2021 ኤፕሪል 25, እሑድ

ዘመዶቼንና የአገሬን ሰዎች ማግኘት የሚፈጥርብኝ የተደበላለቀ ስሜት

 

ዘመዶቼንና የአገሬን ሰዎች ማግኘት የሚፈጥርብኝ የተደበላለቀ ስሜት

11.12.10

ዛሬ ቅዳሜ በለቅሶ ምክንያት ሞጃዎችን ላገኛቸው ችያለሁ፡፡ አንዳንድ ነገርም ስለታሰበኝ ማስታወሻ ያዝኩ፡፡

1.     አደረጃጀታቸው

በሐዘን ጊዜ በአብዛኛው እገኛለሁ፡፡ በደስታ ግን አይቀየሙኝም እያልኩ እቀራለሁ፡፡ ሐዘኑ የወገንን መጎዳት እንደመጋራት ስለሚታየኝ ብዙም አልቀርም፡፡ የቀሩሁባቸውንም ሳገኛቸው ባለመቻል ወይም በሰዓቱ ባለመስማት አለመገኘቴን እናገርና በመጠኑ ለህሊናዬ ይቀለኛል፡፡   

በተገኘሁባቸው አጋጣሚዎች መታዘብ እንደቻልኩት ግን ሞጃዎች ድርጅታቸው ጠንካራ ነው፡፡ ዕድር አላቸው፡፡ ዕድሩ የተሟላ ሲሆን፤ ቁሳቁስ፣ የሠው ኃይል፣ የአመራር ተዋረድ ሥርዓትና አፈጻጸም ክትትል ጭምር አላቸው፡፡

አስገራሚ የሆነ የድንገተኛ ጊዜ አደረጃጀታቸው አሁን በዘመኑ ቴክኖሎጂ ታግዞ በስልክ እየተጠራሩ አንድ ለቅሶ ካለ ከጋውና እስከ አዲስ አበባ ያለ ሰው ለቀብር እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ በፊት ቢሆን መልዕክተኛ ተልኮ ይናገሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በለቅሶ ጊዜ ለለቀስተኛው ምግብ ያቀርባሉ፡፡ በፊት ንፍሮ ይሰጥ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡ ህብረተሰቡም የተጎዳውን ለማጽናናትም ሆነ ሐዘኑን ለመጋራት አይቸገርም፡፡ ሙሾ ያወርዳሉ፡፡ ቀብር ያስፈጽማሉ፡፡ ይሰናበታሉ፡፡ ነፍስ ይማር ይላሉ፡፡ 

ለዚህ የድንገተኛ ጊዜ ችግር ሁልጊዜ ዝግጁ መሆናቸውን የምታውቁት አንድን ሰው ሁሉም ለቅሶ ላይ ከሳሲት ድረስ እየመጣ ስታገኙት ነው፡፡ ስራውን በወቅቱ እየጨረሰ በድንገተኛ ሁኔታ ላይ ለመገኘት መቻሉ ያስደንቀዋል፡፡ በግሉ የግብርና፣ የንግድ ወይም ሌላ ስራም ይስራ፣ ይቀጠርም እንደምንም ተቸግሮ ይመጣል፡፡ ይህ የሚያሳየኝ ለማህበራዊ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥና ነባር ትስስሩንም ከዚህች ተቀያያሪ ዓለም ተጽዕኖ አርቆ እንዳቆየ ነው፡፡ 

 

 

 

2.     ሳትጠይቀን ምነው ጠፋህ?

እንደኔ ያለ ልጃቸውን የሚያገኙት እጅግ አልፎ አልፎ ስለሆነ ሳይሰማቸው አይቀርም፡፡ ደብረብርሃንም እንደሆነ በቀበሌ 09 ተወስኜ የቀረሁ ስለሆንኩ አያገኙኝም፡፡

 

ስራ-ተኮር ሳልሆን አልቀርም፡፡ ስቴፈን ኮቬይ መርህ ተኮር የሚለውን ገና ስላልሆንኩ ስራ ስራዬን ስል ማህበራዊ ጉዳዬን፣ ወዳጅ ዘመዶቼን ስለረሳሁ በልቅሶ ብቻ ላገኛቸው ተገድጃለሁ፡፡

