2024 ሴፕቴምበር 16, ሰኞ

ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች

 

ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች

መዘምር ግርማ

መስከረም 7፣ 2017 ዓ.ም.

ደብረብርሃን

 

ልመና

ዛሬ አንድ አረጋዊ ቤተመጻሕፍት መጥተው በር ላይ ቆሙ፡፡ እኔም እንደተለመደው ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልን›› አልኳቸው፡፡ እርሳቸው ግን ‹‹ሎሚ ትገዛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ አስከተሉ፡፡ ከየት የመጣ ሎሚ እንደሆነ ስጠይቃቸው ከእነዋሪ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ትልልቅ ሎሚ ሲሆን፤ ዋጋው ደግሞ ሦስቱ አስር ብር ነው፡፡ ገዛኋቸው፡፡ ዋጋው በከተማችን ከሚሸጥበት በሦስት እጥፍ የተሻለ ነው፡፡ በጣም የሚበረታታ ስራ መሆኑን ገለጽኩላቸው፡፡ ስለ እርሳቸው ስጠይቃቸው ከወሊሶ አካባቢ ተፈናቅለው የመጡና የእነዋሪ አካባቢ ተወላጅ መሆናቸውን ገለጹልኝ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኘውንና የሚያውቁትን ምርት ይዘው መምጣታቸው መልካም ተግባር ነው፡፡ እኔም ይህን ገልጬ አመሰገንኳቸው፡፡ ሌላ ቀንም እንዲመጡ አሳሰብኳቸው፡፡ ወደ ጎረቤት ሄጄ ሎሚ እንደገዙ ስጠይቅ መግዛታቸውንና መጀመሪያ ሲያዩዋቸው እንደኔው  ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልን›› ማለታቸውን ገለጹልኝ፡፡ከሎሚውም መግዛታቸውን ነገሩኝ፡፡ እኝህ አዛውንት አንድ ሰው አቅመ-ደካማ እና ተፈናቃይ ከሆነ ምጽዋት መጠየቅ አለበት የሚለውን አስተሳሰብ የሰበሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ እንደ እርሳቸው ያሉ ሰርተው መኖር የሚፈልጉ፣ ያንን የመስራት ዕድል ግን ያጡ በርካቶች ይኖራሉ፡፡ የሚሰሩትን ስራ አለማወቅ፣ ለአካባቢው እንግዳ መሆን፣ መነሻ ገንዘብ አለማግኘት ወዘተ ከስራ አርቋቸው ይሆናል፡፡ እኝህ አዛውንት ግን በእኛም ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ አጋልጠዋል፡፡ ይቅርታ ሳልላቸው ስለሄዱብኝም አዝናለሁ፡፡

 

ጨለምተኝነት

ጥናት ባናደርግም ብዙዎች በዚህ ወቅት የሚያስቡት ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ጎጂ የሆኑ ሃሳቦችን ነው፡፡ በየስፍራው ስንሄድ የምናገኘው እሱ መስራት ስለሚችለው ሳይሆን ሌሎች መስራት ኖሮባቸው ስላልሰሩት ጉዳይ ነው፡፡ ስራ ከያዝኩ ወዲህ ባሉት ዓመታ ይህን በሰፊው አይቻለሁ፡፡ እኔ በመስሪያ ቤት፣ በከተማ፣ በኢንተርኔት ወዘተ የማገኛቸው ሰዎች በአመዛኙ ጨለምተኛ ነገር እንጂ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አይናገሩም፡፡ ወይንም የገጠሙኝ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹ ይበዛሉ፡፡ ይህን መንገድ ትተው መስራት ስለሚችሉት፣ ማሰብ ስለሚችሉት፣ መፍጠር ስለሚችሉት ወዘተ የሚያስቡ፣ የሚመክሩና የሚጠይቁ ውሱን ሰዎችንም ግን አይቻለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ብዙኃኑ እንዳደረገው ሁሉ የሚያደርጉ ሳይሆኑ እኔስ ምን ላድርግ የሚሉ ናቸው፡፡ ለአገርም ሆነ ለራሳቸው የሚጠቅመው ይህ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ ብዙኃኑን ከወሰደው ማዕበል ያልተወሰዱ ሰዎችን አይተዋል? በምን ሁኔታ ውስጥ?  

 

2024 ኦገስት 29, ሐሙስ

ከኮርያውያን ጋዜጠኞች ጋር

ወደዚህ የሚመጡበት ጉዳይ ነበራቸው። አብሯቸው የመጣው ወዳጄ ደብረብርሃን እንዳለሁ ስለተረዳ ሻይ ቡና እንበል አለኝና አገኘኋቸው። ኮሪያውያን ናቸው። ደቡብ ወይስ ሰሜን የሚል ጥያቄ ስጠይቃቸው "ደቡብ" ያሉት በኩራትና ሰሜንን በመጠየፍ ዓይነት ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንግሊዝኛ ዲፓርትመንት አብረውን የተማሩት ወጣቶቹ እነ ኦቾልሚን ግን ይህን ጥያቄ ሲጠየቁ "አንድ ኮሪያ" ይሉ ነበር። እነዚህ ምናልባት አዋቂዎች ስለሆኑ፣ ሥራ ስለያዙ፣ እርስበርሳቸው ስለሚጠራጠሩ ይመስለኛል ሰሜን የሚለውን እንደማይወዱት ለማሳየት ይሞክራሉ። ወይም ያስመስሉ ይሆናል። የክፍል ጓደኞቼን ምላሽ አስታውሼ ምናልባት ወደፊት አንድ አገር ትሆኑ ይሆናል አልኳቸው። አንደኛው እንደማይሆኑ ነገረኝ። 

