2023 ጁላይ 8, ቅዳሜ

ሸንቁጤ

 

ሸንቁጤ

ልቦለድ

 

አሸብር ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ ስልክ ተደውሎለት ኖሯል፡፡ ‹‹እናትህ ደክማለች›› ብለው አስደንግጠውት ኖሯል፡፡ የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቷል፡፡ በባህላችን ደክማለች ማለት ሞታለች ማለት ነው ብሎ ተስፋ ቆርጧል፡፡ በቅርቡ በተደጋጋሚ ስልክ ብደውልለት አላነሳልኝም፡፡ እኩለሌሊት ላይ ከገጠር ከተደወለለት በኋላ የጽሑፍ ስራ እየሰራሁ ባለሁበት ደወለልኝ፡፡ ብተኛ ኖሮ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ ብዬ እበሳጭበት ነበር፡፡ ስላልተኛሁ ላወራው እችላለሁ፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ነው አለች ዘሪቱ ከበደ፡፡

ስልኩ ሲጠራ ግን ለማንሳት አልተነሳሳሁም፡፡ የጽሑፍ ስራዬን ተያይዤዋለሁ፡፡ በዚያች ቅጽበት በርካታ ሃሳቦች መጡብኝ፡፡ በአንድ በኩል ‹‹አይ ይኸ ሰው ደጋግሜ ስደውልለት ስልኬን ሳያነሳልኝ ተጸጽቶ ህሊናው እንቅልፍ ነስቶት ነው፡፡ ለመንገድ ስራው እኔ ከሳሲት ከተማ በማስተባበር ስሳተፍ እሱ እዚያው ወንፈስ የተወለደው ስልክ እንኳን ለመመለስ ከብዶት ዝም ስላለኝ ውስጡ ተጎዳ፡፡ ማሰብ ጀመረ፡፡›› የሚል ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ሌላም ሃሳብ መጣብኝ ‹‹ባለፈው ከተማ አግኝቶኝ ስጋ ቤት ሊጋብዘኝ ቢለምነኝ አይሆንም አልጋበዝም፤ በቀን አንዴ ተመጋቢ ነኝ፤ ሰዓቴም አሁን አይደለም ስላልኩት ለሐምሌ አቦ ፆሙ ሲፈታ ሊጋብዘኝ ቀጠሮ ሊያስይዘኝ ይሆን?›› እያልኩ ሳስብ ስልኬ በድጋሚ ጠራ፡፡ ‹‹አሁን ለእኔ ለመንግስት ሰራተኛው አንድ ሺ ብር አውጥቶ ስጋና መጠጥ ከሚጋብዝ እሱ፣ ቤተሰቦቹና ዘመዶቹ ለሚመላለሱበት መንገድ አይለግስም፡፡ ማስተባበር ሲገባው እንዴት ዝም ይለናል!›› እያልኩ እንደተቀየምኩ ልቀር ፈልጌ የነበረ ቢሆንም አነሳሁለት፡፡   

‹‹መዘምር እንዴት አመሸህ? ይቅርታ ከመሸ ደወልኩ፡፡››

‹‹ምንም አይደል ወንድሜ አሸብር፡፡ እንዴት ነህ? ስደውል ዘጋኸኝ ምነው?››

‹‹ምን እባክህ የኔ ነገር ዛሬ ነገ ስል … እ››

‹‹አሁን በደህና …›› ብየ ጥያቄዬን ከጥርጣሬ ጋር አስከተልኩ፡፡

‹‹እናትህ በድንገት ታመመች ብለው በአምቡላነስ አምጥተዋት ሪፈራል ሆስፒታል ገብታ ነበር፡፡ ትርፍ አንጀት ነው ብለውን ነበር፡፡ የምታውቀው ሐኪም ይኖር ይሆን?›› ሲል በፈጣን ንግግር ጠየቀኝ፡፡

‹‹በል አደራህን ማስታገሻ እየሰጡ ያቆዩዋቸው፡፡ አሁን ለአንድ ለማውቀው ዶክተር ልደውልና ልንገረው፡፡ ዶክተር አበራ ይባላል፡፡ ምናልባት ካለ ጠይቁና የሱ ቤተሰብ ነን በሉት›› አልኩት፡፡

ወዲያውኑ ጓደኛዬ ለሆነው ሐኪም ለአበራ ደወልኩ፡፡ ስለ ትርፍ አንጀት የነገረኝ ነገር ስላለ ነው፡፡ እኔ ያንን ነገር የሰማሁት አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ስለ ፕሮፌሰር አስራት በአንድ ቃለመጠይቅ ስትናገር ነበር፡፡ ሌሎች ሐኪሞች ትርፍ አንጀት ነው ብለዋት ቀዶ ህክምና ልትደረግ ስትሄድ አግኝታቸው መርምረው መድኃኒት ብቻ አዝዘው ከመቀደድ እንዳዳኗት ስታወጋ ሰምቼ ነበር፡ ፡ ያንን ለዶክተር አበራ ስነግረው እሱም እንደሚያጥመው ነግሮኝ ነበር፡፡ ደወልኩለትና ስልካቸውን አለዋወጥኳቸው፡፡    

ስራዬንም ቀጠልኩ፡፡ ነገሩ እንደፈራሁት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሐኪሞች ድንገተኛ ህመምን ሁሉ ሆድን ነካ ነካ አድርገው ትርፍ አንጀት ነው የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ይህም ሐኪም ጓደኛዬ የአሸብርን እናት መርምሮ ትርፍ አንጀት አለመሆኑንና በኪንን የሚድን ኢንፌክሽን መሆኑን ደርሶበት ኪንን ተጥቷቸው መሄዱን ስምንት ሰዓት ላይ ደወሉልኝ፡፡ በሜሴጅ አመሰገንኩት፡፡ ሌላ ቀን ደውዬ ወይም በአካል አግኝቼ አመሰግነዋለሁ፡፡

በማግስቱ ቤተመጻሕፍቴን ሳልከፍት በጠዋት የታሸገ ጭማቂ ይዤ ልጠይቃቸው ሄድኩ፡፡ እናትዬዋ አንድ ጥጋት ቁጭ ብለው ራሳቸውን ወደ ግንቡ ተንተርሰዋል፡፡ ጓደኛዬና ሚስቱ እንዲሁም ወንድሞቹ ያወራሉ፡፡ እናትዬዋ ሲያዩኝ እንባቸው መጣ፡፡ ‹‹የነፍሴ ጌታ፤ ውለህ ግባልኛ! ተባረክ፡፡ ያሰብከው ይሙላልህ!›› አሉኝ፡፡ ‹‹ያንተ ውለታ እኮ ነው ከመቀደድ ያዳነኝ፡፡›› ብለው አመሰገኑኝ፡፡ እኔም ያደረኩት ትልቅ ነገር እንዳልሆነ ነገርኳቸው፡፡ አልተስማሙም፡፡ ‹‹እዚያ ደሞ እነ አባተ አሉ ወንድሞቻችን፡፡ የነሱማ ምን ይነሳል ብለህ ነው?›› አሉኝ፡፡ መንገዱ በመሰራቱ አሰሪ ኮሚቴዎቹን ሁሉም ሰው እያመሰገናቸው ስላለ እኔም ከታማሚዋ እናት ጋር አመሰገንኩ፡፡ መንገዱ እንዴት በነፍሳቸው እንደደረሰ መች አወቅሁ፡፡ ለካ ወንፈስ ቆላ ለመንገድ ስራው የወረደ ፒካፕ መኪና ሳሲት ድረስ በትብብር አምጥቷቸል፡፡ ከዚያም በሌላ መኪና ወደ ደብረብርሃን በሰዓቱ ሊደርሱ ችለው ኖሯል፡፡  ሕይወታቸውን የታደጋቸውን መንገድና የመንገድ ስራ ቡድን አመሰገኑ፡፡ በዚህ ፍጥነት ከዚህ ምዕራፍ የደረሰው የመንገድ ስራ አኮራኝ፡፡ የተሳተፉትን ሁሉ በልቤ አመሰገንኩ፡፡

ጓደኛዬ አሸብር በጣም አዘነ፡፡ ‹‹የምን ትካዜ ነው? ደግሞ እናትህ ድነውልህ፡፡ ተመስገን በል›› አልኩት፡፡ ‹‹እሱማ ተመስገን ነው፡፡ እንዲያው ነገሩ እንጂ›› ሲል ጀመረ፡፡ ስልኬን ባለማንሳቱ ፀፀት እንደተሰማው፣ ገንዘብ መስጠት ሲችል ይህን ጠቃሚ ስራ ሳያግዝ እንደቀረ፣ ጓደኞቹን ማስተባበር ቢችል እንደማያቅተውና ስንፍና እንዳገደው ገለጸልኝ፡፡

‹‹መዘምር ይቅርታዬን ተቀበል፡፡ ለመንገዱ ስራ ይኸው በአካውንቱ 10 000 ብር አስገብቻለሁ፡፡›› በማለት ወዲያውኑ በሞባይል ባንኪንግ ያስገባውን አሳየኝ፡፡ ለካ የምንጽፈውን ሁሉ፣ የባንኩን አካውንትም ያውቅ ኖሯል፡፡ መንገዱ እናቱን ሲታደግለት ገባው፡፡ አመስግኜ ተሰናብቻቸው ልሄድ ስል እናትዬዋ ‹‹ለግንቦት አማኔል እንድትመጣ›› በማለት ጋበዙኝ፡፡ እስኪ የዚያ ሰው ይበለን፡፡

