ወዳጆቼ፣
ይህን ለተረጎምኩት መጽሐፍ መግቢያ የጻፍኩትን ጽሑፍ አንብባችሁ አስተያየት ብትሰጡኝ ደስ ይለኛል፤ ስለትብብራችሁ አስቀድሜ አመሰግናለሁ፡፡
ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ
ከስቲቭ ኤርዊን ጋር
ሁቱትሲ
የወጣቷ ልብ አንጠልጣይ ትውስታዎች
ተርጓሚ
መዘምር ግርማ
በተለያዩ ዘመናት በብዙ ሀገራት የሰው ልጅ በዘውግ እየተቧደነ ሲጠቃቃ እንደኖረ ከታሪክ ድርሳናት እንረዳለን፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያክል 13 ሚሊዮን የአሜሪካ ቀደምት ሕዝቦች በአውሮፓውያን መጤዎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ በቤልጅዬሙ ንጉሥ ሊኦፖልድ ዳግማዊ ትዕዛዝ 10 ሚሊዮን ኮንጓውያን በተወለዱበት ቀዬ ሲገደሉ፤ ናዚ ጀርመኖች በበኩላቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎችን በዘመናዊ መንገድ በመግደያ ጣቢያዎች እያከማቹ በጅምላ ፈጅተዋቸዋል፡፡ በመሰረተ-ቢስ ጥላቻና በራስ-ወዳድነት መነሻነት ይህ ሁሉ ሕዝብ በግፍ ተገደለ እንጂ እነዚህን የተጨፈጨፉ ሰዎች የተጠቀሱት ሀገራት ከነጨፍጫፊዎቻቸው ለማኖር የተፈጥሮ ገጸ-በረከቱ ነበራቸው፡፡ በየሀገሩ የተፈጸሙትንና ታሪክ ሲያወሳቸው የሚኖሩትን ጎልተው የወጡ ፍጅቶች በተመለከተ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም እንደጻፉት ቦስኒያ ውስጥ ሰርብ ያልሆኑት ዜጎች መጨፍጨፍ፣ አርመኖች በኦቶማኖች የደረሰባቸው እልቂት፣ ኩርዶች በሳዳም ሁሴን የተካሄደባቸው የዘር ምንጠራ፣ የካምቦዲያው ፖል ፖት ያካሄደው ገደብ የለሽ ጭፍጨፋ በዘር ጥላቻ ላይ ተመስርተው ከተፈጸሙ ግድያዎችና ሰቆቃዎች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በመካለኛው አፍሪካ በምትገኘው በሩዋንዳ የተካሄደውና አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የዘር ማጥፋት በንጹሐን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙ የተደራጁና መጠነ-ሰፊ ዘግናኝ ድርጊቶች አንዱ ነው፡፡ የዚች ሀገር ሁቱ መሪ ከሀገሪቱ ያባረራቸውን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱትሲ ስደተኞች ተመልሰው ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ በሕግ በመከልከልና ሀገር ውስጥ የነበሩትንም በማሰቃየት ቱትሲዎችን ከግፍ ጽዋ እንዲጎነጩ አስገድዷል፡፡ ከ1959 ጀምሮ ሁቱዎች ቱትሲዎችን በጠላትነት እንዲያዩ የሰበከው አገዛዙ ነው፡፡ ይህ ጸረ-ቱትሲ የጥላቻ ውትወታ በየወቅቱ ሁቱዎች ቱትሲዎችን የጥቃታቸው ሰለባ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል፡፡ የሩዋንዳው ጭፍጨፋ ሕዝብ በሰፊው ያተሳተፈበትና ‹ቱትሲዎች መጤዎች ናቸው› በሚለው የቆየ ቅስቀሳ ምክንያትነት በጨፍጫፊዎቹ ዓይን የነባርና የመጤ ግጭት ጉዳይ ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር ሁቱዎች ሥልጣንና ትምህርት እንዲያገኙ ቱትሲዎችን ማጥፋት እንዳለባቸው ተሰበኩ እንጂ በተፈጥሯቸው ገዳዮች ሆነው አይደለም፡፡ መንግሥት የጥላቻውን ስብከት እንዲያቆም፣ በቱትሲዎች ላይ ይፈጽም የነበረውን ግፍ እንዲተውም ሆነ ጭፍጨፋውን እንዳያካሂድ ለማድረግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የተመድ ሳይቃጠል በቅጠል ብለው ጣልቃ አልገቡም፡፡ ይህም ለተጨፍጫፊዎቹ ጀርባቸውን መስጠታቸው እስከአሁን እንዳስተቻቸው ነው፡፡
የሩዋንዳውን ፍጅት ከፈፀሙት ወንጀለኞች መካከል 35 ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ሰዎች በተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሲዳኙ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በሀገር-በቀሎቹ የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች ፍርድ አግኝተዋል፡፡ ሰውን እንደ እንስሳ በማደን ሲደሰቱ የነበሩና ከዘር ፍጅቱ ያመለጡ ሰዎች እንዴት ነው ወደፊት አብረው መኖር የሚቀጥሉት? የሚል ጥያቄ በሁላችንም አእምሮ መምጣቱ አይቀርም፡፡
በሩዋንዳ በቸልታ የታለፈው የዚህ የዘር ፍጅት መዘዝ የዛየርን መፈራረስ እንዳስከተለና እስካሁን መቋጫ ባላገኘው የኮንጎ ጦርነት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ሊያልቅ እንደቻለ ምርምሮች ያሳያሉ፡፡ የሩዋንዳው ሕመም መገረን ወደ ኮንጎ ሊተላለፍ የቻለው ይህች ሀገር የዘር ፍጅቱን የፈጸሙትን ወንጀለኞች በማስጠጋቷ ከሩዋንዳ መንግሥት በደረሰባት ተጽዕኖ ነው፡፡ ወደ ቻድ፣ ማእከላዊት አፍሪካ ሪፐበሊክና ዳርፉርም የዘር-ፍጅቱ ግርሻ ተላልፏል፡፡ ዓለማችን አንድ መንደር ሆናለች እየተባለም የዘር ጭፍጨፋ በዓለም የተለያዩ ክፍሎች በመፈጸም ላይ ነው፤ ስጋቱም እስከአሁን ድረስ እንዳንዣበበ አለ፡፡
ዘውግ-ተኮር የሆኑ መቃቃሮችንና አለመግባባቶችን በኀይል ለመፍታት ሲሞከር የሚደርሰውን ጥፋት አስከፊነት ከሩዋንዳው ጭፍጨፋ በላይ የሚያሳይ የለም ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዚች ሀገር ሕዝብ ሀገሩን ያወደመውን የዘር-ጭፍጨፋ ካስከተሉት ተግባራቱ መማሩንና ችግሩ እንዳይደገም መቁረጡን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በአዲሱ የሩዋንዳ ሕገ-መንግሥት መግቢያ ላይ ‹‹እኛ ሩዋንዳውያን፣ የዘር-ፍጅትንና ሁሉንም መገለጫዎቹን ለመዋጋትና ማናቸውንም ዓይነት የጎሣ፣ የክልልና ሌሎች ክፍፍሎችን ለማጥፋት ወስነናል›› የሚል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ካጡ በኋላ የደረሱበት ውሳኔ ሰፍሯል፡፡ ከውድመቱ ቀድሞ ግን ይህ ቢገባቸው እንዴት ጥሩ ነበር! ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የማጉላትና የማራገብ ጠንቅ የገባቸው በቅርቡ ነው፡፡ የአዲሲቷ ሩዋንዳ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ማንም ሰው ሁቱ ወይንም ቱትሲ ስለሆነ ብቻ የተለየ ጥቅም ወይም አገልግሎት ማግኘትም ሆነ ከሀገሪቱ መባረር የለበትም፡፡ ማናቸውም ሩዋንዳዊ ልጅም ሁቱ፣ ቱትሲ ወይንም ትዋ ነህ ተብሎ እንዲያድግ አይደረግም - ሩዋንዳዊ እንጂ፡፡ ለያይቶ ማየት ነውር ሆኗል፡፡