"ይሁኑ ቢባል እንኳን የሐብት ልዩነቱ እጅግ ተራርቋል" ሲል ሞገተኝ።

"ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን አንድ ሆነው የለም!" አልኩት። 

"ከምስራቅ ጀርመን በጣም የራቀ ኋላቀርነት ላይ ናቸው እነዚህ" አለኝ።

ይሁን ብዬ ጨዋታውን ባጭር ቀጨሁት። ብገፋበት ይህን የተስፋፊነት አባዜህን አቁምልኝ የሚለኝ መሰለኝ።

ከኮሪያ ወደ አፍሪካ ብቸኛው አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ ገልፀውልኝ ሞዛምቢክን መጎብኘትን የሚጨምረው ጉዟቸው በአንድ ሰው የደርሶ መልስ ሦስት ሺህ ዶላር እንደከፈሉ ነገሩኝ። ከአዲስ አበባ ወደ ኮሪያ ደርሶመልስ ከአየር መንገዱ ሳጣራ 200,000 ብር ገደማ ይላል። ከኮሪያ ወደ አፍሪካ ካለው እርቀት ጋር ተመሳሳይ እርቀት ወዳለው ወደ አውሮፓ መጓዝ ግን አማራጭ ስላለ በጣም እንደሚቀንስ ነገሩኝ። አማራ ክልል ወይም ደብረብርሃን ላይ የእስያ ሰው ነጋዴና ኢንቬስተር ስለሚመስል ጋዜጠኛ ናቸው ብሎ ማንም አያስብም። ቢያስብም ችግር የለባቸውም። የካሜራና መቅረፀድምፅ ጋጋታ የለባቸውም። አንዲት የፂም መላጫ የምታክል ቪዲዮ ካሜራ ነች የያዙት። የአዲስ አበባዎቹን የዉጪ ሬዲዮ ሪፖርተሮች እንኳን ብታዩ ትልቅ ማይክ ከኮታቸው ኪስ ጎስረው ሲሄዱ ጋዜጠኞች መሆናቸው ያስታውቃል። የዘመኑ ቴክኖሎጂ መራቀቅና የካሜራቸው ማነስ እኔንም ወዳጄንም አስገርሞናል። እነዚህ ሰዎች ለሁለት ለጉዞ እንኳን 6000 ዶላር ከፍለው፣ በዚያ ላይ ለሆቴል፣ ለአበል፣ ለመኪና ኮንትራት ስንት እንደሚከፍሉ አሰብኩት። ከኮሪያ ጋግነም ስታይልን እንደምወደው ነገርኳቸው። 5.2 ቢሊዮን ጊዜ በዩቱብ የታየ ሙዚቃ ሲሆን ዘፋኙ Psy ይባላል። ሌላ ጀንትልሜን የሚል ቪዲዮውን አሳዩኝ። ለጋግነም ስታይል የተሠራውን ሐውልት አሳዩኝ።  ከዚህ ጽሑፍ ጋር አያይዤዋለሁ። ደቡብ ኮሪያውያን የክርስትና እምነትን መቀበላቸውን የሚያሳብቁ ነገሮች አሏቸው። አንደኛውን ከነዚህ ሰዎች አየሁ። ልብሳቸው 'Press' ከሚል የተለመደ የሚዲያ ሰዎች ልብስ ይልቅ 'World Vision' የሚል መሆኑ አስገርሞኛል። ጥያቄ አልጠየኳቸውም። ደብረብርሃን ወደሚገኘው ሰሜን ኮሪያ አረቄ ቤት ወዳጄ በመኪናው ወሰደንና በደጁ አለፍን። ምክንያቱም ደቡብ ኮሪያውያኑ ለመግባት አልፈለጉም። ፍርሃታቸው አይጣል ነው። ሰሜን ኮሪያ እንዴት አስቸጋሪ አገር እንደሆነች አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ወደዚያ ተጉዞ ሪፖርተር ላይ የጻፈው ማስታወሻ ስላለ እዩት። 

ከብዙ በጥቂቱ ይኸው ነው።



2024 ጁላይ 10, ረቡዕ

የዕለት ውሎዬ፣ የዓመቱ አከራረሜና የትውልዱ ዕጣፈንታ

 የዕለት ውሎዬ፣ የዓመቱ አከራረሜና የትውልዱ ዕጣፈንታ

መዘምር ግርማ

ማክሰኞ ሐምሌ 2፣ 2016 ዓ.ም. 

ደብረብርሃን 



ዛሬ ከደብረብርሃን ወደ ባቄሎ መስመር ሄጄ ነበር። ልጆች ከደብረብርሃን ወደ ባቄሎ አስር ኪሎሜትር በእግራቸው ሲጓዙ አገኘኋቸው። አንደኛው የቤተመጻሕፍት ወዳጆቼ  ያሰፉለትን ዩኒፎርም ለብሶ ወደ ባቄሎ ሲመለስ በርዮ ላይ አገኘሁት። ከሁለት ሌሎች ልጆች ጋር ነው። ወደ ደብረብርሃን የሄዱት ቁራሌ ለመስራት መሆኑን፣ ማለትም የዉኃ መያዣ ላስቲክ ለቅመው ለመሸጥ ቢሆንም ስላላገኙ በእግራቸው እንደሄዱ በእግራቸው እየተመለሱ መሆኑን ነገሩኝ። ተሰናብቻቸው ሲሄዱ ጠርቼ ስኳር ድንች ገዛሁላቸው። ምናልባት መሳፈሪያ ብሰጣቸው ይሻል ነበር። ደብረብርሃን ቶሎ መመለስ ያለብኝ አንድ ወዳጄ የቲያትር መጽሐፍ ፈልጎ ጠርቶኝ ነው። ተመልሼ ቤተመጻሕፍት ገብቼ ሳዋራው ሁለት ተፈናቃዮች ልጆች ገቡ። ሰሌዳውን አጽድተው መጻፍ ጀመሩ። ከግማሽ ሰዓት ገደማ ቆይታ በኋላ ወዳጄ ወደ ቤቱ ሲሄድ አንደኛው ልጅ የሳለውን ስዕል አየሁ። የወንድና ሴት ሥዕል ነው። ምናልባት የቤተሰብን አብሮነት የሚያሳይ ይሆን? እናትዮዋ ጥላ አጥልታ ያሳያል። ምናልባት አባቱ ወለጋ ሰው ሲገደል አይቶ አእምሮውን እየታመመ በመድኃኒት እገዛ ስለሚኖር እናትዮዋ የቤቱ ምሰሶ መሆኗን ለመግለጽ ይሆን? በአራት ዓመቱ እየታዘለ የሚኖረውን የአእምሮ ዕድገት ዝግመት ያለበትን ወንድሙን፣ ያለ ዕድሜዋ የተዳረችውን እህቱን ችግር ተሸክማ የምትኖረውን እናቱን ጥንካሬ ለማሳየት ይሆናል። እሱ ግን ወደ ባቄሎ ካምፕ እምብዛም አይሄድም። ምናልባት በደብረብርሃን የጎዳና ተዳዳሪ የመሆን ዕጣፈንታ ይጠብቀው ይሆናል። በበጋው የቤተመጻሕፍታችን የትምህርትና ምገባ ዝግጅት የትምህርት ጊዜ ሲሆን መምጣትን የሚጠላ፣ ትምህርትንም ጭምር የሚጠላ የሚመስል ልጅ ነው። እኔ ብዙውን ጊዜ ቤተመጻሕፍት ተፈናቃዮች ልጆችን በማስተማር ብቻዬን ከመሥራቴና ከሃምሳ በላይ ልጆችን ከማስተናገዴ አንፃር የተለየ እገዛ ወይም ትኩረት ለሚፈልጉ ልጆች ጊዜና ትኩረት አልሰጥም። ትኩረቴ ብዙኃኑ ላይ ነው። የሚያጠፉትንም እቆጣለሁ። ሲብስም ቤተመጻሕፍቱንም ለቀው እንዲሄዱ አደርጋለሁ። አንድ ቀን አንድ ከዚያን ቀን በፊት አይቼው የማላውቀውን ልጅ ከሌሎች ልጆች ጋር ምግብ በትሪ እንዲመገብ ካንዱ ጠረጴዛ አስቀመጥኩት። አልተስማማውም መሰለኝ አለቀሰ። ወደ ሌላም ቡድን ቀየርኩት። አለቀሰ። በል ካልተስማማህ ውጣ ብዬ ወደ ዉጪ አስወጣሁት። ደግነቱ ሁለት በጎፈቃደኞች (ፅዮንና ታምሬ) ዉጪ ስለነበሩ አባብለው አምጥተው ለብቻው በሳህን ተሰጥቶት በላ። በኋላም ደስ ብሎት ሄደ። ችግሩን አናውቅም። ለመጠየቅም ጊዜ የለንም። ምናልባት ወላጅ አልባ ይሆን? ከቤቱ ዉጪ በልቶ አያውቅ ይሆን? ከዚያ ቡድን የተጣላው ልጅ ይኖር ይሆን? 

