ረቡዕ 8 ፌብሩዋሪ 2017

ኢትዮጵያዊ ሥም ላላቸው ሠዎች ብቻ የተዘጋጀ የመዝናኛ መርሃግብር በራስ አበበ አረጋይ ቤተመፃሕፍት፣ ደብረብርሃን። (Grand Party for Those of You Who Are Named in Ethiopian Languages)




በዓላማው የምትስማሙ ሁሉ ሃሳቦችን እንድትሰነዝሩ ይሁን። አገርኛ ስም ተጠልቶ ህፃናት ለመጥራት እንኳን የሚከብዱ የውጪ ስሞች እየወጡላቸው ሲሆን ትላልቆችም ስም በመቀየር ዘመቻ ላይ ይገኛሉ። እንደኔ አስተያየት ከአገራችን ስሞች ሁሉ የአማርኛ ስሞች በጣም አደጋ ላይ ናቸው። አንደኛ በአማርኛ አፍ የማይፈቱ ህዝቦች ወደየራሳቸው ቋንቋዎች እየተመለሱ ነው። (ያም አገርኛ ሥም ነው በነገራችን ላይ።) የአማርኛ ስም አዲስ ለሚወለዱ አለማውጣት ብቻ ሳይሆን ነባሮቹም ሲቀይሩ አይተናል። በጣም ወደሚቀናን ቋንቋ መመለስ ብዙም ተቃውሞ ላያስነሳ ይችላል፤ የዘር ጥላቻ እስከሌለው ድረስ። ምንም በማንናገረው ቋንቋ ሥም ማውጣት የምን ይባላል? በአጋም አይዘመዱን በቀጋ! ራሱን ጀምስ ንጉጊ ብሎ ይጠራ የነበረው ኬንያዊ ደራሲ ወደራሱ ቋንቋ ተመልሶ ንጉጊ ዋቲዮንጎ በሉኝ በማለቱ ድንቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ይህን ዓይነቱን ነው ወደራስ መመለስ የምለው፡፡ ወላጆቻችሁ በሰየሟችሁ ምክንያት ግን ልንወቅሳችሁ እንደማንችል እዚህ ልብ እንድትሉልን ያሻል!
ስማቸውን ለመቀየር የሚገደዱት ወገኖቻችን ይህን የሚያደርጉት በከፍተኛ የስነልቦና ጫና ውስጥ ሆነው መሆኑን እገነዘባሁ፡፡ የተቃጣብንን ጥቃት መከላከል የምንችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የነዚህ ወገኖቻችን መልካም ትብብርና ቀና አስተያየት ያስፈልገናል፡፡ ማንንም ለማሸማቀቅ አስቤ ወይንም ምንም ዓይነት የጥላቻ አስተሳሰብ ለማራመድ አስቤ እንዳልሆነም ይረዱልኝ፡፡ ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ!
It would be unwise to inform you, my fellow country men and women, that we have been calling ourselves and our loved ones in imported names. Everyone knows that this time around in our country naming oneself or one’s children in local languages has been considered as a grave error. It is we who have to tackle this challenge meant to damage our honor, culture and identity. For this reason, we feel honored to call a party to celebrate our cherished names and denounce the act of systematically imposing other languages and cultures on our people. We know that this causes anger among those people who stand against us, however, we should stress our belief and identity in action.
ይህ ጽሑፍ በፌስቡክ ላይ እንደወጣ የሚከተሉትን ምላሾች አስተናግዶ ነበር
የሀገራችንን ስሞች አደጋ ላይ ከጣልዋቸው ጉዳዮች አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ይመስለኛል፡፡ በርካታ ሰዎች ለልጆቻቸው፤ ስም ሲያወጡ የስም ምንጫቸው መጽሀፍ ቅዱስ ነው፡፡ በዚህም መሰረት፤ ይዲዲያ፤ ቢታኒያ፤ኑሃሚ፤….. የመሳሰሉ ስሞች በከፍተኛ ፍጆታ እየተጠቀምንባቸው፤ እንገኛለን፡፡ እኔ እንደሚገባኝ መጽሐፍ ቅዱስ፤ የተጻፈው፤ ለመላው ዓለም ክርስቲያኖች በእስራኤልና አካባቢዋ እግዚአብሔርና ቅዱሳን፤ያደረጉትን ተጋድሎና ሩጫ ነው፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ስምም ሆነ ባህል ድርጊቱ የተፈጸመበትን ቦታ የሚገልጽ፤እንጂ ኢትዮጲያዊ ስምን የሚተካ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጲዊያን ከሌላው ዓለም ልዩ የሚያደርገን የራሳችን በርካታ መገለጫዎች ያሉን በመሆናችን ነው፡ከነዚህ ደግሞ አንዱ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህልና ማንነትን ተከትለው የሚሰየሙባቸው ስያሜዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በክርስትናም ከሆነ ብዙ ኢትየጲያዊ ክርስትና መሰረት ያደረጉ ስያሜዎች አሉን፡፡ ለዚህ ትልቁ ምሳሌ የበርካታ የትግራይ ክልልና የሌሎች መሰል ክልል ተወላጆች ስም ነው፡፡ ወልደገብርኤል.. /ገብርኤል፣ ለተማርያም፤ገብረእግዚአብሔር፤ተከስተ /ማርME… ታዲያ ይህንን መሰል ኢትዮጲዊ፤ኦርቶዶክሳዊ ስያሜ እያለንን፤ ለምንድነው፤ ፒተር፤ጆን፤ቢዮንሴ፤ማይክል ወዘተ እያል ስማች መጤ የምናደርገው፡፡
ከአማርኛ ስሞች በተጨማሪ የሌሎች ብሔረሰቦች ስያሜዎችም አደጋ፤ላይ ያሉ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት አንዳንድ ማስተካከል ሊገቡን የሚችሉ ስያሜዎች ካሉ ማስተካል እንጅ ፈጽሞ መለወጥ ግን የሚገባኝ አይመስለኝም፡፡ ምሳሌ፤ጸጥ አድርጋቸው፤ የመሳሰሉ የመንዝኛ ስሞችን አንድ አድርጋቸው እያልን
የጎጃም አማሮች ሰም አወጣጥ የራሱ ስርዓት አለው፡፡ የልጁ ስም ከአባቱ ጋር እንዲገጥም ወይንም ዘመኑን እንዲገልጽ ተብሎ ይወጣል፡፡ ምሳሌ ፍቅር ይልቃል፡ ፍቅር ይበልጣል፤ አንዱ አምላክ ይበልጣል፡፡ ሸዋም ሲሰይም ወግደረስ፤ አልፎ አውግቸው፡ ወንደሰን፤ ዋሲሁን፤ብዙአየሁ፤ እንቁ እንዲል
ጥሩ ብለሀል ወንድሜ ወግደረስ ሀሳብህን እጋራለሁ ግን በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ስሞች ድርጊቱ የተፈፀመበት ቦታ የሚገልፅ ቢሆንም ስማቸው የየራሳቸው ትርጓሜ አላቸው ስለዚህ ብንጠቀምባቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ።
በዚህ ዝግጅት ላይ እንድትሳተፉ የተጋበዛችሁ ሰዎች ደስታ ከተሰማችሁ ከማንም በላይ ማመስገን ካለባችሁ ስማችሁን ያወጡላችሁን ነው፡፡ ክብርና ሞገስ በቋንቋቸው ኮርተው ልጆቻቸውን ለሰየሙ ወላጆችና አሳዳጊዎች!
የምወድህም ለዚህ ነው። People should develop the habit of thinking "in side the box". እንዴት አንጀት የሚያርሱ ባህልን ስብዕናን፣ ኩነትን፣ ታሪክንና የማህበረሰብ ፍላጎትን የሚገልፁ ሀገርኛ ስሞች አሉ መሰለህ መዚ። እንዳልከው የሀገራችን ህዝቦች ለስያሜ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጀዊሽነትን እያስቀደሙ ያሁነያ። ያሳዝናል። ውይይቱ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ቢካሄድ ደስ ይለኛል። በባህል ማዕከል በኩል፤ በሴሚናር መልኩ።
Go forward, i am always with you!
Most of the youngest play the role change their amharic name in to other context interms of civilization.
እኔ እንደሚመስለኝ በውጭዎች ቋንቋ ( ስም) መጠራት እንደስልጣኔ የመቁጠር የተሳሳተ ግንዛቤ ውጤት ነው::

