2018 ጁላይ 21, ቅዳሜ

የመስራች እናቶቹ መልዕክተኛ


የጉዞ ማስታወሻ

በመዘምር ግርማ



ዓላማ፡- የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ለአንድ ሳምንት በሠሜን ምዕራቡ የሃገራችን ክፍልና በአዲስ አበባ አድርጌው የነበረውን ጉዞ ማስቃኘት ነው፡፡ ጉዞውን ያደረኩት በሕጻናት ንባብ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን ለማናገር፣ አገር ለመጎብኘትና ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅ ነበር፡፡ መስራች እናቶች በሚባሉ ሴቶች የተመሰረተው የደቡብ አፍሪካ የርቀት ትምህርት ተቋም የሰጠኝ የቤት ስራ አገር እንዳይና ምልከታዎችን እንዳደርግ ስላገዘኝ የጉዞ ማስታወሻዬ እዚያም እዚህም ወጣ ገባ ይላል፡፡



ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 2010

ማላጅ መንገደኛ

መብራት ስለጠፋ በቂ ዕቃ መያዝ አልቻልኩም፡፡ የሆነ ሆኖ ከቤቴ ወጣሁ፡፡ በዕለቱ በደብረ ብርሃን መኪኖች እያሳፈሩ ያሉት ከመናኸሪያው ውጪ ነበር፡፡ በቀደመው ሰሞን ጭቃ በጭቃ የነበረው የዚህ መናኸሪያ ፎቶ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ናኝቶ መጠነ-ሰፊ ዘመቻ ስለተከፈተበት ይመስላል ጠጠር እየፈሰሰበት እንደነበር ሰማሁ፡፡ ከአንድ የኤሌክትሪካል ምህንድስና መምህር ጋር እያወጋን ወደ አዲስ አበባ ሄድን፡፡ አዲስ አበባ በሰላም ከደረስን በኋላ በቅድሚያ ያመራሁት ወደሚከተለው ቦታ ነበር፡፡   



በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሁነኛ ሰው አግኝቻለሁ፡፡ እርሱም ደረጀ ቢሻው ሲሆን 1999 .. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ የመኖሪያ ክፍል የተጋራኝ ልጅ ነው፡፡ እዚያ እንደሚሰራም ያወቅሁት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዘንድሮውን ግምገማቸውን ሲያካሂዱ አግኝቼው ነግሮኝ ነው፡፡ የቅድመ-መደበኛ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ኃላፊ ማግኘት ስላልቻልኩና ጉዳዬን በሠዓቱ መጨረስ ስለነበረብኝ ለኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለሙያዎች ሙሉ ገለጻውን አድርጌና ለልጆች የሚሆኑትን ጽሑፎች አጋርቻቸው ጥሩ መግባባት ላይ ደረስን፡፡  ተማሪዬ የነበረችው ሲሹወርቅም ዌብሳይት ላይ ያለው ስራ የሚመለከታት ሆና ስላገኘኋት አሸሸ-ገዳሜ ሆኖልኛል፡፡ በጣም ግን ልጅ ሆንክብኝ አለችኝ፡፡ እውነትም እሷ ከምታውቀኝ 2006 .. አንጻር አምስት ኪሎ ገደማ ቀንሼ ከስቻለሁ፡፡

በዚህ ቢሮ ከተደረጉልኝ ውለታዎች ውስጥ ለትምህርት ቤቶች ጽሑፎቹ እንደሚሰራጩ ቃል መገባቱና ካለምንም እንግልት በድረ-ገጻቸው ላይ የኛ ተረቶች መለቀቃቸው ነው፡፡ የትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች በነጻ የሚሰጡ የትምህርት መሳሪያዎችን እንደሚወዱና ያለማንገራገር እንደሚቀበሉ የዚህ ቢሮ ሰዎች ከልምድ ነግረውኛል፡፡ ቡና ጋብዘውኝ ተለያየን፡፡



በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ

ቢሮው ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት ባለ አንድ የግል ህንጻ ከሁለተኛ ፎቅ ጀምሮ እንደሚገኝ ትምህርት ቢሮዎች ጠቆሙኝና ሄድኩ፡፡ የቤተመጻሕፍት ሰራተኞቹን ሳናግራቸው ይልቅስ አንድ ዶክተርን እንዳናግር መከሩኝ፡፡ እርሳቸውም በማለፊያ ሁኔታ አስተናገዱኝ፡፡ ይህንም ማለቴ ራሴን እንዳስተዋውቃቸው፣ ገለጻ እንዳደርግና ዘርዘር አድርጌ እንዳስረዳ ዕድል እንደሰጡኝ ለማመልከት ነው፡፡ እርሳቸውም በተዛማጅ ስራዎች ላይ እንደሚሰሩ ገልጸው አበረታተውኛል፡፡ ዶክተሩ ያጠኑት ዶክመንታሪ ሊንጉስቲክስ አይሲቲ፣ ባህልና ሥነ-ልሣንን አጣምሮ ያይዛል፡፡ ለኛ ፕሮጀክት ሁነኛ አጋር ሙያ ነው፡፡ እዚህ ቢሮ ጎራ ያልኩት ባህልና ቱሪዝሞች ከአብያተመጻሕፍት ጋር የሥራ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ስለገመትኩ ነው፡፡



