ሐሙስ 6 ኤፕሪል 2023

‹‹እኛን ንቀሽ!›› - ሕግ አስከባሪ በተሳሳተ እሳቤ ሲመራ

 

‹‹እኛን ንቀሽ!›› - ሕግ አስከባሪ በተሳሳተ እሳቤ ሲመራ

 መዘምር ግርማ

 

የደህንነት አባላት ጋዜጠኛ ገነት አስማማውን በቁጥጥር ስር አውለው ወዳልታወቀ ቦታ ሲወስዷት የተቀረፀውን ንግግር ሰማሁት፡፡ ከድምጽ ፋይሉ ወቅቱ ስለነበሩ ፀያፍ ንግግሮች፣ ወከባ፣ የመብት ጥሰት ትረዳላችሁ፡፡ ‹‹እናትሽን …፣ አንቺን ብሎ ጋዜጠኛ … ወዘተ.›› የሚሉትን ስድቦች ሰምተናል፡፡ ስደብና ድብደባ በኛ ዓይነቱ ሰብዓዊ መብት ባልታወቀበት አገር የተለመደ ስለሆነ አንደነቀኝም፡፡ አንዲት ሌላ ጉዳይ ግን የበለጠ አትኩሮቴን ሳበችው፡፡ ከወሰዷት ሰዎች አንዱ ከተናገረው ንግግር አንዷ ክፍል የደህንነት አባሉን ለዚህ አፀያፊ ተግባር ያነሣሣውን ምክንያት የምታሳይ መሰለኝ፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛዋን ለምርመራ እንደምትፈለግ ነግሮ መውሰድ ሲችል ያደረገውና የተናገረው ሁሉ ትክክል ስላልሆነ ነው፡፡ መቼም አለቆቹ ሳታዋርድና ሳትደበድብ ለምን አመጣህ የሚሉት አይመስለኝም፡፡ ወይም ራሱ ዕድሉን ተጠቅሞ ግለሰቧን ለማዋረድና ለመደብደብ ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ‹‹እኛን ንቀሽ!›› የምትለው ከግለሰቡ የወጣችው ንግግር አደገኛ ነች፡፡ በስንት የመከላከያ፣ የልዩ ኃይል፣ የፖሊስ፣ የደህንነት፣ የሕግ አስከባሪ፣ የምክርቤት ወዘተ አባላት ዘንድ ይህች እሳቤ ትኖር ይሆን? የዚህች እሳቤ ጦስስ የት ያደርሰን ይሆን? ጦሱ የት እንደሚያደርሰን ከማሰብ ይልቅ እሱን ለጊዜ ሰጥተን እሳቤው ስለሚታረምበት ሁኔታ እንምከር፡፡ እሳቤው መታረም አለበት፡፡ የሕዝብ አስተዳዳሪና የሕግ አስከባሪ ቅዠቶችን ማስተናገድ የለበትም፡፡ ትንቀናለች ያለው ግለሰብ እንደምትንቀው በምን ሊያረጋግጥ እንደቻለ  ቢነግረን ጥሩ ነበር፡፡ የሷን ዘገባዎች ሰምቷል ወይስ ያለምንም መረጃ ለድምዳሜ በቅቷል፡፡ ለእኔ ግን ከቅዠት የዘለለ አይደለም፡፡ ፍርደ-ገምድልነትን፣ ብዝበዛን፣ አ-ፍትሐዊነትንና ማናቸውንም አጉል አሰራር መቃወም ንቀት ሳይሆን ለመብት መቆም ነው፡፡ ይንቁናል ያለ ሰው በዚህ የተሳተ እሳቤ ሰውን መጉዳቱ ስለማይቀር ራሱን ከዚህ ሃሳብ ማጽዳት አለበት፡፡  

ይህን ካልኩ በኋላ ግን በግሌ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ መከባበር ወይም መናናቅ የማስበውን ብጠየቅ የምሰጠው መልስ አለኝ፡፡ እስከ ዛሬ ባየሁት መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደማንኛውም አገር ሁሉ ሁለቱም አሉ የሚል ነው፡፡ ሕዝቡ ይከባበራል፣ ይናናቃል፣ ይዋደዳል፣ ይጠላላል፡፡ በሥልጣኔና በጊዜ ሂደት መልካሙ እየጎላ አሉታዊው የሚስተካከል ይመስለኛል፡፡  

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...