2023 ኖቬምበር 28, ማክሰኞ

ቅኝት (የጉዞ ማስታወሻ)

ቅኝት (የጉዞ ማስታወሻ)

በዶክተር ሰላማዊት ታደሰ

የታተመበት ዘመን - 2016 ዓ.ም.

የገጽ ብዛት - 176

ዋጋ - 350 ብር

 

ዳሰሳ - በመዘምር ግርማ (mezemirgirma@gmail.com)

ደራሲዋ ስለ አሜሪካ ቆይታዋ ለሰው ስታወራ መጽሐፍ እንደሚወጣው በተሰጣት አስተያየት መሰረት ወደ ስድስት ቦታዎች ያደረገቻቸውን ጉዞዎች ማለትም ሦስት የዉጪና ሦስት የአገር ውስጥ ጉዞዎቿን አስመልክታ የጻፈችው ማስታወሻ የየአገሩን ልዩነት ለማሰላሰልና በምናብ ለመጓዝ የሚጋብዝ ነው፡፡

ሙያቸው በአማርኛ እንዲጽፉ የማያበረታታቸው ባለሙያዎች ለህዝቡ ይደርስ ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ  የሚያቀርቡት ጽሑፍ  ይወደድላቸው እንደሆነ ከሚገቡበት ጭንቀት የተነሳ የብዙዎችን እገዛ መጠየቃቸው እንደማይቀር እሙን ነው፡፡ በጽሑፍ እንደገለጸችው በአስተያየትና በአርትዖት ያገዟት ሰዎች አስተዋጽኦ ታክሎበት ጭምር ይመስላል የመጽሐፉ ሐሳብና ፍሰት አንባቢን የመያዝ አቅም ከፍተኛ ነው፡፡

ፀሐፊዋ በመጽሐፉ መክፈቻ ገጾች ጉዞን አስመልክቶ ባላት ፍልስፍና ላይ ያጋራችን ሃሳቦች ከልጅነት እስከ እውቀት ስለመኖሪያ ቦታዎቻችንና ስለምንጎበኛቸው ስፍራዎች የሚኖሩንን ምልከታዎች ከየት እንደምናመጣቸው የሚያሳስበን ነው፡፡ በልጅነቷ የአገሯን የተለያዩ ቦታዎች ለመጎብኘት ትፈልግ እንዳልነበር ሁሉ  በስተኋላ ወደ ክፍለሐገር ሄዳ ከአዲስ አበባ መለየቷ መጥፎ ስሜት ውስጥ እንደከተታት እንረዳለን፡፡ በደንብ ብታስብበትና ሰው ብትጠይቅ ኖሮ የክፍለሃገር ቆይታዋን በደስታ ልታሳልፍ ትችል ይሆናል፡፡ ስለተለያዩ ያለፉ ድርጊቶቻቸውና አስተሳሰባቸው ሲጠየቁ እንደዚያ ማድረግ እችል እንደነበር አላውቅም ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ደራሲዋን ይህ ይገልጻት ይሆን?

ቀደም ብላ ለትምህርት፣ ለትምህርታዊ ጉዞና ለሥራ የተለያዩ የአገሯን ስፍራዎች ብትጎበኝም የዚህ ማስታወሻዋ ትኩረት በነዚያ ላይ አይደለም፡፡ ምናልባት ከዉጪ ጉዞዎቿ በኋላ ዘርዘር ያለ ማስታወሻ መያዝ ጀምራ እንዲሁም ባዳበረችው ነገሮችን በተለየ መልክ የማየት ችሎታ ያየቻቸውን ቦታዎች በዝርዝር በመጽሐፏ ታስቃኘናለች፡፡

