2021 ሜይ 14, ዓርብ

የራስ አበበ አረጋይ ማስታወሻ ስያሜ ሽሚያዎችን አስመልክቶ የቤተመጻሕፍታችን አቋም

 

የራስ አበበ አረጋይ ማስታወሻ ስያሜ ሽሚያዎችን አስመልክቶ የቤተመጻሕፍታችን አቋም

በሁለተኛው የኢጣሊያና ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከነበሩ ፈርጦች ግንባር ቀደሙ ራስ አበበ አረጋይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጦር በስኬት በመምራት በዱር በገደል ለአምስት ዓመታት ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ፍልሚያ አድርገው የሃገራቸውን ነጻነት አረጋግጠዋል፡፡ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያን ባንዲራ ካውለበለቡ ጥቂቶች የጦር መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ የኢጣሊያ ፋሽስት መሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ በብሔርና በቋንቋ ከፋፍለው ለመግዛት ይጥሩ በነበረበት በዚያ ወቅት ራስ አበበ አረጋይ በአንጻሩ በሸዋ የአማራና የኦሮሞ ህዝብን አስተባብረው የተራዘመውን ጦርነት በመምራት ለድል የበቁ ናቸው፡፡

ራስ አበበ አረጋይ 1953 መፈንቅለ መንግሥት በአረንጓዴው ሳሎን ግድያ ሕይወታቸውን ያጡት ኢትዮጵያን ከሚወዱትና ለምዕራባውያን ከማይመቹት መሪዎች አንዱ በመሆናቸው ነበር፡፡ 1950ዎቹ ታቅዶ የነበረው ጭሰኝነትን ከኢትዮጵያ የሚነቅል የተባለለት ሰፊ ፕሮጀክትም ሰይፈጸም ቀርቷል፡፡ ከዚያ ወዲህም ሃገሪቱ ወደባሱ ዘርፈብዙ አዘቅቶች በመግባት እድገቷ ቁልቁል እየወረደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ታሪክን ለማስታወስ እነሆ ዘመኑ ደርሶ ራስ አበበ አረጋይም ሆነ ሌሎች የሃገር ባለውለታዎች በትውልድ እየታወሱ ይገኛሉ፡፡ እኔ በግሌ በታሪክ ትምህርት ስለጀግናው ራስ አበበ አረጋይ ተምሬ አልፌያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም በመጀመሪያ ዲግሪ ስመረቅ የመመረቂያ ጽሑፌንም በአርበኞች ተጋድሎ ላይ በተጻፈ ታሪካዊ ልቦለድ ላይ ስሰራ ከዚሁ ፍላጎቴ ይመነጫል፡፡ ከምረቃ በኋላም ታሪካዊ ጉዞዎችን በማድረግ በማስተባበርና የጉዞ ማስታወሻዎችን ጽፌ በማስነበብ አርበኞቻችንና ታሪካችን እንዲታወሱ ጥሬያለሁ፡፡ 2008 .. ከተርጓሚ፣ ደራሲና የትያትር ሰው አሊሹ ሙሜ ጋር ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን ስንመጣ አካባባውንና ታሪኩን እያነሳን መንገድ መንገዱን ስናወራ አንድ ሃሳብ ተነሳ፡፡ ይኸውም አሊሹ ከዚህ ሁሉ ነገር የሚቆጨው ራስ አበበ አረጋይ ለዚህች ሃገር ይህን ሁሉ ውለታ ውለው አለመታወሳቸው መሆኑን ነገረኝ፡፡ በነገራችን ላይ አሊሹ የሃገራችንና የጥቁር ሕዝብ ትግል የሚስበው በማልከም ኤክስንና የማርከስ ጋርቪን ስራዎች የተረጎመ የጥበብ ሰው ነው፡፡ እኔም በጉዳዩ በመስማማት ደብረ ብርሃንም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን በእርሳቸው ለመሰየም ተፈልጎ መንግሥት ስለተቀቃወመ መቅረቱን ነገርኩት፡፡ የሆነው ሆኖ ቀድሞ በነበረኝ ፍላጎትና ቁጭት 2008 . በደብረ ብርሃን ከተማ የግል ቤተመጻሕፍት ስከፍት ስያሜውን በራስ አበበ አረጋይ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ይህም ቤተመጻሕፍት ህብረተሰቡን በነጻ እያስነበበ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት (ወመዘክር) በደብረ ብርሃን ከተማ ባደረገው የንባብ ሳምንት ወቅት እውቅና ሰጥቶናል፡፡ የግል ቤተመጻሕፍት በፖሊሲ በማይደገፍበተ ሃገር በንባብ ላይ የሚሰራው ቤተመጻሕፍታችን በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበር ንቁ ተሳታፊና በዋና ዋና መርሐግብሮች ኢትዮጵያን የወከለ ነው፡፡ የአሜሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበርም በመጽሔቱ ስለቤተመጻሕፍታችን ጸፏል፡፡ ይህ እውቅናና አብሮ የመስራት ፍላጎት ከደቡብ አፍሪካው የርቀት ትምህርት ተቋምና ከሕንዱ ስቶሪ ዊቨርም መጥቶ አብረን እንሰራለን፡፡ በንባብ ላይ ባሳረፍነው አሻራም ምክንያት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን (ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ዩቱብ ቻነሎችና ጋዜጦች) በቤተመጻሕፍታችን ላይ ዝግጅቶችን በማቅረብ የንባብ ባህልና የቤተመጻሕፍት አገልግሎት እንዲስፋፋ ሰርተዋል፡፡ የቤተመጻሕፍቱ አገልግሎትና ስራ ሰፊ ቢሆንም በዚህ ልቋጨው፡፡

ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዲስ በተሰራው የሕክምና ካምፓስ ውስጥ የሚገኘውን ቤተመጻሕፍት በራስ አበበ አረጋይ ስም ለመሰየም መወሰኑን ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ወቅት የነበሩ ግለሰቦች ነገሩኝ፡፡ ይህም ውሳኔ ራስ አበበ አረጋይን ለማስታወስ በማሰብ የተደረገ በመሆኑ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ በፊት አስታዋሽ አጥተው የነበሩትን የሃገር ባለውለታ ዩኒቨርሲቲው ማስታወሱ የሚደነቅ ቢሆንም የራሱ አሉታዊ ጎኖች አሉት፡፡ይኸውም በከተማው ውስጥ በጀግናው የተሰየመ ቤተመጻሕፍት እያለ ሌላ ተጨማሪ መሰየሙ ግርታን የሚፈጥርና አንባቢያንንና ህብረተሰቡን የሚያሳስት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ቤተመጻሕፍታችንም ምንም እንኳን በአነስተኛ ቦታ የተወሰነ ቢሆንም የራሱን አሻራ እያስቀመጠና በግል ቤተመጻሕፍት ዘርፍ ያለውን ክፍተት በማሳየት በትንሽ ገንዘብ፣ የሰው ሃይልና በውሱን አቅም ትልቅ ስራ መሰራት እንደሚችል እየሳየ ያለ ነው፡፡ መጻሕፍትን በማሳተምና በማከፋፈልም በመላ ሃገሪቱ የንባብና የዕውቀት ትሩፋት እንዲደርስ እየጣረ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይህንን ውሳኔውን እንዲያጤነው ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ከተቻለም ቤተመጻሕፍቱ በሌሎች ታዋቂ ደራሲያን፣ ምሁራንና የአገር ባለውለታዎች (ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወዘተረፈ) እንዲሰየም ሊደረግ ይችላል፡፡ ራስ አበበ አረጋይ በብዙ መልኩ እንዲታወሱ ማደረግ ይቻላል፡፡ ግርታን በማይፈጥር መልኩም እስካሁን የታወሱበትንና የተወሰኑ ፍላጎቶችን እናሳይ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በደብረ ብርሃን በግል ቤተመጻሕፍት አስታውሰናቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ በስማቸው መንገድና ትምህርት ቤት አለ፡፡ እነዋሪ ላይ ሆቴል ተሰይሟል፡፡ የባንክ ቅርንጫፍም አለ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰየም ፍላጎት እንዳለም ሰምቻለሁ፡፡ ወደፊት ዩኒቨርሲቲያችን ባለው ተጽዕኖና የሥራ ግንኙነት መሠረት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በሌሎች ክልሎችም ሆነ በፌደራል ደረጃ ለራስ አበበ አረጋይ ውለታ የሚመጥን ወታደራዊ አካዳሚ ቢሰየም ከእርሳቸው ትክክለኛ ወታደራዊ ጀብዱ ጋር የሚስተካከል ማስታወሻ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌሎችም ጀግናውን የሚያስታውሱ ስራዎች ቢሰሩ ለውለታቸው ሲያንስ አንጂ አይበዘባቸውም፡፡

መዘምር ግርማ

የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ሥራ አስኪያጅ

ሰኞ የካቲት 22 2013 ..

ደብረብርሃን

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...