ቅዳሜ 4 ፌብሩዋሪ 2017

ከጠባሴ እስከ ሽሮ ሜዳው የአሜሪካን ኤምባሲ (የሥራ ፈጠራ ውድድር ማስታወሻዬ)




1. ኦባማና አፍሪካ
ባራክ ሁሴን ኦባማ ሊመረጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉም ሆነ ሲመረጡ አስታውሳለሁ፡፡ አፍጋኒስታን ሄደው እዚያ ላለው የአሜሪካ ጦር ንግግር እንዳደረጉ በ2001 ዓ.ም. እጄ ይገባ በነበረው ጋርዲያን ጋዜጣ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች መረዳጃ ማህበር ያስቆጠበኝን ገንዘብ አውጥቼ ቴሌቪዥንና ዲሽ ገዛሁ፡፡ በጥር ወር መጀመሪያ 2001 ዓ.ም ያስገባሁት ቴሌቪዥን ዓላማው የኦባማን የበዓለ-ሲመት ንግግር መስማትና የእንግሊዝኛ ማሻሻያ ሙከራዎችን ማድረግ ነበር፡፡ ፊልም ባለመውደዴ፣ ቢቢሲና አልጀዚራም ስለኢትዮጵያ ባለማንሳታቸው ወይም በየአምስት ደቂቃው ‹‹ዋና ዋና ዜናዎች›› የሚል አንባቢ በቴሌቪዥን መስኮቱ ብቅ በማለቱ ስለጠላሁት ቴሌቪዥንና እኔ ተለያየን - ለዘመድ ሰጠሁት፡፡   (የቴሌቪዥን ታሪኬን ለማንበብ ጉግል ላይ ‹ቴሌቪዥን ሳሲት እንዴት እንደገባ› ብለው ይፈልጉ)

ኦባማ ለአፍሪካ ቃል ገብተው ያልፈጸሟቸው ብዙ ነገሮች በመኖራቸው የተቀየሟቸው የአህጉራችን ሰዎች ሳይበዙ አይቀሩም፡፡ ከአሜሪካዊ መሪ አፍሪካ ብዙ ልትጠብቅ ላይገባት ይችላል፡፡ ጋናን፣ ኬንያንና ኢትዮጵያን እንደጎበኙ የምናስታውሳቸው ኦባማ ከተለመደው የዲፕሎማሲ ወሬ ሌላ የፈየዱት የለም እንል ይሆናል፡፡ አፍሪካ ህብረትም የተናገሩትን ሰማን፡፡ በሃገራቸው ውስጥ ብዙ ፈተና የሚገጥማቸው ኦባማ ለአፍሪካ እንዳሰቡት ለመፈጸም ላይችሉ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ ዋሽንግተን ላይ ስለ ኦባማ ዘመን መጽሐፍ የጻፉ አሜሪካዊት ከአፍሪካ አንጻር የኦባማ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚሉት ‹‹ያሊን›› ነው፡፡ ወደኋላ እንመጣበታለን ያሊን፡፡

2. ኦባማን የምናስታውስባቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ሀ. ባህርዳር ላይ በስማቸው ካፌ መከፈቱን በአሜሪካ ድምጽ ሰምቻለሁ፡፡
ለ. ልደታ ባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ የእንግሊዝኛ ማሻሻያ መርሃ ግብር ስከታተል በዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት ባለ ሆቴል አንድ ሰው ድራፍ ሲያዙ ‹ኦባማ› አድርጊልኝ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ጠይሙን የሀረር ቢራን ምርት መሆኑ ነው፡፡
ሐ. አጎቴ ከሳሲት መጥቶ ‹‹አንተዬ ኦባማ እኮ በቃ በሬ ሆነ›› አለኝ፡፡ ‹‹ደሞ ምን በሬ ይሆናል ለራሱ መሪነት አማሮት›› ስለው እንዳልተግባባን አይቶ ‹‹አይ ኦባማ መኪናውን እኮ ነው፤ እያንዳንዱ ገበሬ እደጁ አንድ ኦባማ አቁሟል›› ሲለኝ ገባኝ፡፡
መ. ኦባማ በአልባሳት ላይም ነግሶ ነበር፡፡
እርስዎስ በምን ያስታውሷቸዋል?

3. ‹ያሊ› ምንድነው?
ቢያንስ አንድ ኦሮምኛ የሚችል ሰው ያሊ ለሚለው ቃል አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን ማለቴ ቃሉ በቋንቋው ትርጉም ስላለው ነው፡፡ ያሊ ማለት ሞክር ወይም ሞክሪ ማለት ነው፡፡ ኦባማ ያስጀመሩትም ‹ያሊ› አፍሪካውያን ወጣቶች የሚሞክሩበትን ዕድል ያቀረበ ነው፡፡  በመንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አመራር፣ በመንግስት ስራ አመራርና በሥራ ፈጠራ የወጣቶችን ብቃት ለማጎልበት የተዘረጋ ነው ያሊ ማለት፡፡ ዘንድሮ በኤሌክትሪክ ኃይልም ሊያሰለጥን ነው፡፡ ከ25 እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ያሉ አፍሪካውያንን ያሳትፋል፡፡ ውድድር ግን አለው፡፡ ዘንድሮ ስለተወዳደርኩበትም ያንን የውድድሩን መንገድ ነው አብረን እንድንጓዝ የፈለኩት በዚህ ጽሑፍ፡፡ በአማርኛ መጻፌም በአብዛኛው በቋንቋ ምክንያት በያሊ ድረገጽ /yali.state.gov/ ላይ ያለውን ገጸበረከት መጋራት ለማይችሉ ኢትዮጵያውያን በሩን ለመክፈት ነው፡፡

4. የፈረንጅ አገር ናፍቆት
‹‹ያላዩት አገር አይናፍቅም›› የምንለው ብሒል የማያስማማው እዚህ ላይ ነው፡፡ ያላየነውን ፈረንጅ አገር የምንናፍቅ ብዙዎች ነን፡፡ የአሜሪካ ወታደር መሆን ሳይቀር የሚመኙ የሥራ ባልደረቦች አሉኝ፡፡ አሜሪካና ስኮላርሺፕ የሚሉትን ቃላት በቀን ሳያነሱ የማይውሉም አሉ፡፡ ልባችን እንዲህ በተጠንቀቅ ስላለ ይመስለኛል አገራችን ላይ ይህ ነው የማይባል ሥራ የማንሰራው፡፡ መሰደድን የሚያስመኝ ቀን የለም ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ መጀመሪያችንም መጨረሻችንም እዚሁ ነው ብለን ካመንን ግን የማይመቹ ሁኔታዎችን ልንቀይር እንችል ይሆናል፡፡ በአስተዳደር፣ በምጣኔ-ሐብት፣ ለኑሮ በመመቸት፣ ረክቶ በመኖር አገራችን ወደፊት ለ50 ዓመታት ለውጥ ማምጣቷን እጠራጠራለሁ፤ እርስዎስ?  ይሁን እንጂ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዲቪ የሞላሁት የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ በ1997 ነው፡፡ ስኮላርሺፕ የሞከርኩት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ ስልጠና፣ ስብሰባ ወይም ጉብኝት ካልሆነ ፈረንጅ አገር ለመሄድ አልፈልግም፡፡ ‹‹የሞጃው ተወላጅ›› የሚለውን የባሻ አሸብርን ዓይነት ኩራት አይመስለኝም የተጠናወተኝ፡፡ የባላባት ስነጽሑፍ (ኢትዮጵያን ሊትሬቸር) እንዳስተምር በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መታዘዜም ላይሆን ይችላል የችግሩ ምንጭ፡፡ አሁን ኩራት አይሆንም ራት ያልኩ ይመስላል!