ረቡዕ፣ ሐምሌ 4 2010

ዓባይን ለመጀመሪያ ጊዜ

ዙረትና ስራ ስላበዛሁ ሳልንከራተት ለመስቀል አደባባይ የሚቀርብ ሆቴል ያዝኩ፡፡ ሌሊት 1000 ላይ ከእንቅልፌ ተነስቼ ከሌሎች ተጓዦች ጋር መገናኘት፡፡ ጥንዶቹ ዕቃ ስላበዙ ሲጎትቷት ፈጥና መከተል ያቃታትን ትንሽ ልጃቸውን እኔ መታቀፍ፡፡ ወደ መስቀል አደባባይ መሄድ፡፡ መርቀውኝ መለያየት፡፡ እዚያም ዓባይ ባስን ማግኘትና ሌላ ቦታ አድሮ ከመጣው የሥራ ባደረባዬና ጓደኛዬ ከገበያው ስጦታው ጋር መሳፈር፡፡ 1100 ላይ ጉዞ መጀመር፡፡ በሱሉልታ መስመር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመውጣቴ ወሬ ለማየት ውጪውን ጉሙና የመስኮቱ ላይ ርጥበት አላሳይህ አለኝ፡፡ አባይ በረሐን በመጠኑ አየሁት፡፡ ድልድዩም ወርደን ፎቶ ተነሣን፡፡ ከጎጃም ምድርም ደርሼ አውላላውንና ለሙን ሜዳ ማየትና ማድነቅ ጀመርኩ፡፡ ተፈጥሮ የሰጠችንን ገጸ-በረከት ብዙም የተጠቀምንበት አይመስልም፡፡ ብንጠቀምበት በህብረተሰቡ እንዲሁም በሃገሪቱ ሁለንተናዊ ኑሮ ላይ ዓይነተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡ የሁላችንም የቤት ስራ ነው፡፡ አይደል?



መንገዳችን ቀና የሆነው የክረምት ወቅት ስለሆነና ፀሐይ ባለመውጣቷ ሲሆን፤ ለምሳ ደብረማርቆስ ከተማ ለመድረስ ችለናል፡፡ በከተማዋ በዕለቱ ዘግየት ብሎ የመጣው ረብሻ ገና ሳይጀምር አልፈነዋል፡፡ ሌሎቹንም ከተሞች አልፈን ባህርዳር ደረስን፡፡ ይህም ረጅም ጉዞ ዕለቱን አስመሸብንና ብዙም ስራ ሳንሰራ እንድናድር ሆነ - በዓለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ ነው መሰለኝ የእንግሊዝ ቡድን የተሸነፈ ዕለት መሆኑ ነው፡፡ ጣና ሐይቅ ዳር ያሉ መናፈሻዎችን በምሽት ማየቴን አልደብቃችሁም፡፡ ሌላ ቀን እመለሳለሁ ብዬ በማሰቤ በዚህ ጉብኝቴ በደንብ ለመጎብኘት ጊዜ አልሰጠሁም፡፡ በጀልባ መንሸራሸር ወዘተ ቀርተውብኛል፡፡



ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 2010

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ

በማለዳ ተነስቼ ከተማውን ከቃኘሁና ራሴን ከከተማዋ ጋር ካስተዋወኩ በኋላ የስራ መግቢያ ሰዓት ሲደርስ ወደ መስሪያ ቤት አቀናሁ፡፡

በዚህ ስፍራ አራት ኃላፊዎች በተሰበሰቡበት ደርሼ ገለጻ አደረግሁ፡፡ ጽሑፎቹን ሰጠሁ፡፡ ከድረ-ገጻችን africanstorybook.org ጋር አስተዋወኳቸው፡፡ በሥልጠና፣ ማማከርና በቁሳቁስ ጭምር እገዛ ልናደርግ እንደምንችልና ጽሑፎቻችን በደንብ በተሞከሩበት በደብረ ብርሃን እንዴት ውጤታማ እንደሆኑ አብራርቻለሁ፡፡ አድራሻ ተለዋውጠንና ክልሉ በስሩ ላሉ ትምህርት ቤቶች ጽሑፎቹን እንደሚጠቀም ተግባብተን ተለያየን፡፡ የሰው መውደድ ማግኘቴና የዕድሌ መቃናት አስደሰተኝ!





በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

በዚህ መስሪያ ቤት የሚመለከታቸው ባይኖሩም ለተወካዮቻቸው ጽሑፎቹን ሰጥቼና ስለአጠቃቀሙ አብራርቼ መርቀውኝ ሄድኩ፡፡ አንዴ ጽሑፎቹን ከተጠቀሙባቸው ወደፊት ከኛ ጋር ለመስራት እንደሚችሉ እተማመናለሁ፡፡ ቢያንስ ህጻናት ልጆች ያሉት ሰው የራሱን ልጆች ማንበብ ማለማመድ ቢጀምርበትና ልጁ ለሚማርበት ትምህርት ቤት ቢሰጥ አንድ ጅማሮ ነው፡፡ ከዚያም ጽሑፎቹን የማጋራትና የመጠቀም ሂደቱ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ለማያነብ ልጅ ፍቱን መድሐኒት የሆኑና በሥዕል ያበዱ ጽሑፎች እንዳሉን ያየ ያውቀዋል፡፡ 



ለካ በያገሩ ወዳጅ ዘመድ አለኝ!