ይህ መጽሐፍ በ1994 በሩዋንዳ ከሁቱ ዘውግ የሚመደቡ ራሳቸውን ያደራጁ አካላት በተቀናጀ መልኩ በቱትሲዎችና አልፎ አልፎም ለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ባካሄዱት ፍጅት ወቅት ከግድያ የተረፈችው የቱትሲዋ የኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ትዝብትና ትውስታ ተተርኮበታል፡፡ ይህ የኢማኪዩሌ መጽሐፍ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመኖች ይሁዲዎችን ሲጨፈጭፉ በተደበቀችበት ማስታወሻ ስትጽፍ ቆይታ መጨረሻ ላይ የናዚ ወታደሮች አግኝተዋት የተገደለችውን የአና ፍራንክን ማስታወሻ የሚያስታውሰን ነው፡፡ ‹ሩዋንዳዊቷ አና ፍራንክ› ብለው የሚጠሯም አሉ፡፡ ከጭፍጨፋው ከገዳዮቿ ጋር በግንባር ጭምር ከተገናኘች በኋላ በተአምር የተረፈችው ይህች ሰው የእምነት ጽናትና ይቅር-ባይነት ቋሚ አርዓያ ነች፡፡ በዳዮቿን በዝምታ ብዛት ሳትቀጣ ምህረት በማድረግ እፎይታን ለግሳቸዋች፡፡ መጽሐፏ ሦስት ክፍሎችንና 24 ምዕራፎችን የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው ክፉ ቀን ዳር ዳር ሲል የሚለው ክፍል ከጭፍጨፋው በፊት የነበራትን ሕይወት ይዳስሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተደበኩባቸው ጊዜያት የሚል ሲሆን ከገዳዮች ተሸሽጋ የነበረችበትን ቆይታዋን ይተርካል፡፡ የመጨረሻውና አዲስ መንገድ የሚለው ክፍል ከጭፍጨፋው ማክተሚያ ቤተሰብ እስከመሰረተችበትና ተረጋግታ መኖር እስከጀመረችበት ጊዜ ያለውን ይይዛል፡፡ መጽሐፉ ስለ ሩዋንዳው ጭፍጨፋና ስለ ኢማኪዩሌ ታሪክ በሚገባ ከማስረዳቱ በተጨማሪ የአንባቢውን ስሜት በእጅጉ በሚስብ አቀራረብ ተጽፏል፡፡ ኢማኪዩሌ ይህን መጽሐፍ ስትጽፍ ለቋንቋው ውበትና ለቅንጅቱ ስምረት ሲባል የረዳት ካናዳዊ ጋዜጠኛና የልብ ወለድ ደራሲ ስቲቭ ኤርዊን ታሪኩን ያቀናበረው ልብ አንጠልጣይ አድርጎና በሚያስተምር መልኩ ነው፡፡ ምስል ከሳች የሆነ ገለጻና ለጽሑፉ ሕይወት የሰጠውን ምልልስ መጠቀሙም ጽሑፉን ማንበብ ከጀመሩ ሳይጨርሱ እንዳያቆሙት ያስገድዳል፡፡ ይህ የኢማኪዩሌ የመጀመሪያ መጽሐፍ እስካሁን ይህ የአማርኛው ትርጉሙ ሳይቆጠር ወደ 17 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ሽያጩም ከሁለት ሚሊዮን ቅጂ በላይ ነው፡፡ ኒው ዮርክ ታይምስ ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘ በማለት ያወደሰው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ‹‹የሰውን ልጅ መንፈስ እጅግ ከፍተኛ እሴቶች የሚያረጋግጥ›› ተብሎ በመወደስ የክርስቶፈር ሽልማትን ለኢማዩሌ አስገኝቷታል፡፡ ታሪኩ በተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጾ በመገናኛ ብዙኃን ቀርቧል፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተበረከተላት ባለ ታሪኳም ስላለፈችበትና ዓለማችንም ወደፊት ስለሚያስፈልጋት ሰላማዊ ዓለም በየአህጉሩ እየተዘዋወረች ታስተምራለች፡፡