 

አገር ቤት ካሉት ወዳጅ ዘመዶቼ ከስንት አንዴ ስሄድ የሚያገኙኝ ወይ ዘመዶቼ ወይ ጎረቤቶቼ ናቸው፡፡ እዚያ የምቆየውም ግማሽ ቀን ይሆናል፡፡

በነዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሳገኛቸው ምነው ሳትጠይቀን ጠፋህ ይሉኛል፡፡ በምንም በምንም አድበስብሼ አልፋለሁ፡፡ በህልፈተ-ህይወታቸው ወይንም በሚጎዱ ጊዜ የምቆጭባቸው ብዙ ትዝታቸው ያሉብኝ ወይም የማስታውሳቸው ሰዎች አሉ፡፡

ከወላጆቹና ዘመዶቹ ጋር አንድ መንደር ኖሮ የሚሞተው ሰው ነው የኛ ዓይነቱ የሚሻለው? ከኛም የባሰ በባዕድ አገር የሚኖሩ አሳዛኝ ፍጥረታት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ኑሮው ቢደላቸው እንኳን ናፍቆቱና ችግሩ አይለቃቸውም፡፡

 

3.     ምን ደረጃ ደረስክ?

ሳድግ እንዳዩኝና እንደሚያውቁኝ ምን ደረጃ እንደደረስኩ ለማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ቤት ሰርቼ እንደሆን፣ ትዳር ይዤ እንደሆን፣ ማዕረግ እንዳለኝ፣ ልጃቸውን አገኘው እንደሆን ወዘተ ይጠይቁኛል፡፡ አንዳንዱ ያለሁበት ሁኔታ ሲያስደስታቸው አንዳንዱ ያስከፋቸዋል፡፡ ይመክሩኛል፡፡ የምስማማባቸው ምክሮች እንዳሉ ሁሉ የማልስማማባቸውም አይጠፉም፡፡ ዓመት ከዓመት የሚመክሩኝና እኔ የማልሻሻልባቸው ነገሮች ሦስት ናቸው፡፡ ለእነሱ እልህ ነው መሰለኝ እኔም አላሻሽል ብያለሁ፡፡ ሞጃዎችን ማናደድ ግን ምን ያደርግልኛል!

 

4.     ቀብሬን አድርገው ባገሬ

እንደ በዓሉ ግርማ የምቀበርበትን አላውቀውም አልላችሁም፡፡ እንደራስ መስፍን ግን ሐውልቴን አላሳንጽም፡፡

ዘመናዊውን ትምህርቴን ከማህበረሰቤ አስተሳሰብ ጋር የማስታርቅበት መንገድ የለኝም፡፡ በአቸቤ ልቦለድ ላይ ያለውን ሚካኤል ኦቢን የሚመስል ስብዕና ያለኝ መሰለኝ፡፡ ቢሆንም

እስከ ቀብሬ ድረስ ግን ብዙ ታሪክ መስራት ይኖርብኛል!

 

የኔልሰን ሩሃሊሃሊሃ ማንዴላን ትልቁን መጽሐፍ - ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም - የሚለውን አንብቤዋለሁ፡፡ እዚያ ላይ እንዳየሁት ማንዴላ የትውልድ መንደራቸውን ኩኑን ጥለዋት የሄዱት የስምንት ዓመት ልጅ ሳሉ መሰለኝ፡፡ ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት እያየ ያስቀበራቸውም ኩኑ ላይ ነው፡፡ በተወለዱበት የመቀበር ዕድል ለማናችንም መነፈግ የሌለበት ይመስለኛል፡፡ ከኩኑ እስከ ኩኑ - ከሳሲት እስከ ሳሲት፡፡  

 

 

5.     ስሜታቸው

ከእነሱ አነስ ስለምል ወንዱም ሴቱም አንቺ የሚሉኝ ሰዓት አለ፡፡ የሚወዱኝና የሚያከብሩኝ እንዳሉ ሀሉ የሚጠሉኝም አይጠፉም፡፡ በየአጋጣሚው ለፍቅሩም፣ ለጥላቻውም፣ ለአክብሮቱም ለንቀቱም ጊዜ ስለነበረው፡፡

