ቁልፍ የሕይወት ክህሎቶች
በአሸናፊ ታደሰ
ዳሰሳ በመዘምር ግርማ
መጋቢት 2015 ዓ.ም
ስለ መጽሐፉ ያለኝን ግምገማ ከማቅረቤ በፊት መጽሐፉን ስላገኘሁበት አጋጣሚ ላንሣ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መምህሬ መምህር ጌቱ ተፈራ ትናንት ሰው ላስተዋውቅህ ብለው መምህር አሸናፊ ታደሰን ይዘዋቸው መጡ፡፡ መምህር አሸናፊን እንደማውቃቸው አላወቁም፡፡ ይሁን እንጂ የኃይለማርያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሥነልቦና አማካሪና መምህር ሆነው እንደማውቃቸው ነገርኳቸውና ተደሰቱ፡፡ አሁን የደብረብርሃን መምህራን ኮሌጅ መምህር ናቸው፡፡ ስለ መጽሐፍ የመጻፍ፣ የማሳተምና የማሰራጨት ጉዳይ ብዙ አወጋን፡፡ መጽሐፉን አንድ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አነባለሁ ባልኩት መሰረት እነሆ አነበብኩት፡፡ የተሰማኝንም ለመጻፍ ቻልኩ፡፡ ‹ቁልፍ የሕይወት ክህሎቶች› የተባለው ይህ መጽሐፍ መምህራችን እኛን በትምህርት እንድንተጋና ክህሎቶቻችን እንዲዳብሩ ይመክሩን የነበረው ነፀብራቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይህን አስተዋጽኦም ከትምህርት ቤታችን በዘለለ ለአሁኑም ትውልድ ማቅረባቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ እነሆ ወደ መጽሐፉ፡፡ ለመሆኑ መጽሐፉ ምን ይዟል? በምንስ ዓይነት አቀራረብ?
‹‹ደስተኛ ሕይወትን ለመኖር የሚያገለግሉ የተፈጥሮና የትምህርት ውጤት የሆኑ ዕውቀትና ክህሎቶች ወይም ብቃቶች›› በሚል ደራሲው የገለጿቸው የሕይወት ክህሎቶች በአእምሯዊ፣ በስሜታዊና በማህበራዊ ዋና ዋና ምድቦች ተከፍለዋል፡፡ ክህሎቶቹን በንባብ ልናገኛቸው ብንችልም ለበለጠ ውጤታማነት ደራሲው የተግባር ሥልጠና ወደመስጠት ሊያሸጋግሩት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ እርሳቸውም ጠቆም ያደረጉት ክህሎቶችን፣ ይዘቶችንና ስልቶችን በሚገባ አጣምሮ ያካተተ የተግባር ስልጠና ያስፈልጋል፡፡
የሕይወት ክህሎቶቹን ከአሁን በፊት ከሥልጠና ሠነድ ባገኘኋቸው ጊዜ በጣም ተሰምቶኝ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተለይም ገጠር ያደግን ህብረተሰብ ክፍሎች ችግር አድርጌ አይቼዋለሁ፡፡ እኔም በግሌ ክህሎቶቹን ከማጣቴ አንጻር ብዙ ችግር ገጥሞኛል፡፡ እስኪ እርስዎም ገጥሞዎት ከሆነ የራስዎን ሁኔታ እያሰላሰሉ ይከተሉኝ፡፡ በመጽሐፉ ‹የንጥል ኩነት ትንተና› የሚሉ ምሳሌዎች ለእያንዳንዱ ክህሎት የቀረቡ ሲሆን፤ እነሱም ሃሳቡን ከአገራዊ ተጨባጭ ምሳሌ ጋር ለመረዳት ይጠቅማሉ፡፡
