በመዘምር ግርማ የተጻፈ የጉዞ ትውስታ
ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፡፡
14.12.2009 ዓ.ም.
ወጧ የጣፈጠላት ባልቴት መስለናል
ብዙዎቻችን ይህችን ቀን ስንናፍቅ የነበርን ሰዎች
ወጣችን ጣፍጧል፡፡ ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ በራስ አበበ ቤተመጻሕፍት ተመዝግበው በዕለተ-እሁድ 14.12.2009 ወደ እንቁላል ኮሶ፣
አንጎላ፣ ጉዞ ያደረጉ 75 ወዳጆቻችንን የፈካ ፊት ስናይ ነው የዋልነው፡፡ በስፍራው የተገኘው ህዝብ የነበረው የአብሮነት ስሜት፣
የአገርና የንጉሥ ፍቅር ብርቱ ስሜትን የሚያጭር ነው፡፡
የአንጎለላ አድባር መርቃችኋለች፡፡
ሰውኛ ፕሮዳክሽን፣ መገዘዝ መልቲሚዲያ፣ ደብረብርሃን
ዩነቨርሲቲ፣ የባሶ ወረዳ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ለዚህ ክብረ-በዓል መስመር የተጉ ወገኖቻችን ባይኖሩ አኛም ለዚህች የደስታ ብስራት ባልበቃን ነበር፡፡ እናመሰግናለን - ባያሌው፡፡ የወጣችሁና የወረዳችሁትን የምታውቁት እናንተ ስለሆናችሁ እኛ ድካማችሁ መሉ በሙሉ አይገባንም፡፡
የዝግጅቱ ሂደት
አንዳንድ ወገኖቻችን ከአዲስ አበባ በፌስቡክ
የተለቀቀውን ቅስቀሳ አንብበውና አዘጋጆቹን አነጋግረው በአጤ ምኒልክ፣ በእቴጌ ጣይቱና በፊታውራሪ ገበየሁ ልደት አከባበር ላይ እንድንሳተፍ
ይወተውቱን ገቡ፡፡ እንኳንም አነቁን፡፡ አንዱ ዳምጠው አድማሱ ነበር፡፡ ወጣቱ የሒሳብ አያያዝ ምሩቅ ሚኪያስ ካሣዬ በአንጻሩ ‹‹እኛ
በያመቱ እዚህ ደብረብርሃን ስለምናከብር ለምንድነው ሌሎች ባዘጋጁት ዝግጅት ላይ የምንሳተፈው?›› የሚል ተቃውሞ አንስቶ ነበር፡፡
ሚኪዬ ምን መሰለህ? ለብቻህ የምታደርገውና ተሰባስበህ የምታደርገው ነገር ውጤቱ ይለያያል፡፡ ያንንም ዛሬ የታዘብክና የረካህ ይመስለኛል፡፡
ይህ ምክክር የተካሄደው ከዝግጅቱ አንድ ሳምንት
በፊት በነበረው ሐሙስ ነበር፡፡ ለነገሩ የፌስቡክ ማስታወቂያውን እኔም ሳላየው ቀርቼ አይደለም፡፡ ያዘናጋኝ ነገር ቢኖር የቤተመጻሕፍቱ
ባልደረቦች በጉዞ እየተቀዛቀዝን መሄዳችን ነበር፡፡ ባላፈው ወደ ግድብ እንደናደርግ በተቀጣጠርነው ጉዞ ላይ ስምንት ሰው ብቻ መገኘቱ
ያልተጠበቀ ነገር ስለነበረ አሁንም ጉዞ ጠርተን የሚቀረው ይበዛል ብዬ ነበር፡፡
ዘንድሮም እንዳምናው
ምን አዚም እንደያዘን አላወቅም፤ ባለፈው ዓመት
ከዘንድሮው የላቀ ዝግጅት አድርገን ዘንድሮ ግን ተቀዛቅዘናል፡፡ የጓደኞቻችን ውትወታ ባይኖር በዓሉ ተቀዛቅዞ ባለፈ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት እኮ ከዩኒቨርሲቲ የአዳማ ልጅ የክረምት የታሪክ ተማሪ ጋብዘን
ነበር በደማቅ ውይይት ያከበርነው፡፡ ቦታ ጠቦ መሬት ላይ ተቀምጠን አታስታውሱም? ባለፈው ሐሙስ በነበረን ሳምንታዊ የውይይትና የስነ-ጽሁፍ
ምሽት የሦስቱን ጀግኖና የራስ አበበ አረጋይን ልደት አክብረናል፡፡ ራስ አበበን ግን አትርሱብን!
ባለፈው አርብ ዕለትም በጌትቫ ሆቴል የልደት
አከባበሩ በደብረብርሃን ወጣቶች ተካሂዶ ነበር፡፡ ወድንኳኗ ውስጥ ያደረግነው ውይይት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አሁን ዶክተር አዲሱ
ይህን በፌስቡክ ስላስታወስከኝ አመሰግናለሁ፡፡
የዛሬ ውሏችንን እነሆ!