ሰላሳ

 


በሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ፣ ደብረብርሃን ስትሰራ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ ነች፡፡ አስቴር ዕድሜዋ ሰላሳ ሊገባ እየተቃረበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወጥታ መኖርን የጀመረችው ለዚህ ስራ ከወጣች ወዲህ ነው፡፡ ሕይወትን በተቻላት መጠን በደስታ ለማሳለፍ ትሞክራለች፡፡ በራሷ ዓለም የምትኖር ወጣት ነች፡፡ ሴቶች የሚፈሩት የተባለውን ዕድሜ ልትነክስ አምስት ወራት ይቀሯታል፡፡ ሴት ልጅ እስከ ሰላሳ አንድ ነገር ይጠበቅባታል፡፡ በእርግጥ ብዙ ነገሮች ይጠበቁባታል፡፡ አንዱን ክር መዘዝ የማድረግ ልማዷ አይለቃትም፡፡ ሕይወትንም በአንድ ጉዳይ መዳኘትና ያንን እንደ መስፈርት መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ ቢገባትም ለማድረግ ትገደዳለች - በፍቅርና በትዳር፡፡

ከአሁን በፊት ሁለት የወንድ ጓደኞች ነበሯት፡፡ ከእነርሱ በኋላ መልሳ ወደ ግንኙነት መግባትን ትፈራለች፡፡ልቧን ለሰው መስጠትን አትፈልግም፡፡ ግንኙነት ደግሞ ብቸኝነት የሚሰጠውን ነጻነት ይነፍጋታል፡፡ ደብረ ብርሃን ከወንድ ጋር ታይታ ስለማታውቅ ሰዎች በጥርጣሬ ዓይን ያይዋታል፡፡ ድንግል ነች የሚል አለ፤ የምትወደው እጮኛዋ ሞቶባት ነው ይሏታል፡፡ ብዙ አስቂኝ መላምቶችን ትሰማለች፡፡ እሷ በራሷ ምህዋርና ዓለም ስለምትኖር አይደንቃትም፡፡  ሦስት አስርት ዓመታት በዚህች ዓለም ላይ መኖሯ ያቃዣታል፡፡ የተሟላ ሕይወት መኖርን ትፈልጋለች፡፡

‹‹አስቱካ›› አላት ከፊት ለፊቷ የሚቀመጠው መሐመድ፡፡ እየጻፈች በነበረው ሪፖርት ላይ አትኩሮቷን ስላደረገች ለጥሪው ምላሽ አልሰጠችውም፡፡ በዚያ ላይ በጆሮ ማዳመጫ የጊታር ሙዚቃ እየሰማች ነበር፡፡ ደግሞ ጠራት፡፡

‹‹አናገርከኝ ሙሔ?››

ኢርፎኗን አውልቃ አትኩሮቷን ሰጠችው፡፡

‹‹እኔ የምልሽ ዛሬ እኮ የጥምቀት ዋዜማ ነው፡፡ ሰዎቹ ቀድመው የወጡት ለዚያ ነው፡፡ አንቺ ደግሞ ሳይሽ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይነካካሽም፡፡ ለምን ወደ ካፌ ወጣ አንልም?›› ሲል ጥያቄውን አቀረበላት፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት መሐመድ አሸምቆ የሚጠባበቀው እሷን ነው፡፡ እዚህ ቢሮ ከገባ አራት ወር ሆኖታል፡፡ ትዳር የለውም፡፡ አስቴርን ለፍቅር ይመኛታል፡፡ አስቴር ተስማማችና ወደ መስሪያ ቤቱ ካፌ ሄዱ፡፡ የካፌው ሰራተኞች ነጭ በነጭ ለብሰው ወደ ከተራ ሊሄዱ እየተዘገጃጁ ነው፡፡ ለመስተናገድ የማይመች ሁኔታ ሲያዩ ወደ ከተማ ለመሄድ ተስማሙና እቃዎቻቸውን ይዘው ወጡ፡፡ መንገዶች ሁሉ ነጫጭ በለበሱ ሰዎች ተሞልተዋል፡፡ በርኖስ ሆቴል ደርሰው ትኩስ ነገር ወሰዱ፡፡ አልኮል ለመጠጣት ብተፈልግም ከመሐመድ ለመመሳሰል ያደረገችው ነበር፡፡ ብዙም ሳያመሹ ተለያዩ፡፡ ደጋግመው ተቀጣጠሩ፡፡ ተገናኙ፡፡ ለተወሰኑ ሳምንታትን በፍቅር አሳለፉ፡፡ የመሐመድ የፀሎት፣ የምግብና መጠጥ ምርጫና ተአቅቦ ከሌሎች ዘንባሌዎቹ ጋር አልጣጣም ስላሏት ተወችው፡፡

ከመሐመድ ጋር ያላትን ግንኙነት ካቆመች ከሁለት ሳምንታት በኋላ በስራ ቅጥር ምክንያት አቤቱታ ይዞ ከአንኮበር ወረዳ የመጣ አንድን አቃቤ ህግም ተዋወቀች፡፡ የስልክ ቁጥሩን ወስዳ ስለነበር ፎቶዎቹን ስታይ፣ አንኮበርን ለማየትና ለማወቅ ያላትን ህልም ለማሳካት አሰበች፡፡ ወደ ጋቸኔና አልዩ አምባም ወርዳ ቆላውን መጎብኘት ፈለገች፡፡ ጠበሰችው፡፡ ኃይለማርያም ይባላል፡፡ አንኮበር ላይ ብዙ ሰው ዘመዱ ስለሆነና ያለው የግል የስልጣኔ ደረጃ ስላልፈቀደለት የትዳርንም ሆነ የፍቅርን ነገር ችላ ብሎታል፡፡ በሳምንት ውስጥ እሷን አንኮበር ይዞ ለመሄድ ቻለ፡፡ እፍ ያለም ባይባል ፍቅር ውስጥ ገቡ፡፡ በየቀኑ ይደዋወላሉ፡፡ ይሄዳል፤ ይመጣል፤ ትሄዳለች፤ ይመጣል፡፡ በተለይ ለሱ ፍቅር የተለየ ዓለምን አሳየው፡፡ ለሁለት ወራት ተዋደው ሰበብ ፈልገው ተለያዩ፡፡ ዋናው ነገር የኃይማኖት ጣጣ ነው ትላለች፡፡ ‹‹ፁሚ፣ ፀልዪ፣ ይህን ልበሽ ይህን አትልበሽ፣ ንስሃ አባት፣ ጥምቀት፣ ፋሲካ ይለኛል፡፡ እኔ እንደዚህ አይመቸኝም፡፡ በነጻነት ያደግሁ ልጅ ነኝ›› አንድ ቀን በወሬ መሃል አብራት ለምትሰራው ለአልማዝ ያለቻት ነበር፡፡

ሃይሌ ሪዞርት ደብረብርሃን በረንዳ ላይ ቢራ ይዛ ስታነብ አንድ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዶክተር የመዋኛውን አቅጣጫ ጠየቃት፡፡ ነገረችው፡፡ መዋኛው ጋ ሄደው ቢራ እየጠጡ ወሬ እንዲያዩ ጠየቃት፡፡ ስለምታነበው መጽሐፍ፣ ስለስራዋ፣ ስለ ሕይወት ጠያይቆ እንደምትሆነው አረጋገጠ፡፡ ፍቅር ደህና ሄደላቸው፡፡ የሕይወትን ወለላ ቀመሱ፡፡ የሆነ ነገር አስጠላት፡፡ በሳምንት ሁለት ቀናት ማታ እንዲሁም አንድ ቀን ጠዋት ሱፍ እየለበሰ ጉባኤ እያለ ይሄዳል፡፡ በመንገድ እየዞረም ይሰብካል፡፡ የይሖዋ ምስክር ነው፡፡ እሷም እንድትሆንለት ይፈልጋል፡፡ ደሞዙ፣ ሥራው፣ ንባቡ ሁሉ ያኮራል፡፡ ቢሆንም ተወችው፡፡ እሷ ሰላሳ ዓመት ካለፋት ስድስት ወር ሞላት፡፡ ዕድሜዋ እየበረረ ነው፡፡ ከአማኝ ጋር መኖር አለመቻሏ አሳሰባት፡፡ እንደማትችል ገባት፡፡

‹‹አለማመን አሰቃየኝ፡፡ ትክክል እንደሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ በአማኝ ባህር ውስጥ ሰጥሜ መሄጃ አጣሁ! ራሴን ደብቄ ለመኖር ተገደድኩ፡፡ የማያምን ወንድ ማግኘት ወይም ለዘብተኛ አማኝ ማግኘት አቃተኝ፡፡ ቻው ማሚ፣ እወድሻለሁ፡፡›› የሚል ማስታወሻ ትታ ራሷን አጥፍታ ተገኘች፡፡ ያዘነላት አልነበረም፡፡

አስከሬኗ ሲሸኝ ‹‹የታባሽ ከሃዲ›› ያለውን የፖሊስ አባል ቃል የተጋራው ብዙ ነው፡፡    

 

የሳሲት ወጎች ቁ. 14 አስኮብላይቱ

 

የሳሲት ወጎች

ቁ. 14

አስኮብላይቱ

 