የኢማኪዩሌን መጽሐፍ ያገኘሁት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ክፍል አነስተኛ የመጻሕፍት ስብስብ ውስጥ ነው፡፡ የመጻሕፍት ስብስቡን ያደራጁት አሜሪካዊቷ ካትሪን ይህን መጽሐፍ ገዝተው አሊያም ከወዳጆቻቸው በልገሳ አግኝተውት ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፉን ማንበባቸውንም ሆነ ሥራዬ ብለው ስለዘር ጭፍጨፋ አውዳሚነት እንድናውቅ ፈልገው ማስቀመጣቸውን ባላውቅም ይህን መጽሐፍ የለገሱን ኢትዮጵያን እንደሚያፈቅሩ አዘውትረው ይነግሩኝ የነበሩት አፍሪካ-አሜሪካዊቷ ጡረተኛ ካትሪን ክራይተን ሼይ ታላቅ ሥራ ሰርተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌፍት ቱ ቴል (Left to Tell) የሚለውን የኢማኪዩሌን መጽሐፍ የተረጎምኩት ምን ልተርጉም ብዬ የሚተረጎም መጽሐፍ ሳፈላልግ አግኝቼው ሳይሆን ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ እጄ ገብቶ ካነበብኩት በኋላ ሥሜቴን በእጅጉ ስለነካውና የሚሰጠው የይቅርታና ከውድመት የማገገም ትምህርት ለሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አስፈላጊ መሆኑን በማመኔና ለአማርኛ አንባቢያን ተርጉሞ ማቅረብ የዜግነት ግዴታዬ መሆኑ ስለገባኝ ነው፡፡ መሳጭና አስተማሪ ታሪኩ በዚች የበርካታ ዘውጎች መገኛ በሆነችው ሀገራችን አብሮነታችንን ተንከባክበን የማቆየትን ጸጋ ስለሚያስተምረንም ነው፡፡ መጽሐፉን ወደ አማርኛ ስተረጉም በታሪኩ ውስጥ የሚነሱትን ማናቸውንም ሃሳቦች እንዳይቀሩ በማሰብ ለይዘት ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ ቋንቋውን ጉራማይሌ ላለማድረግም በተቻለኝ መጠን አማርኛ አማርኛ የሚሉ ቃላትን ለመጠቀም ሞክሬያለሁ፡፡
ኢማኪዩሌን እየተረዳኋት የመጣሁ ይመስለኛል፡፡ ያለፈችበትን እያንዳንዱን ሥቃይ መላልሼ ስላጤንኩትና ስላሰብኩበት አብሬያት የነበርኩ ያህል ይሰማኛል፤ ሰቀቀኗም በአእምሮዬ ይመጣብኛል፡፡ ሁላችንም እርሷ የታደለችው ይቅር ባይነትና መረጋጋት እንዲኖረን እመኛለሁ፡፡ ማናቸውም የሰው ልጅ በተፈጥሮ አስገዳጅነት በሚገባበት ዘውግ መነሻነት ብቻ አላስፈላጊ ሥጋት ውስጥ እንዳይገባ፣ በማናቸውም መንገድ ጉዳት እንዳይደርስበትና ከሌሎች ጋር በመፈቃቀርና በመተሳሰብ እንዲኖር እስኪ እንጣር፡፡
የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ በአፍሪካ ህብረት አሳሳቢነት መላው አፍሪካውያን የኅሊና ጸሎት እንድናደርግ በተላለፈው መልዕክት ምክንያት የፍጅቱን ሰለባዎች እንድናስብ መደረጉን አስታውሳለሁ፡፡ ይህም የተደረገው የዚህ ዓይነቱ ከአብዛኞቻችን አእምሮ መጥፋት የማይችል አሰቃቂ ድርጊት በማንኛውም የዓለም ክፍል ባለ መጪ ትውልድ ላይ እንዳይታሰብም ሆነ እንዳይፈጸም ለማሳሰብ ይመስለኛል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ስለ ሩዋንዳው