ረቡዕ 19 ሴፕቴምበር 2018

ከቤተመጻሕፍት ሠራተኛው ማስታወሻ


ማክሰኞ መስከረም 8፣ 2010 ከሠዓት በኋላ የውኃ ክፍያ ልከፍል በቀበሌ 09 አስተዳደር ግቢ ተገኘሁ፡፡ እዚያም ወረፋ ስጠብቅ አንድ የቀድሞ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ደንበኛ አገኘሁ፡፡ እሱም ምንም እንዳልተፈጠረ ሰላምታ አቅርቦ ዝም አለኝ፡፡ ከወራት በፊት መንገድ ላይ አግኝቼው መጽሐፋችንን መልስልኝ ብዬው መጽሐፍ እንዳልተዋሰ ነግሮ ክዶኝ ነበር፡፡ ዛሬም ይህንኑ ጥያቄዬን ደገምኩለት፡፡ ‹‹መልክ አሳስተህ እንዳይሆን›› አለኝ፡፡ እንዳልተሳሳትኩ ነገርኩት፡፡ ከፈለገም ወደ ቤተመጻሕፍት ሄደን መታወቂያውን እንድናየው ሃሳብ አቀረብኩለት፡፡ በዚህም አልተስማማም፡፡ ‹‹ሌላ ቀን እመጣለሁ›› አለ፡፡
ይህን ምላሽ እያሰላሰልኩ ወደ ቤተመጻሕፍቱ ሄድኩ፡፡ እዚያም ያሉትን መታወቂያዎች ከሌላዋ የቤተመጻሕፍቱ ሰራተኛ ጋር በመሆን በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ለየን፡፡ የተለዩትን መታወቂያዎችም እያየሁ ምሽት ላይ ስልካቸው ላለ ተዋሾች መደወል ጀመርኩ፡፡
ለአንባቢ የችግሩን ሁኔታና ስፋት ለማሳየት ልሞክር፡፡ ቤተመጻሕፍቱ ከመጋቢት 2008 ጀምሮ በስራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት በተዋሱ አንባቢያን ሳይመለሱ ቀርተውበታል፡፡ አንዳንዱ ተዋሽ በመልክ ስለምናውቀው ወስዶ ያስቀረ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መታወቂያ አስይዞ አንድም ሁለትም መጽሐፍ የተዋሰ ነው፡፡ የሚያስቀሩበት ሁኔታም አንድም መጽሐፉን ሳያነቡት ቀኑ እየበዛ ሲሄድ ኪራዩን መክፈል ይከብደናል ብለው፣ አለያም መጽሐፉን የግላቸው ለማድረግ በመደበቅ ወይንም ሸጠው ገንዘቡን ተጠቅመውበት ይሆናል፡፡ በምንም ምክንያት ያስቀሩት በምን እጅግ በርካታ መጻሕፍት ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ አሁን በእጃችን ያሉትን ሁለት መቶ መታወቂያዎች እንኳን ከግምት ውስጥ ብናስገባ የችግሩን መጠን መረዳት እንችላለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንትና ማታ ተውሰው ላስቀሩት መደወል ጀመርኩ፡፡ ካርድ ሞልቼ፣ ፓኬጅ ገዝቼ መሆኑ ነው፡፡ ሌላ ወጪ እያደራረብኩ እገኛለሁ፡፡ ከደወልኩላቸው ውስጥ አንዲት ሰፈሯ ቅርብ የነበረ ልጅ ‹‹ፍሬው›› የተባለውን የአጭር ልቦለዶች ስብስብ መልሳልኝ ሌላ የሚቀርባትን እንደምትፈልግና ካልተገኘም ዋጋውን እንደምትከፍል ነገረችኝ፡፡ ይህች ልጅ አስደስታኛለች፡፡ ሌሎቹም ተስፋ የሰጡኝ አሉ፡፡ በሁለት መታወቂያ የተዋሰው ወጣትም ስልኩ ስላልሰራ ለእናቱ ተደውሎላቸዋል፡፡ ነገሩ የሚገርማችሁ ተመሳሳይ ፎቶ ያለው ልጅ ሁለት የተለያየ ስም እንዴት ኖረው የሚለው ነው፡፡ እናትዮዋ ሲጠየቁ ልጁ ስሙን እንደቀየረና መታወቂያው መጥፋቱን ሪፖርት አድርጎ እንዳወጣ አስረድተዋል፡፡