ጠንፌ የአዲስ አበባ ኑሮ ስርንና መሰረትን ሳይለቁ ካልሆነ እንደማይገፋ ታውቀዋለች፡፡ ስሯ ተጉለቴ ነው፤ መሰረቷ ዥማይ ቆላ፡፡ ለሐዘን እምብዛም አትመጣም፤ አምስት ስድስት ለቅሶ ሲጠራቀም ትደርሳለች፡፡ ለደስታ ግን ማንም አይቀድማትም፡፡ ሠርግ ቢሆን ክርስትና፣ ንግሥ ቢሆን ማህበር ትመላሳለች፡፡ ሦስትና አራት ቀን ከነባሏ እልፍኝ ተቀምጣ ትቀለባለች፡፡ በእርግጥ እዚች ጋ የተሻለና ለስለስ ያለ ቃል አይጠፋም ነበር፡፡ ተራኪው ጣት ላይ ዱብ ያለችው ትቀለባለች ሆነች እንጂ፡፡ ምክንያት ይኖራታል እንጂ ዝም ብላ አልመጣችምና ተራኪውም የታዘዘውን ጫረ፡፡ ለካ መጫር ቀርቷል - ጠቅ አደረገ፡፡

በመጣች ቁጥር ውሱን ስጦታዎችን ትይዛለች፡፡ በጥቂት መቶዎች የሚቆጠር ብር አውጥታ ቤተዘመዱን ታስደስታለች፡፡ በምላሹ ግን ብዙ እጥፍ ታፈራለች፡፡ እህል አትገዛም፤ ቅቤው፣ ማሩ፣ ሙክቱ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉ ነገር ከዥማይ ቤተሰቦቿ ነው፡፡ ገና የ16 ዓመት ኮረዳ ሳለች ተጉለትን ለቃ አዲስ አበባ ገባች፡፡ ለዘመዶቿ በሰራተኛነት ልታገለግል ሄዳ የማታም አስተማሯት፡፡ የማታ ስትማር የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆና አንድ አብሯት የሚማር የሰላሌ ተወላጅ የሆነ ፖሊስ አገባች፡፡ አምስት ረድፍ ያለው የአንገቷ ንቅሳት ጎዳት እንጂ ከፖሊስ በላይ ስራ ያለው ሰው ታገባ ነበር፡፡ በእርግጥ ቶላ ከሷ አንጻር ሲታይ ተጣጣሪ ነው፡፡ እሷ የቤት እመቤት ነች፡፡

እሷ ከአዲስ አበባ ቤተሰቧን ይዛ፣ ታላቅ ወንድሟ ገብረም ከደብረብርሃን ቤተሰቡን ይዞ ቤተዘመዶቻቸውን ሊጠይቁና አክፋይ ሊገቡ ለ1991 ዓ.ም. የፋሲካ ማክሰኞ ዥማይ ወረዱ፡፡ ገብረ እንደ ታላቅ ወንድምነቱ ያከብራታል፤ ይወዳታል፡፡ ጥሩ የሚባል ግንኙነትም አላቸው፡፡ አንድ የማያስማማቸው ጉዳይ ቢኖር እሷ ያላት የብዝበዛ መንፈስ ነው፡፡ ከቤተሰቧ ጋር በማትሆንበት ጊዜ ብቻዋን ካገኛት ‹‹አጅሪት›› ነው የሚላት፡፡ አሁንም ከደብረብርሃን ወደ ሳሲት በሚወርደው የይፍሩ የጭነት መኪና ላይ ከላይ በሸራ ውስጥ ተጭነው ጎን ለጎን ስለነበሩ ከተመደው ‹‹ጤናሽስ?›› ‹‹ቤተሰብሽስ?››  በኋላ ወጉን ጀማመረ፡፡

‹‹አጅሪት፣ እንዲያው መቼ ነው ራስሽን የምትችዪው››  

‹‹እንዴ ከዚህ በላይ!››

‹‹ስትይ? ዕድሜሽ ስለሄደ? ቤተሰብ ስለምታተዳድሪ? ልጅ ልትድሪ ስላሰብሽ?››

‹‹አገኘኸኝ ወንድምጋሼ! ከዚህ በላይ ራስን መቻል ምን አለ?››

‹‹ባለፈው ተነጋግረን መልሰሽ እዚያው! ጥገኝነትን ለትውልድ ልታስተላልፊ ነው? ልጅሽም ከተጉለት ጤፍ ስትጭን ልትኖር ነው? ደሞ የተጉለቱ በበቃ፡፡ ከፍቼም የዚህኑ ያህል ይጋዛል፡፡ እንዲያው ገበሬዎቹ ማለቴ አዛውንቶቹ አያሳዝኗችሁም ወይ? አሁን አባባ ወደ ዝኆንሜዳዋ መሬታችን ሲሄድና ሲመጣ የሚያየው ስቃይ አይታወስሽም?››  

‹‹ሌላም ወሬ የለህ? በዚህ ሁኔታ መንገዱ አይገፋልኝም፡፡ አንተ ቆይ መቼ ነው ሌላ ነገር የማይታይህ? ከፈለግህ አንተስ ለምን አትጭንም!››

‹‹አይነካካኝም፡፡››

‹‹ሃብታም ነሃ! በደህና ቀን ዉጪ ተማርክ፡፡ ያው ሩሲያ እንደ አሜሪካም ባይሆን!››

‹‹እንደምታስቢው የገንዘብ ሃብት አይደለም፡፡ የህሊና ሃብት እንጂ፡፡››

‹‹ደጋግመህ መማርህን ልትነግረኝ አትጣር፡፡ ሳይማር የተማረ ስንት አለ መሰለህ ?››

‹‹ተማሪ፤ ወይንም ነግጂ፡፡ በተቻለኝ እንተጋገዝ፡፡ በሽማግሌዎች እንዴት ትጦሪያለሽ?››

‹‹አረ አግዘኝ፡፡ በሽማግሌ መረዳት እንዳይሆንብኝ እንጂ፡፡ ሸበትክ እኮ ወንድምጋሼ!›› ብላ ፀጉሩን ነካካችውና ልጇ ወደተቀመጠችበት ጥጋት ሄዳ ስለ አስተዳደጓና ስለመንገዱ ወሬ ጀመረች፡፡ 

በይፍሩ መኪና ታጭቀው ከስንት ጉዞ በኋላ ሳሲት ደረሱ፡፡ የሳሲት ተሳፋሪ ወረደ፡፡ ባለ አክፋዮቹ ግን ሳሲት ከመቶ አለቃ ኪዳኔ ቤት ሻይ ቡና ብለው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ፈላ ድረስ መንገድ ስላለ መኪናው እዚያ መሄዱ ግድ ይላል፡፡ እዚያ የወፋ ነገሰ ቀዬ ስላለ ባለጉዳዮች ከተለያዩ አካባቢዎች ይሄዳሉ፡፡ የጠንፌና የገብረ ቤተሰቦች ከዚያ ወደ ዥማይ ብዙ መንገድ ይጠብቃቸዋል፡፡ አስቸጋሪ ስርጥና ቁልቁለት አለ፡፡ በቤተሰብ ፍቅር እየተመሩ ከባዱን መንገድ ቀላል አደረጉት፡፡ ከተማ ተወልደው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገጠር ያቀኑት ልጆቻቸው ግን የጭነት መኪናውም ሆነ የእግር ጉዞው አድክሟቸዋል፡፡

ደግነቱ ቀድመው እንደሚመጡ በመልዕክተኛ ስለነገሯቸው ወጣት ወጣት ዘመዶቻቸው ፈላ ድረስ ወጥተው ተቀብለዋቸዋል፡፡ 

‹‹ሜዳው ደስ አይልም?›› አለች ኤልሳ፣ የጠንፌ ልጅ፡፡

‹‹ያን ሁሉ መኪና ጭንቅንቅ አልፌ እዚህ መድረሴ ገርሞኛል፤ ቆንጆ አገር ነው እነ አባቢ ያላቸው›› ሲል አዳነቀላት የአጎቷ ልጅ አሻግሬ፡፡

የቁልቁለቱ መንገድ አስጊ ነበር፡፡ ታዳጊዎቹ በወላጆቻውና ዕቃዎቻቸውን በተሸከሙላቸው ዘመዶቻቸው ድጋፍ ከአያቶቻቸውና ዘመዶቻቸው ቀዬ ሲደርሱ አቀባበሉ ደማቅ ነበር፡፡ ሁሉም ከየቤቱ የወጣ ይስማቸዋል፡፡

