እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎችና አስተያየት አሉኝ። ይኸውም በአጠቃላይ ስናየው የቋንቋ ትምህርት አስፈላጊ ነው። ማወቅ አይከፋም።
ግእዝን አስመልክቶ የተመረጠበት ምክንያት ይኖረዋል። ምናልባት ቀደምት በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰዎች በግእዝ ትምህርት ስለሚጀምሩ ጥሩ ደራስያንና ጎበዝ ተማሪዎች ሆነዋል። ከዚያ አንፃር ከታየ መጀመሪያ ግእዝ፣ ከዚያ አማርኛ፣ ቀጥሎ እንግሊዝኛ ይማራሉ ማለት ነው። በአፍ መፍቻቸው ይማሩ ከሚለው ጋር ካልተጣረሰ።
ግእዝን መማር ማለት በአውሮፓ ላቲንን እንደሚማሩት ይመስለኛል። በሕንድ ሳንስክሪት።
ግእዝን ከአገር በቀል ዕውቀት ጋርም የሚያይዙት አሉ። የግእዝ የማስተማር ሥርዓት ፈጠራን የሚያበረታታ መሆኑን ቅኔ ከመቀኘት ጋር አያይዤ አየዋለሁ። በጥንት ግሪኮች ተውኔት ሲያቀርቡ ህዝቡ እየተከታተለ እንደሚተቸውና አስተያየት እንደሚሰጥበት ያለ የቅኔ ቤት የፈጠራና አስተያየት የመስጠት ሂደትም አለ። በተጨማሪም መዋዕለ ህፃናት ሦስት ዓመት የሚፈጀውን እንዲሁም በ EGRA ጥናት መሠረት ሦስተኛም አራተኛም ክፍል ደርሰው ማንበብ አይችሉም የሚለውን በማስተካከል ረገድ የግእዝ የማስተማር መንገድ በአንድ ወር ፊደል አስለይቷል የሚል የወላጅ ምስክርነት ሰምቻለሁ።
ሦስት ቋንቋዎችን መማር በልጆቹ ላይ ጫና ይፈጥራል የሚል ሃሳብ ከአሁን በፊት መነሳቱን አስታውሳለሁ።
በአማራ ክልል ግእዝን ሲማሩ በሌሎች ክልሎች አማርኛን እየተዉ መሆኑ ይነገራል። አንድ አገርኛ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ (lingua franca) እንዴት ሊኖረን ይችላል? አማርኛን የምማረው አማራውም የኔን ከተማረ ነው የሚል ሀሳብ ያለ ይመስላል። ምናልባት ቋንቋ ማወቁ አይከፋም ከተባለ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሜሪካ አንድ የዉጪ ቋንቋ መርጠው እንደሚማሩት ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች መርጠው ሊማሩ ይችላሉ። አንድ የአገር ውስጥ የጋራ ቋንቋ ማስፈለጉ ግን አይቀርም። ምክንያቱም የትግራይ ተማሪ የተማረው የአገር ውስጥ ቋንቋ ኦሮምኛ ቢሆን አማራ ክልል መጥቶ ላይግባባ ነው። እንደ ክልል እየታየ በምርጫ ይሁን የሚባለው ጉዳይ መራጩ ማነው የሚል ጥያቄ ያስነሣል። መራጩ ፖለቲከኛው እንጂ ወላጅ አልተጠየቀም። ሊታሰብበት የተገባ ነው። ባለፈም ፓርላማ ላይ ያከራከረ ነው።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