የፍኖተ-ካርታ ውይይት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ሲሆን፤ አንዳንድ ነጥቦች በተወያዮች እየተነሱ ነው፡፡ ስያሜውም ጥያቄ ውስጥ ገብቶላችኋል፡፡ የፖሊሲ ለውጥ አይመስልም፤ የአፈጻጸም የሚለው ላይ አትኩሮት ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ፖሊሲው ችግር አልነበረበትም ማለት ነወይ?
ቋንቋ ላይ ያለኝን ምልከታ በመጠኑ ላስቃኛችሁ።
1. ቋንቋ የተባለው ላይ ልጆች አራት ቋንቋ እንዲማሩ የሚያደርግ አሰራር እየተዘረጋ ሲሆን፤ ትኩረታችን የቋንቋ ፉክክር ላይ ይመስላል፡፡ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይሆን ላለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ስራ ላይ ተጨማሪ ነገር እየተሰራ ነው፡፡ የኔን ቋንቋ ካልተማርክልኝ ያንተን አልማርም ነው እንዴ ነገሩ? አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ ብሔራዊ ቋንቋ ነው፡፡ ሁለት በተለያዩ ቋንቋዎች አፋቸውን የፈቱ ኢትዮጵያውያን ሲገናኙ የሚነጋገሩት በአማርኛ ነው፡፡ ትምህርትም በዚሁ ቋንቋ የሆነው ለዚያው ነበር፡፡ አሁን የአማርኛ ክፍለጊዜ መቀለጃ ሆኗል፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ እንደማይወስዱ የሚያስታውቀው በአማርኛ ሰላምታ እንኳን የማይችሉ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ ነው፡፡ በአፍ መፍቻቸው የተማሩት ነገር ጥሩ ሆኖ ሳለ አሁን እነሱም የማይማሩትን የአማርኛ ክፍለጊዜ ታሳቢ አድርጎ የአማርኛ ተናጋሪውም የነሱን ቋንቋ እንዲማር የሚል አሰራር ሊዘረጋ ይመስላል፡፡
2. ከዚህ በፊት ብሔራዊ መግባባት መቅደም አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን በጎሳ እየተለያየን እየተጠቃቃን መሆኑ ለማናችንም ምስጢር አይደለም፡፡ በዚህ አካሄድ የሚመረጡትን ቋንቋዎች (ለምሳሌ ትግርኛንና ኦሮምኛን) ለማስተማር ወደተለያዩ የሃገራችን ክፍል የሚሄደው መምህር ምን በወጣው ይንገላታል፣ ይደበደባል ባስ ሲልም ይገደላል! ቋንቋዎቹ እንደሚያስፈልጉን ጥርጥር የሌለው ቢሆንም ቅድሚያ መግባባቱ ይቅደም፡፡ ሰው መሆናችን ይቅደም፡፡
3. አሁን የኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ላይ ባሉበት ወቅት ቋንቋቸውን ተምረን ማንነታችንን ብናጣስ? ከድሮውም አማርኛ የሚባል አልነበረም አይባል ይሆን? ማረጋገጫውም ይሄው እናንተ ቋንቋችንን ትችላላችሁ፡፡ ከፈለጋችሁ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ፤ ያለዚያ ባህላችንንም ቋንቋችንንም አክብራችሁና ተከትላችሁ ኑሩ የሚል ጣጣ ቢመጣስ?
4. የውጪ ቋንቋ የተባለው ላይ አረብኛና ኪስዋህሊ ቢካተቱበት ጥሩ ነው፡፡ አረብኛ ልጆቻችን ትምህርት ሲጨርሱ ወደ አረብ አገር ስለሚሄዱ ሲሆን ኪስዋህሊ ደግሞ የአፍሪካን አካባቢያዊ ትስስር አስመልክቶ ነው፡፡ አሁን ደቡብ አፍሪካ የደረሰ ቋንቋ ነው፡፡
ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የዚህ የፍኖተ-ካርታ ጥናት በጠ.ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን የጀመረ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ምግቦቹ የተለጠፉት ባለፉት ዓመታት ተችቼው የነበረውን አራተኛውን የከፍተኛ ትምህርት ዓላማ አስመልክቶ ነው። መማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት በማለው ላይ ደግሶ ማብላት መጨመሩን አብስሬ ነበር።
ተጨማሪ ጽሑፍ ለማግኘት
mezemirethiopia.blogspot.com
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