2019 ማርች 31, እሑድ

የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ፣ የኢትዮጵያና የዓለም ቴሌኮሙኒኬሽን ትረካ

የመጽሐፍ ዳሰሳ
የመጽሐፉ ርዕስ - የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ፣ የኢትዮጵያና የዓለም ቴሌኮሙኒኬሽን ትረካ
ደራሲ - በኩረ ጠቢባን ኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ ወልደ መስቀል
የታተመበት ዘመን - 2011 ዓ.ም.
ዋጋ - 195 ብር
ዳሰሳ አቅራቢ - መዘምር ግርማ mezemir@yahoo.com
መጽሐፉ ለእምየ ምኒልክ መታሰቢያ ተደርጎ በውስጡ ምስላቸውና ውለታቸው የታወሰበት አንድ ገጽ ስላለ፤ እዚህም ላይ የመጀመሪያውን ክፍል ለንጉሠ-ነገሥታችን በአክብሮትና በፍቅር አበረክታለሁ፡፡
ቤተሰቦቻቸው
መጋቢት 2፣ 1928 ዓ.ም. በአንኮበር የተወለዱት የኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ እናት ወይዘሮ አስካለማርያም ታሪክ ልብ ይነካል፡፡ ምክንያቱም ወይዘሮ አስካለማርያም እናታቸውንም ሆነ ልጃቸውን በወሊድ ማጣታቸው ነው፡፡ እናታቸው እሳቸውን ሲወልዱ መሞታቸው ሳያንስ፤ ልጃቸውም ልጇን በወለደች በአስረኛው ቀን በልጅነቷ ተቀጠፈች፡፡ ይህም አነሰዎ ብሏቸው በእህቱ ሞት በተሰማው ጥልቅ ሐዘን ምክንያት ልጃቸው የማነም ራሱን አጠፋ፡፡ በዓመቱም ትልቁ ልጃቸው በበሽታ ምክንያት አርፏል፡፡
ግጥምጥሞሹ ደግሞ የደራሲው አባት መምህር ራስ ወርቅም እናታቸውን በወሊድ ያጡ ነበሩ፡፡ ራስ ወርቅ ምሁርና ደራሲ ነበሩ፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የመጀመሪያው የቋንቋና ሥነምግባር መምህርና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት መስራች ናቸው፡፡ በአስካለማርያም አባት አስገዳጅነት የተጀመረው የተረፈ ቤተሰቦች ትዳር ፍሬ እያፈራና ፍሬው እየተቀጠፈበት ቢያዘግምም በተረፈ ምክንያት ከዛሬ ደርሷልና የእርሳቸውን የሕይወትና የሥራ ጉዞ አብረን እናያለን፡፡
የእህት ወንድሞቻቸው ወግ
እህታቸው ወይዘሮ ሸዋዬ ያሏቸውን ነገር ያለ ቀብራቸው ዕለትም ትንፍሽ ያሉት አይመስል፡፡ በስንብት ቃላቸው ካቀረቡት የሚከተለውን እነሆ፡- ‹‹እንዲያው ይኽ ወዳጅህ (ፕሮፌሰር መስፍንን ማለቷ ነው) እዚሁ ቁጭ ብለን የላችሁም ይበለን፤ እንዲያው በአፉ ሙሉ አማራ የለም ብሎ እኮ ተናገረ፤ መንፈስ አደረገን? ወቸ ጉድ፤ እኛ እንደሆን ቢጨምቁንም ሌላ ዘር አይወጣን፤ ምን ብለው ሊጠሩን ይሆን?››
ለወይዘሮ አበበች ራስ ወርቅ ስንብት ተረፈ የተናገሩት ከልቤ ስለቀረ እነሆ፡- ‹‹የራስ ወርቅ ልጆች አንድ በአንድ ሹልክ እያላችሁ፤ ወደ ዘላለም ቤታችሁ ሄዳችሁ፡፡ ድሮም ስንወለድ መጨረሻ እኔ ነበርኩ፡፡ብቻየን ቀረሁ፤ የቤታችንን ደጃፍ ልዘጋ፡፡››
ሜጀር ዮሐንስ ራስ ወርቅ፡- የተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ተማሪ፣ የጦር መኮንን ምሩቅ የጥቁር አንበሣ፣ የማይጨው ዘማች፣ የነራስ አበበ አረጋይ የዘመን-ጓድ የነጻነት አርበኛ፣ የባንዶች ሰለባ፣ የ1929 ሰማዕት፡፡
አቶ ጥሩነህ፡- የፈረንሳይ ተማሪ፣ የጎረቤላ የጣሊያን አስተርጓሚ፣ የውስጥ አርበኛ፡፡
አቶ የማነ፡- በታናሽ እህቱ ሞት ምከንያት ራሱን ያጠፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተማሪ፡፡
ወይዘሮ አዳነች፡- የምትፈራው ያለዕድሜ ጋብቻ በልጅነቷ በወሊድ ምክንያት የቀጠፋት ቆንጆ፡፡
ተረፈ ራስ ወርቅ በኢጣሊያ ወረራ አንኮበር እስከ ታሪካዊው የምኒልክ ቤተመንግሥት በቦንብ ስትደበደብ በተዓምር የተረፉ ናቸው፡፡ ተረፈ የሚለውም ስም የወጣላቸው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በቅርቡ በዚህ ሰበብ አንድ ሰው የተቀኙላቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
‹‹ያነየ ከእሳት ቃጠሎ የተረፈ የዳነ
ዛሬ በስራው የብዙዎቹን አፍ አስከደነ፡፡››
የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት (ቲኤምኤስ)
ፊደልን በቤት ከአባታቸው፣ አንደኛ ክፍልን በዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም የተቀረውን በተፈሪ መኮንን ተምረዋል፡፡ አንዳንድ የትምህርት ቤት ትዝታ ሲያነሳሱ ‹‹ከትምህርት ቤት ተቀጽላ ስራዎች በጣም የወደድኩትና በህይወቴም ላይ ዘላቂ ለውጥ ያመጣው የቦይ ስካውት ተቋም ነው፡፡ …›› ይሉናል፡፡ አንድ ስካውት በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ በዛሬው ቀን ምን ደግ ነገር ሰርቻለሁ ብሎ ራስን ይጠይቃል ወዘተ. የሚል ቃለ-መሐላም ተቀበሉ፡፡ በጸባይና አስተሳሰባቸው ላይ ዘላቂ ለውጥም አመጡ፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የዉጪ ሃገር መምህራንን ሁኔታና የተማሪዎችን ተቃውሞ የመጀመሪያ ቀናት ሁናቴ ዳሰስ ዳሰስ አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኑሮና ትምህርት
