ማክሰኞ 5 ጁላይ 2016

የማይረሱ ደቂቃዎች በኩሳዬ፤ ተጻፈ በመዘምር ግርማ፣ ደብረ ብርሃን፤ mezemir@yahoo.com 0913658839



ሰኔ 20 ቀን ፈተና ሳርምና ውጤት ስሞላ ያለምንም ፋታ መዋል፡፡ ማታም ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ በሚገኘው መጻሕፍት ቤት ሳስነብብ ማምሸት፡፡ በማግስቱ ከእንቅልፌ አርፍጄ 1፡00 ላይ መነሳት፡፡ የጠዋቷ መኪና ማምለጥ፡፡ በደነባው ተረኛ መኪና መሳፈርና እስኪነሳ መጠበቅ፡፡  



ባለመኪናው አትነሳም ወይ!
መኪናው ‹‹ከረቢ ጫላ›› የሚል ጽሑፍ በፊት ለፊቱ ላይ በጉልህ የተጻፈበት ነው፡፡ ጽሑፉ በአማርኛ ፊደላት መጻፉን ልብ በሉልኝ፡፡ ከተሳፋሪዎቹም የተወሰኑት አማርኛ የሚያወሩት በኦሮምኛ ቅላጼ ነው፡፡ መኪናው ውስጥ የተለያዩ ጥቅሶች ተለጣጥፈዋል፡፡ ‹‹አይደለም ከሥልጣን ከጫት መነሳት ይከብዳል፡፡›› የሚለውን ሳይ ሁለቱንም ገና ስላልተቀመጥኩባቸው የመውረዱን ክብደት ልመሰክር አልችልም ብዬ ዝም አልኩ፡፡ ‹‹ለመውረድ 50 ሜትር ሲቀረው ለረዳቱ ይንገሩ፡፡›› የሚለውም ቢሆን ለኔ ፈታኝ ትዕዛዝ ነበር፡፡ መድረሻዬን በቅጡ ስለማላውቀው ለረዳቱ መንገር አይቻለኝም፡፡ ከ1፡40 እስከ 3፡00 ተሳፋሪ እስኪሞላ ጠብቀን ተነሳን፡፡ ካሁን ካሁን ይነሳል ስል አንዳች ነገር ሳልሰራ ይሄ ጊዜ ተቃጠለ፡፡ ቀሪ ጥቅሶችን ሳስስ ‹‹የሄድክበት መንገድ እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አስብ›› የሚለውን አየሁት፡፡ ይችን ባትመክሩንም አንረሳት! መቼም እንደ ዱሮ ባሪያ ዓይናችን ታስሮ ወደምንወሰድበት አንወሰድምና! ባለ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ የአየር መንገድ አርማ ከበስተኋላዬ ተለጥፎ አየሁ፡፡ አውሮፕላን የመግዛት እቅድ ይኖራቸው ይሆን እንዴ? 



በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ፣
እንዴት አለቀልሽ የጅሩ መንገድ?
መኪናችን በጅሩ መንገድ ታጥፋ ትንገጫገጭ ጀመር፡፡ አንጎለላ ስደርስ ባለፈው ዓመት እና ዘንድሮ ያየሁት የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ትውስ አለኝ፡፡ በመኪናው መስኮት ሳማትር ዝሪት ተዘርቷል፤ ጅረቶቹም እየሞሉ ነው፡፡ መንገዶቹ ሁሉ ጭቃ ውጧቸዋል፡፡ ቁልቋልና ባህር ዛፍ የከበባቸው ቤቶች ይታያሉ፡፡ ሴቶች አከምባሎውን፣ ሞሰቡን፣ ምኑን ይዘው ይጓዛሉ፡፡ ወንዶች ጋቢ ለብሰው፣ ዱላ በየትከሻቸው ይዘው … በየሜዳው ይታያሉ፡፡ መስኩ በከብቶችና በጎች ተሞልቶ፣ እረኞችም በለምለሙ ሳር ላይ ሲቦርቁ ማየት ወርዳችሁ ተቀላቀሏቸው ያስብላል፡፡ ስጥ ጠባቂ ልጆችን እንኳን በስንት ዘመኔ አየሁ? ይህን መኪናው የሚሄድበትን አውላላ ሜዳና አድማስ ድረስ ተንጣሎ የሚታየኝን መስክና ማሳ እነ ራስ አበበና ፊታውራሪ ገበየሁ ያባረሩት ፈረንጅ እንዳያይብን ፈራሁ፡፡ ‹‹ፈልጌዋለሁ›› ካለ ‹‹አያስፈልግህም! አንሰጥም!›› የሚለው ማነው ወንዱ? እንዲያውም ወሳጅ ማምጣትና መስጠት ያስመሰግናል!

