ለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የተላከ የምስጋና መጣጥፍ
መዓልት ሕዳር ፩/፫/፳፻፲፭ ዓ.ም.
ከመምህር ደመረ ጌታቸው
መነሻ ሐሳብ
ደብረብርሃን ከተማ እጅግ ተወዳጁ ደራሲና ተርጓሚ ከበደ ሚካኤል ብሎም ጀግናው ኃይለማርያም ማሞና ራስ አበበ አረጋይ ዘብሔረ እየተባሉ ይጠሩባታል፡፡
ይችን ከተማ የንባብ መዳረሻ ከማድረግ አኳያ በወረዳው በኩል ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ የባሶና ወራና ወረዳ ዋና ከተማ የሚገኘው በተደራቢነት ደብረብርሃን ነው፡፡ ባሶና ወራና ወረዳ በውስጡ 31 ቀበሌዎቸን ይዞ 12 የሚሆኑት በቀይት ንዑስ ወረዳ ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ባሁኑ ጊዜ ቀይት ንዑስ ወረዳ ካንደኛው የደብረብርሃን ሪጂዮፖሊታን ክፍለከተማ ተመድባለች፡፡
ከላይ በተገለፁት አካባቢዎች የንባብ ባህልን ለማዳበር ከተቋቋሙ ቤተመጽሐፍት ብንመለከት አልማ፣ ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ሁለገብ የወጣቶች ማዕከል እና አልማ ቁጥር 2 የሕፃናት ቤተመጻሕፍት ብቻ ናቸው፡፡
እኔ ከታዘብኩት ሁለቱ ወረዳዎች የባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት ቢኖራቸውም መጻሕፍትን በቅርስነት ለማስጎብኘት አንድ ቤተመጻሕፍት ቢከፍቱ ምን ችግር ነበረው? የሁለቱም ወረዳዎች ቢሮ በዚሁ ከተማ ይገኛል፡፡ ይህ እንደ አስተያየት ይሁን፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመስና በከተማችን የግል ቤተመጻሕፍት በር ከፋች ሆኖ ለአንባቢ ትውልድ በነፃ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ራስ አበበ አረጋይ ነው፡፡ የዚህ ጦማር አዘጋጅ ያወቀው ለመጀመሪያ ጊዜ በ2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመንዝ ግሼ ራቤል ወረዳ 5 ዓመት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር ሥራ ቆይቼ በፔዳጎጂ (PGDT) ጊዜያዊ መረጃዬን ለመቀበል ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መጣሁ፡፡ ቤተመጻሕፍቱ በራሱ በጀት ሁለት ሰራተኞችን ቀጥሮ በነፃ እንደሚያስነብብ የውሰት አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ፣ ሐሙስ ደግሞ የሥነ-ጽሑፍ ምሽት እንዳለ ጠይቄ አረጋገጥኩ፡፡ ወዲያውም በዚህ ከተማ በተመሳሳይ ሥራ ተቀጥሬ ገባሁ፡፡ መምህር መዘምር ግርማ የተለየ ባለሀብትና ባጭር አቋራጭ ቢሊየነር ከሆኑት ግለሰቦች መካከል ነው የሚል የተሳሳተ አረዳድ ነበረኝ፡፡ ሆኖም ግን ቀረብ ብዬ መስቀለኛ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ለነገሮች ያለውን አመለካከትና አተያይ ተረዳሁ፡፡ ልክ እንደ መጻሕፍቱ የሚነበብ ሰው ሆኖ አገኘሁትና አረዳዴን ወቀስኩት፡፡ ‹‹ከአንድ ነገር የመጀመሪያው ይልቅ የመጨረሻው ይሻላል፡፡›› ይባል የለ፡፡
የተወደዳችሁ የዚህ ገፅ አንባቢዎችና ባለምጡቅ አእምሮ ደራስያን፣ ወግ ቆማሪዎች፣ ውስጠወይራ ሐሳብ አፍላቂዎች፣ የአፄ ዘርዓያዕቆብ የመጽሐፍ ውይይት ክበብ አባላት፣ በሳሲት የምትገኙ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ቤተሰቦች፣ በዚሁ መጽሐፍ ቤትም ሥር የሠላም ጓድ አበጋዞች፣ ልዩ ልዩ ስጦታ ያደረጋችሁ ወዳጆች ሌሎችም ስማችሁ ያልተጠቀሰ ከዚህ ቀጥሎ የምጽፈውን በደንብ አድምታችሁ የምታውቁ የቅኔ መምህራን ከኔ ብዙ አትጠብቁ! በእርግጥ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን የሠራሁት በአማርኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ይሁን እንጂ የአማርኛ አባት በሆነው ግእዝ ሰርተፊኬት አለኝ፡፡ የወሰድኩት ትምህርት “Basic Geez” ይላል፡፡ መሠረታዊ ግእዝ ከተማረ ብዙ አትጠብቁ፡፡
