2023 ኤፕሪል 28, ዓርብ

ጠባሴ ላይ እንደ አሜሪካ መስራት አትችልም

 ጠባሴ ላይ እንደ አሜሪካ መስራት አትችልም።


ትናንት ምሽት ወደ ቤት የገባሁት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሳይሞላ ነበር። በዕለቱ የነበሩኝን ሥራዎች የሠራሁበትን ሁኔታ ለማጤንና ለተመስጦ የተወሰኑ ደቂቃዎች ወስጄ ነበር። በእርግጥ ሁለት ክፍለጊዜ ከማስተማር በዘለለ የግል ሥራዬን ነበር የሠራራሁት። ሐሙስ እንደመሆኑ መጠነኛ የቤተመጻሕፍት ውይይትም ነበረች። ከተመስጦ በፊት ከሞባይሌና ከወረቀቶች ማስታወሻዎቼን ካየሁ በኋላ ወደ ኮምፒውተሬ ገለበጥኳቸው። ካደረ ስለሚዘነጋና የሐሳቡም መዘግየት ለተግባር ስለማያበቃው ነበር ይቺን በመልክ በመልኩ የማስቀመጥ ተግባር ያከናወንኩት። የመሰብሰብ ሥራ በየሚያስፈልገው ቦታ ተቀምጦ ለመደራጀትና ለመተግበር ካልበቃ ዋጋ የለውም ይል የለ ዴቪድ አለን። በእርግጥ በቀን ከሁለት ያላነሱ ገፆችን ወደ ኮምፒውተሬ አሰፍራለሁ። ይህን አሰልቺ የአሰራር አመል ምናልባት ቁራጭ ወረቀትና እስኪርቢቶ ከማይለየው አንድ ዘመዴ የወሰድኩት ይመስለኛል። ወደፊት እርግፍ አድርጌ ለመተው አስባለሁ። 

"ይህን ሁሉ የሐሳብ ክምር አንድ መላ ካልዘየድኩለት አስጨንቆ ሊገድለኝ ነው።" 

"ምን መላ አለው ብለህ ነው? ካልሞትክ አይተውህም!" 

"ሆሆይ! የስንት መጽሐፍ፣ ገጠመኝና ምልከታ ውጤት እኮ ነው። በቀላሉ መች እተወዋለሁ።"

"ትተወዋለህ። ያቺ ትንሿ ኮምፒውተር ስትበላሽ ይዛ እንደጠፋችው ፋይል።"

"ኧረ ተወኝ። አሁን ከዚያ ተምሬ ጉግል ድራይቭ ላይ አድርጌ የለም ወይ?" 

ሁለታችን ስንጨቃጨቅ ቆይተን የፌስቡክ አመል ውል አለችኝና ገባ ብዬ የዕለቱን ወሬ ቃርሜ ወጣሁ። 

ተመስጦ ለማድረግ በዚህ ዓመት መቸገሬን ባውቅም ገባሁበት። በቪዲዮ የተመራ እንዳላደርግ ኢንተርኔቱ ማታ ደካማ ነው። የአስር ደቂቃዋ ሰላሳ ደቂቃ ትወስዳለች። በዚያ ላይ የዩቱብ በየደቂቃው ማስታወቂያ መልቀቅ አሰልችቶኛል። ስለዚህ በራሴ የተወሰነ የትንፋሽና የማስታወስ ሥራ ሰርቼ በአንድ አፍታ ጨረስኩ።

