እሑድ 3 ኦገስት 2025

ደብረብርሃን የመጠጥና የንባብ ከተማ Drink and Think

 ደብረብርሃን የመጠጥና የንባብ ከተማ


በየአገሩ ስለሚገኙ ልዩ ልዩ የንባብ ፕሮጀክቶች ሳነብ የአሜሪካውን Cops 'n Kids ሁኔታ እንደወደድኩት ባለፈው ገልጬ ነበር። ለፌደራል ፖሊስም ልምድ ይቀስሙ ዘንድ ሀሳቤን በማህበራዊ ሚዲያ አጋርቻለሁ። 

ዛሬ የኬንያውን አነበብኩ። ከኬንያ እስካሁን የተገበርኩት ነበር። ይኸውም የሚያነቡ ልጆችን መመገብ ነበር። በኮቪድ ወቅት ከኬንያ አብያተመጻሕፍት 

ለሚያነቡትን ልጆች (በኦንላይንም ይሆናል) የስንዴ ዱቄትና ዘይት ይሰጥ ነበር። ይህንን ልምድ በመውሰድ በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ለሚያነቡ ተፈናቃይ ልጆች በጎአድራጊዎች ምግብ እንዲያቀርቡ ጠይቄ ቀርቦ ለረጅም ወራት እያነበቡ ተመግበዋል። 

ሌላ እያሰብኩት ያለ ሀሳብ አለ። እሱን ሀሳብ ያጠናከረልኝ ነገር ዛሬ አነበብኩ። ኬንያዊው ታዋቂ ደራሲ ጉጊ ዋቲዎንጎ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ቋንቋ ልቦለዱን እንደፃፈ ህዝቡ በየቦታው አንብቦለታል። በየቤቱ ማንበብ የሚችሉ ልጆች ለማይችሉ የቤተሰብ አባላት አንብበውታል። በየመጠጥ ቤቱም መጽሐፉ ያለው ሰው ይዞ እየዞረ ለሌላቸው ያነብ ነበር። መጠጡን ሲጨርስም ይጋብዙታል። በዚህ መልኩ የጊኪዩ ሥነጽሑፍ ታወቀ። እኔ ወዳሰብኩት ስንመጣ 'Drink and Think' ይባላል። እየጠጡ ማንበብና መወያየትን ይመለከታል። ሀሳቡ የመጣልኝ እየጠጣሁ ሳነብ በጣም ስለሚገባኝና ስለሚያፈጥነኝ ነው። ይህንንም የቢራና የድራፍት ጠርሙስና ብርጭቆ ፎቶ ጭምር እያደረግሁ ሳስተዋውቃችሁ ቆይቻለሁ። አልኮልን ከንባብ ጋር የሚያያይዙ ልምዶች በሌሎች አገሮች አሉ። ሳይንሳዊ ድጋፍም አለው። ሥራውን ለማስኬድ ያሰብኩት ምርቶቹን ለማስተዋወቅ የሚፈልግ የቢራ ፋብሪካ ከተገኘ ነው። የመጻሕፍት ውይይት ተሳታፊዎች የሚመረጡበትን፣ መጻሕፍት የሚገኙበትን፣ አወያይ የሚመደብበትን ወዘተ ሁኔታ ልምድም ስላለን እናመቻቻለን። ደብረብርሃንን የንባብና የመጠጥ ከተማ በሚል ለማስተዋወቅ የሚያግዘውን ይህን ሀሳብ እንዴት ከግብ እናድርሰው?

ቅዳሜ 2 ኦገስት 2025

ካሚሪቱ ኬኒያ

 ካሚሪቱ


በኬኒያ በሚገኘው የካሚሪቱ የማህበረሰብ ትምህርትና ባህል ማዕከል የናይሮቢ ዩኒቨርስቲ መምህራን የጀመሩት በኬኒያ  የመጀመሪያው የአፍሪካ ቋንቋና ከአዳራሽ ዉጪ ቲአትር ሲሆን በቅኝገዢውም ሆነ ከነፃነት በኋላ በመጣው መንግሥት አልተወደደም ነበር። ተዋንያኑ ከህብረተሰቡ ውስጥ የሚመረጡ ናቸው። በተውኔቱ ጽሑፍ፣ በተዋንያን መረጣና በልምምድ ህብረተሰቡ ስለሚሳተፍ እንደ ምዕራባውያን ቲያትር ድብቅነት የሌለውና ሁሉም ችሎታ እንዳለው ያስገነዘበ ተብሏል። ከናይሮቢ ወጣ ብላ በምትገኘው መንደር የሚመደረከውን ተውኔት ኬኒያውያን ከሩቅ ቦታዎች በመኪና እየመጡ ይመለከቱት ነበር።
ከኬኒያ ልዩ ልዩ ብሄሮች ተዋንያንን በማካተት ተውኔቱን ወደ ናይሮቢ ወስደውት በብሄራዊ ታያትርም ሆነ በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ ቲያትር ለማሳየት ያደረጉት ሙከራ በመንግሥት ተስተጓጉሏል።
በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ያሳተሙትና ዓለምአቀፍ ዕውቅና ያላቸው እነ ጉጊ ዋቲዎንጎ በቋንቋቸው ብቻ ለመጻፍ በወሰኑበት ወቅት የነበረው ይህ ቲያትር በአፍሪካ ቋንቋ ህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ መስራት የማህበረሰብ ለውጥን የሚያመጣ፣ አእምሮን ከቅኝግዛትና የእጅአዙር ቅኝግዛት እስር የሚያላቅቅ የተባለለት ነው። መምህራኑ እነ ጉጊ ታሰሩ፤ ተሰደዱ። በ1984 እኤአ ፕሬዚዳንት ሞይ ኪባኪም በቦታው የቲያትሩን ስም ለማጥፋት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሠራ አዘዙ።
ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቲያትር የፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ፋቡላ የቀረበበትን ሁኔታ፣ በሃገር ፍቅር ማህበር አገርን ለመከላከል የጥበብ ሥራዎች የቀረቡበትንም ታሪክ ያስታውሳል። ጉጊ ዋቲዎንጎ በአፍሪካ ቋንቋዎች ስለመጻፍና አእምሮን ከቅኝአገዛዝ እሳቤ ሲጽፍ ቀደምት  ኢትዮጵያውያን ደራስያንን ህሩይ ወልደሥላሴንና ግርማቸው ተክለሃዋርያትን በአርአያነት ያነሣል።

ደብረብርሃን የመጠጥና የንባብ ከተማ Drink and Think

 ደብረብርሃን የመጠጥና የንባብ ከተማ በየአገሩ ስለሚገኙ ልዩ ልዩ የንባብ ፕሮጀክቶች ሳነብ የአሜሪካውን Cops 'n Kids ሁኔታ እንደወደድኩት ባለፈው ገልጬ ነበር። ለፌደራል ፖሊስም ልምድ ይቀስሙ ዘንድ ሀሳቤን በ...