ወዳጅ ዘመድ እንደማላጣ ስላወቅሁት ነው መሰል ከመነሳቴ እየመጣሁ ነው የሚል ነጋሪት ስጎስም ነበር፡፡ በዚሁም መሰረት ስልኩን ለሰጠኝ ዘመዴ ደወልኩ፡፡ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያስበውን ነገር አስረዳኝ፡፡ በንባብና በጉብኝት ያለብኝን ክፍተትም እንድረዳ አደረገኝ፡፡ የተፈጥሮ ሳይንሱ ሰው ግሩም የታሪክ ትምህርት ሰጠኝ፡፡ ገለጻው የንባቡ ውጤት ነው፡፡ የዓሣ ግብዣው - ጣት ያስቆረጥማል! ሁነኛ ቤት ስለሚያውቅ እዚያው እፊት ለፊታችን ሰርተው የሚያቀርቡበት ቦታ ነው የሄድነው፡፡  

ቀጥሎ ወደ አባ መንገሻ ገነሜ የሕዝብ ቤተመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል ‹‹እስኪ ለማናቸውም አናግራቸው›› ብሎ ወሰደኝ፡፡ ሳናግራቸው ጥሩ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ እንደሆኑ ስለገባኝ ጽሑፎቹን ሰጠኋቸው፤ ውይይትም አደረግን፡፡ የአሜሪካን ሴንተርም አላቸው፡፡

ዘመዴን የጠየኩት ጥያቄ የአማራን መደራጀት ይውደደው ይጥላው ሲሆን፤ እርሱም እንደወደደውና ወቅታዊና ግድ እንደሆነ በብዙ ማስረጃዎች አስረድቶኛል፡፡



ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፡-

ከዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ውስጥ አስተዳደርን የሚመለከተው ዊዝደም (ጥበብ) የሚባለው ነው፡፡ እዚያም ሄጄ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተሩን ወጣቱን ዓቢይን መንክርን አገኘሁት፡፡ ይህ የዩኒቨርሲቲው መምህር ገና እንደነገርኩት ወደ ድረገጻችን ገባ፡፡ አንድም ተረትን (ምክር ያስፈታል ከእስር የሚለውን) ከፈተና አነበበ፡፡ ስለሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀማችን ትችት አቀረበ፡፡ እኔም ተቀበልኩት፡፡ በግሌ በትርጉም መጽሐፌ ይህን ነገር ተጠንቅቄ እንደሰራሁ ነግሬው አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ እርማት ማካሄዱ እንደሚያስደስተኝና የጽሑፍ ቅርሳችንን መጠበቅ ከዓላማዬ አንዱ መሆኑን አስገነዘብኩት፡፡ በዚህ በሞክሼ ሆሄያት ጉዳይ ላይ ተቆርቋሪ ተቋም በዚህቸ አገር መኖሩ በእውነት ያኮራል፡፡

አቶ ዓቢይ እንዳስረዳኝ ከሳምንት በፊት ከከተማው የትምህርት መምሪያ ጋር በመሆን ከተማ-አቀፍ የንባብ ሳምንት አካሂደዋል፡፡ ‹‹እንዲያውም አንድ ሳምንት ቀደም ብለህ ቢሆን ማለፊያ ነበር›› አለኝ፡፡ ቢሆን ኖሮ እውነትም አንድ ጥግ ተሰጥቶኝ ስለስራችን ለማስረዳት እችል ነበር፡፡ የሰማዕታት ሐውልት ቤተመጻሕፍት በዓውደ-ርዕዩ ላይ ተባባሪያቸው ነበር፡፡ የከተማ አስተዳሩ በቅድመ-መደበኛና በታች ክፍል ንባብ ላይ ይሰራል፡፡ የፍጥነት ንባብ ላይም እንደሚያሰለጥኑ ሰምቼ ተማርኬያለሁ፡፡ ምክንያቱም ሌላው የፍላጎትና የስራ ፈጠራ ትኩረት ጉዳዬ በመሆኑ ነው፡፡



በተለይ የተረቶቹን ነገር አስመልክቶ ጥራታቸው አንዱ የመነጋገሪያ ርዕሳችን ነበር፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋማቸው - አቋማተ - እና በስሩ ያሉ ባለሙያዎች በአርትዖትና በዝግጅት ሥራ እንዲያግዙን እንደሚደረግ ተነጋግረናል፡፡ ከድረ-ገጻቸው ጋር የአፍሪካን ስቶሪቡክ ድረ-ገጽን ለማስተሳሰርና ማህበረሰቡ ተረቶቹን እንዲያውቃቸው እንደሚደረግ ቃል ተገብቶልኛል፡፡ አንድ የዩጋንዳ ዩኒቨርሲቲ እንዳደረገው የቋንቋ ተማሪዎችና መምህራን በበጎ አድራጎት ስራ ቢሰማሩና ጽሑፎቻችንን ቢተረጉሙልን ዓይነተኛ ስራ መስራት እንደምንችልና በርካታ ልጆችን መድረስ እንደሚያስችለን አምናለሁ፡፡

ለአቶ ዓቢይ የምስራቅ አፍሪካ ኃላፊያችንን ኢሜል አድራሻን ሰጥቼው ስለነበር በዚሁ ዕለት ኢሜል አድርጎላት ኮፒውን ላከልኝ፡፡ አብረን እንስራ የሚለውን ኢሜል ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንቶችና የትምህርት ጉዳይ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች ኮፒ መላኩን ገልጧል፡፡ ወዲያውኑም አለቃዬ ምላሽ ሰጥታው ወደፊት የሚደረጉትን ነገሮች በጉጉት እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡

በዚህ ሁኔታ የምንሰራው ሥራ ከተሣካልን በአማራ ክልል ያሉ የምንደርሳቸው ልጆች ዓለምአቀፉን የንባብ መስፈርት የሚያሟሉ ይሆናሉ። ባህርዳር ዩኒቨርስቲም በዚህ ዘርፍ ጠንካራ አጋርነቱን ካረጋገጠልን ምናልባት በርቀት ትምህርትና ኦፕን ለርኒንግ የምንሠራው የማማከር ሥራ ተጠቃሚ ይሆናል። አእምሮ ላይ መሥራት ውጤቱ አመርቂ ነው። እየደራረበ ውጤቱ ይመጣል፡፡ ባህርዳር በነገራችን ላይ የሚገርም የትምህርት ከተማ ነው፡፡ በየቦታው አብያተ-መጻሕፍትና መጻሕፍት መሸጫዎችን በማየቴ አድንቄያቸዋለሁ፡፡



አጋጣሚው ይገርማል!

