2022 ኖቬምበር 14, ሰኞ

ተማሪዎቻችን የዩኒቨርሲቲውን መውጫ ፈተና ያልፋሉ ብለን ብንነሳስ?

ተማሪዎቻችን የዩኒቨርሲቲውን መውጫ ፈተና ያልፋሉ ብለን ብንነሳስ?

መዘምር ግርማ

እሁድ፣ ሕዳር 4 2015 ..

 

አዲሱን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አስመልክቶ በርካታ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ ይደመጣል፡፡ እኛም ባለጉዳዮችም ሃሳብ ሰጪዎችም ነን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርብ ወራት በመስሪያ ቤቴ በሁለት ስብሰባዎች ላይ ተሳትፌ ግንዛቤ ለመጨበጥ ሞክሬያለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ድረገጽም ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ መምህር ማለትም የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ መስራቹ  ዶክተር ወንዶሰን ታምራት የጻፉትን አንብቤ ግራና ቀኙ ምን እንደሚል ሃሳብ አግኝቻለሁ፡፡ ከሌሎችም የዉጪ ድረገጾችና ትምህርታዊ ተቋማት የቃረምኩት አይጠፋም፡፡ እንዲያው ሁሉንም ካሰላሰልኩ በኋላ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ በቅርብ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ላነሳው ፈልጌ ብዙዎች ሃሳብ ስላነሱና የስብሰባ ጊዜውም ስለገፋ በማለት ተውኩት፡፡ ሃሳቤ በተለይ ፈተናውን ያለ ጥርጥር ሊያልፉ ስለሚችሉት ሳይሆን መካከልና ታች ላይ ስላሉት ተማሪዎች ነው፡፡ ጥቂት ተያያዥ ነጥቦችን አነሳስቼ መደረግ ስላለበት ጉዳይ ባጭሩ ሃሳቤን ለአስተያየት አቀርባለሁ፡፡

 

በአገራችን ያሉት ችግሮች ስር የሰደዱ ሲሆኑ፤ እነዚህ ተመጋጋቢ ችግሮች በአንድ ጊዜ እንደማይፈቱ የታወቀ ነው፡፡ የሥርዓት ለውጥ ብቻውን አይቀይራቸውም፡፡ ሰዎች ቢቀያየሩ አገሪቱ ያቺው ነች፡፡ ህዝቡም ያው ነው፡፡ በመሰረታዊነት ለውጥ ለማምጣት ቢያንስ ብዙ አስርት ዓመታትን ይጠይቃል፡፡ ለለውጥ የተደረገው ዝግጅት ምን ዓይነት ነው? ሁሉም አካል በለውጡ ላይ ተስማምቷል ወይ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ የለውጥ ወቅት የለውጥ ጉዳይ እየነካካቸው ካሉት አንዱ የትምህርት ዘርፉ ነው፡፡

 

የትምህርት ዘርፍን ለመቀየር ፍኖተካርታ ተነድፎ በዘርፉ የተሰማራን አካላት ተወያይተንበታል፡፡ ውይይቱን በመስሪያቤቴ በዩኒቨርሲቲ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በትምህርት ላይ በሚሰሩ ድርጅቶች ውክልና እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር የምሁራን ቲንክ ታንክ በአንድ ትልቅ ሆቴል ተሳትፌያለሁ፡፡ ከመዋዕለ-ሕጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያለውን የትምህርት ዘርፍ ያቀፈው፣ ልዩ ልዩ የሥልጠና ዘርፎችን የሚነካካው፣ ብሎም የትምህርትን ዋና ዋና ጉዳዮች በሚዳስሰው ፍኖተካርታ ላይ ብዙ የተነሣሡ ጉዳዮች ቢኖሩም የተተቸው ግን የመጠነኛ ማሻሻያ ነገር እንደሆነና ስርነቀል ለውጥ እንዳልሆነ ነው፡፡ ከሕገመንግሥቱ ጀምሮ ያልተቀየሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም የሚመነጨው ከሱ ስለሆነ ዓይነተኛ ለውጥ ይምጣ ከተባለ መቀየሩ ግድ ይላል፡፡ ያለዚያ መቀባባት ነው የሚሆነው፡፡ በተጨማሪ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ እነዚያው ሚኒስቴሮች፣ እነዚያው ፈጻሚዎች፣ እነዚያው መሪዎች፣ እነዚያው ፖሊሲ አውጪዎች መኖራቸው የለውጡን ሁኔታ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡

 