‹‹አሻግሬ፣ እዚህ ሁሉም ዘመድህ ነው፡፡ አንድም ባዳ የለህም!›› አለው ገብረ፡፡ አሻግሬ የእድሜ እኩያው ከሆነችው ከአክስቱ ልጅ ከኤልሳ ጋር ስለ እግርኳስ፣ ስለ ፊልም፣ ስለ ትምህርት የሞቀ ወሬ ይዞ የአባቱን ንግግር ብዙም ቁብ አልሰጠውም፡፡ ገብረ በትምህርት ቤት ተዋውቋት ያገባትና የልጆቹ እናት ኤርትራዊቷ ሀዳስ ዘንድሮ ቤት ጠባቂ ሆና ከትንሹ ልጃቸው ጋር ደብረብርሃን ነች፡፡ በቁልቋልና በቅንጭብ የታጠረና ከሩቅ ሲየዩትአረንጓዴ ደሴት ከሚመስል ግቢ ደረሱ፡፡ የአያቶቻቸው ግቢ ነው፡፡ ውሾቹ ቡፍ ቡፍ አሉ፡፡ እንስሶቹ ውጪ ውጪውን ይላሉ፡፡ የሳር ክዳን ካለው ኩሽና ጭሱ ይጫጫሳል፡፡ ወደ ቆርቆሮው እልፍኝ ገቡ፡፡ እርጥብ ቄጠማ ተነጥፏል፡፡ ወንድ አያታቸው ከበሩ በስተቀኝ ቁጭ ብለው ሲቀበሏቸው ልጆቹ ጉልበት ስመው ነው፡፡ እሳቸውም የልጆቹን ጉንጭ ስመው ይመርቃሉ፡፡ አያታቸው ትኩስ ከታረደው የፍየል ስጋ ጉበት፣ ጨጓራ፣ ኩላሊት የተቀላቀለና በሽንኩት፣ ቃሪያና ደቃቅ ጨው የተለወሰ ግብዣ በየእጃቸው ሰጧቸው፡፡ ያንን ይዘው የሴት አያታቸውን ጉልበት ስመው ተቀምጠው መብላት ጀመሩ፡፡ የማር ጠጁና ጠላው ይንቆረቆር ጀመር፡፡ ዳቦው በአንድ ፊት በሰዲቃ ቀረበ፡፡ ስጋ ወጡ በጤፍና በማሽላ እንጀራ በትልቅ ገበታ ቀርቦ ቤተሰብ ሁሉ በላ፡፡ ከምግብ በኋላ ከልጅ እስከ አዋቂ እንግዶቹን  ከበቧቸው፡፡ እነሱም ብርቅ የከተማ ከረሜላዎቻቸውን፣ ብስኩቶቻቸውን፣ አዝራሮቻቸውን፣ ልብሶቻቸውን ሰጧቸው፡፡

ገጠር መዋልና ማደር ያለውን ደስታ አጣጣሙ፡፡ ከዘመዶቻቸው ጋር ተገናኙ፡፡ ራቅ ብለው ዱሩን ያያሉ፡፡ ወንዶቹ በማግስቱ ዋና ሄደው ዓሳ አሰገሩ፡፡ ዱር ሄደው በአጎታቸው በጌታነህና በግጨው በልጅግ ሰስና ድኩላ አደኑ፡፡

ጠንፌ ግን ቤት ቤቱን፣ ጓሮ ጓሮውን ትላለች፡፡ ልጆችን ታዋራለች፤ ስራዎችም አሉባት፡፡ ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና የሦስት ቀኑ ቆይታ ቅዳሜ ጠዋት አበቃ፡፡ በእንባ ተሰናበቱ፡፡ ያ ቁልቁለት ዳገት ሆኖ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡ እንደምን ወጡት፡፡ ከመንገዱ አስቸጋሪነት አንጻር ድጋሚ የሚመጡ አልመሰላቸውም፡፡ ደግሞ የወገን ፍቅር አለ፡፡  የወፋ የችነት መኪኖች አርብ ወደ ፈላና ሳሲት ስለሚመጡ ወደ ደብረብርሃን ለሚመለስ ሰው ያለው ቅርብ አማራጭ ቅዳሜ ብቻ ነው፡፡ ለዚያ ነው እንግዶቹ ከገበያተኛ ዘመዶቻቸው ጋር ወደ ሳሲት የወጡት፡፡ ለሜዳው ፈረስና በቅሎ ተፈልጎ ከተመኞቹ ሴቶች በፈረስ ጋለቡ፡፡

ሳሲት የሰባተኛ ክፍል ተማሪው አድማሱ እስከ ስድስት በፈላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ለሰባተኛ ክፍለ ትምህርቱ ሳሲት መጥቶ ዘመድ ቤት ተቀምጦ ይማራል፡፡ ቅዳሜ ሲሆን ስራው መዞር ነው፡፡ የቤት ስራውን አርብ ማታ ይጨርስና እሁድ ቅዳሜ ቤተሰቦቹ ከዥማይ ስለሚመጡለት እነሱን ያገኛል፡፡ ዘመዶቹ አንድም ሁለትም ብር አይነፍጉትም፡፡ ዘመዶቹንና ቤተሰቦቹን አግኝቶ፣ ስንቁን ተቀብሎና ተሰናብቶ ቅዳሜ ገበያ እህል የሚጭኑትን መኪኖች አይቶ ወደ ከተማው መውጫ ለምግብ ማብሰያ የሚሆነውን እንጨት ለመልቀም ወደ ጫካ ሄዶ ባህርዛፍ ላይ ወጥቶ ጭራሮ ያወርዳል፡፡ ዛፍ ላይ ሆኖአንድ ነገር ውልብ አለው፡፡ ዛፍ ስር የተቀመጠች ልጅ ነበረች፡፡ ዓይኖቹን ማመን አልቻለም፡፡ ወርዶ ያዛት፡፡ የዥማይ ልጅ ነች፡፡ ምን እየሰራች እንደሆነ ጠየቃት፡፡ ልታወጣ አልቻለችም፡፡ ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትወርድ ጠየቃት፡፡ ፍላጎት አላሳየችም፡፡ እጇን ይዞ እየጎተተ እሷም እያለቀሰች ወደ ገበያው ይወስዳት ጀመር፡፡ ገበያውም ጋ ህዝቡ ተሰበሰበ፡፡ ፖሊስም መጣ፡፡ የዥማይ ሰዎችም መጡ፡፡ ዙሪያውን ብዙ ህዝብ ከበበ፡፡ የልጅቱ ቤተሰቦች ዘመዶቻቸውን ለመሸኘት እነሱን ከበውና ዕቃቸውን ይዘው ስለነበር አልመጡም፡፡ የአገር ሰው ሄዶ ጠራቸው፡፡ መጡ፡፡ ክው አሉ፡፡ ጠንፌም ተጠራች፡፡ እንዳላወቀች ሆነች፡፡ ልጅቱን ስትሰብካት ከርማለች፡፡ በእግሯ ሳሲት ወጥታ ከከተማው ዳር ጫካው ውስጥ ተደብቃ እንድትጠብቃት ነበር፡፡ መኪናው እዚያ ሲደርስ አስቁማ ልታሳፍራት አስባለች፡፡ ጠንፌን ፖሊስ አሰራት፡፡ ልጅቱንም ለቤተሰቦቿ አስረከበ፡፡ በህገወጥ የሕጻናት ዝውውር ወንጀል ተፈርዶባት ወደ ደብረብርሃን ወህኒ ቤት ተጋዘች፡፡ ከዘመዶቿ ተቆራረጠች፡፡ ታላቅ ወንድሟ ገብረም እየጻፈ ላለው የኢትዮጵያ ከተሞች በስንፍናና በሆዳምነት ተይዘው ለፍቶአዳሪው ገጠር ላይ እንደመዥገር የተጣበቁ መሆናቸውን ለሚያሳየው መጽሐፉ ግብዓት አገኘ፡፡  


ግለ ታሪክ 2

 በስድስት ዓመቴ ትምህርት ቤት ማለትም አንደኛ ክፍል ገባሁ፡፡ ትምህርት የሚባል አላውቅም፡፡ የአንደኛ ክፍል ስም ጠሪዬ ቲቸር ታደሰ መረብ ኳስ ሲጫወቱ በጓደኛቸው ‹‹እነ መዘምር እኮ ምንም አያውቁም፡፡ ዓመት ሙሉ ተመላልሰው እንዴት ልጣላቸው ብዬ ነው›› ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? አባቴ ዕድሜዬ ሳይደርስ አስገባኝ፡፡ እስከ አራተኛ ክፍል ምንም ሳላውቅ ቆየሁ፡፡ የየክፍሉ ትምህት ይደራረባል፡፡ እሱ ጥሩ ያደረገ መስሎት ወይም ዕድሎችን ሲሻማ እኔ በመሐል ቤት ተጎዳሁ፡፡ የአንድን ሰው ሕይወት ማበላሸቱን አስቡት፡፡ እኔ ያለዕድሜዬ ገብቼ ሦስት ዓመት የሚበልጠኝ ወንድሜ ማለትም እንጀራ ልጁ እኔ ሦስተኛ  ክፍል እስክደርስ በግ እረኛ ሆኖ ቀረ፡፡ ያ ክፋት በኔ ትምህርት አለመሳካት ተካካሰ፡፡ ያ ልጅ በአደጋ ሲሞት አባቴ ምን ተሰምቶት ይሆን? በክፋት ውስጥ አድጌ ይህን ለማጽዳት እየሰራሁ ነው፡፡   

2023 ጁላይ 6, ሐሙስ

የሳሲት ወጎች ቁ. 13 ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ?

 የሳሲት ወጎች

ቁ. 13

ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ?

