2018 ሴፕቴምበር 30, እሑድ

የእንስሳት ሕክምና ወግ



አሰናጅ - መዘምር ግርማ
መስከረም 17፣ 2011፣ በመስቀል ዕለት ማለዳ በናታን ሆቴል፣ ደብረ ብርሃን፣ አንድ እንግዳ አገኘሁ፡፡ እንግዳው ዶክተር ዮሐንስ ሙሉነህ ይባላል፡፡ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ለቃለመጠይቅ ስመኘው ነበርና ዕድሉን ተጠቀምኩበት፡፡ ወዲያውኑ ባለ ሃምሳ ሉክ ደብተርና እስኪርቢቶ ገዝቼ ጥያቄዬን ጀመርኩ፡፡ አጠያየቄም እንደ የሸዋ ፀሐይ ጋዜጣ ሪፖርተርነት ነው፡፡ በቆይታችን ያወጋነውን እንደሚከተለው እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ፡፡

የሸዋ ፀሐይ፡ የት ተማርክ?
ዶክተር ዮሐንስ፡ አርበኞች ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ዩኒቨርሲቲስ?
ዶክተር ዮሐንስ: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረዘይት፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ስለዩኒቨርሲቲው እስኪ ንገረኝ፡፡
ዶክተር ዮሐንስ፡ ነባርና ለረጅም ዓመታት በብቸኝነት በእንስሳት ጤና ዘርፍ ያስመረቀ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ሌሎቹ ዩኒቨርስቲዎች ከ2000 ዓ.ም በኋላ ነው ማስመረቅ የጀመሩት፡፡ ትምህርቱን የሚያጠናክሩ ልምምዶች፣ ስልጠናዎችና ጉብኝቶችን የምንወስደው እዚያው ደብረዘይት፣ አዲስ አበባ ዙሪያና እንደየአስፈላጊነቱ በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች ነው፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ለምሳሌ የት ሄዳችኋል?
ዶክተር ዮሐንስ፡ ብዙ ቦታ፡፡ ለምሳሌ ስለ ገንዲ በሽታ ምልከታ ለማድረግ ወደ ጊቤ በረሀ ሄደን ነበር፡፡ ምክንያቱም በሽታው በአካባቢው የተለመደ ስለሆነ ነው፡፡ ደብረ ብርሃንም የበግ እርባታውን ለማየት መጥተን ነበር፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ የመጨረሻ ዓመት ልምምድ የት ተመደብክ?
ዶክተር ዮሐንስ፡ ኤክስተርንሽፕ የተመደብኩት እዚያው ደብረዘይት ሲሆን፤ የሰራሁትም የጋማ ከብቶች ላይ ነው፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ወደ ሥራው ዓለም እንምጣ፡፡
ዶክተር ዮሐንስ፡ አላጌ TVET ኮሌጅ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ሕጻናት አምባ የነበረው?
ዶክተር ዮሐንስ፡ አዎ፡፡ በሻላና አቢጃታ ሐይቆች አካባቢ ያለ ከመላ ሐገሪቱ ተማሪዎችን የሚቀበልና በግብርና ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ነው፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ የማስተርስ መመረቂያህን በምን ዙሪያ ሰራህ?
ዶክተር ዮሐንስ፡ በወተት ላሞች በሽታ ላይ ነው፡፡ Mastitis የወተት ላሞችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን የወተት ምርትን በመቀነስ ትልቅ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ወደ ደብረ ብርሃን መቼ መጣህ?
ዶክተር ዮሐንስ፡ ከሁለተኛ ዲግሪ በኋላ አላጌ ለአንድ ዓመት አገልግዬ ነው ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2006 ክረምት ላይ የመጣሁት፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ እዚህ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በናንተ የትምህርት ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ዶክተር ዮሐንስ፡ እዚህ የምናስተምረው የእንስሳት ሳይንስ ተማሪዎችን ሲሆን እኛ የጤና ኮርሶችን እንሸፍናለን፡፡ እንስሳት ጤና ላይ ብንሰራ ለአካባቢው ጥቅም ይኖረዋል፡፡ የእንስሳት ጤና ትምህርት ክፍል ቢከፈት በመቶ ሃምሳና ሁለት መቶ ኪሎሜትር ርቀት አካባቢውን ማገልገል ይቻላል፡፡ እስከ አፋርም ድረስ መሄድ ይቻላል፡፡ ለተማሪዎች አንዳንድ የተግባር ምልከታዎችን ወደ ምርምር ማዕከላት በመሄድ እናሳያቸዋለን ፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ አካባቢው ምን ያህል አቅም አለው በእንስሳት ሐብት?