ስለ ራስ አበበ ሳይወራ ውሎ የማያድርባት ምድር!
ከቤቴ ሃያ ኪሎሜትር ገደማ ተጉዤ ኦሮሚያ ክልል ገብቻለሁ፡፡ ትንሽ አልፌ ሌላ የአማራ ክልል ግዛት የምረግጥ ቢሆንም አሁን ያለሁባት አፈር የሌላ ‹‹ክልል›› መሆኗን የሚናገሩ ምልክቶች አሉ፡፡ ደነባ ደርሼ የእነዋሪ መኪና ያዝኩ፡፡ ሰው በሰው ላይ ተጫነ፡፡  ተቆጣጣሪም አላየሁም - ወደ ታች በተወረደ ቁጥር ሕጓ እየላላች ትሄዳለችና፡፡ እንደምንም ብዬ እነዋሪ ደረስኩ፡፡ ከዚያም ወደ ኩሳዬ የሚወስደኝ መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ በመኪናው ውስጥ አብረውኝ ከተሳፈሩት ከአቶ ታምሩ ጋር ወግ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ኩሳዬ ምን አለ?›› ብዬ እንደጠየኳቸው በቀጥታ ወደ ራስ አበበ ጉዳይ ሲገቡ ለካ እኝህ ራስ አበበ እዚህ በደንብ ይታወቃሉ አልኩ፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የጀግናው ደቀመዝሙር እንደሆነ በኩሳዬ ቆይታዬ ታዝቤያለሁ፡፡ ሲያኮራ! ‹‹ራስ አበበ አገሬ ላይ ማዳበሪያ እንዳይገባብኝ ብለው ነበር አሉ፡፡ አሁን ይኸው ማዳበሪያ ወረሰው አገሩን፡፡ እንዲያው ያለሱ አልሆን አለ፡፡ ታዲያ ዋጋው ቀጠለብን ልጄ፡፡ 100 ኪሎ ዳፕ 1450 ብር ነው፤ ነጩ ደግሞ 1200 ነው፡፡ እንግዲህ ለአንዱ ጥማድ የ2650 ብር ማዳበሪያ ያሻል ማለት ነው፡፡ …›› አሉኝ እኝህ አባት፡፡ ‹‹ይህን ያህል ማዳበሪያ ተገዝቶ ምን ሊመረት ነው?›› ብዬ እያሰብኩ ዝሪቱን መስኮት አሻግሬ አማትር ጀመር፡፡ በነገራችን ላይ፣ ሳሲቶች ሆይ ስለማዳበሪያ እንደምሟገት አስታውሳችሁ ወቅሳችሁኛል አሉ ባለፈው! ‹‹አራት ኪሎ ወዳለው የአርበኞች ጽ/ቤት አያቴን እየመራሁ ሄጃለሁ፡፡ ከራስ አበበ ጋር ሆነው ጣሊያንን የተዋጉ ነበሩ፡፡ በአርበኝነት ጊዜ የቦምብ ፍንጣሪ ስለመታቸው መሪያቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ‹አገሯ ለፈረንጅ አትገዛለትም!› ይሉ ነበር አያቴ፡፡ ለአሕዛብ አትገዛም፡፡ አገራችን ሐይማኖተኛ ነው ሕዝቡ - ክርስቲያን፡፡ የሚነግሩኝን እየዘነጋሁት ነውንጅ ብዙ ምስጢር አውርተውኛል፡፡ ታዲያ የአሁኑም ዘመን ትውልድ ንቅ ነው፡፡›› ሲሉኝ እኔ መልሼ ‹‹በንቃት ግን የዱሮው ይበልጠናል ባይ ነኝ፤ አሁን ፈረንጅ ቢመጣ እልል ብሎ የሚቀበለው ይመስለኛል›› ስላቸው ‹‹እሱማ ልክ ነው፡፡ በመማር በኩል ያልተማረ የለም፤ የኛ ልጆች ግን ስለዱሮው አይጠይቁም፤ ብናወራም አያዳምጡንም›› አሉኝ፡፡ ወደ ታሪካቸው ተመልሰው ‹‹ወይዘሮ ጽጌ አረጋይ ደነባ ባለርስት ነበሩ፤ የራስ አበበ እህት ናቸው፡፡ የራስ አበበ ቦታ ለቴሌ፣ እና ለማህበራት ተሰጥቷል፤ ደርግ ማህበራት አደረገው፡፡ እንዲሁ ሆነ የነሱ ነገር፡፡ ታዲያ በጊዜው ጀግኖች ነበሩ መቼስ… ›› 

