'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው የኦሮሞን የሥልጣን የበላይነት በኢትዮጵያ ላይ ከመጫን ጋር እንዴት እንደሚያስማማው የሚያውቀው እሱ ነው። ካየነው የእስካሁን አካሄዱና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ካለው እርቀት፣ መቃቃርና በመጽሐፉ ደጋግሞ የሚክደው የደም ማፋሰስ ልምዱ አንፃር አካታች ሥርዓትን ማንበር ሊሳካለት ይችላል ብሎ ማሰብ ያዳግት ይመስለኛል። እሱንም ሆኑ ሌሎች ኦሮሞዎችን ለትግል ያነሣሣቸው በኦሮሞ ላይ ደረሰ የሚለው መገፋት፣ መናቅና በሌሎች መገዛት መሆኑን ገልፆ አሁን ኦሮሞ እየደረሰበት ያለው ጭቆና፣ በሌሎች እንደ ገዢ እየታየ ሰላም፣ ጥቅምና ትክክለኛ አስተዳደር አለማግኘቱ፣ ብሎም ትግሉ መቀልበሱ ለሌላ ዙር ትግል እንዳነሣሣው ጽፏል።
ስለ ትግራይ ጦርነት ሲጽፍ እሱ በእስር በነበረ ወቅት መካሄዱን ያወሳል። ቀድሞውንም ጦርነቱ እንዳይከሰት ያደረገውን ጥረት አስታውሶ በጦርነቱ ወቅት ግን በእስር ቤት ቀረቡልኝ የሚላቸው ጥሪዎችና ቃሎች እውነት ከሆኑ ለአንድ ኢትዮጵያዊ አስደንጋጭነት አላቸው። ይኸውም የህወሓት ጦር ወደ አዲስ አበባ ቢቃረብ የመንግስት ባለሥልጣኖች፣ ዲፕሎማቶች፣ የህወሓት አመራሮች፣ የኦሮሞ ልሂቃን ወዘተ ይዘዋቸዋል የተባሉ ዕቅዶች ናቸው። ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ሊገጥማት ይችል የነበረ ይመስላል። ነገ ምን እንደሚመጣ በማይታወቅበት በዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመን የአገራችን ዕጣፈንታ አሳሳቢ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል። የጃዋር ግለታሪክ የተለያዩ የሕይወት ገጠመኞቹንና ትውስታዎቹን የያዘ ሲሆን፤ ለአብነት የኦሮሞ ትግል በሕይወቱ ወይም በቤቱ እንዲንፀባረቅ የፈቀደበትን መንገድ ስናይ ልጆቹን የሰየመው ከትግሉና ከማንነቱ ጋር አያይዞ እንጂ እንደ አንድ ሙስሊም የአርሲ ሰው በአረብኛ ቃላት አለመሆኑ ነው። ልጆቹም ኦሮሞ፣ ቄሮ እና ቀብሶ (ትግል) ይባላሉ። ባራክ ኦባማ በ2006 ያሳተመውና በሁለት ዓመታት ውስጥ ለሥልጣን ያበቃው መጽሐፍ The Audacity of Hope ለፕሬዚዳንትነት ለመታጨት ያቀረበው ፕሮፖዛል ተደርጎ ተወስዷል። ስኬታማም ነበር። የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም'ም የብልፅግና ሥርዓት ለኦሮሞ አላሟላለትም የሚላቸውን በማሟላት ሽፋን የግል የሥልጣን ጥሙን ለማርካት አቅዶ ሊያካሂድ ላሰበው ሌላ ዘመቻ ዕቅድ ይመስላል።
* በየክፍሉ ያገኘኋቸውን ነጥቦችና የተሰማኝን በተወሰነ መልኩ ከአሁን በፊት በነበሩት ልጥፎቼ መጻፌ ይታወሳል።
ያነበባችሁት ዕይታችሁን አጋሩን።