ዶክተር ዮሐንስ፡ እንደሚታወቀው ዞኑ በእንስሳት ሐብት የተሻለ አቅም አለው፡፡ የውጭ ዝርያ ያላቸው  የወተት ላሞች፤ የመንዝ በግ ዝርያ፤ በደጋው አካባቢ በብዛት የጋማ ከብቶች (ፈረስና በቅሎ) ሲገኙ በዞኑ የቆላማ አካባቢዎች ደግሞ ከዳልጋ ከብትና በግ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የፍየል እና የግመል ሐብት አለ፡፡ ከዚህ አንጻር የደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ የደጋ ከፍታ ግብርናን  ቀዳሚ ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ አድርጎ መምረጡ የዞኑን የእንስሳት ሐብት ለመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ በሃገራችን በእናንተ ሙያ ዘርፍ ምን ያህል ተሰርቶበታል?
ዶክተር ዮሐንስ፡ ካለን የእንስሳት ቁጥር አንጻር በቂ ስራ ተሰርቷል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ የደስታ በሽታን (Rinder pest) ከኢትዮጵያ ከማጥፋት አንጻር ስኬት ተገኝቷል፡፡ በአጠቃላይ በሽታዎችን ከመከላከልና የህክምና ስራዎችን ከመስራት በተጨማሪ በዚህ ዘመንም በተመረጡ በሽታዎች ላይ (pest des petitis ruminants/ PPR) የማጥፋት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህ ስራ ላይ የሃገር በቀል እና የውጪ ድርጅቶች በዘርፉ በጋራ እሰሩ ይገኛሉ፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ጥሬ ስጋ መብላትን አስመልክቶ የምትለን ነገር ካለ፡፡
ዶክተር ዮሐንስ፡ እንደ ባለሙያ ጥሩ አይደለም ባይ ነኝ፡፡ የበሽታ ጉዳይ ስላለ አይበረታታም፡፡ እንደ ባህል የተለመደ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሰረቱ ንጹህ ስጋ ከሆነ መብላቱ ችግር ላያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን እርድ በብዛት በየቤቱ ስለሚካሄድ ንጽሕናውን ማረጋገጥ ስለማይቻል አስቸጋሪ ነው፡፡  
የሸዋ ፀሐይ፡ የቲቢ በሽታ ጉዳይ ከወተት ጋር እየተያያዘ የሚነሳ ሆኗል፡፡ የችግሩ መጠን እንዴት ነው?
ዶክተር ዮሐንስ፡ አስቸጋሪ በሽታ ነው፡፡ ከሰው ወደ እንስሳ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው፡፡  በአብዛኛው በትንፋሽ የሚተላለፍ በሽታ ነው፡፡ በወተትም ይተላለፋል፡፡ ወተቱን በተገቢው መንገድ ማፍላትና መጠቀም አንዱ የመከላከያ መንገድ ነው፡፡ በ72 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለ15 ደቂቃ ቢፈላ ወይም ፓስቸራይዝድ ቢደረግ ሊጠፋ ይችላል፡፡ እንስሳቱን ማስመርመር ያስፈልጋል፡፡ በሽታው ካለባቸው መዳን ስለማይችሉ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ከእንስሳ ጋር የሚኖረን ቀረቤታ በአብዛኛዉ ጥንቃቄ ያለበት መሆን ይኖርበታል፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ የውርጃ በሽታም ተመሳሳይ ተፈጥሮ አለው ይባላል፡፡
ዶክተር ዮሐንስ፡ አዎ፡፡ የውርጃ በሽታ ወይም ብሩሴሎሲስ እንደ ሳንባ ነቀርሳ ሁሉ ሰውንም እንስሳትንም ያጠቃል፡፡ በወተትና በንክኪ ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ ሰውንም ሆነ እንስሳትን መሃን ያደርጋል፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ እንስሳትንና ሰውን በአንድነት የሚያጠቁ በሽታዎች መጠን እስከምን ድረስ ከባድ ይሆን?