5. ሞክረው ሞክረው
ወዳጆቼ በስልክም በኢንተርኔትም ያሊን እንድሞክረው ነገሩኝ፡፡ ባለፈው ዓመት ነግረውኝ አይሆንም ይቅርብኝ ብዬ ነበር፡፡ ዘንድሮ ሞከርኩት፡፡ ደብረብርሃን ላይ እንዲሞክሩት የገፋፋኋቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ የውድድር ጥያቄዎቹ ተመሳሳይነት ነበራቸው፡፡ ለሁሉም ጥያቄዎች የጽሑፍ መልስ በእንግሊዝኛ መስጠት ግድ ይል ነበር፡፡ እየጻፍኩ ያጠፋኋቸውና የቀየርኳቸው መልሶች ብዙ ናቸው፡፡ ለወዳጅ ዘመዶቼ አሳይቻለሁ፡፡ አሜሪካውያን የሚወዱና የሚጠሉትን የአርሲው ተወላጅ ኦቦ አማን ቃዲሮ ነግሮኛል፡፡ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሬኮሜንዴሽን ሌተር እንዲጽፍልኝ ለመጠየቅ የምችለውና ፊት የማይነሳኝ እሱ ብቻ ስለሆነ ጠየኩት፤ ጻፈልኝ፡፡ የጻፈልኝንም ሆነ ሌሎች ፋይሎችን ለመላክ በወቅቱ ኢንተርኔት በጣም ደካማ ስለሆነ አልቻልኩም ነበር፡፡ ኢንተርኔት ፍለጋ ኤቫ ሆቴል ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብዬ ውያለሁ፡፡  አሁን የመጀመሪያዎቹን ስድስት ጥያቄዎችና የኔን መልሶች እንመልከት፡-
1. ምን እንደሚሰሩ ይግለጹ፡፡ ለምን ይህን ሥራ መረጡት?
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደማስተምር፣ የማሕበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎዎች እንዳሉኝና በተጨማሪም ቤተ-መጻሕፍት በግሌ ከፍቼ እንደምሰራ ጻፍኩ፡፡
2. ማሕበረሰብዎን ለማሻሻል ምን እያደረጉ ነው?
ከንባብ በሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት የአካባቢዬ ነዋሪዎች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲለውጡ አድርጌያለሁ፡፡ የመጽሐፍ ውይይት፣ የቋንቋ ትምህርትና ተዛማጅ አገልግሎቶቻችንም ማህበረሰቡን ያበለጽጋሉ፡፡
3.  በመጪዎቹ 10 ዓመታት በማህበረሰብዎ ምን ሚና ለመጫወት ይፈልጋሉ? አሁንስ ያንን ለማሳካት ምን እያደረጉ ነው?
ከአስተማሪነቴ ጎን ለጎን በገቢ ማመንጫዎች ላይ እሰማራለሁ፡፡ የዕደ ጥበብ ስራና የማስጎብኘት ስራ በመጀመር በማገኘው ገቢ የቤተመጻሕፍቱን ስራ አጠናክራለሁ፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤትና ቤተመጻሕፍቱን በራሴ ሕንጻ ላይ አደርጋለሁ፡፡
4. በማንዴላ ዋሺንግተን ትምህርት ላይ መሳተፍዎ ሲመለሱ ምን ለውጥ ያመጣልዎታል?
ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ እገዛ ማሰባሰብና ደንበኛ መሳብ ላይ የተሻለ ክህሎት እቀስም ይመስለኛል፡፡
5. በስራዎ ላይ ያስመዘገቡት ፈጠራ የታከለበት አስተዋጽኦ ምንድነው?
የዘር ጥላቻ የሚያስከትለውን ውድመት የሚያሳየውን ሁቱትሲ የተባለውን መጽሐፍ መተርጎሜ ነው፡፡
6. ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት አክብሮትና መደማመጥ የተሞላበት ውይይት እንዲደረግ ምን አድርገዋል?
በብሔር ላይ ከተመሰረተ ሐሜት ለመራቅ እየሞከርኩ ነው፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቆዎች መመለስ ለስድስት ሳምንታት አሜሪካ ባለ ዩኒቨርሲቲ ለመሰልጠን በሚደረገው ውድድር ያሳትፋል፡፡ በዘንድሮው ውድድር ከአፍሪካ 62 000 ሰዎች ሲሳተፉ ከኢትዮጵያ 2400 ተወዳድረዋል፡፡ ከአህጉሪቱ 1000 ሰው ሲፈለግ ከኢትዮጵያ 50 ሰው ያልፋል፡፡ ከአንድ ሺዎቹ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሌላ ውድድር አድርገው አሜሪካ ባለ በፈለጉት ዓይነት ድርጅት ውስጥ ተጨማሪ የ6 ሳምንት የስራ ላይ ልምምድ አድርገው ይመጣሉ፡፡ መተግበር የሚችሉ ክህሎቶችን ይቀስማሉ፣ የአሜሪካንን አሰራር ያያሉ፡፡ እኔ ያንን ካለፍኩ በአሜሪካን የቱሪዝም ድርጅት ላይ ለመለማማድ አመልክቻለሁ፡፡



6. የሰው ዓይን አንገርግቦ የበላ
እናቴ ነች እንዲህ የምትለኝ፡፡ በፊት ሰው አልፈራም ነበር፡፡ አሁን የሰው ዓይን በጣም እፈራለሁ፡፡ በየኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት አዳራሽ ስናገር ያየኝ የስራ ባልደረባዬ መድረክ ላይ ያለው ስብዕናዬ ከውጪው እንደሚለይ ከጓደኞቼ ጋር አውግቶናል፡፡ በጣም ትክክለኛ ምልከታ ነው፡፡

7. የቢዝነስ አለባበስ
ሱፍ አልወድም፡፡ እሱን በመጥላቴና ባለመልበሴ ሰበብ እንዳልወድቅ ሰግቼ ነበር፡፡ ብወድቅና ብቀርስ ምን ችግር አለው ለዚያውም ወንድ ለወንድ ከሚጋባ አገር? ሸሚዝና ከረባት አደርጋለሁ፡፡ ጨርቅ ሱሪና ለሱ የሚስማማ ጫማ ማድረግ ነው፡፡