የራስ አበበ ግቢ አሁንም የኩሳዬ እምብርት ነው፡፡
ኩሳዬ ደርሰን አቶ ታምሩ የራስ አበበን ግቢ አሳዩኝ፡፡ ዙሪያውን በቁልቋል የታጠረ ግቢ ነው፡፡ ቁልቋሉ አሁን በቅርቡ የተተከለ መሆኑን ተረዳሁ፡፡  አንድ ፎቶ እንዳነሳሁ ስልኬ ባትሪዋ ድርግም ብሎ ጠፋ፡፡ በዋዜማው ደብረብርሃን መብራት ጠፍቶ ስላደረ ስልኬንም በወጉ ቻርጅ ለማድረግ አልተቻለኝም ነበር፡፡ የራስ አበበ ግቢ አሁንም የኩሳዬ እምብርት ነው፡፡ መኪና የሚቆመው እዚያ ነው፡፡ ሰዉም ማዳበሪያ ፍለጋ የተሰለፈው እዚያው ነው፡፡ ቁምጣ የለበሰ ብዙ ሰው አየሁ፡፡ የቀረ የመሰለኝ ቁምጣ እነዋሪ መለበሱ ለስራ ስለሚያመች ነው ወይንስ በሌላ ምክንያት ብዬ አሰብኩ፡፡ በዛብህ ትልቅ አድርጎ የሳላትና ሲቀርባት መንደር ለማለት ያስደፈረችውን ዲማን አስታወሰችኝ ኩሳዬ፡፡ ገና ብዙ ይቀራታል፡፡ ባለፈው ዓመት የስራ ባልደረባዬ የትውልድ ስፍራዬን ሳሲትን አይቶ የተሰማው ስሜት ተሰማኝ፡፡ እንዲህ ነበር ስሜቱን በማስታወሻዬ የከተብኩት ‹‹የእለቱ ልዩ እንግዳና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ግራርን ያየው የበላይ ዘለቀ ያገር ልጅ መምህር ሳለአምላክ ጥላሁን በሳሲት የቤቶቹ መጠጋጋትና የህዝቡ መጎሳቆል አሳዝኖታል፤ አስገርሞትማል፡፡ እኔ ግን እዚያው ተወልጄ ስላደግሁ ምንም አልመሰለኝም፡፡››

የአርበኝነቱ ቦታዎች ቢጠበቁ፣ ቢጎበኙ!
ኩሳዬ ትምህርት ቤት ወዴት አንደሆነ እኝሁ ሰውዬ በጠቆሙኝ መሰረት ስሄድ አንድ አህያ የሚነዱ ሰው አገኘሁ፡፡ ‹‹ትምህርት ቤቱን አሳዩኝ›› ስላቸው ‹‹ተከተለኝ›› ብለውኝ አብረን መሄድ ጀመርን፡፡ በቆሎ ጭነው ወደ ቤታቸው እየሄዱ ነው፡፡ በ2003 በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የተሰራው ግን ከዚያም በፊት ብዙ ዓመት ያገለገለው ትምህርት ቤት ጋ ደረስኩ፡፡ ተማሪዎች ውር ውር ይላሉ፡፡ መረብ ኳስ የሚጫወቱ ወጣቶችም ታዩኝ፡፡ ስልክ መደወል ስላልቻልኩ ‹ስብሰባው ተበትኖ ይሆን› ብዬ ሰጋሁ፡፡ ርዕሰ መምህሩን አሳዩኝ ብዬ ስጠይቅ ስብሰባ ላይ ናቸው ተባልኩ፡፡ እዚያም ስሄድ ወላጆችን፣ መምህራንንና ተማሪዎችን ሰብስበው አገኘኋቸው፡፡ የስብሰባ አዳራሹ ያላለቀ የጭቃ ቤት ስለሆነ አንድ ልንለው ይገባል፡፡ እንደገባሁ የመናገር እድል ደርሶኝ ስለራስ አበበ፣ በስማቸው ስለተሰየሙት የደብረብርሃኖቹ ሁለት አብያተ-መጻሕፍት፣ ስላመጣሁት እገዛ፣ ስለዓላማዬና ትምህርት ቤቱ ወደፊት ማድረግ ይገባዋል ብዬ ስለማስበው ነገር አወራሁ፡፡ በንግግሬ ለራስ አበበ ሐውልት ቢሰራ፣ የአርበኝነቱ ቦታዎች ቢጠበቁ፣ ቢጎበኙ፣ የአገርህን እወቅ ክበብ ቢጠናከር የሚልም ሃሳብ አንስቻለሁ፡፡ አቤት ቢሳካልን!


