ቅዳሜ 15 ኤፕሪል 2023

በጎፈቃደኝነት - እንስሳትን በመንከባከብ፣ ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ በማድረግ፣ ታማሚዎችን በመጠየቅ ወይስ በሌላ?

በጎፈቃደኝነት

እንስሳትን በመንከባከብ፣ ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ በማድረግ፣ ታማሚዎችን በመጠየቅ ወይስ ሌላ?

 


በቅርቡ ስለበጎፈቃደኝነት ትምህርት ቀርቦልን ነበር፡፡ እንግዳችን በርከት ስላሉ ከበጎፈቃደኝነት ጋር የተያያዙ ነጥቦች ያስተማሩን ሲሆን፤ በወቅቱ ይዤው ከነበረው ማታወሻ አለፍ አለፍ ብዬ ልጠቃቅስ፡፡ እንግዳችን ትምህርቱን ሲጀምሩ ‹‹ማን ምን እንዲያደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?›› የሚል ጥያቄን ለሁለት ተሳታፊዎች በመጠየቅ ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹን እንዲደረግላቸው ለፈልጉት ጉዳይ በምላሹ ምን እንደሚያደርጉም ጠይቀዋቸዋል፡፡  በዚሁም ወደ በጎ ፈቃደኝነት ሃሳብ ገብተው ‹‹ለዚያስ ምን ምላሽ አላችሁ?›› የሚል ነጥብን ጨምረዋል፡፡ ይህም እንዲደረግልን በምንፈልገው አቻ ምን እናበረክታለን የሚል ነው፡፡  

ብዙ ርቀት ከመሄዳችን በፊት ግን እርስዎን ልጠይቅዎት፡፡ በበጎፈቃደኝነት ተሰማርተው ያውቃሉ? ለመጀመሪያ ጊዜስ ስለሃሳቡ መቼ ሰሙ? የዚህን መልስ እያሰቡ ይከተሉኝ፡፡ 

የበጎ አድራጎት ሥራ ሰርቶ ስለማውራት ከአሁን በፊት ስለ ሶሻል ኢተርፕረነርሽፕ ያስተማሩን መስፍን ሰጣርጌ ሲናገሩ ማህበረሰባዊ ለውጥ አራማጆች ስለሠሩት መልካም ሥራ ይናገራሉ ብለውን ነበር፡፡ የዛሬው እንግዳችን ግን ትምህርት ለመስጠትና ለአርአያነት ካልሆነ በስተቀር አድርጌያለሁ ተብሎ አይወራም አሉን፡፡ እርስዎስ ምን ያስባሉ?

መልካምነት ልትገድለው የመጣችውን ትንኝ እስካለማጥቃት የሚደርስ ርህራሄን ሳይቀር እንደሚይዝ አስገንዝበውናል፡፡ ስለበጎፈቃደኝነት ስታስቡ ‹‹ሥራውን ስትሰሩ የሚያውቅላችሁ መዋቅር ያስፈልጋል››ም ብለውናል፡፡ ይህ እንግዲህ የበጎ አድራጎትን ሥራ በተደራጀ መልኩ የመሥራትን ሚና የሚያቅፍ ነው፡፡  ከበጎፈቃደኝነት የሚልቅ አልትሩይዝም (altruism) የሚል ጽንሰሐሳብንም አስተዋውቀውናል፡፡ እስኪ እሱንም እንዲመለከቱት ልጋብዝዎት፡፡ እርስዎ ግን በምን ዓይነት የበጎፈቃደኝነት ዘርፍ ተሰማርተዋል ወይስ ቢሰመሩ ያስደስትዎታል?  እንስሳትን በመንከባከብ፣ ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ በማድረግ፣ ታማሚዎችን በመጠየቅ ወይስ ሌላ?

ራስ ወዳድነትን በተለየ መንገድ እንድናየው ያደረገ ነገርም ጨመሩልን፡፡ በጎፈቃደኝነት ራስን ከማገልገል እንደሚጀምር፣ እንዳንኖር ከሚያደርጉኝ መታቀብ፤ በጤናማ እሳቤ ውስጥ ራስን ማኖርን፣ ከወደቀው እሻላለሁ ብሎ ማሰብንና ጉዳትም ቢያስከትል አገለግላለሁ የሚል እሳቤን እንደሚይዝ አነሱልን፡፡ ራሳችንን ካገለገልን በኋላ ለቤተሰብ የሚተርፍ አስተዋጽኦ ይኖረናል፡፡ ይህን በማድረግ ውስጥ እደሰታለሁ፡፡ በሃገሬ፣ ህዝቤ፣ በሃይማኖቴ በኩል አገለግላለሁ፡፡ ከምንም እሳቤ የበለጠ አስተዋጽኦም እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ ምንም ሳናደርግ ስንቀርና ንቁ ህሊናችን ሲሟገተን ለአእምሮ ህመም ሊዳርግ ይችላል፡፡ በጎፈቃደኝነት ከሱ ውድቀት ያድነናል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት የራሱ መርሆዎች ያሉትና ሰፊ መሆኑን ያስተማሩን መምህራችንን እያመሰገንን እርስዎም በሰፊው እንዲያነቡና በበጎፈቃደኝነት እንዲሰማሩ እጋብዛለሁ፡፡ ከማንም ምንም ሳንጠብቅ መልካም ሥራ ብናደርግና በመልካም ምግባር ብናገለገል ዓለምን የበለጠ ወደ መልካም ቦታነት እንቀይራታለን፡፡ ለበጎፈቃደኝነት ሥራ ፍላጎት ያላችሁ ብታናግሩኝ ሃሳቦችን ማጋራትና ሥራውንም መሥራት እንደምንችል በዚህ አጋጣሚ ላሳስብ፡፡  

 

 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...