8. የትዕዛዝ ጋጋታ ወይስ የኔ ሰበብ
ቀድሞ ያልተነገረኝ ፈተና እንዳዘጋጅ ተነገረኝ፡፡ ከ25 መምህር እኔን ምን አዩብኝ! አንድ እምቢ የማልለው ወዳጄ በሁለት ቀን የማያልቅ ስራ አዘዘኝ፡፡ በቃለመጠይቁ ዋዜማ የሁለት ሰዓት ፈተና ፈታኝ ነበርኩ፡፡ ይህን ሁሉ ስራ ስለምሰራ ለቃለመጠይቁ ለመዘጋጀት አልቻልኩም፡፡ ፈተና መፈተኑን 9፡30 ላይ ጨርሼ ቢሮ ገብቼ ለአንድ ሰዓት ያህል የተለያዩ ፎቶዎችን ማቀናበር ጀመርኩ፡፡ የቤተመጻሕፍቱንና የኔን ተግባራት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከፌስቡኬ እንዳላወርድ ኮኔክሽን የለም፡፡ ያገኘሁትን ፕሪንት አድርጌ ያዝኩ፡፡ አልባሳት ግዢ የሄድኩት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ስገዛዛ መሸብኝ፡፡ ማመልከቻየን መሸምደድ እንዳለብኝና ያልተጻፈ እንዳልናገር ከኢንተርኔት ባገኘሁት ምክር መሰረት አጠር አጠር እያደረኩ ራሴ ለጥያቄዎቹ የጻፍኩትን መልስ በማስታወሻዬ ያዝኩ፡፡ የዝግጅቱን ወጪ የሚሸፍነው ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጊ ድርጅት ጠይቆኝ በዋዜማው አዲስ አበባ እንደምገባ ብናገርም አልቻልኩም፡፡ ማታ እቤቴ አስፈላጊ ሰነዶችን አዘገጃጀሁ፡፡ ጠዋት አዲሱን ሸሚዝ ያው መለካት አይቻልም ስለተባልኩ እንደታሸገ ገዝቼው ነበርና ለካሁት፡፡ ትንሽ የጠበበኝ መሰለኝ፡፡ ለበስኩት፡፡ ለአራት ጓደኞቼ አሳይቻቸው ምንም አይልም አሉኝ፡፡
ሆቴል ሩዋንዳን ያያችሁ፡፡ ልብ ካላችሁት በዚያ ሁሉ ረብሻና የስራ ብዛት መሀል የሆቴል ማኔጀር የነበረው ፖል አንድ ቀን ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ሱፉን ሊለብስ ይሞክራል፡፡ ሸሚዙን ማስተካከልም ሆነ ከረባቱን ማሰር አልሆንለት አለ፡፡ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ተርገፍግፎ አነባ፡፡ እንኳን ሁቱ ገዳዮችና የፖለቲካ ስርዓቱ ቀርቶ ልብሱም አመጸበት፡፡ ያን ዓይነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ አልቅስ አልቅስ አለኝ፡፡ ቅር ቅር አለኝ፡፡ ግን እንደኔ ልማድ ከሆነ መጀመሪያ በፌስቡክ ጉራ የምነዛው ሰዎች ያ ነገር ከምን ደረሰ ብለው እንዲበረታቱኝ ነው፡፡ ቢያንስ ሰው ሰምቶታል ጉዳዩን፡፡ ኦፊ ጉርባ!
ወደ አዲስ አበባም ሄድኩ፡፡ ጉዳዬን ስተኳኩስ ቆይቼ የቃለመጠይቁ ሰዓት ሲቃረብ ወደ አሜሪካን ኤምባሲ አቀናሁ፡፡ መጨናነቅ፣ እቃ እንዳልረሳ ማለት (ደብረብርሃን ላይ ማማልከቻዬን ያጠናክሩልኝ የነበሩ ሦስት ሰነዶችን መርሳቴን ልብ በሉ - የአማንን ደብዳቤ ጨምሮ )፣ እንግሊዝኛዬ ይገባቸው ይሆን ብሎ መፍራት ወዘተ ከቃለመጠይቁ በፊት ያጋጠሙኝ ነገሮች ናቸው፡፡

9. የምናወራው ሌላ ተግባራችን ሌላ
በየፌስቡኩና በየግሮሰሪው ጥቁር ኩሩ ህዝብ እንደሆነ፣ ነጮች እንደበደሉን የምናነሳ ሰዎች ነጮቹ አገር ለመሄድ ስንሽቆጠቆጥ የምንናገረውና የምንተገብረው መለያየቱ ያስተዛዝባል፡፡ ፈረንጅ ባይኖር ይሄኔ በአራት እግርህ ትሄድ ነበር ያለኝ ወዳጄ ትዝ አለኝ፡፡ ሁሉ ነገር የነሱ ነው፡፡ እስኪ የኛ የሆነ ነገር በቤታችንስ ሆነ በመስሪያ ቤታችን ምን አለ?

10. ዋናው በር
ዋናው በር የቱ እንደሆነ አላውቀውም፡፡ በሮቹ ጽሑፍ የላቸውም፡፡ ዋና በመሰለኝ በር ሄድኩ፡፡ ጥበቃዎቹ ጉዳዬን ሳስረዳቸው ዋናውን በር ጠቆሙኝ፡፡ የደረሰኝ ኢሜል ላይ ከቃለመጠይቁ 20 ደቂቃ ቀድመው በዋናው በር ይገኙ ስለሚል፡፡ እኔ እንዲያውም 30 ደቂቃ ቀድሜ ተገኘሁ፡፡ ተፈተሽኩ፡፡ ፍላሽ፣ ቻርጀር፣ ቁልፍ ሁሉንም አብጠርጥረው ፈተሹ፡፡ ግድግዳ ላይ እጅ ወደላይ አስብለው በማሽን ፈተሹኝ፡፡ ሞባይሌን ወስደው ግባ አሉኝ፡፡ ገባሁ፡፡

11. ኢትዮጵያ ውስጥ ያለችው አሜሪካ
የኤምባሲውን ግቢ ውበት የምገልጽበት አማርኛ የለኝም! አይኖረኝምም! ህይወት እንዴት መኖር እንደሚቻልና እንዳለበት ታያላችሁ፡፡ ያለንን በንጽሕና መያዝ እንዴት ሰላም እንደሚሰጥ ታያላችሁ፡፡ እኔ የምሰራበትንና ያንን ቦታ ማወዳደር ንስሃ መግባት ነው፡፡ ምነው እኛ ከዓለም ራቅን!
ግቢውን አልፌ ከአሁን በፊት የማውቃት ክፍል ውስጥ ገባሁ፡፡ የድረምረቃ ተማሪ ሳለሁ ቤተመጻሕፍት እየመጣሁ እጠቀም ስለነበር አንድ ሦስት ጊዜ አይቻታለሁ፡፡ ስሜን ተናግሬ፣ ፎቶ ተነስቼ ተቀመጥኩ፡፡ የቤተመጻሕፍቱን አስነባቢ አውቀው ስለነበር አንዳንድ ነገር አወራን፡፡ እስከዚህ ጊዜ በኤምባሲው ባየሁት መሰረት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በኤምባሲው ይበዛሉ፡፡ እንዲያውም ሌላ ያለ አይመስለኝም! ቆየት ብሎም ተጠራሁ፡፡