 

ገጠርን ስታስቡ ምን ይሰማችኋል? የመዝናናት ስሜት ይመጣባችኋል? ወይስ ይጨንቃችኋል? እስኪ በሁለት በኩል ሊነሱ የሚችሉ ሃሳቦችን እናንሳ፡፡

ገጠር እንደሚያስደስታቸው፣ እንደሚያዝናናቸውና ሰላም እንደሚሰጣቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ገጠር ከሁካታ የራቀ ሰላማዊ ቦታ ተደርጎ ይታያል፡፡ የአየሩ ንጽህና፣ የሰዉ የዋህነት፣ የህይወቱ ቀላልነት፣ የምግቡ ተፈጥሯዊነት ተደማምሮ ገጠርን የመሰለ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ቢል የለባችሁም፤ የቤት ኪራይ ደረሰ አትሉም፡፡ ነዳጅ አያሳስባችሁም፡፡ ምን ብዬ ልንገራችሁ? በተለይ በከተሜ ዓይን ሳየው ይህንን አያለሁ፡፡ ከዚህኛው የወንዙ በኩል ሆኖ ሲያዩት የዚያኛው በኩል የበለጠ ይጣፍጥ ይመስላል እንዲሉ ላሞች፡፡

ገጠር የሚያንገሸግሸው አለ፡፡ አንድ አጎቴ አለ፡፡ አደናውሰኝ ዘነበ ይባላል፡፡ አረም የሚያርምበትም ሆነ እርሻ የሚያርስበት ማሳው ዋሻ በተባለ ቦታ ይገኛል፡፡ ጠዋት የወጣ በዚያ በተራሮች በተከበበ ቦታ በሚገኘው ማሳው ላይ ሲሰራ ውሎ ማታ ሲመለስ ነው ሰው የሚባል የሚያየው፡፡ በጣም ይጨንቀኛል ይላል፡፡ ሌላ ቀን እናቴ ለምናው ከሳሲት ወደ ሰላድንጋይ ከሚወስደውና ወስዶ ከሚመልሰው መኪና መንገድ ዳር ባለው መሬቷ ላይ ሲያርሙ ይውላሉ፡፡ ከሰው ጋር እያወሩ ማረም የበለጠ እንደሚያስደስተው ነገራቸው፡፡ መንገድ ዳር በሚገኘው ማሳ ላይ በመዋሉም መንገደኞችንና መኪኖችን እያየ ይዝናናል፡፡ ከዚህች ንጽጽር እንኳን ስናይ ገጠር የሚያስጨንቀውና ከተማና የሥልጣኔ ትሩፋት የሚያስደስተው አለ፡፡

ገጠር የሚያስደስታቸው ለአንድና ሁለት ቀን የሆነም አይጠፉም፡፡ ዘመድ ለመጠየቅ፣ ለለቅሶ፣ ለሰርግ፣ ለንግሥ፣ ለመንፈሳዊ ጉዞ ወዘተ ብቅ ብለው የሚመጡ አሉ፡፡ ‹‹ክረሙ›› ብተሏቸው ‹‹ግደሉኝ›› ብለው ይቃወማሉ፡፡ ‹‹ልጄ፣ ሜስቴ፣ ዕቁቤ፣ ፓርቲዬ ብለው ልሂድ ይላሉ፡፡

ገጠር የሚያንገሸግሻቸው በአንዳንድ ሁኔታ እንጂ ከገጠር ስብዕና አይወጡም፡፡ የከተማ ሁካታ ሲሰማቸው መልሰው ያቺው ገጠሬ ይላሉ፡፡ ከላይ ያየነው አደናውሰኝ ስለ ሥልጣኔ ለማየት የቻለው ዘግይቶ ነው፡፡ የቄስ እንጂ የመንግስት ትምህርት አልተማረም፡፡ ሰላድንጋይን እንኳን በ30 ዓመቱ አየ፡፡ አዲስ አበባን ቢያይ መንግስተሰማያት ሊመስለው ይችላል፡፡ ቆይቶ ሲኦል ነው ሊልም ይችላል፡፡ ያብለጨለጨ ሁሉ ወርቅ አይደለምና፡፡

አሁን በሚገባ ከተዘናጋችሁና ወደ ወሬው መሐል ከገባችሁ ዘንዳ ወደ ሳሲት ወግ እንምጣ፡፡ ከገጠርና ከተማ የቱ ይሻላል ከሚለው ወጥተን የገጠር ከተማ ላይ ሕይወት ከመዝናናት አንጻር ምን ይመስላል ወደሚለው እንምጣ፡፡   

ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ ስንል እንደየወቅቱ ሁኔታ፣ እንደ ሰውየው ወይም ሴትዮዋ የዕድሜ፣ የሃብት፣ የጾታ ሁኔታ ወዘተ ይለያያል፡፡ የቅዳሜ ገበያ ድብድቦችና ትዝታዎቼ የሚለውን ጽሑፌን መለስ ብላችሁ ብታዩ ቅዳሜ ምን ያህል ሰው የሚዝናናባት አንደሆነች ትገነዘባላችሁ፡፡ ከቴፑ ሙዚቃው ሲንቆረቆር፣ የመኪናው ጡሩምባ፣ የሰዉ ሁካታ፣ የግርግሩ አጠቃላይ ሁኔታ ያቺን የቀዘቀዘች ከተማ ሲያደምቃት በቅዳሜ ገጽታ መዝናናታችሁ የማይቀር ነው፡፡ ልዩ ልዩ ትዕይንት አለ፡፡ ከዚያ እየመረጡ መኮምኮም ነው፡፡ ቅዳሜ ወሬ ልይ ብሎ ለመዝናናት የሚወጣው ሰው ብዙ ነው፡፡  ጠጅ ቤት ጎራ ማለት፣ ብርዝ በዲፎ ዳቦ መብላት፣ ጠላ መኮምኮም፣ ለስላሳና ቢራ ማንቆርቆር፣ ሻይ ፉት ማለትም ይቻላል፡፡ አረቄን አልረሳሁም፡፡ ኮበሌ አቅፎም ባይሆን ጎን ለጎን ሆኖ መንሸራሸርም ይቻላል፡፡ ጠጅ ቤትን ካነሳን የክንፈ ጠጅ ቤት አለ፡፡ የከተማችንን ታዋቂ ሰው ማለትም በከተማው ፒያሳ ላይ ሰፊ ግቢ ያላቸውን የጋሽ ኪዳኔን ልጅ ነው ያገባው፡፡ በደርግ ጊዜ እነ ጋሽ ወጋየሁም ጠጀ ቤት ነበራቸው አሉ፡፡ አልደረስኩበትም፡፡ ሌላው ታዋቂ ጠጅ ቤት ዘቦንቻው ጠጅ ቤት ሲሆን ባለቤቱ ከአዲስ አበባ ወይም ከአንድ ትልቅ ከተማ የመጡ የተማሩ ሰው ናቸው፡፡ እደጅ ቁጭ ብለው የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን በትርፍ ጊዜያው ሲያነቡ አያቸዋለሁ፡፡ ከከተማ የወያኔ ፓለቲካ ያባራቸው ወይም ተጉለቴ ዝርያቸው ወደ ሳሲት ይግፋቸው አላውቅም፡፡ ጥናት እያደረጉም ይሆናል፡፡ ‹‹እናንተ፣ እዚህ ቅንጅት ቅንጅት ስትሉ ኦነግ እንዳይገባላችሁ!›› እንዳሉኝ እንደ ጋሽ ልጃምባው ሁሉ በፖለቲካ የነቁ ተጉለቴ ከተምኛ ጎብኛችን ይሆናሉ፡፡ በየገባችሁበት ጠጅ ቤት አሸናፊ ወርቅሸትንም ሆነ አባቱን ወርቅሸት ተክሌን ማግኘታሁ አይቀርም፡፡ ደግ ስለሆኑ ይጋብዟችኋል፡፡ ሳቃቸው በተለይ አይረሳም፡፡

በበዓላት ያለው መዝናኛ ልዩ ነው፡፡ የፋሲካ ሩር ልገታና እሱን የሚከተለው ከኳስ ሜዳ እስከ ዥንጎዶ ተራ አቧራ የሚያጨሰው ጭፈራ አለ፡፡ ሴቶቹም ከበው ስምንት ቀን ይጨፍራሉ፡፡ ቡሄ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ገና፣ ጥምቀት አሉ፡፡ የየአካባቢው አገር ንግሥም አይረሳም፡፡ ዘመድ መጠየቂያና ልዩ መዝናኛ ነው፡፡

ዘመን አመጣሽ መዝናኛዎችም አሉ፡፡ ጆተኒ፣ ቴኒዝ፣ ሙዚቃ፣ በእጅ ተይዛ ሁለት ዓይን ላይ ተደርጋ የምትታይ ፊልም፣ ኋላ የመጣውና ሙሉ ታሪኩን የጻፍኩለት ቴሌቪዥን አይረሱም፡፡ ቴፕ ወይም ሬዲዮ ያላቸው ወደ ሃብታምነት የተጠጉ ናቸው፡፡ በቴፕ የአስቴር አወቀን ሙዚቃ የሰማ ከሳሲት በታች ያለ ገጠር ውስጥ ያደገ ልጅ አንዲት ሴትዮ ብቻዋን አውራጅም ተቀባይም መሆኗ አግራሞት አንዳጫረበት ነግሮኛል፡፡

ጠላ ጠጥቼ የሰከርኩት አስረኛ ክፍል ሆኜ ግዛው ጌታነህ ጋብዞኝ ነው፡፡ ሌላ የሚያካሂደው ሰው አጥቶ የጋበዘኝ ግዛው ና አጫውተኝ ብሎ ወስዶኝ ነው፡፡ ሁለት ሽክና ጠላ አስክሮኝ ሌላ ዓለም ውስጥ ገባሁ፡፡