ራስን ማወቅ በሚለው ክፍል አእምሯዊና አካላዊ ጥንካሬን፣ ጠባይን፣ ፍላጎትን፣ ምኞትን፣ የምንወድና የምንጠላውን ማወቅ ያለውን ጠቀሜታና አለማወቅ ያለውን ጉዳት እንረዳለን፡፡ ያላወቀ ሰው የሚገጥመውን ጉዳት ለመረዳት በሰዎች ግፊት ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ገብቶ ስላልተሳካለት ግንበኛ የሆነውን ዘርጋው አውሌን ታሪክ ማንበብ በቂ ነው፡፡ ራስን ከማወቅ ጋር የሚያያዘው የራስ ግምት ደግሞ ስለራሳችን ያዳበርነው ግምት ከየት እንደመጣና እንዴት እንደሚሻሻል ያስተምራል፡፡ ከትምህርት፣ ከእርስበርስ ግንኙነትና ከአካላዊ ብቃትዎ አንጻር ለራስዎ የሰጡት ግምት ከፍተኛ ይሁን ዝቅተኛ ለመገምገምና ለማሻሻል ይህን ክፍል ይመልከቱት፡፡
ተቆርቋሪነት ስሜት ክህሎት ሕይወት በሌሎች ሰዎች ዘንድ ምን እንደምትመስል ገምተን መረዳትን ይመለከታል፡፡ በብዙ መልኩ የሚንጸባረቀው ይህ ክህሎት ከጎለበተ ለማህበራዊ ሕይወት፣ ለአገር ብሎም ለሁለንተናዊ የእርስበርስ ግንኙነት እርሾና ለእኔ ብቻ የሚልን አስተሳሰብ የሚያስቀር ነው፡፡ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ እኔና ለእኔ የሚል አስተሳሰብ በመግነኑ ይመስለኛል ምስቅልቅል ውስጥ የገባነው፡፡ የዚህ ክህሎት አለመኖር ይህን ያህል ከጎዳን መኖሩ ምን ያህል ይጠቅመናል?
አስተዋይነትና አመዛዛኝነት ያለው አስተሳሰብ ደግሞ ‹‹መረጃና ልምድን በተጨባጭና ከስሜት ነጻ በሆነ መንገድ የመተንተን ችሎታ›› ተብሎ ተገልጿል፡፡ በአእምሮ ሳያወጡና ሳያወርዱ፣ ሰውን ያስቀይማል አስቀይምም ሳይሉ እንደደቦጭ ሁሉ ከሰዎች ጋር ንግግርና ምልልስ ውስጥ መግባት ግጭት ላይ እንደሚጥልና ያልተፈለገ ነገርን እንደሚያስከትል ከመጽሐፉ ስናነብ ራሳችንንና ሌሎችን ወዳጆቻችንን በአእምሯችን ብንስል መልካም ነው፡፡ ይህ ክህሎት የፍቅር ጓደኛን ከመምረጥና ከሌሎች ወሳኝ የሕይወት ምዕራፎችም ጋር ይያያዛል፡፡ ከአስተዳደግና ከትምህርት ጭምር ያጣናቸው የዚህ ክህሎት ንዑሳን ክፍሎች ስለሚኖሩ ከራሳችን ጋር መነጋገሩ መልካም ነው፡፡
የፈጠራ ችሎታ የሚንፀባረቅበት አስተሳሰብ ሁኔታዎችንና ሃሳቦችን ለየት ባሉ ስልቶች ለመተርጎምና አዳዲስ ሃሳቦችንና ንድፎችን ለማፍለቅ የሚጠቅም ሲሆን በዘመናችን ተፈላጊውን የሃሳብ ተለማጭነትና በነባር አሰራሮች ላይ ለውጥ ማምጣትን ያመጣል፡፡ በአገራችን ካሉ የፈጠራ ሰዎች እስከ ዓለም አቀፎቹ የተጠቀሙቸውን ስልቶች እኛም በዕለትከዕለት ሕይወታችን መጠቀም እንደምንችል መገንዘብና መሞከር ያስፈልጋል፡፡
የችግር አፈታት ክህሎት ልዩልዩና ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትና በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስፈልገው በጥልቀት ማሰብና ማሰላሰል ነው፡፡ ከግል ችግሮቻችን ዓለምን በቅርቡ እስካናወጠው የኮሮና ወረረሽኝ ድረስ ምን ያህል ሳይንሳዊ መንገዶችን ተከትለን መፍትሔ ፈለግን ሲል የሚሞግተን መጽሐፍ መፍትሔውን ያስቀምጣል፡፡
የውሳኔ አሳጣጥ ክህሎት ሌላው ወሳኝ የሆነ ክህሎት ነው፡፡ እርስዎ እስኪ በሕይወትዎ የወሰኑትን አንድ ጉልህ ነገር ያስቡ፡፡ ምን ጠንካራና ደካማ ጎን አለው? ለወደፊቱስ ውሳኔ ከመወሰንዎት በፊት አስፈላጊውን ሳይንሳዊ ሂደት መከተል ያለብዎት አይመስልዎትም? ከውስጣዊ ማንነታችን ጋር የሚጣጣሙ ውሳኔዎችን ለመወሰንና ሕይወታችን እንዳይበላሽ ለማድረግ የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎን ማወቅና መተግበር አለብን፡፡