12. የጥያቄው ሁኔታ
‹‹ኮሊን ጌትሃውስ እባላለሁ፤ በአካል ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል›› ብላ እጇን ዘረጋችልኝ፡፡ ተጨባበጥን፡፡ ወደ ቃለመጠይቁ ቦታ ወሰደችኝ፡፡ ገና በሩ ጋ ሳለሁ ከቃለመጠይቅ አድራጊዎቿ አንዷ ታናግረኝ ኖሯል፡፡ በደንብ አልሰማኋትም፡፡ ተቀመጥ አሉኝ፡፡ ተቀመጥኩ፡፡ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ማስታወሻ ያዝኩ፡፡ ስማቸውን እየጠራሁ እንዳናግራቸውና ጥያቄ እንድመልስ ያግዘኛል፡፡ ስናገርም ልጽፍ ስል ጠረጴዛ ደገፍ እንዳልኩ መሆኔ አንድ ስህተት መሆኑ አሁን ይታየኛል፡፡ ቀጥ ብሎ መቀመጥ ያሻል! የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡
መካከል ላይ አንዲት ፈረንጅ ተቀምጣለች፤ በስተቀኟ አንድ አፍሪካዊ አለ፤ በስተግራ የማንዴላ ፌሎውሺፕ የአምና አሸናፊ ነች የተባልኳት ወጣት ኢትዮጵያዊት አለች፡፡
ፈረንጇ ጀመረች፡፡ ‹‹የእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ መምህር ስለሆንክ በግሌ ደስ ይለኛል፡፡››  ስትለኝ መውደቂያዬ መጀመሩ ገባኝ፡፡ ስለየትኛው አሜሪካዊ ደራሲ ልትጠይቀኝ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ከሦስት ወይም አራት ውጪ አላውቅም፡፡ በስነጽሑፍ ዲግሪ የሰጠኝ ዩኒቨርሲቲ አሹፎብኛል! እድሜዋን ያርዝመው - ሳትጠይቀኝ ቀረች፡፡ የቤተ-መጻሕፍቴን ቀጣይነት ለማስቀጠል ምን እንደማደርግ ጠየቀችኝ፡፡ አንደኛውን እንደዘጋሁት ነገርኳት፡፡ ምክንያቱም የቤት ኪራይ መጨመሩና አንባቢ መቀነሱ ነው አልኳት፡፡
አበሻዋ ለምን ቀነሰ አለችኝ፡፡ የህንጻው መገኛ የንግድ ስፍራ ስለሆነና ቤተመጻሕፍቱም ሁለተኛ ፎቅ ስለሆነ ከበፊቱም የተዳከመ ነበር አልኩ፡፡ አንደኛው እንደተዘጋ እንኳንም ተናገርኩ፡፡ በቅርቡ መጥተው ሊጎበኙ እንደሚችሉ ፍንጮች አግኝቻለሁ፡፡ ለማስታወሻዬ የቅርንጫፍ ላይብረሪው ፎቶና ቪዲዮ ግን አለኝ፡፡ አስነባቢው አማከለው አለምሸትም ትጉህ ልጅ ነበር፡፡ አሁን ስራ ማጣቱ ያሳስባል፡፡ የደብረብርሃን ህዝብ እንዲያነብ እና ጠባሴ ድረስ እንዳይንከራተት በማሰብ ነበር የከፈትኩት ያንን ቤተመጻሕፍት፡፡ ለጉራ አልነበረም፡፡ በትንሹ 16 000 ብር አክስሮኛል፡፡ 
የስራዬን ቀጣይነት አስመልክቶ ግን በማመልከቻዬ የጻፍኩትን ትቼ እገዛ ለማሰባሰብ እሞክራለሁ ማለቴ አንድ ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ማመልከቻው ላይ የዕደጥበብና የቱሪዝም ስራ እሰራለሁ ማለቴን ልብ ይሏል፡፡
ከዩኒቨርሲው ጋር እንዴት ማስተሳሰር ትችላለህ ስትለኝ በዩኒቨርሲው ግቢ የመጻሕፍት መሸጫ መክፈት ብችል ጥሩ ነው አልኳት፡፡ መምህራኑ፣ ሰራተኞቹና ተማሪዎቹ ደንበኞቼ እንደሆኑ ተናግሬ አመራሮቹን ለማሳመን እንደምጥር ገለጽኩ፡፡
(ዘመዴና በአርበኞች ላይ የሚጽፈው የስራ አመራር አማካሪው ጋሽ ጥላሁን ‹‹ለምንድነው ሥልጣን የማትይዘው?›› ይለኛል፡፡ ‹‹ስልጣን እኮ የምትፈልገውን ለማሳካት መሳሪያ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን ብር ላይ ታዛለህ፡፡ ገንዘቡ ለህዝቡ እንዲውል ታደርጋለህ›› ይለኛል፡፡ ‹‹ስልጣን አልፈልግም›› እለዋለሁ፤ ይበሳጫል፡፡ ስልጣን ማለት ህዝቡ እንዲያነብና ችግሮቹን እንዲፈታ የሚጠቅመውን አንብቦ የማስነበብን ስራ የምሰራበትን አቅም የሚፈጥርልኝ መሆኑን ረስቼዋለሁ፡፡ ተያይዞ የሚመጣ ጦስ ግን አለው፡፡)
ከአሜሪካን ሰላም ጓድ ጋር ስለሰራኸው ስራ ንገረን ተባልኩ፡፡
በካምፕ ግሎው 2014 ከዕቅድ እስከ ፍጻሜ ድረስ የነበረኝን ተሳትፎ ተናገርኩ፡፡ በእቅዱ ወቅት የሚተረጎሙ ሰነዶችን በመተርጎም ወደየክልሉ እንዲላኩ ማድረጌን፣ በዝግጅቱም ወቅት ከክፍያ ነጻ ለአንድ ሳምንት መስራቴን ተናገርኩ፡፡ (64 ሴት ተማሪዎች ከሶስት ክልሎች የተሳተፉበትን መርሃግብር ዛሬም እኮራበታለሁ፡፡ ልጃገረዶች ዓለማችንን ሲመሩ የሚለውን ቲሸርት አሁንም በፍቅር እለብሰዋለሁ፡፡ እንኳንም ውሎአበል የለውም ብዬ አልተውኩት፡፡ እንኳንም የምስክር ወረቀት የለውም ብዬ ገለል አላልኩ! (‹‹የምስክር ወረቀት አያስፈልግም፤ ሰርቻለሁ ካልክና ስለስራው ከተናገርክ ይበቃል፤ መርሃግብሩ ላይ መሳተፍክም ስለፕሮጀክት ማኔጅመንት ዕውቀት ያስገኝሃል›› ያለችኝ ልክ ነበር ያቺ ልጅ፡፡) በመንዲዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረኝን የስነጽሑፍ ማሰልጠን ሚና አክዬ ለቁጥር የሚያዳግቱ ስራዎችን እንደሰራሁ ገለጽኩ፡፡ (SIX HOURS AT MENDIDA የሚለውን ጽሁፌን ከጉግል ላይ አንብቡት) እዚህ ላይ ላስታውስዎ የሚገባኝ ነገር አለ፡፡ ባለፈው ፒያሳ ያገኘኝ አሜሪካዊው ወዳጄ ቤንጃሚን በጣም ፈጠራ የተሞላባቸው ስራዎችን እንደምሰራ ለሌላ አሜሪካዊት ልጅ ነገራት፡፡ አንድ ጥያቄም ጠየቀኝ፡፡ ‹‹እንደዚህ ፈጣሪ የሆንከው እኛን አሜሪካውያንን ካገኘህ በፊት ነው በኋላ?›› አለኝ:: እኔም እርግጠኛ ባልሆንም ዱሮም ይህ ነገር እንደነበረብኝ ነገርኩት፡፡ ቢያንስ እንግድዋሻ የተባለውን ዋሻችንን ለማስተዋወቅ ስሞክርና ህዝቡን አስተባብሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰሳ ስናካሂድ አሜሪካ አታውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን አሜሪካ ስልጠናና ገንዘብ ከሰጠችን ይህን ዋሻ የቱሪስት መዳረሻ እናደርገዋለን ብያለሁ ማመልከቻዬ ላይ፡፡
በአካባቢዬ ቤተመጻሕፍትን በደንብ እንዳላስፋፋ የሚያግዱኝም ሁለት ምክንያቶች ሲጠይቁኝ ምላሼ የገንዘብ እጥረትና ከፍቃድ በኩል ያለው ጉዳይ መሆኑን ገለጽኩ፡፡ የቤተመጻሕፍት ፈቃድ ለግለሰብ ይኖር ይሆን እንዴ እኛ አገር? ከሌለ የኢንተርፕረነር አንዱ ችሎታ ፖሊሲ ማስቀየር ስለሆነ ለማሳመን መሞከር ነው፡፡ ዶክተር ፍስሃ የግል ኮሌጅ በኪራይ ህንጻ አይቻልም እንደተባሉ እንዳደረጉት፡፡
ያሊ ስልጠናውን ቢሰጥህ ምን ትጠቀማለህ ሲሉኝ በማመልከቻዬ ላይ ብያቸው የነበሩትን ነገሮች ጠቃቀስኩ፡፡
ጥያቄ ጠይቀን አሉኝ፡፡
ያሊ ብዙ ነገሩ እንደገባኝ ተናግሬ ምክር ካላችሁ ምከሩኝ አልኳቸው፡፡ መጻሕፍትን እንዴት እንደማገኝ መከሩኝ፡፡ አብዛኞቹ የአውሮፓና የአሜሪካ አብያተመጻሕፍት ዲጂታል እየሆኑ ስለሆነ መጻሕፍትን ታገኛለህ አሉኝ፡፡ በጣም የምፈልገው የአማርኛ መጻሕፍት ሊሆን ስለሚችል ቡክስ ፎር አፍሪካን ጠይቅ አሉኝ፡፡
በዋዜማው ያዘጋጀሁትን የቤተመጻሕፍቱና የኔን እንቅስቃሴዎች የሚያሳይ ባለ 24 ገጽ የፎቶ ጥራዝ ከነማብራሪያው ለጠያቂዎቼ እንዲያዩት ስጋብዝ አፍሪካዊው ጠያቂ ተንደርድሮ መጥቶ ተቀብሎኝ ሁሉም አይተውልኛል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ላብራራ ብዬ ስጠይቅ ‹‹ፎቶው ነግሮናል፤ እናመሰግናለን›› አሉኝ፡፡ ምን አስመለከተኝ አልኩ ለራሴ፡፡ ጥሩ እቅድ!