ወደቀደመው ልጅ ስመለስ ትምህርት ሳትማር ለምሳ ለምሳ የምትመጣ ከሆነ እንዳትመጣ ብዬ ነግሬው ነበር። ሌሎችም እኔም በጎፈቃደኞቹም ተው ያልነው ጥፋቶች አሉበት። ሳልረዳ ወይም እሱ ሳያስረዳኝ ውሳኔ ላይ ደርሼ ይሆናል። በወቅቱ ያን ያልኩት ለሱ በማሰብ ቢሆንም ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል። የበጋው ዝግጅት ሊያልቅ አንድ ቀን ሲቀረው በእናቱ ስልክ ደውሎ ቅዳሜ መምጣት ይችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ፈቀድኩለት። ልጆች በልተው ከሄዱ በኋላ መጣ። ቀሪ እንጀራ ስለነበረን በላ። ከባቄሎ ስለሚመጣና መኪና ስላላገኘ እንደመሸበት ነገረኝ። ብዙውን ጊዜ መንገድ ላይ ሲዞር ቢያሳልፍም በፊት በፊት እናቱ ደብረብርሃን ካምፕ ሳለች ልጅ ሲጠብቅላት ከቤተመጻሕፍት እንደሚቀር ጓደኞቹ ሳይነግሩኝ አልቀሩም። ምንም ብለው ግን እርግፍ አድርጎ አይቀርም። በዚህ ዓመት ህዳር አካባቢ መጀመሪያ የተዋወቅሁት ተፈናቃይ ልጅ እሱ ነው። የትውውቃችንም ምክንያት በቤተመጻሕፍት ደጅ ሲያልፍ ጠርቼው ነው። በእሱ ምክንያት ብዙዎችን አወቅሁ። ከማወቅ በዘለለም ለማስተማርና ለማስነበብ እየሞከርኩ ነው። ይህ ባለታሪኩ ልጅ የበጋው ትምህርት የመጨረሻ ቀን የመጣ የመጨረሻው ልጅ ስለሆነ ቤተመጻሕፍት ፊትለፊት ካለ ሻይ ቤት ሻይ ጋበዝኩት። ለዉሱን ደቂቃዎች እኔን የማናገር ዕድል ሲያገኝ እናቱ በችግር ውስጥ እንዳለች ነገረኝ። የምትፈልገው ደግሞ ቤተሰቧን የምትመግበው ነገር ለማግኘት የሚያስችል ሥራ መጀመር ነው። መልዕክቱን አደረሰ። የፈለገችውን ገና አላገኘሁላትም። ስልኳን ለአንድ ወዳጄ ሰጥቻለሁ። ልጁ አብሮት የሚዞር ጓደኛም አለው። ጓደኛው ደግሞ መስማት የተሳነው ነው። መስማት የተሳነው ልጅ አባቱ ነቀምት በእስር ላይ ይገኛል። የእስሩ ምክንያት ለምን ሰፈራችሁን ከጥቃት ተከላከላችሁ የሚል እንደሆነ ሰምቻለሁ። ሁለቱም ልጆች ከተማውን ሲዞሩ ይውላሉ እንጂ ትናንት ለጀመርነው የክረምት ትምህርት ፍላጎት አላሳዩም። እያንዳንዱ ልጅ የየራሱ ታሪክ አለው። እኔ በተለያዩ መርሐግብሮች በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችን አይቼ ይህን ካልኩ በየካምፖቹ የሚሰሩት ወገኖች ብዙ ጥልቅ ምልከታ ይኖራቸዋል። ከተፈናቃዮቹ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል አብሮ እንደቆየ ሰው በእኔ አረዳድ በወለጋ የሚኖሩ አማሮች በአጠቃላይ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው ኑሯቸው ሕይወታቸው እንዲቀጥል ያህል አርሰውና ሰርተው እንዲበሉና እንዲኖሩ እንጂ በቋንቋቸው ተምረው፣ በየመሥሪያ ቤቱ ሰርተው፣ መርጠው፣ ተመርጠው ዕጣፈንታቸውን እንዲወስኑ አይደለም። ተምረው ኮሌጅ የመግባት፣ ስለ ዓለምና አገራቸው ሁኔታ የማንበብና የማሰላሰል ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። አንድ ማህበረሰብ ደግሞ ከውስጡ የተማረ ከሌለው ዕድሉን የሚያቃና አይሆንም። የመጣ የሄደው ዕድሉን ይወስንለታል። ለምሳሌ ተሳደው ወደ ደብረብርሃን ለመምጣት የቻሉት ዕድላቸው በካምፕ ውስጥ በችግር፣ በረሃብና በአእምሮ ጭንቀት ሕይወታቸውን መግፋት ነው። ወደዚህ ለመምጣት ያልታደሉና አካልና ሕይወታቸውን ያጡትን ቤት ይቁጠራቸው። እዚያ የቀሩትንም ሁኔታ አናውቅም። ደብረብርሃን ከመጡ በኋላ ወደ ወለጋ እንዲመለሱ ከተደረጉትም የብዙዎቹ መጨረሻ እዚያው ባሉ ካምፖች ውስጥ ነው። በወለጋና ኦሮሚያ ተብሎ በተከለለው ቦታ የመጤና ነባር አስተያየትና የባለሃገርነት ንፍገት ሲገጥማቸው እንደቆየ ይሰማል። ይህ ትርክት መታረም ይችል ይሆን? ለመሆኑ የኢትዮጵያና የትውልዱ የወደፊቱ ዕጣፈንታስ ምን ይሆን? ስለ አሜሪካ ሰሞኑን እያነበብኩት ካለሁት የባራክ ኦባማ ግለታሪክ 'A Promised Land' እንዲሁም ከሌሎች መጻሕፍት የተገነዘብኩት ዓይነት አንድ ሰው በማንነቱ ሳይሆን በችሎታውና በሥራው የሚወዳደርና የሚዳኝበት ጊዜስ በኢትዮጵያ ይመጣ ይሆን?  