ሳሲቶች ስራ ከሌለባቸው ጠዋትና ማታ ፀሐይ እየሞቁ ተሰብስበው ማውራት ልማዳቸው ነው፡፡ ቀንም ቢሆን እቤት ወይም ጥላ ቦታ ሆነው ማውራታቸው የተለመደ ነው፡፡ ዕለቱ ጠላ የተጠመቀበት ከሆነ ወደተጠመቀበት ቤተ ሄደው እየጠጡ ያወጋሉ፡፡ ውርርድ ይወራረዳሉ፡፡ ጨዋታ አዋቂዎች ይጠራራሉ፡፡ ጓደኛሞች ይገባበዛሉ፡፡ ስራ እየሰሩ ማለትም ሴቶቹ ስፌት እየሰፉ፣ እህል እየለቀሙ፣ ምግብ እያዘጋጁ ይጨዋወታሉ፡፡

ትምህርት ቤት ግቢ ወይም ምድርኮሶ ሄደው ስፖርት የሚሰሩ ወይም የእግርኳስና የመረብኳስ ግጥሚያ የሚያዩ አሉ፡፡ ዓመታዊ የትምህርት ቤቶችን ውድድር ማየቱም አስደሳች ነው፡፡ ሩጫ፣ ዝላይ፣ ኳስ አለ፡፡ አዝናኝ ውድድሮችም እንዲሁ፡፡ የሞጃ ህዝብ የሚገናኝበት ነው፡፡ እኛ አንዲት አንድ ብር በነፍስወከፍ የምናዋጣባት የእግርኳስ ክበብ ነበረችን፡፡ አባላችን ጌትሽ ጠብቄ ወደ ሀረር ወይም ሌላ ከተማ ሄዶ ናፍቀነው ደብዳቤ ልኮልን ተሰብስበን ተነቦልናል፡፡

ትልልቅ ሰዎች ሲሰበሰቡ ሁልጊዜ  ወሲብ ተኮር ወሬ የሚያወሩ አሉ፡፡ በቀልድና ጨዋታ አዋቂነታቸው የሚፈለጉ ደማሞች አሉ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ጨማምሩበት፡፡

2023 ጁላይ 5, ረቡዕ

የሳሲት ወጎች ቁ.12 የቤተክርስቲያናችን ድግሶች

 ሁሉም የሳሲትና የልጅነት ወጎቼ ቢስቡኝም ስለ ቤተክርስቲያናችን ስጽፍ ግን ትዝታው በጣም ያይልብኛል፡፡ ያው ትዝታው የሚገንባችሁ አንድ ነገር ካናደዳችሁ ወይም ካስደሰታችሁ ነው፡፡ ጋሽ ሰለሞን ዴሬሳ ለተፈራ ገዳሙ በአሜሪካ በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ያለው ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ኤደንም ሆስፒታል ልጠይቃት ሄጄ ያለችኝ አይረሳኝም፡፡ ምነው እንደተመራማሪ ምንጭ መጥቀስ አበዛህ እንዳትሉኝ፡፡ የእነርሱን ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡

‹‹ምንድነው ስሜታዊ የሚያደርግህ? ሰሞነኛ ነበርክ እንዴ?›› ለሚለኝ ሰው ‹‹አልነበርኩም፤ የሰሞነኛ ልጅ ግን ነበርኩ›› እላለሁ፡፡ በተለይ ትንሽ ልጅ ሆኜ ምናልባትም አምስተኛ ክፍል አካባቢ ድረስ ቤተክርስቲያናችን ለኔ በጣም ቅርበት ሊኖራት የቻለው አባቴ መርጌታ ስለሆነ በበዓላት ወቅት ስሄድ ሁልጊዜ ከሱ ሳልለይ የቤተክርስቲያኗን አገልግሎቶት ስለምካፈልና ትርዒቱን ሁሉ ስለማይ ነው፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ድግሳቸው ይምጣብኝ፡፡ ቄሶቹ ድግሳቸውን እያሳዩ ያማልሉኛል፡፡ የቄስ ትምህርት ተምሬ ዲያቆን ወይም ቄስ ሆኜ ዳቦ እንድበላ ይመክሩኛል፡፡ በአንጻሩ ወደ መንግስት ትምህርት አዘነበልኩ፡፡ ይኸው መንግስት የቆረጠልኝን የማያድግ ምንዳ እየተቀበልኩ እኖራለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን ትንሽ የሚከብደኝ መቆሙ ነው፡፡ እግራችሁን ያማችኋል፡፡ ባለፈው ወርቅጉር ገብርኤል ከሳሲቱ ከ16 ዓመት በኋላም ሆነ ሳሊተ ምህረት ለዶክተር ፍስሃ ቁርባን ከሃያ ዓመት በኋላ ሳስቀድስ በመምህርነቴ መቆምን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ቅምም አላለችኝ፡፡ አንድ ዘመዴ ደግሞ ይኸውላችሁ ከምሳ ሰዓት እስከ ምሽት ድረስ ለማንቸስተር የዋንጫ ግጥሚያ ሰው በዝቶ ወንበር ሳያገኝ ቀርቶ ቆሞ ነበር፡፡ ይኸውም ቦታ እንዳይያዝ ብሎ ቀድሞ ገብቶ ነው፡፡ ማታ ሲያገኘኝ ››አቤት! ቀን የቆምኩ አሁን አለቀ፡፡ ይሄኔ እኮ ቤተክርስቲያን ቢሆን አንድ አፍታም አልቆምም!›› ያለውም ትዝ አለኝ፡፡ ምሳሌ ሳላበዛ ልመለስ፡፡ ያቺ የኮረብታ ላይ ታቦት ከሩቅ ውበት አላት፡፡ የኖረች ቤተክርስቲያን ነች፡፡ በስተምዕራብ ደጀሰላሙ አለ፡፡ እሱ የቤተክርስቲያኑ ምግብ ቤት ነው፡፡ ሁለት ረጃጅም አግዳሚ ገበታዎች ተሰቅለዋል፡፡ ካህናትና ሌሎች ምዕመናን በረድፍ ተቆምጠው የሚበሉባቸው ናቸው፡፡ ዋንጫዎችም አሉ፤ መስቲና ገንቦም አልረሳሁም፡፡ ‹‹ና፣ አባትህ ጉያ›› እባላለሁ፡፡ መጀመሪያ ዳቦ ይቆረሳል፡፡ መዓዛው የሚያውድ የጥቁር ወይም የነጭ ስንዴ ዳቦ ነው፡፡ ዓይነውርቴም አለ፡፡ እናንተ አነባበሮ ነው የምትሉት፡፡ እንጀራው ይከተላል፡፡ ከታች ቅይጥ ወይም ስንዴ እንጀራ፣ ከላይ ጤፉ ይቀርባል፡፡ ጠላው በዋንጫ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደተሰየመ ነው፡፡ ደብተራ ዘለቀም አሉ፡፡ መምሬ ከፈለኝም አሉ፡፡ መምሬ ሃብቴም አለ፡፡ የአክስቴ የአበባ የሺ ልጆችን ያሉ መሰለኝ፡፡ አንዳርግ ያን ጊዜ ዳቁኖ ይሆን? አሁን መርጌታ ሳሙኤል ተብሏል፡፡ በዘመድ ተከብቤ ወጋቸውን እሰማለሁ፡፡ አይ ወሬ ማሳመር እቴ! ዳቦዬን አጣጥማለሁ አይሻልም? በጣም የሚናፈቅ የቤተዘመድ ጉባኤ ነው፡፡ ሁሉም ዘመዶቼና ወገኖቼ ናቸው፡፡

ማምየለኝ ማርያም ያለው ሌላው የማዕድ ትዕይንት አባቴ ማህበር ጋ ነው፡፡ የአባቴ ማህበር ቤት አንዱ መቃብር ቤት ነው፡፡ ማህበሩ ከነ ጋሽ ብርቅነህ ተክለወልድ ጋር ነበር፡፡ መቃብር ቤቱ ውስጥ የተቀበሩት ሰዎች የለበሱትን አፈር በባዶ እግራችን እየረገጥን ጥግጥጉን ቁጭ ብለን ዳቦና እንጀራ እንበላለን፡፡ ባለፈው እንደጻፍኩላችሁ ጫማ የለንም፡፡ አፈሩን በባዶ እግራችሁ የመርገጥን ስሜት እስኪ ለአንድ ደቂቃ አስቤት - ወዲያውም ኢሜጀሪ ልስራባችሁ፡፡ ጠላም እንጠጣለን፡፡ ቢራ እንጂ ጠላና አረቄ አያሰክረኝም ብያችኋለሁ፡፡ በብዕረኛው የሞጃ ልጅ ነበር በሌላ ጽሑፍ? ማነህ ባለ ሳምንት የሚለው መዝሙራዊ ጥያቄ ከማህበሩ ሥነሥርዓት በተለይ ትዝ ይለኛል፡፡ በማህበር ቤቱ የቄስ ቡራኬም ግድ ይላል፡፡ ከአባቴ ማህበር ቤት ሌላ ከቤተክርስቲያኑ ግቢ ውጪ የነ አበባ በላይነሽ አለች፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ትረካው ምልልስ፣ ልብ ሰቀላ ምናምን ስለሌለው ይቅርታ፡፡ ሌላ ቀን ባያሌው እጨምራለሁ፡፡

