ዓርብ 13 ኖቬምበር 2026

‎ዉጪ ስለሚኖሩ ወገኖች አስተሳሰብና ድርጊት ከታዘብኩትና ከሰማሁት

 ‎

‎ዉጪ ስለሚኖሩ ወገኖች አስተሳሰብና ድርጊት ከታዘብኩትና ከሰማሁት

‎

‎ለመሆኑ ከአገሩ ዉጪ ያለው ሰው በአገሩ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ለማምጣት ይፈልጋል? ብለን ብንጠይቅ መልስ ማግኘቱ ከባድ ይሆናል። ይህ ጉዳይ ሲያሳስበኝ ቆይቶ በተወሰነ መልኩ ለመመለስ ጥረት አድርጌ ነበር። በመሆኑም እኔ እስካሁን ካየሁት፣ ካጋጠመኝና ከታዘብኩት ይህን ጫር ጫር አደረግሁ። አገር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጠየቅሁ። በዉጪ ያሉትንም ለማማከር ጥሬያለሁ። እስኪ ይህችን አጠር ያለች ጽሑፍ አንብባችሁ በአስተያየት አዳብሩልኝ። ከዚያም ለማስፋት እጥራለሁ።

‎በተለያዩ ዘርፎች እንመልከተው።

‎

‎በማህበራዊና ኃይማኖታዊ

‎ከዉጪው ዓለም የወደዷቸውን ማህበራዊ እሴቶች ለማስተላለፍ ይጥሩ ይሆናል። ማለትም ከህብረተሰቡ አኗኗር፣ አለባበስ፣ አስተሳሰብ ጋር በተያያዙ ጉዳየች ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይችላሉ። በንግግራችሁ የእነሱ ቋንቋ ተጽዕኖ እንዲኖርባችሁ ሊያደርጉ ይችላሉ። እነሱ እንደሚለብሱት ሊያለብሷችሁ ይችላሉ። ኃይማኖት ከቀየሩ ሊያስቀይሯችሁ ይችላሉ። ባሉበት ኃይማኖት አክራሪ ሆነው እናንተን አክራሪ ሊያደርጓችሁ ይችላሉ።

‎የሥራ ባህል በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ፣ ስንፍና እንዲቀር፣ ሰዎች የመማርና የመመራመር ልምድ እንዲኖራቸው የሚያስቡ አሉ። ይህ ሃሳብ ከልብ መሆኑን ማወቅ ያዳግታል። ከልብ ከሆነ ለምን ወደ ተግባር እንዲቀየር ስራ አልጀመሩም ያስብላል። ከዉጪ መጥተው የስራ ባህላችንን ለመቀየር የጣሩ ስራ አስኪያጆች፣ ስራ ፈጣሪዎች ወዘተ በተወሰነ መጠን አየሰተናል። አቶ ኤርምያስ አመልጋ አመጋገባችንን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስራዎችን ሲያስተዋውቅ አይቻለሁ። የሚድሮኩን ዶክተር አረጋንም መጥቀስ ይቻላል። ሰሞኑን አራስ ቤቷን ደጅ ደጁን እያከበረች ያለችውንና ራሷን አውሮፓዊት ሀበሻ ብላ የምትጠራውን ኬኔሳ ሙሉነህንም እንጥቀስ።

‎ከአብዛኛው ኦሮሞ ዲያስፖራ በተቃራኒው መሆኑ ነው።

‎

‎ምጣኔሐብታዊ?

‎በገንዘብ ችግር የተሰደደው ሰርቶ ወደ አገሩ ተመልሶ ቋሚ ነገር ማፍራት ስለሚፈልግ ገንዘብ ሊልክ፣ መጥቶም ሊያለማ ይችላል። እዚያ እየለፉ ገንዘብ በመላክ እዚህ ያለውን ስራ ፈት ሊያደርጉም ይችላሉ። የማይፈልጉትን ልብስ በመላክ፣ የማይፈለግ መጽሐፍ ልገሳ በኮንቴነር በመላክ በማመቻቸት ዕቃ መጣያ ያደረጉንም አለ።

‎

‎ፖለቲካዊ

‎አገራቸውን ሲያስቡ በፖለቲካ ዓይን ብቻ የሚመለከቱ አሉ። ስለዚህ ባሉበት የዲያስፖራ ፖለቲካ በድጋፍም በተቃውሞም ማደራጀት፣ በርቀት በገንዘብና በቴክኖሎጂ ማገዝን ልብ ብለው ሊሰሩበት ይችላል። አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ችግሮችም ሆኑ ለውጦች የዲያስፖራው ውጤት የሆኑበትም አጋጣሚ ብዙ ነው።