2024 ጁን 11, ማክሰኞ

ጓደኛዬ ከሃያ ዓመታት በኋላ

 ጓደኛዬ ከሃያ ዓመታት በኋላ

አህመድ መሐመድ ሰዒድ የደብረብርሃን ልጅ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅም ነው። ከአርጎባ ሙስሊም አባትና ከተጉለት ክርስቲያን እናት ይወለዳል። በተለይ የማስታውሰው በስድስት ኪሎ የ505 የተማሪዎች መኖሪያ ህንፃ ቲቪ ሩም ዜናና የ1997 የምርጫ ክርክር ስንከታተል ነው። እኔን አንድ ዓመት ይቀድመኛል። በምርጫው ሰሞን ጠፋ። የት ሄደ ብዬ ሰጋሁ። ደብረብርሃን መጥቼ የቤተሰቦቹን ቤት ፈልጌ አገኘሁት። በብርድልብስ ተሸፋፍኖ ተኝቶ አልገለጥም አለኝ። ሕመሙ የአእምሮ ነው አሉ። አዝኜ ተመለስኩ። 1997 እና 1998ን አርጎቦች ዘመዶቹ ጋር ገጠር ሄዶ ቆየ። መድሐኒቱንም ይወስዳል። በዘመድ ሲታገዝና በአማኑኤል ሆስፒታል ሲታከም ቆይቶ ስላገገመ በ2000 ዓ.ም. ሁለተኛ መንፈቀ-ዓመት ተመልሶ ዩኒቨርስቲ ገባ። በ2002 ተመረቀ። ሁለት ዓመት ሥራ ሳይቀጠር ደብረብርሃን ቆየ። በስራአጥ ተደራጅቶም ነበር። አባቱን በሥራ ያግዝ ነበር። በ2005 ዓ.ም. በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ጋቸኔ ተቀጠረ። እስካሁንም በዚያው እየሠራ ነው። በዚህ ዓመት አንድ ቀን አባቱን ደብረብርሃን መንገድ ላይ አገኘኋቸው። ስለደህንነቱም ጠየኳቸው። ለህክምና ቀጠሮ ስለሚመጣ እደውልልሃለሁ አሉኝ። እርሳቸው ሳይደውሉልኝ እኔ ደውዬላቸው አገኘሁት። ተገናኝተን ብዙ አወራን። ስልክ አልያዘም። የለውም። ጓደኞቻችንንም እያነሳሳን ቆየን። እቤታቸውም ሄድኩ። ቤተሰቦቹም ተደሰቱ። ህመሙ ስኪዞፍሪኒያ የሚባል የአእምሮ ህመም መሆኑን ነግሮኛል። በቀንም ሆነ በህልሜ የሚመጣብኝ ድምፅ አለ ይላል። እንደሱ ገለጻ ጆሮው ላይ ይንሽካሾካል። በዓይኑ ይታየዋል። ይሳደባሉ ይላል። ሥራ ቦታው ተስማምቶኛል ባይ ነው። ጋቸኔ ማታ ሲደብረኝ ወጣ ብዬ እዝናናለሁ፣ ቴሌቪዥን አያለሁ፣ ከዚያ ተመልሼ እጽፋለሁ ይላል። ሬዲዮም ያደምጣል። በሬዲዮ ዜና፣ መዝናኛና የሰዎችን ታሪክ እሰማለሁ ይላል። መጻሕፍት ስላሉ የሚያሳትምልኝ ባገኝ የሚል ሐሳብ አንስቶልኛል። በኔ ሃሳብ ግን ቀዳሚውና አንገብጋቢው ጤናው መመለሱ ላይ መሰራት አለበት የሚል ነው። ይህን ጽሑፍ ጽፌ አነበብኩለት። እንድለጥፈውም ፈቅዶልኛል።


2024 ፌብሩዋሪ 28, ረቡዕ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

 

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም.

መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

 

ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረት መናኸሪያ ወደ ደብረብርሃን እየመጡ እንደሆነ ደውለው ነገሩኝ፡፡ እኔም ሲመጡ እንደምቀበላቸው ነገርኳቸው፡፡ ሲደርሱ ደውለው ቤተመጻሕፍት ተገናኘን፡፡ ከመስሪያ ቤት መጥቼ እዚያ ስላገኘኋቸው አመሰገኑኝ፡፡ እኔም ላደርግላቸው የምችለው ቀላሉ ነገር ስለሆነ እንዳያስቡ ነገርኳቸው፡፡ ወደ ሆስፒታል በቀጥታ ሄድን፡፡ ስላለፋቸው ቀጠሮ ትናንት ጠይቄላቸው ስለነበር በተባለው ክፍል ሄደን አጣራን፡፡ ፋይላቸውን ማስወጣት ያስፈልግ ስለነበር አወጣን፡፡ ሰሞኑን የመታከም ዕድል እንደሚኖራቸው ተነግሮን ወደ ጠባሴ ተመለስን፡፡ ጠባሴም ሌሎች ቤት የተከራዩ ተፈናቃዮች ዘመዶች ስላሏቸው ወደነሱ እሄዳለሁ ስላሉ ምሳ በልተው ሄዱ፡፡ ነገና ሰሞኑን ተከታትለን እንደምናሳክማቸው ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ለእያንዳንዷ ጉዳይ ሲያመሰግኑኝ ዋሉ፡፡ ይህም ለኔ የሚያሳፍር ነበር፡፡ ወደ ወለጋ ከተመለሱ እኔ የማውቃቸው የቤተመጻሕፍት አንባቢ ልጆች የእርሳቸውን ልጅ ስለማውቅና ስልካቸው ስላለኝ ከሄዱ ጀምሮ እንደዋወላለን፡፡  

ቆይታችን የሁለት ሰዓት ገደማ ይሆን ነበር፡፡ የነገሩኝን ነገር እንደሚከተለው አቀርበዋሁ፡፡

‹‹ደውዬ እዚህ ጠይቅልኝ ያልኩህ እዚያ ያለው ሆስፒታል ለአምቦ ጽፎልኝ አምቦ መታከም ስላልቻኩ ነው፡፡ በእርግጥ በስልክ አልነገርኩህም፡፡ አምቦ ሆስፒታል ጥሩ ፊት አላሳዩኝም፡፡ ወጣት ሐኪሞች ናቸው፡፡ ሁኔታው ጥሩ አይደለም፡፡ ሕክምናውም ሆነ ዕቃውም ያላቸውም አይመስለኝም፡፡ ለአዲስ አበባ እንጻፍልህ ሲሉኝ አዲስ አበባ ለመታከም ሰውም ስለሌለኝ እዚሁ ለመምጣት ወሰንኩ፡፡ አዲስ አበባ ሌላ ህመም አሞኝ ከሁለት ዓመት በፊት ታክሜ ድኛለሁ፡፡  ጥሩ ህክምና ያለው ነቀምት ነበር፡፡ ነቀምት አይርቀኝም፡፡ ችግሩ እዚያ እንዴት ተደርሶ! መንገድ ላይ ይገድላሉ፡፡ እዚያስ አላክምም ቢሉ በምን ይታወቃል?

የኛ ነገር ያሳዝል መቼም፡፡ እዚህ ደብረ ብርሃን እኮ 80 ኦሮሞ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ አማራ አግብተው አንለይም ብለው የመጡ፡፡ እዚያ አላስኖር አሏቸው፡፡ እኔ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁለቱ ትልልቆቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ትዳር ይዘዋል፡፡ ሁለቱ ትንንሾቹ ወንዶች ናቸው፡፡ አንተም ጋ ይማሩ ስለነበር ታውቃቸዋለህ፡፡  