የተስፋዬ ገሠሠና የሥብሐት ገብረእግዚአብሔር የዘመን-ጓድ ናቸው፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱን ከልጅነታቸው ጀምሮ ፊትለፊት ማየት ይችሉ ከነበሩት ትውልድ ውስጥ ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የታደሙበት ክርክር ላይ በተከራካሪነት ተሳትፈዋል፡፡ እስከ ፓርላማም የደረሰና ምክር ቤቱ ያላጸደቀው ዕቅድ በዚሁ ምክንያት ሊጠነስሱ ችለዋል፡፡ አያያዛቸው ላቅ ያለና ለሃገር የሚያስቡ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
የሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት (RPI) ትምህርትና ኑሮ
ከ3000 ተማሪ 16 ጥቁሮች ብቻ በነበሩበት ከሌጅ የነበረው ዘረኝነት ፈታኝ ቢሆንም ተረፈ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ለስራ ተመልሰዋል፡፡
የሥራው ዓለም
በእቴጌ ሆቴል ረፍት አድርገው ስራ በመፈለግም ቴሌ ይቀጠራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ የሙያ ስራ እየሰሩ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ፈጠሩ፡፡
ጋብቻ
ወይዘሪት ብርሐኔ አስፋውን ያገኟት በአንድ ሰርግ ላይ ነው፡፡ በርሷ ላይ ያሳዩትን ፍላጎትም ከዳር አድርሰውታል፡፡ ሠርጋቸው በእቴጌ ሆቴል፣ ጫጉላቸው በኬኒያ ናይሮቢ ተካሂዷል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ምስረታ ዕለት የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው ስለተወለደ አንድነት አሉት፡፡ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት ልጆችን ወልደው ለማዕረግ አብቅተዋል፡፡
ዓለምአቀፋዊ ሙያዊ ሥራና ተልዕኮ በዓለም አቀፍ ቴሌኮሚኒኬሽን ማህበር (ITU)
ባመዛኙ በበለጸጉት አገራት ተጽዕኖ ስር ወድቆ በነበረው ማህበር የመጀመሪያው ባለሙያ የአፍሪካ ተወላጅ ሰራተኛ በመሆን መስሪያ ቤቱን የተቀላቀሉት ተረፈ የአፍሪካ ክፍል ዋና ኃላፊትን ወስደዋል፡፡ አፍሪካን በማይክሮዌቭ የማስተሳሰር ስራን በፓናፍቴል ፕሮግራም ተወጥተዋል፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ሳተላይት መገናኛ መረብንም አጥንተዋል፡፡ የአይቱዩ ዋና ጸሐፊ ልዩ የፖሊሲ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ አፍሪካን ማስተሳሰራቸው በህይወታቸው ከሚያኮሯቸው ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በፊት በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በኩል ይስተሳሰርና ለመረጃ ምዝበራ ይዳረግ የነበረውን አህጉር ራሱን አስችለዋል፡፡
ለቢዲቲ ዲሬክተርነት ምርጫ ውድድር ሂደት
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአይቲዩ አባል አገራት በሙሉ ተረፈ ራስ ወርቅ የኛ ዕጩ ስለሆነ ምረጡት ብሎ ድጋፉን ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት (እ.ኤ.አ) ቃሉን አጥፎ ‹‹ለተረፈ ራስ ወርቅ የሰጠነውን የምርጫ ድጋፍ አንስተናል፡፡›› ብሎ የቴሌግራም መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኛ ተወካይ እናድረግህ ቢሏቸውም አይሆንም ብለው በግላቸው በመወዳደር ከአምስቱ ወኪሎች ከሦስቱ አንዱ በመሆን አለፉ፡፡ ከዚያም የሚከተለውን ይሉናል፡፡ ‹‹ይህ አስገራሚ ሁናቴ ሳይበግረው ኢትዮጵያን የወከለው ግለሰብ ተረፈን አትምረጡ እያለ ከሕግ ውጪ የሆነ ቅስቀሳ ያካሂድ ስለነበር መራጭ አገሮችን ያወናብድ ነበር፡፡››
ተረፈም በዚህ ጫና ምክንያት ራሳቸውን ከውድድሩ አገለሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲወዳደሩ የራሳቸው መንግሥት መሰናክል መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን እንደተወዳደሩ ይታወቃል፡፡
ለማንኛውም ከምርጫው በኋላ ከእርሳቸው ጋ ከተወዳደረው ሰው ስር ሆነው የአይቲዩ ውጪ ግንኙነት ኃላፊ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ቦታ በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ የዋና ኃላፊው አማካሪም ሆነው ሰርተዋል፡፡
ወርልድ ቴልን እንደ ተቋም መፍጠር
‹‹በረጅሙ የስራው ዓለም ተካፋይነቴ ካከናወንኩት ውጤቶች ሁሉ የምዕራቡን ቴክኖሎጂ ወደ ቻይና እንዲተላለፍ ያደረኩት አጋፋሪት ታላቅ የመንፈስ እርካታ ሰጥቶኛል፡፡›› ይሉናል፡፡
ለኢትዮጵያ አብነቱ
‹‹በመጀመሪያ ስልክ በኢትዮጵያ የገባው አንኮበር ነው፡፡ በአጼ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት በኢትዮጵያ 3500 ኪሎሜትር የቴሌፎንና ቴሌግራፍ መስመር ተዘርግቶ ነበር፡፡›› የሚለውን የኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅን ቃል ስናነብ የምንገረም ብንኖርም ቴክኖሎጂን የሚወዱትና ወደሃገራቸው በማስገባት ቀዳሚው መሪ እምዬ ምኒልክ አስመራን፣ አዲስ አበባን፣ ጋምቤላን፣ ሐረርን፣ ጂቡቲን ወዘተ ያስተሳሰረ መረብ መዘርጋት ችለው ነበር፡፡
