2019 ማርች 31, እሑድ

የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ፣ የኢትዮጵያና የዓለም ቴሌኮሙኒኬሽን ትረካ

የመጽሐፍ ዳሰሳ
የመጽሐፉ ርዕስ - የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ፣ የኢትዮጵያና የዓለም ቴሌኮሙኒኬሽን ትረካ
ደራሲ - በኩረ ጠቢባን ኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ ወልደ መስቀል
የታተመበት ዘመን - 2011 ዓ.ም.
ዋጋ - 195 ብር
ዳሰሳ አቅራቢ - መዘምር ግርማ mezemir@yahoo.com
መጽሐፉ ለእምየ ምኒልክ መታሰቢያ ተደርጎ በውስጡ ምስላቸውና ውለታቸው የታወሰበት አንድ ገጽ ስላለ፤ እዚህም ላይ የመጀመሪያውን ክፍል ለንጉሠ-ነገሥታችን በአክብሮትና በፍቅር አበረክታለሁ፡፡
ቤተሰቦቻቸው
መጋቢት 2፣ 1928 ዓ.ም. በአንኮበር የተወለዱት የኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ እናት ወይዘሮ አስካለማርያም ታሪክ ልብ ይነካል፡፡ ምክንያቱም ወይዘሮ አስካለማርያም እናታቸውንም ሆነ ልጃቸውን በወሊድ ማጣታቸው ነው፡፡ እናታቸው እሳቸውን ሲወልዱ መሞታቸው ሳያንስ፤ ልጃቸውም ልጇን በወለደች በአስረኛው ቀን በልጅነቷ ተቀጠፈች፡፡ ይህም አነሰዎ ብሏቸው በእህቱ ሞት በተሰማው ጥልቅ ሐዘን ምክንያት ልጃቸው የማነም ራሱን አጠፋ፡፡ በዓመቱም ትልቁ ልጃቸው በበሽታ ምክንያት አርፏል፡፡
ግጥምጥሞሹ ደግሞ የደራሲው አባት መምህር ራስ ወርቅም እናታቸውን በወሊድ ያጡ ነበሩ፡፡ ራስ ወርቅ ምሁርና ደራሲ ነበሩ፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የመጀመሪያው የቋንቋና ሥነምግባር መምህርና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት መስራች ናቸው፡፡ በአስካለማርያም አባት አስገዳጅነት የተጀመረው የተረፈ ቤተሰቦች ትዳር ፍሬ እያፈራና ፍሬው እየተቀጠፈበት ቢያዘግምም በተረፈ ምክንያት ከዛሬ ደርሷልና የእርሳቸውን የሕይወትና የሥራ ጉዞ አብረን እናያለን፡፡
የእህት ወንድሞቻቸው ወግ
እህታቸው ወይዘሮ ሸዋዬ ያሏቸውን ነገር ያለ ቀብራቸው ዕለትም ትንፍሽ ያሉት አይመስል፡፡ በስንብት ቃላቸው ካቀረቡት የሚከተለውን እነሆ፡- ‹‹እንዲያው ይኽ ወዳጅህ (ፕሮፌሰር መስፍንን ማለቷ ነው) እዚሁ ቁጭ ብለን የላችሁም ይበለን፤ እንዲያው በአፉ ሙሉ አማራ የለም ብሎ እኮ ተናገረ፤ መንፈስ አደረገን? ወቸ ጉድ፤ እኛ እንደሆን ቢጨምቁንም ሌላ ዘር አይወጣን፤ ምን ብለው ሊጠሩን ይሆን?››
ለወይዘሮ አበበች ራስ ወርቅ ስንብት ተረፈ የተናገሩት ከልቤ ስለቀረ እነሆ፡- ‹‹የራስ ወርቅ ልጆች አንድ በአንድ ሹልክ እያላችሁ፤ ወደ ዘላለም ቤታችሁ ሄዳችሁ፡፡ ድሮም ስንወለድ መጨረሻ እኔ ነበርኩ፡፡ብቻየን ቀረሁ፤ የቤታችንን ደጃፍ ልዘጋ፡፡››
ሜጀር ዮሐንስ ራስ ወርቅ፡- የተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ተማሪ፣ የጦር መኮንን ምሩቅ የጥቁር አንበሣ፣ የማይጨው ዘማች፣ የነራስ አበበ አረጋይ የዘመን-ጓድ የነጻነት አርበኛ፣ የባንዶች ሰለባ፣ የ1929 ሰማዕት፡፡
አቶ ጥሩነህ፡- የፈረንሳይ ተማሪ፣ የጎረቤላ የጣሊያን አስተርጓሚ፣ የውስጥ አርበኛ፡፡
አቶ የማነ፡- በታናሽ እህቱ ሞት ምከንያት ራሱን ያጠፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተማሪ፡፡
