ከጠጠር ዋሻ አማኑኤል እስከ ወንፈስ ቆላ አማኑኤል የመንገድ ፕሮጀክት
በአማራ ብሔራዊ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሞጃና ወደራ ወረዳ፣ እንግድዋሻ ቀበሌ ከጠጠር ዋሻ አማኑኤል እስከ ወንፈስ ቆላ አማኑኤል የመንገድ ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት ተጀምሮ ተቋርጦ የነበረ ቢሆነም ከሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ እንደሚከተለው ይገለጻል፡-
አካባቢው መንገድ ስለሌለው እናቶች በልምድ አዋላጅ እየወለዱ ሕይወታቸው ማለፉና ጤና ማጣታቸው አሳሳቢ ችግር ላይ ሲሆኑ፤ መንገዱ ከተሰራ ግን ይህ ችግር ይስተካከላል፡፡
ዕቃ አጓጉዞ የመጠጥ ዉኃ መገንባት ባለመቻሉ ማህበረሰቡ በዚህ ዘመን ንጹህ የመጠጥ ዉኃ ያለማግኘቱ እየተቸገረ ይገኛል፡፡ መንገዱ ከተሰራ ግን የዉኃ ችግር ይወገዳል፡፡
ወንፈስ ቆላ አማኑኤል ትምህርት ቤት ቢኖርም የተሻለ በጎአድራጊዎች መርዳት
ቢችሉና ቢገኝ እንኳን በመንገድ ምክንያት ሳይረዳ በመቅረቱ ወይም የተሻለ ግንባታ ባለመኖሩ ትምህርት ላልደረሳቸው ማድረስ አልተቻለም፡፡
መንገድ ካለ ግን ይህ ችግር ይስተካከላል፡፡
በወንፈስ የሚገኘው ገልብጥ አማኑኤል ታሪክ ያለውና የተመሰረተው በአጼ ናዖድ ዘመን ሲሆን የስም ትርጓሜውም ሁለት ወንድማማቾች ተካክደው
በሀሰት ሊምሉ መጥተው በሀሰት ምለው ሲመለሱ መንገድ ላይ በመሞታቸው የተሰየመ ነው ይባላል፡፡ ሌላው የቤተክርስቲያኑን ቅርስ የሰረቀ
ሰው ከነእቃው ተገልብጦ ሞቶ በመገኘቱ ነው የሚባልም አለ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ግራኝ አህመድ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ አብያተክርስቲያናትን
እየዞረ ሲያቃጥል ያልተቃጠለ ብቸኛ በመሆኑ ታሪካዊነት ስላለው ጎብኝዎች ቢያዩት የሚለው አንዱ ዓላማ ነው፡፡ የገልብጥ አማኑኤል
ፀበል ፈዋሽ በመሆኑ በፀበሉ መጠቀም የሚፈልግ ብዙ ማህበረሰብ ቢኖርም በመንገድ ምክንያት ሳይጠቀሙ መቅረታቸው ይታወቃል፡፡ መንገዱ
ከተሰራ ግን ይህ ችግር ይስተካከላል፡፡
እንግድዋሻ የተባለው ታሪካዊና አርበኞች ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር ሲፋለሙ በመኖሪያነትና ህዝቡን ከእልቂት በማትረፊያነት ይጠቀሙበት የነበረው ዋሻ ወንፈስ ስለሚገኝ ለመጎብኘት መንገዱ ወሳኝነት አለው፡፡ ይህም የቱሪስት መስህቡን በማስጎብኘትና የማህበረሰብ ሎጅ ለመገንባት ለአካባቢው ህዝብ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
የመንገዱን ስራ የወረዳው መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተከታታለው ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡም ለመንገድ ስራ ጥሩ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ ግብር በሚክፍሉበት ወቅት በአባወራ 1000 ብር በነፍስ ወከፍ ከፍለው በተዋጣው መዋጮ ስራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ 9 ኪሜ ርዝመት ያለው መንገድ ቆረጣ በ ኤክስካቫተርና ሎደር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ክረምቱ እስከሚገባ ስራው የሚቀጥል ሲሆን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራው እንዳይስተጓጎል ታግዙንና ላልሰሙም ታሰሙልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
ስራው እስካሁን ከተጠቀምነው 1.6 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ በትንሹ 2.5 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ ይኸውም
የቆረጣ 100 ሰዓት 8300 ብር በሰዓት ድምር 830 000 ብር፣ ኤክስካቫተር 100 ሰዓት በሰዓት 4580 ብር ድምር 458000 ብር፣ አፈር መድፋት 450 ድፌት በዳምፕ 2000 ብር ድምር 900000 ብር፣ ሎደር 312000 ብር ስራን የሚያካትት ነው፡፡
የመንገድ ስራው ኮሚቴ አባላት - ከበደ ኃይሉ፣ አባተ ተድላ፣ ጌታነህ በላቸው፣ አውላቸው ገብረጻድቅ፣ ተገሽ ደግነገር፣ ደመረ ተክለጻድቅና ሸዋፈራ ከበደ ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱ አካውንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ ከጠጠር ዋሻ አማኑኤል እስከ ወንፈስ ቆላ አማኑኤል የመንገድ ፕሮጀክት 1000531335938 ነው፡፡