እንደ
አደራዳሪ ተፋላሚዎቹ በየኬላዎቻቸው ያሳለፉኝ ዕለት
የሳሲት
የጉዞ ማስታወሻዬ
በመዘምር
ግርማ
ማክሰኞ
ሕዳር 11፣ 2016 ዓ.ም.
ደብረ
ብርሃን
የሳምንቱ
መጨረሻ እንደ ወትሮው በርካታ ስራዎችን ስሰራ ያሳለፍኩበት ነበር፡፡ እሁድ ከሰዓት ከደብረብርሃን ስደተኞች ካምፕ ወደ ቤተመጻሕፍቴ
(ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት) የመጡ 20 የወለጋ ተፈናቃይ አማራ ሕጻናትን ከሌሎች ስድስት በጎ ፈቃደኞች ጋር የአማርኛና የእንግሊዝኛ
ፊደላትን አነባበብና አጻጻፍ ስናስተምር ቆየን፡፡ ምሽት 1፡00 አካባቢ እህቴ ከሰላድንጋይ ደወለችልኝ፡፡ ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ
‹‹ራት
በልተሃል?›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡
ራት መብላት ከተውኩ አራት ዓመት እየተጠጋኝ እንደሆነ ታውቀዋለች፡፡ ይኸውም በችግር ሳይሆን በቀን አንዴ መመገብን እንደ ግል የሕይወት
መርህ በመቀበሌ ነበር፡፡
‹‹በይ
ወደ መርዶሽ እህቴ!›› አልኩ በሆዴ፡፡ በተጉለት ባህል ማታ መርዶ የሚነገረው ራት ከተበላ በኋላ ነው፡፡ በዚህ የጦርነት ጊዜና
ቀጣና የትኛው ዘመዴ እንደሚሞት ለመገመት አልችልም፡፡ ከሞላ ጎደል መሳሪያ ያልታጠቀ ስለሌለ ሞትንም የዚያኑ ያህል መጠበቅ ግድ
ይለኛል፡፡
ለመጨረሻ
ጊዜ ወደ ሳሲት የሄድኩት በሰኔ ወር ከእንግዶች ጋር በሳሲት ለተከፈተችው አነስተኛ ቤተመጻሕፍታችን ድጋፍ ይዘን ነበር፡፡ ከዚያ
ወዲህ ጣርማበርና ሰላድንጋይ ላይ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ አሁንም ወረዳው በፋኖ ስር ነው፡፡ የጦርነት ቀጣና ሆኖ ወደቆየው ስፍራ መሄድ
እንደሚያስፈራ እገምታለሁ፡፡ በዚያ ላይ መቼ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ ስለማይታወቅ ያሰጋል፡፡ በእግሩ በብዛት በሚንቀሳቀስ ሰውና በመኪና
በሚሄድ ላይ የድሮን ጥቃት ሊኖር ይችላል፡፡ …
ሥልጣንን
ጠመንጃ፣ ዓለምአቀፉ ሁኔታ፣ አገርአቀፉ ክፍተትና ጊዜ ፈቅደውለት የተቆናጠጠው የወያኔ መንግሥት ሰላሳ ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ አንዴ
ከኤርትራ ጋር ከመዋጋቱ በቀር ከሞላ ጎደል በሰላም ኖረ፡፡ ሽብርተኝነትን ልዋጋ ብሎ ፈቅዶ በወዶዘማችነት ከመቅረቡ በቀር፣ ሰላም
