ሐሙስ 23 ኦክቶበር 2025

ልጆችን በቤተ-መጻሕፍት ማሰልጠን

 

ልጆችን በቤተ-መጻሕፍት ማሰልጠን

 


አንድ የቤተመጻሕፍት ኃላፊ ወይም ሰራተኛ ልጆችን በቤተመጻሐፍት ለማሰልጠን የሚጠበቁበት ሂደቶች ይኖራሉ፡፡ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረብርሃንን ልምድ ላጋራችሁ፡፡

ልጆችን የልጆች መጻሕፍት አጻጻፍን አስመልክቶ ሥልጠናዎችን ለተከታታይ ዓመታት ሰጥተናል፡፡ ሥልጠናው በአፍሪካን ስቶሪቡክ የሥልጠና መርሐግብር እንዲሁም በሌኖቮ ፋውንዴሽን ድጋፍ የተሰጠ ነበር፡፡

በመጀመሪያ የሥልጠና ዕቅድ ለደጋፊዎቻችን አስገባን፡፡ አሰልጣኙ እኔ ነበርኩ፡፡ አሰልጣኝ ለመሆን የሄድኩበት ሂደት ሲኖር ይኸውም ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የልጆች መጻሕፍትን በማስነበብና በመጻፍ በበጎፈቃደኝነት ከማገልገል የመጣ ነው፡፡

በሥልጠናው ወቅት ፎቶ በማንሳት፣ ቤተመጻሕፍት በማዘጋጀት፣ ጉዞ በማስተባበር የሚያግዙኝ በጎ ፈቃደኞች ነበሩ፡፡

ልጆች ጨዋታ ስለሚወዱ ጨዋታን ያማከለ፣ ፈጠራቸውን የሚያበለጽግ፣ የቡድን ስራን የሚያበረታታ የሥልጠና መርሐግብር መቅረጽ ያሻል፡፡ ለዚህም በእንግሊዝኛ የተዘጋጁት የሥልጠና መምሪያዎች ጥሩ እገዛ ያደርጋሉ፡፡

ከሥልጠናው ያልተጠበቁ ውጤቶችንም አግኝተናል፡፡ ከትምህርት ቤቶች ጋር ትስስር ለመፍጠር ችለናል፡፡ ልጆችን ወደ ቤተመጻሕፍት ለመሳብም እንዲሁ፡፡

ልጆቹ የጻፉት በሕይወታቸው ከገጠማቸው፣ ከሥርዓተ-ትምህርቱ ካገኙት፣ ወላጆቻቸውና ትልልቅ ሰዎች ከነገሯቸው ወዘተ ነው፡፡  

በቤተመጻሕፍታችንና በአቅራቢያ ትምህርት ቤቶች ልጆች እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ ለጠፍን፡፡

ለራሳቸው ጥሑፎች ሥዕል መሳል የሚችሉ ልጆች እንዲስሉ አደረግን፤ የማይችሉትን ደግሞ ከሚችሉት ጋር አስተሳሰርናቸው፡፡

ሁለት አፕሊኬሽኖች አሉ፡፡ አንደኛው የተረት ማንበቢያ ሲሆን ሌላው ደግሞ መጻፊያና ማሳተሚያ ነው፡፡ የማሰልጠኛ ሰነዶችንና ተረቶችን እንዲሁም ጠቃሚ ፋይሎችን የያዘው ድረገጹም አለ፡፡

ሥልጠናው ለሁለት ወራት የተሰጠ ነበር፡፡

ከሰልጠኞች ጋር የነበረን መስተጋብር ለዓመታት የቆየ ነው፡፡ ወላጅ መጥቶ የሚያስፈቅድላቸው አሉ፡፡ ሐዘን የሚገጥማቸው አሉ፡፡ የስደት ታሪካቸውን የሚጽፉ አሉ፡፡ ከሥልጠና በኋላ ወደ አቅራቢያ ታሪካዊ ስፍራዎች ጉዞም አድርገናል፡፡ 

 


የልጆቹንና የቤተሰቦቻቸውን አስተያየት ተቀብለናል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አብያተመጻሕፍት ጋርም በዋትሳፕ ትስስር ፈጥረናል፡፡ የምንጽፋቸውንና የምናሳትማቸውንም ተረቶች ለማጋራት ችለናል፡፡ ስለሥልጠናው ሂደት ሪፖርት ከመጻፌም በላይ ከደቡብ ወደ ሰሜን የዓለማችን ክፍል ስላለው ያልተለመደ የዕውቀት ሽግግርም አንድ ጽሑፍ ጽፌያለሁ፡፡

ከአሁን በፊት የጽሑፍ ውድድር ሁለት ጊዜ አካሂደናል፡፡ አንደኛው በአማርኛ ሁለቱ በእንግሊዝኛ ነበሩ፡፡ በፊት በአማርኛ ጽፈው፣ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ፣ አርትዖት ተሰርቶለትና ሥዕል ደቡብ አፍሪካ ያለ ሰዓሊ ስሎለት ስለነበረ ረጅም ጊዜ ይወስድ ነበር፡፡ አሁን ግን ሜከር (ASb Maker) የተባለ አፕሊኬሽን ስለተሰራ በሱ እየታገዝን መጻፍ፣ የሳልነውን ሥዕል መጫንና ተረታችንን ማተም እንችላለን፡፡ ይህ ሁሉ ባለንበት ቦታ ሆነን ነው፡፡ 

ለማንበብ የሚጠቅመው አፕሊኬሽን - ASb Reader

ድረገፁ - africanstorybook.org

እናንተስ ምን የማሰልጠን ልምድ አላችሁ? በቤተመጻሕፍታችሁ ለማሰልጠን ትፈልጋላችሁ?

 



 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ልጆችን በቤተ-መጻሕፍት ማሰልጠን

  ልጆችን በቤተ-መጻሕፍት ማሰልጠን   አንድ የቤተመጻሕፍት ኃላፊ ወይም ሰራተኛ ልጆችን በቤተመጻሐፍት ለማሰልጠን የሚጠበቁበት ሂደቶች ይኖራሉ፡፡ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረብርሃንን ልምድ ላጋራችሁ፡፡...