ነጠላ ውጤት፣ ጥድፊያና ቁጥብነት የሚባለው የአጭር ልቦለድ ባህሪ የሚገልጻቸው በትምህርት ዘርፍ ቦግ እያሉ ያሉና እርስበርሳቸው ያልተሳሰሩ ዕቅዶች አይጠፉም፡፡ እነሱም የዘንድሮው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አደረጃጀት፣ ከታች ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ መጻሕፍት በጥድፊያ በሚዘጋጁበት ወይም ባልደረሱበት ሁኔታ የትምህርት ፖሊሲ ቅየራ፣ ስማቸው የሚያማምርና ማን እንደሚያስተምራቸው ግልጽ ያልሆኑ የትምህርት ዘርፎች መኖር፣ የማስተርስና ፒኤችዲ ተማሪዎች ድንገቴ አርቲክል አሳትሙ ጥያቄ፣ ማስተርስ ያላቸው መምህራን በምርምር ዕድገት አያገኙም የሚለው ሃሳብ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ዓይነት ልየታብቻ በርካታ ናቸው፡፡

 

እስኪ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን እንየው፡፡  መውጫ ፈተናው በጤናና በሕግ ትምህርት ዘርፎች ለተወሰኑ ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ዉጪም በቴክኒክ ኮሎጆች የመውጫ ፈተና ጉዳይ ይሰራበታል፡፡ በቴክኒክ ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ሰው የፈተናውን ዓላማ አንስተው ሲነግሩኝ መንግስት ለምሩቃን የሚሰጠው ስራ ስለሌለው የፈጠረው መላ መሆኑን ሹክ ብለውኛል፡፡ መጣልን ዓላማው አድርጎ የሚሰጥ ፈተና የትም አያደርስም፡፡

 

አሁን በሁሉም ዘርፍ ፈተናው ይሰጣል ሲባል ከላይ የመጣ ውሳኔ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ በአገራችን አንዲት ውሳኔ ወይም ደብዳቤ የብዙዎችን ሕይወት የምትነካበት ስርዓት ስላለና ፈተናውንም ማስቀረት ወይም ለሌላ ጊዜ ማራዘም ስለማይቻል አሁን አማራጩ ፈተናውን እንዴት እንዲያልፉ እናድርግ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፈተና አስተባባሪዎች፣ አውጪዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች የየራሳችን ሚና አለን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣውን ትዕዛዝ አስፈጻሚዎች ስለሆኑ ተማሪውና መምህሩ ላይ ለቀውታል፡፡ ተማሪው በተፈታኝነቱ የመጨረሻው ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ መምህሩም ጥራት ያለው ትምህርት መስጠትና አለመስጠቱ የሚታይበት ስለሆነ ከጭንቀት አያመልጥም፡፡ በትክክል ለተማሪ ማለፍና መውደቅ ለሚጨነቅ መምህር አንዳንድ ነጥቦችን ላነሳ እፈልጋለሁ፡፡ የሥነልቦና እገዛ የሚፈልገው ተማሪው ብቻ ሳይሆን መምህሩም ነው፡፡ ይህንን የምለው ከሕይወት ልምዴ በመነሳት ነው፡፡ በብዛት ሰዎች ከነሱ በኋላ የሚመጣውን የመናቅ አዝማሚያ አላቸው፡፡ የዚህ ገፈት ቀማሽ ብዙዎች እንዳሉም ታዝቤያለሁ፤ ከታዘቡትም ጋር አውግቻለሁ፡፡ ለምሳሌ ከታሪክ ለመጥቀስ ታወር ኢን ስካይደራሲ ሕይወት ተፈራ ያን የመሰለ እንግሊዝኛ እየጻፈች የሷ ትውልድ በታላላቆቹ በእንግሊዝኛ አለመቻል ይተች እንደነበር ተናግራለች፡፡ ትችቱ ትክክል ነበር አልነበረም የሚለውን ለአንባቢ እንተወው፡፡ ተማሪዬ ጎበዝ ነው ወይም ያለበትን ሁኔታ ማሻሻል ይችላል ብሎ ማመን ከመምህሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ 

 

የማስተማሪያ ቋንቋ የሆነውን እንግሊዝኛን ብናነሳ የተማሪዎች የቋንቋ ችሎታ ይተቻል፡፡ ስለቀደመው ጊዜ ብናይ በቅርቡ ስለ ዋለልኝ መኮንን ጉዳይ በደረጀ ኃይሌበነገራችን ላይዝግጅት የቀረቡት አቶ ግዛው ዘውዱ እንዳሉን በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ የጽሑፍም ሆነ የንግግር ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆኑን አውስተዋል - በተማሪዎች ስብሰባም ሳይቀር፡፡ አሁን የቋንቋው ይዞታ መውረዱ የብዙዎች ምሬት ምክንያት ሆኗል፡፡ የቋንቋ ችሎታው መውረድ ግን የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህራንም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ጠቃሚ የሆኑ መሰረታዊ ክህሎቶች ላይ መስራት፣ ብቁ ለመሆን መጣርና ለተማሪው መንገድ ማሳየት የተገባ ነው፡፡

 

