ቅዳሜ 4 ፌብሩዋሪ 2017

ከጠባሴ እስከ ሽሮ ሜዳው የአሜሪካን ኤምባሲ (የሥራ ፈጠራ ውድድር ማስታወሻዬ)




1. ኦባማና አፍሪካ
ባራክ ሁሴን ኦባማ ሊመረጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉም ሆነ ሲመረጡ አስታውሳለሁ፡፡ አፍጋኒስታን ሄደው እዚያ ላለው የአሜሪካ ጦር ንግግር እንዳደረጉ በ2001 ዓ.ም. እጄ ይገባ በነበረው ጋርዲያን ጋዜጣ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች መረዳጃ ማህበር ያስቆጠበኝን ገንዘብ አውጥቼ ቴሌቪዥንና ዲሽ ገዛሁ፡፡ በጥር ወር መጀመሪያ 2001 ዓ.ም ያስገባሁት ቴሌቪዥን ዓላማው የኦባማን የበዓለ-ሲመት ንግግር መስማትና የእንግሊዝኛ ማሻሻያ ሙከራዎችን ማድረግ ነበር፡፡ ፊልም ባለመውደዴ፣ ቢቢሲና አልጀዚራም ስለኢትዮጵያ ባለማንሳታቸው ወይም በየአምስት ደቂቃው ‹‹ዋና ዋና ዜናዎች›› የሚል አንባቢ በቴሌቪዥን መስኮቱ ብቅ በማለቱ ስለጠላሁት ቴሌቪዥንና እኔ ተለያየን - ለዘመድ ሰጠሁት፡፡   (የቴሌቪዥን ታሪኬን ለማንበብ ጉግል ላይ ‹ቴሌቪዥን ሳሲት እንዴት እንደገባ› ብለው ይፈልጉ)

ኦባማ ለአፍሪካ ቃል ገብተው ያልፈጸሟቸው ብዙ ነገሮች በመኖራቸው የተቀየሟቸው የአህጉራችን ሰዎች ሳይበዙ አይቀሩም፡፡ ከአሜሪካዊ መሪ አፍሪካ ብዙ ልትጠብቅ ላይገባት ይችላል፡፡ ጋናን፣ ኬንያንና ኢትዮጵያን እንደጎበኙ የምናስታውሳቸው ኦባማ ከተለመደው የዲፕሎማሲ ወሬ ሌላ የፈየዱት የለም እንል ይሆናል፡፡ አፍሪካ ህብረትም የተናገሩትን ሰማን፡፡ በሃገራቸው ውስጥ ብዙ ፈተና የሚገጥማቸው ኦባማ ለአፍሪካ እንዳሰቡት ለመፈጸም ላይችሉ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ ዋሽንግተን ላይ ስለ ኦባማ ዘመን መጽሐፍ የጻፉ አሜሪካዊት ከአፍሪካ አንጻር የኦባማ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚሉት ‹‹ያሊን›› ነው፡፡ ወደኋላ እንመጣበታለን ያሊን፡፡

2. ኦባማን የምናስታውስባቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ሀ. ባህርዳር ላይ በስማቸው ካፌ መከፈቱን በአሜሪካ ድምጽ ሰምቻለሁ፡፡
ለ. ልደታ ባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ የእንግሊዝኛ ማሻሻያ መርሃ ግብር ስከታተል በዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት ባለ ሆቴል አንድ ሰው ድራፍ ሲያዙ ‹ኦባማ› አድርጊልኝ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ጠይሙን የሀረር ቢራን ምርት መሆኑ ነው፡፡
ሐ. አጎቴ ከሳሲት መጥቶ ‹‹አንተዬ ኦባማ እኮ በቃ በሬ ሆነ›› አለኝ፡፡ ‹‹ደሞ ምን በሬ ይሆናል ለራሱ መሪነት አማሮት›› ስለው እንዳልተግባባን አይቶ ‹‹አይ ኦባማ መኪናውን እኮ ነው፤ እያንዳንዱ ገበሬ እደጁ አንድ ኦባማ አቁሟል›› ሲለኝ ገባኝ፡፡
መ. ኦባማ በአልባሳት ላይም ነግሶ ነበር፡፡
እርስዎስ በምን ያስታውሷቸዋል?