በየክልሉ ያሉ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ፣ ደብረ ብርሃን የሚኖሩ ሁሉ እየተደወለላቸው ነው፡፡ እስካሁን ሃያ የሚጠጉ ተደውሎላቸዋል፡፡ ማታ ከደወልኩላቸው የአንዱ ሁኔታ ግን አስገራሚ ስለሆነ ስለሱ ብጽፍ የአንዳንዱን ሰው ተፈጥሮ በትክክል ያስረዳል ብዬ አስባለሁ፡፡   
‹‹ሄሎ››
‹‹ሄሎ››
‹‹አቶ …››
‹‹አዎ ነኝ››
‹‹የምደውልለልዎት ከራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡››
‹‹እሺ››
‹‹ከአሁን በፊት መጽሐፍ ተውሰው አልመለሱም ነበር፡፡ እንዲመልሱልን ለመጠየቅ ነው የደወልኩት፡፡››
‹‹እሺ፡፡ እሺ፡፡››
‹‹እባክዎን እንዲመልሱልን፡፡ ወደ ከሦስት መቶ በላይ መጽሐፍ ነው ተዋሾች ያስቀሩብን፡፡››
‹‹ሥኦስት ሙኦቶ አይደለም፡፡ ሥኦስት ሞቶ ሃምሳ ኖ፡፡››
‹‹እንዴት አወቁት፡፡ ሦስት መቶ ነው እንጂ፡፡››
‹‹ቶስኣስታቿል፡፡ ሥኦስት ሞቶ ሃምሳ ብሚል ዩስቶካኮል፡፡››
ይህን ምላሽ ሲሰጠኝ ኮሜዲያን ክበበው ገዳ እንደሚቀልደው ዓይነት ቀልድ እየቀለደብኝ መሆኑ ገባኝና ስልኬን ዘጋሁ፡፡ በዝጋት አላቆምኩም ህብረተሰቡ በቤተመጻሕፍቱ ላይ ባደረሰው በደል ተናድጄ የሁሉንም ንዴት በዚህ ልጅ ላይ ለመወጣት ፈለግሁ፡፡ የዚህም ንዴት ታሪክ እንደሚከተለው ነው፡፡
የአደጋ ጊዜ ተጠሪ የሚለውን የናቱን ስልክ አይቼ ደወልኩ፡፡
‹‹ሄሎ››
‹‹ሄሎ››
‹‹ወይዘሮ … የ… እናት ነዎት?››
‹‹አዎ ነኝ፡፡››
‹‹ከደብረ ብርሃን፤ ከራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ነበር የምደውለው፡፡››
‹‹እሺ››
‹‹ልጅዎት መጽሐፍ ተውሶ አልመልስ ስላለን ነው፡፡››
‹‹ከዩኒቨርሲቲ ነው ከውጪ?››
‹‹ከውጪ ነው፡፡››
‹‹ውይ የኔ ጌታ እነግረዋለሁ ይመልሳል፡፡ ደብረ ብርሃንን በጣም ይወዳል፡፡ በዓል እንኳን እዚህ አልመጣም እያለ እዚያው ነው የሚያሳልፈው፡፡››
‹‹እባክዎት ይንገሩልን፡፡››
‹‹ምንም ችግር የለም፡፡ ያው ልጆች ታውቃለህ፡፡ ረስቶት ምናምን ነው እንጂ የሚሆነው ይመልሳል፡፡››
እንዲህ እንዲህ እያለ ስለልጇ ክፉ የማታወራው እናት ሙገሳዋን ቀጠለች፡፡ በጣም ትሁት እናት ናት፡፡ እኔን በጥሩ መንገድ አናግራኛለች፡፡ የልጇን ጥፋት ግን ልታምን አልቻለችም፡፡ መጽሐፍ የማስመለሴ ነገር ግን ብዙም ተስፋ የሚጣልበት ሳይመስለኝ ቀጠለ፡፡