ወይዘሮ አዳነች፡- የምትፈራው ያለዕድሜ ጋብቻ በልጅነቷ በወሊድ ምክንያት የቀጠፋት ቆንጆ፡፡
ተረፈ ራስ ወርቅ በኢጣሊያ ወረራ አንኮበር እስከ ታሪካዊው የምኒልክ ቤተመንግሥት በቦንብ ስትደበደብ በተዓምር የተረፉ ናቸው፡፡ ተረፈ የሚለውም ስም የወጣላቸው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በቅርቡ በዚህ ሰበብ አንድ ሰው የተቀኙላቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
‹‹ያነየ ከእሳት ቃጠሎ የተረፈ የዳነ
ዛሬ በስራው የብዙዎቹን አፍ አስከደነ፡፡››
የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት (ቲኤምኤስ)
ፊደልን በቤት ከአባታቸው፣ አንደኛ ክፍልን በዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም የተቀረውን በተፈሪ መኮንን ተምረዋል፡፡ አንዳንድ የትምህርት ቤት ትዝታ ሲያነሳሱ ‹‹ከትምህርት ቤት ተቀጽላ ስራዎች በጣም የወደድኩትና በህይወቴም ላይ ዘላቂ ለውጥ ያመጣው የቦይ ስካውት ተቋም ነው፡፡ …›› ይሉናል፡፡ አንድ ስካውት በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ በዛሬው ቀን ምን ደግ ነገር ሰርቻለሁ ብሎ ራስን ይጠይቃል ወዘተ. የሚል ቃለ-መሐላም ተቀበሉ፡፡ በጸባይና አስተሳሰባቸው ላይ ዘላቂ ለውጥም አመጡ፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የዉጪ ሃገር መምህራንን ሁኔታና የተማሪዎችን ተቃውሞ የመጀመሪያ ቀናት ሁናቴ ዳሰስ ዳሰስ አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኑሮና ትምህርት
የተስፋዬ ገሠሠና የሥብሐት ገብረእግዚአብሔር የዘመን-ጓድ ናቸው፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱን ከልጅነታቸው ጀምሮ ፊትለፊት ማየት ይችሉ ከነበሩት ትውልድ ውስጥ ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የታደሙበት ክርክር ላይ በተከራካሪነት ተሳትፈዋል፡፡ እስከ ፓርላማም የደረሰና ምክር ቤቱ ያላጸደቀው ዕቅድ በዚሁ ምክንያት ሊጠነስሱ ችለዋል፡፡ አያያዛቸው ላቅ ያለና ለሃገር የሚያስቡ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
የሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት (RPI) ትምህርትና ኑሮ
ከ3000 ተማሪ 16 ጥቁሮች ብቻ በነበሩበት ከሌጅ የነበረው ዘረኝነት ፈታኝ ቢሆንም ተረፈ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ለስራ ተመልሰዋል፡፡
የሥራው ዓለም
በእቴጌ ሆቴል ረፍት አድርገው ስራ በመፈለግም ቴሌ ይቀጠራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ የሙያ ስራ እየሰሩ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ፈጠሩ፡፡
ጋብቻ
ወይዘሪት ብርሐኔ አስፋውን ያገኟት በአንድ ሰርግ ላይ ነው፡፡ በርሷ ላይ ያሳዩትን ፍላጎትም ከዳር አድርሰውታል፡፡ ሠርጋቸው በእቴጌ ሆቴል፣ ጫጉላቸው በኬኒያ ናይሮቢ ተካሂዷል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ምስረታ ዕለት የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው ስለተወለደ አንድነት አሉት፡፡ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት ልጆችን ወልደው ለማዕረግ አብቅተዋል፡፡