3. ‹ያሊ› ምንድነው?
ቢያንስ አንድ ኦሮምኛ የሚችል ሰው ያሊ ለሚለው ቃል አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን ማለቴ ቃሉ በቋንቋው ትርጉም ስላለው ነው፡፡ ያሊ ማለት ሞክር ወይም ሞክሪ ማለት ነው፡፡ ኦባማ ያስጀመሩትም ‹ያሊ› አፍሪካውያን ወጣቶች የሚሞክሩበትን ዕድል ያቀረበ ነው፡፡  በመንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አመራር፣ በመንግስት ስራ አመራርና በሥራ ፈጠራ የወጣቶችን ብቃት ለማጎልበት የተዘረጋ ነው ያሊ ማለት፡፡ ዘንድሮ በኤሌክትሪክ ኃይልም ሊያሰለጥን ነው፡፡ ከ25 እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ያሉ አፍሪካውያንን ያሳትፋል፡፡ ውድድር ግን አለው፡፡ ዘንድሮ ስለተወዳደርኩበትም ያንን የውድድሩን መንገድ ነው አብረን እንድንጓዝ የፈለኩት በዚህ ጽሑፍ፡፡ በአማርኛ መጻፌም በአብዛኛው በቋንቋ ምክንያት በያሊ ድረገጽ /yali.state.gov/ ላይ ያለውን ገጸበረከት መጋራት ለማይችሉ ኢትዮጵያውያን በሩን ለመክፈት ነው፡፡

4. የፈረንጅ አገር ናፍቆት
‹‹ያላዩት አገር አይናፍቅም›› የምንለው ብሒል የማያስማማው እዚህ ላይ ነው፡፡ ያላየነውን ፈረንጅ አገር የምንናፍቅ ብዙዎች ነን፡፡ የአሜሪካ ወታደር መሆን ሳይቀር የሚመኙ የሥራ ባልደረቦች አሉኝ፡፡ አሜሪካና ስኮላርሺፕ የሚሉትን ቃላት በቀን ሳያነሱ የማይውሉም አሉ፡፡ ልባችን እንዲህ በተጠንቀቅ ስላለ ይመስለኛል አገራችን ላይ ይህ ነው የማይባል ሥራ የማንሰራው፡፡ መሰደድን የሚያስመኝ ቀን የለም ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ መጀመሪያችንም መጨረሻችንም እዚሁ ነው ብለን ካመንን ግን የማይመቹ ሁኔታዎችን ልንቀይር እንችል ይሆናል፡፡ በአስተዳደር፣ በምጣኔ-ሐብት፣ ለኑሮ በመመቸት፣ ረክቶ በመኖር አገራችን ወደፊት ለ50 ዓመታት ለውጥ ማምጣቷን እጠራጠራለሁ፤ እርስዎስ?  ይሁን እንጂ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዲቪ የሞላሁት የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ በ1997 ነው፡፡ ስኮላርሺፕ የሞከርኩት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ ስልጠና፣ ስብሰባ ወይም ጉብኝት ካልሆነ ፈረንጅ አገር ለመሄድ አልፈልግም፡፡ ‹‹የሞጃው ተወላጅ›› የሚለውን የባሻ አሸብርን ዓይነት ኩራት አይመስለኝም የተጠናወተኝ፡፡ የባላባት ስነጽሑፍ (ኢትዮጵያን ሊትሬቸር) እንዳስተምር በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መታዘዜም ላይሆን ይችላል የችግሩ ምንጭ፡፡ አሁን ኩራት አይሆንም ራት ያልኩ ይመስላል!

