2023 ጁላይ 5, ረቡዕ

የሳሲት ወጎች ቁ. 11 ተናፋቂ የመምህራን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ


ከመምህራን ጋር የነበረን ግንኙነት የፈጣሪና የፍጡር ዓይነት ነው ለማለት አይቻል ይሆን? እንደ ፈጣሪ ሁሉ አክብሮታችንን አንነፍጋቸውም። ለአንዳንድ ጠበቅ አድርገው ለሚይዙን መምህራን ወደ አምልኮ የሚቀርብ አካሄድ ነበረው። ፍቅር ግን በልብ የሚያዝ ስለሆነ እንውደድ እንጥላ በልባችን ስለምንይዘው አይታወቅብንም። መምህራን በዚያ ሁኔታ በአንዲት ትንሽ ከተማ እየኖሩ ለእኛ የዕውቀትን ማዕድ ስላቋደሱን እናመሰግናለን። የሥራ ጫናውንና የኖሩበትን ሁኔታ አስታውሼ ያዘንኩላቸው እኔ መምህር ከሆንኩ በኋላ ነበር። መቼም ከስንት ተወዳጅ መምህር በምን ምክንያት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ የሚጠላችሁ አይጠፋም። እኔና አንድ ሳሲት የተማረ የዕድሜ እኩያዬ መምህር በሳሲት ስለሚጠሉን መምህራን አንስተን ነበር። እሱ የሚጠሉኝ ያላቸው ለኔ ጥሩ ሰው ነበሩ። የሐሳብ አለመስማማት ይሆናል። እኔን የሚጠሉኝና በተቻላቸው አቅም እንደማልችልና እንደማልረባ ይነግሩኝ የነበሩት መምህር ሁኔታ ይደንቀኛል። በአስገራሚ ሁኔታ አንድ ቀን በሆዴ ቂም ይዤ በአጠገባቸው ሳልፍ ጠሩኝ። ጠርተውም ገላመጡኝ። የሰውን ልብ ያያሉ። አሉታዊ ስሜትን ማንበብ ይችላሉ። እርሳቸው ውስጥ ያለውና እኔ ሆድ ውስጥ ያለው ጥላቻ ተጋጨ መሰለኝ። መቼም የማይታረም የለምና ታርመው በአንድ የፌስቡክ ልጥፌ ላይ "ወጣቱ" ብለው የምስጋና ቃል ጽፈውልኝ አገኘሁ። ጓደኛዬን የሚጠሉት መምህር ይሰድቡት ነበር፤ እኔንም የሚጠሉኝ እንደዚያው። እሱን የሚጠሉት ግን እኔን ይወዱኛል። ነክተውኝ አያውቁም። 

የተናፋቂ የመምህራኔን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ ላስከትል። ሁለቱ መምህራን ተወዳጅ ናቸው። መጀመሪያ ስለ ሴቷ አስተማሪያችን ልጻፍ። ታች ክፍል አስተምረውኛል። አንድ ቀን እርሳቸውና ሌላ ሴት አስተማሪዬ ገበያ ላይ አገኙኝ። አምስተኛ  ክፍል እሆናለሁ። ጤፍ ተሸከምልን አሉኝ። በደስታ ተሸክሜ ከኋላቸው ተከተልኳቸው። ወሬ ይዘው ስላላዩኝ አቅጣጫ ቀይሬ ጠፋሁባቸው። ያስደነግጣል? አዎ። አልጠፋሁም። አንባቢዬን ትንሽ ላስደንግጥ ብዬ ነው። ተሸክሜ ተከትያቸው ትምህርት ቤት ግቢ ካለው ቤታቸው ደረስን። ጤፉን አውርጄ ልሄድ ስል ቲቸር ጠራችኝ። "ና፣ እንካ" አለችኝ። ሁለት ባለ ሃያ አምስት ሳንቲሞች ነበሩ። ይህ ገንዘብ ያኔ ዳቦና ሻይ ይገዛል። ወይም ትልልቅ ሰዎች እንዳሉኝ ቢቆጠብ ሳድግ ተጠራቅሞ የአንበሴን መኪና የሚመስል ያስገዛኛል። ቲቸር እጇን ዘርግታ  ብትለምነኝ አሻፈረኝ አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብላ ሰትቆጣኝ ግን ልትቀጣኝ መስሎኝ ተቀበልኩ። በመቀበሌ ግን በጣም ተጨነቅሁ። "ሂድ! ደህና ዋል!" ስትለኝ ሄድኩ። ምን እንደገዛሁበት ረሳሁት። ሌላ ቀን ስድስተኛ ክፍል ሆኜ ወንድ መምህራችን እንደወትሮው እንጀራ እንድገዛ ላኩኝ። ገዝቼ መጣሁና ሰጠኋቸው። ምግብ እየሰሩ ነበር። ከዉጪ ቆሜ እጄን ሰደድ አደርጋለሁ እንጂ ወደ ውስጥ አላይምም አልገባምም። ያን ቀን ግን ጠሩኝ። በእጃቸው ቋንጣ ዘረጉልኝ። አልቀበልም አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብለው ተቆጡኝ። ተቀበልኩ። የሁለቱ መምህራን ግሳፄ እናታዊና አባታዊ ነው። በመምህራን መታዘዝ እንደ መመረጥ ይቆጠር ነበር። ተመርጠን ክፍያ መቀበል በጣም ነውር ነበር። ስለዚያም ነበር አይሆንም ማለቴ። ሲገስፁኝ ተቀበልኩ። ትዝታውም አሁንም አለ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...