አሁን በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ወይም ከጠባሴ ወደ ደብረ ብርሃን በባጃጅ እየሄድኩ የምጠቀምበት የኢንተርኔት አገልግሎት ሳይመጣ ምን ያህል ተለፍቶበታል ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል - ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ ተረፈ ራስ ወርቅ ያለው ልፋት፡፡ ሁላችንንም ያስጠይቃል፡፡ ያንን ትጋትና ጥንካሬ የት አድርሰነው ይሆን? ያስብልማል!
የቤተክርስቲያንን ጉዳይ በተመለከተ ያቀረብኩት አስተዋጽኦና አስተያየቴ ከሚለው ምዕራፍ አንዳንድ ነገር ቃርሜያለሁ፡፡ የአንኮበሩ ጥንታዊ የአፈር ባይኔ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ገዳም መልሶ መገንባት አንድ የተረፈ ገድል ነው፡፡ ለገዳሙ ከፈረንሳየይ አገር የመጣ 225 ኪሎግራም የሚመዝን ልወል ተበርክቶለታል፡፡ ደወሉም ለቅዳሴና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከማገልገል ጎን ለጎን የአንኮበር ህዝብ ለልማት እንዲተጋ ጠዋት፣ ቀንና ማታ በቀን ሦስት ጊዜ ይደውላል፡፡ ይህን ትምህርት እንዴት ዓይነት ቦታ እንደሰጠሁት አልነግራችሁም፡፡
በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ማቋቋምም ቢሆን ከገድል በላይ ነው፡፡ የሙሴ ጽላት ቅጂ ከጥንታዊቷ ክርስቲያን ሃገር ኢትዮጵያ ወደ ስዊዘርላንድ መግባቱ ትልቅ በረከት መሆኑን በሃገሪቱ ያለውን አመራር በማሳመን በመንግሥት ደረጃ ለታቦቱ አቀባበል እንዲደረግና ኢትዮጵያውያ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ተረፈ የመሪነት ሚናውን ተጫውተዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የአስተዳደርና የመንፈሳዊ ስራ ይስተካከል ዘንድ ጳጳሳትና ካሕናት የመንፈሳዊውን አገልግሎት እንዲሰጡና ከምዕመናን የሚመረጥ አካል ደግሞ የገንዘብና የአስተዳደር ስራዎችን እንዲሰራ ሳይሰለቹ ምክራቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው መንግሥትና ኃይማኖት በተለያየ ጊዜ የተፈጠረው ክፍተት ያመጣቸው ችግሮች አሉ የሚል ነው፡፡ በህይወት ታሪካቸው የህይወት፣ ስራና መንፈሳዊ አገልግሎት ተግባራቸውን አጣምረው ማቅረባቸው የአማኑኤል አብርሃምን አቀራረብ አስታውሶኛል፡፡
ታሪካዊ የሆነችውንና የተረሳችውን አንኮበርን እንድታንሰራራ የማድረግ ተግባራቸው ብዙዎቻችን ኤንጂኔሩን የምናውቅበት ስራ ይመስለኛል፡፡ አንኮበር ላይ ጥንታዊው የቤተክህነት ትምህርት የሚያንሰራራበትን አሰራር ለመዘርጋት የካህናት ማሰልጠኛ ስራ በሰሩ ጊዜ ለነፍሳችን እንዲህ የተጨነቁት ወንድማችን ለስጋችንስ ምን አስበውልናል የሚል ይዘት ያለው ቅኔ ቀርቦላቸው የመጣላቸውና በአምስት አመታት ትጋት ከውል ያደረሱት ድንቅ ስራ የአንኮበር ቤተመንግሥት ሎጅ ተገንብቶ ስራ መጀመሩ ነው፡፡
ተረፈ ከ70 አገሮች በላይ ጎብኝተዋል፡፡ 187 አገር ከጎበኙትና ከፒያሳ ልጅ መጽሐፍ ደራሲ እውቁ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ቀጥሎ በዚህ ረገድ የሰማሁት ሁለተኛ ሰው!
ጥሩ ትዳርና ሕይወት አላቸው፡፡ በበጎ አድራጎታቸው ለኖቤል የታጩ ሚስት አሏቸው፡፡ የሚያምር ትዳር በሚያማምሩ ማስረጃዎች፣ የሃምሳኛ ዓመት እዮቤልዮ አከባበርን ጨምሮ፣ በማቅረባቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዶክተር ሲቪል መሐንዲስ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህን አስታውሰውኛል፡፡ በዚህ ብቻም አይደል፡፡ የሸዋ ሰው በመሆን፣ በፋሸስት በመሳደድ፣ በአሜሪካ በመማር፣ በፈጠራ …
የዶክተር ፍስሃ ኃይለመስቀል ጓደኛ መሆናቸው ሁለቱም በበጎ ተግባር ላይ ስለተሰማሩ ትርጉም ይሰጣል፡፡ በዶክተሩ በኩል ያገኘሁት የብላታ ደምሴ ወርቃገኘሁ ዜና መዋዕል ‹‹ሞት ያልገታው ጉዞ›› ከአንኮበሩ ሰው የአርበኛ ቤተሰብነት ጋር የሚመሳሰል አካሄድ ስላለው ቢነበብ፡፡ ሜጀር ዮሐንስ ያላመለጠውን ግድያ ብላታ ተላልፈውት ነበር፡፡
ሀሁ በቀላሉ የኢትዮጵያ ፊደሎች አዲስ መማሪያ ዘዴ የሚል መጽሐፍ የጻፉትና አማርኛ መማርን ያቀለሉት በኩረጠቢባን መልካም ፈቃዳቸው ቢሆንና እንደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት ቢፈቅዱ መጽሐፉ እንደገና ወደ ህትመት ገብቶ ቢሰራበት እላለሁ፡፡
መጽሐፉ በሁለት ቋንቋ ማለትም በአማርኛና በእንግሊዝኛ መቅረቡ የአማርኛው ይዘት ጥልቀት እንዳይኖረው አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት አንባቢው በብዛት በሁለቱም ቋንቋዎች ማንበብ የሚችል መሆኑ ታስቦበት ሊሆንም ይችላል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጓደኛ፣ የእውነተኛው የእድሜ ባለጸጋና የምኒልክ ባሪያ የዘውዴ ነሲቡ ደጋፊ፣ የአለም ሎሬት የጥበበ የማነብርሃን የአገር ልጅ፤
እንደ ሙሉጌታ ኢተፋ የፈረንጅ አገር ዘረኝነት ሰለባ፣
እንደ ያዕቆብ ወልደማርያም የጽሕፈት ባለሙያ፣
እንደ እምዬ ምኒልክ የደሃ አባት፤
በኩረ ጠቢባን ኤንጂኔር ተረፈ ራስ ወርቅ ወልደ መስቀል በመጽሐፉ ብዙ ነገር ስላነሱ መጽሐፉን እንድታነቡት በአክብሮት በመጋበዝና ለደራሲው እድሜና ጤና በመመኘት ልሰናበት፡፡