ከማለዳው 12፡00 ከእንቅልፌ ተነስቼና ባጭር
ጊዜ ዝግጅቴን ጨራርሼ ወደ ቤተመጻሕፍቱ በማቅናት ቤቱን አሳምር ጀመር፡፡ ወንበሮችን በሙሉ ወደ ውጪ አውጥቼ አስቀመጥኩ፡፡ መጻሕፍቱን
አውደ-ርዕይ በመሰለ መልኩ ደርድሬ በቤቱ ላይ ውበት ዘራሁበት፡፡
ልክ እንደትናንተቱ ስልኬ አሁንም አሁንም ይጮሃል፡፡
እኔም መልስ እሰጣለሁ፡፡ እየረፋፈደ ሲሄድ ተጓዦች ይሰባሰቡ ጀመር፡፡ የቲሸርት ያለመኖር ችግር ሁሉንም ያስቆጨ ስለሆነ ለብዙዎቹ
ቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ ከአዲስ አበባ ይመጣል የተባለው ሳይመጣ ስለቀረ ነው የኛ መቀዛቀዝ እንጂ እዚሁ ማሰራት በተቻለ ነበር፡፡
እድሜ ለኢሳይያስ ፍቅሬ - 30 ቲሸርት አሰርቶ ለተወሰኑት ሰዎች አምጥቶልናል! ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ በመቶዎች የሚቆጠር ቲሸርት
ሊሸጥ እንደሚችል እተማመናለሁ፡፡
ተጓዦች በአቅራቢያችን ባሉ ካፌዎችና በቤተመጻሕፍቱ
በበረንዳ ቡናና ሻይ ሲጠጡ፣ ሁለቱ መኪናዎቻችን መጥተው ቆሙ፡፡ ደረጀ ጌታቸው እነዚህን መኪኖች በጥሩ ዋጋ ስላመጣልን አመሰግናለሁ፡፡
ክፍያው በሰላሳ ብር በነፍስወከፍ ስለሆነ ለዳቦና ለለስላሳ ገንዘብ ተርፎን ለስላሳ ለሌሎችም ተሳታፊዎች ለመጋበዝ ተችሎናል፡፡ ይህን
ግብዣ ላስተባበረችው ለጌጤ ፈለገ ምስጋና ባያሌው!
ከጠዋቱ 1፡30 እንነሳለን ብዬ የቀጠርኳቸው
ሰዎች ተሟልተው (ግማሹ በስልክ ጉትጎታ) ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ ተነሳን፡፡ ጉዞ ወደ አንጎለላ፡፡ ስፍራው ስምንት ኪሎሜትር ስለሚርቅ
የደረስንው በአንድ አፍታ ነበር፡፡ የክረምት ልምላሜው የሚያስደስት መስክና ማሳ ይታየናል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ኩሳዬ ትምህርት
ቤት፣ ጅሩ፣ ወደ ራስ አበበ አገር ለወላጆች በዓል ስሄድ እንደጻፍኩት ይህን መስክ እነራስ አበበ አረጋይ ያባረሩት ፈረንጅ እንዳያይብን
ጸልዩ ብያችሁ ነበር፡፡ ጸሎታችሁ ከደመና በታች ቀርቶ ይሁን ጨርሶ ሳትጸልዩ ረስታችሁት ይህ መንገድ ግራና ቀኙ ዓይን እየበዛበት
ነው፡፡ ዓይን ብቻ አይደለም፣ ገመድም ተመትሮበታል!
‹‹ይሄ የማነው ቤት የደራ የኮራ
የምኒልክ ነዋ የዚያ የቀብራራ!››
እንዲህ እያልን በሆያ ሆዬ ወደ አንጎለላው ክሊኒክ
ግቢ ስንቃረብ የነበረውን ትዕይንትና የስለት ስምረት ስሜት የነበራችሁ ታስታውሳላችሁ! በቅርቡ በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትብብርና
ጥረት እንደገና ስራ እንዲጀምር የተደረገው ይህ ክሊኒክ ዛሬ አምሯል፡፡ በባንዲራ አሸብርቋል፡፡ በብርቅዬ አርቲስቶቻችን፣ በምሁራን፣
በአካባቢው ማህበረሰብ አባላት፣ በመንግሥት ተወካዮችና በበርካታ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ምስል ያለባቸውን
ቢጫ ቲሸርቶች የለበሱ ሰዎች በግቢው ውስጥ ይታያሉ፡፡ ፎቶ መነሳት፣ ስራ ማስተባበር፣ በዓል ማክበር ይዘዋል፡፡ በወርቀዘቦ ጌጥ
የተሰራ ጥቁር ቲሸርት የለበሱም አሉ፡፡ አጤ ምኒልክ እንደሚያደርጉት ሁሉ በነጭ ጨርቅ ራሳቸውን ያሰሩ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ባዶ እግሩንም
የሆነ አይቻለሁ፡፡ የኛ የደብረብርሃኑ ቡድንም ቀይ ቲሸርት ለብሶ መቀላቀሉ የበለጠ ድምቀትን አመጣ፡፡ ሁሉም በደስታ ስሜት ፎቶ
ይነሳል፣ ይጨፍራል፣ ይዘምራል፡፡ ዝግጅቱ ጀመረ፡፡
ለበዓሉ ከዞኑ፣ ከወረዳውና ከዩኒቨርሲቲው የተጋበዙት