ከኋላዬ ይጠራኛል፡፡ ማነው ብዬ መለስ ስል አየሁት፡፡ ሽበቱ ትንሽ ጨምሯል፡፡ ደግ ሕንዳዊ መምህር ነው፡፡ ባህርዳር እንደሚሰራም ለምን እንደሆነ አላውቅም ረስቼዋለሁ፡፡ በዚህች ቅጽበት መገናኘታችን ገርሞኛል፡፡ አርጁን በጣም ምስጉን መምህር ሲሆን ተፈጥሮው ምንም ሕንዳዊ አይመስልም፡፡ ቢያንስ የተለመዱትን ማለተ ነው፡፡ ሰውን በጣም የሚጋብዝና የሚግባባ ፍጥረት ነው፡፡ በል ወደ ፖሊ ግቢ እንሂድ ብሎኝ አብሮት ከነበረው ሐበሻ መምህር ጋር ሦስታችን ሄድን፡፡ ሌላ አሻግሬ የተባለ መምህርም አግኝተን ቡና ጋበዘን፡፡

በዚህ ምሽት ወደ ጎንደር የመሄድን ሃሳብም አስትቶኝ እሱ ቤት አደርኩ፡፡ ከጎረቤቱ ህንዳዊያን መምህራን ጋር እያወራን አብረን አመሸን፡፡ ስለ ህንድ አንዳንድ ነገሮችን ስለማውቅ የተግባባንበትና ጥሩ ጊዜ ነበር፡፡ በጣም ተግባቢዎች መሆናቸውን ለመታዘብ ችያለሁ፡፡

የኮንትራት ማሳደሻ ወቅት ስለሆነ ህንዶቹ ተጨንቀዋል፡፡ የአርጁን ግን ታድሶለታል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሕንዳውያን መምህራን የሚያደርገው አቀረረብ በሀገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች እንዳለው ሁሉ አሳሳቢ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ሰላሳና ከዚያ በላይ ሰዓት በሳምንት ያስይዟቸዋል፡፡ ጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ይሰራሉ፡፡  አስቸጋሪና ለህንዶች የተለየ ጥላቻ ያላቸቸው አለቆች አሉ፡፡ የህንዶችን ዕውቀትና ልምድ የማይቀበሉና የሚያናንቁ ሰዎች አሉ፡፡ ካሪኩለሙ ባላስፈላጊ ርሶች ሲሞላ ማሻሻያ እንዲደረግ ህንዳውያኑ ሲጠይቁ እንደባለቤት ራሳቸውን የሚቆጥሩት ኢትዮጵያውያን አይሹም፡፡ ኮንትራት ማራዘም ላይ ከሙስና የሚመነጩ ችግሮች አሉ፡፡

የአርጁን ፍራሹ ትንሽዬ ስትሆን እሷ ላይ ተጣጥፎ ተኛ፡፡  ለባለቤቱና ለልጁ የገዛው ትልቅ ፍራሽ ላይ ሳሎን አስተኛኝ፡፡ አሁን ባለቤቱ ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ መሄዷን አስረዳኝ፡፡ ሕይወቱ በጣም ቀላል ሲሆን የቤት ዕቃም አለው ለማለት ያስቸግራል፡፡

ይቺ ድንቅ ፍጠረት የሆነች ቤት ለብዙ ሰው ትምህርት ትሰጣለች፡፡ ምንም የሚካበድ ነገር የለባትም፡፡ ባለቤቷም እጅግ ቀላል ሊባል የሚችል ህይወት የሚኖር ነው፡፡ ባለ አንድ መኝታ ቤት ነች፡፡ ለዕለታዊ ህይወቱ የሚያስፈልገውን እያንዳንዱን ነገር የገዛ ይመስላል፡፡ ቤቱ ምንም አልተደራጀም፡፡ ሰራተኛየ በቅርቡ መሄዴን አስመልክቶ ስለሄደችና ካገር ልወጣ ስለሆነ ነው የሚለውን ወሬ ካመንን ከዚህ የተሻለ ቤት ነበረውማለት ይቻላል፡፡ ልብሶቹ ሁሉ ወለል ላይ ተጥለዋል፡፡

አልጋ፣ ቲቪ፣ ሶፋ፣ የለውም፡፡ ከሱ ጎረቤት ያለው ህንዳዊ በአንጻሩ በኑሮው በመጠኑ የተደላደለ ይመስላል፡፡

ሞባይል ደጋግመህ አትጠቀም ብሎኛል፡፡ ላፕቶፕም ቢሆን በሚያሰራጨው ኢነርጂ ሰበብ መጥፎነት አለው፡፡ እንደ አርጁን ሁሉ ህይወትን ቀለል አድርጌ መውሰድ ይኖርብኛል፡፡ ሜዲቴትም ያደርጋል፡፡

