ቅዳሜ 21 ፌብሩዋሪ 2026

ሰቆጣ

 

የሰቆጣ ሰዎች በድርቅ ምክንያት በ2008 ዓ.ም. ተፈናቅለው ደብረብርሃን እንደመጡ አንዷ ተፈናቃይ የነገሩኝን ከቆየ ማስታወሻዬ አገኘሁት፡፡

‹‹ክረምት ሲመጣ ተበዳድረን ነው፡፡ ሐብታም የሆነ ችግርን ሊገፋው ይችላል፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ክፈሉ ይሉናል፡፡ እኛ ግን የሚከፈል የለንም፡፡

እርዳታው ከመንግስት ይወጣል መሰል፡፡ ለእኛ ግን አይደርሰንም፡፡

እርዳታ እንደሚያስፈልግ ያወቅነው በሰኔ ነው፡፡

ከመምጣታችን በፊት ከብቶቻችንን አርደን በላን፡፡ የሚጠጣ ውሃ የለም፡፡

እዚህ መጥቼ ቁጭ ብዬ እስከ 7፡00 ድረስ አለቀስኩ፡፡ ወንድሜ ‹ምን አባሽ ያነፋርቅሻል! ሄደሽ እንሰዉ አትለምኚም እንዴ!› አለኝ፡፡ አገሬ ልሂድ ብለው ‹እንዴት አድርገሽ? 300 ብር ከየት ታመጫለሽ?› አለኝ፡፡

አገሩ አዝመራው ጥሩ ነው ስንባል ጊዜ ወደዚህ ወደ ደብረብርሃን መጣን፡፡

ብርድ ሞትን እዚህ፡፡››

አሁንም አሉ፡፡ መፍትሔ ቢፈለግላቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

 

ዓርብ 20 ፌብሩዋሪ 2026

ቲፕ ውዴታ ወይስ ግዴታ?

 የቲፕ ሃሳብ የመጣው ከዉጪ አገር ይመስለኛል። ሦስት ዉጪ አገር የኖሩ ሰዎች ያወጉልኝን ወይም የጻፉትን ላጋራችሁ።



‎ሀ. አንድ ሰው ያወጉልኝ፦ አንድ ቦታ ዕቃ ገዝቼ ዋጋው 99 ሳንቲም ስለነበር 1 ሳንቲሟን ትቻት ሄድኩ። ባለ ሱቁ ጠርቶ መልስህን ውሰድ አለኝ። ተወው አልኩት። እሱም ተገረመ። ከአስተያየቱ እናንተ ጥቁሮች የማታድጉት ገንዘብን ስለማታከብሩ ነው የሚል ነገር ተረዳሁ።
‎ለ. ሌላዋ ደግሞ፦ አስተናጋጅ ሆኜ ሰርቻለሁ።  ሳስተናግድ ሂሳቡን ብቻ ከፍሎ ሊሄድ ቢሞክር ቲፔስ? እለዋለሁ። አንድ ምግብ ዋጋው አስር ዶላር ቢሆንና እኪሴ ያ ገንዘብ ብቻ ካለኝ ገብቼ አላዝም። ምክንያቱም ቲፕ የምሰጠው የለኝም።
‎ሐ. ሌላው የነቢይ መኮንን መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ሲሆን ደሞዝ የማይከፍሉና በቲፕ ብቻ የሚያኖሩ ሆቴሎች በአሜሪካ መኖራቸውን አንዷ አስተናጋጅ እንደነገረችው የጻፈበት ነው።
‎መ. በቲፕ ጉዳይ ላይ ተከራክረንበትም እናውቃለን። 'A Christmas Carol' የተባለውን ድርሰት ያነበብን ሰሞን ጎራ ለይተን ተከራክረናል። ጥገኝነትን ያመጣል ያልን ነበርን። ለሚሰሩ ሰዎች እገዛ ማድረግ ጥሩ ስለሆነ ይበረታታል ያልንም እንዲሁ።
‎አሁን አሁን ግን የዉጪው ባህል ጥንቅቅ ብሎ ገብቷል። ለተስተናጋጅ ብጥስጣሽ ብሮችን መመለስ ተለምዷል። እነዚያን ብሮች ባለታክሲ አይቀበላችሁም። ሌላም ቦታ አይሰሩም። አንድ ቀን ቲፕ ሰጥቶ በቀጣዩ ቀን መዝለል አይቻልም። ዓይን ያወጣ ብልጣብልጥነት ሰፍኗል። ትኩስ ነገር አዛችሁ መቶ ብር አውጥታችሁ ጠረጴዛ ላይ ስታስቀምጡት ይወስዷትና መልሱ በዚያው እንዲቀር ይፈለጋል። ይህን ጉዳይ ባለሃብቶቹ ይወቁ አይወቁ አናውቅም።
‎እናንተስ ምን ገጠማችሁ?
‎ሃሳቡን ትጋሩታላችሁ?

