በክፍል አንድ ያየነውን የንባብ ወግ ዛሬ እንቀጥላለን፡፡ ምን ላንብብ ለሚሉ ወገኖች በርካታ ምላሾች ቢኖሩም ከዓመታት በፊት ሰዎች እናነባለን የሚሉበትንና የማልስማማበት ዓይነት ንባብ አንብቡበት ልላችሁ ነው፡፡ ይኸውም ሶፍት ኮፒ የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን ይመለከታል፡፡ እነዚህ ኢቡኮች በአመዛኙ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረቡ ሲሆን ለኢትዮጵያዊ አንባቢ ያለ ክፍያ የሚገኙ አሉባቸው፡፡ እነዚህን ለማንበብ የሚያስፈልጉ ስልኮች በብዙዎች እጆች ይገኛሉ፡፡ ታብሌትና ኮምፒውተሮችም እንዲሁ፡፡ ለማንበብና በጥሩ ሁኔታ ለመረዳት በእርግጥ የእንግሊዝኛ መረዳት ደረጃችን ይወስነዋል፡፡ ስለሆነም እንግሊዝኛችንን ለማሻሻል መጣር ያስፈልገናል፡፡
የአማርኛ መጻሕፍት በሶፍት ኮፒ ቢኖሩም በውሱን መጠን ነው፡፡ ወቅታዊነትም ይጎድላቸዋል፡፡ በእርግጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ወቅታዊ የአማርኛ መጻሕፍትን በኢቡክ የሚሸጡ አንዳንድ አገርበቀል ድርጅቶች አሉ፡፡ አቅሙ ካለ ከእነሱ መግዛት ይቻላል፡፡ አንዴ ተገዝቶ ለሌላ ሰው መላክ እንደማይቻል የታወቀ ነው፡፡
ከዓመታት በፊት ሰዎች እናነብበታለን ሲሉ የማልስማማበት በሚል ከላይ የገለጽኩት የእንግሊዝኛ ንባብ ሁኔታ ምክንያቴን ልናገር፡፡ ሰዎች በእንግሊዝኛ ለማንበብ ካሰቡ ምን ያህል ይችላሉ የሚለው ያጠያይቃል፡፡ አማርኛ ወይም ማናቸውም የአፍመፍቻ ቋንቋ ማንበብ የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ንባቡ ይገባናል፡፡ የቋንቋ ሃብታችንም እያደገ ይሄዳል፡፡ ሌላው በኢቡክ እናነባለን ሲሉ እቃወምበት የነበረው ምክንያት ሃርድ ኮፒ ለማንበብ አመቺ ነው ከሚል ነበር፤ ፍጥነት፣ ለዓይን መመቸት፣ መብራት አለማስፈለግ ወዘተ፡፡
በእንግሊዝኛ ማንበብ ከንባቡ ዓላማ አንጻር ስናየው ለትምህርት ዓላማ እንጂ በእንግሊዝኛ አንብበን ለመዝናናት ወይም የፀሐፊውን ስሜት ለመረዳት አንችልም የሚሉ አሉ፡፡ መዝገበቃላት ይዤ ማንበብ ይሰለቸኛል የሚሉ አሉ፡፡ በእርግጥ ይህን ያህል የመዝገበቃላት ጥገኝነት አያስፈልግም ነበር፡፡ ይህ ከእንግሊዝኛ ጋር ያለን ግንኙነት በትምህርትና በመደበኛ ሁኔታ ስለሆነ ነው፡፡
ሥነጽሑፍን አስመልክቶ ብዙ ዕይታ አለ፡፡ ስነጽሑፍን ለመረዳት በስነጽሑፍ ውስጥ ያለፈ መሆን ይጠይቃል፡፡ እንኳን በእንግሊዝኛ በአማርኛም አንብቦ የማይገባው ይኖራል፡፡ ገብቶት መተንተን፣ መወያየትና አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ ዳሰሳና ጥናት መጻፍ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ስነጽሑፍ በምን ቋንቋ ይሁን የሚል ክርክር በ1970ዎቹ በታዋቂ ደራስያን በየካቲት መጽሔት ተካሂዶ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ወይም በዉጪ ብለው የሚሟገቱ አሉ፡፡ ትርጉምንም እንደ አንድ መንገድ ያዩታል፡፡
ወደ እንግሊዝኛ ኢቡክ ካመዘንኩበት ምክንያቶች አንዱ የአገራችን የህትመት ዋጋ አልቀመስ ማለቱ ነው፡፡ እሱ እስካልተስተካከለ ድረስ በዚህ መንገድ እንቀጥልና ለማስተካከል ግን አንድ መላ መዘየድ ግድ ይለናል፡፡ መላውም ብሔራዊ መፍትሔ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዕውቀት፣ ለትምህርት፣ ለሳይንስ የተሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ሲሻሻል አብሮ የሚሻሻል ይሆናል፡፡ ከትርፍና ከገንዘብ አንጻር ከማየት ወደ ትውልድ መቅረጽ ትኩረት የሚያደርጉ ሰዎች ወይም ተቋማት የማሳተም፣ ማተምና ማሰራጨትን ዘርፍ ሲገቡበት ይስተካከላል፡፡
አንድ የተዘነጋ የሚመስል ነገር ቢኖር የእንግሊዝኛ ኢቡኮች ወይም መጻሕፍት ሲባል ሁሉንም ነው የሚል ይሆናል፡፡ ሁሉንም ላይሆን ይችላል፡፡ መጀመሪያ ሰፋ አድርገን ጀምረን እያጠበብን መሄድ እንችላለን፡፡ ከዓላማችንም ጋር ይሄዳል፡፡ ለመዝናናት፣ መረጃ ለማግኘት፣ ለትምህርት፣ ክህሎትን ለማዳበር፣ አመለካካትን ለመቅረፅ ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡
ትናንት በክፍል አንድ በጻፍኩት ላይ የሰጣችሁኝ አስተያየት አለ፡፡ ጥሩ ጥሩ ነጥቦች ተነስተዋል፡፡ ዛሬም እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንነጋርበት፡፡