ከ176ቱ ገጽ 96ቱ ስለ አሜሪካ መሆኑን ለመታዘብ ይቻላል፡፡ ይኸውም ምናልባት ከአሜሪካ ስፋት፣ ካየቻቸው አዳዲስ ነገሮችና ሰዎች ብዛት፣ ካገጠሟት አስገራሚ ሁኔታዎች ወይም ካስተዋለችው ተቃርኖ የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡ የአሜሪካ ዕይታችን በአገራችን ሁለንተናዊ ቅኝትና በዜጎቻችን አስተሳሰብ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በማየት ግንዛቤ ለመፍጠርም ይሆናል ይህን ያደረገችው፡፡ የአሜሪካ ቆይታቸውን አስመልክቶ ሙሉ መጽሐፍ የጻፉ/ያስጻፉ እንደ ሙሉጌታ ኢተፋ (ዘ ቢተር ሃኒ) እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዓይነቶቹ ደራስያን ሲታሰቡ የሷም የአሜሪካ ወግ በዛ አያስብልም፡፡ አሜሪካን አስመልክቶ የገጠማትንና ያስተዋለችውን በማስታወሻዬ ለመያዝ ሞክሬ ስለበዛብኝ በመጽሐፉ ላይ ምልክት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ብዙው ሃሳብ በማስታወሻ መያዝ የሚችልና የሚወድቅ የሌለው ነው፡፡ የማስተዋልና የመግለጽ አቅሟም ከፍተኛ ነው፡፡ የተወሰነውን ለመጥቀስ ያህል የኤምባሲው እንግልት፣ ያገኘቻቸው ተጓዦች ታሪክና ስብጥር፣ የተለያዩ የእንግሊዝኛ ቅላጼዎች የፈጠሩባት ግርታ፣ የሰዎች ትብብርና የራሷ ጥንቃቄ ከአትላንታ አደጋዎችና ወሮበላዎች እንዴት እንዳዳናት፣ የሌላ ዘር ሰዎችን ዕድሜ አሳስቶ መገመት፣ የተለያዩ የአሜሪካ በሽተኞች ጉስቁልና፣ የዘርሽ ምንድነው ጥያቄ፣ አገር አለኝ የማለት ኩራት፣ በሞባይል የሚጠቀሙት የጉግል አቅጣጫ መጠቆሚያ ጠቀሜታ፣ በኢንተርኔት ምን የት እንደሚገኝ ማወቅ መቻሉ፣  አዲስ ለሚገባ ያለው የባንክና ስልክ ጣጣ፣ የአዲስ አበባን ሰው ተባባሪነት እዚያ ሄዳ  ወደ ማሽንነት የተቀየሩ የማይተባበሩ ሰዎችን አይታ መረዳቷን ወዘተ.፡፡ ከህክምና ስራዋ ጋር በተያየዘ ለስልጠና ወደ አንድ ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲ የሄደችው ዶክተሯ በተንቀሳቀሰችባቸው የአየር ማረፊያዎችና አውሮፕላኖች የገጠሟትን ሁኔታዎች አስቃኝታናለች፡፡ የሰው ልጅ ማሽተት ባይችልም ማሽተት የሚችለውን ዉሻን ባሪያ አድርጎ በግ በሚያካክሉ ዉሾች የሚያደርገወውን የአደንዛዥ ዕፅ ክትትል መግለጽ ይቻላል፡፡  

በአሜሪካ የተለያዩ ስቴቶች ስላሉ አንዱ ካንዱ የሚለይበትን ካየችውና ከሰማችው ከትባልናለች፡፡ ቆይታዋን በሚገባ አቅዳ ተጠቅማበታለች፡፡ አብረዋት የተማሩና የምታውቃቸውን ሰዎች ጠይቃለች፤ የሚጎበኙ ቦታዎችን ጎብኝታለች፤ በገበያ አዳራሾች ገብይታለች፤ በተለያዩ መጓጓዣዎች ተጓጉዛለች፡፡

ተጨማሪ አትኩሮትን የሚስቡ እንደ ምግብ፣ አሜሪካውያን ለአሜሪካ ያላቸው አስተያየት፣ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበት የቲቢ ምርመራ፣ በረዶ፣ ኡበር፣ የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቶች፣ ስሙር መንገዶችና የከተማ ዕቅድ፣ ግለኝነት፣ ኢሉሚናቲ፣ የልጆች አስተዳደግ ፈተና፣ ዘረኝነት፣ የዲያስፖራ ክፍፍል፣ ሂላሪና ትራምፕ ላይ ያሉ አስተያየቶች፣ በየቦታው ያለ በነጻ የሚጠጣ ውኃ፣ የአሜሪካ አየገር ውስጥ በረራዎች፣ ሆሊውድ፣ ግብረሰዶማውያን ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡  በንባቤ መካከል ብዙ ቦታ ቆም እያልኩ አስቤያሁ፡፡ ለምሳሌ ግንኙነቶች ለምን በኢሜል ሆኑ? ብዬ ጠይቄያለሁ፡፡ ምቹ ስለሆኑ ወይንስ ለሌላ ዓላማ?