በትምህርት ቤቱ የተገኙት ወላጆች ስለተማሪዎችና ስለትምህርት ቤቱ የዓመቱ ስራ አስተያየት ሰጡ፡፡ እንደሚከተለው ያለ፡-
‹‹ቤት መሠረት እንደሚኖረው ሁሉ እኛም ለልጆቻችን አርዓያ የምንሆን መሠረት እንሁናቸው፡፡ ተማሪው ጥናቱን ትቶ ሞባይሉን ይነካካል፡፡ ጥናቱን ያጠና ወይንስ ሞባይሉን ይጎርጉር? አሁን እንደሰማነው እነ ራስ አበበ አረጋይ ለሃገራቸው ጸንተው የተዋጉ ናቸው፡፡ ልጆቻችንም ወዲያ ወዲህ ሳይሉ ጸንተው መማር አለባቸው፡፡ ተማሪዎች ይህን ዛሬ የመጣላቸውን መጽሐፍ ሲያነቡ ሁኔታዎችን የማስታዎስና የማንበብ ሃይላቸው ይጨምራል፡፡ ›› ብለዋል አቶ ሃብታሙ፡፡
ደረጃ ይዘው ከተሸለሙት ተማሪዎች ብዙዎቹ ስሞቻቸው አገርኛ ናቸው፡፡ ጭንብሬ ላይ እንደገጠመኝ ሁሉ ታደሰ፣ በዛወርቅ፣ ንጉስ፣ ገለታው የመሳሰሉ የምወዳቸውን ስሞች ሰማሁ፡፡ ሳምንት ሐሙስ ማታ በራስ አበበ እልፍኝ፣ ደብረብርሃን፣ ከአዲስ አበባ ድረስ መጥተህ ንግግር ያደረግህልን እንግዳችን አከለው የሻነው ደሴ ‹‹አማራ የሚባለው ማኅበረሰብ ስም በመቀየር ተጠምዷል›› ያልከው ትዝ አለኝ፡፡ ቢሆንም ታዲያ አይዞን! ኩሳዬና ጭንብሬ አሉን - የምድረ-በዳ ምንጮች! 

አንተ ምን አገባህ! በእድሜያቸው ይዝናኑ!
ድራማም ቀረበ፡፡ ሳቅን ለመሸፈን በጋቢና በነጠላ ፊታቸውን የሸፈኑ ልጆች ነበሩ ተዋንያኑ፡፡ በጣም አስደሳችና አስተማሪ ድራማ ነው፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት ሄደናል›› እያሉ ስለቦዘኑ ሁለት ወንድማማቾች ነው፡፡ አሥረኛ ጨርሶ ሌባ የሆነው ታላቅ ወንድማቸው ሲሰርቅ ገበያ ላይ መደብደቡ ሰዉን ሁሉ አስቆታል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ ምክንያት እናትዬዋ ነች፡፡ ልጆቹን ሞባይል እየገዛች አቀበጠቻቸው፡፡ አባትዬው አንድ ቃል የተነፈሰ እንደሆነ ‹‹አንተ ምን አገባህ! በእድሜያቸው ይዝናኑ! ገና ከፈለጋቸው ሌላም እገዛላቸዋለሁ›› ትላለች፡፡ ልጆቹ ትምህርት ቤት እንደማይሄዱ ከጎረቤት ልጅ የሰማው አባት የጭቃ ጅራፉን ያመጣው ይመስለኛል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በሚፈጸመው ድራማ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ እኔም በትምህርት ቤት ድራማዎች የነበረኝን ተሳትፎ አስታወስኩ - በዓይነ ህሊና፡፡
‹‹… ሚኒስትሪ ሲፈተን ፈተናውን ትቶ ፍሪዙን የሚቋጥር ልጅ አጋጥሞናል፡፡ አስረኛ ወድቆ ወላጆቹን መሬት አምጡ እያለ የሚጣላ አይተናል፡፡ በደንብ ከተማረ ግን መሬት አይሻማም፤ አይረብሸንም፡፡ ‹‹ተማር›› ስንለው ‹‹የአባቴ መሬት አለ›› ይላል፡፡ እንደነንጉስና ገለታው ዓይነት ተማሪ ሺ ይወለድ- እኛንም አስመስግነው፡፡›› የሚሉት መምህር ጥላሁን አንደበተ ርቱዕ ናቸው፡፡ በአነጋገራቸው ስምረት የመንፈስ ቅናት እንደተሰማኝ ብደብቅዎት ቃል አባይ ያደርገኛል፡፡