እሁድ እሁድ ከሆነ ወይም ለፍልሰታ ሁሉም ሰው ቆሎና ዳቦ ያመጣና ያ አንድ ላይ ተደባልቆ እየተቀነሰ ይታደላል፡፡ ጣዕሙ ልዩ ነው፡፡ የእሁዱና የፍልሰታው እንዲሁም ሌላው የሚበላው ቅዳሴ ጠበል ከተጠጣ በኋላ ነው፡፡ ስጽፍ በመጨናነቅ ሳይሆን አንዴ ጽፌ በመላክ ነው፡፡ እንደወረደ ይባላል፡፡ ዋናው ዓላማዬ በጊኒያዊው ደራሲ ካማራ ሌ አምሳል በእንግሊዝኛ መጻፍ ነው፡፡ ያው እሱ በፈረንሳይኛ ቢጽፍም ትርጉሙ እንግሊዝኛ ነው፡፡ ያውም ሙሉ መጽሐፉን አላገኘሁትም - ፍለጋ ላይ ነኝ፡፡ የዩቱቡን ትረካ ቀድሜ ማድመጥ ስላልፈለግሁ ነው፡፡ ሁለት ቅንጫቢ ምዕራፎችን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት አግኝቼ ተለከፍኩ፡፡  ቤተክርስቲያናችን ብዬ ርዕስ ብሰጠውም ከቤተክርስቲያኗ ውጪ የሚካሄዱ በዓላትም አሉን፡፡ ከአሁን በፊት ስለ ጥምቀት ስጽፍ ነካክቻቸዋለሁ፡፡ ጥምቀትና አስተርዕዮ ማርያም ታቦት የሚወጣባቸው ናቸው፡፡ ይህም ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ያኔም ድግስ አለ፡፡ ለጥምቀት ታቦት ባደረበት ሲሆን አለስተርዮ ደግሞ በቤተክርስቲያንና የማርያም ማህበር ባላቸው ዘንድ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው ወገኖቼ    

ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ በአሜሪካው ቤቱ ለተፈራ ሲያወጋ ‹‹ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ባህል ነበር ያደግሁት›› ያለውና ኤደን ሆስፒታል ሳለች ‹‹እንደ ዱሮው ቤተክርስቲያን ሳሚ ብትሆን ደስ ይልህ ነበር?›› ያለችኝ ትዝ አለኝ፡፡ የሰለሞንን አስተዳደግ እጋራዋለሁ፡፡ ለኤደን ጥያቄ ምላሼ ከእርሷ ምኞት በተቃራኒው ነበር፤ እሷ ቤተክርስቲያን ሳሚ መሆን ባትፈልግም እኔ ግን እፈልጋለሁ፡፡ ጂጂ ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታው እንዳለችው ናፈቀኝ የማሪያም ድግስ ልበል እንዴ?

 

የሳሲት ወጎች ቁ. 11 ተናፋቂ የመምህራን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ


ከመምህራን ጋር የነበረን ግንኙነት የፈጣሪና የፍጡር ዓይነት ነው ለማለት አይቻል ይሆን? እንደ ፈጣሪ ሁሉ አክብሮታችንን አንነፍጋቸውም። ለአንዳንድ ጠበቅ አድርገው ለሚይዙን መምህራን ወደ አምልኮ የሚቀርብ አካሄድ ነበረው። ፍቅር ግን በልብ የሚያዝ ስለሆነ እንውደድ እንጥላ በልባችን ስለምንይዘው አይታወቅብንም። መምህራን በዚያ ሁኔታ በአንዲት ትንሽ ከተማ እየኖሩ ለእኛ የዕውቀትን ማዕድ ስላቋደሱን እናመሰግናለን። የሥራ ጫናውንና የኖሩበትን ሁኔታ አስታውሼ ያዘንኩላቸው እኔ መምህር ከሆንኩ በኋላ ነበር። መቼም ከስንት ተወዳጅ መምህር በምን ምክንያት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ የሚጠላችሁ አይጠፋም። እኔና አንድ ሳሲት የተማረ የዕድሜ እኩያዬ መምህር በሳሲት ስለሚጠሉን መምህራን አንስተን ነበር። እሱ የሚጠሉኝ ያላቸው ለኔ ጥሩ ሰው ነበሩ። የሐሳብ አለመስማማት ይሆናል። እኔን የሚጠሉኝና በተቻላቸው አቅም እንደማልችልና እንደማልረባ ይነግሩኝ የነበሩት መምህር ሁኔታ ይደንቀኛል። በአስገራሚ ሁኔታ አንድ ቀን በሆዴ ቂም ይዤ በአጠገባቸው ሳልፍ ጠሩኝ። ጠርተውም ገላመጡኝ። የሰውን ልብ ያያሉ። አሉታዊ ስሜትን ማንበብ ይችላሉ። እርሳቸው ውስጥ ያለውና እኔ ሆድ ውስጥ ያለው ጥላቻ ተጋጨ መሰለኝ። መቼም የማይታረም የለምና ታርመው በአንድ የፌስቡክ ልጥፌ ላይ "ወጣቱ" ብለው የምስጋና ቃል ጽፈውልኝ አገኘሁ። ጓደኛዬን የሚጠሉት መምህር ይሰድቡት ነበር፤ እኔንም የሚጠሉኝ እንደዚያው። እሱን የሚጠሉት ግን እኔን ይወዱኛል። ነክተውኝ አያውቁም። 

የተናፋቂ የመምህራኔን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ ላስከትል። ሁለቱ መምህራን ተወዳጅ ናቸው። መጀመሪያ ስለ ሴቷ አስተማሪያችን ልጻፍ። ታች ክፍል አስተምረውኛል። አንድ ቀን እርሳቸውና ሌላ ሴት አስተማሪዬ ገበያ ላይ አገኙኝ። አምስተኛ  ክፍል እሆናለሁ። ጤፍ ተሸከምልን አሉኝ። በደስታ ተሸክሜ ከኋላቸው ተከተልኳቸው። ወሬ ይዘው ስላላዩኝ አቅጣጫ ቀይሬ ጠፋሁባቸው። ያስደነግጣል? አዎ። አልጠፋሁም። አንባቢዬን ትንሽ ላስደንግጥ ብዬ ነው። ተሸክሜ ተከትያቸው ትምህርት ቤት ግቢ ካለው ቤታቸው ደረስን። ጤፉን አውርጄ ልሄድ ስል ቲቸር ጠራችኝ። "ና፣ እንካ" አለችኝ። ሁለት ባለ ሃያ አምስት ሳንቲሞች ነበሩ። ይህ ገንዘብ ያኔ ዳቦና ሻይ ይገዛል። ወይም ትልልቅ ሰዎች እንዳሉኝ ቢቆጠብ ሳድግ ተጠራቅሞ የአንበሴን መኪና የሚመስል ያስገዛኛል። ቲቸር እጇን ዘርግታ  ብትለምነኝ አሻፈረኝ አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብላ ሰትቆጣኝ ግን ልትቀጣኝ መስሎኝ ተቀበልኩ። በመቀበሌ ግን በጣም ተጨነቅሁ። "ሂድ! ደህና ዋል!" ስትለኝ ሄድኩ። ምን እንደገዛሁበት ረሳሁት። ሌላ ቀን ስድስተኛ ክፍል ሆኜ ወንድ መምህራችን እንደወትሮው እንጀራ እንድገዛ ላኩኝ። ገዝቼ መጣሁና ሰጠኋቸው። ምግብ እየሰሩ ነበር። ከዉጪ ቆሜ እጄን ሰደድ አደርጋለሁ እንጂ ወደ ውስጥ አላይምም አልገባምም። ያን ቀን ግን ጠሩኝ። በእጃቸው ቋንጣ ዘረጉልኝ። አልቀበልም አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብለው ተቆጡኝ። ተቀበልኩ። የሁለቱ መምህራን ግሳፄ እናታዊና አባታዊ ነው። በመምህራን መታዘዝ እንደ መመረጥ ይቆጠር ነበር። ተመርጠን ክፍያ መቀበል በጣም ነውር ነበር። ስለዚያም ነበር አይሆንም ማለቴ። ሲገስፁኝ ተቀበልኩ። ትዝታውም አሁንም አለ።

2023 ጁላይ 3, ሰኞ

በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የመኖር ጥበብ - ክፍል 1 - ከጉዞ በፊት መደበኛ ሚዲያን፣ ማህበራዊ ሚዲያንና ማናቸውንም መረጃ መከታተል


ይህን ጽሑፍ የሚያነብ ሰው የእርስበርስ ጦርነት የሚለውን አገላለጽ ለምን ተጠቀምክ ሊለኝ ይችላል፡፡ ስያሜው የሚያጣላን አይመስለኝም፡፡ በመፍረስ ላይ ባለች አገርም ሊሆን ይችላል፡፡ የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ትንቅንቆች የፈጠሩት ሽብርም ሊባል ይችላል፡፡ ውስጣዊ ቅኝግዛትም ተባለ መንግሥታዊ ሽብር፣ ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚደረግ መውተርተርም ተባለ በስንት ስለት የተገኘ ሥልጣንን የማስጠበቅ የውልየለሽ አጥፊ አጀንዳዎች ትርዒት፣  የዘር ማጽዳትም ተባለ በዉጪ ኃይሎች የሚዘወር አለመረጋጋት ለማናቸውም ስያሜውን ለጊዜው ለባለሙያዎች እንተውላቸው፡፡

