ዓርብ 23 ኤፕሪል 2021

‹‹ዓለም ጭፍጨፋ ሲካሄድ ፀጥ ይላል፤ ጭፍጨፋው ሲያልቅ መታሰቢያ ያደርጋል›› የሆሎኮትስ መታሰቢያ ሙዚየም (ያድ ቫሸም) ጉብኝትና ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ

 

ዓለም ጭፍጨፋ ሲካሄድ ፀጥ ይላል፤ ጭፍጨፋው ሲያልቅ መታሰቢያ ያደርጋል

የሆሎኮትስ መታሰቢያ ሙዚየም (ያድ ቫሸም) ጉብኝትና ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ

መዘምር ግርማ

ሚያዝያ 13፣ 2013 ዓ.ም.

በእስራኤል የሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም (ያድ ቫሸም) ያዘጋጀውን ጉብኝት ለኢትዮጵያውያን መምህራን ትልቅ ጠቀሜታ ያለውና ለሃገራችንም እጅግ ወቅታዊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ አምባሳደር ረታ ዓለሙና አቶ ኑርሁሴን ኑሩ ባደረጉልን ግብዣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የሚዲያ ተቋማት የተውጣጣን ሰዎች ሁለት ሰዓት በፈጀው ጉብኝት ላይ ተሳትፈናል፡፡ 

ከጉብኝቱ በፊት ለተወሰኑ ቀናት ባደረኩት ንባብና ዳሰሳ ስለ አይሁድ ህዝብ ስደት (ዲያስፖራ) እና ለሺዎች ዓመታት በዓለም ዙሪያ ስለዘለቀው የዘርፍጅት፣ የመሳደድና የሃገር አልባነት ታሪክ ለመረዳት ችያለሁ፡፡  የአይሁድ ህዝብ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ሃገራቸውን መስርተው ያለፈውን ለመመርመር፣ የአሁኑን ህይወታቸውን ለማቃናትና ለወደፊቱም በሚገባ ለመዘጋጀት እንደቻሉም ተረድቻለሁ፡፡

በጉብኝቱ ዕለትም ለአንድ ሰዓት ተኩል ስለሙዚየሙ ገለጻ ተደርጎልናል፡፡ የቪዲዮ ጉብኝትም አድርገናል፡፡ በዕለቱ ከሙዚየሙና የምርምር ተቋሙ ሦስት እስራኤላውያን የተሳተፉ ሲሆን በሚገባ ገለጻ ድርገውልናል፡፡ አወያይተውናል፡፡ ውይይቱ ሲጀምር አቶ ኑርሁሴን ኑሩ በሰጡኝ ዕድል ራሴንና ስራዬን እንደሚከተለው አስተዋውቄያለሁ፡፡ በአንዲት ሩዋንዳት የተጻፈ መጽሐፍ ‹ሁቱትሲ› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ መተርጎሜንና ለንባብ ማብቃቴን ገልጫለሁ፡፡ ይህንኑ መጽሐፍም ወደ አፋን ኦሮሞ አስተርጉሜ ለህዝቡ አዳርሻለሁ፡፡ በትግርኛም ተተርጉሟል፡፡ በሚዲያ ስለ ዘረኝነት አስከፊነት ለተለያዩ ሚዲያዎች ቃለመጠይቆች ሰጥተናል፡፡ የኔ ጥረት ህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ ፈጥሯል፡፡ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ዘንድ ግን መድረሴን እርግጠኛ እንዳልሆንኩ ተናግሬያለሁ፡፡

በ1953 የተመሰረተው ይህ ሙዚየም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮፓ በፀረ-ሴማዊ ዘረኛ አይዲዮሎጂና ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ሕይወታቸው ላለፈው አይሁዶች መታሰቢያ ነው፡፡ ጥላቻ የሚያስከትለውን ጉዳትና በማናቸውም ቦታ የምንገኝ የሰው ልጆች በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ማድረግ ስለማይገቡን መጥፎ ነገሮች ያስተምራል፡፡ የዓለምአቀፉ ፖለቲካም የዘርማጥፋትን ለመከላከል ፍላጎት ያሳየበት እነዚህ ተመራማሪዎች የሚያውቁት ጊዜና ክስተት እንዳልነበረ ገልጸውልናል፡፡ ዓለም ጥሩ የሆነችው የዘርማጥፋት ከተፈጸመ በኋላ ሰለባዎቹን በማስታወስ ነው ብለውናል፡፡

የያድ ቫሸም የቪዲዮ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ ሲጠናቀቅ ግንዛቤያችንን በሚገባ አሳድጎታል ለማለት እችላለሁ፡፡ ለአስርት ዓመታት በጉዳዩ ላይ የተመራመሩ ምሁራን ያደረጉልን ገለጻ ትምህርት ሰጪ ነበር፡፡ በመጨረሻ የጥያቄ ዕድል ተሰጥቶ ሁለት ጥያቄዎችን ጠይቄያለሁ፡፡ እነሱም