ከደብረብርሃን ሲወስዱን ሌሊት ነው ካምፕ መጥተው ስም እየጠሩ የወሰዱን፡፡ እኔ ማክሰኞ የሕክምና ቀጠሮ ስላለኝ ልጆቼና ባለቤቴ ይሂዱ እኔ ታክሜ ልሂድ ብል አይሆንም ብለው ወሰዱኝ፡፡ እዚያ እንደደረስን አቀባበሉ ደማቅ ነበር፡፡ የገባን ዕለት እንጀራ አበሉን፡፡ 15 ኪሎ ሩዝም ሰጡን፡፡ ጀሪካን ሰጡን፡፡ ብረት ድስት የሌለው ስላለ በምን አብስሎ ይብላ? ሰዉ ተራበ፡፡ ለልጆቻችን ሩዝ አብስለን ስንሰጣቸው ማታ በልተው ጠዋት አልደግም አሉ፡፡ ትምህርት የለ ምን የለ! ልጆቻችን ተሰላችተዋል፡፡ ደብረብርሃን ከካምፕም ወጥተው ይሰሩ ነበር፡፡ ትምህርት ቤትም ይሄዳሉ፤ ቤተመጻሕፍትም ቅዳሜና እሁድ ይመጣሉ፡፡ ልጆቼን እንደልጃቸው አድርገው የሚይዙልኝ ባገኝ አሾልኬ እልካቸው ነበር፡፡ ከገበያ የሚገዛውን ሸራ ዳስ ሰርተው እሱ ውስጥ ነው በካምፕ የሚያኖሩን፡፡ ፖሊስና ሚሊሻ ነው የሚጠብቀን፡፡  ትልልቁ ሰው መጣችሁልን ብሎ መጥቶ ጠየቀን፡፡ ተደሰተ፡፡ ለምን ሄዳችሁ ጠየቃችሁ እንባላለን ብለው ፈርተውም የቀሩ አሉ፡፡ እኔ ነዋሪነቴ ከተማ ነበር፡፡ የገጠሮቹ ቤታቸው ስለተቃጠለ መመለሻ የላቸውም፡፡ የህይወትም ዋስትና የለም፡፡ የኔ ግቢ ትልቅ ነው፡፡ ሰርቪሱ ውስጥ የተከራዩ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ እኛ ወደ ደብረብርሃን ስንሰደድ ግቡበት አልናቸው፡፡ እነሱ ግን አንገባም አሉ፡፡ ሴቷ በተለይ ‹‹ለነሱ ያልሆነ ቤት ለኛም አይሆነንም፤ አንገባም!›› አለች፡፡ ከደብረብርሃን ደውለን ለምነን ነው ያስገባናት፡፡ አሁን ባሏም እሷም እየተፈራረቁ እንጀራ እየያዙ ይጠይቁናል፡፡

የሰላሙ ነገር አሁን የተረጋጋ ቢመስልም ችግሩ መልሶ ይነሳል፡፡ ይህን ሰሞን ህክምናዬ ቢያልቅልኝ እመለስ ነበር፡፡››

እኔም ተከታትለን እንደምናሳክማቸው ነግሬ ሸኘኋቸው፡፡

ማስታወሻ - ይህ ምስክርነት ከደብረብርሃን ወደ አንድ የኦሮሚያ ወረዳ የተወሰዱትን ብቻ የሚመለከት እንጂ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የተወሰዱትን አይመለከትም፡፡


ሁለተኛ ቀን

ከወለጋ ተመልሰው ደብረብርሃን የሕክምናቸውን ሁኔታ የሚከታተሉትን አዛውንት ለሁለተኛ ቀን አገኘኋቸው። ስለአሜሪካ ድምፁ ዘገባም ነገርኳቸው። ችግሩን አስመልክተው እዚያ ከካምፕ መውጣት ከባድ መሆኑን፣ ቢወጡም በፖሊስ አጀብና በዓይነቁራኛ ተጠብቀው መሆኑን ነገሩኝ። ስጋቱ በተቃዋሚዎች እንዳይጠለፉ እንጂ እንዳይጠፉ አይደለም። እነሱን ጠልፎ ማስረከብ ገንዘብም እንደሚያስገኝ ይገምታሉ። ፈንጂ ወይም መሳሪያ ተጠቅመው ካምፑን እንዳያጠቁም ስጋት አለ። በምጽዋት መኖር እንዳንገፈገፋቸው ነገሩኝ።  ደብረብርሃን አቅም ላለው የጉልበት ሥራም ሰርቶ ለመኖር ህዝቡ ካለው ተቀባይነት አንፃር የተሻለ መሆኑን ነገሩኝ። ሕክምናቸውን በዘመናዊም በባህላዊም እየተከታተሉ ነው። 

ከሰዓት 

ድንገተኛ ለውጥ

አዛውንቱ ከወለጋ ተመልሰው ደብረብርሃን ለዓይን ቀዶ ሕክምና ቀጠሯቸው መጡ። ሐኪሙ ተቀይሮ ኖሮ የዕለቱ ተረኛ ሐኪም ቀዶ ሕክምና አይሰራም ብሎ መድሐኒት አዘዘላቸው። ለሳምንት ወስደው እንየው አላቸው። በዚያም ሲበሳጩ የሰሙ ሌላ ታካሚ የሕመሙን ሁኔታ አይተው ወደ ባህል ሐኪም ላኩን። በጥጥ ብዙ ጉድፍ ወጣላቸው። የሚቆረቁረኝ ተሻለኝ አሉ። የባህል ሐኪሟ መድሐኒቱን ተዉት አሏቸው። ውጤቱን እናያለን። 

 


 

2024 ፌብሩዋሪ 20, ማክሰኞ

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

 

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

ረቡዕ፣ የካቲት 13፣ 2016 ዓ.ም.

 

ከብዙ ጭንቀት በኋላ በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 4፡15  ስልክ ደወልኩ፡፡ የደወልኩላቸው የአንደኛው ተማሪ አባት ያውቁኝ ዘንድ የልጃቸውን ስም ጠርቼ ‹‹የእከሌ መምህር ነኝ›› አልኳቸው፡፡ አወቁኝ፡፡ ከእርሳቸው ጋር ልዩ ትዝታ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ልጃቸውን ከዘመድ የተላከ 800 ብር ልሰጠው ብዬ ወላጅ አምጣ አልኩት፡፡ እሱም አንድ ወጣት ይዞ መጣ፡፡ እኔም ‹‹ይህ ወላጅ አይሆንም!›› ብዬ መለስኩት፡፡ ከሰዓት በኋላም አባቱን ይዞ መጣ፡፡ ገንዘቡን ያሰብነው ሃያ ልጆች አነስተኛ ስራ እንዲጀምሩ ለእያንዳንዳቸው 800 ብር በመስጠት ነበር፡፡ ልጆቹ ያንን ገንዘብ ይዘው ፎቶ ተነስተው ለላኩልኝ ወዳጄ እልካለሁ፡፡ ይህም ልጅ እንደዚያው ለማድረግ ወላጅ ማምጣት ነበረበት፡፡ ስለሆነም አባቱ መጡ፡፡ ‹‹ትምህርት አልማር አለኝ፡፡ ጠላብኝ፡፡ እኔ እንዲማርልኝ ነው የምፈልገው፡፡ አትስጡብኝ፡፡›› አሉኝ፡፡ እኔም ይህን በመረዳት ‹‹በቃ! ንግዱ ይቅር፡፡ ለእለት ችግርዎ ያውሉት›› ብዬ ተማሪውን ወደ ቤተመጻሕፍት አንብብ ብዬ አስገብቼ ከሌሎቹ ጋር ቀላቀልኩት፡፡ ገንዘቡን ለአባቱ ሰጠሁ፡፡ የተቀበልኩት ምርቃት አንድ ሚሊዮን ብር የሰጠሁ ያህል ነበር! ቀደም ብለን ለ33 ልጆች ካሰፋነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ አንዱ ተጠቃሚ የእርሳቸው ልጅ ስለነበርም ያን እንደውለታ ያስታውሳሉ፡፡ ብቻ ሁኔታው ልብ ይነካል! ልጃቸውም እንደአብዛኞቹ ልጆች በኦሮሚያ ሳለ በአማርኛ ስላልተማረ ከስድስተኛ ወይም ከሰባተኛ ክፍል ወደ አንደኛ ተመለስ ተብሎ ይሆናል ትምህርት የጠላው፡፡ ልጆቹ ካዩት ሰቆቃና ካሳለፉት ግፍ እነዲሁም እየገፉ ካሉት ከባድ ሕይወት አንጻር ትምህርት የሚያስወድድ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም፡፡ ለማንኛውም በምሽቱ የደወልኩት ለእርሳቸው ነው፡፡