የሚወደዱ ልጆችና ቤተሰብ አለው፡፡ ህይወትን አቅልሎ የሚያይና ጥሩ ጓደኞች ያሉት ሰው ቀኑ በደስታና በተትረፈረፈ ሁለንተናዊ ሃብት ይሞላል ብሎኛል፡፡  የቤቱ ውኃ ችግር አለበት፡፡ ቧንቧው ሲያንጠባጥብ ይረብሻል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በማይክሮኤሌክትሮኒክስና በኢምቤድድ ሲስተምስ የማስተርስ ፕሮግራም ማስተማር ሊጀምር ነው፡፡

‹‹ወደ ኢንዳስትሪው ሄደን ለማገዝ ከትምህርት ክፍሉ ደብዳቤ አይሰጠንም›› ይላል፡፡ ‹‹ህንዶች እዚህ ለገንዘብ ሲሉ ነው ያሉት ብለው ያስባሉ፡፡ ተመራቂ ተማሪዎቻችን በየሚሄዱበት ለትምህርትና ስልጠናቸው የማይመጥን ቀላል የመገጣጠም ስራ ይሰራሉ እንጂ  የሚማሩትን የፕሮግራሚንግ ትምህርት አይተገብሩትም፡፡ ዩኒቨርሲቲ የህንድ መምህራንን ተሰጥኦና ዕውቀት የሚጠቀምበትን ስርዓት አልሰራም፡፡ ኢንዱስትሪውን ሳይቀር ማገዝ እንችላለን፡፡›› ብሎኛል፡፡



አርብ፣ ሐምሌ 6 2010 ..

ወደ ጎንደር

በባህርዳር ያለኝን ተልዕኮ በሚገባ ፈጽሜ የጎንደሩን ለቀጣይ ቀን አስቀምጬው ነበር፡፡ ጓደኛዬ አርጁን ቁርሴን ጋብዞ ወደ ጎንደር ሸኘኝ፡፡ እዚህ ባህርዳሩ አዲሱ መናኸሪያ ላይ ፈሶ ያየሁት ሽምብራ የሚመስለው አሸዋ ለደብረ ብርሃንም እንዲሆን ተመኘሁ፡፡ ምን ይመስላችኋል ብዬም የማህበራዊ ሚዲያ ወዳጆቼን ጠየቅሁ፡፡ መሰራት የሚችል ግን ይመስለኛል፡፡ ሳሲት ላይ ይህ አሸዋ በገፍ ስላለ ማምጣት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡

የጎንደር መኪና ይዤ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ አዲስ ዘመን አቅራቢያ ለፍተሻ ወረድን፡፡ የሩቅ ቦታ መታወቂያ መያዜ ከጥርጣሬ እንዳያስገባኝ ሰግቼ ነበር፡፡ በሰላም አለቀ፡፡ አዘዞ ላይ ወርጄ ወደ ጎንደር በታክሲ አቀናሁ፡፡ ፒያሳ ኢትዮጵያ ሆቴል ስደርስ ለወዳጄ ለሰለሞን ግርማ ደወልኩለት፡፡ ሰለሞን በደብረብርሃን አብሮኝ የሰራ ጥሩ ሰው ነው፡፡ አሁን ቤተሰቡ በሚኖርበት ከተማ ስላገኘሁት ተደስቻለሁ፡፡ እቤቱ ወስዶ ጋበዘኝ፡፡ የእርሱና የባለቤቱ የቅድስት እናቶች ስም አበባ መሆኑን ያወኩት አማቱን ሲያስተዋውቀኝ ነው፡፡



የአጼ ፋሲል ግንብ

የዚህን ታሪካዊ ስፍራ ዝርዝር ሁኔታ ልቅም አድርጎ የሚያውቀው ሰለሞን ግርማ ነው አስጎብኝዬ፡፡ 70 000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ግቢ ውበቱና ግርማው ያማልልዎታል፡፡ በቤተመንግሥቱ ዙሪያ ያሉት ድልድዮች የንጉሣውያን ቤተሰቦች የሚቋርጡባቸው ሲሆኑ ተራው ዜጋ በውስጣቸው ያልፋል፡፡ ሲያቋርጥ ግን ቆቡን አውርዶና አጎንብሶ ስለሆነ እነዚህ ስፍራዎች ቆባስጥል ተባሉ፡፡ ስለቤተመንግሥቱ በበይነ-መረብ መረጃ ስለሚገኝ ከዚያ እንድታዩ በማሰብ አንዳንድ የሳቡኝን ነገሮች ብቻ ነው የማነሳሳው፡፡ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጉብኝት ያየሁትን ስለሆነም ገላጭ አይሆንም፡፡  

ግዝፈትና ውፍረት ያላቸውን ታሪካዊ ግንቦች ሳይ ‹‹ለካ 2  ምስል ማየት እንዲህ ያሳስታል!›› ነው ያልኩት፡፡ 3 በተለይም በአካል ማየት ትክክለኛውን ምስል ይሰጣል፡፡ በአካል ሳያቸው ያላቸው ታላቅ ታሪካዊና ኪነ-ሕንጻዊ ቦታ ገባኝ፡፡ ትልቅ ታሪክ ይዛለች ለካ ጎንደር!

የኢጣሊያን ፋሽስቶች በአዲስ አበባ ከተሸነፉ በኋላ አንለቅም ካሏቸው ቦታዎች አንዱ ጎንደር ስለነበር ቤተመንግሥቱ በአውሮፕላን በእንግሊዞች ተደብድቧል፡፡ ዕድሜና የእንክብካቤ ማጣትም አለ፡፡ ቢሆንም ለዛሬ ደርሷል፡፡ ለወደፊቱም እኔና እርስዎ አለንለት!