የዘር-ጭፍጨፋ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች፣ በመጻሕፍት፣ በተንቀሳቃሽ ምስል ትዕይንት (ለምሳሌ፣ ሆቴል ሩዋንዳ፣ ሹቲንግ ዶግስ፣ ሳምታይምስ ኢን ኤፕሪል) እና በሌሎችም መንገዶች ግንዛቤ አግኝተናል፡፡ የሀገራችን ሰላም አስከባሪ ሠራዊትም ሩዋንዳ ከጭፍጨፋው ታገግም ዘንድ ማገዙ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሩዋንዳው ችግር ላይ በአማርኛ የተጻፉ ጽሑፎችን እጥረትም በመጠኑ በመፍታት ሌሎችም እንዲጻፉ ያነሳሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ችግሩ በአንዲት ከጭፍጨፋው በተረፈች ግለሰብ ዓይን እንዴት እንደሚታይ እንታዘብበታለን፡፡ በነገራን ላይ ጨፍጫፊዎቹንና ራሳቸውን ቱትሲዎቹንም ጨምሮ ቱትሲዎች ከኢትዮጵያ የሄዱ ናቸው የሚሉ አካላት አሉ - ፡፡
አንድ ዘውግ ሌላውን በጠላትነት ፈርጆ ሲያጎሳቁል፣ ሲያገል፣ ሲያሳድድ፣ ሲያስር፣ ሲገድል፣ ብሎም እጅግ የከፋውን የዘር-ፍጅት ሲፈጽም ምን ዓይነት ውድመት እንደሚያስከትል ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ አንድ በመቻቻል ላይ የተጻፈ ጽሑፍ እንደሚያትተው ዘውግን መነሻ ያደረገ ጭፍን ጥላቻ፣ አግላይ ብሔራዊ ስሜት (የሌላን ሀገር ዜጎች እንዲጠሉ የሚያደርገው)፣ ወገናዊነትና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት የሚያሳድጉት በዓለማችን የተወሰኑ ክፍሎች የነገሰው ተቻችሎ ያለመኖር አውሬ ሰዎችን በሰውነታቸው እንዳንቀበል፣ ይቅር ባይ እንዳንሆንና ሰላማዊ ግንኙነትም እንዳይሰፍን ያደርጋል፡፡ የዘር-ፍጅት እንዳይፈጸም በመከላከልና ሲፈጸምም በማስቆም ላይ የሚሰራው ተቋም የጄኖሳይድ ዎች ሊቀመንበር የሆኑት ግሪጎሪ ስታንተን ባቀረቡት ምርምር የሰው ልጆችን የደደረ ልብ የሚጠናወተው ይህ አውዳሚ አባዜ ስምንት ደረጃዎች እንዳሉት ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸሙት ደረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ. መከፋፈል (Classification) - እኛና እነርሱ ብሎ በመከፋፈል ለየት ይላሉ ተብለው የሚታሰቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀልድም ጭምር በማንቋሸሽ በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት አለማክበር
ለ. የሚታይ መገለጫ መስጠት (Symbolization) - ይህ የጥላቻ ግልጽ መገለጫ ሲሆን ይሁዲዎች በናዚ ጀርመን ቢጫ ኮከብ ያለበት ልብስ እንዲለብሱ እንደተደረገው ነው፡፡
ሐ. ከሰው ክብር ዝቅ ማድረግ (Dehumanization) - ይህ ተግባር ከራስ የተለዩትን ሰብዓዊ ክብርም ሆነ መብት በመንፈግ ይፈጸማል፡፡ በሩዋንዳ ሁቱዎች የቱትሲ ዘውግ ተወላጆችን ‹በረሮ› ይሏቸው እንደነበረው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሂደት ገዳዮቹ ‹እየገደልን ያለነው ሰው አይደለም፤ ታዲያ ድርጊታችን ምኑ ላይ ነው ጥፋትነቱ?› እንዲሉ መንገዱን ይጠርግላቸዋል፡፡