ስለትምህርት ቤቱ መጠናከር አስቡበት!
ከደብረብርሃን የአንድ ሺህ ብር መጽሐፍ ይዤበት በሄድኩበት ቦርሳ ሙሉ የዳቦ ሥንቅ ያደረጉልኝ አቶ አሳምነው ናቸው፡፡ ብግደረደርም አልሆነም፡፡ አንዱ የመማሪያ ክፍል ሙሉ በሙሉ ተማሪዎች ላመጡት ዳቦ ተለቋል፡፡ ርዕሰ መምህሩ አቶ ኃይሌ ምሳ እየተሰራልህ ነው ቢሉኝም ቸኩያለሁ በማለቴ ምክንያት ከአቶ አስጨናቂ ጋር ተነሳሁ፡፡ ‹‹ከአንደኛ እስከ አራተኛ ላሉት የተለያዩ አጋዥ መጻሕፍት፣ ከአምስት እስከ ስምንት ላሉት የኅብረተሰብ አጋዥ መጻሕፍት፣ ኮምፒውተር ስላለን እዚያ ላይ ጭነው የሚጠቀሙባቸው መጻሕፍት፣ ማይክሮስኮፕ … ዋናዎቹ ችግሮቻችን ናቸው፡፡›› ሲሉ ስላለው ሁኔታ በመንገዳችን ላይ አስረዱኝ፡፡ ያየሁት ቤተመጻሕፍታቸው ለዚያ ቦታ የተደራጀ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ስለመምህራን የመፈናቀል ችግር፣ ስለቤት ችግራቸው፣ መንግስትም እነዋሪ ላይ ቦታ ቢሰጣቸው ለመስራት አቅም ማጣታቸውን አስገነዘቡኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለቀው መግባት መጀመራቸውን ነገሩኝ፡፡ ከቀበሌ አስተዳደር የመጡት እኝህ ሰው ከትምህርት ቤቱ ጋር ያላቸው ቁርኝት ያስደስታል፡፡ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ እነዋሪ ላይ በከፈተው የርቀት ትምህርት ማዕከል እየተማሩ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡
በመንገዳችን ላገኛናት አንዲት ሴትዮ ዳቦ ብዪ ብለን ሰጠናት፡፡ ‹‹እስቲ አንጡት የማርያም ማበሬን በቡና አርክሼ እኔማ ዛሬ›› አለች፡፡ ‹‹እንዲያው ይህን እንኳን ልቅመስ›› ብላ ችየተቆጨች ሄደች፡፡
የአበበ አረጋይን አባት ቦታ ተመልሰን አየነው፡፡ ‹‹ራስ አበበ የተሸለሟቸው ቅርሶች ቤተክርስቲያን ስላሉ ሌላ ቀን መጥታችሁ እንድታዩ፡፡›› አሉኝ አስጎብኝዬ፡፡ እነዋሪ አለ የተባለውን ምሽግና ራስ አበበ በጥይት መትተው የጣሏትን አውሮፕላንም ወደፊት እንደማይ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ራሴ እየጎበኘሁ በጽሑፍ ላስጎብኝ /armchair tourism ይሉታል እነ አጅሬ/ እንጂ በቡድን አገር አሳያለሁ ያልኩት ሃሳብማ እየከሰመ ነው፡፡ኩሳዬ የውሃ ችግር አለባት፡፡ የተሰራው የውሃ አውታር አገልግሎት በማይሰጥበት መልኩ ተበለሻሽቷል፡፡ ንቅዘት ነው አሉ መንስኤው፡፡ ጥምሽን ያድርቅልሽ ወዳጄ! ከምንጭ ውሃ ሲያመጡ ያየኋቸውም እንዲየርፉ ጸልዩ! 