13. የገረመኝ ጥያቄ!
‹‹ሠሚራን ታውቃታለህ?›› የሚለው ነው፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ ነው! ‹‹እንዴ አውቃታለሁ!›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ትመጣለች እኮ፡፡›› የዚህ ጥያቄ ዓላማ እኔ በእውነት ከደብረብርሃን መምጣቴን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሠሚራን ባላውቃት ግን ሊሰርዙኝ ነበር እንዴ!
ተመሰጋግነን ተለያየን፡፡
ጠባሴ፣ ደብረብርሃን፣ የዱሮው ባህር ሃይል ያሁኑ ዩኒቨርሲቲና መከላከያ ኢንጂነሪንግ ከሚገኙበት ስፍራ የጀመረው የአሜሪካ ልክፍት እስከ እንጦጦ ጥግ፣ ሽሮሜዳ፣ አዲስ አበባ ቀጥሏል፡፡ በዚሁ ይቀጭ ይሆን?

14. አንዳንድ ጥያቄዎች
አልፍ ይሆን?
ትራምፕ ጭራሹኑ መርሃግብሩን ይሰርዙት ይሆን?
እርስዎም ያሊን እንዲጠቀሙበት በማሳሰብ ልሰናበት፡፡ በድረገጻቸው ኦንላይን በነጻ በመማር፣ በፌስቡካቸውና በያሊቻት ስለአፍሪካ ልማት በመወያየትና እንደ እርስዎ ባለ ሁኔታ ያሉ አፍሪካውያንን ሁኔታ በማጤን ለለውጥ ይነሱ፡፡ የያሊ መሪዎች መርሃግብሩን ለማስቀጠል መጠባበቂያ እቅዶች ላይ እየተወያዩ ይመስለኛል፡፡ ወደ አፍሪካ ለማምጣት ሳይታሰብም አይቀር፡፡ ሁላችንም መሪዎች መሆን እንችላለን!
መታሰቢያነቱ
ለባራክ ሁሴን ኦባማ