5. ሞክረው ሞክረው
ወዳጆቼ በስልክም በኢንተርኔትም ያሊን እንድሞክረው ነገሩኝ፡፡ ባለፈው ዓመት ነግረውኝ አይሆንም ይቅርብኝ ብዬ ነበር፡፡ ዘንድሮ ሞከርኩት፡፡ ደብረብርሃን ላይ እንዲሞክሩት የገፋፋኋቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ የውድድር ጥያቄዎቹ ተመሳሳይነት ነበራቸው፡፡ ለሁሉም ጥያቄዎች የጽሑፍ መልስ በእንግሊዝኛ መስጠት ግድ ይል ነበር፡፡ እየጻፍኩ ያጠፋኋቸውና የቀየርኳቸው መልሶች ብዙ ናቸው፡፡ ለወዳጅ ዘመዶቼ አሳይቻለሁ፡፡ አሜሪካውያን የሚወዱና የሚጠሉትን የአርሲው ተወላጅ ኦቦ አማን ቃዲሮ ነግሮኛል፡፡ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሬኮሜንዴሽን ሌተር እንዲጽፍልኝ ለመጠየቅ የምችለውና ፊት የማይነሳኝ እሱ ብቻ ስለሆነ ጠየኩት፤ ጻፈልኝ፡፡ የጻፈልኝንም ሆነ ሌሎች ፋይሎችን ለመላክ በወቅቱ ኢንተርኔት በጣም ደካማ ስለሆነ አልቻልኩም ነበር፡፡ ኢንተርኔት ፍለጋ ኤቫ ሆቴል ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብዬ ውያለሁ፡፡  አሁን የመጀመሪያዎቹን ስድስት ጥያቄዎችና የኔን መልሶች እንመልከት፡-
1. ምን እንደሚሰሩ ይግለጹ፡፡ ለምን ይህን ሥራ መረጡት?
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደማስተምር፣ የማሕበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎዎች እንዳሉኝና በተጨማሪም ቤተ-መጻሕፍት በግሌ ከፍቼ እንደምሰራ ጻፍኩ፡፡
2. ማሕበረሰብዎን ለማሻሻል ምን እያደረጉ ነው?
ከንባብ በሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት የአካባቢዬ ነዋሪዎች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲለውጡ አድርጌያለሁ፡፡ የመጽሐፍ ውይይት፣ የቋንቋ ትምህርትና ተዛማጅ አገልግሎቶቻችንም ማህበረሰቡን ያበለጽጋሉ፡፡
3.  በመጪዎቹ 10 ዓመታት በማህበረሰብዎ ምን ሚና ለመጫወት ይፈልጋሉ? አሁንስ ያንን ለማሳካት ምን እያደረጉ ነው?
ከአስተማሪነቴ ጎን ለጎን በገቢ ማመንጫዎች ላይ እሰማራለሁ፡፡ የዕደ ጥበብ ስራና የማስጎብኘት ስራ በመጀመር በማገኘው ገቢ የቤተመጻሕፍቱን ስራ አጠናክራለሁ፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤትና ቤተመጻሕፍቱን በራሴ ሕንጻ ላይ አደርጋለሁ፡፡
4. በማንዴላ ዋሺንግተን ትምህርት ላይ መሳተፍዎ ሲመለሱ ምን ለውጥ ያመጣልዎታል?
ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ እገዛ ማሰባሰብና ደንበኛ መሳብ ላይ የተሻለ ክህሎት እቀስም ይመስለኛል፡፡
5. በስራዎ ላይ ያስመዘገቡት ፈጠራ የታከለበት አስተዋጽኦ ምንድነው?
የዘር ጥላቻ የሚያስከትለውን ውድመት የሚያሳየውን ሁቱትሲ የተባለውን መጽሐፍ መተርጎሜ ነው፡፡
6. ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት አክብሮትና መደማመጥ የተሞላበት ውይይት እንዲደረግ ምን አድርገዋል?
በብሔር ላይ ከተመሰረተ ሐሜት ለመራቅ እየሞከርኩ ነው፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቆዎች መመለስ ለስድስት ሳምንታት አሜሪካ ባለ ዩኒቨርሲቲ ለመሰልጠን በሚደረገው ውድድር ያሳትፋል፡፡ በዘንድሮው ውድድር ከአፍሪካ 62 000 ሰዎች ሲሳተፉ ከኢትዮጵያ 2400 ተወዳድረዋል፡፡ ከአህጉሪቱ 1000 ሰው ሲፈለግ ከኢትዮጵያ 50 ሰው ያልፋል፡፡ ከአንድ ሺዎቹ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሌላ ውድድር አድርገው አሜሪካ ባለ በፈለጉት ዓይነት ድርጅት ውስጥ ተጨማሪ የ6 ሳምንት የስራ ላይ ልምምድ አድርገው ይመጣሉ፡፡ መተግበር የሚችሉ ክህሎቶችን ይቀስማሉ፣ የአሜሪካንን አሰራር ያያሉ፡፡ እኔ ያንን ካለፍኩ በአሜሪካን የቱሪዝም ድርጅት ላይ ለመለማማድ አመልክቻለሁ፡፡



