ረቡዕ 4 ኖቬምበር 2026

‎ግብዣን የሚከተል ቁዘማ

‎ግብዣን የሚከተል ቁዘማ

‎

‎አንድ ሰው አንድ ቦታ አግኝቶኝ ሂሳብ ከከፈለልኝ ወይም ከጋበዘኝ በጣም እጨነቃለሁ። ሁልጊዜ በተቻለኝ መጠን እንዳይከፍሉልኝ እጥራለሁ። ይህን ማሳካት ግን ከባድ ነው። ሳታዩአቸው ይከፍሉላችኋል። አንድ መልካም ወንድሜ አሁን በአቅራቢያዬ ተቀምጦ ኖሮ ከፍሎልኝ ኖሯል። ከሰላምታው አይቼ በመጠርጠር ሳይከፍል ለመክፈል የካፌውን የንግድ ባንክ አካውንት ተጠቅሜ ለመክፈል ብሞክር ሁለት ጊዜም አስቸገረኝ። የባንኩ አፕሊኬሽን አልሰራልኝም። ሰርቶልኝ ቢሆን መክፈሌን ለአስተናጋጇ አሳይቼ ተከፍሏል ትልልኝ ነበር። ይህን የማደርገው ስፕሪሱ ገና ሳይመጣልኝ ነበር። ሲመጣልኝ እሱ የተጠቀመውን ጨርሶ ከፍሎ ተሰናብቶኝ ሄዷል።

‎እኩለቀን ዩኒቨርስቲ ካፌ ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጬ ትኩስ ነገር ለሦስተኛ ጊዜ በማዘዝ ሂሳብ ሰራተኛዋን ከማሰለች ብዬ እግረመንገዳችሁን ቀሽር ግዙልኝ ማለት። እነሱም በሰጠኋቸው ገንዘብ ላይ አስር ብር ጨምረው መግዛት። አዲሱ ሂሳብ መሆኑ ነው። እኔ መጨመሩን እረስቼዋለሁ። ከዚያም ከዚህ ሃምሳ ብር ላይ አስር ብር ቁረጡ ማለት። ጋብዘንሃል፤ ለምሳ ከተዋጣው ብር ላይ ነው የቀነስነው አሉኝ። የአራት ሰው ባለዕዳ ሆንኩ። ባለፈው አንድ ጠባሴ የማውቀው ስሙን የማላውቀው ወንድም ወደ ከተማ ስንሄድ ሰላሳ ብር ከፈለልኝ። ለዚያውም የኤሌክትሪክ ባጃጅ ክፍያው ሃያ ብር ሆኖ ሳለ። በስሜ አስር ብር ቲፕ ሰጠልኝ ማለት ነው። እኔ ግን ድፍን ሃምሳ ብር ይዤ ነበር። ሃያ ብር ቢሆን ወደ ጋቢና ወርውሬ እገላገል ነበር። ሁልጊዜ ወደ ከተማ ወይም ከከተማ ስሳፈር ዝርዝር ብር ይዤ ነው። ሁልጊዜ አይሞላልኝም። ይከፍሉልኝና ቁዘማዬን እጀምራለሁ። መቼና የት አገኛቸው ይሆን? ብድሬን እንዴት እከፍል ይሆን? ስንት ነበር የከፈሉት? ገጠር ለቅለሶ ዕድርተኞች የሚያመጡትን የእንጀራ ብዛት መዝግበው በዚያችው ቁጥር እንደሚከፍሉት ለማድረግ እንዳልችል መዝገብ የለኝ። ዝም ብዬ መቆዘም። የሆነ አፕሊኬሽን ቢያበለጽጉልኝ ይሻል ይሆን?

‎ይህን ከምን አመጣኸው የሚል አይጠፋም። ከየት አመጣዋለሁ? ባህላችን ነው። እስከማውቀው ድረስ። አንድ ነገር ይደረግላችኋል፤ ሳታሳንሱ ሳታተርፉ ትመልሳላችሁ። ባህላችን ይህ አይደለም? እኔ ያየሁት ይህንን ነው። በእርግጥ አእምሯችን ውስጥ የሚተራመሱ ሐሳቦች አሉ። "ምን ቸገረህ! ይክፈል! ነገ አታገኘው!" ይለናል። በሌላ በኩል "ለምን ይከፍላል? ከየት ያመጣል? እሱስ ወንድምህ አይደል!" የሚል ይመጣል። ከዚህ ሁሉ ሙግት በኋላ የራሴን ልክፈል ስል ውጫዊ ጫና ይመጣል። "ልክፈል" ይሉኛል። ለማስረዳት ጊዜና ሁኔታዎች አይፈቅዱ ይሆናል። ሙግት ይከተላል። ማን ሆነህ ነው የማይከፈልልህ ማለት ይመጣል። ስንት ችግረኛ በሞላበት አገር ልክፈል እያሉ የሚመጡት ሰዎች በቀን ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ የማትረሳው ግብዣ ከተባልኩ በጦስኝ አምባ ሆቴል ምግብ አዝዤ ከተመገብኩ በኋላ ልክፈል ስል ተከፍሏል ተባልኩ። ቀና ስል የቤተመጻሕፍቴ አንባቢ ልጅ አባት ነው። ይህ አስደስቶኛል።

‎ግብዣ ፍራቻ በእግሬ ልሂድ እላለሁ።

‎ትምህርት ሚኒስቴር ከስራ ቢያባርረኝ ይጋብዙኝ ይሆን በማለት አስባለሁ።

‎እንወያይበት። እንከራከርበት።


‎

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

‎ግብዣን የሚከተል ቁዘማ

‎ግብዣን የሚከተል ቁዘማ ‎ ‎አንድ ሰው አንድ ቦታ አግኝቶኝ ሂሳብ ከከፈለልኝ ወይም ከጋበዘኝ በጣም እጨነቃለሁ። ሁልጊዜ በተቻለኝ መጠን እንዳይከፍሉልኝ እጥራለሁ። ይህን ማሳካት ግን ከባድ ነው። ሳታዩአቸው ይከፍሉላ...