ማክሰኞ 25 ሜይ 2021

በዩኒቨርሲቲዎች ሊተገበር ስለታሰበው የትምህርት ክፍሎች መዘጋት (እየተጻፈ ያለ)

በዩኒቨርሲቲዎች ሊተገበር ስለታሰበው የትምህርት ክፍሎች መዘጋት (እየተጻፈ ያለ)

በመዘምር ግርማ

በሃገራችን ታሪክ ውስጥ እንደ አማርኛ፣ ታሪክና ፍልስፍና የመሳሰሉት የማህበራዊ ሳይንስና የሰብዓዊነት ትምህርት ዘርፎች በየጊዜው ጫና ሲደረገባቸው እንደቆየና ሲንገዳገዱ እዚህ እንደደረሱ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚካሄዱ መድረኮች የውይይትና የክርክር ርዕሶች ነበሩ፡፡

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ዩኒቨርሲቲዎችን በተለያየ ዘርፍ ለመመደብ ያለመ ነው፡፡ ዲፈረንሼሽን (ወይም ልየታ ልንለው እንችላለን) የተሰጠው ስያሜ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲዎችን የምርምር፣ አፕላይድና ኮምፕሪሄንሲቭ በሚል ይከፍላል፡፡

የትምህርት ክፍሎችን በጫና፣ ተማሪ እንዳይመርጣቸው በማድረግ፣ የስራ ዕድል በማሳጣትና በሴራ ሲዘጉ የቆዩ ፖለቲከኞች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ አሰራር ቀጥሎም በሃገር አቀፍ ደረጃ ከላይ ወደታች ለማለት በሚቻል መልኩ የዩኒቨርሲቲዎች የወደፊት ዕጣ የተወሰነ ይመስላል፡፡

እኔ እንደ ከፍተኛ የትምርት ተቋም ሰራተኛነቴ ሃሳቤን አልተጠየኩም፡፡ ምንም ዓይነት መረጃም እንዲደርሰኝ አልተደረገም፡፡ እኔ ካልደረሰኝ ሚዲያዎች አልሰሙ ይሆናል፡፡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ የየአካባው ማህበረሰብም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት አልሰሙ ይሆናል፡፡ ስለጉዳዩ ጥቂት መረጃ ለመስጠት ያህል በየጊዜው የሚዘጋና የሚከፈተው የትምህርት ክፍል ወሬ ይቀያየራል፡፡ ብዙ ቅሬታንና ግርታን የፈጠረ ጉዳይ መሆኑ ግርምትን አጭሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ራዕይና ተልዕኮ ያለውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ከመሆኑ የተነሳ እንደዚህ ያሉ ድንገተኛና ግብታዊ ውሳኔዎች ሊተገበሩበት አይገባም፡፡ የየአካባቢው ህዝብም ሆነ የአገሪቱ ህዝብ ሊወያይና ለወስነበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ልሞክር፡፡ ከመጀመሪያው የትምህርት ክፍሎቹ ለምን ተከፈቱ?

አያስፈልጉም ነበር ወይ?

አንድ አንኮበር፣ ሸዋሮቢት፣ ደብረብርሃን ወይም መዘዞ ያለ መምህር፣ ዳኛ፣ ነርስ፣ ወይም ሌላ ነዋሪ ዲግሪና ማስተርስ ተምሮ ራሱን ለማሸሻል ስለማይችል ዕድገቱ ይቆማል፡፡ ወደ ሌላ ክልል እንዲሄድ ለምን ይገደዳል? መሄድስ ይችላል? ካሁን በፊት አማርኛ ለመማር ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልል ይመጡ ነበር፡፡ አሁን አማርኛ ሲዘጋ ወዴት ክልል ይሂዱ?

በርካታ ተማሪ ወደ ሌላ ቦታ በጸጥታም ሆነ በቤተሰብ ጉዳይ ለመሄድ ባለመቻሉ በቅዳሜና እሁድ መርሃግብሮች እንደሚማር ይታወቃል፡፡ የትምህርት ክፍሉ ከተዘጋ ግን በዞኑ መማር ስለማይችል የመጨረሻው የትምህርት ደረጃው በ12ኛ ክፍል ተገድቦ ይቀራል ማለት ነው፡፡ ይህ ፍትሐዊ ነው?

የዳሰሳ ጥናት ተሰርቷል?

ዕቅዱን በነባርና ስንትና ስንት ቢሊዮን የግብር ከፋይና የእርዳታ ገንዘብ በፈሰሰባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመሞከር አዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ከፍቶ መሞከረ ታስቦበታል?

ዕቅዱ የማን ራዕይ ነው? አስፈላጊነቱስ? አንገብጋቢነቱስ?

የህዝቡ ፍላጎት ተጠይቋል?

የሰራተኛው ፍላጎትስ?

ዩኒቨርሲቲው እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ያስተማራቸው መምህራን ባሉበት ለምን ትምህርት ክፍሎችን ይዘጋል?

ስንት ተለፈቶባቸውና በሚሊዮን ገንዘብ ወጥቶባቸው የተሰሩ ቤተሙከራዎች፣ መሰረተ ልማቶችና የስራ ክፍሎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

ይህ አካባቢ ወይም ህዝብ ምህንድስና ያስፈልገዋል፣ ታሪክ አያስፈልገውም ለማለት ወሳኙ ማነው? በሌላ አካባ ያለውስ ቢሆን ቋንቋ መማር ተፈቅዶለት ማኔጅመንት መማር ለምን ይከለከላል?

የማስተርስ ፕሮግራም ለመክፈት አስጸድቀው የነበሩ የትምርት ክፍሎች ለምን እንቅስቃሴያቸው ታገደ?

በአካባቢው ያሉ ከተሞች የጂአይኤስ ባለሙያና የሳይንሱ ትሩፋት አያስፈልጋቸውም?

 

ስለ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ

የተመደበበት፡- Applied Sciences

ይቀጥልባቸዋል የተባሉት ዘርፎች፡- Engineering and technology, Business and Economics, highland agriculture, other Health sciences

የቀረበው ምክንያት ፡- Industry zone, proximity to central market, strength in health education

ይህን እንዴት አያችሁት?

 


1 አስተያየት:

  1. በዚህ መልክ የታቀደ ነገር ካለ ለውይይት ክፍት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ይህ ሳይሆን በቀጥታ ወደ ውሳኔና ትግበራ የሚኬድ ከሆነ ሀሳቡ ቅቡልነት የሚጎድለው ከመሆኑም በላይ የአንድ ወገን/አካል ፍላጎት እና ግብን የተሸከመ ውሳኔ ነው የሚል ጥርጣሬንም ያጭራል። የሚዘጉ የትምህርት ክፍሎች ከዚህ ቀደም ለምን እየተተገበሩ እንደነበር፣ የነበራቸው እና ያላቸው ሀገራዊ ፋይዳ እንዲሁም ስለተዘጉ ሊመጣ የታሰበው ለውጥ በጥናት ተደግፎ ሊቀርብና ሰፊ ውይይት በምሁራን እና በማህበረሰቡ ሊደረግባቸው ይገባል።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...