በ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› መጽሐፍ ምረቃ ወቅት ደራሲው ከተናገሯቸው

በ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› መጽሐፍ ምረቃ ወቅት ደራሲው ከተናገሯቸው ሃሳቦች የወሰድኩት ማስታወሻ
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በእናቱ አንኮበሬ ነው፡፡ ቡም ቡም ቡም … ኢትዮጵያ ተፈጠረች አለ ጸጋየ ገብረመድህን አውሮፓ ጠርቼው መጥቶ ለፈረንጆቹ ንግግር እያደረገ፡፡ የሚገርም ችሎታ ያለው ሰው ነው፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ለአንኮበር የተቻላቸውን ባለመስራታቸው ይቆጩ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ወደ ጨረቃ የተላከው የአፈወርቅ ስም ነው፡፡
እዚህ የምንጃር፣ የጅሩ፣ የተጉለት ሰው ወይም ዘፈን እያልን እናጠባለን እንጂ ጎንደሬ ጎጃሜ እንደሚለው አናሰፋም፡፡ እንደ ሃገር (ኢትዮጵያ) ትልቅ ህዝብ ነው የያዝነው፡፡ አሁን መፍረክረክ የጀመርን ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ ግን አትወድቅም፡፡ ዛሬ ብዙ ኃይል አለን፡፡ 43 ዩኒቨርሲቲ አለን፡፡ የትምህርት ጥራት ጉዳይም ከሆነ ትምህርት አንጎልን መክፈት ብቻ ነው፡፡ ሰፋ አድርገን እንድንመራመር ያስችላል፡፡ ውጤት ያመጣል፡፡
የቢዲቲ ውድድር ላይ የገጠመኝ ችግር ትግሬ አማራ በሚባል በማይረባ ነገር ለ190 አገር ቴሌግራም ተላከ፡፡ የመንግሥት ባለስልጣኖችን ከመውቀስ ይልቅ ማስተማርን እመርጣለሁ፡፡ ዶክተር ቴድሮስ መመረጡ ብዙ ሰውን ያነሳሳል፡፡ አገርንም ይጠቅማል፡፡ ደስተኛ ነኝ፡፡
ኮፊ አናን መጀመሪያ ስራ የጀመረው አዲስ አበባ ነው፡፡ ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ 40 ዓመት እዚያ ኖሮ የሚበላው እንጀራ፣ የሚያስበው የሃገሩን ፖለቲካ ነው፡፡ ያንን ኃይል መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ልጄ ከ500 – 600 ሰራተኛ ያለው ድርጅት ለንደን ላይ አላት፡፡
ጠባብ ማንነት የሚባል አዲስ ማንነት አልሰማም - ኢትዮጵያዊነታችንን እንጂ፡፡ በአጼ ምኒልክ አስተሳሰብ ሁሉም አንኮበር ነው፡፡ አዲስ አበባም አንኮበር ነው፡፡ የአንኮበሩን ሙዚየም የምንከፍተው የአስተዳደሩን ስራ ጨርሰን ነው፡፡ ቦይ ስካውት ደርግ አጠፋው እንጂ ጥሩ ነገር ነበር፡፡ አሁንም አላንሰራራም፡፡ አንድ ስካውት ሁልጊዜ ያፏጫል፣ ፈገግታም ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ማዕከል ነች፡፡ ፈረንጆች ይፈሩናል፡፡ እኛም በራሳችን እንተማመን ነበር፡፡ ጥቁር የኛን ባንዲራ ነው የሚያውለበልበው፡፡ ፈረንጁ የሚያጠቃን ለዚህ ነው፡፡ ደብረ ብርሃን እንዲህ ሆና ማየቴ ያስደንቀኛል፡፡ መጽሐፉ ሽቦሽቦ እንዳይሸት የግል ታሪኬን ጨመርኩ እንጂ ዋናዎቹ አባሪዎቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ Is global telecommunication feasible የሚል አለበት፡፡ የዓለም ሕዝብን ማስተሳሰር ይቻላል፡፡ ቴሌኮሚኒኬሽን በሁሉም ውስጥ ያለ ነው፡፡ በደንብም ለመብላትና ለማስተዳደር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል፡፡ From Tam tam to the Internet የሚል ኮፊ አናንና ማንዴላ መግቢያውንና መቅድሙን የጻፉበት መጽሐፍም አለኝ፡፡ ለምርምር መነሻ ይሆናሉ፡፡
ግራሃምቤል ስልክን በፈጠረ በሰባት ዓመት ውስጥ አንኮበር ስልክ ገብቷል፡፡ የመጽሐፉን ርዕስ ሆን ብዬ ነው ያደረኩት፡፡ አንድ ሁለት ቀንም ቢሆን ፍየል አግጃለሁ፡፡ አንድ የአንኮበር ባላገር ከአንኮበር ተነስቼ፣ 70 አገር ጎብኝቼ፣ የዓለም መሪዎችን አግኝቼ፣ የዓለምን ቴሌኮሚኒኬሽን ለውጬ፣ አንድ ሰው ተግቶ ከሰራ የት መድረስ እንደሚችል ምሳሌ እንዲሆናችሁ ነው፡፡
ድሮ አፍሪካ በቴሌኮሚኒኬሽን ከሌላው ዓለም ትበልጥ ነበር፡፡ አንድ መርከብ ናይጀሪያ ሰምጣ በሶስተኛው ቀን ምስራቅ አፍሪካ ተሰምቶ ነበር፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ታሪክ ትዘጉ! 43ቱም ታሪክ አስተምሩ፡፡
በመጽሐፋቸው ላይ ያቀረብኩትም ዳሰሳ ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› በሚል ርዕስ ከገጼ ይገኛል፡፡

2018 ዲሴምበር 1, ቅዳሜ

Learn Amharic in English

ኦባንግ ሜቶ በደብረ ብርሃን




በመዘምር ግርማ
19.3.2011

-የንግግሩ ሁኔታ የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግን ይመስላል፡፡
- አማርኛው አድምጡኝ አድምጡኝ ይላል፡፡



ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መጥተው ንግግር እንደሚያደርጉ በግሌ ከአንድ ሳምንት በፊት ሰምቼ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በግልጽ ማስታወቂያ የተነገረው መምጫቸው ሲቃረብ ነበር፡፡ ረቡዕ ሕዳር 19. 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የዩኒቨርሲቲው
ማኅበረሰብ በሰዓቱ ወደ መመረቂያ አዳራሽ መትመም ጀመረ፡፡ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የተለያየ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰራተኞች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች የፊተኛውን ረድፍ ይዘው በጉጉት ይጠብቁ ያዙ፡፡ እንግዳው ምን ሊናገሩ እንደሚችሉ ያወጋሉ፡፡
በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሰራተኛ የሆነው አቶ ጌታመሳይ አሳልፈው ተማሪዎችን በተመደበላቸው ቦታ ለማስቀመጥ ሲጥርና ይህም ተግባር ሲያስችግረው ያየው መምህር ጌታቸው ገብሩ ከአጠገቤ ተነስቶ ‹‹እኔስ ባስተባብር›› ብሎ ስርዓት አበጅቶ ተማሪዎችን፣ ሰራተኞችንና መምህራንን በየተመደበላቸው ስፍራ ማስቀመጥ ያዘ፡፡ ከዚህም የተማርኩት አንድ ሰው ቆሞ ከመመልከት ይመለከተኛል ብሎ መስራት እንዳለበት ነው፡፡ እኔ ያላደረኩትን ስላደረገ ጌታቸው በዚህ ይለያል ማለት ነው፡፡ ቆይተን እንደምናየው የአቶ ኦባንግም ንግግር ይህን ዓይነት የተግባር ስራ ጅማሮ መልዕክት የተላለፈበት ነበር፡፡
አንድ ሱፍ የለበሰና መነጽር ያደረገ ሰው በሩ ላይ በግርማ ሞገስ ሲታይ ማህበረሰቡ የጠበቀውን በማግኘቱ በአግራሞት ልቡ ወከክ አለ፡፡ እንደኔ ምልከታ ከወትሮው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ውጪ ብዙም የተለየ ነገር በማታይበት ግቢ ንግግር የሚያደርግ እንግዳ መምጣቱ ለሁላችንም አዲስ ነገር ነው፡፡ እስከዛሬ የመጡ ቢኖሩም በአንድ ኬሌጅ የስብሰባ ዝግጅት ወይም ትምህርታዊ ጉባኤ ሊሳተፉ ስለሚሆን ሁላችንንም የሚያሳትፍ ላይሆን ይችላል፡፡
ኦባንግ ሜቶ ከእድሜያቸውም ሆነ ለሰው ካላቸው ቅርበት የተነሳ አንቱ ሊባሉ ሳይሆን እንደ ታላቅ ወንድም አንተ ቢባሉ ይሻላል ብዬ ስለማስብ አንባቢዬን ይቅርታ በመጠየቅ አንተ እያልኩ ጽሑፌን እቀጥላለሁ፡፡ የመድረክ ዝግጅቱ ተደረገ፡፡ በዚህም የቅድመ ዝግጅት ሂደት ድምጽ ማጉያው መስራቱን ለማረጋገጥ ባለሙያው አቶ እጀጌታው በተለያዩ ያገራችን ቋንቋዎች ‹‹ሙከራ 1፣ 2፣ 3›› እያሉ ተሳታፊውን አዝናንተዋል፡፡ ክስተቱ ለየቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች ለእናንተም እውቅና እንሰጣለን ዓይነት መልዕክት የተላለፈበት ይመስለኛል፡፡ እዚህ ባይተዋር የለም ማለቱ መሰለኝ ባለሙያው፡፡
የእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ዶክተር ታደለ ፈንታው መድረክ መሪ ነበሩ፡፡ ስለ አብሮነት አንዳንድ ነገሮችን እየተናገሩና ስለኦባንግም መረጃ እየሰጡን መድረኩን በሚገባ አስተናብረዋል፡፡ ዝግጅቱ በማህበራዊ ሳይንስና ሰብዓዊነት ኮሌጅ አስተባባሪነት የተዘጋጀ መሆኑን እዚህ ጋ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለወደፊቱም እንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ቢካሄድ መልካም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ለዚህ ተግባራዊነት በዝግጅቱ ላይ ቃል ገብቷል፡፡
አዲስ የተመረጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኃይለማርያም ብርቄ የመክፈቻ ንግግር አድርገው እንግዳውን ጋብዘዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ትንሿ ኢትዮጵያ እንደሆነችና የጋራ መግባባት ሊኖረን እንደሚገባ ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ በኦባንግ ንግግር መርካታቸውን መስክረዋል፡፡ የእንግዳው ማንነትና የህይወት ልምድም በዶክተር ታደለ ቀርቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከመጀመሪያው ጀምረው እስከ ዝግጅቱ ፍጻሜ ድረስ በማወያየትና የአቶ ኦባንግን ንግግር በመከታተል አብረውን ስለቆዩ ማመስገን ይገባናል፡፡ ወደፊትም የእውነት የትምህርት ተቋም ይኖረን ዘንድ የሚያግዙ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶችን በማቀድ፣ በመፍቀድና በማካሄድ ደብረ ብርሃንን እንደስሟ ብርሃን ያደርጓታል ብዬ አምናለሁ፡፡

አቶ ኦባንግ ሜቶ ንግግሩን የጀመረው በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎችን በእንግሊዝኛ ካቀረበ በኋላ ስለቋንቋ አጠቃቀሙ አንዳንድ ነገር መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ለእኔ የሚቀናኝ እንግሊዝኛ ነው፡፡ በልጅነቴ እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማርኩት አማርኛ እየጠፋብኝ ስለሆነ አሁን እንደገና እየተማርኩ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ጎንደር ሄጄ አማርኛ መምህር ልሆን እችላለሁ›› ብሏል፡፡ ከዚህም በማስከተል ንግግሩን በአመዛኙ በአማርኛና አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥቅሶችን በእንግሊዝኛ አቅርቧል፡፡
ውድ አንባቢዬ፣ ይህን ያህል ደጅ ካስጠናሁዎት ዘንዳ አሁን ኦባንግ በደብረ ብርሃን ምን ተናገረ ወደሚለው እንምጣ፡፡  

ማንነቱ
ኦባንግ እንደየሁኔታው የአኝዋክ ተወላጅ፣ ጥቁር፣ ውጪ የተማረ፣ ኢትዮጵያዊ ወዘተ ሊባል ይችላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ታጋይ የሚለው ግን እኛም ዛሬ ስለሱ እንጽፍ ዘንድ ያስገደደን ስለሆነ በዚህ ብንጠራው ጥሩ ይመስላል፡፡ ኦባንግ የተለየ ግርማ ሞገስ አለው ሲል ከተናገረው ከዶክተር ታደለ ጋር የማይስማማ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ እርጋታ፣ ቅንነት፣ ትህትና ወዘተ መልካም ቃላትን ሁሉ ብንደረድር ለኦባንግ ይገባዋል፡፡