‹‹የዉጪ ቋንቋ የማያውቅ የራሱንም አያውቀውም›› እንዲል ዮሀን ቮልፍጋንግ ጌተ የውጪ አገርን የማያውቅ ሰው የራሱን አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ የአሜሪካው ምልከታዋ የአገሯን ሁኔታ ለማጤን እንደጠቀማት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እኛስ ምን ያህል ተጉዘናል? ወደፊትስ ለመጓዝ ያለን ፍላጎት ምን ያህል ነው?

ስለ ጣሊያን ያላትን መልካም ያልሆነ አመለካከት የቀየረው የጣሊያን ጉዞዋ ከአሜሪካው አጠር ያለ ሲሆን እሱና ከሱ በኋላ ያለው ጽሑፍ ፍሰት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ጽሑፍ መስሎኛል፡፡ ያየችውንና የታዘበችውን ነገር ቁጭ ቁጭ ያደረገችበት ነው፡፡ ለፍሰትና የአንባቢን ስሜት ለመያዝ እንደ አሜሪካው ብዙ አልተጣረበት ይሆናል፡፡ የመጽሐፉ ከግማሽ በላይ ያለ ክፍልም ስለሆነ መላልሶ ለማየት እርሷም ሆነች አርታእያን በደከሙበት ሰዓት የሚያገኙት ሆኖ ይሆናል፡፡ የቋንቋ ችግር የሚፈጥርባትን ግርታ፣ የሰዎቹ ትብብርና መልካምነት፣ የወረራው መጠነኛ ተጽዕኖ፣ የምግባቸው ጣዕም፣ ከአሜሪካ የሚለይ ማህበረሰብ በአጭሩ ቀርበውበታል፡፡

ዱባይ በኢትዮጵያውያን የሚዘወተርና ስደተኞች የሚበዙበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዱባይ ጉዞዋም ዘመድ ጋ ቆይታ ያየችውን አስቃኝታናለች፡፡ የዱባይን ልማትና ለውጥ ታስቃኘናለች፡፡ በዱባይ የኢትዮጵያውያንን አኗኗር፣ የስደትን ኑሮ፣ የሄደችበትን ኤግዚቢሽን ሁኔታ ጨምሮ ሌሎችን አዳዲስ ጉዳዮች በፓቶሎጂስቷ ዕይታ እናያለን፡፡

በሦስት ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ የሕክምና ትምህርት ቤቶች የሚማሩ የሕክምና ተማሪዎችን ለመፈተን በሄደችባቸው ጊዜያት ያየቻቸውንና የታዘበቻቸውን ያሰፈረችበት የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ደብረብርሃን፣ ደሴንና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎችን ከነከተሞቻቸው ያስቃኘናል፡፡ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን በበጎ ስታነሳው የምንሰራበት ሰዎች ከምናየው የተለየ ስለሆነ ገርሞናል፡፡ ልቀጠር ብላ ያቀረበችው ጥያቄም ቢሳካላት ጥሩ ነበር፡፡ ከተማውም ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሰለብኝ ትላለች፡፡ ደሴ ዩኒቨርሲቲና ከተማንም ኮምቦልቻን ጨምሮ አስቃኝታናለች፡፡ የዩኒቨርሲቲው የፈተና ዝግጅት የማስተባበር ድክመት ላይ ግንዛቤ ጨብጫለሁ፡፡ የዘውግ ፖለቲካን ፍሬ አስመልክቶ ከመቀሌ ከመጣ መምህር ጋር ያደረገችው ወግም ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ጎንደርን በእንግዳ ተቀባይነቱ አመስግናለች፡፡ ህዝቡም ለዩኒቨርሲቲውና ለሐኪሞች ያለውን ፍቅር አድንቃለች፡፡     

በመጨረሻም መጽሐፉ ወደ እንግሊዝኛ ቢተረጎም፣ በቃለመጠይቅ ለህዝቡ ሃሳቧን ብታቀርብ ወይም ሌላ የተደራሽነት መንገድ ቢፈለግ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደኔ ሁሉ ሌሎች እሷ ያየችውን እንዲረዱት ነው፡፡ ከእርሷ የበለጠ ዉጪ የመኖርና የመጓዝ ዕድል ያገኙ ብሎም በአገር ውስጥ የመጓጓዝ አጋጣሚዎች የነበሯቸው ሰዎች እንዲጽፉ የሚያነሣሣና የሚያሳስብ መጽሐፍ ይመስለኛል፡፡ ዶክተር ሰላማዊትም ብትሆን በሌሎች በተረጋጉ አጋጣሚዎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች ብትሄድ ሌሎች ሰፋፊ ትረካዎችን እንደምታስነብበን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...