2021 ኤፕሪል 25, እሑድ

ነገ ጨለማ ወይስ ብርሃን?

 

ነገ ጨለማ ወይስ ብርሃን?

በመዘምር ግርማ

 

እነሆ ብዙ ትናንቶችን አሳልፈን ከዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ እንምጣ ዛሬ ካለንበት የደረስነው ሁሉ ስለነገ ልናስብ ግድ ይለናል፡፡ የዛሬ ሩጫ ስለሚያደክመን ግን ለነገ የምናስብበት ዕድል ጠባብ ይመስላል፡፡ ነገን ከምን አንጻር እናስብ ስንል ከብዙ ነገር አንጻር ይሆናል፡፡ ከተወሰኑ ፍላጎቶቻችን አንጻር ነገን ለማየት እንሞክር፡፡ በኔ ምናብ የሚታየኝን አይቼ የናንተን በቀጣይ ጊዜያት ልታጋሩን ትችላላችሁ፡፡

ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ማለትም ከምግብ፣ ከመጠለያና ከአልባሳት አንጻር እንኳን ያየን እንደሆነ ከዕለት ዕለት ለብዙኃኑ አዳጋች እየሆነ ያለ ነገር ነው፡፡ ለምን ያህሉ ዜጋችን በዕለት የሚያስፈልገውን ማቅረብ ችለናል? በጊዜ ሂደት እየተወደደ የመጣው ኑሮ ስንቱን ከመሃል ከተማ ገፋ! ስንቱስ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱ ለማግኘት ቻለ? ይህን ለማሟላት ባለመቻልስ ስንቱ የበዪ ተመልካች ሆነ? የሰው እጅ ለማየት የበቃውስ? በበጎ አድራጊ ወይም በመንግስት ድርጅት ስም በስማቸውስ ስንት ገንዘብ ተወራረደ? ስንቶችስ በለጸጉ? ነገን በዛሬና ዛሬን ከትናንት አነጻጽረን በምናገኘው ውጤት ስናየው እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ የሚሄድ አለመሆኑን ነው፡፡ እየተሻሻለ የማይሄድ ነገ ይዘን እንዴት ስለነገ ሳናስብ እንቀመጣለን? ለምንስ የችግሩን ምንጭ ለመረዳት አንሞክርም! ከችግር ፈጣሪነት ገለል ለምን አንልም? ከተቻንስ መላ ለምን አንዘይድም!

ከትምህርት አንጻር ነገ ምን ይመስል ይሆን ብለን እንይ፡፡ ትምህርት ከትናንት በበለጠ ተደራሽ መሆኑን ለማየት በትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች መብዛት ማየት ይቻላል፡፡ በፊት በዞን ከተማ የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሁን በወረዳ ደረጃ እየሆነ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በዞን ባይዳረስ ኮሌጅ አይጠፋም፡፡ የዚያን ያህል ትምህርት ለውጥ አምጥቷል ወይ ነው ነገሩ፡፡ ያመጣቸው ለውጦች ይኖራሉ፡፡ የትምህርትን ፍሬ ግን ለህብረተሰባችን ለማዳረስ ችለናል ወይ? የተማረ እንደመብዛቱ፣ ትምህርት ቤት በየደጁ እንደመከፈቱና ሰው በርቀትም ሆነ በቴክኖሎጂ የመማር ዕድል እንደማግኘቱ የባህሪ ለውጥ ማምጣትና ችግር መፍታቱ ላይ ጥቂት የተማሩ ሰዎች ከነበሩባቸው ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ነገስ ምን ይዞ ይመጣል? ቆም ብለን ካላሰብን እየባሰ እንጂ እየተሻለ እንደማይሄድ ነው፡፡

በሰዎችስ መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት ምን ይታየኛል ብዬ ራሴን ስጠይቅ ከተወሰኑ ዓመታት ከነበረው ጊዜ አንጻር አሁን ምን ይመስላል? አሁን ብሷል! ሰው ለሰው አላዘነም! ልዩነቱ እንጂ ሰውነቱ አልታየውም፡፡ በዚያም ልዩነት ሰበብ ማጥቃት እንጂ መደገፍ አልቻለም፡፡ ነገስ? ነገ ምን አይቶ ይሻሻላል? ምንም! አሁን ቆም ብሎ ማሰቢያውና ነገን መቀየሻው ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም አሁን ያልተጠቀንምበት ዕድል ነገ ብንጮህ ላይገኝ ስለሚችል፡፡ ዛሬ የሚሰራው መጥፎ ስራ ትናንት ከነበረን ዕድል በላይ ነገን እያበላሸው ስለሚሄድ፡፡

መንፈሳዊ ነገሮችና እርካታንስ አስመልክቶ፡፡ የባሰው ነገር እዚህ ጋ ነው፡፡ ሰው ለመንፈሳዊ እርካታው እየሰራ ሳይሄድ ሲቀር፣ ባጠቃላይ ባለው ነገር የማይረካ ሲሆን የበለጠ ተስፋ መቁረጥና ደስታ ወደማጣት ይሄዳል፡፡ የዚያም ድምር ውጤት ነገን ያጨልማል፡፡ ተስፋ እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ነገ የባሰ እንዳይሆን አሁን ራስን ቆም ብሎ ምን ያህል መንፈሳዊ ነገር ላይ ሰርቻለሁ፣ አጠቃላይ ስብዕናዬና እርካታዬስ ምን ላይ ይገኛል ብሎ ማሰቢያው አሁን ነው፡፡

ነገን ጨለማ ለማድረግም ሆነ ብርሃን ሁላችንም ኃላፊት አለብን፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ መሰራት አለበት፡፡ ሥልጣኔ እየበዛ ሲሄድ ህይወታችን እየተበላሸ መሄድ የለበትም፡፡ የእናንተን ዕይታ በአስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጡልኝ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...