አንድ ጣታችንን ሌላ ሰው ላይ ስንጠቁም ሦስቱ ራሳችን ላይ ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ጥቅስ በሚገባው ቦታ ተጠቅሞበታል ኦባንግ፡፡ አሁን አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት ብቸኛ ሙሴ አለ አይደለም የኦባንግ ንግግር፡፡ ሁላችንም ለጠፋው ጥፋት መድህን መሆን አለብን ይለናል፡፡ 
‹‹ከእናንተ እንጂ ዶክተር ዓቢይ አይደለም፡፡ ከእናንተ እንጂ ከዶክተር ኃይለማርያም አይደለም፡፡ ከእናንተ ነው ይህች አገር ብዙ የምትጠብቀው፡፡ ለውጥ ማምጣት የምንችለው 100 ሚሊዮኑ ሲተጋ ነው እንጂ በተወሰኑ ሰዎች አይደለም፡፡›› ይለናል መርፌ ቢወድቅ በሚሰማበት፣ ኮሽታ ባልነበረበት ትልቁ አዳራሽ የተገኘው ጥቁር ሰው!
 ‹‹ይህች ጥንታዊት ከተማ፣ ይህች የእምዬ ምኒልክ እትብት የተቀበረባት ስፍራ፣ ይህች ውብ ስፍራ፣ ደብረ ብርሃን እንደዚህ የሆነችው ደሃ ስለሆንን አይደለም - የአመራር ድህነት፣ የአስተዳደር ችግር፣ የቅንነት መጥፋት ስላጠቃን እንጂ›› ይለናል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች ኦባንግ፡፡
በአኝዋክ ባህል የመጀመሪያ ልጅ ኦባንግ እንደሚባል ሰምቼ ነበር፡፡ ኦባንግ እውነተኛ የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ መሆን አስመስክሯል፡፡ የታሰሩ፣ የተገደሉ፣ የተሰደዱ፣ የተንገላቱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንደሚያሳስበው ብቻ አይደለም የተረዳነው፡፡ አገር ውስጥና ውጪ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እየተከታተለ የሚታገዙበትንና ችግራቸው የሚፈታበትን መንገድ የሚቀይሰው ከአኝዋክ ወይም ከጋምቤላ ስለመጡ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አብረን በመኖራችን ስለሚያውቃቸው እንጂ፡፡ ያስተማረውን ህዝብ ለመካስ እንጂ!
በጃፓን፣ በማልታ፣ በኖርዌይ፣ በሜክሲኮ በበርካታ አገሮች በመዘዋወር ችግር ላይ ያሉና ቀን የከፋባቸውን ኢትዮጵያውያን አግኝቶ አጽናንቷል፡፡ ከጎናቸው እንዳለ አስመስክሯል፡፡ ከሃያ በላይ ሃገር ዞሮ ዜጎቻችንን የሚረዳው ህሊና ስላለው ነው፡፡ ከጎሳ ይልቅ ሰብዓዊነትን እናስቀድም በሚል መርህ የሚንቀሳቀሰውን የኦባንግን ጅማሮ ለማግኘት በበይነመረብ solidaritymovement.orgን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለተጀመረው ተስፋ ሰጪ ጉዞ ሁላችንም አለኝታነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ 

ለብሔራዊ መከባበርና መተሳሰብ መንገዱ የተጠረገበት ስብሰባ ዋና ክፍል የኦባንግ ገለጻ ነው፡፡ ርዕሱም THE WAY FORWARD: CAN THE RIGHT CHANGE BE SUSTAINED IN ETHIOPIA? ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ ማለትም በውጪ የነበሩ ኦባንግን ጨምሮ በአሸባሪነት የተፈረጁና አገራቸው እንዳይገቡ እገዳ የተጣለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋጮች መግባታቸው፣ እስረኞች መለቀቃቸው፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ ወደ ሰላማዊ ጉርብትና መቀየሩ፣ ሚዲያዎች በነጻነት እንዲሰሩ መፈቀዱ፣ ለሃገራዊ መግባባት መንገድ እየተጠረገ መሆኑ፣ አሁን ያለው አጠቃላይ የለውጥ ተስፋና የዶክተር ዓቢይ ቡድን እያስመዘገበ ያው ውጤት የንግግሩ ማጠንጠኛ ነበር፡፡ እንደዚህ ተገናኝተን ስለ ሰብዓዊነታችን፣ ስለኢትዮጵያዊነታችንም ሆነ ስለችግሮቻችን መነጋገር ወንጀለኛና አሸባሪነት ተደርጎ እንደነበረና መሰብሰባችን በራሱ አሁን ያለው ለውጥ ውጤት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ለውጥ ትክክለኛ እንሆነ፣ ልንንከባከበው እንደሚገባ፣ በተለይም ወጣቱ ዋነኛ የለውጡ ጠበቃ መሆን እንደሚኖርበት ኦባንግ አስገንዝቧል፡፡ ይህን ለውጥ ለማምጣትም ሆነ ኢትዮጵያን እንደሃገር ለማቆየት ለተጉና ሕይወታቸው ላለፈ ሁሉ የሕሊና ጸሎት በማድረግ ነበር ዝግጅቱ የተጀመረው፡፡

በበኩሌ ስለሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተርጉሜው የነበረውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ለእንግዳው አበርክቻለሁ፡፡ ለእርቅና ለአብሮነት ለሚያደረርገው ስራ የበኩሌን ለመወጣት ፍላጎትም አለኝ፡፡

ተሳታፊ የነበራችሁ ሰዎች ‹‹እስካሁን ያጠፋነውን በመቶ ዓመት አለንመልሰውም›› ሲል የተናገረውን እንዴት አያችሁት? ‹‹ሳናውቀው የጎሳ አስተሳሰብ ተጠቂ ነን›› ያለውንስ? የዘነጋኋቸውን ነጥቦችም እያነሳሳችሁ ብንወያይበት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

አንድ የኦባንግ አብሮ አደግ በቅርቡ አዲስ አበባ ሻይ ቡና ለማለት በተገኛኑበት ጊዜ ‹‹እኔ ጉራጌ ነኝ፡፡ ጉራጌ ነኝ፡ ጉራጌ፣ ጉራጌ…›› እያለ እንዳስቸገረውና ይህንም ዛሬ ያወቀው ይመስል እንደደጋገመበት ነግሮናል፡፡ የጎሰኝነትን አባዜና የገባንበትን አጣብቂኝ በብዙ ምሳሌዎች አስረድቶናል፡፡ ‹‹በምርጫችን አይደለም ከተፈጠርንበት ብሔር የተፈጠርነው›› ይለናል፡፡ 
ኦባንግ ውጪ ሲማር ከ3000 ተማሪ ብቸኛው ጥቁር እንደነበረ ነግሮናል፡፡ ‹‹ጥቁርነቴ ትዝ አይለኝም፡፡ ቆዳየን ልጆች በአግራሞት ቢነካኩም፡፡ በትምህርት ቤታችን በጣም ጥቁር ልጅ አለ እያሉ ለቤተሰብ ቢናገሩም፡፡›› ይለናል፡፡

ሕገመንግስቱ ስላለበት ችግርም ነጻ አውጪዎች ያወጡት እንደሆነና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎ እንዳልነበረበት አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ነጻ አውጪዎቹ ከማነው ነጻ የሚወጡት - ከኢትዮጵያ ነው፡፡ እነሱ ኢትዮጵያን መሪ ለመሆን በቁና ይህን ሁሉ ጥፋት አመጡ፡፡›› ብሎናል፡፡

ከንግግሩ በኋላ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ተሳታፊዎችን ከዝግጅቱ በኋላ አናግሬ በዝግጅቱ እንደረኩ ነግረውኛል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምሳሌ የሚሆን ንግግር ነው፡፡ እንደሱ ዓይነት ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ እንደዚያ የምናገር ምሁር ቢኖር አገራችን ትለወጥ ነበር፡፡›› ወዘተ በማለት ለንግግሩ ያላቸውን አድናቆት ነግረውኛል፡፡

ሰላማዊ የትምህርት ሂደት የሚካሄድበት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ስለ እርቅ፣ ሰላም፣ የፍትሕ መመለስ በሃገሪቱ እየተዘዋወረ ከዜጎች ጋር መነጋገርና ያለውን ሁኔታ በመረዳት ላይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ታጋይ መጋበዙ ያስመሰግነዋል፡፡

ሰብዓዊነት ይለምልም!

