2018 ሴፕቴምበር 12, ረቡዕ

በኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ግቢ ከ14 ዓመታት በኋላ



በመዘምር ግርማ
እሁድ ነሐሴ 27 ስብሰባ ስለነበረብኝ ወደ ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ሄጄ ነበር፡፡ ገና በሩ እንደደረስኩ ብዙ ትዝታዎች መጡብኝ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት 1993 እስከ 1996 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደመማሬ ትዝታ መኖሩ ግድ ይላል፡፡
በሩ ያው ነው፡፡ መማሪያ ክፍሎቹም ያው ናቸው፡፡ የተቀየረው ጥበቃው ነው፡፡ ወዴት እንደምሄድ የጠየቀኝ ጥበቃ ከዱሮዎቹ አንዱ ሳይሆን ከእኔ በዕድሜ የሚያንስ ወጣት ነው፡፡ የበፊቶቹ የት እንደሄዱ ብጠይቀው ትልቀኛው ሱቅ ከፍተው ሃብታም እንደሆኑ ነገረኝ፡፡ ስለበፊቱ የትምህርት ቤት ትዝታዬ ነገርኩት፡፡ ዘበኞቹ ከተማሪዎችና ተማሪ ሳይሆኑ ከሚመጡ ጋር ያደርጉት የነበረውን ግብ ግብ ነገርኩት፡፡ እሱም በአሁኑ ወቅት መምህርም ሆነ ጥበቃ ተማሪን እንደማይደበድብና ዘመኑ እንደተቀየረ አወጋልኝ፡፡ አብዛኞቹ መምህራን እንደለቀቁ ወይንም በጡረታ እንደተገለሉና የአሁኖቹ ማስተርስ እንዳላቸው ተረዳሁ፡፡
በዕለቱ ይካሄዳል የተባለው ስብሰባ እስኪጀምር ድረስ ግቢውን ዘወር ዘወር ብዬ እንድቃኝ ስለተፈቀደልኝ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ እነዚያ ከበሩ እስከ ሰልፍ መሰለፊያው የነበሩት ትልልቅ ጽዶች አሁን የሉም፡፡ አለመኖራቸውም ትምህርት ቤቱን ግርማ ሞገስ የነፈገው ይመስላል፡፡ ቤተመጻሕፍቱን፣ የአስተዳደር ህንጻዎቹንና የተለያዩ ወርክሾች የነበሩበትን አልፌ ወደ ውስጥ አቀናሁ፡፡
የኢጣሊያ ቅሪቶች በትምህርት ቤታችን በሽበሽ ናቸው፡፡ ከበሩ እንደገባን በስተግራ ከተጠረቡ ጣውላ መሳይ ግንዶች የተሰራው ሰፊና ትልቅ የውኃ በርሜሎች ማስቀመጫ ማማ አለ፡፡ የመምህራን በረፍት ሰዓት ማረፊያ ከሆነው ስፍራ ጎን ማለት ነው፡፡ ሃያ አምስት በርሜሎችን ይዟል፡፡ በኢጣሊያውያን የተሰራ ይመስለኛል፡፡ አሁን ከጎኑ ሁለት ትልልቅ ጥቋቁር የውኃ ታንከሮች ቢኖሩም የዱሮዎቹም በርሜሎች ስራቸውን ያቆሙ አይመስለኝም፡፡ ውሃ ስለሚያንጠባጥቡ፡፡
በዚሁ በስተቀኝ ያለው አሁን የአይቲ ማስተማሪያና የጂኦግራፊና የሌሎችም ትምህርት ክፍሎች ያሉበት የባንዲራው መስቀያ ያለውም ህንጻ አለ፡፡ በመሃሉ መግቢያ ያለውና ስትገቡ መካከል ላይ አነስተኛ ግቢ የምትመስልና ሰማዩን የምታሳይ ቦታ ያለችውን ማለቴ ነው፡፡ ሚኒ ሚዲያም እዚያው ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው አዳራሹ ነው፡፡ ቀለመሙ ቢለቅም ውበቱና ግርማ ሞገሱ አሁንም አልተለየውም፡፡ ወደ ውስጡ ዘልቄ የሚያምረውን ጣራውን፣ መድረኩን፣ መስኮቶቹንና ወለሉን አይቼ ትውስታ በትውስታ ሆንኩ፡፡ በድራማ ክበብ በዓይነስውሩ የአማርኛ መምህር ክንፈ አስተባባሪነት አንዳንድ ስራዎችን ሰርተንበታል፡፡ መድረኩም ላይ በተዋናይነት ብቅ ብዬ ነበር፡፡