ሀ. ያደረጋችሁልን ገለጻ በጣም አስተማሪ ነው፡፡ የአይሁድ ሕዝብና ጀርመን አሁን ሰላማዊ ግንኙነት ማድረጋቸው ከጥፋት በኋላም እንኳን ሰዎች ተራርቀው እንደማይራራቁ አስተማሪ ነው፡፡ የዘርማጥፋት አደጋን ለማስወገድ ግን አሁን ካለንበት የእሳት ማጥፋት ደረጃ አንጻር በቀጥታ ሚና ያላቸው ፖለቲከኞቹ ላይ የእስራኤል መንግስት ግፊት አድርጎ ብሄራዊ እርቅ ቢደረግ አይሻልም ወይ?

ለ. እናንተ ተመራማሪዎቹ በዚህ በአይሆዶች የዘርማጥፋት ጉዳይ ላይ ዘወትር ስታነቡ፣ ስትወያዩና ስትመራመሩ አእምሯችሁ አይጎዳም ወይ? እኔ በግሌ ስለገጠመኝ ነው፡፡

ስለ መጽሐፌ ስለ ሁቱትሲ ለመግለጽ ያህል የዚህን መጽሐፍ የእንግሊዝኛ ቅጂ ያገኘሁት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቤተመጻሕፍት በ2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ መጽሐፉን ሳነበው ከሩዋንዳ የቱትሲ ዘርማጥፋት ሂደት አንጻር ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው ዘር ተኮር ፖለቲካ አሰጋኝ፡፡ ስለሆነም በ2008 ዓ.ም. መጽሐፉን ተርጉሜ አሳተምኩ፡፡ በህብረተሰቡም ዘንድ ስለዘር ጥላቻ አደገኛነት ውይይትን ለማጫር በቃ፡፡ በ2012 ዓ.ም እንደገና መጽሐፉን በማሳተም 2ኛ፣ 3ኛና 4ኛ ዕትም አውጥቼ ለማሳተም በቃሁ፡፡ ወደ ኦሮምኛም ያስተረጎምኩት ህዝቡ በሚችለው ቋንቋ ሃሳቡ እንዲደርሰው በማሰብ ነው፡፡ ከትግርኛው ተርጓሚም ጋር በመገናኘት የሚዲያ ቃለመጠይቆች ሰጥተናል፡፡ መጽሐፉ እየሄደበት ያለው ፍጥነትና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዘር ማጥፋት አሳሳቢነት ስላልተመጣጠነ መጽሐፉን በፒዲኤፍ ለህብረተሰቡ በነጻ ለመልቀቅ ወስኜ ለቅቄያለሁ፡፡ ይህም በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑና በክፍለሃገር የሚገኙ ወጣቶች እንዲያገኙት በማሰብ ነው፡፡ ደርሷቸው አንብበው የሚደውሉልኝ አሉ፡፡ ‹‹ዘረኛ ነበርኩ፤ ከአሁን በኋላ ግን አልሆንም!›› የሚል መልዕክት የላከልኝም አንባቢ አለ፡፡

በጉብኝቱ የቱትሲና የአይሁዶች የዘርማጥፋት ስላላቸው ተመሳሳይነት ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ይህም የሆነው ገለጻ አድራጊዎቹ ከተናገሩትና ራሴም ከወሰድኩት ግንዛቤ ነው፡፡ ተመሳስሎው የዘር ጥላቻን ከመቀስቀስ አንጻር፣ ፍጅቱ ሴትንም ሆነ ህጻናትን ካለመማሩ አንጻርና ከአደረጃጀቱ ሁኔታ አንጻር ነው፡፡  

ለማጠቃለል ያህል የዘርማጥፋት ስጋት ለዛሬ ለነገ የምንለው አይደለም፡፡ ህብረተሰቡን ማስተማር ይገባናል፡፡ ታዋቂ ሰዎችን፣ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን፣ ጄኔራሎችን ሳይቀር ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ማስተማር አለብን፡፡ ምክንያቱም ከዘር ማጥፋት የሚያተርፍ ስለሌለና በሆሎኮስትም ሆነ በሩዋንዳ እንደታየው የዘርማጥፋትን ደግፎና አካሂዶ ከተጠያቂነት የሚያመልጥ እንደሌለ ለማስገንዘብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጥሩ አስተዳደር ካገኘች ለሁሉም ህዝብ የሚበቃ ሃብት ያላት ሃገር ነች፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የተለያዩ ህብረተሰቦች በሰላም የሚኖሩት የዘር ጥላቻንና ዘርተኮር ፖሊሲን ስናስወግድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በውይይትና በመግባባት የነገውን የሃገራችንን እጣ ፈንታ ለማስተካከል እንችላለን፡፡ ለዚህም በያድ ቫሸምና በኢምባሲችን የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብርና ድጋፍ እንዲቀጥል ያስፈልጋል፡፡

 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...