የዚያን ጊዜ ይህች ልጅ የምትገባበት አጣች፡፡ አለቀሰች፡፡ ትንቀጠቀጥ ያዘች፡፡ የሀገሯን ምስጢር የነገረችው በሆነ መንገድ ከዚህ ቦታ ከወጣች ይህን ሰው የምታስወግድበትን መንገድ አስባ ነበር፡፡ አሁን ግን መውጫ ቀዳዳ የሌለውን ነገር አመጣባት፡፡
አንድ ቀን አንዳንድ ነገሮችን እየተጠራጠረ ሲመጣና በተመሳሳይ ጾታና ተያያዥ መጤ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋም ሲያይ የፌስቡክ የይለፍ ቃሏን ያውቅ ስለነበረ እስካሁን ድረስ በፌስቡክ የተላላከቻቸውን መልዕክቶች ሁሉ ወደኮምፒውተሩ አውርዶ ያዘ፡፡ ከዚያም የልጅነት ፎቶዋን አገኘው፡፡ ስምንተኛ ክፍል ሳለች የተነሳችው፡፡ ያኔ ወንድ ነበረች፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ተመጣጣኝ ሕክምና ወደሚገኝበት ወደ ሕንድ ሄዳ ሙሉ በሙሉ ጾታዋን አስቀየረች፡፡ ወንድነትን ፈጽሞ አትፈልገውም፡፡
ማይክል ጃክሰን ወደ ነጭነት መቀየሩን ያውቃል፡፡ በልጅነቱ ቡዳ የበላቸው ሰዎች ወደ እንስራነት እንደሚቀየሩና እንደሚሰወሩ ከመስማቱ በቀር ይህን ዓይነት ጡት የሚያበቅልና ሁለመናን ሴት የሚያደርግ ነገር አልሰማም፡፡ እንዴት ይጠርጥር?
ይህን ሁሉ ጉድ ካወጣ በኋላ፡፡ ‹‹ገደል ከምሰድሽ በፊት የምትናገሪው ነገር አለሽ?›› ሲል ጠየቃት፡፡ ‹‹ያለሁበትን ሁኔታ ተረድተህና እኔም አፍሪካዊት እህትህ እንደሆንኩ አስበህ ይቅርታ አድርግልኝ›› አለችው፡፡ ከአሁን በኋላም እንደማትሳሳት ቃል ገብታ ወደ ገዳም አብረው እንዲመንኑ ነገረችው፡፡ እኔ እንዳንቺ ያለን ከሃዲ ገዳም አልወስድም ብሎ የተፈጸመውን ለማንም እንዳትናገር አድርጎ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ ጉዳያቸውም በሚገርም አዘጋገብ ተዘገበ - ለማንም ሳያሳውቁ ጉብኝት ሄደው የነበሩት ጥንዶች ተገኙ፡፡  በ24 ሰዓታት ውስጥም ይህች/ይሀ አሜሪካዊ ስፍራውን ለቆ/ቃ እንዲ/ድትሄድ ተደረገ፡፡ የደረሰበ/ባትን ግን ለማንም ትንፍሽ አላለ/ችም ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ማተሚያ ቤት የገባ ‹‹ድብቁ የአጋች ታጋች ድራማ በሐበሾች ምድር›› የሚል መጽሐፍ ጽፎ/ፋ መግቢያውን ጻፍልኝ ሲል/ስትል የመጽሐፉን ሶፍት ኮፒ ለመንዜው መምህር ላከ/ችለት፡፡
‹‹መጽሐፉን በነጻ በኢንተርኔት ልልቀቀውና ላክስራት ወይንስ እንዳሰበችው መግቢያ ልጻፍላት?›› እያለ ይብከነከናል፡፡ ራሱን በራሱ ለማዋረድ ይፍቀድ ወይንስ ምን ይሻለዋል ትላላችሁ?
‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› ብሎ ጨክኖ ይጻፍላት ወይ? በ1977 እኤአ አሜሪካውያኑን ጠራርገው እንዳስወጧቸው እንደነ መንግስቱ ኃይለማርያም አይነት ወኔ አምጥቶ ይጨክንባት? ‹‹ ዛሬ አገሪቱ ለአሜሪካ እጅ ሰጥታ ከጉያዋ ተደብቃ ሳለ የኔ እምቢተኝነት የምን ይሉታል?›› እያለ እያንገራገረ ነው፡፡  
ይቺ ሴት ቢያንስ እንግሊዝኛ ያሰለጠነችውንና ዘመናዊነትን ያስተማረችውን እንዴት ይዘነጋዋል? እሱን ለመጉዳት ብላ ያደረገችው ነገር ነበር እንዴ? መንዝ ላይ በ2500 ብር ደምወዝ በዚያ ብርድ ተሰቃይታ ህዝቡን ያገለገለችውንስ? ለሷ መግቢያውን ከጻፈላት እሱም ሲጽፍ የቆየውን ማስታወሻውን ማሳተምና ለሀገሩ ሕዝብ ማጋራት ይችላል፡፡ አሜሪካንን ለመጎብኘት ያቀረበችለትንም ሀሳብ ይስማማበት ይሆናል፡፡ መጽሐፉንም አብረው ሊያስመርቁም ይችላሉ፡፡ የሱንም መጽሐፍ ህትመት ስፖንሰር ልታደርግለት ትችላለች፡፡ ነገሩ ሁሉ እርቃኑን ሲያስቀረው ተበሳጭቶ የሚገባበት አጥቶ ራሱን ቢያጠፋስ?


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...