ዉሻና ሰው
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዉሾችን አስመልክቶ እየተካሄደ ያለ ዘመቻ መኖሩን በማህበራዊ ሚዲያ እንመለከታለን። ዉሾቻችን ተገደሉበትን ያሉ ሰዎች እያለቀሱ የለቀቋቸው ቪዲዮዎች ታይተዋል። ንፍሮም የታየበት ቦታ አለ። ይህን የዉሾችን መግደል የተቃወሙ እንዳሉ ሁሉ ያፌዙበት ወይም ያቃለሉት አሉ። ለምን ታፌዛላችሁ ብለውም የተቆጡ የዉሾች ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው ቁጣቸውንና ስድባቸውን አውርደዋል።
በዚህ አጊጣሚ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። እንደ ህብረተሰብ የራሳችን ዉሻ የሚኖረን ጊዜ አለ። ቤት ጠባቂ ነው። በቂ ምግብ ላይሰጠው ወይም እንክብካቤ ላይደረግለት ይችላል። የሌላን ሰው ዉሻ ግን በፍርሃት እናያለን። አሳደንም በድንጋይ እንመታለን። እኔም የተለየሁ አይደለሁም። ሳሲት ሳድግ አንዲት የጋሽ ማንደፍሮ ዉሻ ነክሳኛለች። የነከሰችኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ሙጃ ቆርጬ ላመጣ ስሞክር የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነበር። ከትምህርት ቤታችን ጎን ባለው ክሊኒክ ታከምኩ። ያከሙኝ የሐኪም ቤቱ ዘበኛ ጋሽ አድማሱ ነበሩ። ሌላ ቀን ለሥራ ዘመቻ ወደ ችግኝ ጣቢያ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ስንሄድ መንገድ ላይ አንድ ዉሻ ያልፍ ነበር። በርካታ ተማሪዎች በድንጋይ መቱት። ደሙ ፈሶ ሞተ። ተዉ ያለ መምህር አልነበረም።
ሌላ ቀን አንድ አሜሪካዊ በአገራቸው የዉሻ ዋጋ እስከ 5,000 ዶላር እንደሚደርስ ነገሩኝ። ጉግል ሳደርግ ልክ ነው። ከእኛ አገር የበሬ ዋጋ በለጠ። የዉሻና ድመት ምግብ ከሱፐርማርኬት የሚገዛ ሲሆን በዓመት እስከ 68 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። በአንድ ወቅት ያየሁት የአውስትራሊያው የዉሻና ድመት ምግብ ከወቅቱ የኢትዮጵያ በጀት ይበልጥ ነበር።
በአገራችንም በሠይፉ ሾው የቀረበውን ዉሻ አርቢ አይተናል። ዉድ ዉሾችን ከዉጪ ያስመጣል። ያሳድጋል። ያረባል። ይሸጣል። የዉጪ ዜጎች በአዲስ አበባ በተባለው ቡድንም ውስጥ በመኪና የተገጨ የጎዳና ዉሻ ሲኖር ጠቁሙኝ እያለ ሲጠቆም ሄዶ የሚያክምና በዚያውም ማስታወቂያ የሚሰራ ሐኪም አለ። በቅርቡ በቲክቶክ ያየናት አንዲት ባለዉሻ በቀዶ ሕክምና ወቅት ማደንዘዣ አሰጣጡን አሳስቶ ዉሻዬን ገደለብኝ ስትል ያቀረበች ሴት አይተናል። ዶክተሩም ይቅርታ ጠይቆ ቪዲዮ ለቋል። ሥራው ስለሆነ ስሙን ማደስ ስለላበት ነው። ለዉሻቸው ከልኳንዳ ስጋ የሚገዙ እንዳሉ እናውቃለን። ደብረብርሃንም አንድ ሰው ነበር። ወገኖቼ ይህ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ወግ ነው። ከአንድ ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ አለው የሚባለው ብዙኃን ኢትዮጵያዊ በዚህ የቅንጦት ሕይወት ላይ ጥያቄ ቢያነሣ ማንም አይሰማውም። ጉዳዩ አከራካሪ ነው። ክርክሩ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ከሉሉ የጀመረ ነው። የወሎና የትግሬ ሕዝብ እፍኝ ጥሬ አሮበት በሜመዳው የአሞራ ሲሳይ ሆኖ ሳለ የአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ሞቶ ሐውልት ተሰርቶለታል፤ ይለቀስለታል፤ በሚል የቀረበውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ ያስታውሷል።
በዘመነ ኢህአዴግም ሰልፍ ተከከክሎ ሳለ ሚሚ ስብሃቱ የተገኘችበት የእንስሳት መብት ሰልፍ ይታወሳል። ሰዎች ምግብ፣ ሰብዓዊ መብት፣ መጠለያ አላገኙም በሚባልበት አገር የተነሣ ጥያቄ ስለሆነ ነው የተወዛገበነው።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