በርትራንድ ሩሸል ‹‹አንድ ነገር እንደሚሆን ማረጋገጫው በዋናነት ሌሎች ስለሠሩት ነው፡፡›› ይላል፡፡ ዴ ዋትስ ‹‹በጎ አስተሳሰቦች የስኬታማ ሕይወት ማስፈንጠሪያ ናቸው፡፡ አእምሮህን ለማዘዝ ድሀ ወይም ሀብታም … መሆን ትችላለህ፡፡ ባዘዝከው ነገር ሁሉ ስልጡን ነውና›› ይለናል፡፡ ይህን ያነሣሁበት ምክንያት በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ከጅማሬው ሳሲት ላይ ስለሚሰነዘረው አሉታዊ እሳቤ ነው፡፡ የሚገርመኝ የሰው ልጅ አረዳድ አንድ ሰው የገደለውን ወንጀለኛ፣ አንድ ሺ የገደለውን ጀግና ብሎ መፈረጅ ከባድ ስህተት መሆኑ አለመታየቱ አሁን ኑሮ ተራራ መግፋት በሆነበት በግብረገብነት የህልም ያህል በራቀበት ዘመን አንድ መልካም ሰው ቢገኝ እንደ ደራሽ ዉኃ ማስገምገም መዘምር ግርማን የመሰሉ እልፎች ከተወለዱበት አካባቢ አይጠበቅም፡፡ እኔ ‹ትል› አልወድም፤ ነገር ግን ከዚች ሚጢጢ ፍጡር የምማረውን ነገር እወደዋለሁ፡፡ ሰባት ጊዜ ወድቆ መነሣትን እንኪያስ እናንተም ይህን የልማት አርበኛ ቢያንስ ወርቃማ ሐሳቦቹን መቀበል ይገባችሁ ነበር፡፡ ጥያቄው በይደር ይቆይና የቤት ሥራ ሰጥቻችሁ ልሰናበት፡፡
ውዳሴ ግጥሞች
በሥነ-ጽሑፍ ወይም በቋንቋ ታሪካችን ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን (አምደ ጽዮን) ከተባለው ንጉሥ በዚህ ዘመንም ቢሆን ከተፃፉት ወዳሴ ግጥሞች ጋር ተያያዥነት ያለው ግጥም ነው፡፡ በወቅቱ ታለቅ ድል ላደረጉ ነገሥታትና ሌሎች ጀግኖች ይዘጋጅ ነበር፡፡
1. ኩልክሙ አካላተ ርእሰ አበበ ቤተ መጽሐፍት
ንኡ ንሑር ጽርሐ አርያም ሰማየ ሰማያት
ትርጉም፡- የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጽሐፍት አባል የሆናችሁ በሙሉ ኑ ወደ ሰማይ ጣራ ወደሆነችው ጽርሐ አርያም እንሂድ ማለት ነው፡፡ ‹‹ሐረ›› ሔደ አንድም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀስን ያመለክታል፡፡ ሔደ በህሊናው ከአድማስ አድማስ ያለገደብ መሔድ ነው፡፡
ምስጢር፡ - ራስ አበበ ቤተመጽሐፍት ሄዳችሁ ስታነቡ ወደ ጽርሐአርያም የሚያደርስ ልቦና በንባብ ታገኛላችሁ፡፡ ሂዱ እንሂድ ማለት ነው፡፡
2. ኦ ትዕይንተ ደብረብርሃን መኑ ይመስለኪ?
እንዘ ይምህር/ይምሕር ሐዳስ ለም እመንኪ፡፡
ትርጉም፡- ደብረብርሃን ከተማ ሆይ የሚመስልሽ ማነው?
ለሕዝብሽ የሚያስተምር/የሚራራ መምህር አግኝተሻልና፡፡
መሀረ - አንድም አስተማረ፣ ሰበከ ይለዋል፡፡ ምሁር ያለው ከዚህ ተነሥቶ ነው፡፡
መሐረ - ጠብቆ ይነበብና ይቅር አለ፣ ራራ፣ የዋህ ሆነ፣ አስተዋይ ማለት ነው፡፡
ምስጢር፡- አስተምሮ ለሌሎች ርህራኄ/ምሕረት አድርጎም የሚኖር ሰው ስላለሽ የሚመስልሽ ማነው? የመዘምር ግርማን የሥራ ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ መምህርነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባለው ቀና አስተሳሰብ የሕዝቡን የማንበብ ረሀብ፣ ችጋር እንዳይገድላቸው በመራራት ቤተመጻሕፍት ከፈተ ማለት ነው፡፡
አንድም የመምህርነት ሙያ በትክክል ካልተሠራበት ትውልድን ይገድላል፤ ከህሊና ወቀሳ በፀዳ መልኩ ከተሰራበት ደግሞ ይፈውሳል፤ ያድናል፡፡
3. ለምንት ይት ለዐሉ ርእሰሙ ከመ ንሥር
ማዕዚ ኃሠሡ ሲሳዮሙ ለክሙ ዘየኅድር
ትርጉም፡- ሰዎች ለምንድነው ራሳቸውን እንደንሥር ወደ ላይ ከፍ የማያደርጉት? የነፍስ ማደሪያ ምግባቸውን መቼ ፈልገው አገኙና?
