የቲፕ ሃሳብ የመጣው ከዉጪ አገር ይመስለኛል። ሦስት ዉጪ አገር የኖሩ ሰዎች ያወጉልኝን ወይም የጻፉትን ላጋራችሁ።
ሀ. አንድ ሰው ያወጉልኝ፦ አንድ ቦታ ዕቃ ገዝቼ ዋጋው 99 ሳንቲም ስለነበር 1 ሳንቲሟን ትቻት ሄድኩ። ባለ ሱቁ ጠርቶ መልስህን ውሰድ አለኝ። ተወው አልኩት። እሱም ተገረመ። ከአስተያየቱ እናንተ ጥቁሮች የማታድጉት ገንዘብን ስለማታከብሩ ነው የሚል ነገር ተረዳሁ።
ለ. ሌላዋ ደግሞ፦ አስተናጋጅ ሆኜ ሰርቻለሁ። ሳስተናግድ ሂሳቡን ብቻ ከፍሎ ሊሄድ ቢሞክር ቲፔስ? እለዋለሁ። አንድ ምግብ ዋጋው አስር ዶላር ቢሆንና እኪሴ ያ ገንዘብ ብቻ ካለኝ ገብቼ አላዝም። ምክንያቱም ቲፕ የምሰጠው የለኝም።
ሐ. ሌላው የነቢይ መኮንን መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ሲሆን ደሞዝ የማይከፍሉና በቲፕ ብቻ የሚያኖሩ ሆቴሎች በአሜሪካ መኖራቸውን አንዷ አስተናጋጅ እንደነገረችው የጻፈበት ነው።
መ. በቲፕ ጉዳይ ላይ ተከራክረንበትም እናውቃለን። 'A Christmas Carol' የተባለውን ድርሰት ያነበብን ሰሞን ጎራ ለይተን ተከራክረናል። ጥገኝነትን ያመጣል ያልን ነበርን። ለሚሰሩ ሰዎች እገዛ ማድረግ ጥሩ ስለሆነ ይበረታታል ያልንም እንዲሁ።
አሁን አሁን ግን የዉጪው ባህል ጥንቅቅ ብሎ ገብቷል። ለተስተናጋጅ ብጥስጣሽ ብሮችን መመለስ ተለምዷል። እነዚያን ብሮች ባለታክሲ አይቀበላችሁም። ሌላም ቦታ አይሰሩም። አንድ ቀን ቲፕ ሰጥቶ በቀጣዩ ቀን መዝለል አይቻልም። ዓይን ያወጣ ብልጣብልጥነት ሰፍኗል። ትኩስ ነገር አዛችሁ መቶ ብር አውጥታችሁ ጠረጴዛ ላይ ስታስቀምጡት ይወስዷትና መልሱ በዚያው እንዲቀር ይፈለጋል። ይህን ጉዳይ ባለሃብቶቹ ይወቁ አይወቁ አናውቅም።
እናንተስ ምን ገጠማችሁ?
ሃሳቡን ትጋሩታላችሁ?
.jpeg)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