እንግዶች አጤ ምኒልክን በብዙ የአሀኑን መንግሥት በመጠኑ አሞገሱ፡፡
አጤ ሚኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱና ፊታውራሪ ገበየሁ
ልደታቸው ሲከበር የታወሱ ግጥሞች አሉ፡-
‹‹ባቡሩም ሰገረ ስልኩም ተናገረ
ምኒልክ መልዓክ ነው ልቤ ጠረጠረ››
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ
ትዝ
ይሉኛል፡፡
ሽልማትና ችግኝ ተከላ
ለበዓሉ ስምረት አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦችና
ድርጅቶች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበረከተ፡፡ በፈረስ ጉግስ ውድድር ላሸነፉ ሰዎችም ሽልማት ቀረበ፡፡ ይህም ሽልማት የዳቦና የፎቶ
ነበር፡፡ ፎቶዎቹ በጥሩ ሁኔታ የተሰሩ የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ ዕውቅናው ለወደፊትም የሚያበረታታ በመሆኑ ያስደስታል፡፡
ከህብረተሰቡና ከተሳታፊው የተመረጡ 12 ሰዎች
የንጉሡ እትብት በተቀበረበት ስፍራ የኮሶ ችግኝ ተከሉ፡፡ ቦታው እንቁላል ኮሶም አይደል! ቦታውን አሳምረው ያሳጠሩትን የእምዬን
ወዳጆች ማመስገን ይገባል፡፡
የመጨረሻው መጀመሪያ
ዝግጅቱ ሊያላልቅ ሲል ዝናቡን አመጣዋ! አብዛኞቻችን
ከድንኳን፣ ሌሎቻችን ደግሞ ከክሊኒኩ በረንዳ ተጠለልን፡፡ በዝግጅቱ ላይ አንድ ዘፈን እንዲያቀርብልን የፈለግነው የኛ ቡድን አባል
መምህር ታደለ አንባዬ እንዲያቀርብ ብጠይቅም ጊዜ የለንም አሉ እንጂ ጣዕመ-ዜማም እንሰማ ነበር፡፡ እጅግ የተደሰትንበት ይህ ዝግጅት
አልቆ ወደየመኪናዎቻችን አቅንተን ያለንን ዳቦና ለስላሳ ቀማምሰን ጉዞ ወደ ደብረብርሃን ሆነ፡፡ ግማሾቹ ጎብኝዎች ወደ አንጎለላ
ኪዳነምህረት ሄደው የንጉሥ ሣህለሥላሴን ቤተመንግስት ፍርስራሽና የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም ሳይጎበኙ አልቀሩም፡፡ እኛም በመጪው
ዓመት ማየት ይኖርብናል፡፡ ምንም እንኳን እኔና የተወሰንነው ጓደኞቼ በየካቲት የዓድዋን በዓል በማሰብ በየዓመቱ በምናደርገው ጉዞ
እየጎበኘነው ቢሆንም፡፡ ሌሊት በመነሳቴ ስለደከመኝ የጥናትና ምርምር መድረኩ ላይ በሕይወት ሆቴል ባልገኝም አስተማሪ መድረክ እንደነበር
የተገኙ ወዳጆቼ ነግረውኝ ተደስቻለሁ፡፡
ከዚህ ዝግጅት ብዙ ትምህርት ቀስመናል፡፡ ለወደፊቱም
የምናደርጋቸውን ጉዞዎች (የአንኮበሩን የየካቲት 23ቱን ጨምሮ) እንደዚህ ማቀናጀት ይኖርብናል፡፡ ለዝግጅቱ ብዙ ወጪ ያወጡት ወንድሞቻችንና
እህቶቻችን የገንዘብ ድጋፍ ሳናደርግላቸው ይህን ዝግጅት ስላደረጉልን ብዙ መስዋዕትነት ሳይከፍሉ አልቀሩም፡፡ ለወደፊቱም ደብረብርሃንም
የራሷን ብትወጣና ከስፖንሰር የጸዳ የበዓል አከባበር ብናደርግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ራስን የመቻልን ትምህርት ምኒልክ ሳያስተምሩንም አልቀሩ!
ማሳሰቢያ
አጤ ምኒልክን የማይወዱ ሰዎች አለመውደዳቸውን
በደንብ እንዲመረምሩት አሳስባለሁ፡፡ እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ ይህንን ጽሑፍ በአሉታዊ አስተያየት እንዲያበላሹብኝ አልፈልግም፡፡
ቢጽፉም የማይሆን ምላሽና ስድብ አትመልሱላቸው፡፡ አሉታዊ ነገር ሲበዛ ዓላማችንን ስለምንስት፡፡ ከፌስቡክ ወዳጅታቸውም ባትሰርዟቸው
- የሐሳብ ብዝሃነት ስለማይከፋ፡፡
ስለጉዞው የዘነጋሁትን አናንተ ሙሉልኝ፤ ፎቶዎቻችሁንም
በአስተያየት መስጫው ላይ አስገቡልኝ፡፡