ሦስት ፎቅ ያለው ትልቁ ህንጻ ሰማዩ ጥርት ባለ ቀን ሶስተኛ ፎቁ ላይ ከወጡ ጎርጎራን ማሳየት ያስችላል - 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ማለት ነው፡፡ እነሆ በቤተመንግሥቱ፡- ሀ. ሳውናም አለ፡፡ ሁ. የፈረስ ማቆያው ቤትም የመደበኛውን ሰው ቤት ያስንቃል፡፡ ሂ. የግብር ማብያ ወይም መሰብሰቢያ አዳራሹ ግዙፍ ነው፡፡ ሃ. የአንበሳ ቤት አለ - ከደርግ ዘመነ-መንግሥት ወዲህ አንበሶቹ ባይኖሩም፡፡ ሄ. ከጣራው የሚወርደውን ውኃ የሚያቆዩበት ገንዳ አለ፡፡ ህ. የጉልበተኞች ማደባደቢያ ትዕይንት ማያ አለ! ሆ. ማናቸውም ነገር የተሟላለት የነበረው ቤተመንግሥቱ ለነዋሪዎቹ መንፈሳዊ ፍላጎት መሟላት የሚያግዙ አብያተ-ክርስቲያናትም አሉት፡፡ ምናለፋችሁ! በየዘመኑ የተሰሩት አብያተ መንግሥታት የሰሯቸው የተለያዩ ነገስታት ስም ሳይቀር ተጽፎ ይገኛል፡፡ አብያተ መንግስታቱ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ ይህን ስታዩ ታሪክ አለኝ ትላላችሁ፡፡ በሌላ የአፍሪካ አገራት እንዲህ የሚመኩበት ቅርስ ብዙም እንደሌለ ዩጋንዳዊው ተናግሯል፡፡



አበቄለሽ ጎንደር

በየዘፈኑ ስሙ የሚነሳሳለትን አበቄለሽ ጎንደርን ሰለሞን ግርማ አስጎበኘኝ፡፡ የጠጅ ኩምኮማ (ዳዲ ጌረሩ እንዲሉ እነ ሰለሞን ዴሬሳ) ስራችንን እንደተለመደው ጀመርን፡፡ አዝማሪው አለ፡፡ የእመት አበቄለሽ ጎንደር ሶፋ እንደተከበረ ከነመቋሚያቸው ተሰይሟል፡፡ እርሳቸው ቢያልፉም መልካም መንፈሳቸው አለ፡፡ ጠጅ ጠጪው ቀንሷል ተብላችኋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ደብረ ብርሃን ላይ ጠጅ የምንጠጣበትን እማሆይ ጠጅ ቤትን ያስታውሷል፡፡ አዳራሽ አረቄ ቤትም አለ፡፡ ያ ውርስ (ሌጋሲ) ቀጠለ ማለት ነው! በነዚህ ቤቶች ብዙ ትዝታቸው ያለብን ጓደኞቻችን በየአቅጣጫው እንደ ጨው ዘር ተበትነዋል፡፡



የጎንደር ተጋቢኖ ስለሚወራለት ለመመገብ ፈልጌ ነበር፤ ሰለሞን ጋበዞኛል፡፡

ጃንተከል ዋርካ መሬት ሲነካ

ወንዱም አምጪ አምጪ ሴቱም እንካ እንካ

የተባለለትን የጃንተከል ዋርካንና ሰፊውን መናፈሻም አይቻለሁ፡፡

ዋርካው መሬት እንዳይነካ በእንጨት አስደግፈውታል፡፡

የጣሊያን ቅሪቶች በከተማው አሉ፡፡ ቢጫ ቀለም ያላቸው ህንጻዎች ጣሊያን ሰራሽ ሲሆኑ ጎንደር ላይ ጣሊያን እግሩን ሰዶ እንደነበር ከማሳየትም በላይ ከተማይቱን አስመራ ያስመስላታል፡፡ 





ቅዳሜ፣ ሐምሌ 7 2010 ..

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፡-

በስልክ ስላናገርኩት ብቻ እሁድ በማለዳ 100 ከቢሮው ገብቶ ያስተናገደኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን እንደ ባህርዳሩ ሁሉ ወጣት ነው፡፡ ገጠመኙ ገርሞታል፡፡ በዕለቱ ወደ መዋዕለ-ሕጻናት ምርቃት ለመሄድ ነበር ማልዶ የተነሳውና እኔን ቅድሚያ ማስተናገድ ያስፈለገው፡፡

የጽሑፎቹን አዘገጃጀት፣ አመራረጥ፣ ህትመትና ትርጉም አስመልክቼ አንዳንድ ገለጻ ካደረኩለት በኋላ ጽሑፎቹን አስመልክቶ ማድረግ የምንችለውን ነገር ተወያየን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ሃብትና የሰው ኃይል ስላላቸው ለስራችን ሁነኛ አጋር ናቸው፡፡ ጎንደር ላይም ያየሁት ያንን ነው፡፡ በስተኋላ ወደ ፒያሳ አብረን አቀናን፡፡ በመንገዳችንም ስለፕሮጀክታችን አስፋፍቼ ተናገርኩ፡፡ ሌላ ምን እንደሚሰሩና የእርሱ ሙያ ምን እንደሆነ ጠይቄው ሆርቲካልቸር እንደሆነና በከተማ ግብርና ላይ እየሰሩ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ይኸውም የጓሮ አትክልት ዘርን በአነስተኛ መጠን እንደገና አሽገው ማከፋፈልን ይጨምራል፡፡ አስደስቶኛል፡፡

እኔም ከዚያ በኋላ የደባርቅ መኪናዬን ያዝኩ፡፡ 



ወደ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ!