6. የሰው ዓይን አንገርግቦ የበላ
እናቴ ነች እንዲህ የምትለኝ፡፡ በፊት ሰው አልፈራም ነበር፡፡ አሁን የሰው ዓይን በጣም እፈራለሁ፡፡ በየኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት አዳራሽ ስናገር ያየኝ የስራ ባልደረባዬ መድረክ ላይ ያለው ስብዕናዬ ከውጪው እንደሚለይ ከጓደኞቼ ጋር አውግቶናል፡፡ በጣም ትክክለኛ ምልከታ ነው፡፡

7. የቢዝነስ አለባበስ
ሱፍ አልወድም፡፡ እሱን በመጥላቴና ባለመልበሴ ሰበብ እንዳልወድቅ ሰግቼ ነበር፡፡ ብወድቅና ብቀርስ ምን ችግር አለው ለዚያውም ወንድ ለወንድ ከሚጋባ አገር? ሸሚዝና ከረባት አደርጋለሁ፡፡ ጨርቅ ሱሪና ለሱ የሚስማማ ጫማ ማድረግ ነው፡፡

8. የትዕዛዝ ጋጋታ ወይስ የኔ ሰበብ
ቀድሞ ያልተነገረኝ ፈተና እንዳዘጋጅ ተነገረኝ፡፡ ከ25 መምህር እኔን ምን አዩብኝ! አንድ እምቢ የማልለው ወዳጄ በሁለት ቀን የማያልቅ ስራ አዘዘኝ፡፡ በቃለመጠይቁ ዋዜማ የሁለት ሰዓት ፈተና ፈታኝ ነበርኩ፡፡ ይህን ሁሉ ስራ ስለምሰራ ለቃለመጠይቁ ለመዘጋጀት አልቻልኩም፡፡ ፈተና መፈተኑን 9፡30 ላይ ጨርሼ ቢሮ ገብቼ ለአንድ ሰዓት ያህል የተለያዩ ፎቶዎችን ማቀናበር ጀመርኩ፡፡ የቤተመጻሕፍቱንና የኔን ተግባራት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከፌስቡኬ እንዳላወርድ ኮኔክሽን የለም፡፡ ያገኘሁትን ፕሪንት አድርጌ ያዝኩ፡፡ አልባሳት ግዢ የሄድኩት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ስገዛዛ መሸብኝ፡፡ ማመልከቻየን መሸምደድ እንዳለብኝና ያልተጻፈ እንዳልናገር ከኢንተርኔት ባገኘሁት ምክር መሰረት አጠር አጠር እያደረኩ ራሴ ለጥያቄዎቹ የጻፍኩትን መልስ በማስታወሻዬ ያዝኩ፡፡ የዝግጅቱን ወጪ የሚሸፍነው ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጊ ድርጅት ጠይቆኝ በዋዜማው አዲስ አበባ እንደምገባ ብናገርም አልቻልኩም፡፡ ማታ እቤቴ አስፈላጊ ሰነዶችን አዘገጃጀሁ፡፡ ጠዋት አዲሱን ሸሚዝ ያው መለካት አይቻልም ስለተባልኩ እንደታሸገ ገዝቼው ነበርና ለካሁት፡፡ ትንሽ የጠበበኝ መሰለኝ፡፡ ለበስኩት፡፡ ለአራት ጓደኞቼ አሳይቻቸው ምንም አይልም አሉኝ፡፡
ሆቴል ሩዋንዳን ያያችሁ፡፡ ልብ ካላችሁት በዚያ ሁሉ ረብሻና የስራ ብዛት መሀል የሆቴል ማኔጀር የነበረው ፖል አንድ ቀን ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ሱፉን ሊለብስ ይሞክራል፡፡ ሸሚዙን ማስተካከልም ሆነ ከረባቱን ማሰር አልሆንለት አለ፡፡ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ተርገፍግፎ አነባ፡፡ እንኳን ሁቱ ገዳዮችና የፖለቲካ ስርዓቱ ቀርቶ ልብሱም አመጸበት፡፡ ያን ዓይነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ አልቅስ አልቅስ አለኝ፡፡ ቅር ቅር አለኝ፡፡ ግን እንደኔ ልማድ ከሆነ መጀመሪያ በፌስቡክ ጉራ የምነዛው ሰዎች ያ ነገር ከምን ደረሰ ብለው እንዲበረታቱኝ ነው፡፡ ቢያንስ ሰው ሰምቶታል ጉዳዩን፡፡ ኦፊ ጉርባ!
ወደ አዲስ አበባም ሄድኩ፡፡ ጉዳዬን ስተኳኩስ ቆይቼ የቃለመጠይቁ ሰዓት ሲቃረብ ወደ አሜሪካን ኤምባሲ አቀናሁ፡፡ መጨናነቅ፣ እቃ እንዳልረሳ ማለት (ደብረብርሃን ላይ ማማልከቻዬን ያጠናክሩልኝ የነበሩ ሦስት ሰነዶችን መርሳቴን ልብ በሉ - የአማንን ደብዳቤ ጨምሮ )፣ እንግሊዝኛዬ ይገባቸው ይሆን ብሎ መፍራት ወዘተ ከቃለመጠይቁ በፊት ያጋጠሙኝ ነገሮች ናቸው፡፡