ዓለምአቀፋዊ ሙያዊ ሥራና ተልዕኮ በዓለም አቀፍ ቴሌኮሚኒኬሽን ማህበር (ITU)
ባመዛኙ በበለጸጉት አገራት ተጽዕኖ ስር ወድቆ በነበረው ማህበር የመጀመሪያው ባለሙያ የአፍሪካ ተወላጅ ሰራተኛ በመሆን መስሪያ ቤቱን የተቀላቀሉት ተረፈ የአፍሪካ ክፍል ዋና ኃላፊትን ወስደዋል፡፡ አፍሪካን በማይክሮዌቭ የማስተሳሰር ስራን በፓናፍቴል ፕሮግራም ተወጥተዋል፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ሳተላይት መገናኛ መረብንም አጥንተዋል፡፡ የአይቱዩ ዋና ጸሐፊ ልዩ የፖሊሲ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ አፍሪካን ማስተሳሰራቸው በህይወታቸው ከሚያኮሯቸው ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በፊት በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በኩል ይስተሳሰርና ለመረጃ ምዝበራ ይዳረግ የነበረውን አህጉር ራሱን አስችለዋል፡፡
ለቢዲቲ ዲሬክተርነት ምርጫ ውድድር ሂደት
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአይቲዩ አባል አገራት በሙሉ ተረፈ ራስ ወርቅ የኛ ዕጩ ስለሆነ ምረጡት ብሎ ድጋፉን ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት (እ.ኤ.አ) ቃሉን አጥፎ ‹‹ለተረፈ ራስ ወርቅ የሰጠነውን የምርጫ ድጋፍ አንስተናል፡፡›› ብሎ የቴሌግራም መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኛ ተወካይ እናድረግህ ቢሏቸውም አይሆንም ብለው በግላቸው በመወዳደር ከአምስቱ ወኪሎች ከሦስቱ አንዱ በመሆን አለፉ፡፡ ከዚያም የሚከተለውን ይሉናል፡፡ ‹‹ይህ አስገራሚ ሁናቴ ሳይበግረው ኢትዮጵያን የወከለው ግለሰብ ተረፈን አትምረጡ እያለ ከሕግ ውጪ የሆነ ቅስቀሳ ያካሂድ ስለነበር መራጭ አገሮችን ያወናብድ ነበር፡፡››
ተረፈም በዚህ ጫና ምክንያት ራሳቸውን ከውድድሩ አገለሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲወዳደሩ የራሳቸው መንግሥት መሰናክል መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን እንደተወዳደሩ ይታወቃል፡፡
ለማንኛውም ከምርጫው በኋላ ከእርሳቸው ጋ ከተወዳደረው ሰው ስር ሆነው የአይቲዩ ውጪ ግንኙነት ኃላፊ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ቦታ በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ የዋና ኃላፊው አማካሪም ሆነው ሰርተዋል፡፡
ወርልድ ቴልን እንደ ተቋም መፍጠር
‹‹በረጅሙ የስራው ዓለም ተካፋይነቴ ካከናወንኩት ውጤቶች ሁሉ የምዕራቡን ቴክኖሎጂ ወደ ቻይና እንዲተላለፍ ያደረኩት አጋፋሪት ታላቅ የመንፈስ እርካታ ሰጥቶኛል፡፡›› ይሉናል፡፡
ለኢትዮጵያ አብነቱ
‹‹በመጀመሪያ ስልክ በኢትዮጵያ የገባው አንኮበር ነው፡፡ በአጼ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት በኢትዮጵያ 3500 ኪሎሜትር የቴሌፎንና ቴሌግራፍ መስመር ተዘርግቶ ነበር፡፡›› የሚለውን የኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅን ቃል ስናነብ የምንገረም ብንኖርም ቴክኖሎጂን የሚወዱትና ወደሃገራቸው በማስገባት ቀዳሚው መሪ እምዬ ምኒልክ አስመራን፣ አዲስ አበባን፣ ጋምቤላን፣ ሐረርን፣ ጂቡቲን ወዘተ ያስተሳሰረ መረብ መዘርጋት ችለው ነበር፡፡