በየሚሄዱባቸው ቦታዎች ያሉ ሰዎች በስልካቸው እየደወሉ ብትመጡ እናደርስባችኋለን ያሏቸውን የግፍ አገዳደል ስለነገሩን ስጋት ላይ ነን፡፡ የፖለቲካውም ነገር ስላላስተማመነ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ አካል ይኖራል ብሎ የሚያምን ሰው አልገጠመኝም፡፡ የደወልኩላቸው ተፈናቃይ ባኮ እንደገቡ ነገሩኝ፡፡ ባኮ ሸዋ ውስጥ ነው፡፡ ከአምቦ ይርቃል፡፡ የተጠለሉት በሳምንት ውስጥ ሊበጣጠስ በሚችል ከገበያ የሚገዛው ሸራ ውስጥ ነው፡፡ የተወሰዱት ከነቤተሰባቸው ነው፡፡ ምን እንደሚፈልጉ ስጠይቃቸው ‹‹ማሰብህ ብቻ በቂ ነው!›› አሉኝ፡፡ ‹‹እንመለሳለን ብለን በምንም ነገር አላሰብንም፡፡ ባለፈው ሳምንት በድንገት እዚያው ደብረብርሃን ውስጥ ወዳዘጋጁት ቦታ አስገቡን፡፡ አትወጡም ተባልን፡፡ ተከለከለ፡፡ እዚያም ውለን አድረን ከደብረብርሃን ጫጫ ድረስ የአማራ ክልሎቹ አመጡን፡፡ ከጫጫ የኦሮሚያው ‹መከላከያ› ተረከበን፡፡ አምቦ ዙሪያ ነው የምትሰፍሩት ብለው በመከላከያ አምቡላንስ ተቀበሉን፡፡ ጥሩ አቀባበል አደረጉልን፡፡ 15 ኪሎ ሩዝ ሰጥተውናል፡፡ አንተስ ደህና ነህ ወይ? ቤተሰብህስ?›› አሉኝ፡፡

እኔ ደህና መሆኔን ነገርኳቸው፡፡ ቤተሰቦቼ ያሉበት ሳሲት አቅራቢያ በድሮን የተመቱ ሰዎች መኖራቸውን ገልጬ የኔ ቤተሰቦች ግን ለጊዜው ደህና መሆናቸውን ነገርኳቸው፡፡

ልጃቸው እንደተኛና ጠዋት እንደሚያገናኙን ነገሩኝ፡፡

ግርታ ገባኝ፡፡  ለአሁኑም ቢሆን ፈጽሞ ሰላም ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. እና የስራ ባልደረቦቼ ከደብረብርሃን ወደ አምቦ ስንሄድ የመጠቃት ወይም የሆነ አደጋ የማጋጠም ስጋት ጠብቀን ነበር፡፡ ስንደርስ ግን በቀለ ባየታ ቶለሳ የተባሉ አንድ ድንቅ የአምቦ አዛውንት መንገድ ላይ በስተቀኝ ስንሄድ አይተው እንግዶች መሆናችንን አውቀው ተቀብለው ምግብ ቤት አሳይተው ስለ ኢትዮጵያዊነት እያወጉልን ራት በልተን እስክንጨርስ ጠብቀው ወደ ማደሪያችን የሸኙንና በአምቦ በሰላም ከርመን የተመሰለስነው ትዝ አለኝ፡፡

ብሔራዊ ፈተናም በዩኒቨርሲቲ መሰጠት በጀመረ ዓመት ወደ ነቀምትና ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች ለመፈተን የሄዱ መምህራን ሲመለሱ ቃለመጠይቅ አድርጌ ስለቆይታቸው ጽፌ ነበር፡፡ የጽሑፉ ርዕስ ‹‹ከወለጋ መርዷቸው ሲጠበቅ ተሸልመው የመጡት አማሮች›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹ይህን ጽሑፍ ስታነቡ በአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመረዳት እንደማታለቅሱ ዋስትና አልሰጣችሁም!›› የሚል ማሳሰቢያም ነበረው፡፡

 

የዛሬው የስልክ ጥሪ እነዚህን ከአሁን በፊት የታዘብኳቸውን ምልከታዎች አስታወሰኝ፡፡ ከአሁን በፊት የታዘብኳቸው ጉዳዮች እንደሚያሳዩት መንግስት ከፈለገ ሰዎች በሰላም መኖር እንደሚችሉ ነው፡፡ አንድ አማራ መምህር ደምቢዶሎ ሄዶ ፈትኖ መምጣት ከቻለ ከደምቢዶሎ ወዲህ ባለ ቦታ ሌላ አማራ ለምን ይሞታል! ስደት፣ የግፍ ግድያ፣ አካል ጉዳትና ሌሎችም አሰቃቂ ድርጊቶች ለምን ይፈጸማሉ? መንግስት እነዚህ ከደብረብርሃን የተመለሱ አማራ ተፈናቃዮች በሰላም እንዲኖሩ ከፈለገ እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ በአምቦና በባኮም የተደረገላቸው አቀባበል ይህንኑ ያሳያል፡፡

 

በደብረ ብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ከሁለት መቶ ያላነሱ የኦሮሚያ ተፈናቃይ አማራ ልጆችን በሳምንት መጨረሻ ቀናት ስናስነብብ፣ ስናስተምር፣ ስንመግብና ስናበረታታ ቆይተናል፡፡ ይህን ልናደርግ የቻልነው ጊዜ ተርፎን አይደለም፤ ገንዘብም የለንም፤ አቅማችንም ውሱን ነበር - ነውም፡፡ የደብረብርሃን ህዝብ በሚያደርገው ድጋፍ፣ በቤተመጻሕፍት መረባችን ምክንያት የተዋወቅናቸው ወገኖቻችን በሚያደርጉልን እገዛ፣ የቤተመጻሕፍቱ አባላት የሆኑ ወጣቶች በድህነት፣ በኑሮ ውድነትና ተስፋ መቁረጥ እየተገረፉ በሚያደርጉት ልገሳና በጎፈቃደኝነት ነው፡፡ እነሱ ሳይመቻቸው ቅዳሜና እሁድን ከቤተክርሰቲያን ቀርተው፣ ስራቸውን አስታጉለው፣ እረፍታቸውን ትተው ለእነዚህ ልጆች አስበው ሲያስተምሩ፣ ሲመግቡና ሲያበረታቷቸው ቆይተዋል፡፡ አንድ ቀን አርባ ተፈናቃይ ልጆች ቢመጡ በቀጣዩ ዘጠና ይመጣሉ፡፡ ስድሳና ሰባ አማካይ የልጆች ዕለታዊ ቁጥር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በአጠቃላይ ከወይንሸት ካምፕ ቤተመጻሕፍቱን ብዙ ልጆች አይተውታል፡፡ ከትልልቆቹ የቻይና ካምፕና ባቄሎ ካምፕ ተብለው ከሚጠሩት የሚመጡት ዉሱን ናቸው፡፡ ዋነኛው ምክንያት የቦታው እርቀት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ዙር ተመላሽ ተብለው ሊሄዱ የተዘጋጁት ወደ ልዩ ጊዜያዊ ማቆያ ከገቡ በኋላ ዉጪ ባሉት ዘንድ የነበረውን መሸበር የምገልጽበት ቃል የለኝም፡፡ አሁንም ልገልጸው አልችልም፡፡ ለማናቸውም ሄዱ፡፡ ከሄዱ በኋላ ስለሚገጥማቸው ሁኔታ ያለን ስጋት ጽኑ ነው፡፡