9. የምናወራው ሌላ ተግባራችን ሌላ
በየፌስቡኩና በየግሮሰሪው ጥቁር ኩሩ ህዝብ እንደሆነ፣ ነጮች እንደበደሉን የምናነሳ ሰዎች ነጮቹ አገር ለመሄድ ስንሽቆጠቆጥ የምንናገረውና የምንተገብረው መለያየቱ ያስተዛዝባል፡፡ ፈረንጅ ባይኖር ይሄኔ በአራት እግርህ ትሄድ ነበር ያለኝ ወዳጄ ትዝ አለኝ፡፡ ሁሉ ነገር የነሱ ነው፡፡ እስኪ የኛ የሆነ ነገር በቤታችንስ ሆነ በመስሪያ ቤታችን ምን አለ?

10. ዋናው በር
ዋናው በር የቱ እንደሆነ አላውቀውም፡፡ በሮቹ ጽሑፍ የላቸውም፡፡ ዋና በመሰለኝ በር ሄድኩ፡፡ ጥበቃዎቹ ጉዳዬን ሳስረዳቸው ዋናውን በር ጠቆሙኝ፡፡ የደረሰኝ ኢሜል ላይ ከቃለመጠይቁ 20 ደቂቃ ቀድመው በዋናው በር ይገኙ ስለሚል፡፡ እኔ እንዲያውም 30 ደቂቃ ቀድሜ ተገኘሁ፡፡ ተፈተሽኩ፡፡ ፍላሽ፣ ቻርጀር፣ ቁልፍ ሁሉንም አብጠርጥረው ፈተሹ፡፡ ግድግዳ ላይ እጅ ወደላይ አስብለው በማሽን ፈተሹኝ፡፡ ሞባይሌን ወስደው ግባ አሉኝ፡፡ ገባሁ፡፡

11. ኢትዮጵያ ውስጥ ያለችው አሜሪካ
የኤምባሲውን ግቢ ውበት የምገልጽበት አማርኛ የለኝም! አይኖረኝምም! ህይወት እንዴት መኖር እንደሚቻልና እንዳለበት ታያላችሁ፡፡ ያለንን በንጽሕና መያዝ እንዴት ሰላም እንደሚሰጥ ታያላችሁ፡፡ እኔ የምሰራበትንና ያንን ቦታ ማወዳደር ንስሃ መግባት ነው፡፡ ምነው እኛ ከዓለም ራቅን!
ግቢውን አልፌ ከአሁን በፊት የማውቃት ክፍል ውስጥ ገባሁ፡፡ የድረምረቃ ተማሪ ሳለሁ ቤተመጻሕፍት እየመጣሁ እጠቀም ስለነበር አንድ ሦስት ጊዜ አይቻታለሁ፡፡ ስሜን ተናግሬ፣ ፎቶ ተነስቼ ተቀመጥኩ፡፡ የቤተመጻሕፍቱን አስነባቢ አውቀው ስለነበር አንዳንድ ነገር አወራን፡፡ እስከዚህ ጊዜ በኤምባሲው ባየሁት መሰረት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በኤምባሲው ይበዛሉ፡፡ እንዲያውም ሌላ ያለ አይመስለኝም! ቆየት ብሎም ተጠራሁ፡፡