ወደ ደባርቅ ከተማ ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡ ደባርቅ ልንገባ ስንልም ፍተሻ ነበር፡፡ ምክንያቱም በማግሥቱ ሰላማዊ ሰልፍ ስለነበር ነው፡፡ ደባርቅ አብሮኝ የተማረውን የልብ ጓደኛዬን ፈንታዬ ጥላሁንን አግኝቼው ወደ ቤቱ ሄድን፡፡ የተደረገልኝ መስተንግዶ በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ጎንደር ላይ የሰለሞን እናትና አማት ስማቸው አበባ ነው እንዳልኩት የፈንታዬም ሚስት እንዲሁ አበባ ነው ስሟ፡፡ ይገርማል!

ከቤቴ 960 ኪሎሜትር ርቄ ብገኝ ይህም ቤቴ ነው። በየሄድኩበት በወዳጅ ዘመድ ግብዣ ተንበሽብሻለሁ። በደርግ ጊዜ ለአንድ ግዳጅ ወታደሮች ለሦስት ቀናት በእግራቸው ሲሄዱ አንደኛው አለ የተባለው ትዝ አለኝ፡፡ "አሁን ይሄ ሁሉ የኛ አገር ነው? እንዲያው ነገር ፍለጋ ነው እንጂ!" ነበር ወቴ ያለው፡፡


የህዝቡንና የባህሉን መመሳሰል ታዝቤያለሁ። አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ማንነት ነው ያየሁት፡፡ ከዚህም እጥፍ ባለ ርቀት ላይ ብንንቀሳቀስ እምብዛም ልዩነት የሌለውን ህብረተሰብ ማግኘት እንችላለን፡፡  በዚህ ዕለት የጎበኘኋቸው ስፍራዎች ነበሩ፡፡ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤትን አየሁ፡፡ ወደ ሊማሊሞም ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ጣሊያኖች ገደሉን እየቆረጡ የሰሩት ወደ ሽሬ የሚወስድ መንገድ ነው፡፡ ዋልያቹን በዚህ የክረምት ወቅት በቀላሉ ማየት ስለማይቻል ወደ ፓርኩ አልዘለቅሁም፡፡



ስለ ወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ በየቦታው ይነሣል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ሐሳቦችን ለማየት ሞክሬለሁ፡፡ "ለውጡ አስደስቶኛል። እስካሁን መልካም ነው። ይሁን እንጂ ወደ አንድ ብሔር ሥልጣኖች ሁሉ ሄደው አምባገነንነት እንዳይነግስ እሰጋለሁ።"
"
ሌሎች ለምን እንደኛ ኢትዮጵያዊነት አይሰማቸውም?"
"
ዶክተር ዓቢይ በሥልጣን ብሎም በህይወት እስካለ አልሰጋም። ከዚያ በኋላ ግን የሚያሰጋ ነገር ሊመጣ ይችላል።"

‹‹በዚህ የለውጥ ወቅት ሠሜን ሸዋ ምንም እንቅስቃሴ አለማድረጉ ለምንድነው?›› ያሉኝም አሉ፡፡



ደባርቅ አዲስ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተላትና አዲሱ ሰሜን ጎንደር ዞን ማዕከል የሆነች ከተማ ነች፡፡ በዋዜማ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፡- ‹‹በሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደባርቅ / አብይ ያስመዘገቡትን ለውጥ በመደገፍ እሁድ ለሚደረገው ልፍ የከተማዋ ወጣቶች ከተማዋን በሰንደቅ አላማ የማስዋብና የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረጉ ነው፡፡››

ፈንታዬና አንድ በሱ ስር ያለ ሰራተኛው ሰኞ ማታ ለፌደራል የሚላክ ሪፖርት ሲያጠናቅሩ ሰራተኛው ቁጣ የሚመስል ንግግር ፈንታዬ ሲመልስ ሊጣሉ መስሎኝ ነበር፡፡ የንግግር ዘያቸው መሆኑ ወዲያው ገባኝ፡፡ እንግሊዝኛ እንደ ሮቦት በአንድ ድምጽ አታውሩ ድምጻችሁን ከፍና ዝቅ አድርጉ የተባለው በደንብ የገባኝ የጎንደርን አማርኛ ስሰማ ነው፡፡ ሪፖርታቸውን ሲጽፉ ታይፕ በማድረግ አግዣቸው አጠር ባለ ጊዜ ጨራርሰን ቅዳሜ ምሽት ላይ ወደቤት ገባን፡፡

በዚህ ዕለት በደባርቅ ከተማ ሰልፍ ነበር፡፡ ለዶክተር ዓቢይ የተደረገ የድጋፍ ሰልፍ ሲሆን የወልቃይት ኮሚቴዎች ተገኝተዋል፡፡ ከመተማ የመጡ አንዲት ሴትዮ ባለቤታቸው እንደተገደሉባቸው ተናግረው ህብረተሰቡ የመጣውን ለውጥ እንዲደግፍ አሳስበዋል፡፡ በደባርቅ የወጣው ባንዲራ እርዝመት 430 ሜትር ነበር፡፡ ምክንያቱም ከደባርቅ አስመራ 430 ኪሎሜትር ስለሚርቅ ነው፡፡ ሰልፉ በማንኛውም የሃገሪቱ ክፍል በተደረጉ ሰልፎች ላይ እንደታየው ተስፋ የሰነቀ ነበር፡፡ 