ከዚህ ህንጻ ቀጥሎ ከበሩ እንደገባን ፊትለፊት ያለውን ባለ ምድር ቤት መማሪያ ክፍል ቃኘሁ፡፡ አሁን መምህራን ኮሌጁ ስለጠበበ የክረምት ትምህርት እያስተማሩበት ስለሆነ አንዳንድ በየበሩ ላይ የተለጠፉ የዲፓርትመንትና ሴክሽን ስያሜዎች፣ በየሰሌዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎችም አሉበት፡፡ ስጀምር እንዳልኩት ዕለቱ እሁድ ስለሆነ ግን ግቢው የተወረረ መስሏል፡፡ ጸጥታው ያስፈራችኋል፡፡  ይባላ ይመስላል፡፡
ከዚህ ህንጻ ቀጥሎ ያሉትና ከአዳራሹ ፊት ለፊት የሚገኙት ክፍሎችም አሉ፡፡ እነዚህን ክፍሎች ሳስብ ብዙ ጊዜ የሚመጣብኝ ትዝታ አለ፡፡ ይኸውም ከክፍሎቹ ግንብ ላይ የተሳሉት ሦስቱ ሥዕሎች ናቸው፡፡ ሥዕሎቹ ሲሳሉም እዚያው ነበርን፡፡ እንዲያውም ሠዓሊው ወጣት ከትምህርት ቤቱ ጋር በክፍያ ሳይስማማ ቀርቶ ቀለም ረጭቶባቸው ነበር፡፡ በኋላ ተስማምተው አስተካክሎ አስረክቧል፡፡ እኔ ከትምህርት ቤታችንም ልጆች ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ስወያይ የማነሳው ስለነዚህ ሥዕሎች ነው፡፡ ሦስቱ ሥዕሎች የሦስት የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥታት ናቸው፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ዮሐንስና የአጼ ምኒልክ፡፡ በሸዋ እምብርት፣ በደብረ ብርሃን፣ ሦስቱንም ነገሥታታችንን እኩል እንድንወድና እንድናከብር ይህ መደረጉ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ሥዕሎቹ ይሳሉ የሚለውን ሃሳብ ያነሳው ሰው መከበር አለበት፡፡ ትርጉሙ ከምንም በላይ ነውና፡፡
ከነዚህ ክፍሎች አጠገብ ጥጋቱ ላይ ሻይ ቤት ነገር አለች፡፡ ጽዶች ተተክለውና ቅርንጫፎቻቸው ተያይዘው የተሰራች ናት፡፡ ከክፍሎቹ ጀርባ እንደምታውቁት የስፖርት ሜዳችን አለ፡፡ በስፖርት ክፍለጊዜ ቅርጫት ኳስ ስጫወት ኳሷን ረግጫት የወደኩበት አስቂኝ ገጠመኝ አለኝ፡፡
ከኳስ ሜዳው ማዶ ላይ ከግንብ አጥሩ ስር ባለአንድ ፎቅ ህንጻ እየተሰራ ግንባታውም እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ቤተመጻሕፍት እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ሳይቤሪያ የሚባለውም ከሜዳው ወደታች ያለው ኮሪደር አለ፡፡ አስረኛ ክፍልን የተማርኩት እዚያ ነው፡፡ ዘጠነኛን፣ አስራ አንደኛንና አስራ ሁለተኛን ግን ከሜዳው ወደላይ ባሉት ክፍሎች ተምሬያለሁ፡፡
ከሜዳው ወደታች ባለው ወደ መምህራን ኮሌጅ አጥር በሚወስደው ለምለም ቦታ የእረፍት ጊዜያችንን እናሳልፍ ነበር፡፡ ሙስሊም ተማሪዎች ለረመዳን ጾም ሲሰግዱ አይተን ገርሞናል፡፡ ክርስቲያን ብቻ ካለበት የገጠር መንደር እንደመምጣታችን ብንገረም አይደንቅም፡፡ ሙስሊሞቹ ልጆች ራሱ ስንገረም ይስቁ ነበር፡፡ የኛ ክፍሎቹ በሽርና አብዱም አሉበት፡፡