12. የጥያቄው ሁኔታ
‹‹ኮሊን ጌትሃውስ እባላለሁ፤ በአካል ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል›› ብላ እጇን ዘረጋችልኝ፡፡ ተጨባበጥን፡፡ ወደ ቃለመጠይቁ ቦታ ወሰደችኝ፡፡ ገና በሩ ጋ ሳለሁ ከቃለመጠይቅ አድራጊዎቿ አንዷ ታናግረኝ ኖሯል፡፡ በደንብ አልሰማኋትም፡፡ ተቀመጥ አሉኝ፡፡ ተቀመጥኩ፡፡ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ማስታወሻ ያዝኩ፡፡ ስማቸውን እየጠራሁ እንዳናግራቸውና ጥያቄ እንድመልስ ያግዘኛል፡፡ ስናገርም ልጽፍ ስል ጠረጴዛ ደገፍ እንዳልኩ መሆኔ አንድ ስህተት መሆኑ አሁን ይታየኛል፡፡ ቀጥ ብሎ መቀመጥ ያሻል! የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡
መካከል ላይ አንዲት ፈረንጅ ተቀምጣለች፤ በስተቀኟ አንድ አፍሪካዊ አለ፤ በስተግራ የማንዴላ ፌሎውሺፕ የአምና አሸናፊ ነች የተባልኳት ወጣት ኢትዮጵያዊት አለች፡፡
ፈረንጇ ጀመረች፡፡ ‹‹የእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ መምህር ስለሆንክ በግሌ ደስ ይለኛል፡፡››  ስትለኝ መውደቂያዬ መጀመሩ ገባኝ፡፡ ስለየትኛው አሜሪካዊ ደራሲ ልትጠይቀኝ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ከሦስት ወይም አራት ውጪ አላውቅም፡፡ በስነጽሑፍ ዲግሪ የሰጠኝ ዩኒቨርሲቲ አሹፎብኛል! እድሜዋን ያርዝመው - ሳትጠይቀኝ ቀረች፡፡ የቤተ-መጻሕፍቴን ቀጣይነት ለማስቀጠል ምን እንደማደርግ ጠየቀችኝ፡፡ አንደኛውን እንደዘጋሁት ነገርኳት፡፡ ምክንያቱም የቤት ኪራይ መጨመሩና አንባቢ መቀነሱ ነው አልኳት፡፡
አበሻዋ ለምን ቀነሰ አለችኝ፡፡ የህንጻው መገኛ የንግድ ስፍራ ስለሆነና ቤተመጻሕፍቱም ሁለተኛ ፎቅ ስለሆነ ከበፊቱም የተዳከመ ነበር አልኩ፡፡ አንደኛው እንደተዘጋ እንኳንም ተናገርኩ፡፡ በቅርቡ መጥተው ሊጎበኙ እንደሚችሉ ፍንጮች አግኝቻለሁ፡፡ ለማስታወሻዬ የቅርንጫፍ ላይብረሪው ፎቶና ቪዲዮ ግን አለኝ፡፡ አስነባቢው አማከለው አለምሸትም ትጉህ ልጅ ነበር፡፡ አሁን ስራ ማጣቱ ያሳስባል፡፡ የደብረብርሃን ህዝብ እንዲያነብ እና ጠባሴ ድረስ እንዳይንከራተት በማሰብ ነበር የከፈትኩት ያንን ቤተመጻሕፍት፡፡ ለጉራ አልነበረም፡፡ በትንሹ 16 000 ብር አክስሮኛል፡፡ 
የስራዬን ቀጣይነት አስመልክቶ ግን በማመልከቻዬ የጻፍኩትን ትቼ እገዛ ለማሰባሰብ እሞክራለሁ ማለቴ አንድ ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ማመልከቻው ላይ የዕደጥበብና የቱሪዝም ስራ እሰራለሁ ማለቴን ልብ ይሏል፡፡
ከዩኒቨርሲው ጋር እንዴት ማስተሳሰር ትችላለህ ስትለኝ በዩኒቨርሲው ግቢ የመጻሕፍት መሸጫ መክፈት ብችል ጥሩ ነው አልኳት፡፡ መምህራኑ፣ ሰራተኞቹና ተማሪዎቹ ደንበኞቼ እንደሆኑ ተናግሬ አመራሮቹን ለማሳመን እንደምጥር ገለጽኩ፡፡
(ዘመዴና በአርበኞች ላይ የሚጽፈው የስራ አመራር አማካሪው ጋሽ ጥላሁን ‹‹ለምንድነው ሥልጣን የማትይዘው?›› ይለኛል፡፡ ‹‹ስልጣን እኮ የምትፈልገውን ለማሳካት መሳሪያ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን ብር ላይ ታዛለህ፡፡ ገንዘቡ ለህዝቡ እንዲውል ታደርጋለህ›› ይለኛል፡፡ ‹‹ስልጣን አልፈልግም›› እለዋለሁ፤ ይበሳጫል፡፡ ስልጣን ማለት ህዝቡ እንዲያነብና ችግሮቹን እንዲፈታ የሚጠቅመውን አንብቦ የማስነበብን ስራ የምሰራበትን አቅም የሚፈጥርልኝ መሆኑን ረስቼዋለሁ፡፡ ተያይዞ የሚመጣ ጦስ ግን አለው፡፡)