 

6.     ትዝታቸው

ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ሳገኛቸው ከኔ ጋር ያላቸውን ብዙ ትዝታ ይነግሩኛል፡፡ አንዱ ልጅ ከገጠር ሳሲት መጥቶ ከኔ ጋር እንደመጣላት እንዳለና ‹‹አፍንጫህን ነው የምልህ›› እንዳልኩት፡፡ ከኔ በቁመቱና በአቅሙ ከፍ ቢልም ‹‹ትመታኝ ይሆን እንዴ ይቺ ልጅ›› ብሎ ሰግቶ ሳይጣላኝ እንደሄደ እንዳወጋቸው ዛሬ ያገኘኋቸው ነገሩኝ፡፡ እኔ ግን ረስቼዋለሁ፡፡ አስቆኛል፡፡ እንዲያውም ለጠብ የሚደፍሩት እኔን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

በተያያዘ ዜና አንድ ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚባል ጥቁር ልጅ ሳሲት ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ታዲያ የፈላ ተማሪዎች በሳሲት ጉድኝት ለስፖርት ውድድር መጥተው አሸንፈው ኖሯል፡፡ ዛሬ ከነሱ አንዱ ሲነግረኝ ማለት ነው፡፡ ትምህርት ቤት ያለውን የከፍታ ዝላይ ምናምን ውድድር ጨርሰው ወደ መስክ ለሩጫ ሲሄዱ በሆታ ነበር፡፡ ‹‹ፈላ ጉድ አፈላ›› እያሉ፡፡ ያ ልጅ ስለ ሳሲት መሸነፍ አዝኖ ይሁን ወይም ለጠብ ፈልጓቸው አነስ ያለውን ልጅ እየተከተለ ይተናኮላል፡፡ አነስ ያለውም ልጅ ሊጣላው ይጋበዛል፡፡ ጠጋ ሲለው ያ ትንሽ የመሰለው የሳሲት ልጅ ደረቱ ላይ ጸጉር ያወጣ ጎረምሳ መሆኑን ያያል፡፡ ጠቡን ትቶ ሸሸት የሚለውን ትንሽ ልጅ ጎረምሳው መተናኮሉን ቀጥሏል፡፡ በመጨረሻ ትልልቆቹ ጣልቃ ገብተው አስጣሉኝ አለን፡፡ ሁሉም ለኔ ጋር ትውስታ ካላቸው እያንዳንዱን ጠባሴ፣ ደብረብርሃን በሚገኘው ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ባገኛቸውና ባናግራቸው ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያው እኔ ለቅሶ ከመጣብኝ ቤቴ ባዶ ስለሆነች ራስ አበበ ቤተመጻሕፍት ለቀስተኛ እንደምንቀበል ከጓደኞቼ ጋር ስለምንቀልድ እውነትም ይሆን ይሆናል፡፡

 

7.     ምን አደረኩላቸው

ይህ ስሜት የሚሰማን ልንኖር እንችላለን፡፡ ተሰምቶን የሆነ ነገር እናድርግ ብንል በሆነ መልኩ ልንሞክርና ልንፍጨረጨር እንችላለን፡፡ በአብዛኛው ግን ዝምተኞችና አቅም ያጣን ነን፡፡ አጠቃላዩ ነገር ከላይ እንዲሻሻል በማሰብ ከፖለቲካ እስከ ውትድርና በሃገር ደረጃ የሚፍጨረጨሩ ሞጃዎች ይኖራሉ፡፡ ሁሉም በጊዜ ሂደት ውጤቱ የሚታይ ይሆናል፡፡ የህብረተሰቡም ለውጥ እንደዚያው፡፡

ሞጃዎች የሚፈልጉት ግን ምንም እንድናደርግላቸው አይደለም፡፡ ልጃችን እዚህ ደረጃ ደረሰልን ለማለት እንጂ፡፡ ይህም የኛን ጥሩ በመውደድ ነው፡፡ ይህ የአብዛኛው ሁኔታ ነው፡፡