እንዳልኳችሁ በጉብኝቴ ወቅት በትምህርት ቤቱ ውስጥ ፍጹም ጸጥታ ሰፍኖ ቤተክርስቲያን የመሰለ ተመስጦ የሚያመጣና የሚያስተክዝ ሁኔታ ነበር፡፡ እንባ እንባ አለኝ፡፡ ወደ መሰለፊያው ቦታ ልመልሳችሁ፡፡ እዚያ ሄጄ ቁጭ አልኩ፡፡ በትዝታ ባህር ሰመጥኩላችሁ፡፡: ብዙ ትውስታዎች ያሉን የአንድ ክፍል ተማሪዎች አንድ ላይ ሆነን እዚህ ቦታ ብንገናኝ ምን እንደሚከሰት አስቡ፡፡ እዚህ ስንመጣ የየራሳችን በርካታ ትዝታዎች ስላሉን መነጋገር እንኳን የምንችል አይመስለኝም፡፡ እስኪ ራሴን ላዳምጥበት የምንል ይመስለኛል፡፡ ያኔ ያሳለፍነውን እናስባለን፡፡ እንደሚከተለው፡-
ጥበቃዎቹን፡- በሰውነታቸው ግዙፍ የሆኑትን የሚያስፈራ ፊት ያላቸውን ጥበቃ አስቡ፡፡ እንኳን ተቆጥተው ይቅርና ወደእናንተ እያዩ ከሆነ እጢያችሁ ዱብ ይላል፡፡ ዩኒፎርም ለብሰው ትምህርት ቤት እየገቡ የሚያስቸግሩት ወጣቶች እሳቸው ሲደርሱባቸው በመምህራን ኮሌጅ የግንብ አጥር ላይ እንደ ዝንጀሮ ሲሮጡ እሳቸው በድንጋይ ሲያሳድዱ አይተናል፡፡ በግንቡ ላይ መዝለል አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ግንቡን እየረገጡ መሮጥ እንጂ፡፡
ጠያይሞቹን ጥበቃዎችም እናስታውሳለን፡፡ ሁሉም ግን ተፈሪ ነበሩ፡፡ ባይፈሩ ይከበራሉ፡፡ አንድ ቀን ያረፈደ ሰው ያወቀዋል የነሱን ነገር፡፡ ግንብ ዘሎ ለመውጣት ወይም ለመግባት የሞከረም እንዲሁ፡፡ የሆነ ወቅት ትምህርት ቤቱ በሞገደኝነት ይታወቅ ነበር፡፡ በተማሪዎቹ ማለት ነው፡፡ ለዚያም ይሆናል ጥበቃዎቹ ጠንከር ያሉት፡፡
አስተማሪዎቻችንን እናስታውሳለን፡፡ ከሁሉም በላይ ወደማይቀርበት የሄዱትን መምህር ባልከውን የአማርኛ መምህራችንን፡፡ ነፍስ ይማር ብለናል፡፡
ከአስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ
መምህር በላይ ጂኦግራፊ፣ አማረ ታሪክ፣ መኮንን ሲቪክስ፣ ጫኔ ሒሳብ፣ ሙላት ሒሳብ፣ ምንይሉ ስፖርት፣ ሙላት እንግሊዝኛ (ሁለት ናቸው) (ኢኮኖሚክስ፣ ሲቪክስ፣ አይቲና ቢዝነስ መምህራን ስማቸውን የረሳኋቸው) አብርሃም እንግሊዝኛ፣ አብርሃም ጂኦግራፊ፣ ወዘተ
ከዘጠኝና ዐሥር
በኃይሉ ታሪክ፣ በርሔ ኬሚስትሪ፣ ሙላት እንግሊዝኛ (ቀዩ) አማሪ ጂኦግራፊ፣ ስንቅነሽ አማርኛ፣ ዝናቡ ኬሚስትሪ (ነፍስ ይማር) ግሩም ፊዚክስ፣ ምንይሉ ሒሰብ፣ ወንድሙ እንግሊዝኛ፣ ሲቪክስ በትረ፣ ኃይለሚካኤል ቦንጋ ባዮሎጂ፣ ሂሳብ ረጅሙ መምህር፣ ግዑሽ ኬሚስትሪ፣ ሰይድ እንግሊዝኛ፣ ወዘተ፡፡ መምህራን የተለያየ ብሔርና ኃይማኖት ያላቸው፣ ከልዩ ልዩ ቦታዎች የመጡና በብዙ ነገር ውስጥ ያለፉ እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህች ሃገር የተማሩትን ልጆቿን መጀመሪያ ፋሺስት ጣሊያን፣ በኋላ አብዮትና የእርስ በርስ ጦርነቶች በልተውባታል፡፡ በዚህም ምክንያት ታዳጊ ልጆቿ ያለ አይዞህ ባይ ታላቅ ወንድምና እህት እንዲያድጉና የድህነትና ድንቁርና ሰንሰለቱ እስካሁን እንዲቀጥል ግድ ብሏል፡፡ እነሆ ከዚያ ሁሉ መከራ የተረፉት ታላላቆቻችን እኛን ለማስተማር በቁ፡፡ ከብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንም ውሰጥ እኛ ዕድለኞች ነን ማለት ይቻላል፡፡  