መ. ማደራጀት (Organization) - በጥላቻ ላይ የተመሠረቱ መንግሥታት አንድን ሕዝብ የሚያጠፋላቸውን ኀይል ያሰለጥናሉ፡፡
ሠ. በተቃራኒ ጎራዎች ማሰለፍ (Polarization) - ሕዝቡ በዘውጉ ከጨፍጫፊውና ከተጨፍጫፊው ወገን ሚናውን እንዲለይ ይደረጋል፡፡ በብዛት ይህ የሚሆነው በጥላቻ ቡድኖች ውትወታ በጋዜጣና በመገናኛ ብዙሃን የጥላቻውን መርዝ በመርጨት ነው፡፡ አንዱን ዘውግ ከሌላው ለይቶ በማውጣት ጠላት ነው ብሎ ማወጁ ጀርመኖች ይሁዲዎችን ከመፍጀታቸው በፊት በምዕራብ አፍሪካ በሄሬሮዎች ላይ የ20ኛውን ክፍለዘመን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሲፈጽሙ፣ ይሁዲዎችን ሲፈጁና የሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ሲጨርሱ የገዳዩን ዘውግ አባላት በቀላሉ ለማሳመንና ለህሊናው እንዲቀለው ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡
ረ. ዝግጅት (Preparation) - ሰለባዎቹ በልዩነቶቻቸው ተለይተው ይፈረጃሉ፡፡ የጭፍጨፋው ንድፍ አውጭዎች ሰዎችን በመኖሪያ አድራሻቸውና በሌሎችም መለያዎች ይፈርጁና ለፍጅት ያዘጋጇቸዋል፡፡
ሰ. ፍጅት (Extermination) - በታቀደና ሆነ ተብሎ በተመቻቸ ዘመቻ የጥላቻ ቡድኖቹ ሰለባዎቻቸውን ይጨፈጭፋሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘር-ፍጅት ማንነታቸውን መለየት እስኪከብድ ድረስ ተጨፍጭፈዋል፡፡
ሸ. ክህደት (Denial) - ግድያውን የፈጸሙት ወይንም ቀጣይ ትውልዶች ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልተፈጸመ በማስመሰል ክህደት ይፈጽማሉ፡፡
ከዚህ የጭፍጨፋ ሂደት የምንረዳው የዘር-ፍጅት በአንድ ሌሊት ያለምንም ዝግጅት የሚፈጸም አለመሆኑን ሲሆን ራሳችንን ከላይ ከተጠቀሱት በሌላው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ክስተቶች ፈጽሞ ማራቅና የዕለት ከዕለት ድርጊቶቻችንን መገምገምም ያስፈልገናል፡፡ እነዚህን የዘር ፍጅት አመላካች ሂደቶች በማናቸውም ደረጃ በእንጭጩ መቅጨት ከተቻለ የዘር ፍጅትን ማስቀረት ይቻላል፡፡
በመጨረሻም ይህን መጽሐፍ አንዴ አንብበን ስንተወው ሳይሆን ደግመን ደጋግመን ስናነበው፣ ሃሳቡን ስናብላላውና ስንወያይበት ታላቅ ትምህርት እንቀስማለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ እርስዎም ይህን አስከፊ ታሪክ አንብበው ሲጨርሱ ከአሁኑ በላቀ ሁኔታ ለሰው አዛኝ፣ ርህሩህና በጎ-አሳቢ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡ እንደ ሩዋንዳው ችግር ባሉ ጠንቆች ላይ የራሳችንን ግንዛቤ ለማጎልበትና ሀገራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የማኅበረሰባችንን ጤናማ መስተጋብር ለማጠናከር እንጠቀምበት ዘንድ የሚረዳንን ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡት በአክብሮት እጋብዝዎታለሁ፡፡
መልካም ንባብ!
መዘምር ግርማ (mezemir@yahoo.com)
ደብረ ብርሃን
2008 ዓ.ም.