የኔ ተማሪዎች በተለይም የእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካነበሩበት ይልቅ በስራ ላይ ሲሰማሩ የተሻለ እንግሊዝኛ አንደሚጽፉ ከማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎቻቸውና መልዕክቶቻቸው አይቻለሁ፡፡ ይህም በመምህርነት ስራቸው ምክንያት ትምህርቱን ስለሚያጠሩት መሰለኝ፡፡ አንብበው የወደዷቸውንም ሙያዊ መጻሕፍት ይጠቁሙኛል፡፡ ከዚህ በመነሣት ተማሪዎች ያንን በስራ ላይ የሚያገኙትን መሻሻል ከግምት ውስጥ አስገብተን ያን መሰል መጠነኛ እገዛ ከዩኒቨርሲቲ ሳይወጡ ብናደርግላቸውና እነሱም ቢተጉ የመውጫ ፈተናውንም ያልፉታል፤ ብቃታቸውም ይጨምራል፡፡ ቢቻል ፍላጎታቸው ከውስጥ ፈንቅሎ እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሚያጠኑት ለፈተና ብቻ ብለው ባይሆንም መልካም ነው፡፡ ለዚህ አንዳንድ መነሻ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የመጡበትን የትምህርትና ምዘና ስርዓት ከግምት ውስጥ ያስገባ እገዛም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በአንድ ወቅት ያደረጉት ቃለምልልስ በተበላሸ ስርዓት ያለፉትን መልሶ ስለማስተማር የሚለው አለው፡፡ ያንን መልሶ ማስተማርን ምልስ አሸባሪዎችን በጥሩ የኃይማኖት መሪዎች ከማሰልጠንና ወደ ጠቃሚ ዜጋነት ከመመለስ በዘለለ ተማሪዎችንም ወደ መስመር ለማስገባት መጠቀም መቻሉ አይቀርም፡፡ በመምህር እንኳን ለማስተማር ጊዜና ሀብት ባይኖር ተማሪዎች በግላቸው እንዲማሩ ሀብቱንና ጊዜውን ማመቻቸት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ለፈተና የተመረጡ ቁልፍ የትምህርት ዓይነቶች እንዳሉት ሁሉ ከዩኒቨርሲቲ በታች ባሉት ክፍሎችም ያጡትን ያካክሱ ዘንድ ምክር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን ትምህርት ለመሸከም የማይችል ጫንቃ ያለው ተማሪ ከታች ማጥራት ያለበት ነገር ስለሚኖር ነው፡፡ በየትምህርት ዓይነቱ እነዚህ ቁልፍ ዕውቀቶችና ክህሎቶች ይታወቃሉ፡፡ 

 

ለረጅም ጊዜ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የከፍተኛ ትምህርት ስርዓት ትምህርት አሰጣጥ፣ አመራር፣ ምዘና አሁን እንዴት የመውጫ ፈተና ለመስጠት እንደበቃ ግልጽ አይደለም፡፡ ተማሪዎችም ከታች ክፍል ጀምረው አመጣጣቸው እየታወቀና ቢያንስ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መውጫ ፈተና እንደሚፈተኑ ሳይነገራቸው ይህ ድንገቴ ውሳኔ ግርታን ሳይፈጥር አይቀርም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የተማሩት የትምህርት ሚኒስትር የሚያስተዋውቋቸው ለውጦች ታሳቢ ያደረጉት ምንን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ቀድሞ ያለማሳወቅን ነገር የዩኒቨርሲቲ አመራሮች የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ወረቀት አሳትሙ ካሉት ጋርም ይሄዳል፡፡

 

በመውጫ ፈተናው ወድቆ ያለዲግሪ ለሚሰናበት ተማሪ ኪሳራውን ማን ይከፍላል የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ ለሱ የአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የወጣው ገንዘብ ለአጭር ስልጠና ቢውል ይህን ጊዜ ሀብትና ንብረት አፍርቶ አምራች ዜገ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ፈተናውን ባያልፍ አነስ ያለ የትምህርት ደረጃ ይሰጠውም እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በሌላ አገር 12 ክፍል እንዲሁም የእያንዳንዱ ዓመት የዩነቨርሲቲ ቆይታ ለስራ ዋጋ እንዳለው እየታወቀ የአሁኑ የኛ አሰራር በደንብ የታሰበበት አይመስልም፡፡ ከግልና ከመንግስት ተቋማት አንጻር፣ ከመደበኛ፣ ርቀትና ተከታታይ ትምህረት ተማሪዎች አንጻር፣ ከየትምህርት ዘርፉ የአፈታተን ሁኔታ አንጻር ወዘተ ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች ቢኖሩም እነሱን ማነሣሣት ጊዜና ቦታ ስለሚፈጅ በዚሁ ላብቃ፡፡ ባይሆን ለዝርዝር ጉዳዮች ከላይ የተጠቀሰውን የዶክተር ወንዶሰንን ጽሑፍ ይመልከቱ፡፡ 

 


 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...