መምህር ተፈራ ጋሻው፡- አስረኛና አስራ አንደኛ ክፍል አማርኛ ያስተማሩን መምህር ተፈራ ጋሻው በጣም የምንወዳቸው መምህራችን ናቸው፡፡ አሁንም ደብረ ብርሃን ላይ እንደሚኖሩ ሰምቼ ላገኛቸው ቀጠሮ ይዣለሁ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ከገጠመን የምዝገባ ችግር አንስቶ እስከመጨረሻው ይተባበሩንና በስነምግባር ያንጹን የነበሩ ናቸው፡፡


ርዕሳነ መምህራን አባዲና ካሳና ገብረመድህን ይታወሱኛል፡፡ አብርሃም አማራ ልማት ማህበር ገብቷል ብለውኝ ነበር፡፡ ጋሽ ደመላሽ ጠባሴ ቪክትሪ ኮሌጅ ስለሆኑ አብረን ነን፡፡
ተማሪዎቹም አይረሱም፡፡ 12 ክፍል ሆነን የክፍላችን ቀልደኛው ልጅ ብርሃኑ መኮንን፣ የአስተማሪያችን ልጅ ሜሮን ምንይሉ፣ ጎበዟ ሙስሊሟ ልጅ፣ ጎበዙ ልጅ መዓዛ ወዘተ፡፡ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሚታወቁም ነበሩ፡፡ የሞጃው ተወላጅ የሸዋሉል፣ ሐውለት፣ ዓለም ሰለጠነ ወዘተ ስማቸው ሲጠራ እንሰማለን፡፡ አብዛኛው ተማሪ ከሰሜን ሸዋ ወረዳዎ የሚመጣና በስንቅ የሚማር እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ይሁን እንጂ በሃገሪቱ በነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አለመስፋፋት ችግር ብዙ ጎበዝ ልጆች በትምህርታቸው ሳይገፉ እንደቀሩ ይታወቃል፡፡ በተቻለ መጠን እነሱንም እያፈላለጉ የት እንደደረሱ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
አስተዳደሮቹንስ ማን ይረሳል! ቤተመጻሕፍት፣ ጸሐፊዎች፣ አባዢዎች ሁሉ ስለተረባረቡ ነው ትምህርት ቤቱ በእግሩ መቆም የቻለው፡፡ የተማሪ ህብረት ፕሬዚዳንቶች - የማይረሳውን ኃይሌ ገብረሥላሴን አስታውሱ፡፡ በኛ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ሙሉጌታ ታደሰ ነበር መሰለኝ የኛ ክፍል ልጅ፡፡
የትምህርቱን ጥራት አስመልክቶ በኛ ድክመት ካልሆነ በትምህርት ቤቱ ድክመት ምንም የመጣ ችግር የለም፡፡ በተቻለው መጠን አስተምሮናል፡፡ የዩኒቨርሲቲ እንጂ የሁለተኛ ደረጃ የማይመስል ጥራት ነበረው፡፡ ምን አልባት በአንዳንድ ትምህርቶች ላይ ከታች ክፍል ጥሩ መሰረት የሌለን ልጆች ተቸጋግረን ይሆናል፡፡
በተማርንባቸው ወቅቶች የነበሩትን ክስተቶች፣ ጥፋቱን፣ ልማቱን፣ ቤተመጻሕፍቱን ወዘተ ማስታወስ ቻልኩ፡፡ እናንተም እስኪ አስታውሱ፡፡
ቀይ ዩኒፎርም የለበሰ እልፍ አእላፍ ተማሪ ጠዋት ሠዓት እንዳይረፍድበት በብርድ ሲሯሯጥ፣ ትምህርቱን በትጋት ሲከታተል፣ ረፍት ሲወጣ፣ ለምሳ ሲለቀቅብቻ ሁሉም ታሪክ ነው፡፡ እኔ ዛሬ ለአንድ ሰዓት እንኳን እዚህ ትምህርት ቤት አልቆይም፡፡ ጓደኞቼ፣ አስተማሪዎቼ፣ በትምህርት ቤቱ ምክንያት የማውቃቸው ሁሉ በየስፍራው፣ በየወረዳው፣ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም ዓለም ዙሪያ ተበትነዋል፡፡ በሕይወት የሌሉም አሉ፡፡  እንባ በዓይኔ ሞላ፡፡
እኔና ጓደኞቼ እዚህ ብንገናኝ ከዚያ ወዲህ ስላጣን ስላተረፍነው ነገርም እናወጣ እናወርዳለን፡፡ ሕይወት ምን አተረፈችልን? ምን አጎደለችብን?