በመልስ ጉዞ ያገኘኋቸው ጥቅሶች
‹‹ፍቅር የለለው ሕይወት አበባና ፍሬ እንደሌለው ዛፍ ነው፡፡››
‹‹እያንዳንዱ ያለፈ ቀን ለሚቀጥለው መምህር ነው፡፡››
‹‹ምከረው ምከረው፤ እምቢ ካለ መከራ ይምከረው፡፡›› - የቤት ስራ ሳንሰራ ሒሳብ መምህራችን ሲገርፉን የሚጠቅሷት ጥቅስ አስታወሰኝ፡፡
‹‹ የማይሰሩ እጆች ፒን ኮድ የላቸውም፡፡››
‹‹ምላጭ ምላጭን አይቆርጥም፤ ሌባም ሌባ አይሰርቅም፡፡››
‹‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል፡፡›› 
ተጋርዶ ሰፈሯ?
ለመረጃ ያህል አብቁተ እነዋሪ ቅርንጫፍ መክፈቱን እወቁት፡፡ ማዳበሪያም በዱቤ ቀርቶ በአብቁተ ሆኗል፡፡ ትንሽ ወሰብሰብ እንዳለ ነው የግብዓት ነገር፡፡ አንድ ከአካባቢው የበቀለ የግል ወይም የአክስዮን ኩባንያ ቢኖር አትሉም! ንግድ ባንክን አበጀህ ብያለሁ፡፡ አምቡላንስም አይቻለሁ፡፡ ባለፎቅ ህንጻ እየተገነባ ነው፡፡ ‹‹እንዲያው የምንድነው?›› ብዬ ከጎኔ የተሳፈሩትን ብጠይቅ ‹‹ፍርድ ቤት›› አሉኝ መሰለኝ፡፡ ማን የምትባል አገር ነች አሉ ፍርድ ቤቶቿን እየዘጋች ያለችው? መጥታ ባስተማረችን፡፡
የመኪናው ውስጥ ዘፈን ይሰማል፡፡ ዶፉን ያወርደዋል፡፡ መኪናው ዶፉን ሰንጥቆ ሲያልፍና መብረቁ አረፍ አረፍ እያለ ሲያደበላልቀው በደብረብርሃን ብሩህ ተስፋ ትምህርት ቤት ባለፈው ሳምንት በመብረቅ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈውን ሁለት ልጆችና የቆሰሉትን ሌሎቹን አሰብኩ፡፡ በኩሳዬ ትምህርት ቤት ግን የመብረቅ ጥንቃቄ መረጃ በሦስት ቋንቋዎች በትልቅ ሰሌዳ በማሽን ተጽፎ ተለጥፏል፡፡ በጎ አድራጊ ሰጥቷቸው ይሆናል፡፡ ዘፋኙ ቀጠለ፡-
‹‹አልገለጥ አለ ተጋርዶ ሰፈሯ፣
ቀረች ከሕዋው ላይ ከጠረፍ ድንበሯ፣
ምን ይሆን የጸሐይ ማፈሯ፣
ነይ ጸሐይ… ››
ይህን ዘፈን የንባብ፣ የዕውቀት፣ የፍቅር፣ የበጎ ነገር ሁሉ ፀሐይ እንድትወጣልን ለምትመኙና ለምትጥሩ ጋብዣችኋለሁ፡፡ ጅሩ የሚልም ዘፈን አለ - አድምጡልኝ፡፡ ስለራስ አበበ የተሰራ ቪዲዮም! ፎቶዎች!
ከኩሳዬ ያመጣሁትን ዳቦ አቶ አሳምነው ባሳሰቡኝ መሠረት ጓደኞቼን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍተ ጠርቼ ከአንባቢያን ጋር ስለኩሳዬ እያወራን በላነው፡፡ ጅሩ መጥተህማ ሳትይዝ አትሄድም የተባልኩትን ዳቦ ሁሉም ወደዱልኝ፡፡ ባለመሄዳቸው ቅር ሳይላቸው አልቀረም፡፡
አንድ የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ‹‹ከዘመናዊው ዓለም ጀግኖች አንዱ›› ያላቸው ራስ አበበ የድንቅ የጦር መሪና የኢትዮጵያን ባንዲራ ለአምስት አመታት እንዲውለበለብ ያደረጉ ናቸው፡፡ በእርሳቸው ድርጊትና ዝና ተነሳስቼ ያደረኩት ጉዞ ይህን ይመስላል፡፡