አሁን በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ወይም ከጠባሴ ወደ ደብረ ብርሃን በባጃጅ እየሄድኩ የምጠቀምበት የኢንተርኔት አገልግሎት ሳይመጣ ምን ያህል ተለፍቶበታል ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል - ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ ተረፈ ራስ ወርቅ ያለው ልፋት፡፡ ሁላችንንም ያስጠይቃል፡፡ ያንን ትጋትና ጥንካሬ የት አድርሰነው ይሆን? ያስብልማል!
የቤተክርስቲያንን ጉዳይ በተመለከተ ያቀረብኩት አስተዋጽኦና አስተያየቴ ከሚለው ምዕራፍ አንዳንድ ነገር ቃርሜያለሁ፡፡ የአንኮበሩ ጥንታዊ የአፈር ባይኔ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ገዳም መልሶ መገንባት አንድ የተረፈ ገድል ነው፡፡ ለገዳሙ ከፈረንሳየይ አገር የመጣ 225 ኪሎግራም የሚመዝን ልወል ተበርክቶለታል፡፡ ደወሉም ለቅዳሴና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከማገልገል ጎን ለጎን የአንኮበር ህዝብ ለልማት እንዲተጋ ጠዋት፣ ቀንና ማታ በቀን ሦስት ጊዜ ይደውላል፡፡ ይህን ትምህርት እንዴት ዓይነት ቦታ እንደሰጠሁት አልነግራችሁም፡፡
በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ማቋቋምም ቢሆን ከገድል በላይ ነው፡፡ የሙሴ ጽላት ቅጂ ከጥንታዊቷ ክርስቲያን ሃገር ኢትዮጵያ ወደ ስዊዘርላንድ መግባቱ ትልቅ በረከት መሆኑን በሃገሪቱ ያለውን አመራር በማሳመን በመንግሥት ደረጃ ለታቦቱ አቀባበል እንዲደረግና ኢትዮጵያውያ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ተረፈ የመሪነት ሚናውን ተጫውተዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የአስተዳደርና የመንፈሳዊ ስራ ይስተካከል ዘንድ ጳጳሳትና ካሕናት የመንፈሳዊውን አገልግሎት እንዲሰጡና ከምዕመናን የሚመረጥ አካል ደግሞ የገንዘብና የአስተዳደር ስራዎችን እንዲሰራ ሳይሰለቹ ምክራቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው መንግሥትና ኃይማኖት በተለያየ ጊዜ የተፈጠረው ክፍተት ያመጣቸው ችግሮች አሉ የሚል ነው፡፡ በህይወት ታሪካቸው የህይወት፣ ስራና መንፈሳዊ አገልግሎት ተግባራቸውን አጣምረው ማቅረባቸው የአማኑኤል አብርሃምን አቀራረብ አስታውሶኛል፡፡
ታሪካዊ የሆነችውንና የተረሳችውን አንኮበርን እንድታንሰራራ የማድረግ ተግባራቸው ብዙዎቻችን ኤንጂኔሩን የምናውቅበት ስራ ይመስለኛል፡፡ አንኮበር ላይ ጥንታዊው የቤተክህነት ትምህርት የሚያንሰራራበትን አሰራር ለመዘርጋት የካህናት ማሰልጠኛ ስራ በሰሩ ጊዜ ለነፍሳችን እንዲህ የተጨነቁት ወንድማችን ለስጋችንስ ምን አስበውልናል የሚል ይዘት ያለው ቅኔ ቀርቦላቸው የመጣላቸውና በአምስት አመታት ትጋት ከውል ያደረሱት ድንቅ ስራ የአንኮበር ቤተመንግሥት ሎጅ ተገንብቶ ስራ መጀመሩ ነው፡፡
ተረፈ ከ70 አገሮች በላይ ጎብኝተዋል፡፡ 187 አገር ከጎበኙትና ከፒያሳ ልጅ መጽሐፍ ደራሲ እውቁ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ቀጥሎ በዚህ ረገድ የሰማሁት ሁለተኛ ሰው!