ማክሰኞ 10 ፌብሩዋሪ 2026

ዉሻና ሰው

 ‎ዉሻና ሰው

‎ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዉሾችን አስመልክቶ እየተካሄደ ያለ ዘመቻ መኖሩን በማህበራዊ ሚዲያ እንመለከታለን። ዉሾቻችን ተገደሉበትን ያሉ ሰዎች እያለቀሱ የለቀቋቸው ቪዲዮዎች ታይተዋል። ንፍሮም የታየበት ቦታ አለ። ይህን የዉሾችን መግደል የተቃወሙ እንዳሉ ሁሉ ያፌዙበት ወይም ያቃለሉት አሉ። ለምን ታፌዛላችሁ ብለውም የተቆጡ የዉሾች ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው ቁጣቸውንና ስድባቸውን አውርደዋል።

‎በዚህ አጊጣሚ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። እንደ ህብረተሰብ የራሳችን ዉሻ የሚኖረን ጊዜ አለ። ቤት ጠባቂ ነው። በቂ ምግብ ላይሰጠው ወይም እንክብካቤ ላይደረግለት ይችላል። የሌላን ሰው ዉሻ ግን በፍርሃት እናያለን። አሳደንም በድንጋይ እንመታለን። እኔም የተለየሁ አይደለሁም። ሳሲት ሳድግ አንዲት የጋሽ ማንደፍሮ ዉሻ ነክሳኛለች። የነከሰችኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ሙጃ ቆርጬ ላመጣ ስሞክር የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነበር። ከትምህርት ቤታችን ጎን ባለው ክሊኒክ ታከምኩ። ያከሙኝ የሐኪም ቤቱ ዘበኛ ጋሽ አድማሱ ነበሩ። ሌላ ቀን ለሥራ ዘመቻ ወደ ችግኝ ጣቢያ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ስንሄድ መንገድ ላይ አንድ ዉሻ ያልፍ ነበር። በርካታ ተማሪዎች በድንጋይ መቱት። ደሙ ፈሶ ሞተ። ተዉ ያለ መምህር አልነበረም።

‎ሌላ ቀን አንድ አሜሪካዊ በአገራቸው የዉሻ ዋጋ እስከ 5,000 ዶላር እንደሚደርስ ነገሩኝ። ጉግል ሳደርግ ልክ ነው። ከእኛ አገር የበሬ ዋጋ በለጠ። የዉሻና ድመት ምግብ ከሱፐርማርኬት የሚገዛ ሲሆን በዓመት እስከ 68 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። በአንድ ወቅት ያየሁት የአውስትራሊያው የዉሻና ድመት ምግብ ከወቅቱ የኢትዮጵያ በጀት ይበልጥ ነበር።

‎በአገራችንም በሠይፉ ሾው የቀረበውን ዉሻ አርቢ አይተናል። ዉድ ዉሾችን ከዉጪ ያስመጣል። ያሳድጋል። ያረባል። ይሸጣል። የዉጪ ዜጎች በአዲስ አበባ በተባለው ቡድንም ውስጥ በመኪና የተገጨ የጎዳና ዉሻ ሲኖር ጠቁሙኝ እያለ ሲጠቆም ሄዶ የሚያክምና በዚያውም ማስታወቂያ የሚሰራ ሐኪም አለ። በቅርቡ በቲክቶክ ያየናት አንዲት ባለዉሻ በቀዶ ሕክምና ወቅት ማደንዘዣ አሰጣጡን አሳስቶ ዉሻዬን ገደለብኝ ስትል ያቀረበች ሴት አይተናል። ዶክተሩም ይቅርታ ጠይቆ ቪዲዮ ለቋል። ሥራው ስለሆነ ስሙን ማደስ ስለላበት ነው። ለዉሻቸው ከልኳንዳ ስጋ የሚገዙ እንዳሉ እናውቃለን። ደብረብርሃንም አንድ ሰው ነበር። ወገኖቼ ይህ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ወግ ነው። ከአንድ ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ አለው የሚባለው ብዙኃን ኢትዮጵያዊ በዚህ የቅንጦት ሕይወት ላይ ጥያቄ ቢያነሣ ማንም አይሰማውም። ጉዳዩ አከራካሪ ነው። ክርክሩ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ከሉሉ የጀመረ ነው። የወሎና የትግሬ ሕዝብ እፍኝ ጥሬ አሮበት በሜመዳው የአሞራ ሲሳይ ሆኖ ሳለ የአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ሞቶ ሐውልት ተሰርቶለታል፤ ይለቀስለታል፤ በሚል የቀረበውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ ያስታውሷል።

‎በዘመነ ኢህአዴግም ሰልፍ ተከከክሎ ሳለ ሚሚ ስብሃቱ የተገኘችበት የእንስሳት መብት ሰልፍ ይታወሳል። ሰዎች ምግብ፣ ሰብዓዊ መብት፣ መጠለያ አላገኙም በሚባልበት አገር የተነሣ ጥያቄ ስለሆነ ነው የተወዛገበነው።

እሑድ 8 ፌብሩዋሪ 2026

የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?

 የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?


ትምህርት አጉል አቅጣጫ እየሄደች ይመስላል። ለዚህ ማሳያ የተወሰኑ ክስተቶችን ላንሳ። ከሰሞኑ አንዲት መምህር እያስተማረች የነበረበት ክፍል ለፈተና ተፈልጎ እንድትወጣ ስትጠየቅ በጥያቄው ተስማምታ ስትወጣ አየኋት። አንዱ ተማሪ ዲቫይደሯን፣ ሌላኛው ፕሮጀክተሯን ይዘውላት  ይሄዳሉ። አንዳቸውም ደብተር አልያዙም። የያዙትን ለመገመት አትቸገሩም - ስማርት ስልኮችን ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ ተማሪዎች ነበሩን። ሳስተምር ሰሌዳውን ፎቶ ያነሱታል። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሆነ ሰነድ ምናልባት የክፍለጊዜ ድልድል ሊያሳዩኝ ስልኮቻቸውን ሲከፍቱ የምናስተምራቸው መምህራን ሰሌዳው አጠገብ ቆመን ያነሱን ፎቶዎች አሉ። እኔ ማክሰኞና ሐሙስ ክፍለጊዜ ቢኖረኝ የአንዱን ሳምንት ጽሑፌን ከሌላው እንዴት እንደሚለዩት ግራ ይገባኛል። ከኔ በፊት ወይም በኋላ ያስተማሯቸውንስ? ነገሩ ግራ ይገባል። በፕሮጀክተር የሚያስተምሩ መምህራንን ፓወርፖይንት በስልካችን ይዘናል ብለው ደብተር የማይዙት የሌሎች ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችም ሆኑ እኛ የሥነጽሑፍ ተማሪዎች ደብተር አለመያዛቸው ምንም ምክንያታዊ ሆኖ አይታየኝም። መጻፍ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው። መምህራን ከፓወርፖይንት ዉጪ የሚያስተምሩት ነገር አለ። መጻፍ የመማር አካል ነው። አንዱን ትምህርት ከሌላው ለይተን ማስታወሻ መያዝ ይገባናል። ትምህርት ምን ዓይነት አጉል አቅጣጫ እየሄደ ነው? የትምህርት ዓላማ አእምሮን ማልማትና ችግርፈቺ ዜጎችን ማፍራት ነው። ሰናይ ተግባር የሚሰሩ ወጣቶችንም መፍጠር አለበት። ለዚህ ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ ምንም ሳይሰስቱ መማር ተገቢ ነው። ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ በአሳይመንት፣ በንባብ፣ በፈተና፣ በምርምርና በሌሎችም የትምህርት ጉዳዮች እያመጣ ያለውን ችግር ትገምታላችሁ ብዬ አልነካካሁትም። ፈተናው እውነት ሀሰትና ምርጫ ሆኖስ ተማሪዎች ምን ያህል ለማሰብና ቤተመጻሕፍት ገብተው ከፓወርፖይንት በላይ ለማንበብ ይነሳሳሉ?

በማካካሻ (remedial) ፕሮግራም የሚባክነው የአገር ሀብት ሌላው ነው። ተሻለሎ ለማይሻሻል ክህሎት የተማሪዎች ዕድሜና የአገር ሀብት ይባክናል። በትምህርት ዘርፍ ማየት ያለብን በርካታ ጉዳዮች አሉ። 

የከተማ ልጆች በኮምፒውተር እየነተፈኑ የገጠሩ በወረቀት መፈተኑ ያመጣው ኢፍትሃዊነት ዘንድሮ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት ባስጠላቸው የከተማ ወጣቶች ለመሞላታቸው ምክንያት አልሆነ ይሆን?  ኮምፒውተሩ ፈተና የሚሰሩ ሶፍትዌሮች እንዳሉት የተፈተነ ተማሪ ነግሮኛል። እንወያይበት።

ሰቆጣ

  የሰቆጣ ሰዎች በድርቅ ምክንያት በ2008 ዓ.ም. ተፈናቅለው ደብረብርሃን እንደመጡ አንዷ ተፈናቃይ የነገሩኝን ከቆየ ማስታወሻዬ አገኘሁት፡፡ ‹‹ክረምት ሲመጣ ተበዳድረን ነው፡፡ ሐብታም የሆነ ችግርን ሊገፋው ይችላል...