የጎንደር የንግግር ዘዬ ከለመድኩት ከሸዋው ተለየብኝ፡፡ ዘዬው ከአንዳንድ ነገሮች አንጻር ልዩነት አለው፡፡ ከቃላት ማጥበቅና ማላላት አንጻር ለምሳሌ ‹መለያያ› የሚለውን ቃል ሁለቱንም ያዎች አጥብቃ አንዲት የከተማ ጽዳት ሰራተኛ ስትገር ሰማሁ፡፡

ይህን መለያያ የሚለውን ቃል የተጠቀመችው ደግሞ አንድን የዛፍ ቅርንጫፍ ለምትጎትት ጓደኛዋ መለያያውን ያዢና ጎትቺው ለማለት ነው፡፡ በሸዋ ይህ ነገር ምንድነው የሚባለው? ደብረ ብርሃን ተመልሼ ሁለት ጎረቤቶቼን ጠይቄ ‹‹ቅጥያ ወይም ክንፍ›› ሊሉት እንደሚችሉት ነገሩኝ፡፡   

ኤዲ….ያ፣ ኧረ ወዘተ የመሳሰሉ በንግግር መገረምን ወይንም አለስማማትን የሚያመለክቱ ቃላትም በሰፊው ይነገራሉ፡፡ ቃላቱን ሲናገሩ ድምጻቸውን ከፍና ዝቅ አደራረጋቸው የራሱ ውበት አለው፡፡



እሁድ፣ ሐምሌ 8፣ 2010 ዓ.ም.

ፈንታዬ ጥላሁን ማነው?

ጎንደር - አምባጊዮርጊስ - ዳባት - ደባርቅ - አዲርቃይ - ጠለምት የሚለውን መስመር ይዛችሁ ከሄዳችሁ ወደ ፋንታዬ የትውልድ መንደር መዝለቅ ትችላላችሁ፡፡ መንደሩ በተከዜ ተፋሰስ ትገኛለች፡፡ በፈንታየ አገር ዓሳ ይለማል፡፡ 95 በመቶ የተከዜ ሃይድሮኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ውሃ ያረፈው እነርሱ  ወረዳ መሬት ላይ ነው፡፡ ተፈናቅለው መጠነኛ ካሳ ተክሰዋል፡፡ የልማቱ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ስላላቸው አሁንም እንደሚጠይቁ ነግሮኛል፡፡  ጎንደርም ላይ እንዳየሁት የዚህ አካባ ነዋሪዎች ዓይናቸው ላይ 11 ቁጥር ምልክት አላቸው፡፡ አማርኛ እንጂ ትግሪኛ አይችሉም፡፡ ወደ አጎራባች የትግራይ ከተሞች እየገቡ የበለጸጉም አሉባቸው፡፡


እሁድ ጎንደር ተመልሼ ገበያውንና ሰለሞንን አገኘሁ፡፡ ማታ በተኛሁበት ወቅት ሌሊት 10፡00 የተከሰተውን አስመልክቼ በፌስቡክ ይህን ለጠፍኩ ‹‹ታየ በላይ ሆቴል፣ ጎንደር የተነሣው መጠነኛ እሣት ጠፍቷል። ለሠላሣ ደቂቃ አንዱ ክፍል ነዶ ነበር። ችግሩ የኤሌክትሪክ ይመስላል። መብራቱ ቆጣሪም ጠፍቶ ብልጭ ድርግም ይላል። እኔ ከጎኑ ባለ ፔንሲዮን በሰላም እገኛለሁ።››

በዚህ ጊዜ በርካታ የፖሊስ አባላትም መሳሪያዎቻውን ይዘው መጥተው ነበር፡፡ እንግዲህ አጋጣሚ መሆኑ ነው፡፡



ሰኞ ሐምሌ 09፣ 2010

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍሬ ቦሌ ደረስኩ፡፡ አንድ ወዳጄንም ተቀጣጥረን አገኘሁት፡፡ ብዙ ልምድ ያለው ስለሆነም የዶክተር ዓቢይን ነገር እንዴት እንዳየው ጠየኩት፡፡ እንደወደደው ነገረኝ፡፡ እጁ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ማድረጉን አየሁ፡፡ ለድምር ሰልፍም እንደተገኘ ነግሮኛል፡፡



ማክሰኞ ሐምሌ 10፣ 2010 ዓ.ም.

ወደ አዲስ አበባ ሰኞ ስለተመለስኩ ማክሰኞ ጠዋት ሳርቤት ወደሚገኘው ወደ ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሄድኩ፡፡ በዚያም የታዳጊ ልጆች ንባብ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች አገኘሁ፡፡ ለእነርሱም በኦሮምኛ ቋንቋ የተዘጋጁትን 45 ተረቶች ሰጠሁ፡፡ የአማርኛና የእነንግሊዝኛም ጨምሬላቸዋለሁ፡፡ አድራሻ ተለዋውጠንና ወደፊትም በጋራ ለመስራት ተነጋግረን ተለያይተናል፡፡

ለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የ20 000 ብር መጻሕፍት ከአከፋፋይ ገዝቼ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ የአንድ ሳምንት ቆይታዬም በዚሁ ተጠናቋል፡፡




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...