‎

‎ፈጠራ

‎በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በፈጠራ፣ በሥነጽሑፍ  ልህቀት በማሳየት አርአያ ሊሆኑ ይችላሉ። በየሚዲያው ሲቀርቡ ያኮራሉ፤ ያስተምራሉ። በጀርመን ድምፅ፣ በአሜሪካ ድምፅ፣ በሸገር ኤፍኤም ቀርበው ወይም ታሪካቸው ቀርቦ ያነቃቁ አሉ። የሌላቸውን ዲግሪ አለኝ ብለው ያጭበረበሩና እስካሁን ያልተነቃባቸው አሉ። በየዘርፉ አይነኬ የሆኑ አጥፊ ሆነው ያልተመሰገኑ አሉ።

‎

‎

‎ከላይ ያሉትን ስንመልስ መቼ፣ ለምን፣ እንዴት ሄዱ የሚለው ወሳኝነት አለው። በቦሌ ወይስ በባሌ? በደስታ ተሸኝተው ወይስ በእግር ከሞት አምልጠው? ስለአገራቸውስ ምን ያስባሉ? የሚሉት ወሳኝነት አላቸው። በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የተሰደዱ ምን ያስባሉ? በዲናው መንግስቱም ሆነ በመዓዛ መንግስቴ ልቦለዶች ታሪካቸው በተወሰነ ተነካክቷል። በደርግ የተሰደዱትን ከፖለቲከኞች እስከ ኢኮኖሚ ስደተኞች ልብ በሉ። ስደት የጀመረውስ በቅርብ አስርት ዓመታት አይደል? በኢህአዴግ የተሰደዱም አሉ። ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች፣ ለትምህርት የተሰደዱ ወዘተ። አሁንም የቆመ አይደለም የስደት ነገር። ወደ አረብ አገርም ሆነ ወደ ምዕራቡ የተሰደዱ አሉ። የመሰረት በቀለን 'ቋንቋ' የተሰኘ ቀልድ መመልከት ለቤተሰብ የአረቡ ወይስ ምዕራቡ ጥቅም  ያመዝናል የሚለውን ለመገንዘብ ያስችላል።

‎

‎በተለያዩ አጋጣሚዎች ከያዝኩት ማስታወሻም ሆነ ሰዎች ከነገሩኝ የተለያዩ ዉጪ አገር የሚኖሩ ሰዎች አስተሳሰብና ንግግር እንደሚከተለው ተሰንዷል

‎

‎አሉታዊ

‎"የኢትዮጵያን ህዝብ ተቀይሜዋለሁ።"

‎"አማርኛ መርሳት እፈልጋለሁ።"

‎"ልጄ አማርኛ አይችልም።"

‎"እባክህ ከኢትዮጵያ ተፈናቃይ ይልቅ የጋዛ ጉዳይ ነው የሚያሳስበኝ።"

‎አገር ውስጥ ያለውን ሰው በጉልበቱ እንጂ በእውቀቱ እንደማያገለግል የሚያስቡም አሉ። ይህን የነገርኩት አንድ እዚህ ኢትዮጵያ ያለ ሰው ይህ አስተሳሰብ ያው የነጮቹ መሆኑ ነው ብሎኛል።

‎

የአንድ ዉጪ አገር ሰላይ ነው የተባለ አለ።

‎

‎አዎንታዊ

‎በዓለም ዙርያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይኖራሉ ያለኝ አለ።

‎በድርቅና በህገወጥ ስደት ስለሚሰቃየው በየቀኑ መረጃ የሚያሰናዱ አይቻለሁ።

‎የምዕራቡን የትምህርትና የቴክኖሎጂ ዕድል ገጠር ያሉትን ለማገዝ መጠቀም አለብን የሚሉና የሚሰሩ

‎እንደ ብዙዎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያሰባስቡና የሚሰጡ አሉ።

‎መጥቶ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚመኝም አለ።

‎

‎

‎

‎

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

‎ዉጪ ስለሚኖሩ ወገኖች አስተሳሰብና ድርጊት ከታዘብኩትና ከሰማሁት

  ‎ ‎ዉጪ ስለሚኖሩ ወገኖች አስተሳሰብና ድርጊት ከታዘብኩትና ከሰማሁት ‎ ‎ለመሆኑ ከአገሩ ዉጪ ያለው ሰው በአገሩ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ለማምጣት ይፈልጋል? ብለን ብንጠይቅ መልስ ማግኘቱ ከባድ ይሆናል። ይህ ጉዳ...