ከአሜሪካን ሰላም ጓድ ጋር ስለሰራኸው ስራ ንገረን ተባልኩ፡፡
በካምፕ ግሎው 2014 ከዕቅድ እስከ ፍጻሜ ድረስ የነበረኝን ተሳትፎ ተናገርኩ፡፡ በእቅዱ ወቅት የሚተረጎሙ ሰነዶችን በመተርጎም ወደየክልሉ እንዲላኩ ማድረጌን፣ በዝግጅቱም ወቅት ከክፍያ ነጻ ለአንድ ሳምንት መስራቴን ተናገርኩ፡፡ (64 ሴት ተማሪዎች ከሶስት ክልሎች የተሳተፉበትን መርሃግብር ዛሬም እኮራበታለሁ፡፡ ልጃገረዶች ዓለማችንን ሲመሩ የሚለውን ቲሸርት አሁንም በፍቅር እለብሰዋለሁ፡፡ እንኳንም ውሎአበል የለውም ብዬ አልተውኩት፡፡ እንኳንም የምስክር ወረቀት የለውም ብዬ ገለል አላልኩ! (‹‹የምስክር ወረቀት አያስፈልግም፤ ሰርቻለሁ ካልክና ስለስራው ከተናገርክ ይበቃል፤ መርሃግብሩ ላይ መሳተፍክም ስለፕሮጀክት ማኔጅመንት ዕውቀት ያስገኝሃል›› ያለችኝ ልክ ነበር ያቺ ልጅ፡፡) በመንዲዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረኝን የስነጽሑፍ ማሰልጠን ሚና አክዬ ለቁጥር የሚያዳግቱ ስራዎችን እንደሰራሁ ገለጽኩ፡፡ (SIX HOURS AT MENDIDA የሚለውን ጽሁፌን ከጉግል ላይ አንብቡት) እዚህ ላይ ላስታውስዎ የሚገባኝ ነገር አለ፡፡ ባለፈው ፒያሳ ያገኘኝ አሜሪካዊው ወዳጄ ቤንጃሚን በጣም ፈጠራ የተሞላባቸው ስራዎችን እንደምሰራ ለሌላ አሜሪካዊት ልጅ ነገራት፡፡ አንድ ጥያቄም ጠየቀኝ፡፡ ‹‹እንደዚህ ፈጣሪ የሆንከው እኛን አሜሪካውያንን ካገኘህ በፊት ነው በኋላ?›› አለኝ:: እኔም እርግጠኛ ባልሆንም ዱሮም ይህ ነገር እንደነበረብኝ ነገርኩት፡፡ ቢያንስ እንግድዋሻ የተባለውን ዋሻችንን ለማስተዋወቅ ስሞክርና ህዝቡን አስተባብሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰሳ ስናካሂድ አሜሪካ አታውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን አሜሪካ ስልጠናና ገንዘብ ከሰጠችን ይህን ዋሻ የቱሪስት መዳረሻ እናደርገዋለን ብያለሁ ማመልከቻዬ ላይ፡፡
በአካባቢዬ ቤተመጻሕፍትን በደንብ እንዳላስፋፋ የሚያግዱኝም ሁለት ምክንያቶች ሲጠይቁኝ ምላሼ የገንዘብ እጥረትና ከፍቃድ በኩል ያለው ጉዳይ መሆኑን ገለጽኩ፡፡ የቤተመጻሕፍት ፈቃድ ለግለሰብ ይኖር ይሆን እንዴ እኛ አገር? ከሌለ የኢንተርፕረነር አንዱ ችሎታ ፖሊሲ ማስቀየር ስለሆነ ለማሳመን መሞከር ነው፡፡ ዶክተር ፍስሃ የግል ኮሌጅ በኪራይ ህንጻ አይቻልም እንደተባሉ እንዳደረጉት፡፡
ያሊ ስልጠናውን ቢሰጥህ ምን ትጠቀማለህ ሲሉኝ በማመልከቻዬ ላይ ብያቸው የነበሩትን ነገሮች ጠቃቀስኩ፡፡
ጥያቄ ጠይቀን አሉኝ፡፡
ያሊ ብዙ ነገሩ እንደገባኝ ተናግሬ ምክር ካላችሁ ምከሩኝ አልኳቸው፡፡ መጻሕፍትን እንዴት እንደማገኝ መከሩኝ፡፡ አብዛኞቹ የአውሮፓና የአሜሪካ አብያተመጻሕፍት ዲጂታል እየሆኑ ስለሆነ መጻሕፍትን ታገኛለህ አሉኝ፡፡ በጣም የምፈልገው የአማርኛ መጻሕፍት ሊሆን ስለሚችል ቡክስ ፎር አፍሪካን ጠይቅ አሉኝ፡፡
በዋዜማው ያዘጋጀሁትን የቤተመጻሕፍቱና የኔን እንቅስቃሴዎች የሚያሳይ ባለ 24 ገጽ የፎቶ ጥራዝ ከነማብራሪያው ለጠያቂዎቼ እንዲያዩት ስጋብዝ አፍሪካዊው ጠያቂ ተንደርድሮ መጥቶ ተቀብሎኝ ሁሉም አይተውልኛል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ላብራራ ብዬ ስጠይቅ ‹‹ፎቶው ነግሮናል፤ እናመሰግናለን›› አሉኝ፡፡ ምን አስመለከተኝ አልኩ ለራሴ፡፡ ጥሩ እቅድ!