ጥሩ ትዳርና ሕይወት አላቸው፡፡ በበጎ አድራጎታቸው ለኖቤል የታጩ ሚስት አሏቸው፡፡ የሚያምር ትዳር በሚያማምሩ ማስረጃዎች፣ የሃምሳኛ ዓመት እዮቤልዮ አከባበርን ጨምሮ፣ በማቅረባቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዶክተር ሲቪል መሐንዲስ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህን አስታውሰውኛል፡፡ በዚህ ብቻም አይደል፡፡ የሸዋ ሰው በመሆን፣ በፋሸስት በመሳደድ፣ በአሜሪካ በመማር፣ በፈጠራ …
የዶክተር ፍስሃ ኃይለመስቀል ጓደኛ መሆናቸው ሁለቱም በበጎ ተግባር ላይ ስለተሰማሩ ትርጉም ይሰጣል፡፡ በዶክተሩ በኩል ያገኘሁት የብላታ ደምሴ ወርቃገኘሁ ዜና መዋዕል ‹‹ሞት ያልገታው ጉዞ›› ከአንኮበሩ ሰው የአርበኛ ቤተሰብነት ጋር የሚመሳሰል አካሄድ ስላለው ቢነበብ፡፡ ሜጀር ዮሐንስ ያላመለጠውን ግድያ ብላታ ተላልፈውት ነበር፡፡
ሀሁ በቀላሉ የኢትዮጵያ ፊደሎች አዲስ መማሪያ ዘዴ የሚል መጽሐፍ የጻፉትና አማርኛ መማርን ያቀለሉት በኩረጠቢባን መልካም ፈቃዳቸው ቢሆንና እንደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት ቢፈቅዱ መጽሐፉ እንደገና ወደ ህትመት ገብቶ ቢሰራበት እላለሁ፡፡
መጽሐፉ በሁለት ቋንቋ ማለትም በአማርኛና በእንግሊዝኛ መቅረቡ የአማርኛው ይዘት ጥልቀት እንዳይኖረው አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት አንባቢው በብዛት በሁለቱም ቋንቋዎች ማንበብ የሚችል መሆኑ ታስቦበት ሊሆንም ይችላል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጓደኛ፣ የእውነተኛው የእድሜ ባለጸጋና የምኒልክ ባሪያ የዘውዴ ነሲቡ ደጋፊ፣ የአለም ሎሬት የጥበበ የማነብርሃን የአገር ልጅ፤
እንደ ሙሉጌታ ኢተፋ የፈረንጅ አገር ዘረኝነት ሰለባ፣
እንደ ያዕቆብ ወልደማርያም የጽሕፈት ባለሙያ፣
እንደ እምዬ ምኒልክ የደሃ አባት፤
በኩረ ጠቢባን ኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ ወልደ መስቀል በመጽሐፉ ብዙ ነገር ስላነሱ መጽሐፉን እንድታነቡት በአክብሮት በመጋበዝና ለደራሲው እድሜና ጤና በመመኘት ልሰናበት፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...