ላስከብር ብሎ በየአፍሪካ አገሩ ከመዝመቱ በቀር፣ ወንዝ-አፈራሽ ሽፍቶችን ‹‹ይቺ ባቄላ ካደረች…›› ብሎ ሊያድን ከመሰማራቱ በቀር
ያላንዳች ጥይት ጩኸት ከፋፍሎ ገዝቷል ማለት ይቻላል፡፡ ዘመኑም እንደጥላ እምብዛም ሳይታወቅ እልፍ ብሎልን ይሆናል፡፡ አልፎ አልፎ
ምርጫ ሲመጣ ሰላም የሚደፈርስ ያስመስልበትና መልሶ የሚያረጋጋበትም አዚም ነበረው፡፡ ያም እሱ ፈቅዶና ሊቆጣጠረው በሚችለው ጨዋታ
የሚመጣ ድባብ ነበር፡፡ ወዳለፉት ጥቂት ዓመታት ስንመጣ በቅዠት አሳልፈናቸዋል ማለት ይቀላል፡፡ አምስት ዓመቱ ሃምሳ ዓመት መሰለኝ፡፡
ዕድሜዬም 82 ዓመት የሆነ መሰለኝ፡፡
ስለ
ሩዋንዳ የቱትሲ ዘር ጅምላ ጭፍጨፋ በ2008 ዓ.ም. ተርጉሜ ያሳተምኳትን መጽሐፍ ‹ሁቱትሲ›ን ይዘት የሚያስታውስ ይመስለኝና ደግሞ
ሌላ የሚያስብለኝ ቀውስ ውስጥ ከረምኩ፡፡ ‹‹የዩጎዝላቪያንም ተርጉምልን›› ይሉኛል፡፡ ‹‹የኩርዶችን ታሪክ ልንደግመው ነው›› ብለው
ይጽፉልኛል፡፡ ብቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
ከጠበቅሁት
ዉጪ በዕለት አደጋ አንድ የቅርብ ዘመዳችን ማረፉን እህቴ ነገረችኝ፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 ገደማ ሲሆን ሁለት መኪና ሞልተን ከተማዋን
ለቀን ወጣን፡፡ ደሴ መውጫ ያለው ኬላ ላይ የአካባቢው ሚሊሻ አባል የሚመስል የሚሊሻ የደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ መኪናው ገብቶ
ከቃኘ በኋላ ሁሉም ጋቢ፣ ነጠላ ወይም ጥቁር ሻሽ መልበሱን አይቶ ‹‹ሁሉም የኛው ነው›› ብሎ ሰላማዊ ፊት አሳይቶ ወረደ፡፡ መንገዳችንን
ቀጠልን፡፡ ዘመዳሞቹና የአገር ልጆቹ በአንድ ከተማም ብንኖር ስለማንገናኝ እናወጋ ጀመር፡፡ ከግል ወሬ ጎን ለጎን በአካባቢያችን
ስላለው ሁኔታም ይነሣል፡፡ መንቀሳቀስ ማሳቀቁን አልተደባበቅንም፡፡ ከቤቱ የወጣ በሰላም መግባት መቻሉን እርግጠኛ አለመሆኑን እናወራለን፡፡
ከደብረብርሃን ጥቂት ኪሎሜትሮች ተጉዘን በስተግራችን የባቄሎ ስደተኞች ካምፕ በሜዳው ተንጣሎ ታየን፡፡ አስታዋሽ የሌላቸው በሺዎች
የሚቆጠሩ ከወለጋ የተፈናቀሉ የዘር ፖለቲካ ሰለባዎች! ይህ ደብረብርሃን ካሉት ካምፖች በተጨማሪ ነው፡፡ የወያኔዎች አባት የስብሃት
ነጋ ‹‹አማሮችን መንዝ ላይ ጥለናችሁ ነው የምንሄደው›› ዛቻ ፍሬ አፍርቶ አየሁ፡፡ ምን ያላፈራው አለ!