ሁላችሁም በተቻላችሁ መጠን ትምህርት ቤቶቻችሁን ጎብኙ፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የተማራችሁባቸውን፡፡ የምታዩትንና የሚሰማችሁን ጻፉልን፡፡
‹‹Pax et Bonum!››
ይህን በትልቁ አዳራሽ ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ወደ ማስታወሻ ደብተሬ ገለበጥኩ፡፡ ትርጉሙንም ከኢንተርኔት ፈለግሁ፡፡ ‹‹Peace and Goodness be with you›› የሚልና ከካቶሊክ ቤተክርሰቲያን ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ‹‹ሰላምና መልካምነት ከእናንተ ጋር ይሁኑ›› የሚል ትርጉምም ሰጠኝ፡፡ 
የነባር ህንጻዎች ጣራ ካማርጀቱ በስተቀር ግንባቸውና አሰራራቸው ጥሩ ነው፡፡ ቅርስም ይሆናል፡፡ የኢጣሊያ ቆይታ በኢትዮጵያ ይጠና ወይም ይታይ ቢባል ትምህርት ቤቱ አንድ መነሻ ነው፡፡ እዚያ ግቢ የነበሩትን የፋሺስት ወታደሮች ብዛትና ዲሲፕሊን ከብላታ ደምሴ ወርቃገኘሁ መጽሐፍ አንብቤያለሁ፡፡
የዚያኔዎቹ ኢጣሊያውያን የሚጠጡት፣ የሚበሉት፣ የሚለብሱት፣ የሚያደርጉት ሁሉ በስርዓት እንደሆነ ከግቢው ሁኔታና ወታደራዊ ደንብ ምን እንደሚመስል ከምንሰማው መገመት ይቻላል፡፡ ያንን ፍላጎታቸውን የሚያሟሉበት ግቢ ይህ ነበር፡፡ አርበኛና እንግሊዝ ሲያሶጧቸው ሰልፍ አሳምረውና አንገታቸውን ደፍተው ‹‹ይሁና!›› እያሉ ነበር፡፡ እነሱ የጀመሩት ስልጣኔ አሁን ስር ሰደደ ወይስ በዚያው ጠፋ? በእነሱ እግር በአርበኛው ልጅ ኃይለማርያም ማሞ የሰየምነው ትምህርት ቤት ያመጣውስ ውጤት እንዴት ይመዘናል? ባላምባራስ አበራ ሠይፈ ያሉኝን እነሆ ‹‹ያንቺ አያቶች ምድር ሰጋጥ የጃንሆይ የግላቸው ርስት ነበር፤ ከርስቱም የሚያገኙትን ለኃይለማርያም ማሞ አዳሪ ትምህርት ቤት ይሰጡ ነበር፡፡››  
የመሰናበቻ ሃሳብ
ትምህርት ቤታችንን ዘወር ብለን ማየት አንዳለብን ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ነገር ታይቶኛል፡፡ የነባር ህንጻዎቹ ጣሪያዎች በሸክላ ጣሪያ ቢቀየሩ ምን ይመስላችኋል? አንዳንድ ያሰብኳቸው ነገሮች አሉ፡፡ በዚህ ላይ መስራት የሚፈልግ ሊያናግረኝ ይችላል፡፡
አመሰግናለሁ፡፡

1 አስተያየት:

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...