ረቡዕ 20 ኤፕሪል 2016

ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት




ጤና ይስጥልን፣
በደብረብርሃን ከተማ የጀመርነው መጻሕፍትን ባሉበት የማድረስ ተግባራችን በይፋ ተጀምሯል፡፡ የሚፈልጉትን መጻሕፍት ይዘዙን፡፡ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች፡-
1.
የራስዎ አነስተኛ የመጻሕፍት ስብስብ እንዲኖርዎት እናግዛለን (የመጻሕፍት መደርደሪያ ሞዴሎችን እናቀርባለን)
2.
ምን እንደሚያነቡ እናማክራለን
3.
የንባብ ችግር ካለብዎት እናግዛለን
4.
በኢንተርኔት፣ በስልክ፣ በሶፍት ኮፒ ሱስ ከተጠመዱ ወደ መጽሐፍ እንዲመጡ እናደርጋለን፡፡
4.
የፍጥነት ንባብ (speed reading with a better comprehension) እናለማምዳለን
5.
ያገለገሉ መጻሕፍትን እንገዛለን፡፡ ገዝተውት ሳያነቡት የተቀመጠ መጽሐፍ ካለ ለምን ሸጠውልን ሌሎች አያነቡትም? መጻሕፍትን ከእስር ነጻ እናውጣቸው!
6.
ያገለገሉ መጻሕፍትን እንገዛለን፣ እናከራያለን፡፡ በነጻ እናስነብባለን፡፡ መጻሕፍትን እንሸጣለን፡፡
7.
ከእኛ የገዙትን መጽሐፍ አንብበው ንጽሕናውን እንደጠበቀ ከመለሱልን ከዋጋው 50 ፐርሰንት እንገዛለን፡፡
8.
ከእኛ የገዙትን መጽሐፍ ማንበብዎን በስልክና በኢንተርኔት እንከታተላለን
9.
መጽሐፍ ለሚያሳትሙ ደራሲያን የምክር አገልግሎት እንሰጣለን
10.
የመጻሕፍት ውይይትና የስነጽሑፍ ምሽት ዘወትር ሐሙስ ማታ ከ12፡00 ጀምሮ እናካሂዳለን
11.
የመጻሕፍት ዕቁብ እናስጀምራለን፤ መጻሕፍቱን እናቀርባለን፤ በቡድኑ ምን ይነበብ በሚለው ላይ እናማክራለን
12.
በሌሎች ከተሞችም የመጻሕፍት ሽያጭና እኛ ከምንሰራው ጋር የሚመሳሰል ስራ ለመጀመር ለሚያስቡ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
ለተጨማሪ መረጃ 0913 6588 39 ወይንም 0970 38 10 70 ይደውሉ፡፡
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!
መገኛችን ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ ከእቴነሽ ሆቴል አጠገብ ነው፡፡ ስልክ 0970381070