ቤቱ በአጭር ዓመታት ማርጀቱ የለውጥን አስፈላጊነት አስታወሰኝ። ይህንና በርካታ የኑሮ ዘይቤ ለውጦችን ሳይቀር ነው በማስታወሻዬ የማሰፍረው። እንደገባሁ የሌሊት ልብስ ስለብስ ነበር ብርዱ የጀመረኝ። ስቶቭ ለኩሼ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እሳት መሞቅ ጀመርኩ። ሁልቀን ትዝ የሚለኝ የኢዮብ መኮንን "ተርቦ እሳት ይሞቃል" የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ። በፈቃዴ ያደረኩት መራብ አእምሮዬን ያሰላዋል። የፍላጎቶች መገደብ የሚያመጣውን ሁሉ እፈልገዋለሁ። ሰዓቴን ሳይ የክለብሐውስ የኦንላይን ቡክ ክለብ ውይይታችን መድረሱ ታወሰኝ። እዚያው እሳቱ ጋ ሆኜ መሳተፍን ፈለግሁ። በእርግጥ ማስታወሻ የያዝኩት በኮምፒውተሬ ነው። ኮምፒውተሩንም ኩሽና አምጥቼ ከፈትኩ። ኢርፎኔን ሞባይሌ ላይ ሰክቼ ውይይቱን ስከታተል አንድ ቅር የሚለኝ ነገር አለ። ይኸውም ተኩስ ቢሰማ አያሰማኝም የሚል ነው። "ቢሰማህስ ምን ልትሆን!" ይለኛል

አእምሮዬ። "ለጠቅላላ ዕውቀት ነው።" 

የዛሬው ውይይት ሰማኒያ በመቶ ሴቶች ያሉበት ነው። በእርግጥ ወደ ሴቶች የመጽሐፍ ውይይት ክበቦች እየተጋበዝኩ መግባት ጀማምሬያለሁ። ያው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ትዳር ስለማይገኝባቸው 12 መንገዶች ከፃፍኩ በኋላ ምከረኝ ባዩ በዝቷል። ለምክር ነው እንጂ እንደኔው ዕድሜ የተላለፋቸውን ሴቶች ለትዳር አልፈልጋቸውም። ምን አለፋችሁ! ውይይቱ ቀለጠ። መወያያው የፒተር ቲል "ዚሮ ቱ ዋን" ነበር። ከዚህ መጽሐፍ አንድ ሰው አዲስ ነገር መፍጠር ስለሚችልበት ሁኔታ ደራሲው ከኖረው ልምድ ለመገንዘብ ችለናል። የተለያዩ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን የመሰረተውና ባለ አክስዮን የሆነው ቲል የራሱ ሰራተኞች ከሱ በቀሰሙት ትምህርት ቢሊየነር የሆኑለት ነው። 

አወያይዋ በጽሑፍ እንዳወራ ጋበዘችና ፈቃደኛነቴን ስለገለጽኩላት ገባሁ። ሃሳቤም እንደሚከተለው ነበር። "እኔ ይህን መጽሐፍ ያነበብኩት እንደ አንድ ሥራ ፈጣሪና ነገን እየሠራ እንዳለ ሰው ነው። ከአስር ዓመቴ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን የሰራሁ ሲሆን አንድን እንግዳ ነገር ለመሞከር ወደኋላ አልልም። ፒተር ቲልም ሌሎች ካንተ ጋር የማይስማሙበትን ነገር ለይ ይለናል። ሰው ምን ይላል ብዬ ሳይሆን ይህን ሥራ ብሰራው ያስደስተኛል ወይ ከሚለው አንፃር ነው የማየው። የኔን ሕይወትና ገጠመኝ ሌላ ማንም ሰው ስላልኖረው የምሠራው ሥራ ማንም ከሚያስበው ዉጪ መሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። እስኪ እኔ ወሬ እንዳላበዛ አንድ ጥያቄ መልሱልኝ። የምዕራባውያን የስኬት መጻሕፍት ለእኛ አገር ይሰራሉ ብላችሁ ታስባላችሁ?"