እዚህ ደረጃ ላይ ለምን ደረስን የሚለውን ሁላችንም በልምድና ዕውቀታችን ልክ ለመመለስ እንሞክር፡፡ እዚህ እሳት ውስጥ ራሳችንን ላለማግኘት ለምን አልሞከርንም የሚለውንስ አስበንበት ይሆን? ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም እንዲሉ አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ መውደቃችንን እንጂ ስላለፈው ብዙ መጨነቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ሞቶ፣ ሌሎች ሚሊዮኖች የአገር ውስጥ ስደተኞች ሆነው፣ ከቁጥጥር ዉጪ ሊወጣ የሚታገል የኢኮኖሚ ችግር ነግሦ፣ በየቦታው ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ፣ ረሃብ ፀንቶ፣ የአጋች ታጋች ድራማዎች በዝተው፣ ኢትዮጵያ የማትመስል አገር ውስጥ እየኖርን፣ ስለነገ ፈጽሞ እርግጠኛነት አጥተን እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት አስጊ ሁኔታዎች ብዙዎቹን እያስተናገደች ባለች አገር ውስጥ እንዴት እንኑር? እስካሁንስ ያለፉትን አምስት ዓመታት እንዴት ኖርን? እነሆ አንዳንድ ነጥቦች፡፡

ሰዎች በተለያዩ ነገሮች ተጠምደዋል፡፡ ነጋዴዎች ሆነው በየዕለቱ በሚንረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ብራቸው ሚሊዮን ገብቶ ሲራባ ልባቸው ጠፍቶ ሌሎች ሚሊዮኖችን ፍለጋ ይቃትታሉ፡፡ ወይም ሁለት ከተሞች ላይ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ሆነው ከአንዱ ወደ ሌላው ከተማ እየተመላለሱ ይኖራሉ፡፡ ባሉበት እንደምንም ሊያሟሉት የሚችሉትን አገልግሎት ለማግኘት ወደ ትልቅ ከተማ ይሄዳሉ፡፡ በአጭሩ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እስከ ዛሬ በብዙ ሰዎች ዘንድ ያየሁት ክፍተት ቢኖር መጓጓዛቸውን እንጂ የሚጓጓዙበት መንገድ ወይም መዳረሻቸው ሰላም መሆኑን እንደማይከታተሉ ነው፡፡ በእርግጥ ሰላም ባይሆን ሾፌሩ ይነግረን ነበር፣ መንገድ ይዘጋ ነበር፣ እንሰማ ነበር ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ በአጋጣሚ ስለ መንገዱና መዳረሻቸው ከሌላ አካል መረጃ ልንሰማ እንችል ይሆናል ከማለት ሌሎችን የማወቂያ መንገዶች ሆነ ብሎ ማጥናትና መፈለግ ግድ ይላል፡፡ ሾፌሩ ያልነገራችሁ እሱ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ከሱ ብሄር፣ ከመኪናው ታርጋ፣ ካለው ትውውቅ፣ ከኃይማኖቱ ወይም ከሚናገረው ቋንቋ አንጻር በግሉ ችግር አይገጥመው ሆኖስ ቢሆን? መንገዱ ያልተዘጋው ያን ያህል ለትራፊክ አሳሰቢ ነገር የለም ብለው በወሰኑ የመንገድ ትራንስፖት ሰዎች ወይም አገሩ ሰላም ነው የሚል ስዕል ለመሳል በፈለጉ ፖለቲከኞች ውሳኔ ቢሆንስ? አንዳንዴ መሄድ ችግር የለው ይሆናል፡፡ መምጣት ከባድ ይሆናል፡፡ ለአንዱ ችግር የሌለው ለሌላው ይኖረዋል፡፡ ሚሊዮኖች በሚሞቱበት አገር መቶ ሰዎች ሊሞቱ ወይም የተወሰኑ ሺዎች ሊንገላቱ ይችላሉ ብሎ የሚጠነቀቅላችሁ ያለ ይመስላችኋል? እንዳትታለሉ! እንሰማ ነበር የሚለውም አይሰራም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አይገመቴ ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሾፌሩም አይነግራችሁም፣ መንገዱም አይዘጋም፣ ልትሰሙ የምትችሉበትም ዕድል የለም፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ተሻለን?›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ገና ለገና ችግር ሊመጣ ይችላል ብሎ አስጨነቀን ብላችሁኝም ይሆናል፡፡ ግድ የላችሁም፡፡ ትንሽ ሃሳብ እናፍልቅ፤ ካለፉትም ጊዜያት እንማር፡፡ የሚፈጠሩት ችግሮች በአመዛኙ በፖለቲካ ውሳኔ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን ወይም አካል አንድን ግብ ለመምታት ሲል የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ እንጂ ተራ የእንትን ብሔር ወይም ኃይማኖት አባል ተበድዬ፣ ምን ብዬ ብሎ አይነሳም፤ አይነካችሁምም፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በጣም ውሱን ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች የሚያንቀሳቅሷቸውን ርዕሰጉዳዮች መከታተልና የአካሄዳቸውን አዝማሚያ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎቹ ከየት ይገኛሉ ከተባለ ከመደበኛ ሚዲያዎች፣ ከማህበራዊ ሚዲያዎችና ከሌሎች ምንጮች ይሆናል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ አካሄድ በንቃት መከታተል ሕይወትን የሚታደግ ውሳኔ ላይ ሊያደርስዎት ይችላል፡፡ ፖለቲካውን እንኳን ባይከታተሉ መደበኛ ዜና ይከታተሉ፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች ጭራሽ የማይዘግቧቸው ወይም ዘግይተው ምናልባትም አዛብተው የሚዘግቧቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ቴሌቪዥን አይቼ፣ ሬዲዮ ሰምቼ፣ የእንትን ሚዲያን አካውንት ሰብስክራይብ አድርጌ ዩቱብ ላይ ሰምቼ አይሰራም፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች መረጃዎቹን አጣርተው፣ አለቆቻቸውን አስፈቅደው፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ ወሬውን እስኪለቁት ብዙ ውድመቶች የመጡባቸውን ጊዜያት አስቡ፡፡ መረጃ እንዲዳፈንም ይደረጋል፡፡ መረጃ ተዛብቶ ይደርሳችኋል፡፡ ወይም ይዘገያል፡፡ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ስንመጣ ታማኝ የሚሏቸውን ዘጋቢዎች ይለዩ፡፡ እነርሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ አውቀው የሆነ ዓላማ ለማሳካት፣ ብዙ ተከታይ ለማግኘት፣ ሰበር ዜና ለማውጣት ወይም የመረጃ ምንጭ አሳስቷቸው፣ ምናልባትም ከሁለት ወገን ሳያጣሩ ዘግበው ሊሆን ይችላል፡፡ መረጃዎችን ማን ለቀቃቸው የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ያንን መረጃ ከየት አመጣው የሚለውም እንዲሁ፡፡ ግነትም ካለ ልብ ይበሉ፡፡ ስለዚህ የማህበራዊ ሚዲያን መረጃ በሚገባ ማጣራት ያሻል፡፡ በፌስቡክ ገጽዎ የመጡልዎትን ወይም እርስዎ ላይክ ካደረጓቸው ገጾችና አካውንቶች ገብተው ያዩትን ብቻ አይጠቀሙ፡፡ ፈልግ የሚለውን ተጠቅመው ይፈልጉ፡፡ ፍለጋዎትን መረጃው በተለቀቀበት ጊዜ፣ ቦታ፣ ምንጭ መሰረት ማጥራት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ከሆነ በከተሞቹ ስም፣ በብሔሮች፣ በፓርቲዎች፣ በኃይማኖቶች ወዘተ የዕለቱን መረጃ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የፌስቡኩ ለትዊተርም፣ ከቲክቶክም ይሰራል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን በዚህ መልኩ ከተጠቀሙ ወደሚያውቋቸው ሰዎች መረጃ ፍለጋ መደወል ሊኖርብዎት ይችላል፡፡ ከሚዲያ ሚዲያ፣ ከአካውንት አካውንት፣ ከግለሰብ ግለሰብ የወሰዱትን መረጃ ማማሳከርና በውሳኔ ግብዓትነት መጠቀም እንጂ ሌሎች ሰላም ነው ብለው በወሰኑት ውሳኔ ተመስርተው ሕይወትዎንና የሚወዷቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ አይጣሉ፡፡ ዘዴ ይፈልጉ፡፡ የመስሪያ ቤት መታወቂያ ያሳያሉ ወይስ የቀበሌ፣ በግልዎ መኪና ይሄዳሉ በህዝብ ትራንስፖርት፣ በሚኒባስ ወይስ በአውቶቡስ፣ ቢጠየቁ ሙያዎትንና ስራዎትን ይደብቃሉ ወይስ ግልጹን ይናገራሉ? መታወቂያው ላይ ስሙ የፊደል ግድፈት እንዳለው ላስቆሙት አካላት በመንገር ራሱን የሌላ ኃይማኖት አባል በማስመሰል  ሸወዶ እንዳለፈው ወዳጄ ሕይወትዎን ያተርፋሉ? ከመንገዱ በኋላስ? የሚያርፉበት ከተማ ሰላም ነው? እስከመቼ? ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ እንወያይበት፡፡

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...