2018 ኦክቶበር 30, ማክሰኞ

The Ethiopian Education Development Roadmap In the Eyes of NGOs



October 18 – 19, 2018
Mezemir Girma
Addis Ababa, Ethiopia

About the report:
This report has been compiled to inform the South African Institute for Distance Education (SAIDE) of the Roadmap. Since the institute is working in Ethiopia, it needs information about the roadmap.

About the compiler:
Mezemir Girma represents SAIDE in Ethiopia in their project African Storybook Initiative (ASb) which can be accessed on africanstorybook.org.

The Roadmap:
It is expected to go operational from 2018 - 2030 to reform “the education sector in accordance with the national vision and national development goals.”  The roadmap was prepared by a team of experts who used “desk review, benchmarking visits and field data on educational practices and implementation.”

Components:
This report focuses on pre-primary education since this is ASb’s main focus. However, one should note that the roadmap covers all aspects of education in the country.

The Procedure of the Workshop:
On the first day, Thursday, October 18, 2018, officials from the ministry of education (MoE) gave a PowerPoint presentation on the overall roadmap. The afternoon of this first day and the morning of the second day were allotted to group discussion. Two groups were formed and the participants had discussions on the contents of the roadmap. In the late morning of Friday, October 19, the two groups met and their chairs presented a summary of the discussion. A report was given to the ministry officials and the meeting was finalized. The discussants did not receive a copy of the roadmap file beforehand. Therefore, the discussion was mainly based on the PowerPoint presentation.

Pre-school Policy and Curriculum:
Non-governmental organizations’ (NGO) representatives inquired if the MoE has a clear policy on KG learning because it should have one. In the report only the New Early Child Care and Education Policy Framework (NECCEPF) (MoE, 2010) which is prepared by a group of ministries is mentioned. As to NGOs the community should be convinced on preschool.

O Class:
The issue of O class has been a point of contention. It is a major challenge as there are disparities and unclear policy guidelines among regions. Also called ‘school readiness program’ it is commendable as it saves children from straight grade one. As in the country pre-primary education has been left for the advantaged few in towns and cities, this scheme is an alternative. “What is the difference between O class and kindergarten?” asked participants.

Teacher Training:
The lack of adequate teacher training on pre-school has also been raised. The roadmap lacks clarity and credibility as there are less tangible plans with an inadequate budget. Participants asked, “Is there any preschool teachers’ training college in the country?”

Medium of Instruction:
The study found out that in pre-school 85 percent of the lesson is in mother tongue and 15 percent in Amharic in emerging regions used. These emerging regions use Amharic as a medium even if it is not the children’s mother tongue.  The roadmap recommends that the teachers should be trained in a language which is the children’s mother-tongue.

Kindergarten Textbooks:
Different organizations, private kindergartens, community schools and others are using their own textbooks. There should be a strict guideline on this.

Age Six:
The NGOs commented, “The suggested grade one starting age of six should be revised or justified as the kids do not cope-up with the lesson. What is your justification?” It was at seven years of age that children enroll in elementary schools. The suggested six years of age is debatable.

School Distance:
Since the farmers need their children nearby to keep their houses or animals, schools should be built at walking distance from home. As 85 percent of the schools in the country are in the rural areas, the roadmap should consider them. 

The Near Future:
The ministry aspires to involve all stakeholders in discussions and improve the document. Some aspects of the roadmap seem to be implemented at this time too.

Conclusion:
The African Storybook Initiative (ASb) recommends the application of well-researched reforms in the education sector. The fact that the reform goes in line with national and international development and educational goals is commendable. We hope that the gaps and shortcomings are addressed.

2018 ኦክቶበር 25, ሐሙስ

በትምህርት ጉዳይ

ሰሞኑን በትምህርት ጉዳይ አንዲት አነስተኛ ጽሑፍ እየጻፍኩ የተለያዩ ሰዎችን አወያይቼ ነበር፡፡ እስካሁን የማላውቀውና አሁን የሰማሁት መረጃ አለ፡፡ ይኸውም በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የነበሩት እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ሦስት ብቻ እንዲቀሩ መደረጉን ነው፡፡ ምክንያቱም በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሰረት የመሰናዶ (ከ11ኛ -12ኛ) ትምህርት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ሦስቱ ብቻ ሲሆኑ ሌሎቹ እስከ አስረኛ ብቻ እንዲያስተምሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም ውሳኔ መሰረት ጥሩ ውጤት ኖሯቸው ደብረብርሃን፣ ሞላሌ ወይም ደብረሲና ሄደው መማር ያልቻሉ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ፣ ግብርና ኮሌጅ ወይንም ቴክኒክ እንዲገቡ ተደርገዋል ማለት ነው፡፡
የዚህን ችግር ስፋትና ጥልቀት እንገነዘብ ዘንድ በወቅቱ የውሳኔው ሰለባ የሆናችሁ ጻፉልን፡፡
ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ብቻ የተደረገ ነበር ወይ?
እስከ 12ኛ የሚያስተምረውን ትምህርት ቤት ለአራት አመታት ዘግተው በ1997 ምርጫ ማግስት ለምን ከፈቱት? ውሳኔው የፖለቲካ እንጂ የትምህርት ባለሙያ ላይሆን ይችላል፡፡