ሃምሳ
ኪሎሜትር ተጉዘን ጣርማበር ደርሰን ወደ ሰላድንጋይ ታጥፈን መቶ ሜትር ያህል እንደሄድን የመከላከያ ኬላ ቆሞ አየን፡፡ የተሳፈርንበት
ቅጥቅጥ አይሱዙ ከሌሎች መኪናዎች ኋላ ተራውን ይዞ ቆመ፡፡ የኦሮምኛ ቅላጼ ባለው አማርኛ የሚናገር ወታደር ክላሽ በደረቱ በተጠንቀቅ
ይዞ ብቻውን ወደ መኪናው ገብቶ መታወቂያ አስወጥቶ አየት አየት አደረገ፡፡ ‹‹ሁሉም ሰላማዊ ሰው ነው? ምንም ጽንፈኛ የለም?››
ብሎ ትንሽ ፈገግታ ከተቸረው በኋላ ወረደ፡፡
ለተወሰኑ
ደቂቃዎች ከተጓዝን በኋላ ሌላ ኬላ ላይ ቆምን፡፡ ከፊታችን አንድ መኪና ቆሞ ይፈተሻል፡፡ የወትሮው የጻድቃኔ ማርያም ጸበለተኛ ግርግር
ስለሌላ ፍተሻው አያቆየንም፡፡ ይህኛው የፋኖ ኬላ ነው፡፡ ሲቪል የለበሱ ወጣቶች መታወቂያ አስወጡን፤ አየት አየት አደረጉ፡፡ አንዱ
ታጥቋል፤ ሌላኛው አልታጠቀም፡፡ ዉጪ ላይ የእነሱ አባላት የሚመስሉ ውሱን ወጣቶች ቆመዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ባለው መንገድ ወይ እንደ
ጸበለተኛ ‹‹አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ …›› አልተዘመረበት፣ ወይ ‹‹አንተ ጎዳና …›› አልተዘፈነበት በለቀስተኛ ቁዘማ ደብረምጥማቅ
ጻድቃኔ ማርያም ደረስን፡፡ አዲስ የተሰራው ቤተክርስቲያን በግዝፈቱ ወደር የለሽ ነው፡፡ ኮንግረስ ላይብረሪን አክሏል፡፡ አጼ ዘርዓያዕቆብ
ቢኖሩ አጠገቡ የእኛን ኮንግረስ ቤተመጻሕፍት ያሰሩልን የነበረ ይመስለኛል፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ‹‹ትውልድ አይደናገር …›› በሚለው
መጽሐፉ የኛን የኃይማኖት ተቋማት ከአውሮፓዎቹ ጋር እያነጻጸረ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ባለመቀየራቸው የተቸው ትዝ አለኝ፡፡ ጻድቃኔን
አልፈን ከወይዘሮ አትሞችሆኖ ከተማ ሰላድንጋይ ገባን፡፡ ከአሁን በፊት ወደ አንዲት ግራር፣ ማለትም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ወደተመሰረተባት ስፍራ
ለበዓል ስንሄድ በጻፍኩት የጉዞ ማስታወሻ ላይ የገለጽኩት የቅዱስ ማርቆስና የወይዘሮ ዘነበወርቅ ሰገነት በሁለት ትይዩ ተራሮች ላይ
ጎን ለጎን መቀመጥን አስመልክቼ የቤተመንግሥትና የቤተክርስቲያንን ተጠባብቆ ኑሮ ያሳያል ብዬ ነበር፡፡ አሁን በሰገነቱ ቦታ ሌላ
ቤተክርስቲያን ተሰርቶ አየሁ፡፡
ሰላድንጋይ
በፋኖ ቁጥጥር ስር ያለች ከተማ ነች፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ወያኔዎች ለዳግም ግዛት አዋጅ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የተገቱት
ከሰላድንጋይ ጥግ ያለው ሸለቆ ውስጥ ወይም ሞፈርዉኃ ጅረት ነው፡፡ ያኔ በርካታ ፋኖዎችና መከላከያዎች በአንድ ላይ ተሰልፈው መክተዋል፡፡
