ማክሰኞ 20 ኦክቶበር 2026

ምን ልንብብ?

 

ምን ልንብብ?

ዕይታ

መዘምር ግርማ

ከደብረብርሃን

ጥቅምት 10፣ 2019 ዓ.ም.

 

ብዙዎቻችሁ ስታገኙኝ ከምትጠይቁኝ ጥያቄዎች አንዱ ‹‹ምን ልንብብ ትለኛለህ?›› የሚል ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት አንድ አጋጣሚ ላንሳ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. የትርጉም መጽሐፌን የመጀመሪያ ዕትም አሳትሜ በግሌ በማሰራጨት ላይ ሳለሁ መጽሐፏን የሸጥኩለት አንድ አብሮ አደጌ አንድ ነገር በግልጽ ነገረኝ፡፡ ‹‹በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ አንብቤ ጨረስኩ›› ነበር ያለኝ፡፡ ይህንን ስሰማ ማመን አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ጓደኛዬ ከኔ ጋር የትምህርት ደረጃው ተስተካካይ ስለነበረ ነው፡፡ በተመሳሳይ አጋጣሚ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዳለው አንድ በማዕረግ ተመርቆ አርበኞች ግንቦት ሰባትን በኤርትራ በረሃ የተቀላቀለ ወጣት ከትምህርቱ ዉጪ አላነበበም ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ትውልዱ ያለበትን ሁኔታ ያስረዳለት ዘንድ ያንን ወጣት አነሳ እንጂ ስልጣን ይዞ ትውልዱ እንዲማር፣ አንዲመራመርና ለአገሩ ለውጥ እንዲሰራ ለማድረግ ግን አልቻለም፡፡ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ስልጣን ያንን ለማሳካት ሊያግዘው ይችል ነበር፡፡ 

 


ወደ ፍሬ ነገሬ ስመለስ ጨርሶ አንባቢ በሌለበት እንዴት ምን እናንብብ ትላለህ የሚል ጥያቄ ሊነሳብኝ ቢችልም ምን እናንብብ የሚለውን ጥያቄ ግን ለመመለስ መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለመነሻ ያህል ማንኛውንም ነገር እናንብብ፡፡ ማንኛውንም ማግኘት የቻልነውን ነገር እናንብብ፡፡ ማንኛውንም ነገር እንድናነብ ነበር ያ ጓደኛዬ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ አንብቤ ጨረስኩ ካለኝ በኋላ ወደ እርምጃ የገባሁት፡፡ በደብረብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትን ከፍቼ ህብረተሰቡን ከስምንት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ለማስነበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ይህን ያደረኩት ይህ የተማረ ወጣት ጓደኛዬ ካላነበበ ሌላው ህብረተሰብማ ጨርሶ ጠፍቷል ወይም ሊጠፋ ነው በማለት ነበር፡፡ ሳስነብብና ንባብ ተኮር መርሐግብሮችን ሳካሂድ የታዘብኳቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ከርዕሱ ጋር የሚሄደውን ለዛሬ ላንሳ፡፡ ‹‹ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የሚመጣው የደብረብርሃን ሰው ምን ያነባል?›› የሚል ጥያቄ እናንሳ፡፡ ወደ ቤተመጻሕፍቱ ስለሚመጡት ሰዎች ብዛትና ስለሚያቡት መጽሐፍ የዳሰሳ ጥናት የሰራንባቸው ሳምንታት ነበሩ፡፡ በመጻሕፍት ወይይት ወቅትም እንታዘባለን፡፡ በዚህም መሰረት ወደ ልቦለድ፣ ስነልቦናና ታሪክ መጻሕፍት የሚያመዝኑ ይመስላል፡፡ከትዝብቴ የማስታውሰው ለትምህርት ዓላማ ከሚያነቡ ተማሪዎች ውጪ ያሉት አብዛኞቹ ጠጠር ያሉ ነገሮችን ለማንበብ አይፈልጉም፡፡ ታዲያ ይህንን ለማስተካከል የሄድንባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመጻሕፍት ውይይት ሲካሄድ የሚመረጡት መጻሕፍት የተሰባጠሩ እንዲሆኑ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ የልቦለድ፣ ፍልስፍና፣ ግጥም፣ ስነልቦና፣ ታሪክ፣ የሕይወት ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ስነ-ትምህርት ወዘተ መጻሕፍትን እያሰባጠርን ለማንበብና ለመወያየት ጥረናል፡፡ ይህ የራሱ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በዚህ መልኩ እያሰባጠረ የሚቀጥል ይኖራል፤ ተመልሶ ወደሚወደው ልቦለድ ወይም ግጥምም ሊሄድ ይችላል፡፡

 


ከትዝታውና ከግል ልምዴ ወደ አሁን ስመጣ ማንበብ የሚፈልግ ሰው ብዙ ፈተና አለበት፡፡ በዚህ ጊዜ ምንም የሚጠበቅበት የስራ ኃላፊነት ሳይኖር ለማንበብ ጊዜ ቢያገኝ እንኳን መጽሐፍ የሚያገኘው ስንቱ ነው? የመጽሐፍ ዋጋ አልቀመስ አላለምን? ከተማሪዎች እንኳን ስንቱ ናቸው መጽሐፍ የደረሳቸው? ይሁን እሺ በችግር ላይ ችግር ላነሳ አልፈልግም፡፡ ለችግሩ መፍትሔ የሚያመጣ ከሆነ እንጂ ካልሆነ ምንም አያግዘንም፡፡ በተወሰነ መጠን ይህ መሰናክል ሳያግደን ልናነብበት የሚገባን መንገድ አለ፡፡ ያንን በክፍል ሁለት እመጣበታለሁ፡፡ በእርግጥ ከላይ በርዕሱ ያነሳሁትን ጥያቄ እንዳልመለስኩ ይገባኛል፡፡ እስከዚያው የናንተን ሐሳብ ስጡኝ፤ እሱን አንብቤ ምላሼን ይዤ እመጣለሁ፡፡

 

 

     

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ምን ላንብብ? ክፍል 2

በክፍል አንድ ያየነውን የንባብ ወግ ዛሬ እንቀጥላለን፡፡ ምን ላንብብ ለሚሉ ወገኖች በርካታ ምላሾች ቢኖሩም ከዓመታት በፊት ሰዎች እናነባለን የሚሉበትንና የማልስማማበት ዓይነት ንባብ አንብቡበት ልላችሁ ነው፡፡ ይኸውም ሶፍት...