ራሳችንንና በዙሪያችን ያለውን ዓለም በምናይበት መሰረታዊ የሕይወት መመሪያ ወይም አመለካከታችን ላይ መስራት ከፍተኛ የሆነ ጠቃሚ ለውጥ ያመጣልናል፡፡ ይህ የሕይወት መመሪያችን የአመለካከታችን፣ የባሕሪያችንና ከሌሎች ጋር ያሉን ግንኙነቶች መነሻ እንደመሆኑ፤ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስለሆነም እርሱ ላይ ለመሥራት የሚጠቅሙ አስር ጥያቄዎችን ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡ ለጥያቄዎቹ ለእያንዳንዳቸው ከአራት እስከ አስር መስመር የሚሆን ምላሽ ይጻፉ፡፡ በመጨረሻም ራስዎን ለመመልከት ዕድሉን ያገኛሉ፡፡ ምላሽዎ ምስጢራዊ ካልሆነ እሱን፤ ከሆነ ደግሞ አጠቃላይ አስተያየትዎን ይላኩልኝ፡፡
1. በተሳሳተ ግምት ምክንያት ወደ ውሳኔ በፍጥነት የሄዱበት የሕይወት አጋጣሚ አለዎት? እስኪ ያንን ሁኔታ ይግለጹት፡፡
2. ያ የተሳሳተ ግምት ምን ነበር?
3. ስለ ሌሎች ሰዎች የነበሩዎትን የተሳሳቱ ግምቶችንም ያስቡ፡፡ ከነዚያ ግምቶች በዚህ ሳምንት አንደኛውን ለማስተካከል ምን ማድረግ ይችላሉ?
4. ከአገርዎ ውጪ ወይም በአገርዎ ውስጥ ወደ ሌላ የአገርዎ ክፍል ሄደው ያውቃሉ? እዚያ ምን የተለየ ነገር ተመለከቱ?
5. የሰዎች ሁኔታና አድራጎት እንደጠበቁት ነበር? እርስዎስ ስለ ድርጊቶቻቸው ምን አሰቡ?
6. የጉዞ ገጠመኝዎን አሁን መለስ ብለው ሲመለከቱት ሰዎች ስለ እርስዎ ምን ያሰቡ ይመስልዎታል? እነርሱ ስለ እርስዎ የነበሯቸው ሃሳቦች እርስዎ ስለእነርሱ ካነበሩዎት ጋር ይመሳሰሉ ይመስልዎታል?
7. በጉዞዎ ሰዎችን ለመተዋወቅ ችለው ከነበረ ያ አጋጣሚ ስለነእርሱ የነበሩዎትን አስተሳሰቦች እንዴት ቀየራቸው?
8. ወደ ቤትዎ ወይም ወደ ስራ ቦታዎ ሊወስዱዎ የሚችሉ የተለያዩ መንገዶችን ያስቡ፡፡ የተወሰኑት መንገዶች ከሌሎቹ በበለጠ ውስብስብ ናቸው? አንዱ መንገድ ከሌሎቹ በተለየ አመቺ ነው? ለምን ሆነ? ወይስ ለምን አልሆነም?
9. ወደ ቤትዎ የሚወስድ እስካሁን የማያውቁት መንገድ አግኝተው ያውቃሉ? በተለያዩ መንገዶች መሄድ ያመጣብዎት ያልተጠበቁ ስሜቶች ምንድን ነበሩ?
10. አሁን ከሰዎች ጋር የሚግባቡበትንና የሚኖሩበትን መንገድ ያስቡ፡፡ የተለያዩ ሰዎችን የመቅረቢያ መንገዶች ያሉ ይመስልዎታል? ምን ዓይነት አዳዲስ መንገዶችን ሊሞክሩ የሚችሉ ይመስልዎታል?