ወያኔ መንግሥት ሳለ በመንገድ ሥራ ስም መንዝ ላይ በቀበረው መድፍ በመጠቀም ሰላድንጋይን ደብድቧል፡፡ ዝርዝሩ የራሱ የማላውቀው
ሰፊ ታሪክ ስላለው ያዩና የተሳተፉበት ቢጽፉበት ጥሩ ነው፡፡ በወቅቱ ደብረብርሃን ሆኜ የጻፍኳቸውን ማስታወሻዎች ስብስብ በብሎጌ
‹‹በጦርነት ወላፈን ዳር›› ብዬ ለጥፌ ነበር፡፡ ለማንኛውም ሰላድንጋይን አንድም በተፋላሚው ጽናት አለያም ህዝቡ እንደሚለው በታቦቶቹ
ተዓምር ወያኔ ሳይረግጣት ተመልሷል፡፡ ያኔ አብረው የተሰለፉት ፋኖና መከላከያ በአሁኑ ወቅት እርስበርሳቸው እየተዋጉ ነው፡፡
ሰላድንጋይ
ላይ ተጨማሪ ለቀስተኞችን ጭነን ወደ ሳሲት ገሰገስን፡፡ ሳሲት እንደደረሰስን ቀጥታ ወደ ለቅሶው ቦታ ሄድን፡፡ ሰው ከየቦታው እየመጣ
ይቀላቀላል፡፡ በጾመኝነቴ የተነሳ ‹ሸንቃጦች› እያልኩ የማደንቃቸው ተጉለቶች ጉዳታቸው ታየኝ፡፡ አልቅሳ የምታስለቅስ አልቃሽ መሃል
ገብታ ታወርዳለች፡ በቅርብ ዓመታት በከሚሴ፣ በይፋት፣ በወሎ ወዘተ በጦርነት የሞቱትን ወጣቶች ስም እየጠቀሰች ዝም ያለውን አልቃሽ
ሐዘን እየቀሰቀሰች ታስለቅሳለች፡፡ ወደ ክቡ ተጠግቼ ሳያት በዕድሜ የገፋች ነች፡፡ በ2014ቱ ይመስለኛል የአርበኞች በዓል አከባበር
ሦስተኛውን መጽሐፌን ‹‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ››ን ወደ አንዲት ግራር በብዛት ይዤ ሄጄ ስለነበር በቦታው የተገኘው ወጣት ሁሉ ይዞ
ፎቶ ተነስቶ መርቆልኝ ነበር፡፡ ከነዚያ ውስጥ ዘመዴና ተማሪዬ አበበ አበባየሁ ይፋት በፋኖነት ወርዶ በአጭር ዕድሜው ተቀጨ፡፡ ወንድምገዛሁም እንዲሁ፡፡ ሳላስተምረውም አልቀር፡፡
ከበረውም እንዲሁ ይፋት ተጠቃች ተብሎ ሰው ሁሉ ወደ ደጋው ሲሸሽ እሱ ወርዶ ተቀጠፈ፡፡ የነሱም ስሞች ተነሱ፡፡
በለቅሶው
ቦታ ያየሁት የታጣቂ ቁጥር ለወትሮው ከማየው አይበልጥም፡፡ ምናልባት ሃያ ይሆኑ ይሆናል፡፡ አንድ የተለየ ነገር ግን አየሁ፡፡ ይኸውም
ከለቀስተኛው ውስጥ መሳሪያ ያልያዙ ‹‹Ethiopian Army›› የሚል የለበሱ አሉ፡፡ የአማርኛ አቻው ‹‹የኢትዮጵያ ጦር›› የሚለው
የለበትም፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙን ባለሙያ ቢያይ linguistic
landscape ይከበር ይላል፡፡ ሰዎቹ የውትድርና ልምድ ያላቸው
መሆናቸውን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ሌሎችንም የክልሉን የደንብ ልብሶችን የለበሱ ታጣቂዎችን አልፎ አልፎ አይቻለሁ፡፡ ብዙዎቹ ጠመንጃ
አልያዙም፡፡ ‹‹Ethiopian Army›› የሚል የለበሰ ሰው እኔና ሌሎች ከቆምንበት አቅራቢያ መጣና ከፊት ለፊቴ ጀርባውን ሰጥቶኝ
ቆመ፡፡ አቀባብሎ ወደ ሰማይ ሁለት ጥይት ተኮሰ፡፡ አንደኛዋ ቀለህ በጋቢዬ እጥፋት ውስጥ ገብታ አነሳኋት፡፡ ታቃጥላለች፡፡ ጥይት