ማክሰኞ 10 ጃንዋሪ 2017

የፈረንጁ ተልዕኮዎች - ከሠሞኑ ጉዳይ ጋር የሚሄድ ልቦለድ ታሪክ





መቼም አሜሪካዊ ሆኖ እንጓዝ ከተባለ እምቢ የሚል አይኖርም - እንደውሃ መሄድ ልምዳቸው ነውና፡፡
ከመሐል ሜዳ ሸሾ ድረስ ያለው መንገድ በጣም ሩቅ ነው፡፡ ቢሆንም ያን ሁሉ መንገድ ግማሹን በመኪና ግማሹን በእግራቸው  ለመሄድ ተዘጋጁ፡፡ መንዝ ብዙም ለዓይን የሚስብ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ልማት የለውም፡፡ ያንንና ሌሎችንም እያወሩ በእግራቸው ሄዱ፡፡ ከቆሎ ማርገፊያ ወዲያ ያለው የእግር መንገድ አሰልቺና የመንዝን እርቃን የሚያሳይ አሳባቂ ነው፡፡
መንገድ ላይ ልትስመው ትፈልጋለች፤ ልትላፋው ትጥራለች፡፡ እሱ ግን ግድም አልሰጠውም፡፡ ‹‹ምን ነካው!›› የሚል ዓይነት ጥያቄ አጭሮባታል፡፡ ‹‹ያለወትሮው ደግሞ ምን አኮራው!›› የሚል ሃሳብ በአእምሮዋ ቢመጣም በዚህ ሰው ዝር በማይልበት መንገድ ላይ ምንም ጥያቄ አንስታ ልትጨቃጨቀው አልፈለገችም፡፡ በሰው አገር የሰው ሆዱ ምን ይታወቃል?
እሱ በመሐልሜዳ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ሲሆን፤ እሷ ደግሞ ከአሜሪካ በበጎ ፈቃደኝነት የመጣች ጥቁር አሜሪካዊት ነች፡፡ ከጥቁር ይልቅ አፍሪካን አሜሪካን ሲሏት ነው ደስ የሚላት፡፡ ሄደው ከእናቱ ቤት ደረሱ፡፡
መንገድ ላይ ፍዝዝ ብሎ ሲያስብም ሆነ በተደጋጋሚ ፊት ሲነሳት አንዳንዴም ከንፈሩን ሲነክስ ምን ሆነ ብላ አስባለች፡፡ ጓደኛዋ ያለወትሮው አልሆን ስላላት በዚህ ‹‹ያልሰለጠነ›› አገር ነጻነትና ስለ ሕልውናዋ ዋስትና አልተሰማትም፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በሚሰራበት መስሪያ ቤት በሚገኘው የመምህራን ቢሮ በር ላይ አንድ ልጅ ቆሞ ‹‹ጋሼ ሀብቱ አሉ?›› ይላል፡፡ ተማሪው ቢሮ መፈለጉን ሊነግረው ከርዕሰ መምህሩ ዘንድ የተላከ ልጅ ነው፡፡ ርዕሰ መምህሩም በታማኝነቱና እንግሊዝኛም እንደሚሞካክር በማወቃቸው ሀብቱን ወደ አዲስ አበባ ለአንድ ተልዕኮ ሊልኩት እንደሆነ ነገሩት፡፡ አዲስ አበባ ሄዶም በጎ ፈቃደኛዋን ከፈረንጆችና ኢትዮጵያውያን አስተባባሪዎች ተረክቦ ትልቅ አደራ ተሸክሞ መጣ፡፡
አሜሪካዊቷ ካሏት ድብቅ አላማዎች አንዱ መጥበስ ነው፡፡ ወንድ ጓደኛ መፈለግ፡፡ ከዚህ ሌላ ማድረግ እንደሚያስቀስፋት ታውቃለች፡፡ ሌላውን ለሌላ ጊዜ ለራሷ የቤት ስራ ሰጥታ ለአሁኑ ይህንን መምህር በፍቅር ወጥመዷ ውስጥ አስገባችው፡፡ መንዝ ካሉት ሴቶች ያነሰ ውበት ስለነበራት በመጀመሪያ ያልተሸነፈላት ይህ ለፍቅር አዲስ የነበረ ወጣት መምህር ተሸነፈ፡፡ ‹‹የሴት ልጅ ልቧ ከንፈሯ ላይ ነው›› የተባለው ለወንዶች የተነገረ ይመስል ገና ስትስመው ልቡ ፍስስ አለች፡፡
በመሐል ሜዳ ብርድ የሷን ፍላጎት ለማሟላት ማታ ማታ ከከተማው አንደኛው ወደሌላኛው ጠርዝ  የእግር ጉዞ አብሯት ያደርጋል፡፡ የሰው አፍ እንደእሳት በላኝ ብሎ ያስባል፡፡ በሳይክል ወደ ሃያ ኪሎሜትር ወደሚርቀው ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ አብሯት ይሄዳል፡፡ እሱ ራሱን ለማዝናናትና እሷን ለማጀብ ሲሆን፤ እሷ ደግሞ በዚያ ያሉ በእንስሳትና እጽዋት ሀብት ላይ የሚመራመሩ አሜሪካውያንን በካምፓቸው ለማግኘትና የሆድ የሆዷን ለማውራት ስለምትፈልግ ነው፡፡ በቃ እነዚህ ደግሞ አንዴ ከገጠሙ ይልና የጓሳን ጥብቅ ስፍራ በሳይክል ሲዞር፣ ዝንጀሮ፣ ቀበሮና አይጥ ሲያይ ይውላል፡፡ የጓሳውን ምድር ሽታ ይናፍቀዋል፤ ሰላም ከከተማ ወጥታ እዚያ የተደበቀች ይመስለዋል፡፡
ድሮም አንድ አንድ አሜሪካዊ የማያጣውን መንዝ ይህች ልጅ - ሊዛ ሲንግልተን - ትንሸራሸርበት ይዛለች፡፡ ትምህርት ቤቱም ከተለመደው አሰራሩ በመጠኑ ለየት ያሉ አሰራሮችን ጨምሯል፡፡ የእንግሊዝኛ ክበቡ በጣም ተጠናክሯል፤ መምህራን በቋንቋ ስልጠና እየታገዙ ነው፡፡ አንዳንድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ ጊዜ አጠቃቀምንና የማንበብ ልምድን የመሳሰሉትን ከአሜሪካዊቷ ለመኮረጅ የሚሞክሩ እየበዙ ነው፡፡  
ሀብቱ ከዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ ልቦለድ ላይ ‹‹እንግዲህ ምን አውቃለሁ … በእንዴት ያለ መንገድ ቅኝ አገዛዛቸውን ሊቀጥሉ እንደሚፈልጉ ነጮች›› የሚለውን የአደፍርስን ንግግር ሸምድዶ ሁሌ ሰው አጥብቆ ሲጠይቀው ይናገረዋል፡፡ ለማናቸውም እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው አልገባ ብሎታል ሀብቱ፡፡ ሙሉጌታ ኢተፋ የተባሉ ደራሲም የአሜሪካ ቆይታቸውን በተረኩበት ዘ ቢተር ሃኒ በተባለው መጽሐፋቸው በበጎ ፈቃደኝነት ስም የሚመጡት ሰዎች የአገሪቱ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ መልምሎ የሚያሰለጥናቸው አባላቱ እንደሆኑ የጻፉትን አንብቧል፡፡ በቅርቡ ያነበበው በዊኪሊክስ አፈትልኮ የወጣ ፋይልም ኢትዮጵያ ያለ ማናቸውም አሜሪካዊ ሰላይ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ አንድ ዘመዱን አዲስ አበባ አግኝቶ ጠይቋቸው ግን ‹‹ልጄ ልሙትልህ ፕሬዚዳት ኬኔዲ የኢትዮጵን ሕዝብ በቅንነት ለመርዳት ያቀዱት ነው፡፡ ምንም ሌላ ተልዕኮ የለውም›› ብለውታል፡፡
‹‹አሁን እኛስ ብንሆን አሜሪካ ሄደን ስለአገራነችን መጥፎ ሊደረግ ነው የሚል ነገር ብንሰማ ዝም እንላለን?›› እያለ ራሱን ያጽናናል፡፡ አገራቸውን የሚጎዳባቸውን ነገር መከታተል ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ዓላማ የሰውን አገር የሚጎዳ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉም ይገምታል፡፡ እሱንም እየሰለለችውና የመረጃ መሰብሰቢያ እያደረገችው እንደሆነ ይጠረጥራል፡፡ ራሱን እንደከሃዲ የሚቆጥርበትም ጊዜ አለ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት መቼም መጥፎ ይሰራሉ ብሎ ቢያስብ አያስገባቸውም ነበር›› ብሎም ሳያስብ አልቀረም፡፡
በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ወቅት ይግባባቸው የነበሩት ሕንዳዊ መምህሩ በሀገሩ ላይ የአሜሪካ ተጽዕኖ መብዛቱ በጣም እንደሚያሳዝናቸው ነግረውት ወደፊት ግን ይህን ለመቀልበስ መሰራት እንዳለበት አሳስበውት ነበር፡፡ ‹‹ሕንድ በፍጹም አሜሪካውያንን ወደ ፖለቲካዋ አታስገባም›› ያሉትን አይረሳም፡፡ ‹‹ብናስገባ እንደ ሽንት ቤት ወረቀት ተጠቅመው እንደሚጥሉን እናውቀዋለን፤ እስኪ ኢራቅንና አፍጋኒስታንን እይ!››
በዚህ ሁሉ መሀል የወደዳት የዚህች ልጅ ነገር ይከነክነዋል፡፡ መቼም አንድ ጊዜ ተነካክቷል፡፡ ‹‹ወይ አሜሪካ ትወስደኝ ይሆናል›› እያለም የተመኘበት ጊዜ አለ፡፡ እዚያ ሄዶ እንደሁኔታው አብሯት ለመኖር ወይንም ትቷት ላሽ ለማለት አስቧል፡፡ እቤታቸው በተሰቀለው የቀን መቁጠሪያ ላይ ሳይቀር የኖሯቸውን ቀናት እየሰረዘ አሜሪካ ለመሄድ የቀሩትን ቀናት ይቆጥራል፡፡ እንደ እርጉዝ አድርጎታል፡፡ የምን እርጉዝ ነው ደሞ? ይቺ ልጅ አታስረግዘው!