አንዳንዴ የሚከሰቱና መታረም ያለባቸው ነገሮች አሉ፡-

‹‹አንተ››

‹‹ወይ››

‹‹እንተናን ታቀዋለህ››

‹‹የቱን››

‹‹ያን አብሮን የተማረውን››

‹‹አዎ››

‹‹እንትን አገር በእንትንነት እየሰራ ብዙ ገንዘብ ያገኛል››

‹‹ምናባቱ አሁን እሱ አይጥ››

‹‹ምን አረገህ››

‹‹ተወው እባክህ››

 

ይህን አይነት ወግ አሳልፌያለሁ፡፡ ለዚች አጭር እድሜ እስኪ እንዋደድ፡፡ ደግ ደጉን እንመኝ፡፡ የቤተሰብ ቂም፣ የግል ፉክክር፣ መጥፎ ስሜት የትም አያደርሰንም፡፡ ራሳችንን ይጎዳናል፡፡

 

ብዙ ላደረገልን ህዝብ ምንም ውለታ ስላልከፈልን እስኪ በዚህ ዙሪያ እናስብ፡፡

 

8.     ለቅሷቸው

በደስታ ጠርታችሁኝ አልመጣሁም፡፡ እስኪ ወደፊት ጥሩኝ፡፡ ደጋግማችሁ ጥሩኝ፡፡ ልጅ ልካችሁ አስወስዱኝና ደስታንም ልላመደው፡፡ በሐዘን ብቻ ሳገኛችሁ ዘመዶቼ ሁልቀን ተጎዱብኝ እያልኩ ማሰቡ ይግዳኛል፡፡ እናንተም እኔን በለቅሶ ላይ ብቻ ካለ ትዝታ ጋር ማስተሳሰርን ትተዉ ይሆናል፡፡

 

9.     ሞጃ በፖለቲካ

ሞጃ እንደማንኛውም ማህበረሰብ ፖለቲካ የገባት ነች፡፡

አሁን ያለው ተስፋ ሰጪም ተስፋ አስቆራጭም ሁኔታ ያሳሰባችሁ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ምልከታችሁ ገብቶኛል፡፡

ከኢትዮጵያ ህዝብ የጦርነት ልምድ ያለው ህዝብ እንዳለ ነግራችሁኛል፡፡

ተዘዋውራችሁ ያያችኋት ለምለም አገራችንን የማስተዳደር አቅምና ፍቅር እንዳጣን አጫውታችሁኛል፡፡

ከአገራችን ህብረተሰቦች በአገዳደል ሳይቀር አረመኔነት የሚታይባቸው እንዳሉ ተማምነናል፡፡

 

10.  ማጠቃለያ

እያንዳንዳችሁ በማህበራዊ ጥሪ ላይ ስትገኙ የምትመጡት ቤታችሁን ዘግታችሁ፣ ስራችሁን አቋርጣችሁና ልጆቻችሁን በትናችሁ ስለሆነ ያስመሰግናችኋል፡፡

ከሃያ ዓመት በኋላ ስለተያየንና ደግመን ስለማንተያይ የምንነፋፈቅና ተራርቀን የምንቀር ሰዎች መኖራችን ይገርመኛል፡፡

የደብረ ብርሃን ቀበሌ 08 የሚገርም ሰፈር ነው፡፡ ነዋሪው በብዛት ሁሉም የሞጃ ተወላጅ ነው፡፡ አንድ ላይ የተሰባሰብንበት እውነተኛ ምክንያት አልገባኝም፡፡ ማህበራዊ ይሆን? የጸጥታ? የንግድ?

ያለን ሐብት እህል ብቻ ነው እንዴ?

በተሻለ መንገድ እንዴት እንገናኝ?

የልብ ህመም ያመማት አንድ እህታችን ወደ ህንድ አገር ሄደሽ ካልታከምሽ አትድኚም ስለተባለች እንዴት እናሳክማት?

የቤተሰቡ አባል የሚሞትበትን ሰው ከእድር ውጪ የምናግዝበት አደረጃጀት መፍጠር እንችል ይሆን?

መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ፡፡ እወዳችኋለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...