ተኩስ ሲለማመድ ቀለሁ ተፈናጥሮ ጥርሱን የሰበረውን አንድን ሰው አስታወስኩ፡፡ ከሰሞኑም ወደ ሰማይ የተተኮሰ ጥይት ተመልሶ ሰው
ሊገድል ስለመቻሉ ከድረገጽ ያነበብኩት ጽሑፍም ትዝ አለኝ፡፡ በየድግሱ ለደስታ በሚተኮስ ጥይት ተመትተው ሞቱ ሲባል በፌስቡክና በዜና
የሰማኋቸውንም እንዲሁ፡፡ ሌላ የገረመኝ ለውጥ ግን ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በተጉለት በንግሥ ወይም በማህበራዊ ክስተት ላይ ጥይት
ሲተኮስ ካየሁ 25 ዓመት አልፎኛል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ለአስተርዕዮ ማርያም ንግሥ የተኮሱት አረጋዊው አርበኛና ታጣቂ ጋሽ ተጌ ነበሩ፡፡
እዚያው ንግሡ ላይ የኢህአዴግ ሰዎች ከበው ሲያዋክቧቸው አይቻለሁ፡፡ በዚያው ቀረ፡፡ ዱላ እንኳን ከገበያተኛ እየተሰበሰበ ይቃጠል
ነበር፡፡ አሁን ያ ለማህበራዊ ጉዳዮች ጥይት የመተኮስ ነገር ተመልሶ መምጣቱን አየሁ፡፡ ሌላ ሲቪል የለበሰ ግለሰብ እንደዚሁ ሁለት
ጥይት ወደ ሰማይ ተኮሰ፡፡ ጉዞ ወደ ቤተክርስቲያን፡፡
ከአንድ
ጥግ አያቴን ታፈሰችን አገኘኋትና ሰላም አልኳት፡፡ ሰውነቴ እንደ ገበሬ ሰውነት መሆኑን በአግራሞት ነገረችኝ፡፡ ስለምፆም ወይም
ምግብ ስለቀነስኩ መሆኑን ነገርኳት፡፡ ‹‹አይርብም እንዴ ታዲያ?›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ እንደማይርበኝና ፈቅጄ እንደማደርገው ነግሬ
አስገረምኳት፡፡ በዓመት አንዴ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ያለ ምግብ የምቆይበትን የ21ኛው ክፍለዘመን አካላዊ ጀብዱ እንዳልነግራት
እንዳትደነግጥ ፈርቼ ነው፡፡
ፍትሃት፣
ደረት ምት፣ ዋዬ ዋዬ መንገድ ላይ ሁለት ቦታ ቀጠለ፡፡ ከቤት ሳይለቅ እስከ ቤተክርስቲያን የደረሰውን ሰው ብዛት ሳይ በመጠኑም
ቢሆን የድሮን ጥቃት አሰጋኝ፡፡ የድሮን ቅኝቱ እንዳለና ተማሪዎችም በሱው ስጋት ከትምህርት ቤት እንደቀሩ ዛሬ ከነዋሪዎች ተረድቻለሁ፡፡
ቤተክርስቲያኑ ጋ እቤት ያልመጡ ለቀስተኞች ከየአቅጣጫው መጥተዋል፡፡
የሳሲቱን
ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትም አየሁት፡፡ ያሉትን ሁለት አነስተኛ ክፍሎች እያስተካከለ ለንባብ ዝግጁ በማድረግ ላይ ነው፡፡ በእድሳትና
ግንባታ ስራው ምክንያትም በውሰት ላይ አተኩረዋል፡፡ ኢንተርኔት ስለተቋረጠ ዋይፋዩን ፈልጎ የሚመጣ ተማሪ የለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት ቤቱ ትምህርት ስላልጀመረ አንባቢ መቀዛቀዙን ተረዳሁ፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው ብዬ አጽናናኋቸው፡፡
መኪናው
ላይ ልንሳፈር ስንል አንድ ወጣት ጠመንጃና ሸራ (ለመኝታው ይመስለኛል) ይዞ ሁለት እዚያው የሚኖሩ የሚያውቁት ወጣቶች አግኝተው