ዘ አዲስ ኦብዘርቨር የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ‹‹አሜሪካዊቷ መንዝ ውስጥ ታግታለች›› የሚል ዘገባ ይዞ ከወጣ ወዲህ ነገሮች በጣም ተካረዋል፡፡ በሁለቱ መንግስታት በጋራ የሚመራ ግብረሃይል ተቋቁሞ መንዝን ያስስ ይዟል፡፡ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፍለጋው ተጧጡፏል፡፡ ልጅቱ ያለችበትን ላወቀ የሚሰጥ ገንዘብ ግን የአሜሪካ መንግስት ቃል አልገባም፡፡ በአገሪቱ ህግ ይህን ማድረግ አሸባሪዎችን የበለጠ ስለሚያጠናክር አይበረታታም - ወንጀልም ነው፡፡
መንዞች ደርግ በአውሮፕላን ስለደበደባቸው አውሮፕላንም ሆነ ማናቸውንም በሰማይ ላይ የሚበር አካል ይፈራሉ፡፡ አሁን ሄሊኮፕተሮች መንዝን ያስሷት ገቡ፡፡ ድሮኖችም በፍለጋው ተሰማርተዋል፡፡ ህዝቡም እንዳሞራ ይቆጥራቸው ይዟል፡፡ ከየማሳው ዳር ሄሊኮፕተሮች እያረፉ ገበሬዎችን ይጠይቁ ይዘዋል፡፡ የመሐልሜዳው ትምህርት ቤት መምህራንና ማህበረሰብ፣ የልጅቱ ቤት አከራዮችም ሆኑ ጓሳ ላይ ያሉት አሜሪካውያን ይታመሳሉ፡፡ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር መጥፋቷን የሚጠቁሙ መረጃዎች የደህንነት ባለስልጣናት አግኝተዋል፡፡ ግን ወዴት ጠፉ ነው ጥያቄው፡፡ አሜሪካዊቷን የሚያውቋት ሰዎች በአንድ መሐልሜዳ ባለ ጠጅ ቤት ስለጉዳዩ ያወራሉ፡፡ ‹‹አሁን ይችን ባሪያ የአሜሪካ መንግስት ፈልጓት ይሆን? ጠብሶስ ቢበላት ምን ቸገረው? የያዘችው የስለላ መረጃ ይኖራል እንጂ? ደሞ ለጥቁር ምን አስጨነቃቸው! የማናውቃቸው!›› ይላል አንድ የቀድሞ ወታደር፡፡ ጡረተኛው ወታደር ብዙም ለሕይወቱ ስለማይሰጋ ነው እንጂ ሰላይ እንደ አፈር ሞልቶበታል በሚባለው ከተማ ማንም ደፍሮ ስለዚህ ጉዳይ አያወራም፡፡
ሀብቱ በቤተሰቦቹ ቤት አቅራቢያ ባለ ዋሻ አጠገብ እንደታየ የአካባቢው ሰዎች ጥቆማ ሰጡ፡፡ ለመሾምና ለመሸለምም ተጣጣሩ፡፡
‹‹አሁን ሆድሽን ሳልዘረግፈው እውነቱን ታወጫለሽ አታወጪም?›› እያለ ጩቤውን እያሳየ ዋሻ ውስጥ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ያሽቆጠቁጣታል፡፡ ‹‹እዚህ አገር ለምንድነው የምትላኩት?› ዓላማችሁስ ምንድነው? ባለፈው ከጓደኞችሽ ጋር በስፓኒሽ ስታወሩ ቋንቋውን አያውቅም ብላችሁ ነበር?›› እያለ ወጥሮ ይዟታል፡፡ ጎንደር አስጎብኚ ለሆነ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብሮት ለተማረ የቅርብ ጓደኛው ከጓደኞቿ ጋር ሲያወሩ የቀረጸውን ኦዲዮ ልኮለት ትርጉሙ ባለፈው ሳምንት ነው የደረሰው፡፡ ‹‹በሀገሬ ላይ የምታደርጉትን አውቃለሁ›› አላት እንባው እየፈሰሰ፡፡ በስፓኒሽ ካወሩት ውስጥ ወንዶቹ አሜሪካውያን ወንድ ኢትዮጵያውያን ፍቅረኞች እንዳሏቸው ያወራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መጤ ሳይሆን ነባር እንደሆነ ህዝቡን ማሳመን እንዳለባቸው ያቅዳሉ፡፡
ሊጨክንባት እንደሚችል በመገመት ሁሉንም አፍረጥርጣ ነገረችው፡፡
‹‹እሺ እኔንስ የሰራሽኝ ጉድ?›› ብሎ አንድ ከእናቱ ጋር የቆመ ልጅ ፎቶ አወጣ፡፡ የዚያን ጊዜ ይህች ልጅ የምትገባበት አጣች፡፡ አለቀሰች፡፡ ትንቀጠቀጥ ያዘች፡፡ የሀገሯን ምስጢር የነገረችው በሆነ መንገድ ከዚህ ቦታ ከወጣች ይህን ሰው የምታስወግድበትን መንገድ አስባ ነበር፡፡ አሁን ግን መውጫ ቀዳዳ የሌለውን ነገር አመጣባት፡፡
አንድ ቀን አንዳንድ ነገሮችን እየተጠራጠረ ሲመጣና በተመሳሳይ ጾታና ተያያዥ መጤ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋም ሲያይ የፌስቡክ የይለፍ ቃሏን ያውቅ ስለነበረ እስካሁን ድረስ በፌስቡክ የተላላከቻቸውን መልዕክቶች ሁሉ ወደኮምፒውተሩ አውርዶ ያዘ፡፡ ከዚያም የልጅነት ፎቶዋን አገኘው፡፡ ስምንተኛ ክፍል ሳለች የተነሳችው፡፡ ያኔ ወንድ ነበረች፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ተመጣጣኝ ሕክምና ወደሚገኝበት ወደ ሕንድ ሄዳ ሙሉ በሙሉ ጾታዋን አስቀየረች፡፡ ወንድነትን ፈጽሞ አትፈልገውም፡፡
ማይክል ጃክሰን ወደ ነጭነት መቀየሩን ያውቃል፡፡ በልጅነቱ ቡዳ የበላቸው ሰዎች ወደ እንስራነት እንደሚቀየሩና እንደሚሰወሩ ከመስማቱ በቀር ይህን ዓይነት ጡት የሚያበቅልና ሁለመናን ሴት የሚያደርግ ነገር አልሰማም፡፡ እንዴት ይጠርጥር?
ይህን ሁሉ ጉድ ካወጣ በኋላ፡፡ ‹‹ገደል ከምሰድሽ በፊት የምትናገሪው ነገር አለሽ?›› ሲል ጠየቃት፡፡ ‹‹ያለሁበትን ሁኔታ ተረድተህና እኔም አፍሪካዊት እህትህ እንደሆንኩ አስበህ ይቅርታ አድርግልኝ›› አለችው፡፡ ከአሁን በኋላም እንደማትሳሳት ቃል ገብታ ወደ ገዳም አብረው እንዲመንኑ ነገረችው፡፡ እኔ እንዳንቺ ያለን ከሃዲ ገዳም አልወስድም ብሎ የተፈጸመውን ለማንም እንዳትናገር አድርጎ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ ጉዳያቸውም በሚገርም አዘጋገብ ተዘገበ - ለማንም ሳያሳውቁ ጉብኝት ሄደው የነበሩት ጥንዶች ተገኙ፡፡  በ24 ሰዓታት ውስጥም ይህች/ይሀ አሜሪካዊ ስፍራውን ለቆ/ቃ እንዲ/ድትሄድ ተደረገ፡፡ የደረሰበ/ባትን ግን ለማንም ትንፍሽ አላለ/ችም ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ማተሚያ ቤት የገባ ‹‹ድብቁ የአጋች ታጋች ድራማ በሐበሾች ምድር›› የሚል መጽሐፍ ጽፎ/ፋ መግቢያውን ጻፍልኝ ሲል/ስትል የመጽሐፉን ሶፍት ኮፒ ለመንዜው መምህር ላከ/ችለት፡፡
‹‹መጽሐፉን በነጻ በኢንተርኔት ልልቀቀውና ላክስራት ወይንስ እንዳሰበችው መግቢያ ልጻፍላት?›› እያለ ይብከነከናል፡፡ ራሱን በራሱ ለማዋረድ ይፍቀድ ወይንስ ምን ይሻለዋል ትላላችሁ?
‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› ብሎ ጨክኖ ይጻፍላት ወይ? በ1977 እኤአ አሜሪካውያኑን ጠራርገው እንዳስወጧቸው እንደነ መንግስቱ ኃይለማርያም አይነት ወኔ አምጥቶ ይጨክንባት? ‹‹ ዛሬ አገሪቱ ለአሜሪካ እጅ ሰጥታ ከጉያዋ ተደብቃ ሳለ የኔ እምቢተኝነት የምን ይሉታል?›› እያለ እያንገራገረ ነው፡፡  
ይቺ ሴት ቢያንስ እንግሊዝኛ ያሰለጠነችውንና ዘመናዊነትን ያስተማረችውን እንዴት ይዘነጋዋል? እሱን ለመጉዳት ብላ ያደረገችው ነገር ነበር እንዴ? መንዝ ላይ በ2500 ብር ደምወዝ በዚያ ብርድ ተሰቃይታ ህዝቡን ያገለገለችውንስ? ለሷ መግቢያውን ከጻፈላት እሱም ሲጽፍ የቆየውን ማስታወሻውን ማሳተምና ለሀገሩ ሕዝብ ማጋራት ይችላል፡፡ አሜሪካንን ለመጎብኘት ያቀረበችለትንም ሀሳብ ይስማማበት ይሆናል፡፡ መጽሐፉንም አብረው ሊያስመርቁም ይችላሉ፡፡ የሱንም መጽሐፍ ህትመት ስፖንሰር ልታደርግለት ትችላለች፡፡ ነገሩ ሁሉ እርቃኑን ሲያስቀረው ተበሳጭቶ የሚገባበት አጥቶ ራሱን ቢያጠፋስ?


የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...