የዓመት ግብራችን እነሆ።


የፍኖተ-ካርታ ውይይት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ሲሆን፤ አንዳንድ ነጥቦች በተወያዮች እየተነሱ ነው፡፡ ስያሜውም ጥያቄ ውስጥ ገብቶላችኋል፡፡ የፖሊሲ ለውጥ አይመስልም፤ የአፈጻጸም የሚለው ላይ አትኩሮት ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ፖሊሲው ችግር አልነበረበትም ማለት ነወይ?
ቋንቋ ላይ ያለኝን ምልከታ በመጠኑ ላስቃኛችሁ።
1. ቋንቋ የተባለው ላይ ልጆች አራት ቋንቋ እንዲማሩ የሚያደርግ አሰራር እየተዘረጋ ሲሆን፤ ትኩረታችን የቋንቋ ፉክክር ላይ ይመስላል፡፡ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይሆን ላለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ስራ ላይ ተጨማሪ ነገር እየተሰራ ነው፡፡ የኔን ቋንቋ ካልተማርክልኝ ያንተን አልማርም ነው እንዴ ነገሩ? አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ ብሔራዊ ቋንቋ ነው፡፡ ሁለት በተለያዩ ቋንቋዎች አፋቸውን የፈቱ ኢትዮጵያውያን ሲገናኙ የሚነጋገሩት በአማርኛ ነው፡፡ ትምህርትም በዚሁ ቋንቋ የሆነው ለዚያው ነበር፡፡ አሁን የአማርኛ ክፍለጊዜ መቀለጃ ሆኗል፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ እንደማይወስዱ የሚያስታውቀው በአማርኛ ሰላምታ እንኳን የማይችሉ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ ነው፡፡ በአፍ መፍቻቸው የተማሩት ነገር ጥሩ ሆኖ ሳለ አሁን እነሱም የማይማሩትን የአማርኛ ክፍለጊዜ ታሳቢ አድርጎ የአማርኛ ተናጋሪውም የነሱን ቋንቋ እንዲማር የሚል አሰራር ሊዘረጋ ይመስላል፡፡
2. ከዚህ በፊት ብሔራዊ መግባባት መቅደም አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን በጎሳ እየተለያየን እየተጠቃቃን መሆኑ ለማናችንም ምስጢር አይደለም፡፡ በዚህ አካሄድ የሚመረጡትን ቋንቋዎች (ለምሳሌ ትግርኛንና ኦሮምኛን) ለማስተማር ወደተለያዩ የሃገራችን ክፍል የሚሄደው መምህር ምን በወጣው ይንገላታል፣ ይደበደባል ባስ ሲልም ይገደላል! ቋንቋዎቹ እንደሚያስፈልጉን ጥርጥር የሌለው ቢሆንም ቅድሚያ መግባባቱ ይቅደም፡፡ ሰው መሆናችን ይቅደም፡፡
3. አሁን የኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ላይ ባሉበት ወቅት ቋንቋቸውን ተምረን ማንነታችንን ብናጣስ? ከድሮውም አማርኛ የሚባል አልነበረም አይባል ይሆን? ማረጋገጫውም ይሄው እናንተ ቋንቋችንን ትችላላችሁ፡፡ ከፈለጋችሁ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ፤ ያለዚያ ባህላችንንም ቋንቋችንንም አክብራችሁና ተከትላችሁ ኑሩ የሚል ጣጣ ቢመጣስ?
4. የውጪ ቋንቋ የተባለው ላይ አረብኛና ኪስዋህሊ ቢካተቱበት ጥሩ ነው፡፡ አረብኛ ልጆቻችን ትምህርት ሲጨርሱ ወደ አረብ አገር ስለሚሄዱ ሲሆን ኪስዋህሊ ደግሞ የአፍሪካን አካባቢያዊ ትስስር አስመልክቶ ነው፡፡ አሁን ደቡብ አፍሪካ የደረሰ ቋንቋ ነው፡፡
ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የዚህ የፍኖተ-ካርታ ጥናት በጠ.ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን የጀመረ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ምግቦቹ የተለጠፉት ባለፉት ዓመታት ተችቼው የነበረውን አራተኛውን የከፍተኛ ትምህርት ዓላማ አስመልክቶ ነው። መማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት በማለው ላይ ደግሶ ማብላት መጨመሩን አብስሬ ነበር።
ተጨማሪ ጽሑፍ ለማግኘት
mezemirethiopia.blogspot.com

ሰከን ካሉ ሰዎች አማራጮች መቅረብ ይኖርባቸዋል

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መግቢያ ወቅት መቃረቡን አስመልክቶ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ምድብ ቦታቸው ላለመሄድ እያንገራሩ ነው። ከዚህ ያልተናነሰ ስጋትም አለ። ይኸውም የዩኒቨርስቲ መምህራንም ወደ ትውልድ አካባቢዎቻቸው በዝውውር እየፈለሱ ነው። ይህ ትልቅ ሥጋት ይመስለኛል። ለሚፈናቀሉ ዋስትና ሰጥቶ ተረጋግተው እንዲቀመጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ቢያንስ ህብረተሰቡ አለኝታነቱን የሚያረጋግጥበት መንገድ ይቀየስ። የእድር፣ የኃይማኖት፣ የተቋማት ወዘተ መሪዎች "ችግር ቢመጣም ዋስትና እንሰጣችኋለን፤ ልጆቻችን አይነኳችሁም" ብለው መምህራኑን ሰብስበው መለመን አለባቸው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ወይም ዓይነተኛ መፍትሔ ካልተፈለገ ሁሉም ወደ ትውልድ ቀዬው ሲሰበሰብ የባሰ አደጋ ያመጣል። ሠው በሃገሩ ተዘዋውሮ መስራትና መኖር ይሳነዋል። ሰከን ካሉ ሰዎች አማራጮች መቅረብ ይኖርባቸዋል።

አገር በቀል የሌብነት እና ዝርፊያ ዘዴዎችስ?

Inside the mind of a thief (የሌባው አስተሳሰብ)
በሚለው ዝግጅት ይህ ሌባ ምክር ይለግሳል። ለረጅም ጊዜ ሳይያዝ ሲሰርቅ የኖረ ሲሆን አሁን ፖሊስ እጅ ላይ ወድቋል። ከሃያ እስከ ሠላሳ ዓመት እስርም ይጠብቀዋል ተብሏል። የሚጠቀማቸው የስርቆት ዘዴዎች የሚከተሉትን ከግምት ውስጥ ያስገባሉ፦
ሀ. የውሾችን መኖር አለመኖር
ለ. የአላርምን ሁኔታ (ዋየርለስ ነው?)
ሐ. ቀን ወይም ማታ
መ. በፊት ለፊት ወይስ በጓሮ
ሠ. ከደጅ የተቀመጠ ፖስታና መልዕክት ወይም ያደገ ሳር ካለ ሩቅ አገር ሄደዋል ማለት ነው
ረ. መብራት ካበሩ (የውጪውን ወይም የውስጡን)
ሰ. ቀድሞ የተቀረጸ ድምጽ ከለቀቁ (የውሻ ወይም የራሳቸውን)
ሸ. ጎረቤት እዩልን ካሉ
ወዘተ
አሁን የዚህ መረጃ አስፈላጊነት ወዲህ ነው። በየአካባቢው ሌቦች፣ ዘራፊዎች እና ወንጀለኞች እየተበራከቱ ስለሆነ ለቅድመ ጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ የማጥቂያ ዘዴዎቻቸውን እንነጋገር። እንዴት እንከላከል? እርስዎ ምን ዓይነት ዘዴ ሠሙ?
የምትነግሩኝን አጠናቅሬ ለሁላችንም ደህንነት ስል እጽፋለሁ። መልካም ቀን!

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...