 

እነዚህ ተፈናቃዮች በእጅጉ የሚያሳዝን ሕይወት ያሳለፉና እያሳለፉ ያሉ ናቸው፡፡ ደብረብርሃን እንዳይቆዩ እርዳታ ቆሟል ብለውኛል፡፡ እርዳታ ብቻም ሳይሆን ቤት ተከራይቶ ለመኖር አይችሉም፡፡ ሁሉ ነገር ታጥሯል፡፡ እስረኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ለአካል ጉዳተኛ ልጄ የተሰጠኝን ዊልቼር የሚገዛ ፈልግልኝ ብለው ልጃቸውን የላኩብኝ እናት አሉ፡፡ የሚገዛ ሰው ግን አላውቅም፡፡ ሌላዋ እናት እሁድ 10/06/16 ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው ለአንዷ ስለተሰፋው የደንብ ልብስ አመስግነው ወደ ወለጋ ሊሄዱ የመሆናቸውን ወሬ አስረድተውኛል፡፡ በብዛት አዋቂዎችን አላገኘሁም፡፡ የተሸበሩት ልጆች ግን ሁሉንም ጉዳይ ነግረውኛል፡፡ እኝህ እናት ስላሉት አማራጮች ስጠይቃቸው ደብረብርሃን መቅረት እንደ ወንጀል መታየቱን አልሸሸጉኝም፡፡ ወደ ወሎም ለመሄድ እዚያ ያሉትን ዘመዶቻቸውን አያውቋቸውም፡፡ አክስትም አጎትም ቢባሉ በደህናው ቀን ስላልጠየቋቸው የመሄድ ድፍረት የላቸውም፡፡ ልሂድ ቢሉስ መሳፈሪያ ይኖራቸው ይሆን? ልጆቹ ዛሬ ቤተመጻሕፍት ሊያነቡ መጥተው ነገ ስለመመለሳቸው እርግጠኞች አይደሉም፡፡  

 

የደወልኩላቸውን ተፈናቃይ ‹‹የወለጋዎቹስ እንዴት ሆኑ?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ መረጃ የላቸውም፡፡ ደብረብርሃን ላሉት ደውዬ በደህና እንደገቡ ነግረውኛል፡፡ ወደፊትም እከታተላለሁ፡፡ መኪኖቹ ከአምቦና ወለጋ ወደ ደብረብርሃን ሲመለሱ ሌሎቹን በየተራ እንደሚወስዱ ትናንት ምሽት ያገኘሁት ልጅ ነግሮኛል፡፡ የሚመልሳቸው አንድ የትራንስፓርት ድርጅት ኮንትራት ይዞ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ በአሁኑ አካሄድ ቅድሚያ የተሰጣቸው እዚያ ተመን ኖሯቸው ግብር የሚገብሩትን ነው ተብሏል፡፡ የስም ዝርዝራቸውም ከዚያው ከኦሮሚያ ይኖሩበት ከነበረው ስፍራ መጥቶ ነው፡፡ ግብር የማይገብርና የሰው መሬት ተከራይቶ የሚያርሰውን ለጊዜው አልወሰዱም፡፡ በሂደት ይወስዱ ይሆናል፡፡ የደብረብርሃን ሰዎች ስጋት ግን እነዚህን መሬት ያላቸውን ሰዎች ለምን ወሰዷቸው የሚል ሲሆን፤ ምናልባት ወደፊት ሰላም ሲሰፍን መሬታችንን መልሱ ብለው በህግ እንዳይጠይቁ ይሆን ወይ የሚል ነው፡፡

የእነዚህ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ሰላም ባልሰፈነበትና እርግጠኝነት በሌለበት ሁኔታ ባይሄዱ እጅግ ተመራጭ ነው! 

ልጆቹን በመጨረሻ ቀናችን ያልኳቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ሁላችሁም ስልኬን፣ ስሜንና የቤተመጻሕፍቴን ስም ያዙ፡፡ አዲስ ነገር ሲኖር ደውሉልኝ፡፡ አገር ሰላም ከሆነ ወለጋ ያላችሁበት ጋ መጥቼ ቤተመጻሕፍት እንከፍት ይሆናል!››

ብቻ ሰላም እንደናፈቀን እንዳንቀር!

 

 

2024 ጃንዋሪ 23, ማክሰኞ

የ ቋ ን ቋ ወግ

 የቋንቋ 


ለመሆኑ ኦሮምኛ? አማርኛ? ትግርኛ? እንግሊዝኛ? የትኛውን ተማራችሁ? 


ሁለት የደብረብርሃን ልጆችን አውቃለሁ። ስለ ቋንቋ ጉዳይ ያወጉኛል። ስለ እንግሊዝኛ ተነጋግረናል። ከእንግሊዝኛ አንፃር የተሻለ ችሎታ አላቸው። ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። የከተማ ልጆች ስለሆኑ፣ የተማረ ወላጅ ስላሳደጋቸው ወይም በሌላ ምክንያት። 

ኦሮምኛን አስመልክቶም አንዳንድ ነገሮችን አንስተውልኝ እንደነበር አስታወስኩ። ለማወቅ ይፈልጋሉ። ምክንያታቸውን ስጠይቅ "የኦሮምኛ ሙዚቃ ለመስማት፣ ወደ ሌላ ቦታ ስንሄድ እንድንጠቀምበት" አሉኝ። 

አፋን ኦሮሞ የሚማሩ ሰዎች "ኦሮምኛ ለምን ትማራላችሁ?" ተብለው ቢጠየቁ ኦሮሞ ስናገባ አማቶቻችን ጋር ስንሄድ እንድናወጋበት ሊሉም ይችላሉ። ዘውግ-ዘለል ፍቅር ባልተጠናከረበት በዚህ ጊዜ።

የኦሮምኛ ቃላት ለመያዝ ሐሳቡ የመጣልኝ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የክፍሌ ልጅ ከሆነው ምናልባትም ከብቸኛው የቋንቋው ተናጋሪ ከተክሌ ወልዱ ጋር 

ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስንሄድ ተክሌ ያቺን ልጅ "ኢንተሎ ነኤጊ" በላት አለኝ። ምን ማለት እንደሆነ ስጠይቀው "አንቺ ልጅ፣ ጠብቂኝ" ማለት መሆኑን ነገረኝ። ጠብቂኝም አላልኩ፤ አረፍተነገሩን ብቻ ተማርኩ።

ፈተና ተፈትነን ውጤት ስንጠብቅ የሳሲቱ ጎበዝ ተማሪ አንዳርጌ ገብረማርያም ዩኒቨርስቲ ስንገባ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ተማሪዎችን እንደምናገኝ ጠቅሶ ቋንቋዎቹን መማር እንዳለብን አነሣ። ተስማማን። ከነዚህ ቋንቋዎች በጓደኞች መኖርና በአጋጣሚዎች የአፋን ኦሮሞው ተሳካና ጀመርኩ። ያው ያዝ ለቀቅ ነው። 

ከወለጌው ነብዩ ዓለማየሁ ጋር የምንግባባው በእንግሊዝኛ ነበር። እሱ አማርኛ አያውቅም፤ እኔም ኦሮምኛ አልችልም። አንድ ቀን ከጓደኛው ጋር ሲገናኙ ሲያስተዋውቀኝ ጓደኛውን "ኮቱ" አልኩት። ሰላምታ መስሎኝ። 

ሌላ ቀን ተውላጠ ስሞችን ማለትም አኒ፣ ኑ፣ አቲ፣ ኢሲን፣ ኢሺ፣ ኢኒ፣ ኢሳን ተማርኩ። መጠይቅ ተውላጠ-ስሞችን ኤኙ፣ ማሊ፣ ኤሳ፣ ኢሳ ከሚ፣ ዮም፣ ማሊፍ፣ አከም ለበለብኩ። 

የሳምንቱ ቀናት በደፍኖ ወይስ በዊጠታ የሚጀምረው ይሻልሃል ተብዬ ሰባት ከሰባት ደፈንኩ። 

የዓመቱ ወራትን ፉልባና፣ ኦንኮሎልሳ ...