13. የገረመኝ ጥያቄ!
‹‹ሠሚራን ታውቃታለህ?›› የሚለው ነው፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ ነው! ‹‹እንዴ አውቃታለሁ!›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ትመጣለች እኮ፡፡›› የዚህ ጥያቄ ዓላማ እኔ በእውነት ከደብረብርሃን መምጣቴን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሠሚራን ባላውቃት ግን ሊሰርዙኝ ነበር እንዴ!
ተመሰጋግነን ተለያየን፡፡
ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ የዱሮው ባህር ሃይል ያሁኑ ዩኒቨርሲቲና መከላከያ ኢንጂነሪንግ ከሚገኙበት ስፍራ የጀመረው የአሜሪካ ልክፍት እስከ እንጦጦ ጥግ፣ ሽሮሜዳ፣ አዲስ አበባ ቀጥሏል፡፡ በዚሁ ይቀጭ ይሆን?

14. አንዳንድ ጥያቄዎች
አልፍ ይሆን?
ትራምፕ ጭራሹኑ መርሃግብሩን ይሰርዙት ይሆን?
እርስዎም ያሊን እንዲጠቀሙበት በማሳሰብ ልሰናበት፡፡ በድረገጻቸው ኦንላይን በነጻ በመማር፣ በፌስቡካቸውና በያሊቻት ስለአፍሪካ ልማት በመወያየትና እንደ እርስዎ ባለ ሁኔታ ያሉ አፍሪካውያንን ሁኔታ በማጤን ለለውጥ ይነሱ፡፡ የያሊ መሪዎች መርሃግብሩን ለማስቀጠል መጠባበቂያ እቅዶች ላይ እየተወያዩ ይመስለኛል፡፡ ወደ አፍሪካ ለማምጣት ሳይታሰብም አይቀር፡፡ ሁላችንም መሪዎች መሆን እንችላለን!
መታሰቢያነቱ
ለባራክ ሁሴን ኦባማ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...