ሲያዋሩት እሰማለሁ፡፡ ወዴት እንደሚሄድ ሲጠይቁት ወደ ካምፕ መሆኑን ነገራቸው፡፡ አዲስ ምልምል መሆኑን መረዳታቸውን ከገለጻቸው
ሰማሁ፡፡ በሁኔታውና በመሳሪያው ተስበዋል፡፡ ለመግባት የፈሩም ይመስላሉ፡፡ የሰጡት አስተያየት ሁለቱንም የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹እጅን
በደረት አድርጎ ማየት አይሻልም?›› ሲሉት ሳይመልስላቸው ሄደ፡፡ ሊከራከራቸው የፈለገ አይመስልም፡፡
የአጃናዋን
ዘመዴን ወለተሰዕማትንና ልጇን ከቅሶ ሲመለሱ መኪና ውስጥ አገኘኋቸው፡፡ መኪናው ስለሞላ አጠገቤ ከሾፌሩ ጀርባ ካለው ሞተር ጫፍ
ላይ ተጨናንቃ ተቀመጠች፡፡ በ1994 ዓ.ም. አስረኛ ክፍል ጨርሼ ለሰኔ ሚካኤል ልጠይቃቸው ሄጄ ያደረኩትን ሁሉ አስታውሳ ታወራልኝ
ጀመር፡፡ ያኔ አሳዳጊ አክስቷና ለኛም ዘመዳችን አሸነፈችም ነበረች፡፡ እንደሞተችም ለለቅሶ ሄጃለሁ፡፡ አሸነፈች ዓይኗ የሩቁን ስለማያሳያት
ወንድሟና ቅድመአያታችን ሊሙ (ጅማ አቅራቢያ) የሚኖሩት ሻምበል ናደው አዲስ አበባ ወስደው አሳክመዋት መነጽር ስለተገዛላት በደንብ
ታያለች፡፡ ወለተሰማዕት ወጓን ቀጥላለች ‹‹ለእማማ የሰጠሃት የፀሎት መጽሐፏና መቀሷ አሁንም አሉ፡፡ እኔም ወርሻለሁ፡፡›› አለችኝ፡፡
መቀሷ መቼም የማትደንዝ ከቢክ እስኪርቢቶ ከፍ ያለችና ጥቁር እንደሆነች አስታወስኩ፡፡ እስከዛሬ የቤተሰቡን ጸጉር በማስተካከል ታገለግላለች
ማለት ነው፡፡ የፀሎት መጽሐፏን ግን እረስቻታለሁ፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት ለንግሥ ሄጄ የሰጠኋቸው አሁንም መኖሩ ገረመኝ፡፡ ምንም
የሌለኝ ተማሪ ነበርኩ፡፡ አሁንስ? ምንም የሌለኝ መምህር!
‹‹አሁን
ምን ያስፈልጋችኋል? ምን ልላክላችሁ?›› ስላት፤
‹‹መጥተህ እየን›› አለችኝ፡፡
‹‹አይሞላልኝማ!››
‹‹ከነገ
ወዲያ የሕዳር ሚካኤል ነው፡፡ እሱም ሊያልፍህ ነው፡፡ ለመቼው ሚካኤል ነው የምትመጣው?››
በእርግጠኝነት
ለመናገር አልቻልኩም፡፡
አራቱም
የፊት ጥርሶቿ የሉም፡፡
አሳዘነችኝ!
አጃና
ሚካኤል ስትሄዱ ጠይቋት፡፡ የኔን ስም ከጠራችሁ ተጋብዛችሁ ትመለሳላችሁ፡፡
ስንመለስ
ጣርማበር 12፡00 ሳይሞላ ለመድረስ መኪናችን ገሰገሰ፡፡ ከዚህ ሰዓት ከዘገየ እዚያው ብርድ ላይ ያሳድሩናል ተባለ፡፡ የፋኖው ኬላ
ጋ ስንደርስ እንደጠዋቱ አሉ፡፡ አሳለፉን፡፡ ለብርዱ ሸማቸውንና ሽርጣቸውን ለብሰው በተንተን ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ገባ ብለው አይተው
አሳለፉን፡፡ የመከላከያውም ጋ በሰዓቱ ደርሰን እንዲሁ አሳለፈን፡፡ ወደ ደብረብርሃን ስንቃረብም የፌደራል ፖሊስ መለያ ልብስ የለበሰ
ወታደር ከለቅሶ መምጣታችንን ስንነግረው ‹‹ቤተክርስቲያን ሳሚ እየመሰሉ ይመጣሉ፡፡ ስለምንይዝ ነው፡፡›› ብሎ መታወቂያ ወጣ ወጣ
እንድናደርግ ጠይቆ አሳለፈን፡፡ በሰላም ተመለስን! ነገ ምን እንደሚመጣ አናውቅም፡፡