ዶክተር ዮሐንስ፡ እነዚህ ሰውንና እንስሳን የሚያጠቁ በሽታዎች Zoonotic disease ይባላሉ፡፡ ከ75% በላይ የሚሆኑት የዓለማችን በሽታዎች Zoonotic ናቸው፡፡ ሰማንያ በመቶ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው፡፡ ከ Zoonotic disease መካከል እንደ የእብድ ዉሻ በሽታ(Rabies)፡ አባሰንጋ ( Anthrax) የሳንባ ነቀርሳ (Tuberculosis ) የውርጃ በሽታ(Brucellosis) እና የኮሶ ትል (Taeniasis) መጥቀስ ይቻላል፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ሙያችሁ አስፈላጊው እውቅና ተሰጥቶት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ይወጣ ዘንድ ምን መደረግ ይኖርበታል?
ዶክተር ዮሐንስ፡ በእርግጥ አርብቶአደሩ በተወሰነ ያውቀዋል፡፡ አስፈላጊነቱም ምንም አያጠያይቅም፡፡ በመንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ያው ለብዙ ጉዳይ መንግስት ይባላል እንጂ ሁሉም አካላት ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ካለን ሃብት አንጻር መጠቀም አለብን፡፡ ባለሙያው ተገቢውን ድጋፍ ካገኘ ብዙ ስራ መስራት ይችላል፡፡ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እና የላቦራቶሪ እቃዎች በየወረዳው መሟላት አለባቸው፡፡ በተጨማሪ ክትባት ለተወሰነ ጊዜ የሚቀመጥበት ያስፈልጋል፤ ለዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ በወረዳዎች ላይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክትባቶች በተገቢው ሁኔታ ካልተቀመጡ እና ተገቢውን የሙቀት መጠን ካላገኙ ይበላሻሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሀብት ብክነትን ከማስከተል በተጨማሪ በሽታዎች እንዲስፋፉ እድል ይሰጣል፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ በእንስሳት ህክምና ዘርፍ ከተመደቡ በኋላ ሰዎች የሚሰማቸውን ነገር ታዝበህ ይሆን?
ዶክተር ዮሐንስ፡ ሳይፈልግ የሚገባ ይኖራል፡፡ ከገባ በኋላ ግን መውደድ ይኖርበታል፡፡ ስትመረቅ ደስ ብሎህ መውጣት አለብህ፡፡ ሳይፈልጉት ገብተው ነግር ግን ወደውት ጠንክረዉ ሰርተው የተሻለ ውጤት እያገኙ የሚመረቁ ብዙ ናቸው፡፡ ሙያውን ስታውቀው ነው መውደድ የምትችለው፡፡ ዘርፉ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ ወደፊት ምን ይደረግ?
ዶክተር ዮሐንስ፡ መሟላት ያለባቸው ነገሮች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ የአቅም ውስንነት ቢኖርም በተቻለው አቅም ጥረት መደረግ አለበት፡፡ የውጪ ድርጅት እገዛ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ግን መንገድ ያስይዘናል እንጂ ሁሉንም ነገር መስራት አይችሉም፡፡ በህብረተሰብ ውስጥም ብዙ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ከ Zoonotic disease ፤በሽታን ከመከላከል እና እንስሳትን ከማሳከም አንጻር፡፡  ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፤ ያንን ለማሻሻል ከሰራን ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡
የሸዋ ፀሐይ፡ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ዮሐንስ፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡


2 አስተያየቶች:

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...