አንደኛዋ ዉጪ ያለች ልጅ ስፔን መሰለኝ መናገር ጀመረኝ። የአማርኛዋ ሁኔታ ትግሬ ወይም ኤርትራዊ እንደሆነች ያስታውቃል። በእርግጥ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሙስሊም፣ የተለያዩ እንዳሉ ታዘሰቤያለሁ። "አርፍደህ ስለገባህ ነው እንጂ መጀመሪያ ላይ አዘጋጇን ሰላማን እየጠየቅናት ነበር። በኋላ ደግማ ልትነግርህ ትችላለች። የስኬት መጽሐፍ የማንበብ ፍላጎት ያለውም የሌለውም አለ። በተለይ ኢትዮጵያ ሆኖ ካለው አሠራርና የግንዛቤ ደረጃም አንፃር የምዕራቡን ሐሳብ እንዳለ ለመውሰድ ይከብዳል። የተለያዩ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት። ለምሳሌ ባህሉ፣ ኢኮኖሚው፣ ቢሮክራሲው አንድን ሐሳብ ወደ መሬት ላውርድ ስትል ተስፋ ሊያሰቆርጥህ ይችላል። ሌሎች እንደ ጽናት፣ ግብ ማውጣት፣ ጥረት የመሳሰሉት ሁሉም ጋ አሉ። በአካባቢህ ያለው የሥራ ባህል አለመኖር ለሥራ ላያነሳሳህ ስለሚችል እነዚህ መጻሕፍት የማነቃቃት ሥራ ይሰሩልሃል። ብቻ አመጣጥነህ መሄድ አለብህ።" በሐሳቧ ላይ ደጋፊም ነቃፊም ሐሳቦችን ሰምተን ለኔ የማሳረጊያ ዕድል ተሰጠኝ። ሥራን ለመፍጠር ፈጽሞ አዲስ ሥራ የሚለውን በተለይ ለቴክኖሎጂ የሚሆነውን እንደወደድኩት፣ ሌሎች የወሰዱትን ኮፒ የማድረጉን የቻይናን ዓይነቱን ተግባርም እንደየሁኔታው ልሞክረው እንደሚችል ገለጽኩ። አንድ ቦታ ጀምሬ ቀስበቀስ ማስፋፋትን፣ ጠቅልሎ የመያዝንና ብዙኃኑን በዚያ መጥቀሙን መውደዴን ተናገርኩ። ስለመጽሐፉ ስላየኋቸው ዳሰሳ ቪዲዮዎችና ጽሑፎችም አሳወቅሁ። ስላሉኝ ዕቅዶች አቅጣጫ ስናገር ሌሎቹም አብረው የመሥራት ፍላጎታቸውን ገለጹልኝ። ምህንድስና የተማረች ልጅ ከጀመረችው አዲስ ድርጅት ፈጠራ፣ የአእምሮ ንብረት ምዝገባ፣ የገንዘብና ኢንቬስተር አለመኖርን ከሲሊከን ቫሊ ጋር እያነፃፀረች አወጋች። ከተወያዮች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሆነ አዲስ ነገር የሚሞካክሩ መሆናቸው ውይይቱን አድምቆታል። የተለያዩ ድረገፆችንና ጠቃሚ አድራሻዎችን አየተላላክን ነው። ቡድናችን በመጽሐፍ፣ በንባብና በውይይት ላይ አንድ ድርጅት ቢመሰርት ጥሩ ነው በማለት ላነሣ ስል ዋይፋዩ ተቀበረጠና ከውይይቱ አስወጣኝ። ዛሬ ስለቀረው ውይይት ነግረውኛል። ስለሐሳቤም እያወራን ነው።

1 አስተያየት:

  1. ስላካፈልገን አመሰግናለሁ! ሃገራችን ላይ በተለይ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አዲስ ነገር ለመጀመር አይደልም፥ ነባር የሆኑ ነገሮችን እንኳ ለመቀጠል የደህንነት ስጋቱ ከባድ አድርጎታል። ይሄን ሁሉ ተጽዕኖ አልፈው መውጣት የቻሉትን በቂ ያድናቆት ቃላት የለኝም! በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ እየተንቀሳቀሱ ለመስራት እጅግ ፈታኝ ሆኗል። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ልሰራ ያሰብኩትን ለመጀመር ቤት ኪራይ እየከፈለኩ በጸጥታ ችግር ምክንያት ሁለቴ አክስሮኛል። ይሄ አመት ይለፍ እስኪ…በሚል ስጠብቅ 2 አመት አለፈ። ቀጣይ ላይ የተሻለ ከመጣ ለማየት ተስፋ አድርግያለሁ! በዚህ ሁኔታ የሚባክነው ጊዜ ቀላል አይደለም!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...