ከኦሮምኛ ወቅቶች የተረሳኝ ቢራ/ፀደይ ነበር። ራ ይጠብቃል። 

ቁጥሮች ወይም ለኮፍሶታ መጀመሪያ ቢለክፉኝም አሁን ተግባብተናል። 

ቃላትን ልክ እንደአማርኛው ገጣሚ ሰለሞን ዴሬሣም ባይሆን የቱን ከማን እንደተማርኩ አስታውሳለሁ። 

ከታሪኩ አነጋ አዳነ - ኢዶ፣ ዳኢመ፣ ነዲዴ፣ አኮ፣ ሊቄፈቹ፣ 

ከሌሊሴ ከበደ - ኡታልቻ መልካ በለኣ ቦረፈቱ ደንዳ፤

ኛታ ወጪቲ ዲጶ ፈላነቱ ደንዳ፤

ነሚቻ ኢየምሲሴ፤

ከአማን ቃዲሮ አቢቹ - ሸመረን፣ ዊርቱ፣ ኩፉ፣ አሬዳ

ከዘውዲቱ - ደፊሱ፣ ፉናና

ከአብዮት ዲባባ - ከጠፋም ይጥፋ እንጂ የድመትን ዓይን አያጥቡላትም የሚለውን የኦሮምኛ ምሳሌ

ከለማ ሚደቅሳ- ጉቡ (በእርግጥ በጣት የሚቆጠሩ ቃላት ይመስለኛል የሚያውቀው።) አንድ ቀን ቡናው ፈጀኝ ለማለት። "ነ ዱኩቤ" ስል "ነ ጉቤ ጀዲ" ብሎኛል።

በዚህች አነስተኛ ጽሑፍ አትኩሮቴን የሳበችውን ነጥብ ላንሣ ብዬ እንጂ ምንም ቢጻፍ መሬት ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም።

በአዲስ አበባም ቋንቋው ይሰጣል ይላሉ። እውነት ነወይ? እስኪ አስቡት ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ኦሮምኛ ለማስተማር ክፍል ገብቶ "ኢጆሌ ፊንፊኔ አከም ጅርቱ" የሚለው በርሲሳ የሚሰማውን ስሜት። በርሲሳ በሉኝ ብሎ ራሱን ያስተዋውቃል። "ቀብሶ ኬኛ ጡመረሜራ" የሚል ይመስለኛል። በቋንቋዎች ዲፓርትመንት ከአማርኛ መምህር ጋር ይነጋገራሉ ወይስ ይኮራረፋሉ የሚለውን መመለስ አልችልም። እንደ ሰዎቹና አውዱ ይወሰናል። ከተማሪዎችም ጋር ሰልፍ ላይ በባንዲራና መዝሙር ጦርነት ነበር ይባላል።

ወጣም ወረደ ቋንቋዎቻችን ሀብቶቻችን ስለሆኑ እንንከባከባቸው። የልዩነትና የጦርነት መነሻ ባይሆኑ መልካም ነው። የማንነት ፖለቲካ መጨረሻው የሚያምር አይመስለኝም።

የጀመርኩት በሁለቱ ልጆች ጉዳይ ነበር። ባልገመትኩት ሁኔታ ቋንቋውን እየለመዱ ነው። ጠቃሚ ሐረጋትንና ቃላትን ለምደዋል። በአማራ ክልልና በኦሮሚያ የተማሩ ሲሆን ከክፍልና ዶርም ጓደኞቻቸው እገዛ ተደርጎላቸው ከዚህ ደርሰዋል። የቋንቋ ፖሊሲ ከወጣና የአሁኑ ወይም ያለፈው ሁኔታ ከተቀየረ ምናልባት በአማራ ክልል ያሉ ተማሪዎች ኦሮምኛ ሊማሩ ይችላሉ። ያኔ የብሔር ፖለቲካ የሚያበቃለት ይመስለኛል። ምክንያቱም ማን ምን እንደሚያወራ መረዳት ይቻላል። ቋንቋውን ተጠቅሞ ኬላ ላይ አላሳልፍም የሚለው ፖሊስ ስራውን በትክክል ይሠራል። (ኬላ ላይ ስለማላሳልፍህ ቋንቋዬን ተማር ዓይነት ሒሳብ ያስቀኛል።) ቋንቋ ከቻለ ወደ ስም ማጣራት ይገባል። በኃይማኖት ወይም በሌላ መንገድ ይከፋፍላል። በአንፃሩ ኦሮምኛ መማር ማለት ከአክራሪ ፖለቲከኞች "እናንተ ሌላ ማንነት የላችሁም። ይኸው ኦሮምኛ ትችላላችሁ። ኦሮሞዎች ናችሁ።" የሚል ጫና ሊያመጣ ይችላል። ማንነታችን ይዋጣል የሚሉ ይኖራሉ። ሌሎች እንደዚህ ሊጠያየቁና ሊመላለሱ ይችላሉ፦ 

- በላቲን ለምን ትጽፋላችሁ? 

* በምንስ ብንጽፍ!

- ኢትዮጵያዊነት ይሸረሸራል።

* ጥርግ ይበል። ፖለቲካው የብዙ ዘመን የትግል ታሪክ ስኬት አይደለም ወይ? ድላችንን እናጣጥምበት።

- የዉጪ ኃይሎች አገራችንን ለማፍረስ ያቋቋሟቸው ፓርቲዎች ህዝቡን ከፋፈሉት።

* እንዲያውም የህዝቡ ትግል ውጤት ነው። ከውስጥ ነው የፈነዳው። በታሪክ ሁነኛ ምዕራፍ ላይ አይደለንም ወይ?

- የምን ምዕራፍ?

* ኦሮምኛ የአማርኛን ቦታ ይተካል። እኛ አማርኛን ተቸግረን እንደተማርነው አንተም ትማራለህ።

- መተባበር ይሻላል ወይስ መፎካከር? 

* የኛ ዕድል ሲደርስ ስለ ትብብር ታወራለህ።

ሁለቱም ግን ተናገርልኝ ብሎ የወከላቸው ህዝብ የለም። 

ትውልዱ የራሱን መንገድ ይዞ ይቀጥላል። 

ሰላማዊ አገርና ወደፊትን እመኛለሁ።


W. F., the boy who alerted his family to the dangers of armed individuals in the woods

  W. F., the boy who alerted his family to the dangers of armed individuals in the woods I am W. F., a native of Menz Kebele , Dano Wer...