ቅዳሜ 19 ማርች 2016

መጻሕፍት



ጤና ይስጥልኝ፣
በደብረብርሃን ከተማ የጀመርነው መጻሕፍትን ባሉበት የማድረስ ተግባራችን በይፋ ተጀምሯል፡፡ የሚፈልጉትን መጻሕፍት ይዘዙን፡፡ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች፡-
1. የራስዎ አነስተኛ የመጻሕፍት ስብስብ እንዲኖርዎት እናግዛለን (የመጻሕፍት መደርደሪያ ሞዴሎችን እናቀርባለን)
2. ምን እንደሚያነቡ እናማክራለን
3. የንባብ ችግር ካለብዎት እናግዛለን
4. በኢንተርኔት፣ በስልክ፣ በሶፍት ኮፒ ሱስ ከተጠመዱ ወደ መጽሐፍ እንዲመጡ እናደርጋለን፡፡ (እንደ እኔ)
4. የፍጥነት ንባብ (speed reading with a better comprehension) እናለማምዳለን
5. ያገለገሉ መጻሕፍትን እንገዛለን፡፡ ገዝተውት ሳያነቡት የተቀመጠ መጽሐፍ ካለ ለምን ሸጠውልን ሌሎች አያነቡትም? መጻሕፍትን ከእስር ነጻ እናውጣቸው!
6. እናከራያለን (የሚከራዩት ገንዘብ አስይዘው ሲሆን፤ ክፍያው በቀን ሁለት ብር ነው፡፡)
7. ከእኛ የገዙትን መጽሐፍ አንብበው ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ንጽሕናውን እንደጠበቀ ከመለሱልን ከዋጋው በ60 ፐርሰንት እንገዛለን፡፡
8. ከእኛ የገዙትን መጽሐፍ ማንበብዎን በስልክና በኢንተርኔት እንከታተላለን
9. መጽሐፍ ለሚያሳትሙ ደራሲያን የምክር አገልግሎት እንሰጣለን
10. የመጻሕፍት ውይይት እናካሂዳለን
11. የመጻሕፍት ዕቁብ እናስጀምራለን፤ መጻሕፍቱን እናቀርባለን፤ በቡድኑ ምን ይነበብ በሚለው ላይ እናማክራለን
12. በሌሎች ከተሞችም የመጻሕፍት ሽያጭና እኛ ከምንሰራው ጋር የሚመሳሰል ስራ ለመጀመር ለሚያስቡ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
ሌላ ምን አገልግሎት ብንጨምር ጥሩ ነው ትላላችሁ? ለተጨማሪ መረጃ በ 0913 6588 39 ወይንም 0970 38 10 70 ይደውሉ፡፡ ጊዜያዊ ማዕከላችን ጓሳ ቡና ሲሆን መገኛውም ደብረብርሃን፣ ጠባሴ፣ ከእርሻ ሰብል ፊት ለፊት ነው፡፡

ሐሙስ 10 ማርች 2016

አንድን ትምህርት በሁለት ቋንቋ የምታስተምሩ ሆይ!




በቅርቡ ወደ አንድ የግል ትምህርት ቤት ሄጄ ከመምህራን ጋር በምነጋገርበት ወቅት አንድን ትምህርት በሁለት ቋንቋ እንደሚያስተምሩ ነገሩኝ፡፡ ይህም ማለት ሂሳብንና ሳይንስን የመሳሰሉትን ትምህርቶች በአማርኛም በእንግሊዝኛም ያስተምራሉ፡፡ ነገሩ የወላጆችንም የመንግስትንም ፍላጎት ለማሟላት መሆኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል ወላጅ ልጁ በእንግሊዝኛ እንዲማርለት ይሻል፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በአፍ መፍቻ ቋንቋ አስተምሩ ይላል፡፡ በመሃል ቤት ተማሪው ጫና ያርፍበትና አሥራ ምናምን ትምህርት እንዲማር ይገደዳል፡፡ አሥራ ምናምን የሚገባው ኮምፒውተሩ፣ የእንግሊዝኛ ንግግሩ ሲጨማመር ነው፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች የተሻለ የትምህርት አሰጣጥ መኖሩ ባይካድም ተማሪው ግን ይህ ጫና ሊወገድለት ይገባል - በአንዱ ቋንቋ ብቻ ሊማር ይገባዋል፡፡ ይህን ጉዳይ የሚከታተሉት የትምህርት ሹማምንት ትምህርት ቤት ድረስ ሄደው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ተማሪዎቹ በሁለት ቋንቋ አይማሩም የሚል አቋም አላቸው፡፡ አንድ ቅር የሚያስብለው ነገር ግን ግብረገብንና ግዕዝና የመሳሰሉት ትምህርቶችም ሊሰጡ አይገባም መባሉ ነው፡፡ የትምህርቱ ጠቀሜታ እየታየ ተማሪዎች እንዲማሩት ቢደረግ ክፋቱ አይታየኝም፡፡ እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ የተሻለ የሚያውቁ ከሆነ ሃሳብዎን ያጋሩኝ፡፡

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...