በንዴትም ለልጁ የሞባይል መልዕክት አከታትዬ ላኩለት፡፡ መጽሐፉን በህጋዊ መንገድ እንደማስመልስ ነገርኩት፡፡ ቆይቶም ደወለ፡፡ ትርፍ ንግግሮችንም ሊናገር ሞካከረ፡፡ እኔም ንብረታችን እስካልተመለሰ ድረስ እንደማንላቀቅ ደጋግሜ ነገርኩት፡፡ አጠገቡ የነበረና ጓደኛው ነኝ ያለ ሌላ ሰው ስልኩን ተቀብሎ ሊያረጋጋኝ ሞከረ፡፡ ልጁ መመረቁን ነገረኝ፡፡ በዚህ ዓመት ትምህርታቸውን ሊከታተሉ ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለሚመጡ ተማሪዎች መጽሐፉን እንደሚልክልኝና ሁለተኛ በዚያ ስልክ እንዳልደውል አሳሰበኝ፡፡ በዚህም ሁሉ መሃል ስናደድና የማደርገውን ሳጣ ጓደኛዬ እያየኝ ይገረማል፡፡ የመፍትሔ ሃሳብ ነው የሚለውንም ይሰነዝራል፡፡
ዛሬ ረቡዕ ደግሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ስለ ልጁ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ አንድ ኮርስ እንደተበላሸበት፣ እንዳልተመረቀ፣ የስነ ምግባር ችግር እንዳለበት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግልኝና ልጁ ሲመጣ መረጃ እንደሚሰጠኝ ተነግሮኛል፡፡ ያኔም ልጁን አግኝቼ መጽሐፌን እንደሚመልስልኝ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
ከምሳ ሰዓት በኋላም ወደ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ጎራ ብዬ ልጁ የተከራየውን መጽሐፍ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ ‹‹የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ›› የሚል የመሪራስ አማን በላይ መጽሐፍ ነው፡፡ ዋጋው 172 ብር ይላል፡፡ ልጁ ትልቁንና ተፈላጊውን መጽሐፍ መርጦ መውሰዱን ተገነዘብኩ፡፡ ይህንንም መራራ እውነት ከዩኒቨርሲቲ ከቃረምኩት መረጃ ጋር አያይዤ ለናቱ ደውዬ ነገርኳቸው፡፡ የእናት ጣጣ!
መልሼ ልደውል ብለው እናት ብዙ ነገር ነገሩኝ፡፡ በልጃቸው እንደሚተማመኑና እንደተመረቀ፣ ጥሩ ጸባይ እንዳለው፣ ለጋስ እንደሆነ ወዘተ አስረዱኝ፡፡ ከአስር በላይ ደቂቃ ተነጋግረናል፡፡ ልጃቸውን እንርተወው፣ ገንዘቤ እንደሚላክልኝ ወዘተ ነገሩኝ፡፡ እስኪ እናያለን ብያለሁ፡፡ ትንሽ አስፈራርተውኛል፡፡ ቢሆንም ንብረቴ እስኪመለስ ወደኋላ የምል አይመስለኝም፡፡
ይቀጥላል፡፡ 
ከጽሑፉ በኋላ
ዩኒቨርስቲውን አሁን ጠየኩ። "የዲፓርትመንቱ፣ የወደቀበት ኮርስ፣ ያለመመረቁ ጉዳይ፣ የሠጠንህ መረጃ ሁሉ ልክ ነው። 101 ፐርሰንት እርግጠኛ ነን። ተማሪያችን ነው። በሁለተኛው ሲሚስተር ተደብቆ መጥቶ ኮርሱን ሊወስድ ነው ተመርቄያለሁ ያለው።" ብለውኛል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...