ሐሙስ 13 ሴፕቴምበር 2018

ደብረ ጥበብ የቴአትርና የሥነጽሑፍ ክበብ


ነሐሴ 27 2010 እሁድ ነበር የዋለው፡፡ በኃይለማርያም ማሞ መሰናዶ ትምህርት ቤት ስምንት ሰዓት ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ምክንያቴም ደብረ ጥበብ የቴአትርና የሥነጽሑፍ ክበብ ያደረገልኝ ጥሪ ሲሆን ከዝግጅቱ ግማሽ ሠዓት ቀድሜ የሄድኩትም የተማርኩበትን ትምህርት ቤት ለመጎብኘት ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱን ጎብኝቼ ያልኩትን ነገር በሌላ ጽሑፌ ያገኙታል፡፡

በሰዓቱ ያልተጀመረው ስብሰባ ጥሩ ምልከታዎችን ለማድረግ ስላስቻለኝ አላማረርኩም፡፡ ከሌላው የከተማችን ክፍል አንጻር በግቢው አጫጭር ህንጻዎች ስላሉ ሰማይ ጥርት ብሎ የታየኝ ድንቅ ትዕይንት ስለነበር ላንዱ የደብረ ጥበብ አባል አሳይቼዋለሁ፡፡ አንደኛው አባላቸው በደብረብርሃኑ የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት ዳንዴው ጨቡዴ የተባለውን ቴአትር ላሰራ እንደሄድኩ እንደሚያውቀኝ ነገረኝ፡፡ ያኔ ተዋናይም ሳይሆን አይቀርም፡፡ የምንሰራት እያንዳንዷ ስራ በሰዎች ልብ ውስጥ ምን ያህል ተቀርጻ እንደምትቀር አየሁ፡፡ የዛሬዋም እንደዚሁ፡፡

ምክክራችን በትልቁ አዳራሽ ተጀመረ፡፡ እርግቦች የሚሯሯጡበት አዳራሽ ጸጥታው ርጋታን አላብሶታል፡፡ የክበቡ አባላትና በጥበብ ዙሪያ የሚሰሩ የከተማዋ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ የዕለቱ ስብሰባ ሃሳብ የመጣው አብረን እንስራ ብሎ በጠየቃቸው በመምህር ሃይማኖት እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ስለ ክበቡ አንዳንድ ገለጻዎች ተደረጉ፡፡ የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን መምህራቸው አቶ ክበባባቸው አነሳስተው በ2008 ማህበሩ የተመሰረተ፡፡ ክበቡ በቴአትርና ስነጽሑፍ ላይ ይሰራል፡፡ አምስት የግጥም ምሽቶችን አዘጋጅቷል፡፡ በጎ ስራ ላይ ተሳትፏል፡፡ የስዕል ኤግቢሽንም አሂዷል፡፡ ደብረ ብርሃን ላይ የቴአትር ውድድር አሸናፊ ሲሆን ክልል የመሄድና የመሳተፍ ዕድል አግኝቷል፡፡

ዝናውን ቀድሜ የሰማሁለት ይህ ክበብ ከዝግጅቶቹ ቀድሞ እንደዚህ ምክክር ማድረጉ የሚያሳድገው እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ በጥበብ ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር ትስስር ለመፍጠር ይፈልጋሉ፡፡ በበኩሌ በትርጉም፣ በስልጠና፣ በትስስርና በቴክኖሎጂ  ላግዝ እንደምችል ቃል ገብቻለሁ፡፡ ከቴአትሩ ሰው አሊሹ ሙሜ ጋር ላስተሳስራቸው ፈለግሁ፡፡ ደብረ ብርሃን እየመጣ አማተሮችን የሚያግዝ ቅን ሰው ስለሆነ እርሱ ነው አእምሮዬ ላይ የመጣልኝ፡፡  ስለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትና እየተንገዳገደ ስላለወ የዘወትር ሐሙስ ምሽቱ የስነጽሑፍ ምሽት ገለጻ አደረግሁ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል ጋር ቢገናኙ፣ ገቢ ቢያመነጩና የጽሑፍ እጥረት አለብን ላሉት ራሳቸው ጸሐፊዎችንን ለማግኘት ቢሞክሩ የሚሉ ምክሮችን ለግሻለሁ፡፡ የአደራጃጀት ጉዳይን አስመልክቶ አስፈላጊውን ህጋዊ ነገር እንደፈጸሙ ተረድተናል፡፡

ከክበቡ ጋር በምንሰራው ስራ አስተዋጽኦአችን ምን ሊሆን እንደሚችል፣ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ምን እንደሚመስልና በአጭር ጊዜ ምን ልንሰራ እንደምንችል ጠይቀውን ውይይት አድርገናል፡፡ ሩቅ ያሉትን የክበቡን አባላት እያቀረቡ እንደሚገኙና አንዳንዶቹንም በቴክኖሎጂው እንደሚያገኟቸው ነግረውናል፡፡ ያው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ዩኒቨርሲቲ ስለገቡ የመበታተን አደጋ አንዣቦባቸው ነበር፡፡ ምን ስነጽሑፋዊ ነገር አላችሁ ብለው ለዕለቱ ባቀረቡት ጥያቄም የተወሰኑ ሰዎች ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡ ክበቡን ከትምህርት ቤቱ ጋር የማስተሳሰር ስራም ሊሰሩ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡ ለህብረተሰቡ አማራጭ የመዝናኛ መንገድ ስለሆኑ ቢጠናከሩ ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው፡፡

‹‹ሰኞ፣ ማክሰኞና ሐሙስ ማታ 11፡30 ጀምሮ በሲኒማ ደብረ ብርሃን ሌላ ስራ ከሌለ በቀር  ስለምንለማመድ ተገኙልን›› ሲሉ ጥሪ አቅርበውላችኋል፡፡ ይህን ውጥን ለጀመሩት ለመምህር ክበባቸው አድናቆቴን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከክፍል በዘለለ የተማሪዎችን ተሰጥኦ የሚያይና የሚያጎለብት መምህር ብዙም ስለማላይ የእርሳቸው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ትስስር ለመፍጠር የምትፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ብታናግሯቸውና አንድ ደረጃ ከፍ እንዲሉ ብታደርጉ ደስተኞች ናቸው፡፡



ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...