ስሜትን በአግባቡ የማስተናገድ ወይም የመቆጣጠር ክህሎት ሳይንሳዊ መሰረትና ማብራሪያ ያለው ሲሆን፤ ስሜታችንን በአግባቡ መግለጽን ካልተማርን ጤናማ ስሜትንና ሥነምግባርን ማዳበር ላንችል እንችላለን፡፡ ስሜትን መቆጣጠርም ሆነ ውጥረትን መቋቋም ሕይወትን የሚያሰምርና ከበሽታና ከችግሮች የሚያድን ነው፡፡ ስሜታችንን ለይተን መቆጣጠር ስንችል፣ ውጥረትን የመቋቋም ክህሎትን ስናዳብርና የውጥረትን ምልክቶች ለይተን ስናውቅ ስሜትን በአግባቡ ማስተናገድም ሆነ መቆጣጠር እንችላለን፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ሲሆን፤ መጽሐፉም መነሻ ይሆነናል፡፡
መግባባት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ብንገነዘብም ከግል እስከ አገር መግባባት ሲያቅተን ይስተዋላል፡፡ የመግባባት ክህሎት እንዴት ያለ መሆኑን ከመጽሐፉ ስንረዳ እንደ ጎንጥ ችግሮቻችንን በጠብና በማስፈራራት ከመፍታት ይልቅ የተሻለ አማራጭ እንወስዳለን፡፡ በልዩ ልዩ መንገዶች ተግባቦትን ለማሳካት ስናስብ መልዕክቱ፣ የመልዕክቱ ማስተላለፊያ መንገድ፣ የተግባቦቱ ማዕቀፍ፣ መልዕክት አደናቃፊዎችና የተቀባይ ግብረመልስ በሚለው መንገድ የምንጠቀም ሲሆን ይህም ሂደት በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ሊሳካ ወይም ሊስተጓጎል ይችላል፡፡
የእርስበርስ ግንኙነት ክህሎት በተለያዩ አውዶችና ዓላማዎች ከሰዎች ጋር የሚኖሩንን ግንኙነቶች የተመለከተ ሲሆን የዚህም ስኬትና ውድቀት ግንኙነታችን የተሳካ እንዲሆን ወይም እንዲቋረጥ እስከማድረግ የራሱ የሆነ ሚና አለው፡፡ ልዩ ልዩ ጥቅሞች ያሉት የእርስበርስ ግንኙነት ደረጃዎችም አሉት፡፡ ትውውቅ፣ ማጎልበት፣ መቀጠል፣ መበላሸትና ማቋረጥ ሲሆኑ፤ በተለያዩ የግንኙነት ዓይነቶች ውስጥ የሚሰሩና ከግል ሥነምግባር ጋርም ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡
የአቻ ግፊትን የመቋቋምና የራስን አቋምና ስሜት ፊት ለፊት የመናገር ብቃት በሚል ከቀረበው ምዕራፍ የአቻ ግፊትን በቀላሉ ሊገጥመን በሚችል ሁኔታ ይጀምራል፡፡ ተማሪ ሆነህ ጓደኞችህ ደብሮናልና ሻይ ጠጥተን እንምጣ ያሉትን ሃሳብ ተቀብለህ ሄደህ ግብዣው ወደ ምግብና አልኮል እንዲድግ የተደረገበትን ሁኔታ ተጠቅሷል፡፡ ይህ መጥፎ ግፊት በሚለው ሊመደብ ይችላል፡፡ የዚህን ዓይነቱን ግፊት እንዴት ልንመረምርና ምላሽ ልንሰጠው እንችላለን? ይህ ቀጥተኛ ሲሆን በተዘዋዋሪ የሚመጣብን በማየታችን ብቻ ለማድረግ የሚገፋፋ ቀጥተኛ ያልሆነም ግፊት አለ፡፡ በይሉኝታም ይሁን ውጤቱን ባለማመዛዘን ከመግባት የራስን አቋምና ስሜት በግልጽ ስለመናገርና ስለአፈጻጸም ሂደቱ በመጽሐፉ የተጠቀሱትን ነጥቦች መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡
የመደራደር ክህሎት የመነጋገርና የመተማመን ብቃትን የሚጠይቅ ሲሆን ስኬቱ ክህሎቱን በማወቅ፣ በመለማመድና በመተግበር ይጎለብታል፡፡ የክህሎቱ አለመኖር የሚያመጣውን ቀውስ አስቡት፡፡ ሁለታችንም ተደስተንና ረክተን ጉዳያችንን ለመፈጸም የሚጠቅመው ክህሎቱ የራሱ ደረጃዎች ያሉትና ያለመሰልቸት መተግበር ያለበት ነው፡፡
የማዳመጥና የጥናት ክህሎቶችን ስታስቡ በእናንተ የትምህርት ሕይወት እንዴት ይገለጻሉ? መጽሐፉ የውጤታማ አድማጭነት መመሪያዎችን ሲያቀርብ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ያለ የማዳመጥ ሂደትን በልዩ ሁኔታ ያቀርብልናል፡፡ ከማስታወሻ አያያዝም ጋር አስተሳስሮ ያቀርባል፡፡ መደበኛ የጥናት ፕሮግራም መኖር፣ በንባብ ወቅት መከተል ያለብን ተግባራት፣ የንባብ ስልቶችና ዓይነቶችን ያቀርባል፡፡
የጊዜ አጠቃቀም ክህሎት ለውጤታማነትም ሆነ ለሕይወት ትልቅ ግብዓት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ የጊዜ ብክነትን የሚያመጡ በርካታ ምክንያቶች የተጠቀሱ ሲሆን በእኔ በኩል በጣም የሚያጋጥመኝና በመጽሐፉ የተጠቀሰውን አላስፈላጊ ከሰላምታ የሚከተሉ ጨዋታዎች መኖርን እንደምሳሌ መጠቀም ይቻላል፡፡ የቀረበውን የጊዜ አጠቃቀም መመዘኛ ሰንጠረዥ ተጠቅመን አጠቃቀማችንን ነጥብ እንድንሰጥ የሚጋብዘው ይህ ክፍል ስለ ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ጠባያት ያስተምረናል፡፡
ገንዘብን በአግባቡ የመቆጠብ ችሎታ ወይም ልምድ በትምህርት ቤት ያልተማርነው ወይም የትም ያልሰለጠነው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ገንዘብን ለአስፈላጊው ጉዳይና በተገቢ መንገድ ማዋል፣ መቆጠብ፣ ብድርን በትክክል መጠቀምና ከዕቅድ ጋር ማስኬድ የተገባ ነው፡፡ ለዚህም ዝርዝር ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡
ራስን ከአደጋ የመጠበቅ ብቃት በጣም አስፈላጊ ሆኖ የቀረበ ሲሆን በአሜሪካ በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ያሉ ሰዎች ለአደጋ የሚጋለጡባቸውን ምክንያቶች በማቅረብ ይጀምራል፡፡ የመኪና አደጋን አስመልቶ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ 30 እጥፍ አደጋ እንዳለ ሲገልጽ ለልዩ ልዩ አደጋዎች ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄ ያስገነዝባል፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ለየትኛው አደጋ መከላከል ክህሎቱ አለዎት? መጽሐፉ መነሻ ክህሎቶችን አስቀምጧል፡፡
የግልና አካባቢ ንጽህናን የመጠበቅ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም የደን ደህንነትን የመጠበቅ፣ የመተካትና የመጠቀም ዕውቀትና ክህሎት ቀጣዮቹ ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ለጥቅም የዋሉትን ቃላት በሙዳዬ ቃላት በይነዋል፡፡ የማጣቀሻ ጽሑፍ ዝርዝርም ተካቷል፡፡ ትክክለኛው መጽሐፍ በትክክለኛው ጊዜ!