ኃሠሠ፡- አሰሰ፣ ፈለገ፣ ሻ፣ ፈልጎ አገኘ፡፡ ኃሣሢ - አሳሽ
ንሥር ምግቡን ለማግኘት ወደ ሰማይ ይወጣል፡፡ ከሩቅ ሆኖ ምድርን ይመለከታል፡፡ ምግቡ ያለበትን ቦታ በዓይኑ አማትሮ ያነሣል፡፡ እንደገና ወደ ሰማይ ይወጣና በዐለት ላይ ይለቀዋል፡፡ በውስጡ ያለውንም የላመ ጣዕም ምግቡን ያገኛል፡፡ ንሥርን ያመጣሁት ራሱን ለማደስ ለ80 ዓመታት የህል የሰው ዕድሜ እኩል የተሰጠው መሆኑን ለማነፃፀር ስለተመቸኝ ነው፡፡ በ40 ዓመቱ ራሱን ያድስና እንደገና 40 ዓመት ይቆያል፡፡
ኀሠሠ - የሰው ልጅ ለቁመተ-ሥጋው ብቻ የሚሆነውን ምግብ በመፈለግ አይኑር፤ የተመቸው ጊዜም ቤተ መጽሐፍት እየሔደ ለነፍሱ ማደሪያ ያንብብ፡፡
ምስጢር - ንሥር ምግቡን ፍለጋ ወደ ሰማይ እንደሚበር እናንተም ሰዎች ወደ ላይ ለመብረር የኑሮ ፈላስፋ የሆኑ መጽሐፍትን አንብቡ ማለት ነው፡፡
4. በከመ አዕማደ ይቀውሙ መጽሐፍት ለሥላጤ
አልቦ ዘነበረ አናጎኒስጢስ ለውላጤ
ትርጉም - መጽሐፍት እንደ ምሰሶ ለሥልጣኔ ቆመዋል፤
ለመለወጥ ቁጭ ብሎ የሚያነባቸው ግን ጠፍቷል፡፡
‹‹ቆመ›› አንድም ከተቀመጠበት ብድግ አለ፡፡
ቆመ - አንድም ስለሌሎች ጸሎት ጸሎት ወይም ጥያቄን አቀረበ ይለዋል፡፡
ምሥጢር፡- ቆመው የሚኖሩ መጽሐፍትን አናጎኒስጢስ (አንባቢም) ቆሞ በማንበብ ስለኛ ለማንኛውም ነገር እንዲቆሙልን ያደርጋል፡፡ ወይም እኛ ቆመን ብናነባቸው እነሱም ስለኛ ለመቆም ታማኞች ናቸው፡፡
5. ውእቱኒ ይከውን ድርሰተ ሐራ
ከመ ይብሎ ጥበበ አይቴ ብሔራ
ትርጉም - ሰው ሁሉ የድርሰት ወታደር የሚሆን
ጥበብ ያለችበትን ሀገር ለማግኘት ነው
ጥበብ - በባሕል ልብስ ዙሪያ በዘርፍነት የሚሰራ ጌጥ ነው፡፡ መጽሐፍ ውበታችን ጌጣችን ነውና፡፡
ጥበብ - ደራስያን ጽሑፋቸውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙበት ስልት ነውና፤ ወይም ብልሃት እንበለው፡፡ ተጠበው ተጨንቀው ‹‹ጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው?›› ለሚሉ ጠያቂዎች መልስ የሚሰጡ መጽሐፍት በደራሲ ወታደር በሆኑ ሰዎች የተዘጋጁ ራስ አበበ ዘንድ አሉና አንብቧቸው፡፡
ግብረ ክፍል (የክፍል ሥራ)
መቼም አስተምሮ የክፍል ሥራ የማይሰጥ የለም፡፡ ይህችን ደግሞ እናንተ ሞክሩ
ውእቱ ይርኅው ማህደረ መጽሐፍት
አላ ይሀልው ነዊኅ ተምኔት
በልዩነት መዘምር ግርማን ለመግለጽ
መዘምር የሚለው ሲተነተን
መ - መንክር - ድንቅ
ዘ - ዘኩሎ ይእኀዘ - ሁሉን የያዘ
ም - ምርዳእ - መረጃ
ር - ርዕይ - የሚያይ
ጥቅል ትርጉም፡- ድንቅና ሁሉን የያዘ መረጃ የሚያይ ሰው ማለት አስገራሚና ብዙ ጠቃሚ ሃሳብ ያለውን መጽሐፍ የሚያነብ ግለሰብ ለማለት ነው፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